ተስፋ የሚሠጥ ምርምር (ኤች አይ ቪን ማዳን)

ምናልባትም ብዙ ለማያውቁ ሰዎች፣ በኤች አይ ቪ የተለከፉ ሰዎች የጤንነት ሁኔታ በጣም ተሻሽሎ የዕደሜ ጣሪያቸው ከሌሎች ጋር እየተቀራረበ ነው፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ዕድሜያቸው ከ70 አመታት በላይ እሰከሚሆን እንደሚኖሩ ግልፅ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን አስፈላጊ መድሐኒቶች በትክክል ከወሰዱና ህክምናም በጊዜ ከጀመሩ ነው፡፡
ከሌሎች በሽታዎች ጋር ሲነፃፀር፣ ኤች አይ ቪ በጣም የተሻለ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ይህን ለማለትም ያስደፈረው በየጊዜው እየተሻሻሉ የዳርቻ ጉዳታቸው መጠነኛ የሆኑ መድሐኒቶች በየጊዜው እየተሠሩ  ለህሙማኑ በመቅረባቸው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በቀን አንድ እንክብል ብቻ በመውሰድ ብዙዎች ሰዎች በሽታውን በመቆጣጠር ይኖራሉ፡፡ ታዲያ ትልቁ ጥያቄ መቼ ነው ይህን ቫይረስ ከሰውነት አስወግዶ መድሐኒት ማቆም የሚቻለው ነው፡፡


ለዚህም ብዙ ምርምሮች ይካሄዳሉ፡፡ በክትባት መልክ፣ መድሐኒቶች የመሳሰሉትን ጨምሮ፡፡ አብዛኞቹ ጥናቶች ደግሞ በዝንጀሮዎች ላይ ነው የሚካሄዱት፡፡
በቅርቡ በቦሰትን ከተማ በተደረገው አመታዊ የሳይንሳዊ ኮንፈረንስ በጣም ተስፋ የሚሠጥ የጥናት ውጤት በይፋ ለተስብሳቢዎች ቀርቧል፡፡ ጥናቱን ከመግለፅ በፊት ኤች አይ ቪን ለምን ማዳን እንደሚከብድ ማብራራት ተገቢ ነው፡፡


ሰዎች በኤች አይ ቪ በሚለከፉበት ጊዜ፣ የቫይረሱ ፕሮቲን ወይም የዘር ሰንሰለት በሰውነት በሚገኙ ሴሎች ውስጥ ይደበቅና ይቀመጣል፡፡ እነዚህ ሴሎች ደግሞ በባህሪያቸው ወደ ደም ዝውውር ብቅ ሳይሉ አርፈው በሰውነት ውስጥ ይቀመጣሉ፡፡ ታዲያ  ሰዎች መድሓኒት ቢወስዱም እነዚህ በእረፍት ላይ ያሉ ሴሎች ውስጥ የተደበቀውን የቫይረስ ክፍል ማግኘት አይችሉም፡፡ ነገር ግን በደም ውስጥ የሚዘዋወረውን ቫይረስ በቁጥጥር ስር ማዋል ስለሚችሉ፣ የቫይረሱ  መጠን በደም በሚለካበት ጊዜ፣ ላቦራቶሪዎች ቫይረስ የሚባል አላየንም ብለው ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ከህሙማን ጋር በሚደረገው ገለፃ (Undetectable ) ተብሎ ይጠራል፡፡ ቸግሩ ሰዎቹ መድሐኒት ሲያቋርጡ ወይም ሲያቆሙ፣ በነዚያ በእረፍት ላይ ባሉ ሴሎች ውስጥ ተደብቆ የተቀመጠው የቫይረስ ክፍል፣ በሴሎቹ ኪሳራ (የራሱን ልጆች እንበል) በሚሊዮን በሚቆጠር ቫይረሶቸ ማራባት ይችላል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ መድሐኒቱን ያለማቋረጥ መውሰድ የሚገባቸው፡፡ አለዚያ በሚሊዮን የሚቆጠረው ቫይረስ፣ ለሰውነት መከላከያ  የሚሆኑትን ሴሎች በማጥቃት ሰዎችን ወደ ኤይድስ ደረጃ ይወስዳል ማለት ነው፡፡ መድሐኒት እየወሰዱም በሽታውን ቀርቶ ቫይረሱን መቆጣጠር በራሱ ትልቅ ውጤት ነው፡፡  ወደ ማዳኑ ጥናት እንመለስ፡፡


