ኮቪድ-19 ሰው ከተገናኘ መሠራጨቱ አይቀርም
ቤተክርስቲያኖችን መሠራጫ ቦታ አድርጓቸዋል 5/19/2020 


በ Morbidity and Mortality weekly report (MMWR) በሜይ 19 ባወጣው እትሙ፣ አርካንሳስ በተባለ ሰቴት ባንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ የኮቪድ-19 ሥርጭትና ውጤቱን ያትታል፡፡ ዝጉ ሳይባል፣ ለደረሰው አደጋ ተወቃሽ ባይኖረም፣ ዝጉ ከተባለ በኋላ፣ አገልግሎት ለመሥጠት በራቸውን የከፈቱ ቤተ ክርስቲያኖች በደረሰባቸው አደጋ ምክንያት መልሰው እየዘጉ ነው፡፡

ይህ የሆነው በቴክሳስና በጆርጂያ ስቴቶች ነው፡፡ እንደ ዋሽንግተን ፖስት (ጋዜጣ) ዘገባ፣ እነዚህ፣ ቀድመው እንከፍት ብለው የከፈቱ ናቸው፤ በጆርጂያ ስቴት፣ ካቶሳ ባፕቲስት ታበርናክል ተብሎ የሚጠራ፣ በሪንግጎልድ ከተማ፣ በሩን ከፍቶ፣ ምንም እንኳን የመራራቅና ፅዳት በማድረግ የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል ቢሞክሩም፣ ብዛት ያላቸው ቤተሰቦች በቫይረሱ ሰለተያዙ፣ ቤተክርስቲያን በሩን እንደገና እንዲዘጋ ተገዷል፡፡ በቴክሳስ፣ በሂዩስተን፣ ሆሊ ጎስት ተብሎ የሚጠራ ቤተክርስቲያን፣ በሩን ላልተወሰነ ጊዜ አንዲዘጋ ተገዷል፡፡ ይህም የሆነው፣ አምስት የቤተክርስቲያኑ አባላት በኮቪድ መያዛቸው ከተረጋገጠና፣ ከቄሶቹ መሀከል አንዱ ሰለሞተ ነው፡፡

በመግቢያው እንደተጠቀሰው በአርካንሳስ የታየው፣ ገጠራማ በሚባል ቦታ የሚገኝ 92 አባላት ያሉት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ 35 በኮቪድ መያዛቸው በላቦራቶሪ ሲረጋገጥ፣ ከመሀከላቸው ሶስት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ የዚህ ሳይበቃ፣ ከቤተክርሰቲያኑ በኮቪድ መጋለጥ ጋር በተያያዘ፣ ከነዋሪዎች መሀከል 26 ሰዎች ተይዘው፣ ከመሀከላቸው የአንድ ሰው ህይወት አልፏል፡፡ ሥርጭቱ በአንድ ቦታ እንደማይቆም መረጃም ነው፡፡ ይሁንብኝ ብለው ደፍረው ለቫይረሱ ወደሚጋለጡባቸው ቦታ መሄድ፣ ከተያዙ፣ በሽታው በነሱ ብቻ አይቆምም፡፡ አልሄድም ላለው ወይም ላልሄደው ሰውም ይተርፋሉ ማለት ነው፡፡

የአርካንሳውን ነገር ጨመር አድርገን ስንመለከት፣ በስቴቱ እንደ ገጠር የሚቆጠር፣ 25ሺ ነዋሪዎች ብቻ ባሉበት ካውንቲ፣ በማርች 16፣ የመጀመሪያ የተባሉ ባልና ሚስት በኮቪድ መያዛቸው ሪፖርት ለጤና ቢሮው ይደርሳል፡፡ ባልየው፣ በአካባቢው የሚገኝ ቤተክርሰቲያን ቄስ ነው፡፡ ባልና ሚስቱ፣ በማርች6-8 ባለው ጊዜ ውስጥ ቤተክርስቲያኑን በሚመለከት ፕሮገራሞች ላይ ይሳተፋሉ፡፡ ቆየት ብለው፣ ከሶሰትና ከአራትና ቀናት በኋላ የበሽታ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ባልየው ግን ስሜት ከመሰማቱ በፊት፣ የመፅሐፍ ቅዱስ ፕሮግራሞች ይሳተፋል፡፡ በነዚህ ፕሮግራሞች ተሳትፈው ከተጋለጡ 92 ሰዎች መሀከል፣ 35ቱ በላቮራቶሪ የተረጋገጠ በኮቪድ-19 መያዛቸው ይታወቃል፡፡ ከነዚሀ መሀከል ነው ሶስት ሰዎች የሞቱት፡፡ በዕድሜ ተከፋፍሎ የተያዙ ሰዎች ሁኔታ ሲታይ፣ በቫይረሱ በመያዝ፣ ዕድሜያቸው ከ18 በታች ለሆኑት 6.3%፣ ዕድሜያቸው ከ19-64 ለሆኑት ደግሞ፣ 59.4%፣ ከ65 አመት በላይ ለሆኑት 50% ነበር፡፡ ፕረስንቱ የሚጠቁመው፣ በአድሜ ክልል ለቫይረሱ ተጋልጠው የተያዙትን ነው፡፡

ከዚያ በኋላ፣ መደበኛ የሆነው፣ የተጋለጡ ሰዎች ክትትል ሲደረግ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ 26 ሰዎች በተጨማሪ መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ እነዚህ 26 የሚሉት፣ በቤተክርሰቲያኑ ፕሮገራም ተሳትፈው ከነበሩት ሰዎች ጋር ግንኙነት እንደነበራቸውና ቫይረሱንም ከነሱ ነው ያገኘነው፡፡ የቤተክርሰቲያኑን ፕሮግራም ያልተሳተፉ፣ ነገር ግን፣ ፕሮግራሙን በተሳተፉ ሰዎች አማካኝነግ በቫይረሱ ከተያዙት ከ26 ሰዎች መሀከል፣ አንድ ሰው ሕይወቱ አልፏል፡፡

ከዚህ ሪፖርት መማር የምንችለው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው በግልፅ፣ ከሰው ጋር መገናኘት ለቫይረሱ መጋለጥን ያስክትላል ነው፡፡ እንግዲህ በአዳራሽም ውስጥ ሆነው፣ መደበኛ መራራቅ አደረግን ባሉት ቤተክርስቲያኖች፣ ሰዎች ተጋልጠዋል፡፡ ሰለዚህ የቫይረሱ አደገኛ ችሎታ ነውና፣ ሰው ለሰው በተለይም ብዛት ያለው ሰው ባንድ ቦታ መገናኘቱን ለተወሰነ ጊዜ ማቆም አለበት፡፡

