አልዛይመር በሽታ Alzheimer Disease 


በዚህ ፅሁፍ ማቅረብ የምንፈልገው ዕድሜ በገፉ አዛውንቶች ላይ ሰለሚከሰተው የአእምሮ መታወክ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው አጠራር አልዛይመር በሽታ ስለሚባለው ነው፡፡ ይህ በሽታ በአዛውንቶች ላይ የማሰታወስ ችሎታን መታወክን ጨምሮ ሌሎች የተያያዙ ችግርችን በማሰከተል ቀዳሚ ደረጃ ላይ የሚገኝ በሽታ ነው፡፡

የበሽታው መንስኤዎች  


በሽታው የአእምሮ እንደመሆኑ በአንጎል ውስጥ የሚገኙ የነርቭ ሴሎችን (ኒውሮንስ) የሚያጠቁ የተለያዩ ፕሮቲኖች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም ከዚህ በሽታ ጋር የተያያዙ ሁለት ፕሮቲኖች በእንግሊዝኛ  β-amyloid and tau ተብለው የሚጠሩ በአንጎል ሴሎች ላይ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ይታወቃል፡፡ የእነዚህ ፕሮቲኖች በነርቭ ሴሎች ውስጥ መከማቸት ከጊዜ ብዛት የነርቭ ሴሎቹ እንዲሞቱ ያደርጋል፡፡ የአንጎል ነርቭ ሴሎች መሞት ደግሞ በተራው የአንጎል ጤናማ ስራን ሰሊሚያውክ በእንግሊዝኛ አጠራር (Dementia) ተብሎ የሚታወቀውን የአእምሮ መዳከምን ሁኔታ ያስከትላል፡፡ በአማርኛ ትክክለኛ ትርጉም ባይኖረውም በተለምዶ በሀገር ቤት አእምሮ ስቷል ተብሎ አንደሚነገር ይታወቃል፡፡ እንግዲህ ለመስማማት ዲሜንሽያ ወይም አእምሮ መሳት ብንለው ይመረጥ ይሆናል፡፡ አእምሮ መሳት ከመርሳት ጀምሮ አእምሮ በትክክል ማሰብ አለመቻል ወይም የማገናዘብ ጉድለትና የቋንቋ ችሎታ መቀነስንም ይጨምራል፡፡ በብዛት የሚታወቀው ግን በመርሳት ነው፡፡ ይህም አንድ ሰው የመርሳት ሁኔታ ሲፈጠርበት ሌሎች ቶሎ ማወቅ መገንዘብ ሰለሚችሉ ነው፡፡
ይህ በሽታ በትክክል በምን ምክንያት አንደሚቀሰቀስ አይታወቅም፡፡  በሽታው በቤተሰብ ማለትም በዘር የሚታላለፍ መሆኑ ይታወቃል ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዛት ያላቸው የዘር ሰንሰለት (ጂኖች) መኖራቸውም ይታወቃል፡፡ እነዚህ የዘር ሰንሰለቶች በትውልድ ከወላጆች ወደ ልጆች  በሚተላለፉበት ጊዜ ዝርያው ያለባቸው ሰዎች ለዚህ በሽታ ይጋለጣሉ ማለት ነው፡፡ ይህ በሽታ የሚከሰተው እድሜያቸው 65 አመት ያለፋቸው ሰዎች ላይ ቢሆንም በቤተሰብ ወይም በዘር የሚታላለፈው ከሆነ ከዚህ እድሜ ቀደም ብሎ ሊከሰት ይችላል፡፡
 


የበሽታው ምልክቶች


የበሽታው ምልክቶች ከመጠነኛ እሰከ ከፍተኛ ደረጃ በሆነ መልክ ሊገለፁ ይችላሉ፡፡ አዚህ ላይ ማሰተዋል ያለብን ከእድሜ ጋራ በተያያዘ የሚከሰቱ የመርሳት ወይም የመዘንጋት ሁኔታዎች ሊኖሩ አንደሚቸሉ ነው፡፡ አንዚህ ግን በሽታው እንዳለባቸው ሰዎች መቆጠር የለባቸውም፡፡
የበሽታው ምልክቶች ከሆኑት አንዱ የመርሳት ሁኔታ ነው በተለይም በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ነገሮች መርሳት ወይም ሰዎችን ማስታወስ አለመቻል ቀደም ብሎ የሚከሰት የበሽታው ምልክት ነው (ሰዎች የድሮ ነገሮችን የማሰታወስ ቸሎታቸው እንደተጠበቀ ሊቆይ ይቸላል)፡፡  መርሳት የሚጨምረው ነገር እቃዎችን ያለቦታቸው ማስቀመጥ፤ አቅጣጫና ቦታን መዘንጋት በተለይም ከዚህ ቀደም በሚያውቁት ሰፈር ሆነ ቤት አካባቢ መጥፋት፤ ድሮ ይሰሩ የነበሩ ነገሮችን ማከናወን አለመቻል ለምሳሌ የወር የሚከፈሉ እዳዎችን መክፈል አለመቻል፤ የፀባይ መቀየር ያልተለመደ ወይም አዲስ ባህሪ ማሳየትን ይጨምራል፡፡  ይህ አንግዲህ የበሽታው መጠነኛ ምልክቶች ናቸው፡፡

