ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

የአዋቂ ስኳር በሽታ (Diabets Type 2) ላለባቸው ሰዎች ቡና እና አረንጓዴ ሻይ መጠጣት ዕድሜ ይጨምራል ወይ?
11/01/2020
 
ስለ ሁለቱ መጠጦች የተጠናውን ጥናት ውጤት ከማካፈሌ በፊት፣ ስኳር በሽታ ሲባል የትኛውን ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለብኝ፡፡ የስኳር በሽታ ብዙ አይነቶች ቢኖሩትም፣ በዋናነት የሚታወቁት ግን፣ በአሁኑ ጊዜ አይነት አንድና ሁለት የሚባሉት በእንግሊዝኛ (Tyep 1 and Tyep 2 Diabetes Mellitus) ተብለው የሚጠሩት ናቸው፡፡ በዚህ ርዕስ የምንጠቅሰው፣ ሁለተኛውን አይነት፣ ማለትም በአማርኛ የአዋቂዎች ብለን የምንጠራውን ነው፡፡ ለምን? ይኼኛው የሚከሰተው በልጅነት ሳይሆን በአዋቂ የዕድሜ ዘመን ውስጥ ባሉ ሰዎች ነው፡፡

ወደ ርዕሱ ስንመለስ፣ የምግብና የመጠጥ አይነቶችን በተመለከተ፣ በብዛት፣ ሰውነት ላይ ጉዳት የሚያመጡት ይታወቃሉ፡፡ ለሰውነት ጠቃሚ ናቸው የሚባሉም፣ በግምት ጓደኛና ጎረቤት ከሚያወሩት ውጭ በጥናት ብዙም አይወጡም፡፡ አሁን ግን ብቅ ብቅ አያሉ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ተጠንተው፣ ከበሬታ ባላቸው የሳይንስ መፅሔቶች ታትመው ለህዝብ ከሚቀርቡት መሀል፣ አንዱ የቡና ታሪክ ነው፡፡ ይህም ቡና መጠጣት በጉበት ላይ የሚያስከትለው ጤናማ ለውጥ ተደጋግሞ ሰለቀረበ፣ አሁን በመርህ ደረጃ፣ በጉበት ውስጥ ትርፍ ጮማ (Fatty Liver Disease) ላለባቸው ሰዎች በቀን አስከ ሶስት ኩባያ ቡና እንዲጠጡ በሀኪም ደረጃ ይመከራል፡፡ እኔም፣ ከሥራዎቼ አንዱ ሰለሆነ ይህንን ነገር በስፋት ለበሽተኞች ለመምከር እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ የመከርኩበትም ጊዜ አለ፡፡

ወደ ዋናው ርዕስ ስንመለስ፡ ቡና መጠጣትና ከሱም ጋር አብሮ አረንጓዴ ሻይ መጠጣት፣ የአዋቂ ስኳር በሽታ ላለባቸው ሰዎች ላይ ዕድሜ ይጨምራል ሲሉ፣ ከጃፓን በኩል ተመራማሪዎች ያቀረቡት ጥናት BMJ Open Diabetic Res Care በተባለ መፅሔት የወጣውን ነው የማቀርብላችሁ፡፡ ይህ መፅሄት፣ ከበሬታ ያለው ብቻ ሳይሆን፣ ከአሜሪካው የዳያቤትስ አሶሴሽን (ADA American Diabetes Association)ጋር በመተባበር ሰለሚሰራ፣ በዚህ መድረክ ታትሞ የወጣ የምርምር ጥናት በደንብ ታይቶ ተመክሮበት ነው እንዲታተም የሚደረገው በሚል ለአንባብያን እያቀረብኩ ነው፡፡ ሰለዚህ እንዲህ አይነት ነገር ለህዝብ ሲቀርብ፣ መታተሙ ሳይሆን እነማን ናቸው ጥናቱን ከፍተኛ ግምት ሠጥተው፣ በትክክለኛው መንገድ መጠናቱን አይተው የተቀበሉት የሚለውን መመልከት ከዛም እንደ መረጃ አድርጎ መቀበል ወሳኝ ነው፡፡ በድረ ገፅ የተቀመጠውን ሁሉ፣ ማንበብ ባይጎዳም ለመቀበል ግን አስቸጋሪ ነው፡፡