ሁለተኛው ትምህርት፣ የአርካንሳው ቄስ፣ በቫይረሱ ተይዞ፣ ግን የበሽታ ሰሜት ሰላልተሰማው፣ የመፅሐፍ ቅዱስ ፕሮግራም ላይ በመሳተፉ ነው፣ ለተሳታፊዎች መያዝ ምክንያት የሆነው፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ሥርጭቱን ለመግታት አስቸጋሪ የሚያደርገው፤ የበሽታ ሰሜት እሰኪሰማቸው ድረስ፣ ስሜት አልባ የሆኑ ሰዎች፣ ቫይረሱን ያስተላለፋሉ፡፡ ሰለዚህ እንዴት ብለን ነው ማን አለበት ማን የለበትም ማለት የምንችለው፡፡ ለዚህ ነው፣ ከሰው ጋር በምትገናኙበት ቦታ ማስክ፣ ወይም አፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርጉ የሚባለው፡፡ ዋናው ግቡ፣ እንደቄሱ በቫይረሱ ተይዘው ስሜት አልባ የሆኑ ሰዎች አፍና አፍንጫቸውን በመሸፈን የቫይረሱን ሥርጭት እንዲገድቡ ነው፡፡

ሶስተኛ ትምህርት የሚሆነው፣ ከሰማችሁ የጤና ባለሙያተኞችን ምክር ስሙ፡፡ ኮቪድ-19 በፖለቲካ ሆነ በእምነት ምክንያት ማድረግ የሚገባንን የመከላከል ተግባር ከማድረግ እንዳንቆጠብ ትምህርት እየሠጠን ነው፡፡ የሀይማኖት መሪዎችና ምዕመናን ልብ ሊሉት የሚገባ ነገር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንደመከርኩት፣ የሀይማኖት ቤቶች ቤተክርሰቲያኖችም፣ በራቸውን ከመክፈታቸው በፊት ብዙ ማስተዋል ይኖርባቸዋል፡፡ በሽታው በቁጥጥር ሥር ሆኗል፣ ህብረተሰቡ ላይ አደጋ የለም እሰከሚባል ድረስ መታገስ መልካም ነው፡፡ መንግሥት ክፈቱ ቢል እንኳን፣ መንግሥት ራሱ ያወጣውን መመዘኛ በተግባር ማዋሉን መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡

ምዕመናንም፣ ቤተክርስቲያንም ሆነ ሌሎች የሀይማኖት ቤቶች፣ ስታደርጉላቸው የነበራችሁትን ምፅዋት አትንፈጉ፡፡ ኮቪደ-19 ለጊዜው በር ቢያዘጋም፣ የእናንተ እጅ ከተሰበሰበ፣ በሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነገር ሊዘጋ ይችላል፡፡ ፈተና ነው!

ቨርጂኒያ ሰቴት በአለክሳንደሪያ በሚገኝ የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን የኮቪድ-19 ሥርጭት 08/21/2020

 
 በዚህ ሥርጭት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በትክክል ባይታወቅም፣ ቁጥራቸው ከሀምሳ በላይ የሆኑ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ነው ተብሎ ይነገራል፡፡ ለኮቨደ-19 ተጋልጠው ሊሆን ይችላል የተባሉት ቀናት አገስት 14-17 ባለው ጊዜ ነው፡፡

በዚህ ሥርጭት በቫይረሱ ከተያዙ መሀከል ሰባት ሰዎች ሆሰፒታል ገብተው ርዳታ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ከነዚህ መሀከል ደግሞ ሶስቱ በICU እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ የታመሙት ሰዎች ባካባቢው ባሉ ሁለት ሆስፒታሎች ውስጥ ነው ርዳታ እየተደረገላቸው ያለው፡፡ በተላላፊ በሽታዎች መጋለጥ ሲኖር የሚደረገው የተጋለጡ ሰዎች ክትትልና ምርመራ ይካሄዳል፡፡ ለዚሀም ከላይ የሚታየው በራሪ ወረቀተ በአካባቢው የጤና ቢሮ በኩል ጥሪ እንዳደረገ ያሳያል፡፡

መረዳት ያለብን፣ ምርመራ ማድረግ የሚገባቸው ሰዎች፣

  1. በዋናነት በቤተ ክርስቲያኑ በተጠቀሱት ቀናት አገልግሎት ለማግኘት የሄዱ ሰዎች
  2. ቤተክርሰቲያን ሄደው ምርመራ ተደርጎላቸው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቤተሰቦች
  3. በቤተክርስቲየኑ የነበሩ ምርመራ ባያደርጉም፣ የኮቪድ-19 ህምም ስሜት ያለቸው ሰዎች ቤተሰቦች
  4. ከላይ የተጠቀሱት ሰዎቸ ጋር በቫይረሱ ሊጋለጡ በሚችሉበት ደረጃ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎቸ

እንደሚታወቀው በቫይረሱ ተይዘው ምንም አይነት የበሽታስሜት ላይኖራቸው የሚችሉ ሰዎች አሉ፡፡ የበሽታ ስሜትና ምልክት ባይኖራቸውም ቫይረሱን ወደሌሎች ማስተላለፍ እንደሚችሉም ይታወቃል፡፡ አሳዛኝ ሆኖ የነዚህ ሰዎች ቁጥር እስከ 40% ወይም ከዛ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰለዚህ በቤተክርሰቲያኑ ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት የሄዱ ሰዎች በሙሉ ምርመራ አድረገው በቫይረሱ አለመያዛቸው አስኪረጋገጥ ድረስ፣ ራሳቸውን ከቤተሰብና ከቤተዘመድ ወይም ከሥራ ቦታ አግልለው መቆየት የግድ ነው፡፡ ሰብኣዊነትም ነው፡፡

በአጠቃላይ፣ ቫይረሱ ከሚዛመተባቸው ቦታዎች አንዱ ሰዎች በብዛት የሚሰበሰቡት ቦታ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በተለይም በቤት ውስጥ በቂ ጥንቃቄ፣ ማለትም መራራቅና ማሰክ ማድረግ ቢኖርም፣ በሌሎች የአሜሪካ ከተሞች ቤተክርስቲያናት እንደተዘገበው ሥርጭት ሊኖር ይችላል፡፡ ዋናው ችግር ደግሞ፣ ወደ ቤተክርስቲያን ከሚሄዱት ምዕመናን መሀከል በዕድሜ የገፉ በቫይረሱ ቢያዙ ከፍተኛ ችግር ላይ ሊወድቁ የሚችሉ ሰዎች አሉበት፡፡