በቀረበው ጥናት መሠረት፣ 44 ረሱስ (Rhesus monkey) የሚባሉ ዝንጀሮዎች የሰዎችን የሚመስል ግን በራሳቸው (SHIV ) በሚባል ቫይረስ እንዲለከፉ ይደረጉና በሰባተኛው ቀን መደበኛ የኤች አይ ቪ (TDF/FTC/DTG) መድሓኒት እንዲጀመርላቸው ይደረጋል፡፡ ከዚያም ያላማቋረጥ ለ96 ሳምንታት መደበኛውን የኤች አይ ቪ መድሐኒት ከወሰዱ በኋላ ከአራት ወገን ይከፈሉና፣


  • አንደኛው ወገን በደም ሥር የሚሠጥ አንቲቦዲ(antibody) (PGT121 ) በየሁለት ሳምንቱ ይሠጣቸዋል (ጠቅላላ አምስት ጊዜ ብቻ)
  • ሁለተኛው ወገን ደግሞ GS-9620  የተባለ መድሐኒት በአፍ በኩል በቱቦ ተደርጎ በየሁለት ሳምንቱ ይሰጣቸዋል( ጥቅላላ አስር ጊዜ ብቻ)
  • ሶስተኛው ወገን ደግሞ ሁለቱም መድሐኒቶች PGT121 እና GS-9620 እንዲሠጣቸው ይደረጋል፡፡
  • አራተኛው ወገን ደግሞ ምንም መድሐኒትነት የሌለው ማስመሰያ ነገር ይሠጣቸዋል፡፡ በእያንዳንዱ ወገን 11 ዝንጀሮዎች ነው ያሉት፡፡


ከዚያ በ130ኛው ሳምንት ሁሉም መደበኛውን የ ኤች አይ ቪ መድሓኒት እንዲያቋርጡ ይደረግና፣ ሰውነታቸው ውስጥ ቫይረሱ ተመልሶ ለመምጣቱ ምርመራና ክትትል ይደረጋል፡፡
በምድብ አራት በሚገኙ የማሰመሰያ መድሐኒት በተሠጣቸው ዝንጀሮዎች መደበኛውን መድሐኒት ባቋረጡ በ21 ቀናት ውሰጥ በሁሉም 11 ዝንጀሮዎች ላይ ቫይረሱ ተመልሶ ታየ፡፡
PGT121 እና GS-9620 የተሠጣቸው ዝንጀሮዎች ላይ ግን ከ11 በ6ቱ ላይ (55%) ቫይረሱ ተመልሶ ቢታይም በደም ምርመራ ጊዜ የቫይረሱ ቁጥር በሁሉም ላይ ከ400 በታች ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ቫይረሱ ተመልሶ የታየው ከ140 ቀናት በኋላ በመሆኑ ዘግየት ያለ ሁኔታ ታይቷል፡፡ ሌሎቹ በተናጠል PGT121 ብቻ በተሠጣቸው ሁለቱንም አይነት መድሃኒቶች ከወሰዱት ባነሰ ሁኔታ ነው ውጤቱ የተዘገበው፡፡
እነዚህ በምድብ ሶስት የሚገኙት 11 ዝንጀሮዎች በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ ሳይቆጠር ወይም ሳይገኝ እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ እንግዲህ መድሐኒቱንም አቁመው ነው፡፡
ማጠቃለያው በኤች አይ ቪ ከተለከፉ በኋላ መደበኛ መድሐኒት በመውሰድ ቫይረሱን በደም ዝውውር ስር በቁጥጥር ሥር ካዋሉ በሁላ፣ ቫይረሱን የሚያጠቃ አንቲቦዲና የሰውነት የተፈጥሮ መከላከያ የሚያነቃቃ መድሐኒት በመሥጠት በእረፍት ላይ ባሉ ሴሎች ተደብቆ የተቀመጠውን ቫይረስ በሚገባ ኢላማ ውስጥ ማስገባት ይቻላል ነው፡፡
ለወደፊት የነዚህ የ11 ዝንጀሮዎች ክትትል በጉጉት የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡
ምክር
1. በበሽታው ላለመለከፍ መጣር
2. ከተለከፉ ግን ቶሎ ወድ ህክምና ቀርቦ መድሐኒት መጀመር
3. መደሐኒት በየቀኑ ያለማቋረጥ በመውሰድም ቫይረሱን መቆጣጠርና የሰውነት የተፈጥሮ መከላከያ ቅስመ ሳይሰበር ረዥም ዕድሜ መኖር፡፡ 
4. ይህ ተስፋ የሚሠጠው የምርመር ውጤት በሰዎች ላይ ተሠርቶ የሚሰራ ከሆነ ደግሞ ወደሚጠበቀው ወደ ማዳን በመሸጋገር መድሐኒት ሳይወስዱ መኖር ለሚቻልበት ሁኔታ ተዘጋጅቶ መገኘት ነው፡፡
5. መድሀኒት አለመውሰድና ድብብቆሽ መጫወት ግን በሽታው ወደ ኤይድስ ደረጃ ተቀይሮ ለህይወት ህልፈት እንደሚዳርግ ማወቅ ጥሩ ነው፡፡
6. ሌለው ጠቃሚ ነገር፣ መድሐኒት እየወሰዱ ቫይረሱን የሚቆጣጠሩ ሰዎች ቫይረሱን ያን ያህል እንደማያስተላለፉ ማወቅ ነው፡፡ ያም ሆኖ መከላከያ ኮንዶም እንዲጠቀሙ ምክሩ ይቀጥላል፡፡

