ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ
Community health
education in Amharic
ደረጃ (ትርጉም) | Hgb A1c (percent) | Fasting blood glucose (mg/dl) | Oral glucose tolerance test (mg/dl) |
ጤናማ | Below 5.7 | 99 or below | 139 or below |
ቅድመ ሰኳር በሽታ | 5.7 to 6.4 | 100 - 125 | 140 - 199 |
የስኳር በሽታ | 6.5 or above | 126 or above | 200 or above |
Pre diabetes ቅድመ ስኳር በሽታ
ምልክት ሳይሠጡ ሳያስጠነቅቁ እያዋዙ ብቅ ከሚሉ በሸታዎች አንዱ የስኳር በሽታ ነው፡፡ በመረጃ በአሃዝ እንደሚታየው በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሄዱ ግልፅ ነው፡፡ አደጉ በሚባሉ አገራት አዋቂ ከሆኑ በኋላ፣ የስኳር በሽታ የሚከሰትባቸው ሰዎች ባሕርይ ለየት ያለ ነው፡፡ ያም በተለይ በሰውነት ገዘፍ ያሉና፣ ሰውነታቸው ላይ ያልተስተካከለ ውፍረት የሚታይባቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡ በአገር ቤት ግን የተለየ ነው፡፡ እኔም እንደ ሕክምና ባለሙያ በአእምሮዬ የሚመላለሰው ለምን ይሆን በአገር ቤት የስኳር በሽታ በብዛት የሚከሰተው፣ ከተከሰተም ደግሞ በሰውነት ገዘፍ ያላሉ ሰዎች ላይ ነውና ምክንያቱ ምን ይሆን የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
ታዲያ ነገሩ እንዲህ ከሆን፣ የስኳር በሽታ ማን ላይ መከሰት እንደሚችል አስቀድሞ የሚጠቁም ምልክት ወይም ምርመራ ሰለሌለ፣ ሁሉም ሰው ሰለዚህ የስኳር በሽታ ግንዛቤ ማግኘትና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት በሚል ትምህርት በተከታታይ ለማቅረብ ፈለግሁ፡፡
እያንዳንዱ ሰው ማስተዋል የሚገባው ነገር፣ ዋናው የስኳር በሽታ ከመከሰቱ በፊት ቀደም ብሎ እንደ ማስጠንቀቂያ የሚታይ፣ ለዋናው የስኳር በሽታ ዋዜማ የሚመስል ቅድመ ስኳር የሚባል ሁኔታ መኖሩን ነው፡፡ በአንግሊዝኛው አጠራር Pre diabetes ይባላል፡፡
ሰለዚህ ሁኔታ አንዳንድ እንበል፤
ይህ ሁኔታ እንግዲህ፣ ምንም ምልክት ወይም ስሜት አይሰጥም፡፡ በደም ውስጥ የስኳር መጠን ሲለካ፣ መጠኑ ከፍ ያለ ሆኖ ግን የስኳር በሽታ የሚባል ደረጃ ሳይደርስ ሲቀር ነው፡፡ በቂ ክትትልና ጥንቃቄ ካልተደረገ፣ ይህ ሁኔታ በአስር አመታት ወይም ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ ስኳር በሽታ ይሻገራል፡፡ ይህ ቅድመ ስኳር በሽታ በታየበት ጊዜ ምልከት ባይሰጥም፣ ክስኳር በሸታ ጋር ተያይዘው ብቅ የሚሉት የልብና የደም ሥር በሸታዎች አብረው በጊዜ እየጀመሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰለዚህ ማስጠንቀቂያነቱ ከስኳር በሽታ ያለፈ ሰለሆነ በቂ አትኩሮት ሊሠጠው ይገባል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ይህንን ጉዳይ ቀደም ብለው ከነቁበት፣ ጤንነትዎን በመንከባከብ፣ ዋናው የስኳር በሽታ እንዳይከሰት የማድረግ ዕድል አለዎት፡፡ ያም አንግዲህ፣ ጤናማ አመጋገብ፣ መደበኛ የሆነ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ የሰውነት ክብደት በመጠበቅ በደም የሰኳር መጠን ዝቅ እንዲል ማድረግ ይችላሉ፡፡
