ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

በኮቪድ ምርመራ ውጤት ምክንያት ጉዞዎ እንዳይራዘም ማድረግ የሚችሉት ነገር

መቼም አዲሱ ዝርያ መላ አለምን ማዳረሱ ግልፅ ነው፡፡ ቀደም ብለው እንደታዩት ዝርያዎች ሰዎችን ለክፈተኛ ህመም ሞት አልዳረገም፡፡ ያ ሁኔታ በብዛት የሚታየው በተከቡ ሰዎች ነው፡፡ ያልተከተቡ ሰዎች፣ ህፃናትን ልጀችን ጨምሮ የብዙ ሰው ሕይወት እያለፈ ነው፡፡ ሞት ሲለመድ በገሀድ እያየን ነው፡፡

የዛሪው ርዕስ ዋናው ነገር ሰለ ኮቪድ ምርመራ ነው፡፡ ምርመራዎች ሁለት አይነት ናቸው፡፡ አንደኛው ምርመራ፣ በምርመራ የተወሰደውን ናሙና የቫይረስ ፕሮቲን መኖርና አለመኖሩን አጣርተው፣ የተገኘውን ፕሮቲን በማጉላት ወይም በማባዛት የኮሮና ቫይረስ ነው ይሉናል፡፡ ይህ የምርመራ ዘዴ በአንግሊዝኛው አጠራር Molecular/ PCR ይባላል፡፡ ይህ የምረመራ ዘዴ ነው ከጉዞ በፊት እንዲያደርጉ የሚጠየቁት፡፡ ሌላኛው፣ በፍጥነት የሚደርሰው ፈጣን አንቲጂን የሚሉት ነው፡፡ Rapid Antigen test ይባላል፡፡ ወደ PCR ከመሻገራችን በፊት ሰለዚህኛው ትንሽ ልግለፅ፡፡

በመጀመሪያ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ለማወቅ በሚደረገው ምርመራ Rapid Antigen test ትንሽ ጉልበት ያንሰዋል፣ ማለትም ሰዎች በቫይረስ ተይዘው አልተያዙም የሚል መልስ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ሁለተኛ አንድ ሰው በቫይረሱ ከተያዘ ከቀናት በኋላ ነው ይህ ምርመራ መደረግ የሚችለው፣ በትኩሱ መሠራት ሰለማይችል፡፡ ሰለዚህ ጠቀሚታ ቢኖረውም በጥንካሬና ጥራት ከ PCR ጋር አይወዳደርም፡፡ ሆኖም፣ ሰዎች በየቤታቸው እንዲመረመሩ ሊያስችላቸው የምርመራ ዘዴ በመሆኑ፣ በዚህ በኩል ትልቅ ርዳታ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን በአንግሊዝኛ False negative የሚባል ሁኔታ ሰለሚፈጥር፣ አንድ ሰው ተጋልጦ የበሽታ ስሜት እያለበት ይህ ምርመራ ዘዴ በቫይረሱ አልተያዘም የሚል ውጤት ሰላሳየ ብቻ፣ የለብኝም ብሎ መዘነጋት የለበትም፡፡ ጉዳቱ እንዴት ነው፣ የተያዘው ሰው አልተያዝኩም ብሎ በመዘናጋት ለሌሎች ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ በተጨማሪም፣ አሁን መድሐኒት ባለበት ሀገር የሚኖሩ ከሆነና ኮቪድ ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥላቸው ሰዎች ወገን ከሆኑ፣ በአፍ የሚወሰደውን እንክብል በአምስት ቀናት ውሰጥ ካልወሰዱ ውጠታም ሰለማይሆን በመዘናግት ምክንየት ችግር ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ከፍተኛ ጥርጣሬ ኖሮ Rapid Antigen test በቫይረስ አልተያዙም (Negative) ውጤት ካለው PCR እንዲያደርጉ ነው የሚመከረው፡፡