ሰለዚህ በኣካባቢው የኮቪድ ሥርጭት በሚገባ መጠን ባልወረደበት፣ በተለይም በማሀብረሰቡ ውስጥ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ባለበት ሁኔታ፣ አማራጩ፣ የሥርጭቱ ቁጥር በሚገባ እስኪወርድ ድረስ፣ የሰዎች ስብስን ማቆም ነው፡፡ በተለይም በዕድሜ የገፉ ሰዎችና ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሰዎች፡፡ ይህ ማለት፣ እያንዳንዱ ሰው የአካባቢውን የኮቪድ ሥርጭጥ መከታተል፣ በተለይም በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የኮቪድ መጠን ማወቅ ይገባዋል፡፡ በበቂ መረጃ ቁጥር መሥጠት ባይቻልም፣ የኢትዮጵውያኑ ማህበረሰብ ከሚገባው ድርሻ በላይ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች እንዳሉበት የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ፡፡ ችግሩ ሌሎች በተለይም ዕድሜያቸው ያልገፋ ሰዎች ወጣ ወጣ ቢሉና ቢያዙ ተመልሰው ወደየቤቱ መውሰዳቸው አይቀርምና፣ ለሌሎች ሰዎች፣ ለማህበረሰቡም ሲሉ በቂ ጥንቃቂ ቢያደርጉ ሰብአዊነት ነው፡፡ በቅርቡ በወጣ ዘገባ፣ የበሽታውን ሥርጭት የሚያጋግሉት ዕድሜያቸው በ30ዎችና በ49ዎች አመታት ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡

እንደ ማህበረሰብ ማሰብ ሰለሚኖርብን፣ በቂ ጥንቃቄ አለማድረግና ቫይረሱ እንዲሠራጭ ምክንያት መሆኑ የሚያሰክትሏቸውን መመልከት ያስፈልጋል፡፡

  1. በቫይረሱ ተይዘው የሚታመሙ ከዛም ህይወታቸው ሊያልፍ የሚችሉ ሰዎች መኖራቸው
  2. በማህበረሰቡ ውስጥ ሥርጭቱ ከፍ ባለ ቁጥር ማህበረሰቡ በሌሎች በኩል በተለየ አይን መታየት ሊጀምር ይችላል
  3. በንግዱ ወይም በቢዝነስ ላይ ያለው ወገን፣ ሥርጭቱ ቶሎ ወርዶ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲመለስ በሚመኝበት ወቅት፣ አዲስ የቫይረስ ሥርጭት ሲካሄደ ቢያዩ በፀጋ የሚቀበሉትም ነገር አይደለም፡፡
  4. ከላይ ቤተክርስቲያኑ በኩል ሥርጭት ሲከሰት፣ የመንግሥት አካላት በተለይም CDC ሰለ ሥርጭቱ ጥናት ማድረጉ የሚቀር ነገር አይደለም፡፡ ጥናት ካደረጉ ደግሞ ሁሉም ነገር በደንብ አጥንተው በፅሁፍ ማውጣታች አይቀርም፡፡ ሰለዚህ የኢትዮጵውያን ማሀበረሰብ ተብሎ መጠቀሱም አይቀርም፡፡ በእንደዚህ አይነት ጥናታዊ መግለጫ ስማችን መጠራቱም ሌላ ስሜት የሚፈጥር ነገር ነው፡፡

ሰለዚህ ቫይረሱን የምትደፍሩ ሰዎች፣ ለቤተሰብ፣ ለጓደኛ፣ ለማህበረሰቡም ስትሉ ሥርጭቱ ለመቀነስ ከሚታገሉ ሰዎች ጋር በመተባበር የሚገባውን ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ እዚህ ላይ፣ በቫይረሱ ተጋልጠው፣ ነገር ግን ምርመራ አናደርግም በማለት ምንም እንደሌለ አድርገው ከቤተሰብና ከሌሎች ጋር የሚደባለቁ ሰዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም፣ በእንደዚህ አይነት ፅሁፍ ላይ እከሌ ወይም እነከሌ ማለት አግባብ ሰለማይሆን እንጂ፣ መታመማቸውን እያወቁ ወደ ሥራ ቦታ በመሄድ ሌሎቹን ሰዎች ያጋለጡ ሰዎች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ በአሸማጋዮች ሁል ጊዜ የሚጠቅስ ነገር ቢኖር፣ አባክህን “ለሰው ብለህ” የሚለው አባባል ነው፡፡ 

ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

የሚመሰገን ሥራ መመስገን አለበት

በኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዋሸንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት በነሐሴ 23፣ 2012 ዓ.ም. ያወጣው መመሪያ ለብዙዎቻችን እፎይታ የሠጠ ብቻ ሳይሆን ታላቅ ምስጋና የሚገባው ነው፡፡


ከ August 23 አስከ Sept 14፣ 2020 (ከነሐሴ 17 እሰከ መስከረም 4፣ 2013) ባለው ጊዜ ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያናት እንዳይመጡ መመሪያ አስተላልፏል


እንደሚታወቀው የኮቪደ-19 ሥርጭት መተላለፊያ ከሆኑ መንገዶች አንደኛው የሰዎች ስብስብ (congregation) ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከሌሎች የሰዎች መሰባሰቢያ ቦታዎች ጋር፣ የተለያዩ አብያት ክርስቲያናት ተጠቂ መሆናቸው በደንብ የተዘገበ ነገር ነው፡፡ ብዙ የአብያተ ክርስቲያናት ካህናትና አመራሮች ባሉበት፣ እንደ ባለ ሙያ ተጋብዤ፣ ቸግሩን እንድገልፅና እንዳስረዳ  አጋጣሚውን ለፈጠሩልኝ በሙሉ፣ ለተሰጠኝ አክብሮትና ዕድል ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ፡፡

ሆኖም እንደባለሙያና እንደ ዜጋም፣ አንድ ወጥ ያልሆነ አሰራር ሲሰራ እንደሌሎች ባለሙያተኞች ሁሉ በመጨነቅ ነበር የተመለከትነው፡፡ ከዚሀ ቀድም አደባባይ ያልወጣ፣ በሌሎች ስቴቶች በኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የኮቪድ-ስርጭት እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ ግን በቨርጂኒያና በሜሪላንድ፣ የኮቪድ ሥርጭት ተከስቶ፣ ሰዎች መታመማቸው ከዛም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የነበረች ሰው ህይወት ማለፉ ይታወቃል፡፡