1.       በበሽታው ላለመለከፍ መጣር
2.       ከተለከፉ ግን ቶሎ ወድ ህክምና ቀርቦ መድሐኒት መጀመር
3.       መደሐኒት በየቀኑ ያለማቋረጥ በመውሰድም ቫይረሱን መቆጣጠርና የሰውነት የተፈጥሮ መከላከያ ቅስመ ሳይሰበር ረዥም ዕድሜ መኖር፡፡  
4.       ይህ ተስፋ የሚሠጠው የምርመር ውጤት በሰዎች ላይ ተሠርቶ የሚሰራ ከሆነ ደግሞ ወደሚጠበቀው ወደ ማዳን በመሸጋገር መድሐኒት ሳይወስዱ መኖር ለሚቻልበት ሁኔታ ተዘጋጅቶ መገኘት ነው፡፡
5.       መድሀኒት አለመውሰድና ድብብቆሽ መጫወት ግን በሽታው ወደ ኤይድስ ደረጃ ተቀይሮ ለህይወት ህልፈት እንደሚዳርግ ማወቅ ጥሩ ነው፡፡
6.       ሌለው ጠቃሚ ነገር፣ መድሐኒት እየወሰዱ ቫይረሱን የሚቆጣጠሩ ሰዎች ቫይረሱን ያን ያህል እንደማያስተላለፉ ማወቅ ነው፡፡ ያም ሆኖ መከላከያ ኮንዶም እንዲጠቀሙ ምክሩ ይቀጥላል፡፡

 ለሌሎችም ያካፍሉ

04/03/2018


March 4–7, 2018 | Boston, Massachusetts
Abstract Number: 73LB
PGT121 COMBINED WITH GS-9620 DELAYS VIRAL REBOUND IN SHIV-INFECTED RHESUS MONKEYS
Author(s): Erica Borducchi1, Peter Abbink1, Joseph Nkolola1, Mark G. Lewis2, Romas Geleziunas3, Dan Barouch1
1Beth Israel Deaconess Medical Center, Boston, MA, USA,2BIOQUAL, Inc, Rockville, MD, USA,3Gilead Sciences, Inc, Foster City, CA, USAየለንደኑ ኤች አይ ቪ(HIV) በሽተኛ ሊፈወስ ይችላል ተባለ
03/14/2020
 