ቅድመ ስኳር ምንም ምልክት ላይኖረው ቢችልም፣ በቆዳ ላይ የሚታይ አንድ ምልክት ግን ከዚህ ሁኔታ ጋር ሊያያዝ ይችላል፣ በተጨማሪም ለስኳር በሽታ መከሰት ምልክት ይሆናል የሚባል ነው፡፡ በቆዳ ላይ ጠቆር በማለት በጉልበት፣ በክርን፣ በአንገት፣ በብብት፣ የእጅ ጣቶች ላይ የሚታይ ነገር ነው፡፡ ለማንኛውም ይህ ምልክት ኖረም አልኖረም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ቅድመ ሰኳር ሁኔታው ደግሞ ወደ ስኳር በሽታ ከተሸጋገረ የሚታዩ ምልክቶችና ስሜቶች አሉ፡፡ እነሱም፣ የውሀ ጥም መጨመር፣ ቶሎ ቶሎ ሽንት መሽናት፣ ድካም ስሜት፣ አይን ብዥ ማለትን ያካትታሉ፡፡ ይህ አይነት ስሜት ጤናማ ስላልሆነ ወደ ሀኪም መሄድ የግድ ይሆናል፡፡
ለመሆኑ ለቅድመ ስኳር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች አሉ ወይ? እነዚህን ሀኔታዎች በጥሞና መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ቤተሰብ ወይም ጓደኛን መምከርም አስፈላጊ ነው፡፡
ሁኔታዎቹ፤
እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ካሉብዎት፣ ለቅድመ ስኳር አጋላጭ ሰለሆኑ፣ ወደ ሀኪምዎ ጎራ ብለው ምርምራ እንዲረግ መጠየቅ አለብዎት፡፡ በዚህ አጋጣሚ፣ ለዚሁ ሲሉ ወደ ሀኪም የሚሄዱ ከሆኑ፣ ለስምንት ሰአታት ሳይመገቡ በባዶ ሆድ መሄድ ምርምራው ባንድ ቀን እንዲጠናቀቅ ይረዳዎታል፡፡ ከመመላለስ አይሻልም ወይ?
ስለ ላቦራቶር ምርመራዎች፡
A1c Test (Hemoglobin A1c, Hgb A1c) ይህ የደም ምርመራ፣ የስኳር በሽታ ለማወቅና ለመከታተል፣ በተጨማሪም ቅድመ ስኳር ሁኔታ መኖሩን ለማወቅ የሚሠራ ነው፡፡ ከላይ ሠንጠረዡን ይመልከቱ፡፡ ብቻውን ወይም ከሌሎች ምርመራዎች ጋር አብሮ ይሠራል፡፡ ለዚህ ምርመራ ባዶ ሆድ መሆን አያስፈልግም፣ በማንኛውም ጊዜ መሠራት ይችላል፡፡ መጠኑ የሚጠቁመው፣ በቀይ የደም ሴሎች ውስጥ በሶሰት ወራት ውስጥ የነበረውን አማካኝ የስኳር መጠን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የስኳር በሽታው ላለባቸው ሰዎች፣ የስኳር መጠኑ በቁጥጥር ሥር እንደሆነ ለማሳየት ለክትትል ይታዘዛል፡፡
Fasting blood glucose (FBS) ይህ ደግሞ በባዶ ሆድ ማለትም ለስምንት ሰኣታት ምግብ ሳይበሉ የሚሠራ የደም ምርመራ ነው፡፡ በተለይም በጠዋት ከተሠራ ጥሩ መረጃ ይሠጣል፡፡
Oral glucose tolerance test (OGTT) ይህ ምርመራ ባሁኑ ጊዜ ለነብሰ ጡር ሴቶች የሚታዘዝ ነው፡፡ ምርመራው የደም ሲሆን፣ ስኳር በአፍ ከተወሰደ በኋላ ጊዜ እየጠበቁ ደም በመውሰድ የስኳር መጠኑን በመለካት የሚሠራ ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የምርመራ አይነቶች ጠንከር ያለ መረጃ ወይም የተሻለ መረጃ ይሠጣል፡፡ ምርመራው ውስብስብ ያለ ነው፡፡ ሰዎች ባዶ ሆድ (ስምንት ሰአታት) ከሆኑ በኋላ፣ 75 ግራም ስኳር በውሃ ተበጥብጦ እንዲጠጡ ይደረግና፣ ከሁለት ሰአታት በኋላ በደም ምርመራ የስኳር መጠን ይለካል፡፡ ሰለአተረጓጎም ሠንጠረዡን ይመልከቱ፡፡