ተደጋግሞ እንደሚነገረው ይህን ቫይረስ የሚያመላልሰው ሰው ነው፡፡ ብዙዎች ከባድ ህመም ላይ አይወድቁም ቢባልም፣ ቫይረሱ ዞሮ ዞሮ የሚገድለውን ሰው ያገኛል፡፡ ሰለዚህ በአንድ ቤት ጣራ ሥር አብረን የማንኖር ሰዎች የምንገናኝ ከሆነ በታላቅ ጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡

ወደ መሠረታዊው ነገር ስንመለስ፣ ለህዘብ በይፋ የተነገረውና የሚታወቀው የስድስት ጫማ ወይም የሁለት ሜትር ርቀት ጠብቁ ነው፡፡ በዚህ የርቀት ጉዳይ ላይ ግን፣ ይህን ያህል ርቀት የት ቦታ ላይ ነው የሚተገበረው? የማይየሰራበትስ ቦታ ይኖር ይሆን የሚል ጥያቄ አለ፡፡ የጥናት ፅሁፎችና ኤክስፐርቶች፣ በጭንቀት የሚናገሩት ነገር፣ ይህ ቫይረስ ወደ አየር ብናኝነት(Airborne) የመቀየር ባሕሪ አለው:: አንደዛ አይነት ባህሪ ካለው ደግሞ፣ እንደ ድሮፐሌቶች በክብደት ምክንያት በስድስት ጫማ ክልል ውስጥ መውረዱን ይተውና በአየር ላይ በመንሳፈፍ በርቀት ይሄዳል ነው፡፡ እንግዲህ ምን አደባበቀን፣ እሰከ አሰራ ሁለት ጫማ ወይም ከዛ በላይ ድረስ ማለት ነው፡፡ ይህ በተለይ አደጋ የሚፈጥረው በቤቶች ወይም በመስብሰቢያ ቦታዎች ውስጥ ነው፡፡ ለምን? አየር ላይ እየተንሳፈፈ ያለውን ቫይስ ጠርጎ የሚወሰድ ነፋስ ወይም ደግሞ አርቴፊሻል የሆነ አየሩን ወደ ውጭ የሚስብ ነገር የለም ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ አየሩን ወደ ውጭ መሳብ (Negative air pressure) ይባላል፡፡ ሰለዚህ፣ ሰሚ ጠፋ እንጂ በቤት ውስጥ (In door gathering) በሚደረግበት ጊዜ ስድስት ጫማ በቂ ስላልሆን፣ ስብሰቡን ተው ተብሎ ይነገር ነበር፡፡ አንግዲህ የኢኮኖሚ ነገር፣ የፖለቲካ ነገር፣ የአውቃለሁ ባይ ነገር ተጨምሮበት፣ ሰሚ አላገኝም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሥርጭቱን ለመካለክለ፣ ማስክ በማድረግ ተገቢ ጥንቃቄ ማድረጉ የሚረዳ ቢሆንም፣ ዋናው ሚስጥር ያለው ግን፣ በቫይረሱ የተያዘና የታመመ ሰው፣ ወይም በቫይረሱ የተያዘና የህመም ስሜት የሌለበት ሰው ወደዚህ ስብስብ እንዳይደርስ ማድረግ ነው፡፡ እንዳየነው ከሆነ፣ እንደሰማነውም ከሆነ፣ አይደለም የበሽታ ስሜት የሌለበት፣ የበሽታ ስሜት ያለበት ሰው፣ እያወቀ ወደ ቤተ ክርሰቲያን የሄደበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያን ብቻ የተወሰነ አይደለም፣ በሥራ ቦታዎችም እያመማቸው የሄዱ ሰዎቸ አሉ፡፡ ወደ ሲያትል፣ በጀርባ በሚነገር አንድ አጋጣሚ፣ እያመመው ሲሰራ የነበረ ባለሙያ ጓደኞቹንና በሽተኞችን አስይዟል ይባላል፡፡ ማስተዋል ያለብን፣ በቴሌቪዢን የምናያቸው የስፖርት ውድድሮች፣ ከእግር ኳስ ጀምሮ፣ ተመልካች በሌለበት ነው የሚካሄዱት፡፡ የማይነግሩን ነገር ቢኖር፣ በሜዳው ውሥጥ የሚሰለፉ ሰዎች ሁሉም፣ ለኮቪድ ምርመራ አድርገው ነፃ መሆነቸው ሲታወቅ ብቻ ነው የሚሰለፉት፡፡ እንደ ሰፖርት አይነቱ፣ በየሶስት ቀናቱም ምርመራ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዋሸንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት በላኩት መመሪያ፣ “ካህናትን በተመለከተ ከወረርሽኙ ነፃ መሆናቸው በተረጋገጠ ካህናት ብቻ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጥ” የሚል አረፍተ ነገር አለበት፡፡ በጣም መመስገን የሚገባው አስተዋይነት የተመላበት ርምጃ ነው፡፡ ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ ተጎጂ የሚሆኑት በአብዛኛው ካህናቱና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው፡፡

እንግዲህ፣ በቫይረሱ ያልተያዘ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ካልዘለቀ እኮ ችግር አይኖርም፣ ግን በምን ይታወቃል? በተለይም፣ የበሽታ ስሜት የሌለባቸው፣ ነገር ግን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ40 ፐርሰንት በላይ በሆነበት ሁኔታ፡፡

