ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ በድፍን ኢትዮጵያ ተወዳጅና ገናና ሰለነበሩት ንጉሥ ስለ አፄ ቴዎድሮስና ሰለ መቅደላ ዘመቻና ፍፃሜ ለአንባብያን አቅርበዋል፡፡
አሜሪካዊ ጋዜጠኛ በአካል መቅደላ ተገኝቶ ያየውንና የዘገበውን የሚገልፅ ፅሁፍ ትርጉም ሲሆን፤ ከዚህ በፊት ብዙም የማናውቃቸውን ነገሮች አካቶ፣ የምናውቃቸወን ደግሞ በጥልቀት ይገልፃል፡፡
ስለ ንጉሡ አሟሟት ግልፅና በሆነና በማያሻማ ሁኔታ ይገልጣል፡፡
ዶ/ር ገበየሁ ተፊሪ፣ ከትርጉሙ በተጨማሪ በርካታ ፅሁፎችን በመመርመር፣ ስለ አፄ ቴዎድሮስ ባህሪ ቁመናና ጥንካሬ መረጃዎችን በግርጌ ማስታወሻ መልክ ለአንባቢ አቅርበዋል፡፡
ሌሎች ብዛት ያላቸው የንጉሡን ሃሳብና ጥልቀት የሚመዝኑ ወይም የሚገልፁ መረጃዎች ተካተውበታል፡፡
ይህ ፅሁፍ ስለ አፄ ቴዎድሮስ አጠቃላይና ጥልቅ ግንዛቤ ከመስጠቱም በላይ፣ የመቅደላን ሁኔታ በስዕላዊ መንገድ ስለሚገልፅ አንባቢ ራሱን መቅደላ አምባ ላይ ቢያሰቀምጥና ሁኔታውን ቢከታተል የሚገርም አይሆንም፡፡
ከአንባቢዎች የተሠጡ አስተያየቶች
ስለ መፅሐፉ የተሠጡ አስተያቶች
ሁላችንም እንደምናውቀው ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው መሪ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ነበሩ፡፡ ገና በካሣነታቸው ዘመን፣ ጥቃትና መገፋትን እንቢ በማለት የፈነኑት ጀግና፣ የተጋፈጣቸውን በሙሉ ድል በማድረግ ለንግሥ የበቁ ናቸው…፡፡ ዶ/ር ገበየሁ ላበረከትክልን ቁም ነገር ባለውለታችን ነህና እናመሰግንሃለን፡፡
አርቲስት አለምፀሐይ ወዳጆ
በጊዜው የነበረውን አኗኗር፣ የጦርነቱን ውሎ፣ ወዘተ. በአይነ ኅሊና የሚያስቃኝ መጽሐፍ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቢያነቡት ይጠቀሙበታል እላለሁ፡፡ ዶ/ር ገበየሁ፣ ሰፋ ያለ መረጃ ለመስጠት ያዘጋጃቸው ማስታወሻዎች ራሳቸውን ችለው አንድ መጽሐፍ ሊወጣቸው ይችል ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡
ዶ/ር እንዳላማው አበራ
ይህን መቅደላ የቴዎድሮስ ዕጣ የተሰኘ መጽሐፍ ከእንግሊዝ ጦር ጋር የተጓዘው ስታሌይ የሚባለው ጋዜጠኛ የዘገበውን ትረካ ወደ አማርኛ በመተርጎም ዶ/ር ገበየሁ ለታሪክ ተመራማሪያን ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም የአፄ ቴዎድሮስን ዘመን ለመረዳት የሚፈልግ አንባቢ ታላቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡
ዶ/ር አሉላ ፓንክረሰት
ይህ መፅሐፍ አፄ ቴዎድሮስ በግዛት ዘመናቸው የነበረባቸውን ተግዳሮቶችና፣ የእንግሊዝ ጦር የሳቸውን ሠራዊት ለማጥቃት ያደረገውን ከፍተኛ የጦርነት ዝግጅት በዝርዝር ያቀርብልናል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል መልክዓ ምድር የነበረውን አስደማሚ ውበት በውጭ አገር ጋዜጠኛ አይን በሚገባ ይገልፃል፡፡
ፋሲል ጊዮርጊስ፣ አርክቴክት፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር
"መቅደላ የቴዎድሮስ ዕጣ" በአማርኛ በሚመስጥ መልክ የተዘጋጀ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያነበው ዘንድ እመክራልሁ። ይልቁንም፣ እንደ አንድ ሃገሩንና ወገኑን የሚወድ ኢትዮጵያዊና እንደ የንጉሠ ነገሥት ዓፄ ቴዎድሮስ ቤተሰብ አባልነቴ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪን በእራሴና በቤተሰቦቼ ስም ላመሰግን እወዳለሁ። እግዚአብሔር ያክብርልኝ። (ለሙሉ አስተያዬት ወስጥ ይመልከቱ) አብዩ በለው
“መቅደላ የቴዎድሮስ ዕጣ” ስለ ቴዎድሮስ ከተፃፉ በርካታ መፃህፍት በተለየ የእንግሊዝ ሠራዊትን ዝግጅት፣ ጉዞና፣ ውጊያ በዝርዝር የሚያሳይ ነው፡፡ መፅሐፉ፣ ለወደፊት ፊልም ሥራዎች ተዝቆ የማያልቅ ጥሬ ሀብት ነው፡፡ ጌትነት እንየው
ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ
Community health
education in Amharic