አጥኝዎቹ ያደረጉት የአዋቂ ስኳር በሽታ ያለባቸውን የ4923 ሰዎች መረጃ ነው የመረመሩት፡፡ ከነዚህ መሀል 2790 ወንዶች ነበሩ፡፡ አማካይ ዕድሜ 66 አመት ነበር፡፡ የክትትል ጊዜ በአማካይ 5.3 አመት ሲሆን፣ በዚህ አመታት ባሉ ጊዜ ውስጥ እነዚህ ሰዎች ቡናና አረንጓዴ ሻይ እንዴት እየጠጡ እንደነበር መረጃ ይሰበሰብ ነበር፡፡ ይህም ሰዎች ራሳቸው ሰለ ቡናና አረንጓዴ ሻይ አጠጣጣቸው መልስ የሚሠጡበት መጠይቅን በመሰብሰብ ነበር፡፡ ጥናቱ እየተካሄድ በጥናቱ ከታከተቱት መሀል 309 ሰዎች ሞተዋል፡፡

በጥናቱ ውጤት አድርገው ተመራማሪዎቹ ያቀረቡት፣ ቡና መጠጣት፣ ሻይ መጠጣት ወይም ሁለቱንም አንድ ላይ መጠጣት በአጠቃላይ ከሌሎች ጋር ሲወዳደር በማንኛውም ምክንያት የሚከሰተውን የሞት መጠን ከመቀነስ ጋር የተያያዘ ነው የሚል ነገር ነው፡፡ እዚህ ላይ ስታቲሰቲክስ በአሃዝ ሲገለፅ ትንሽ ግር የሚል ሁኔታ ቢፈጥርም፣ ድምዳሜው ተቀባይነት ያገኘው ደግሞ በስታቲስቲክስ ሰለተገለፀ ነው፡፡ እኔም እሱኑ ላቅርብላቸሁ፣ ወደፊት ግን መልመድ ይኖርብናል፡፡

በዚህ መሠረት

አርንጓዴ ሻይ የሚጠጡ ሰዎች ከማይጠጡት ጋር ሲወዳደር፣ አነሰ ቢባል በቀን እንድ ኩባያ የሚጠጡት ሰዎች ባጠቀቃይ የመሞት ሁኔታ አደጋው በአሃዝ (Hazard Ratio) 0.85 ነው፡፡ በቀን ሁለት ወይም ሶስት ኩባያ ሻይ ለሚጠጡ ሰዎች ደግሞ አደጋው ወደ 0.73 ይወርዳል፡፡ በቀን አራት ኩባያ ለሚጠጡ ሰዎች ደግሞ አደጋው ወደ 0.6 ይወርዳል ይላሉ፡፡ የኋለኛውን ግን ማሰብ ይከብዳል፡፡ በቀን አራት ጊዜ? ለማንኛውም ጃፓኖች ናቸውና አይገርምም፡፡ ባህልም ሳይሆን ይቀራል?

ወደ ቡናው ስንሄድ ደግሞ፣ በቀን ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ኩባያ ቡና የሚጠጡ ሰዎች ከማይጠጡት ጋር ሲወዳደር፣ የሞት አደጋው ወደ 0.59 (HR = 0.59, 95% CI, 042-0.82) ይወርዳል፡፡ ህም፡፡

አሁን የቀረው፣ ሁለቱንም የሚጠጡ ሰዎች ምን ተጠቀሙ የሚለው ነው፡፡ እንደ ጥናቱ ውጤት ከሆነ፣ ሁለቱንም እንጠጣለን ብለው መጠይቁን ለሞሉ ሰዎች ጭራሽ ቡናም ሆነ ሻይ ከማይጠጡ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር ትልቁ ጠቀሚታ የታየው ሁለቱንም እንጠጣለን ብለው ለሞሉ ሰዎች ነው፡፡ በአሃዝ ሲገለፅ፣ በቀን ከሁለት አስከ ሶስት ኩባያ ሻይና በተጨማሪም ሁለት ኩባያ ቡና ለሚጠጡ ሰዎች የሞት አደጋው በግማሽ ቀንሷል፡፡ Hazard Ratio 0.49 (HR = 0.49, 95% CI, 024-0.99)፡፡ በሌላ በኩል፣ አራት ኩባያ ሻይና አንድ ኩባያ ቡና የሚጠጡ ሰዎች፣ በቀን ማለት ነው፣ Hazard Ratio የሚባለው ነገር (HR = 0.37 95% CI, 018-077) ወረደ ይላሉ፡፡