ወደ PCR ስንመለስ፣ በቫይረሱ ተይዟል ለለማለት ወሳኝ የምርመራ ዘዴ ሲሆን፡ እየታየ ያለው ችግር ደግመ፣ አንድ ሰው በኮቪድ ከተያዘና ካገገመ በኋላ የ PCR ምርመራው (Positive) እየሆነ ለረዥም ጊዜ የሚቆይበት ሁኔታ ጨመር እያለ መታየቱ ነው፡፡ ሰውየው ካገገመ በኋላ፣ በተለይም ከአስር ቀን በኋላ ይህ የ PCR ምርመራ ፖዘቲቭ እንደሆነ ለረዥም ገዜ ይቆያል፡፡

በዚህ ምክንያት ሰፋ ያሉ ጥናቶች በተለያዩ ሀገራት ተደርገው የተገኘው ውጤት፣ አንድ ሰው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ፣ አገግሞ አስር ቀን ካለፈው በኋላ በ PCR ምርመራ ቫይረሱ ተገኘ ቢባልም የተገኘው ውጤት በውነት መራባት የሚችል ቫይረሰ ነው ወይስ፣ የቫይረሱ ርዝራዥ ፕሮቲን ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሠጣሉ፡፡ በመሠረቱ፣ በምርማራ የተገኘው ውጤት በውነት መራባት የሚችል ቫይረሰ መሆኑ የሚታወቀው፣ ቫይረሱን በተለያዩ ማሳደጊያ ማሳደግና ማራበት ሲቻል ነው፡፡ በእንግሊዝኛ culture ይባላል፡፡ የተወሰደው ናሙና ቫይረስ ማደግ የሚችልበት ሁኔታ ካልፈጠረ፣ በ PCR የተገኘው ነገር የቫይረሱ ርዝራዥ ነው ይባላል፡፡ የተለያዩ ጥናቶች የሚጠቁሙትም፣ ሰው ተይዞ ካገገመ አስር ቀን ካለፈው፣ በ PCR ፖዘቲቭ ቢሆንም፣ መራባት የማይችል የቫይረሱ ርዝራዥ ሰለሆን፣ የተየዘው ሰው ከመገለያ መውጣት ይችላል ነው የሚሉት፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ለሁሉም ሰዎች አይደለም፡፡ በመጀመሪያ የተፈጥሮ የበሽታ መከላከያ አቅማቸው በተለያዩ ምክንያቶች ደክም ያለባቸው ሰዎች፣ ውነተኛ መራባት የሚችለው ቫይረሰ ከአስር ቀናት ወይም ከዛም በላይ ሊገኝባቸው ሰለሚችል ማስተላለፍ ይችላሉ ነው፡፡ ሁለተኛው ወገን ደግሞ፣ በኮቪድ ምክንያት በጠና ታመው፣ የመተንፈሻ ርዳታ ሲደረግላቸው የነበሩ ሰዎች ቢያገግሙም መራባት የሚችለው ቫይረስ ከአስር ቀናትና ከዛ በላይ ሊገኝባቸው ሰለሚቸል ማስተላለፍ ይችላሉ፡፡ ሰለዚህ እነዚህ ወደኋላ የተጠቀሱ ሰዎች PCR ፖዘቲቭ ሲሆን እንደ እውነተኛ ቫይረስ ነው የሚቆጠረው፡፡
አሁን ቸግር የመጣው ወደ ሥራ የመመለስ በተጨማሪም የእውፕላን ጉዞ ላይ ነው፡፡ በዚህ መንገደኞችን በተመለከተ፣ የአሜሪካው የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (CDC)፣ ለዘብ ያለ መመሪያ አውጥቷል፡፡
በመመሪያው መሠረት ወደ አሜሪካ ለሚመለሱ ወይም ለሚመጡ ሰዎች፣ በኮቪድ ተይዘው፣ አስር ቀናት ካለፈ በኋላ የ PCR ምርመራው ፖዘቲብ ቢሆንም አንኳን የተወሰኑ መስፈርቶችን እሰካሟሉ ድረስ፣ ወደ አሜሪካ መጓዝ ይችላሉ ይላል፡፡ ይህንን መመሪያ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የተመለሱ ቤተሰቦችም አውቃለሁ፡፡
ሰለዚህ መንገደኞች ይህንን CDC መመሪያ አንብበው በአግባቡ በመጠቀም ከጉዞ መጉላላት እንዲድኑ እመክራለሁ፡፡