ሌላው እንደዚህ አይነት ሥርጭት በሚከሰትበት ጊዜ፣ ጉዳዩ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ተወስኖ የሚቀርም አይደለም፡፡ ምዕመናኑ ከአንድ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላው እንደሚሄዱ ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ በመመሪያው በግልፅ እንዳስቀመጡት፣ ሌሎች ቤተ ክርስቲያኖች አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ወደ ቤትና ወደ ሥራ ቦታም ይዞት ይሄዳል፡፡ ሰለዚህ የሥርጭቱን መጠን በአካበቢው በተለይም በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲጨምር ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለእምነት ቤቶች ብቻ ሳይሆን  ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ትልቅ ችግር ይፈጥራል፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ ፀሎት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት መጀመሪያ መታወቅ ያለበት በአካባቢው ያለው የኮቪድ-19 ሥርጭት ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው የኮቪድ-19 ሥርጭት መጠን ነው፡፡ ሰለዚህ በሚኖሩበት ሰቴት የሥርጭቱ መጠን ወርዷል ቢባልም፣ በአካባቢውና በማህበረሰቡ ውሥጥ ያለው የሥርጭት መጠን ካልወረደ በሰተቀር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሀገር ቤት ከሆነ ደግሞ፣ ሥርጭቱ ወደ የት እየሄደ ነው ብሎ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ከምርመራ አቅም ጋር በተያያዘ የሚዘገበው ቁጥር አነስተኛ ቢመሰልም፣ አቅጣጫው ግን ጠቋሚ ነው፡፡ በኮቪድ ከመጣ “ካልታዘልኩ አላምንም” የሚያዋጣ ነገር አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው የኛ ማህበረሰብ የሚኖርበት በአብዛኛው ወይም የሚሠራበት ቦታ በአብዛኛው በቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቁት የአፍሪካን አሜሪካውያን ወይም ጥቁር አሜሪካውያን ጋር ነው፡፡ እኔ በማውቀው፣ በዋሽንግተን ዲሲ በብዛት ጥቁር አሜሪካውያን በሚገለገሉበት የጤና ተቋም፣ በኮቪድ መያዛቸው የተረጋገጠ የሰዎች ቁጥር በፐርስንት ሲታይ ከዲሲ ከተማ አማካይ ወይም ከሌሎች የዲሲ አካባቢዎች በጣም የበለጠ ነው፡፡ ሰለዚህ ቤተ ክርስቲያኗ በየወቅቱ መከታተል የሚገባት ቁጥር የአካባቢና የማህበረሰቡ የኮቪድ ሥርጭት መሆን አለበት፡፡

ከዚህ ቀደም በሚደረግ ውይይት፣ ቤተ ክርሰቲያኖች ይከፈቱ የሚሉ ምዕመናን እንዳስቸገሩም ይነገራል፡፡ የድምፅ ቆጠራ አለመደረጉ ነው እንጂ፣ በአንፃሩ፣ ለምን ቸኩለው ይከፍታሉ የሚለው ምዕመናን ቁጥር በጣም ከፍ ያለ እንደሆነ ነው የሚገመተው፡፡ ባካችሁ አትቸኩሉ፣ ፀሎቱ በሌላ መንገድ ይቀጥል የሚል ምክር ሲሰጥም፣ ምክሩን ወደ አለማዊና መንፈሳዊ ነገር የቀየሩትም አሉ፡፡ በተጨማሪም ሳይንስን የእምነት ጠላት አድርገው ያዩም የሚናገሩም አሉ፡፡ ሳይንስና እምነት በነገራችን ላይ ልዩነት ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ሰሞኑን ከሰማኋቸው ንግግሮች ሁለቱን መጥቀስ እወዳለሁ፡፡ አንደኛው ከዚህ ከኮቪድ 19 ጋር በቀጥታ አይገናኝም፡፡ ነገር ግን፣ ነገር ሲበላሽ፣ ሰው ሲበደል፣ ሌላም ሌላም ነገር ሲደረግ ዝም ብሎ ማየት የሚበጅ አይደለም፡፡ የራሴ አባባል “ዝም ይነቅዛል!” ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ለፕሬዜዳንትንት የሚወዳደሩት ጆ ባይደን “Silence is Complicity”  “ዝምታ ተባባሪ መሆን ነው” ሲሉ ሰማሁ፡፡

ወደ ኮቪድ-19 ስንመለስ፣ ሳይንስና እምነትን ለመነጣጠል፣ ሳይንስን ቅዱስ ያልሆነ ስራ አድረገው ለሚገልፁ ሰዎች ጥሩ መልስ የሰጡት፣ የአሜሪካው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ናቸው፡፡ ልብ በሉ ይህን አባባል፡፡ እሳቸው የሚሉት ሳይንስና እምነት አይለያይም፡፡ እንዲያውም ሳይንስ ለፀሎታችን መልስ ነው፡፡ “Science is the answer to our prayer” ትክክል! ረጋ ብለን ስንመለከት፣ የምንውጣቸው መድሀኒቶች፣ የሚሠጡን ህክምናዎች በሙሉ የሳይንስ ውጤቶች ናቸው፡፡ ታዲያ የሳይንስ ውጤትን እየተጠቀምን፣ ኮቪድ ላይ ግን በሳይንስ የተመረኮዘ ምክር ሲሰጥ፣ “ወራጅ አለ” ማለት ተመፃዳቂ አያደርገንም ወይ? ስንፀልይም እኮ፣ ምህረቱን ስጠን ነው አንጂ፣ በምን መልክ ምህረት እንደሚሰጠንም አንጠይቅም፡፡ ሳይንስ፣ ፈውስ ሆኖ ሲቀርብ፣ ሴትዮዋ እንዳሉት፣ የፀሎታችን መልስ አይደለም ወይ?

በኮቪድ ሲመጣ፣ ቅዱሱን መፅሐፍ በደንብ የሚያውቁት አባቶችም ሆነ የሀይማኖት መሪዎቸ፣ በየቤታችሁ ቆዩ ለሚለው መልክት ከመፅሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳሉ፣ ያሰተምሩማል፡፡ ለኔ፣ ከኦሪት ዘፀአት ጋር አገናኝተው የነገሩኝ፣ ስማቸውን የማልጠቅሰው አቡን ናቸው፡፡ ታዲያ እስከ መቼ ነው ባላነበበና ባላወቀ ሰው ተፅእኖ የምንቀሳቀሰው? የሀይማኖት ህግጋት የተሠጡ የተፃፉ ናቸው፡፡  ደግነቱ፣ እዛ ላይ ዲሞክራሲ የሚባል ጫጫታም የለበትም፡፡

በሳይንሱ በኩል የሚደረገው እየተደረገ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ከሆነ ሚስጥሩን ወይም መልክቱን የሚነገሩን የሀይማኖት መሪዎች መሆን አለባቸው፡፡ ለምን?