በዚህ በኮሮና ተጠምደን እያለን፣ አንድ ሽው ብሎ ያለፈ በአጥኝዎች የቀረበ ዘገባ አለ፡፡ በቦሰተን ከተማ በተካሄደው፣ የኤች አይ ቪ HIV ወይም የተላላፊ በሽታ ሰፔሺያሊሰቶችንና ሌሎች ሳይንቲሰቶች ጨምሮ የሚያሰባስበው CROI የተባለ አመታዊ መድረክ አለ፡፡ ዘንድሮ አልተመቸም በቦታው አልተገኘንም፡፡ ያም ሆኖ በኮሮና ምክንያት ብዙ ሰው ሰብሰባውን በኮምፒተር ነው የተከታተለው፡፡

 ነገሩ፣ አንዲህ ነው፡፡ ከዚህ በፊት HIV ያለበት፣ የበርሊን በሽተኛ ተብሎ የሚታወቅ ሰው፣ በተደረገለት ህክምና እሰካሁን ድረስ፣ ቫይረሱ ተመልሶ ባለመምጣቱ፣ የ HIV መድሐኒት እየወሰደ አይደለም፡፡ የሱን ፈለግ በመከተል፣ ተመሳሳይ ህክምና ለብዙ ሰዎች ተሠጥቶ፣ ውጤቱም አልተሳካም፡፡ እሰካሁን ድረስ፡፡

ከሁለት አመታት ቀደም ብሎ፣ ይህ ተመሳሳይ ህክምና በጀርመንና በለንደን ከተማ ለ HIV በሽተኞች ተደርጎ፣ በየጊዜው ውጤቱን እየተከታተልን ነው፡፡

አነዚህ ልዩ ህክምና ሰለተደረገላቸው ሰዎች ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡

ሰዎቹ HIV ያለባቸው ሲሆን፣ የHIV መድሐኒትም እየወሰዱ ነበር፡፡ ያለ ዕድል ሆኖ በካንስር ተይዘው ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ የካንሰር አይነቶች ሲኖሩ፣ እነዚህን ሰዎች የያያዛቸው፣ ከደም ሴሎች የተነሳ ወይም የተገናኙ፣ Leukemia, lymphoma የተባሉ ካንሰሮች ናቸው፡፡ የለንደን በሽተኛ ተብሎ የሚታወቀው ሰው፣ ሆደጂክንስ ሊምፎማ Hodgkins Lymphoma ነው የተገኘበት፡፡ ለእንደዚህ አይነት ካንስር ዋናው ህክምና፣ የሰውየውን የካንሰር ሴሎች ጥርግ አድርጎ አውጥቶ፣ በሌላ ሰው ከተሠጠ ትክ የደም ሴሎች በመሥጠት ነው ካንሰሩን ማስወገድ የሚቻለው፡፡

ታዲያ፣ ከበርሊኑ በሽተኛ፣ ትምህርት በመውሰድ፣ የሌላ ሰው ደም ሴሎች በሚሠጡበት ጊዜ፣ በተፈጥሯቸው HIV ከማይዛቸው ሰዎች ደም ሴሎች ተሰብሰቦ ነው የተሠጠው፡፡ አዎ፣ HIV ጭራሽ የማይዛቸው ሰዎች አሉ፡፡ እሱን ለሌላ ቀን እናድርገው፡፡

የለንደኑ በሸተኛ ይህንን ህክምና ካደረገ በኋላ፣ ካንሰሩ በቁጥጥር ሥር ሆነ፡፡ HIV ውም ቢሆን በቁጥጥር ሥር ሆኖ የHIV መድሐኒት መውሰድ አቆመ፡፡ ይህ ሲሆን፣ ሀኪሞቹ በየጊዜው የደምና ሌሎች ምረምራ እያደረጉ፣ ቫይረሱ ማንሰራራቱን ይከታተላሉ፡፡ ህክምና በተደረገለት በ18 ወራት፣ ሀኪሞቹ፣ የሰውየው ሁኔታ አቅርበው፣ ቫይረሱ እንዳልተመለሰ አስታወቀው ነበር፡፡

