​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

እንስሳትም የራሳቸው ኤይድስ የሚያመጣ ቫይረስ አላቸው

በሥራ ቦታ እያለሁ አብራኝ የምትሠራው ነርስ እየደጋገመች ስልክ በመደወል ሚር ብራውን እንዴት ነው እያለች ከስልኩ ባሻገር ያሉትን ሰዎች ስትጠይቅ እሰማለሁ፡፡ የተቀመጥነው ጎን ለጎን ስለነበር ጨረፍ ያለ ወሬ ማዳመጤን አልክድም፡፡ ይህ በመጀመሪያው ሳምንት ነበር፡፡ በሚቀጥለው ሳምንትም ተደጋጋሚ ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ነገሩ ምንድን ይሆን በሚል አሰተያየት ተመለክትኳት፡፡ ምንም ሳታቀማማ ሚሰተር ብራውን ድመቴ ነው፡፡ የእንስሳት ህክምና ሆስፒታል ገብቶ እየታከመ ነው አለችኝ፡፡ ስሜቴን እንደምንም ተቆጣጥሪ በጣም አዝናለሁ አልኩኝ፡፡ ግን የነርሷን ድመት ያመመው በሽታ ምን ይሆን ብዬ ማሰቤም አልቀረም፡፡ የገባት ይመስለኛል ሀሳቤ፡፡ ኤች አይ ቪ ሰላለበት ኤየድስ ደረጃ ደርሶበታል አለችኝ፡፡ ይህ እንኩዋን ብዙም አላስደነገጠኝም በሙያዬ ነው ግን የማልክደው ነገር የመጀመሪያው ኤይድስ ያለበት ድመት ታሪክ በመሰማቴ መደነቄን ነው፡፡ ነርሷ ወጭ እየጨመረባት መሄዱን ነግራኛለች፡፡ ስለ ሚሰተር ብራውን የመጨረሻ ሁኔታ በሁዋላ ልግለፅና ብዙዎቻችሁን ምናልባትም ያስገረማችሁን የድመቱን በኤይድስ መያዝ ላብራራ፡፡

በጎሽ ድረ ገፅ ስለ ኤች አይ ቪ ቫይረስ ዝርያዎች የተፃፉትን እናስታውስና አንዚህ ግን ሰዎችን በመልከፍ ብቻ የታወቁ መሆኑን ማስረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን ብዛት ያላቸው እንስሳት የራሳቸው የሰውነት መከላከያ አቅም ማድከም የሚችል በአንዳንዶቹ ግን በሰውነታቸው ውስጥ ብቻ የሚኖር አንደ ኤች አይ ቪ አይነት ቫይረስ አላቸው፡፡

ለመጀመር ዋናው እንዳውም ከነሱ ዘሎ ወደሰዎች ተሸጋግሯል የሚባለው የቺምፓዚዎች ቫይረስ በእንግሊዝኛ (Simian Immunodeficiency Virus – SIV) ተብሎ የሚታወቀ ነው፡፡ እንዴት ከቺምፓዚዎች ወደ ሰዎች እንደተሸጋገረ የተለያዮ መላ ምቶች አሉ አንዳንዴም አከራካሪ ወይም አወዛገቢም ናቸው፡፡ እንግዲህ አንድ በሳይንሳዊ ጥናት የሚታወቅ ነገር ቢኖር ምእራባውያን ሳይንቲሰቶቸ ወደ ምዕራባዊ አፍሪካ በመሄድ የነዚህን ቺምፓዚዎች አይነ ምድር በመሰብሰብ በውስጥ የተገኘውን ቫይረስ የዘር ሰንሰለት በሚመረምሩበት ጊዜ አጠቃላይ ሁኔታው በሰዎች ላይ ከፍተኛ ችግር ከሚያስከትለው የኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋራ ቀጥታ ተመሳሳይ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ Molecular dead ringer ነው ያሉት፡፡ መቼም ይሄ የሌላ ጊዜ ርዕስ ይሆናል፡፡

ከቺምፓዚዎች ውጭ ደግሞ ዝንጀሮዎች ተመሳሳይ ቫይረስ አላቸው፡፡ ከዝንጀሮዎችም ቢሆን በተለይ ሱቲ ማንጋቢ የሚባል ዝንጀሮ ዝርያ የኤች አይ ቪ የመሰለ የራሱ ቫይረስ እንዳለው ይታወቃል፡፡  እንዳውም ወደሰዎች የመጣው ቫይረስ ከቺምፓዚዎች ሳይሆን ከዝንጀሮውችም ነው የሚባል ሁኔታ አለ፡፡