በሽታው ሰው ከሰው ጋር እንዳይገናኝ የሚያደርግ፤ ትንፋሽን ከውን የሚል፤ በቤትህ ተከተት የሚል ነው፡፡ በዚህ ላይ ግን፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የጤና ባለሙያተኞችን የማይሰሙበት፤ ህዝቡም ቢሆን መግባባት ያልቻለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እንደ ባቢሎን ግንብ ልሳን ባይቀየርም፣ መግባባት ግን አልተቻለም፡፡ ታዲያ ሚስጥሩ ምንድነው? መልክቱስ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ፣ መላሾቹ የሀይማኖት መሪዎች መሆን አለባቸው እላለሁ፡፡ ይህ ቫይረስና በሽታ፣ ፈጣሪ ሳያውቅ በድብቅ የሚሆን ነገርም አይደለም፡፡ ሚስጥር አለው፣ መልክትም አለው፡፡

ህብረተሰቡ ትዕግሥት ያጠረው ይመስላል፡፡ የትዕግሥት ነገር ከመጣ፣ እናቶቻችን፣ እህቶቻችንና ባለቤቶቻችን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ውነት እርግዝና የሚመች ሆኖ ነው? ነገር ግን፣ ዘጠኝ ወራትን በትዕግሥት ጠብቀው ነው የሚገላገሉትና እስኪ እነሱንም እናዳምጥ፡፡

ይሀ በሽታ እንደዛሬ መቶ አመት እንደታየው የህዳር በሽታ ካህናቱንም፣ ዶክቶሮችንም እያጠቃ ነው፡፡ እነሱ በቫይረሱ የሚያዙት በአገልግሎት ነው፡፡ እንግዲህ ይህን ቫይረስ በጥንቃቄ ከሚዋጉ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና ባለሙያተኞች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የአሜሪካን አሃዝ ብንጠቅስ፣ ከመቶ ሰላሳ ሺ በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያተኞች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ፣ ሌሎቻችን በማስተዋል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖረብናል፡፡ አሳዛኝ ሆኖ ከስድስት መቶ በላይ ነርሶች፣ ሀኪሞች በዚህ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፡፡ ለነሱም ማዘን ተገቢ ነው፡፡ ይከፈት እያልን የምንጮህበት ቤተ ክርስቲያነ አገልጋይ ከሌለው ምን ይሆናል? ሥርጭቱን አናባብሰው፡፡ የዛን ጊዜው የህዳር በሽታ ከመጠን በላይ የተሠራጨው የህዳር ሚካኤል በተከበረ ከሁለት ሶስት ቀናት በኋላ ነው፡፡ ይህን በማስታወስ ሰንመለከት፣ የዲሲ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የመስቀል በአልን በተመለከተ የወሰደው እርምጃ በጣም የሚከበርና የሚደነቅ ነው፡፡ (ሰለ ህዳር በሽታ በትረካ መልክ የተዘጋጀውን የፕሮፌሰር ፓንክረስት ጽሁፍን ትርጉም በዚሁ ድረ ገፅ ያዳምጡ)

በአሜሪካ፣ የግድ በቅፅር ግቢው ውስጥ ባይሆንም፣ ፀሎት በሌላ መንገድ በዙም፣ በዩቱብ እየተደረገ ምዕመናን ከቤታቸው ሳይወጡ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ነገር ግን፣ ለቴሌቪዥን ሥርጭት፣ በኢንተርኔት ሲኒማም ሆነ ሌላ ፕሮገራም ለማየት በየወሩ የምንክፍለው ነገር አለ፡፡ በሰልክም ቢሆን ለስልኩ የሚከፈል አለ፡፡ ታዲያ የሀይማኖት መሪዎችና ካህናቱ፣ ፀሎቱን በየቤታችን እንዲደርስ ሲያደርጉ፣ ለሌሎች የምንከፍለውን ያህል፣ በየሰበካችን መክፈል የምንችለውን መክፈል አለብን፡፡ ምንም አይነት አግልግሎት፣ መንፈሳዊም ቢሆን የራሱ ወጭ አለው፡፡ ሰለዚህ ካህናቱም ሆነ ዲያቆናቱ የተለመደውን አገልግሎት አንዲሠጡ፣ ቤተ ክርስቲያኖችም ቢሆን እንዳሉ እንደነበሩ እንዲቆዩ፣ ይህ ደመና ሲገፈፍም አንድ ላይ ተመልሰን ለምስጋና እንድንገናኝ አጃችን ፈታ ማድረግ ይረዳል፡፡ የወንድሜ ልጅ፣ ሲነግረኝ፣ “እነሱስ ከየት ያመጡታል?” በማለት የስድስት ወር የሚሆን ክፍያ በአንድ ጊዜ እንደላከ አጫወተኝ፡፡

እንግዲህ ይህን ጽሁፍ ሳዘጋጅ ዋናው የተነሳሁበት ምክንያት፣ በኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዋሸንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤትን ለማመስገን ነው፡፡ የኔ ቢጤ ጤና ባለሙያተኞችም ሆነ፣ ይህ ጉዳይ በከፍተና ደረጃ ሲያሳስባችሁ የነበራችሁ ሰዎችም እንደኔ ምስጋና ማቅረብ የምትፈልጉ መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ለጽሕፈት ቤቱም ሆነ፣ በተለይ ይህንን አመራር ለማውጣት ስብሰባ ላይ ለነበሩና ለሰብሳቢው ለአቡነ ፋኑኤል እንደ ባለሙያተኛ የከበረ ምሥጋና አቀርባለሁ፡፡ ሌሎችም ከዚህ ቀደም በአክብሮት ጠርታችሁ ውይይት አድርጋችሁ፣ በፅናት፣ አገልጋዮችንም ሆነ ምዕመናኑ ለመጠበቅ በወሰዳችሁት ርምጃ እግዚአብሔር ያክብራችሁ አላለሁ፡፡

Community health 

education in Amharic 

ቤተክርስቲያንና ፀሎት ቤቶች፣ በአሁኑ ጊዜ የተለመደውን አገልግሎት መሥጠት አይችሉም


በኮቪድ ሥርጭት፣ አንድ ሲደመር አንድ ከሁለት በላይ ነው 
አንድ ሰው ይበቃል! 5/13/2020
ምዕመናንም ሆነ የሀይማኖት መሪዎች ሊያነቡት የሚገባ 

የአሜሪካው CDC ሲዲሲ በሜይ 12 ባወጣው MMWR ዕትም፣ የቤተክርስቲያን ዘማሪዎች ልምምድ በሚያደርጉበት ጊዜ፣ አንድ የበሽታ ስሜት የነበረው ሰው በቦታው ከነበሩት ዘማሪዎች ከሰባቱ በስተቀር ለሁሉም በኮቪድ መያዝ ምክንያት መሆኑን ዘግቧል፡፡

ይህ ቫይረስ (ሳርስ ኮሮና ቁ2) ሳኮ2፣ ስመ ጥር የሆነበት አንዱ ባህሪው፣ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ መሻገሩ ነው፡፡ ዋናው መተላለፊያ መንገዱ በትንፋሽ በኩል የሚወጣው ቫይረስ ወደ ሌሎች ሰዎች መተንፈሻ አካላት ሲደርስ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ እንግዲህ፣ ቫይረሱን የተሸከሙት ከሰው መተንፈሻ አካል የሚወጡት ብናኞች መንሳፈፍ የሚችሉበት ርቀት ውስጥ የተገኘ ሰው በቀላሉ ለመያዙ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

ይህ ቫይረስ ሰው ሰብሰብ ሲል ይወዳል፣ የቁጥር ጉዳይ አይደለም፣ አንድም ሰው ይሁን ወይም ከዛ በላይ ቫይረሱ ካለበት ሰው አካባቢ ከተገኘ፣ ሥጦታውን መቀበሉ አይቀርም፡፡ ለዚህ ነው፣ ይህ ነገር እስኪያልፍ ከሰው ራቁ የሚባለው፡፡ ያም በአካል ርቀት ማለት ነው፡፡ ዘመኑ፣ በተለያዬ መንገድ ከሰው ጋር በርቀት መገናኘት ሰለሚችል፣ ማህበራዊ መራራቅ የሚለውን አባባል መቀበል ያዳግተኛል፡፡ Social distancing ከሚባል physical distancing ቢባል ይሻላል፡፡ ምን ይመስላችኋል?