ፍራቻው ምንድነው ካላችሁ፣ በደም የሚዘዋወረው ቫይረስ፣ አይደለም በዚህ አይነት ህክምና፣ በመድሐኒቶችም ቢሆን ቁጥጥር ሥር ይውላል፡፡ ይሄ ራሱን የቻለ ርእስ ነው፡፡ ነገር ግን ቫይረሱ፣ በደም ሴሎችና በሌሎች የሰውነት ከፍል ሴሎቸ፣ አንጎልና ዕጢዎች ውስጥ ተደብቆ መቆየት ይችላል፡፤ የሚገርም ነው፡፡ በጣም አድፋጭ ቫይረስ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በተደረገ ጥናት ስሌት፣ ቫይረሱ ሜሞሪ ሲሎች memory cells ውስጥ በመደበቅ እሰከ ስልሳ አመታት ድረስ መቆየት እንደሚችል ከተገነዘብን ቆይተናል፡፡ ታዲያ ለፈውስ ችግር የሆነው፣ ይህ አድፋጭ፣ በሴሎች ውስጥ ተደብቆ የሚቆየው ቫይረስ ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ ሰዎች ተዘናግተውም ሆነ በሌላ ምክንያት የHIV ድሓኒቶቻቸውን ሲያቋርጡ ቫይረሱ ተመልሶ የሚመጣው፡፡ አሁን ግን ካስተዋላችሁ፣ በካንሰሩ ምክንያት የተደረገው ህክምና፣ የሰውየውን የራሱን ቫይረሶች ሙልጭ አድርጎ በማውጣት ሰለሆነ፣ ተስፋና ግምቱ፣ አድፋጩን ቫይረስ ደብቀው የሚያሰቀምጡ ሜሞሪ ሴሎች የሉም ነው፡፡

በዚህ በለንደን በሽተኛ በተደረገው ክትትል፣ ቫይረሱ ሊደበቅባቸው የሚችሉ ሴሎችና ሥፍራዎችን በየጊዜው ይምረመሩ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ በሰውነት ውስጥ ቫይረስ ሲኖር፣ በኬሚካል ደረጃ ሰውነት የሚያሳያቸው ኮምፓውንዶቸ ሳይቀር ምርመራ ይደረጋል፡፡

ሰውየው፣ ይህ ሕክምና ከተደረገለት ከሁለት አመት ተኩል በላይ ሆኗል፡፡ መድሐኒትም (የHIV) አይወስድም፡፡ አስካሁን ድረስ፣ ነብስ ያለው ቫይረስ ዝር አላlበትም፡፡ የተደረጉት ምርመራዎችም ቢሆን፣ በሰውነት ውስጥ ቫይረስ መኖሩን የሚጠቁም ሆነው አልተገኙም; ይላሉ፣ የሰውየው ሀኪሞችና ተመራማሪዎቹ፡፡ አሁን፣ ደፈር ብለው፣ ስሌትም በመጨመር፣ ሰውየው ከHIV ሊፈወስ ይችላል ብለው መግለጫ ሠጡ፡፡ የወደፊት አነጋገር ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ፣ እነ ቀንጭቦ፣ ለቀም አድርገው በማህበራዊ ሜዲያ፣ HIV ዳነ ብለው መለፈፍ የጀመሩት፡፡

ነገሩ እንደሱ አይደለም፤ የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጭ ነው፡፡ ነገር ግን፣ በሰውየው አካል፣ በአንዳንድ ቦታዎች፣ ቫይረሱ ከመጠን በታች በሆነ ቁጥር አለ፤ ነገር ግን ስንኩል (Defective) ስለሆነ፣ ማንሠራራት የማይችል ነው፡፡ እሰካላንሠራራ ድረስና ሰውነት ምልክት አስካላሰየ ድረስ፣ የHIV መድሐኒት መውሰድ አስከቆመ ድረስ፣ እንደፈውስ ሊቆጠር ይችላል ነው፡፡ ያ ግን የማባራ ረዥም ጊዜ ክትትል ያስፈልገዋል፡፡

ይሁን፣ ጭራሽ መዳን ቢቻልስ ይህ አይነት ህክምና ለሁሉም በHIV ለተያዘ ሰው መደረግ ይቻላል ወይ? በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በዚህ መንገድ ህክምና ተድርጎላቸው ውጤቱ ያልተሳካ ሰዎች ጉዳይስ?