ወደ ሚስተር ብራውን ስንመለስ ድመቶች የራሳቸው ቫይረስ አላቸው በእንግሊዝኛው አጠራር (Feline Immunodeficiency Virus or FIV) ተብሎ ይታወቃል፡፡ በዚህ ቫይረስ የሚለከፉት ድመቶች ዱር ወይም ውጭ አዳሪዎች ናቸው ብዙ ጊዜ በንክሻ ነው የሚታለለፈው የሚባለው እንደሰው ኤች አይ ቪ ቫይረስ አዝግሞ ነው የኤይድሰ በሽታ የሚያስከተለው፡፡ እኔም ነርሷን አንዴት ሊይዘው ቻለ ብዬ ጠይቄ ነበር፡፡ ድመቱን ከመጠለያ እንደገዛቸው ነገረችኝ፡፡ እንግዲህ ቤት ውስጥ ያላደገ ወይም ቤትየለሽ ነበር ማለት ነው፡፡ አመንዝራ ይሆን ብለን መሳሳቃችን አልቀረም፡፡

በላሞች ላይ የሚገኝ እምብዛም በብዛት የማይታይ ደግሞ (Bovine immunodeficiency Virus or BIV) ተብሎ የሚጠራ አለ

 እንደ ከብቶቹ ባይሆንም በጎች ደግሞ የራሳቸው የሰውነት መከላከያ ቅስምን የሚሰብርና ለሌሎች በሽታዎች አጋልጦ የሚሰጥ (Visna virus) ተብሎ የሚጠራ ቫይረስ አላቸው፡፡ በስውነታቸው ውስጥ የተለያዬ ክፍል በሚያጠቃበት ጊዜ ሌላ የተለያዬ ስም ይኖረዋል፡፡

ሌላው ጥያቄ ደግሞ ውሾች የራሳቸው የሆነ አንደ ኤች አይ ቪ አይነት ቫይረስ አላቸው ወይ ነው፡፡ ማለትም (Canine immunodeficiency virus) እህ! እዚህ ላይ ወራጅ አለ ቢባል ይሻላል፡፡ በአንድ ጠናት የውሾች ደም ተምርምሮ የተለያዩ ኤች አይ ቪ ቫይረስ የሚመስሉ ፕሮቲኖች ቢኖሩም የራሳቸው የተለየ እንደ ድመቶች አይነት ቫይረሶች የላቸውም አስከሚታውቀው ድረስ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ መፍረድ ከተፈለገ ድመቶች አመንዝራ ናቸው ማለት ነው?

ልባችሁ የሚሰተር ብራውንን ነገር እንደሚያንሰላስል እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሚሰተር ብራውን አንድ ቀን ተሻለው ሌላ ቀን ደግሞ ደክሞ ምግብ በክንድ መርፌ እየወሰደ ነው እየተባለ ሪፖርቱ በየጊዜው ለምትደውለው ባለቤቱ ይነገራታል፡፡ በዚያው ልክ ግን ክፍያው ወይም ወጭ እየጨመረ ሄደ፡፡ በመጨረሻም ነርሷ መወስን ነበረባት፡፡ ውሳኔው እንግዲህ ወጭውን ሰላልቻልኩ አሰናብቱልኝ ነበር፡፡ እኔ ግን የአይን ምስክር ነኝ፡፡ ይህን ውሳኔ ስትሠጥ በጣም ተጨንቃ ነበር፡፡ አሜሪካኖች ውሾችና ድመቶቻቸውን እንዴት እንደሚወዱ ካወቃችሁ የሴትዮዋ መጨነቅ አያስገርምም፡፡ በነርሷ ውሳኔ መሰረት ድመቱ በእንስሳት ሀኪሞች እርደታ ህይወቱ አንዲያልፍ ተደረገ፡፡ ከዚያ በሁዋላ እኔም ሆነ ነርሷ ስለ ሚስተር ብራውን አንስተን አናውቅም፡፡ የሚሰተር ብራውን ነብስ ይማር!

በነገራችን ላይ ኤይድስ የሚያመጣው የድመቶች ቫይረስ በመላው አለም ተሰራጭቶ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