ወደ ዘገባው እንመለስ፡፡

በማርች 17፣ 2020፣ በዋሽንግተን ሰቴት ሰካጊት ካውንቲ የቤተክርስቲያን ዘማሪዎች አባል የሆነ ሰው፣ ለካውንቲው የጤና ቢሮ ሪፖርት ሲያደርግ፣ 122 አባላት ያሉበት የዘማሪዎች ቡድን ውስጥ ብዙ ሰዎች ታመዋል ብሎ ነበር፡፡ ከነዚህ መሀል ሁለት ሰዎች የሰካጊት ካወንቲ ነዋሪዎች፣ አንድ ደግሞ ከሌላ ቦታ በሳኮ2 ወይም ኮቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ ይረጋገጣል፡፡ ሌሎች 25 የሚሆኑት ደግሞ፣ የኮቪድ-19 የበሸታ ስሜትና ምልክት ይታይባቸዋል፡፡

በዚህ ምክንያት፣ የካውንቲ የጤና ቢሮ፣ የዘማሪዎችን ስም ዝርዝር ይቀበልና ክትትል ሲያደርግ፣ በማርች 10 አንድ ላይ ልምምድ ሲያደርጉ ከነበሩ 61 ዘማሪዎች ውስጥ፣ የበሽታ ስሜትና ምልክት የነበረው አንድ ሰው ብቻ እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ የጤና ቢሮው በማርች 18 ባደረገው ክትትል፣ ከተከታተሏቸው 53 ሰዎች መሀከል፣ 33 በምርመራ የተረጋገጡ፣ 20ዎቹ ደግሞ፣ በኮቪድ-19 ተይዘዋል የሚያስብል የበሸታ ምልክት የነበራቸው ሆነው ይገኛሉ፡፡ በበሽታው ከተያዙ፣ ከ53 መሀከል፣ ሶስቱ ታመው ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፣ ሁለት ሰዎች ሞተዋል፡፡

በዚህ ሁለት ሰአት ተኩል በጨረሰ ልምምድ፣ ቫይረሱ በድሮፕሌትና(በአየር ላይ) በዕቃ ንክኪ አማካኝነት ለመተላለፍ አጋጣሚ አግኝቷል፡፡ በዚህ መሀል፣ ጎን ለጎን ተቀምጠው ምግብ አንድ ላይ ሲበሉ በነበሩ ሰዎች መሀከልና፣ ከዛ በኋላ ደግሞ ልምምዱ ሲያልቅ፣ ወንበሮችን መልሰው በደረደሩ ሰዎቸ መሀከል ነው ሊተላለፍ የቻለው፡፡ በልምምዱ ላይ ጮክ ብሎ መዘመርም፣ ከአፍ የሚወጣውን ድሮፕሌት አየር ላይ እንዲረጭ በማድረግ አሰተዋፅኦ አድርጓል፡፡

አንድ ነገር ማወቅ የሚኖርብን ቢኖር፣ ሰዎች አኩል ላያሠራጩ አንደሚችሉና፣ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ፣ ከሌሎች በበለጠ ብዛት ያለው ቫይረስ ከመተንፈሻ አካላታቸው ሰለሚወጣ ብዙ ሰው ማጋለጥ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ አነዚህ ሰዎች በእንግሊዝኛ፣ Super spreaders or superemitters ይባላሉ፡፡ ከዚህ በፊት የጎሽ ፅሁፎችን ተከታትላችሁ ከሆነ፣ በቅፅል ስም፣ “ዝናቡ” ሰለሚባል ሰው ያነሳሁትን ነጥብ ማሰታወስ ትችላላችሁ፡፡

ይህ ዘገባ፣ እንዳስተዋላችሁት ከሆነ፣ ለሳኮ2 በቀላሉ ለመተላለፍ አመቺ ሁኔታ መፈጠሩን ነው የሚያሳየው፡፡ ይህንን ምሳሌ ወደኛ ህብረተሰብ ብንወሰደው ትልቅ ትምህርት ይገኝበታል፡፡

ፀሎት ቤቶችን እንውሰድ፡፡ ቤተክርስቲያን ወይም መስጊድ ሌሎችም 

1ኛ፡ ሰው ተጠጋግቶ የሚቆምበት ወይም የሚፀልይበት ቦታ

2ኛ፤ ቅዳሴውን ወይም ፀሎቱን ተቀብሎ ማስተጋባት፣ ከመተንፈሻ አካል የሚወጣውን ቫይረስ ወደ አየር እንዲበተን ጥሩ አጋጣሚ መፍጠር

3ኛ፣ ለፀሎት መንበርከክ፣ መስገድ፣ ራሱ የትንፋሽ ጉልበትን እንደሚጨመር፣ በዚህም በተጨማሪ ሀይል፣ ቫይረሱ ያለበት ሰው አካባቢ ያለውን አየር እንደሚበክል ነው፡፡

4ኛ፤ በዚህ ዘገባ እንዳየነው፣ ዘማሪዎች የተቀመጡበትን ወንበር መልሰው የደረደሩ ሰዎች፣ ወንበሮቹ ላይ ከነበረው ቫይረስ ጋር በእጅ ንክኪ ስላደረጉ መተላለፍ መቻሉን ነው፡፡