ይህ መመሪያ የሚሠራው ወደ አሜሪካ ለመመለስ ወይም ለመግባት እንጂ ከአሜሪካ ወይም ከሌላ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ግን፣ የኢትዮጵያ ህግ ወይ ደንብ ነው የሚሠራው፡፡ የሚጓዙ ወይም የተጓዙ ከሆነ፣ ይሀን ነገር በትክክል እንደሚያጣሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ወይም የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱየት ያወጣውን መመሪያ ነው የሚከተለው፡፡
መልካም ንባብ አካፍሉ፡፡ 

በቂ እንቅልፍ የሰውነት መከላከያ አቅምን ያጠነክራል

እንቅልፍና ክትባትን ምን አገናኘው? 02/14/2021

 በቅርቡ ከአሪዞና ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ጋር ኮቪድን በሚመለከት ውይይት ስናደርግ፣ ለተጠየቁ ጥያቄዎች መልስ ስሠጥ፣ በቂ አንቅልፍ መተኛት ለጤንነት ብሎም የሰውነት መከላከያ አቅምን ለማጠናከር ጥሩ ነው ብዬ ነበር፡፡ ያ አንግዲህ በቂ እንቅልፍ ካለማገኘት ጋር በተያያዘ ሊደረሱ የሚችሉ የሚታወቁ የጤና ችግሮችንና በማስታወስና የሰውነት የበሽታ የመከላከል አቅምም በእንቅልፍ ማነስ ደካማ ሊሆን እንደሚችል የሚታወቁ መረጃዎችን በማገናዘብ ነው፡፡

ሆኖም ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፣ ከኮቪድ 19 ጋርም ግንኙነት ያለው ሁኔታ ይኖር ይሆነ ብዪ ክትትል ቀጠልኩ፡፡ “የሚገርም ነው!” ይላል ሶሰት አመት የሞላው የእህታችን ልጅ፡፡ American Academy of Sleep Medicine (AASM) የሚባል የባለሙያተኞች ማህበር ይህንን በሚመለከት ያወጣወን መካሪ ሀሳብ አየሁኝና እንደተለመደው ለናንተም ላካፍል ብዬ ወሰንኩ፡፡ በነገራችን ላይ፣ እንቅልፍ ከተነሳ፣ አሜሪካውያን ከሚገባው በላይ ደፋሮች ናቸው ይባላል፡፡ ያለ በቂ እንቅልፍ መኖር፣ ማለትም ቡናም ሆነ ሌሎችን አነቃቂ መጠጦች በመውሰድ በጣም መጠነኛ እንቅልፍ ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ ወፍ እንደ አገሩ ይጮሃል አንደሚባለው፣ እኛም ነገሩን እንደ ጥሩ አርኣያ ወስደን እንቅልፉን ናቅ አድገን እንውተረተራለን፡፡ አደጋ አለው፡፡

ወደ ምክሩ ልመልሳችሁ፡፡ ከዛ በፊት ግን በጥናት የወጡ ሌሎች መረጃዎችን አንድ ሁለት ልበል፡፡ በ2020 የወጣ ጥናት የሚጠቁመው፣ የኢንፍሉዌንዛ ክትባት ከመወስዳቸው በፊት ለሁለት ቀናት በቂ እንቅልፍ ያገኙ ሰዎች ለክትባቱ ጥሩ ምላሽ አሳይተዋል የሚል ነው፡፡ በሌላ ተመሳሳይ ጥናት ደግሞ አንደዚሁ ከክትባቱ በፊት በቂ እንቅልፍ የነበራቸው ሰዎች ለሄፓታይትስ ኤና ሄፓታይትስ ቢ ክትባት ጥሩ ምላሽ አሳይተዋል የሚል መረጃ አለ፡፡