ህክምናውን መልሰን እናስተውል፡

በጣም አታካች የሆነ፣ ውድም የሆነ አሠራር ነው
የሌላ ሰው ደም የግድ መኖር አለበት፤ ያ ሰውም HIV የማይዘው መሆን አለበት
የሰውነት የደም ሴሎችና ሌሎችም ከሴሎቹ ጋር የተያያዙ ክፍሎች ከሰውነት ጥርግ ብለው ሲወጡ፣ አዲስ የተሠጡት ሴሎች፣ በተቀባዩ ሰውነት ውስጥ አድገውና ተባዝተው፣ በሽታ መከላከል እስኪጀምሩ ድረስ፣ ሴል ተቀባዩ ሰው በጣም በከፍተኛ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚሆነው፡፡ ከውጭ ኢንፌክሽን ቢይዘው፣ በባዶ ቤት፣ መከላከያ በለለበት አስጊ በሽታ ይፈጠራል፡፡ አሁን፣ ይህ አይነት ህክምና እየተሻሻለ በመምጣቱ፣ ይህን አደጋ ቀነስ ማድረግ ተችሏል፡፡

ስለዚህ ይህ አይነት ህክምና ለማንም ዝም ብሎ የሚደረግ አይደለም፣ የለንደኑም ሆነ የበርሊኑ በሽተኛ፣ የደም ካንሰር ስለነበራቸው፣ አማራጭም ሰላልነበራቸው ነው የተደረገው፡፡

እና ዜናው ጥሩ ነው፣ ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ ሊያሸጋግር ይችላል፡፡ ተስፋም ይሠጣል፡፡ ለሁሉም የሚሆን ግን አየደለም፡፡

አሁን የHIV መድሐኒቶች በቀን ወደ አንድ ኪኒን ብቻ ከተቀየሩ ሰንብተዋል፡፡ እንደ ሁኔታቸው፣ ሁሉም HIV ያላቸው ሰዎች በቀን አንዲ ኪኒን ብቻ ላይወስዱ ይችላሉ፡፡ ከዋጋ ወድነት አንፃርም፣ በሚያድጉ አገሮች፣ ወጭውን መሸፈን ሰለማይቻልም፣ ከሁለትና ከዚያ በላይ መድሓኒቶች ይወሰዳሉ፡፡ እነዚህን መድሐኒቶች ያለማቋረጥ በመውሰድ፣ ቫይረሱን በመቆጣጠር፣ የመከላከያ አቅማቸውን አጠንክረው የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ አስተውላችሁ ከሆነ ደግሞ፣ የነዚህ ሰዎች ዕደሜ ጣራ HIV ከሌለባቸው ሰዎች ጋር እየተቀራረበ፣ ረዥም አመታት እየኖሩም ነው፤ ሊኖሩም እንደሚችሉ ነው፡፡

ማሳረጊያው፣ “ጎመን በጤና” ነው፡፡ ገና በምርምሩ የተገኘው ውጤት ተስፋ ሠጭ ቢሆንም፣ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች፣ ኪኒኖችን እየወሰዱ በሰላም መሰንበት ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ የነቀንጭቤን ወሬ ሰምተው፣ ሰዎች እንዳይዘናጉ ነው፡፡ መዘናጋት ደግሞ በሁለት በኩል ነው፡፡ አንደኛ ቫይረሱ ያላቸውና መድሐኒት የሚወስዱ ሰዎች፣ ተስፋ አድረገው እንዳያቆሙ፤ ሁለተኛው ደግሞ፣ መዳን ከተቻለማ ብለው፣ ቫይረሱ የሌለባቸው ሰዎች በመዘናጋት በቫይረሱ ሊያዙ ወደሚችሉባቸው አስጊ ነገሮች እንዳያመሩ ነው፡፡

መድሐኒቱ ከተገኘና በትክክል ከተወሰደ፣ ሥር ከሠደዱ በሽታ ከሚባሉ ሁሉ አንደ HIV በቁጥጥር ሥር የሚውልና፣ ቫይረሱ ላለበት ሰው፣ አንደማንም ሰው ሰላማዊ ኑሮ መቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ የለም ብዬ ስናገር፣ ከሙያ አንፃርም ነው፡፡