5ኛ፣ በዕቃ ንክኪ በእጅ አማካኝነት ወደ አፍና አፍንጫ ከተሻገረ፣ መስቀል፣ መፅሀፍ ቅዱስ፣ የካህኑን እጅ መሳለም እንዴት ሊሆን ነው? አደጋው ለአሳላሚውም ለተሳላሚውም ነው፡፡ በዚህ ዘገባ እንዳየነው፣ በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ነው የተያዙትና የታመሙት፡፡ ፀሎት ቤት ደግሞ በብዛት ተገልጋዮች በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ቫይረሱ እንደልቡ እየተሠራጨ ባለበት በአሜሪካ፣ ቤተክርስቲያን፣ መስጊድና ሌሎችም ፀሎት ቤቶች ተመልሰው አገልግሎት ለመሥጠት ገና ረዥም ጊዜ መቆየት አለባቸው፡፡ መንግሥት በቂ ምርመራ አድርጎ፣ የተያዘውን ካልተያዘው ለይቶ፣ ሥርጭቱ በሚገባ መቀዝቀዙን፣ ቪቻል ቆሟል ካላለ በስተቀር፣ ተመልሶ ለመግባት ከባድ ነው፡፡

እዚህ ላይ፣ ሲዲሲ የሚለው፣ የሥራ ቦታ እንኳን ተመልሶ ይከፈት ቢባል፣ የሥራ ቦታው ሠራተኞቹን የማያጋልጥ ሁኔታ የመፍጠር ሀላፊነት የሥራው ባለቤት ወይም አሠሪው ነው ይላል፡፡ ግቡና አንብቡት፡፡ ሰለዚህ፣ ማንም ስብሰባና ሌሎችም ነገሮች የሚጠራ፣ ሰዎችን በርከት ብለው አንድ ላይ የሚገኙበት ሁኔታ የሚፈጥር ሰው፣ መሰብሰቢያ ቦታው ሰዎችን እንዳያጋልጥ ሀላፊነት ሊወሰድ ነው ማለት ነው፡፡

ምክሩ አንግዲህ

1ኛ. ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ፊት ለፊት የሚያደርጉትን ግንኙነት ማቆም አለባቸው፡፡ መሳሳምና መተቃቀፍ መቼ እንደሚመለስ አይታወቅም፡፡ አዚህ ላይ፣ ህንድና አካባቢው ቫይረሱ አሁን ካለበት ደረጃ የበለጠ ያልተሠራጨው በባሕላቸው እንደሚያደርጉት የርቀት ሠላምታ ስለሚጠቀሙ ነው የሚል ትንተናም ተመልክቻለሁ፡፡ የፈረንጁን ሰላምታ ለጊዜው ዞር አድርጉት፡፡ እሱማ በሀሉት በኩል ነው፣ በትነፋሽና እጅን ማኖ በማስነካት ጭምር ሰለሆነ፡፡

2ኛ. ከቁጥር በላይ መሰበሰብ አስፈላጊ አይደለም፡፡ አንደባበቅ እዚህ ላይ፡፡ አብሮ የሚኖር ቤተሰብ ካልሆነ፣ ከሌላ ሰው ጋር መገናኘቱ መቀራረቡ ተገቢ አይደለም

3ኛ. ከቤትዎ መውጣት የግድ ከሆነ፣ የስድስት ጫማ ርቀት (ሁለት ሜትር)፣ መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡

4ኛ፣ ከሰው ጋር በሚያገናኝዎት ቦታ ሁሉ፣ አፍና አፍንጫን መሸፈን ያስፈልጋል

5ኛ፣ ሰዎች፣ ጓንት ወይም ግላቭ ሲያደርጉ ይታያል፡፡ አድርጉ የሚል ምክርም የሠጠ የለም፤ ህክምና ቦታ ካልሆኑ፣ ወይም የታወቀ ታማሚን የሚረዱ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ዋናው ምክር የተጋለጠን እጅ (በንክኪ) ካልታጠቡ በስተቀር፣ አይን፣ አፍንጫና አፍዎን አይንኩ ነው የተባለው፡፡ ሰለዚህ ጓንት አድርገው፣ ጓንት ባደረጉበት እጃቸው ፊታቸውን የሚነኩ ከሆነ፣ ጥቅሙ ምን ላይ ነው፡፡ ማክሰኞ ዕለት፣ ቴሌቪዢን ሰመለከት፣ ሰማቸውን መጥቀስ የማልፈልገው ሴናተር፣ ጓንት አድርገው አየሁኝ፣ ጥቂት ቆየት ብለው፣ አገጫቸውና አፋቸውን አካባቢ ሲነካኩ ተመለከትኩና ባይገርመኝም፣ ምክሩን ማጋራት ፈለግሁ፡፡ ይልቁንስ፣ ጓንቱን አታስወድዱት፣ ለሚያሰፈልጋቸው ሰዎች አገልግሎት ይዋል፡፡ ከነካችሁ በኋላ፣ እጃችሁን ቶሎ ቶሎ ታጠቡ ነው ምክሩ፡፡ ቫይረሱ በእጅ በኩል በቀጥታ በቆዳው አልፎ አይገባም፡፡

ከመዝጋቴ በፊት አንድ ሲደመር ከሁለት በላይ ነው ያልኩበትን ላብራራ፡፡ በዚህ ዘገባ፣ አንድ ሰው ብቻ፣ ለሌሎች አቀብሎ፣ ሌሎች ደግሞ በተራቸው ለሌሎች ማቀበላቸው ይገለጣል፡፡ ይህ በአንግሊዝኛ Secondary attack ይባላል፡፡ የተላላፊ በሽታዎች ጉልበት መለኪያም ነው፡፡ ምክንያቱም የመዛመት ሀይሉን ሰለሚያሳይ፡፡ ሳኮ2፣ በዚህ ላይ ጉልበቱን አስመስክሯል፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ፣ መልሶ ማጥቃት እንበለው በፐርስንት ሲታይ 86.7 ነበር፡፡ ተጋልጠው በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መሀከል በተራቸው ቫይረሱን ለሌሎች ያሻገሩ ሰዎች ቁጥር ነው፡፡ መዛመት ይሏችኋል እንዲህ ነው፡፡


ቤተክርስቲየንና ፀሎት ቤቶች፣ በአሁኑ ጊዜ የተለመደውን አገልግሎት መሥጠት አይችሉም፡፡ ነገር ግን፣ ህዝብን የሚያገለግሉና በህዝብ የቆሙም ሰለሆነ፣ ሌላው ቢቀር፣ መደበኛ ወጪያቸውን መሸፈንም ሰለሚኖርባቸው፣ ድሮ ስታደርጉት የነበረውን ምፅዋት እንድትቀጥሉም ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ ነገ፣ ደመናው ሲገፈፍ፣ በአካልም ተገናኝቶ በጋራ መፀለይም እንዲቻል ርዳታችሁ በየሰበካችሁ አይለይ፡፡

 መልካም ንባብ