በምግብ መብያ ቦታ (Break room) ማሰክ ማውለቅ ያስከተለው ጣጣ 11/10/2020

 በኮቪድ መሰላቸት የብዙ ሰው ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ የጤና ባለሙያተኞችንም ይጨምራል፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ቸልተኝነት የሚያሰከትለው አደጋ እየታየ ነው፡፡ የተወሰኑ ሰዎች፣ ወይ ራሳቸው ካልታመሙ፣ አለዚያም የቤተሰብ አባልና የቅርብ ጓደኛ ታሞ ካላዩ፣ ኮቪድ-19 እንደሌለ ወይም የሌሎች ሰዎች ቸግር እንደሆነ ብቻ ያደርጉታል፡፡

በማንኛውም ቦታ ቢሆን፣ ከቤት ውጭ ማስክ የሚወለቅ ከሆነ አደጋ እንደሚጨምር ግልፅ ነው፡፡ በተለይም በቤት ወይም በክፍል ውስጥ ሲሆን፡፡ ከዚህ ቀደም፣ ቆየት ብሎ በጎሽ ድረ ገፅ ለማስጠንቀቅ የተሞከረው፣ በሥራ ቦታ፣ ምግብ የሚበላባቸው ክፍሎቹ፣ መፀዳጃ ክፍሎች፣ ኢሊቤተሮች አደጋ አላቸው ተብሎ ተገልጧል፡፡ አሁን በቅርብ ከወደ አውስትራልያ በኩል በተደረገ ጥናት፣ ቫይረሱ በአንዳንድ ዕቃዎች ላይ ለሳምንታት እንደሚቆይ ይታወቃል፡፡ ከጠብታ አልፎ ደገሞ በአየር ብናኝ (ኤርቦርን) እንደሚተላለፍም ግልፅ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተጠና ጥናት፣ ቫይረሱ በአየር ላይ አስከ ሶስት ሰአታት ሊቆይ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ አየር በደንብ በማየዛወርባቸው ክፍሎች ማለት ነው፡፡

በሆስፒታል ውስጥ፣ ማስክ የሚወለቀው፣ ሠራተኞቹ በሚመገቡት ጊዜ ነው፡፡ በአብዛኛው ይህ ደግሞ ጠበብ ባሉ የጋራ ምግብ መብያ ወይም (Break room) ክፍሎች ነው፡፡ አሁን የማጋራችሁ፣ በዚህ በ Break room አማካኝነት፣ 15 የሆስፒታል ሠራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀበት፣ ከማሳቹሴትስ የመጣ ሪፖርት ነው፡፡ ሆልዮክ ሜዲካል ሴንተር በሚባል ሆስፒታል በተከሰተው የ15 ሠራተኞች በኮቢድ መያዝ፣ ክትትል ሲደረግ፣ ከአንድ በኮቢድ ከተያዘ ሰው በ Break room ውስጥ ምግብ የተመገቡ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ይሀ የሆነው ሠራተኞቹ ባንድ ላይ በ Break room ምግብ ሲመገቡ ነው፡፡ እንግዲህ ለማንም ገልፅ እንደሆነው፣ ምግብ ሲበላ ማስክ መውለቁ አይቀርም፡፡

የሆስፒታሉ ሃላፊ አንደገለፁት፣ ሠራተኞቹ የህመም ሰሜት የታየባቸው ከሁለት ሳምንታት በፊት ሲሆን፣ በኮቪድ መያዛቸው ከተረጋገጠ ከ15ቱ አስሩ በድንገተኛ ክፍል ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያተኞች ናቸው፡፡ ሰውየው የሚሉት፣ በኮቪድ መሰላቸት ሲመጣ፣ በአካል መራራቅ ስድስት ጫማ ይሁን የተባለው እያነሰ እያነሰ ሰዎችም እየተጠጋጉ መታየታቸው አይቀርም፡፡ ሆስፒታሉ ህብረተሰቡ ውስጥ ያለ ተቋም እንደመሆኑ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ የኮቪድ ሥርጭት በቀጥታም ሀነ በተዘዋዋሪ ያገኘዋል፡፡ ይህ ሆስፒታል ባለበት አካባቢ የኮቪድ ሥርጭት እንደገና አገርሽቶ የታየበት ቦታ ነው፡፡ የታመሙት የጤና ባለሙያተኞች የግድ ከሥራ እንዲገለሉ ተደርገዋል፡፡ አስካሁን ሁለቱ ብቻ፣ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ሥራ የተመለሱት፡፡