ለመሆኑ Hazard Ratio ማለት ምንድን ነው? አብሮት የሚገለፅ CI (Confidence Interval) የሚባል ነገር አለ፡፡ Hazard Ratio የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖረው Confidence Interval የሚባለው ነገር በ95% ይገለፃል፣ ማለትም የታየው ለውጥ በተሰጠው ገደብ ውስጥ ለመሆኑ 95% ርግጠኛ ነው ለማለት ነው፡፡  በተለይ ግን በ Confidence Interval መሀከል ያለው የገደብ ስፋት ጠበብ ሲል Hazard Ratio ገላጭነቱ በጣም ያነጣጠረ ይሆናል ማለት ነው፡፡ Hazard Ratio የሚገልፀው፣ መድሀኒት ሆነ፣ በዚህ ጥናት እንደተጠቀሰው መጠጥ ወይም ምግብ ወይም ሌላ ነገር የወሰዱ ሰዎች ካልወሰዱ ሰዎች ጋር ሲወዳደር፣ የተጠቀሱትን ነገሮች በማድረጋቸው ያገኙት ጠቀሚታ ወይም ጉዳት መጠን በአሃዝ በስታቲስቲክ መግለጫ ነው፡፡ በዚህ ጥናት እንደታያው፣ ሻይ፣ ቡና ወይም ሻይና ቡና እንድ ላይ የሚጠጡት ሰዎች፣ ከማይጠጡት ጋር ሲወዳደር በተለያዩ ምክንያቶች የመሞት አጋጣሚው በሚጠጡት ሰዎች ላይ ቀንሶ መገኘቱ፣ የተገኘው የሞት አደጋ መጠን ደግሞ በምን ያህል እንደሆነ ነው የሚያሳየን፡፡ ለምሳሌ Hazard Ratio 0.5 ነው ቢባል፣ ቡናና ሻይ ጠጭዎች የሞት አደጋ ከማይጠጡት ጋር ሲወዳደር በግማሽ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ይበቃል ሰታቲሰቲክ፡፡ የመፅሔቱ ሰዎች አይተው የተቀበሉትም ነገር ስለሆነ፣ በሳይንሳዊ መንገድ የተሰላም ሰለሆነ እኛን ከድካም ያድነናል ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ከላይ እንደታየው፣ ጠቀሜታው ግልፅ ነው ቢባልም፡፡ ይህ ጥናት Observational Study ከሚባሉት ውሥጥ ሰለሆነ ስንቀበለው በጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ፡፡ ጥቅም ታይቷልና ስኳር ያላበችሁ በሙሉ ጠጡ ከማለታችን በፊት፣ ቡናና ሻይ መጠጣት ችግር የሚያመጣበት ሁኔታ መኖሩንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የልብ ህመምና የደም ግፊት ባለባቸው ሰዎች ላይ ቡና መጠጣት ግፊቱንም ሰለሚጨምር አደጋ አለው፡፡ ሌላው፣ እንደ ቀላል እየታየ ነገር ግን ብዙ ችግር የሚያስከትለው ዕንቅልፍ ማነስ ወይም ማጣት ነው፡፡ ቡናና ሻይ ሲያዘወትሩ በዚያ በኩል የሚመጣውን አደጋ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ቡናና ሻይ ጠጡ የሚል ምክር ሲሰነዘር ደግሞ፣ ስኳር የሌለበት መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ አለዚያማ ትርፍም የለውም፡፡

ይህ እንግዲህ ሳይንሳዊ ውጤት ነው፡፡ ወደፊትም ለማጋራት ዝግጁ ነኝ፡፡ በነገራችን ላይ የAmerican Diabetes Association የጠቀስኩት ለዚህ ጥናት ውጤት ክብደት ወይም ተቀባይነት ከፍ እንዲል የዚህ ድርጅት የመፅሔቱ ተባባሪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በአሜሪካ ስለ ስኳር በሽታ ህክምና ሆነ ምክር መመሪያዎችን የሚያወጣው ይህ ድርጅት በመሆኑ ነው፡፡ እኔ ካላመንኩበት ለናንተም አላቀርብ፣ ተገቢም አይደለም፡፡

ይህንን ፅሁፍ ላልሰማ አካፍሉ፣ በፌስ ቡክም ሆነ በጎሽ ድረ ገፅ ተከታታይ ለመሆን፣ በፌስ ቡክ Like በማድረግ፣ በድረ ገፁ ደግሞ በኢሜይልዎ በመመዝገብ ይሳተፉ፡፡ ለንግድ እንደማይሠራበት ተከታታዮች በግልፅ የምታዩት ነገር ነው፡፡

የከርሞ ሰው ይበለን፡፡
 
Mereja: Komorita Y, Iwase M, Fujii H, et al. Additive effects of green tea and coffee on all-cause mortality in patients with type 2 diabetes mellitus: the Fukuoka Diabetes Registry. BMJ Open Diab Res Care 2020;8:e001252. doi:10.1136/ bmjdrc-2020-001252