ለምን ወይም እንዴት ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ባጠቃላይ፣ እንቅልፍ በሚወሰድን ጊዜ፣ ሰውነታቸውን በቀን ከነበረው ውሎ ማረፍ ብቻ ሳይሆን፣ ለሚቀጥለው ቀን ዝግጅትም ለማድረግ ብዙ ሥራዎችን የሚሠራበት ጊዜ ነው፡፡ በመጀመሪያ ሲሰሩ የዋሉ ጡንቻዎችን ማደስ፣ የተጎዱ ሴሎችና የሰውነት ክፍሎችን መጠገን የሚደረገው በእንቅልፍ ጊዜ ነው፡፡ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ በሆርሞኖች አማካኝነት፣ የመከላከያ አቅምን ማጎልበትና ማደስ፣ የተለያዩ፣ ሜታቦሊክ ይባላሉ፣ ሁኔታዎች ማስተካክልም ያደርጋል፡፡ አንጎል ደግሞ በተራው፣ በምንተኛበት ጊዜ፣ አዳዲስ ያገኛቸውን መረጃዎች በየቦታው በማስቀመጥ ለሚቀጥለው ቀን ዝግጁ ያደርገናል፡፡ እንደ ባለሙያተኞቹ ገለፃ አዳዲስ መረጃዎችን በየቦታው በማስቀመጥ የአዕምሮ ስሜታችን የተረጋጋ እንዲሆን በማድረግ እንደገናም ለሚቀጥለው ቀን ዝግጁ ያደርገናል፡፡ ይህን ሁኔታ ለመገንዘብ በቂ በየቀኑ የምናያቸው ነገሮች አሉ፡፡ በቂ እንቅልፍ ያልተኛ ሰው ጋር ውይይትም ማድረግ ይከብዳል፤ አንዳንዶች ቀጥታ ወደንጭንጭ እንደሚሄዱም እናውቃለን፡፡ ይህ የሚያሳየው በሀያ አራት ሰአት ውስጥ የሚገባንን የእንቅልፍ ድርሻ እንደምንም ብለን ማግኘት እንደሚኖርብን ነው፡፡ አለዚያ ሰውነታችን በውስጥ በኩል ለተሀድሶና ለጥገና ጊዜ አያገኝም፡፡ ይህን ነገር ሰው ሠራሽ በሆነው በመኪና እንኳን ብንመለከት፣ መኪናውን ለረዥም ጊዜ አቆመዋለሁና ያለማቋረጥ ለረዥም ጊዜ ላሽከርክረው የሚል ያለ አይመስለኝም፡፡ መኪናው በየተወሰነ ሰኣት መቆምና መብረድም ይኖርበታል፡፡ 

አሁን በዚህ በወረርሽኙ ጊዜ የታየ ነገር ቢኖር ብዙ ሰዎች በቂ እንቅልፍ የማያገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በኮምፒውተር ወይም በስልኮቻችን ቤታችን ሆነን ስብሰባና ሥራዎችን ማካሄድ መቻላችን ደግሞ እንቅልፍን መናቅ ወይም ችላ ወደ ማለቱ አድርረሶናል፡፡ ከላይ የጠቀስኩት የባለመያተኞች ማህበር ይህንን በሚመለከት ባደረገው ሰፋ ያለ መጠየቅን የተመረኮዘ ጥናት፣ ከተጠየቁት ሰዎች 33% የሚሆነት በቂና ጤናማ የሆነ የእንቅልፍ ሁኔታ የተዛባባቸው መሆኑን፣ 30% የሚሆኑት ደግሞ በሰኣቱ እንቅልፍ ሊወስዳቸው ያልቻለ መሆኑን ሲመልሱ 29% የሚሆኑት ደግሞ በማታ የሚተኙት የዕንቅልፍ ጊዜ መጠን ላይ ለውጥ ያለ መሆኑን መልሰዋል፡፡

በቂ እንቅልፍን በሚመለከት፣ የባለሙያተኞቹ ማህበር የሚመክረው አብዛኞች ሰዎቸ በየቀኑ ሰባት ሰአታት መተኛት አለባቸው ነው፡፡ በየቀኑ የሚለውን ማስመር አስፈላጊ ነው፡፡ ብዙዎቻችሁ ይቀልዳል እንዴ ሳትሉ አትቀሩም፡፡ ሰባት ሰአት ከየት ይመጣልም ሳትሉ አትቀሩም፡፡ ዋናው ነገር፣ ከሚቀጥለው ቀን መበደር ክልክል ነው፡፡ ሰባት ሰአት እንቅልፍ ለአብዛኛቹ አዋቂ ሰዎች የሚሆን ምክር ነው፡፡