Health and History

ከኤች አይ ቪ የተፈወሰችው ሶሰተኛ ሰው 02,19,2022

 ከኤች አይ ቪ (HIV) ፈውስ ማግኘት ቀላል ነገር አለመሆኑን ከተገነዘብን ሰንብተናል፡፡ ከዚሀ ቀደም ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው ከዚህ ቫይረሰ ተፈውሰው መድሐኒት መውሰድ ያቆሙት፡፡ የመጀመሪያው ሰው የበርሊን ሰውዬ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከኢንግላንድ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሰዎች የተፈወሱበትን መንገድ ወይም ዘዴ ተከትሎ ሙከራዎች ቢደረጉም አልተሳካም፡፡

አሁን በቅርቡ፣ በኤችአይቪ ሳይንስ በከፍተኛ ደረጃ የሚታወቀው የባለሙያተኞች ስብሰባ (CROI) ላይ የቀረበ መረጃ እንደሚያሳያው፣ ሶሰተኛ ሰው በአሜሪካ፣ ከኤች አይቪ ተፈውሳ መድሀኒት ካቆመች 14 ወራቶች የሆናት ሴት ጉዳይ በይፋ ተገልጧል፡፡

ከሷ ቀደም ብለው የተፈወሱት ሰዎች፣ የደም ካንሰር ተገኝቶባቸው፣ ለዚህ የደም ካንሰር ህክምና አንዱ ዘዴ ደግሞ በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኛውን ካንሰር ያለበትን የነሱን ደም ጠርጎ አውጥቶ በሌላ መተካት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ለነዚህ ሁለት ሰዎች የተደረገው ነገር፣ የሌላ ሰው ደም በሚሠጣቸው ጊዜ፣ ኤች አይ ቪ በተፍጥሯቸው መያዝ ከማይችሉ ሰዎች ደም ተወስዶ ነበር፡፡ አዎ፣ በተፈጥሮ ኤች አይ ቪ ቫይረስ የማይያዙ ሰዎች አሉ፡፡ የሌላ ጊዜ ርዕስ እናድረገውና ወደ ፈውሱ እንመለስ፡፡

ይህች ከኤች አይ ቪ ተፈወሰች የተባለችው የመጀመሪያዋ ሴት፣ የኤች አይ ቪ መድሐኒት እየወሰደች እያለች፣ ማይሎይድ ሊውከሚያ የሚባል የደም ካንስር ተገኝቶባት፣ ለካንሰሩ ህክምና ተደርጎላት ከካንስሩ ነፃ ከሆነች አራት አመት ተኩል ሆኗታል፡፡ ከዚህ ቀደም የተጠቀሱትን ሰዎች ፈለግ በመከተል፣ ለዚህ በሽተኛ የደም ሴሎች ትክ ሲደረግ፣ በኤች አይ ቪ ከማይያዙ ሰዎች ሴሎች ተወስዶ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ሴትዮዋ የኤች አይ ቪ መድሐኒት እየወሰደች እያለችም፣ ቫይረሱ በቁጥጥር ሥር ነበር፡፡ በአንግሊዝኛ undetectable ማለትም በደም ምርመራ ለቁጥር የሚበቃ ቫይረስ አልነበራትም፡፡ በዚህ ወቅት መደሐኒታቸው በትክክል የሚወሰዱ ሰዎች ይህ ቫይረሱን የመቆጣጠር ችሎታ አላቸው፡፡ ቸግሩ ምንድን ነው መቆጣጠር ማለት ፈውስ ስላልሆነ፣ መድሐኒት ሲያቆሙ ቫይረሱ እንደገና ብቅ ይላል፡፡ ለዚህ ነው ያለማቋረጥና ያለመታከት መድሐኒት እንዲወስዱ የሚደረገው፡፡ እንግዲህ ሲትዮዋ ለካንሰር ህክምና ሲደረግላት ከቫይረስ ነፃ የሆኑ ሴሎች ብቻ ሳይሆን በቫይረሱ የማይያዙ ሴሎች ሰለተቀበለች፣ መድሐኒት ስታቆም ተመልሶ የታየ ወይም የተቆጠረ ቫይረስ ባለመኖሩ ነው ተፈውሳለች ተብሎ ሪፖርት የተደረገው፡፡