በርግጥ ሁላችንም እንደምናስተውለው፣ ኮቪድ አገርሽቶ በአውሮፓ ሁለተኛ ዙር ጀምሯል፡፡ ከሥርጭቱ መክፋት የተነሳ አንዳንድ የአውሮፓ ከተሞች እንቅስቃሴ እንዲገደብ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ በሁለተኛው ዙር ክፉኛ የተመቱ እንደ ቸኮዝሎቫኪያ የመሠሉ አገሮች አሉበት፡፡

ከመሰላቸቱ በተጨማሪ፣ አንዳንዶች እንደ ንቀትም አይነት ስሜት ያላቸው ይመስላል ወይም መዘናጋት እንበለው፡፡ በሚቀጥለው ፅሁፍ የማካፍላችሁ፣ በኮቪድ ተይዘው የበሽታ ስሜት የማይሰማቸው ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት፣ ዘላቂ ሊሆን የሚችል አደጋ መታየቱ ነው፡፡ ስለዚህ የሚሞት ሰው ወይም በጠና የታመመ ሰው አላዩምና ወይም በቀላሉ እንወጣዋለን የሚባል አስተሳሰብ አደጋ ሊኖረው እንደሚችል ግንዛቤ መኖር ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ፅሁፍ መረዳት እንደምትችሉት
1ኛ. ለሥርጭት አንድ ሰው ሊበቃ እንደሚችል
2ኛ› ማስክ የሚወለቅበት ቦታ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ
3ኛ. ይህ ችግር ሆስፒታል ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሥራ ቦታዎችም ሊጠነቀቁበት የሚገባ መሆኑን
4ኛ› ከመታመሙ፣ በአንዳንዶችም ላይ የህይወት ማለፍ አደጋ ከማስከተሉ፣ ቫይረሱን መልሶ ማሠራጨት ወይም ከሥራ ቦታ ወደቤት ይዞ መሄድ ባሻገር፣ በሥራ ላይ የሚፈጥረውን ቸግር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የሚሠሩበት ሥራ ቦታ ከተዘጋ፣ ወይም አግልግሎት መሥጠት ካቋረጠ፣ ለሁለት ሳምንታት ቢሆን፣ ከኮቪድ ውጭ ሌላ ችግር ይፈጥራል፡፡ ባጭሩ የኮቪድ ፓንደሚክ ራሱ የኢኮኖሚ ችግርም ነው፡፡ ሰለዚህ በሽታውን ቀለል አድርጎ ማየት፣ እናም ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረግ፣ ኢኮኖሚው እንዲጎዳ አስተዋፅኦ ማድረግም ነው፡፡

ሌላው ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት፣ የግድ ለሥራ ሲባል ከቤት የሚወጣበት ሁኔታ ቢኖርም፡፡ ቤተሰብ ከቤተሰብና ከጓደኛ ጋር ለመገናኘት ሲባል፣ ድግስ አድርጎ መገባበዝም እየታየና እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ በክረምቱ በቤት ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ምግብ ሲበላም ማሰክ አይደረግም፡፡ እና ከሆስፒታል Break room በምን ይለያል? ማሰብ ያለብን፣ ለ15ቱ ሰዎች መያዝ ምክንያት የሆነው ሠራተኛ ምናልባትም ቫይረሱን ከሥራ ቦታ ሳይሆን ከውጭ ሊያገኘው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከበሽተኛ ጋር በሚደረገው ግንኙነት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሰለሚደረግ ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ሥርጭቱ ከፍ ሲል የሰዎች የመያዝ ዕድል ሊጨምር የሚችለው፡፡ በአሜሪካ የሚታየው፣  በቀን በበሽታው መያዛቸው የሚረጋገጡ ሠዎች ቁጥር፣ ኢትዮጵያ በወራት ካስመዝገበችው በላይ ነው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን የምንለው፣ አብዛኛው ሰው በቀላሉ ሊያልፈው ሲችል፣ ቫይረሱ ዞሮ ዞሮ የሚገድለው ሰው ያገኛል፡፡ እነማን አደጋ ላይ እንደሚሆኑ ደግሞ ግልፅ ነው፡፡ የተያዘ ሁሉ በጠና ይታመማል፤ የተያዘ ሁሉ ይሞታል ብለንም አናውቅም፡፡ ግን በስድስት ወር ውስጥ ከእሩብ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሰው ሲሞት ማየት ደግሞ ትንሽ ሰቅጠጥ እንድንል የሚያደርግም ነገር ነው፡፡ ህመሙና ሞቱንም ችላ ለሚሉ፣ ኢኮኖሚው የግድ እንዲዘጋ የሚያደርግ የሥርጭት መጠን ሲፈጠር ሁሉንም እንደሚጎዳ ማስታወስ ነው፡፡

መልካም ንባብ 

Community health 

education in Amharic 

ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