በሽታው እየከፋ ሲሄድ ደግሞ የተባባሰ የመርሳት ወይም የመዘንጋት ሁኔታ መከሰት፤ በመርሳት ምክንያት ደግሞ ግራ መጋባት፤ ባህሪ መቀየርና በተጨማሪም ሰዎችን መጠራጠር አለመተባበር እንዲሁም ሰዎችን የማጥቃት የመደባደብ ሁኔታን ይጨምራል፡፡ በዚህ ደረጃ ደግሞ የቤተሰብ አባላትን ማወቅ አለመቻል ጓደኞችንም መዘንጋት ይጨምራል፡፡ ልብስ በደንብ አለመልበስ ወይም ለመልበስ የሰው እርደታ ማስፈለግን የመፀዳዳት ችሎታም አለመኖር ማለትም በተገኘበት ቦታ ሽንትም ሆነ ሠገራን መልቀቅ ይጨምራለ፡፡
በጣም የከፋ ደረጃ ሲደርስ ደግሞ የመነጋገር ችሎታም ማነስና ለማንኛው ነገር የሌሎች ሰዎችን እርዳታ የሚያሰፈልግበት ሁኔታ ይፈጠርና ለመልበስ፤ ለመብላት፤ ለመፀዳዳት የሰዎች እርደታ አስፈላጊ ወይም የግድ ይሆናል፡፡
በእድሜ ምክንያት የመዘንጋ ሁኔታ ቢፈጠርም ከላይ ለተጠቀሱት አለት ከእለት ለሚደረጉ ሁኔታዎች ግን የሰዎች እርደታ አስፈላጊ አይሆንም፡፡ ለመድገም ያክል በእድሜ ምክንያት የሚዘነጉ ሰዎችን ይህ በሽታ እንዳለባቸው አድርጎ መቁጠር ተገቢ አይደለም፡፡


​ምርመራዎች


የተለያዪ አእመሮንና አንጎልን የሚመለከቱ ምርመራዎች ይደረጋሉ፡፡ የምርመራዎች አንዱ ምክንያት የተከሰተው በሽታ በሌሎች ምክንያቶች አለመሆኑን ማረጋገጥ ይጨምራል፡፡ የአእመሮ መዘንጋት ወይም መሳትን (ዲሜንሽያን) የሚያሰከትሉ ሌሎች ሁኔታዎች አንዳሉ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ እንግዲህ ሀኪሞች ደም ምርመራዎችን ጨምሮ ከሰረሰር ፈሳሽ በመውሰድ ምርመራዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ህክምና


ይህን በሽታ የሚያድን ህክምና በአሁኑ ጊዜ የለም፡፡ በሽታውን  የሚያዘገዩ መድሃኒቶች ቢኖሮም በሽታውን መመለስ አይችሉም፡፡ ከበሽታው ጋራ በተያያዘ የሚፈጠሩ የአእምሮ መጨነቅ መረበሽ እንቅልፍ ማጣትን የመሳሰሉትን ሁኔታዎች በህክምና ማርገብ ይቻላል፡፡  ይህ በሽታ አስከፊ ደረጃ ሲደርስ ቤተሰብ ላይ የሚፈጥረው ጭንቀት ከባድ ነው፡፡ በተለይም አብረው የኖሩት ሰው ሚስቱን ወይም ባሉን አለማወቅ ደረጃ ሰዲርስ፣ በኖረበት ቤት እንግዳ ሆነ መታየት ከባድ ነው፡፡ በዚህ በሽታ ችግር ከደረሰባቸው ከሚታወቁ ቤተሰቦች አንዱ የቀድሞው የአሜሪካው ፕሬዚደንተ ሮናልድ ሬገንን ይጨምራል፡፡ ይህ ሁኔታ የአደባባይ ሚስጥር ስለሆነ በዚህ ድረ ገፅ መጥቀሳችን ክፋትነት አይኖረውም፡፡ በሽታውን ለማከም ምርምሩ የቀጠለ መሆኑንም ለማሰታወቅ እንወዳለን፡፡ ከህዝብም ሆነ ንብረት ካካበቱ ሰዎች በኩል ከፍተኛ ግፊት አለ፡፡

መልካም ንባብ

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History