አሁን የኮቪድ ክትባት በስፋት ለህብረተሰቡ እንዲዳረስ ጥረት እየተደረገ ነው (በአሜሪካ)፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን፣ ባለሞያተኞቹ ከፍተኛ ጥረትና ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ ትልቁ ማነቆ በቂ ምርት አለመኖሩ ሲሆን፣ በቂ ምርት ሲኖር ደግም ያው ሁላችንም የምናውቀው የኢኮኖሚ አቅም ወሳኝ ሊሆን ነው፡፡ ግን እዚህ ላይ፣ አጋጣሚው ቢፈጠር እንደተለመደው ሰብሰብ ብለን ክትባቶች ለኢትዮጵያውን እንዲዳረስ በመጠኑም ቢሆን አስተዋፅኦ ማድረግ የምንችል ይመሰለኛል፡፡

በአሜሪካ አሁን ክትባትና የክትባት አሠጣጥ በየስቴቶቹ መንግሥታት በኩል ሰለነበር፣ ያም እንደምናወቀው ችግርም ሰላለበት፣ በአሜሪካ አዲሱ ሳይንስ የሚያከብረው አስተዳደር፣ ክትባቱ በቀጥታ ወደጤና ተቋማት እንዲደርሰ በማድረግ ክትባት ማግኘት የሚገባቸው ሰዎች አንዲያገኙ ለማድረግ እየሞከረ ነው፡፡ እዚህ ላይ፣ አዳዲስ በሚከሰቱ የቫይረሱ ዝርያዎች ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር በማስተዋል፣ ክትባቱ ቶሎ ተዳርሶ፣ ከሌሎች የበሽታው ሥርጭት መከላከያ ተግባራት ጋር በመተጋገዝ የቫይረሱን በስፋት መሠራጨት ማቆም ተገቢ ነው፡፡ ቫይረሱ ካልተሠራጨና ካልተራባ አዲስ ዝርያ የለም፡፡ ይህን ሁሉም ማወቅ አለበት፡፡

ታዲያ የኮቪድ-19 ክትባት ከመውሰድዎ ከአንድ ቀን በፊት በቂ እንቅልፍ መተኛት ክትባቱን ከወሰዱ በኃላም እንዲሁ ለአንድ ቀን በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ የሰውንት የመከላከያ አቅምዎን ስለሚያጎለብተው ለክትባቱ ጥሩ ምላሽ ይኖረዎታል ይላሉ ባለሙያተኞቹ፡፡ ይህ ምክር ከመሥመር የወጣም አይደለምና ሁላቸንም በፅሞና ልንቀበለውና ተግባራዊ ልናደረገው ይገባል፡፡

ባጠቃላይ ግን፣ በቂ እንቅልፍ አለማግኘት በሰውነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ዝርዝ ሰፋ ያለ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሰውነት ግዝፈት ወይም ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው ሰዎች አልጋ ላይ ጋደም ቢሉም በቂ እንቅልፍ የማያገኙበት ሁኔታ አለ፡፡ በእንግሊዝኛ Sleep apnea ይባላል፡፡ ትንፋሻቸው እየተቆራረጠ በቂ ኦከስጅን ወደ ሰውነታቸው ሰለማይደርስ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ያገራችን ልጆች ጨምሮ ብዙ ባለሙያተኞች ምርመራ፣ ህክምናና ርዳታ የሚያደርጉም አሉ፡፡ ለወደፊት ትምህርቱን በቀጥታ ከነሱ ማግኝት አንችላለን፡፡ እስከዛ ደረስ ግን ምክሩን አስተውሉም አካፍሉም፡፡ በቂ እንቅልፍ ማግኘትን መናቅ የለብንም፡፡

መረጃ፡ Temporal Links Between Self-Reported Sleep and Antibody Responses to the Influenza Vaccine, International Journal of Behavioral Medicine (2020)