ይህ አይነት ህክምና ፍንጭ የሚሠጠው የኤች አይቪ ቫይረሰን ከሰውነት ጠርጎ ለማውጣት በሴል ደረጃ ህክምና መደረግ እንደሚችል ነው፡፡ የዚች ሴትዮን ህክምና ለየት የሚያደርገው ሴሎች የተገኙት ከዕትብት ሲሆን፣ ነገር ግን በቂ ደም ሴሎች ማግኘት ባለመቻሏ፣ በቫይረሱ መያዝ የማይችሉ ከዘመዶቿ ተጨማሪ ደም አግኝታለች፡፡

መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር፣ ሶሰቱ ሰዎች እሷን ጨምሮ ወደዚህ አይነት ህክምና የሄዱት የደም ካንሰር ሰለነበራቸው ነው፡፡ እናም ይህ አይነት ህክምና በአለም ላይ በአሁኑ ወቅት 36 ሚሊዮን ይሆናሉ ለሚባሉት በኤች አይ ቪ ለተያዙ ሰዎች የሚሠጥ ህክምናም አይደለም፡፡

ወደ ሴትዮዋ ስንመለስ፣ የሌላ ሰው የደም ሴሎች ከተቀበለች በኋላ፣ አዲስ የተቀበለቻቸው የደም ሴሎች በሰውነቷ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተራብተው በቂ ደረጃ ከደረሱ በኋላ በ17 ቀናት ውስጥ ከካንስሩ ነፃ ስትሆን፣ ከሆስፒታል ስተወጣ የኤች አይ ቪ ምርመራ ሲደረግላት በኤች አይ ቪ አልተያዘችም የሚል ምላሽ ነው ያገኙት፡፡ ከላይ እንደተቀሰው፣ የኤች አይ ቪ መድሐኒት መውሰድ ካቆመች በኋላም በተደረገው ክትትል ከቫይረሱ ነፃ እንደሆነች ተገልጧል፡፡ እንግዲህ የበርሊኑ በሸተኛ፣ የለንደኑ በሽተኛ ከሚባሉት ጋር ተደምራ ሶስተኛ የሆነቸው ሰው ታሪክ ይህ ነው፡፡ አሳዛኝ ሆኖ የበርሊኑ ሰው ከኤች አይ ቪ ነፃ ቢሆንም በሌላ ምክንያት ህይወቱ ካለፈ ሰንበት ብሏል፡፡

ዋናው ነገር፣ ፈውስ አልተገኘም አንጂ፣ መድሐኒታቸውን በትክክል የሚወሰዱ ሰዎች ቫይረሱን መቆጣጠር ሰለሚችሉ በቫይረሱ ምክንያት ሊመጣ ከሚችለው በሽታ ነፃ ሆነው ረዥም ዕድሜ እየኖሩ መሆኑን መታወቅ አለበት፡፡ በተጨማሪም፣ መድሐኒት በመውሰድ ቫይረሱን የሚቆጣጠሩ ሰዎች፣ ቫይረሱን ወደሌላ ሰው ማስተላለፍ እንደማይችሉ ከታወቀም ሰንብቷል፡፡ በዚህ ምክንያት መድሐኒት አያቁሙ አንጂ በአንግሊዝኛ አጠራር Functional cure ከበሽታው ተፈውሰዋል ነው የሚባሉት፡፡ ከቫይረስ ፈውስ ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ መድሐኒት ያለማቋረጥ መውሰድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሌሎች በሸታዎች ጋር ሲነፃፀር፣ በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎችን የተሻለ ደረጃ ላይ ነው የሚያስቀምጣቸው፡፡ ምክንያቱም መድሐኒት እየተወሰደ እንኳን በሽታው እንደ ኤች አይ ቪ በቁጥጥር ስር የሚሆኑ የበሽታ አይነቶች ካሉ እንኳን በጣም ጥቂት ቢሆኑ ነው፡፡ በአብዛኛው አንድ ኪኒን ብቻ በመውሰድ በሽታ ላይ ሳይወድቁ እንደ ሌሎች ሰዎች የመኖር ሁኔታ በራሱ ተመስገን የሚያስብል ነው፡፡ 
መልካም ንባብ

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic