​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

መርሳ (MRSA)

Methicillin-Resistant Staphylococcus Aureus ሜቲሲሊን ሬሲስታንት ስታፍሎኮከስ ባጭሩ መርሳ( MRSA ) ተብሎ የሚታወቀው ባክቴሪያ በተፈጥሮው ለብዙ ፀረ ህዋስ (antibiotics) መድሃኒቶች የማይመለስ ወይም የማይድን በሽታ ይፈጥራል፡፡ ባለፉት አስር አመታት ይህ ባክቴሪያ በሰዎች ላይ የሚያደርሰው ቁሰለት (infection) እየጨመረ በመሄዱ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ነው፡፡ ይህ ባክቴሪያ እንደስሙ አጠራር ሜቲሲሊን የተባለ ፀረ ህዋስ መድሃኒትን መቋቋም የሚችል ሲሆን ከሜቲሲሊን አልፎ ሌሎች መድሃኒቶች እነደ ፔኒሲሊን፤ አምፒሲሊን፤ ኦከሳሲሊን የመሳሰሉትን የመቋቋም  ችሎታ አለው፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት መድሃኒቶች ደግሞ ለቁስልና ለሌሎች አይነት ቁስለቶች ሀኪሞች በየጊዜው የሚጠቀሙባቸው መድሃኒቶች ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ መድሃኒቶች የማይሠሩ ከሆነ ችግሩ የከፋ ሊሆን ነው፡፡

ወደ ባክቴሪያው ስንመለስ የመርሳ ሁለት አይነት ባክቴሪያዎች እንደሚከተሉት ናቸው፡፡ (Community acquired) በህበረተሰብ ውስጥ የሚገኝ (Hospital acquired) ደግሞ በሆስፒታል ውስጥ የሚገኝ ናቸው፡፡ ሁለቱም ክበደቱና አይነቱ የተለያየ ቁስለት ወይም ልክፍት ያስከትላሉ፡፡ በአብዛኛው ጊዜ በህበረተስብ ውሰጥ የሚታየው በሽታ ቆዳና ከቆዳ በታች የሆነውን የሰውነት ክፍል በመልከፍ የታወቃል፡፡ በአብዛኛው እንደ ቡግንጅ አንዳንዴም ሰፋ ያለ የመግል መቋጠር ያለበት ቁስለት ይታያል፡፡ አልፎ አልፎ ግን በተለይ በህፃናት ላይ ወደ ሳንባ በመዝለቅ ለህይወት አስጊ የሆነ የሳንባ ምች (pneumonia) ያስከትላል፡፡ በአዋቂዎች ኢንፍሉዌንዛን ተከትሎ የሳንባ ምች በማምጣት ይታወቃል፡፡ በህብረተሰቡ የሚታየው ባክቴሪያ ከላይ ለተጠቀሱት ፀረ ህዋስ መድሃኒቶች የማይመለስ ቢሆንም ለሌሎች በአፍ መወሰድ ለሚችሉ ውድ ባልሆኑ ፀረ ህዋስ መድሀኒቶች (ቴተራሳይክሊን፤ ዶክሲሳይክሊን፤ ክሊንዳማይሲን፤ ባክትሪም) መታክም ይችላል፡፡ ቡግንጅ ወይም መግል በመቋጠር የሚከሰቱ በሽታዎች አይነተኛ መፍትሄ መግሉን ከሰውነት ማሰወገድ ነው፡፡ ይህንን በሚመለከት ለአንባብያን “መግልና ሽንት ከሰውነት መውጣት አለበት” ተብሎ የሚነገር አባባል እንዳለ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

ሌላው አይነት ደግሞ ሰዎች በሆስፒታል ቆይታቸው የሚጋለጡበት የሆስፒታል አይነቱ መርሳ ነው፡፡ ይሄኛው ባክቴሪያ ጠንከር ያለ ለህይወት አስጊ የሆነ የውስጥ ሰውነት ክፍሎች በሽታ በማምጣት የሚታወቅ ነው፡፡ አሳዛኝ ሆኖ ይህ ባክቴሪያ የሚታከመው በጣም ቁጥራቸው ባነስ በመርፌ አማከኝነት በሚሰጡ መድሃኒቶች ነው፡፡ የነዚህ መድሃኒቶች ዋጋ ደግሞ ባገራችን አነጋገር የትየ ለሌ ነው፡፡ ይህ የባክቴሪያዎች መድሀኒትን የመቋቋም  (Resistance) ችሎታ በአሁኑ ወቅት በጣም አሳሳቢ ደረጃ ደርሶአል፡፡ ከመርሳ ውጭ ሌሎች ፀረ ህወሳት መድሃኒቶቸን መቋቋም የሚችሉ ለህይወት አስጊ የሆነ በሽታ የሚያመጡ በርከት ያሉ ባክቴረያዎች አሉ፡፡ ፀረ ህዋሳት መድሃኒትን ያለአግባብ መጠቀም ወይም የታተዘዙ መድሃኒቶችን በትክክል አለመጨረስ የዚህ የባክቴሪያዎች መቋቋም ችሎታ መንስኤ መሆኑ ይታወቃል፡፡

መርሳ ባጠቃይ ስታፍ ኦሪየስ ተብሎ የሚጠራው የባክቴሪያ ዘር ነው፡፡ ሰዎችን ብዙ የሚያስገርመው ነገር ይህ ስታፍ ኦሪየስ የሚባለው ባክቴሪያ በብዙ ሰዎች የሰውነት ክፍል በመቻቻል የሚኖር ነው፡፡ ከ 20 ሰከ 25% በሚሆኑ ሰዎች ይህ ስታፍ ኦሪየስ የሚባል ባክቴሪያ ባፍንጫቸው ውስጥ ይገኛለናል ተብሎ ነው የሚገመተው፡፡ ይህ አይነት የባክቴሪያዎች ቁስለት ሳያመጡ በሰውነት ክፍል መገኘት (colonization) ይባላል፡፡ ከ 2% ያነሱ ሰዎች ደግሞ መርሳ ባፍንጫቸው ውስጥ እንደሚኖር ይገመታል፡፡

በአብዛኛው ችግር እየፈጠረ ያለው መርሳ የሚያመጣው በቆዳ ላይ የሚከሰቱ ቁስሎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ላይ ቁስሎች በተደጋገሚ የሚከሰቱ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ታዲያ ይህንን በመርሳ የሚመጣውን የቆዳ ቁስል እንዴት መከላከል ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ማስታወስ የሚገባን ነገር ቢኖር መርሳ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ባክቴሪያ መሆኑን ነው፡፡ የአንድ ሰው ቁስል በጥንቃቄ ካልተጠበቀ የቤተሰብና የህብረተሰብ ችግር ነው፡፡

ለራስዎና ለሌሎች ሲሉ የሚከተሉትን ምክሮች ልብ ብለው ይከታታሉ 
 
ራስዎን ከመርሳ  ቁስል መከላከል

  • በየጊዜው የራስዎን የሰውነት ንፅህና የሚጠብቁ ነገሮችን ማድረግ በሽታውን ለመከላከል ይረዳል፡
  • እጅዎን በደንብ በሳሙና መታጠብ አለዚያም አልኮሆል ባለባቸው የእጅ ፈሳሾች እጅዎን በደንብ መወልወል
  • በቆዳ ላይ የሚታዩ የመቆረጥ ወይም ሎሎች ቁስለቶችን በንፅህና መጠበቅ በተጨማሪም እስከሚድኑ ድረስ በቁስል መሸፈኛዎች መሸፈን
  • የሌሎች ሰዎችን ቁስሎች ወይም የተጠቀሙባቸውን የቁስል መሸፈኛዎች ከመንካት ይቆጠቡ
  • የግል መፀዳጃወችን፤ ፎጣዎችን፤ የፂም መላጫዎችን ከሌሎች ሰዎች ጋራ አይጋሩ


 መርሳ ካለብዎት ደግሞ በሽታው እንዳይዛመት ማድረግ የሚገባዎት ነገሮች

  • ቁስልዎትን ይሸፍኑ
  • መግል ወይም ሌላ አይነት ፈሳሽ የሚታይባቸው ቁስሎቸን እስከሚድኑ ድረስ በንፁህ የቁስል መሸፈኛዎች ይሸፍኑ፡፡ የተጠቀሙባቸውን የቁስል መሸፈኛዎች በአግባቡ የቆሻሻ መጣያ ውስጥ ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡ መግልና መግሉን የነኩ መሸፈኛዎች መርሳ ስለሚኖርባቸው ወደ ሌሎች ሰዎች በቀላሉ መዛመት ይችላሉ፡፡ የሀኪምዎን ምክር ይከታታሉ፡፡
  • ቁስልዎን ከነኩ በሁዋላ እጅዎን በሚገባ እሰካልታጠቡ ድረስ ሌላ የሰውነት ክፍልዎን ከማከክ ወይም ከመነካካት ይቆጠቡ፡፡ በሽታው በቀላሉ ከአንድ የሰውነት ክፍል ወደ ሌላ እነዳይዛመት፡፡
  • እርስዎም ሆነ የቅርብ ቤተሰብዎ እጅዎን በደንብ በሳሙና መታጠብ አለዚያም ከላይ እነደተጠቀሰው አልኮሆል ባለባቸው የእጅ ፈሳሾች እጅዎን በደንብ መወልወል፡፡ በተለይም ቁሰሎችን ካፀዱ ወይም የቁስል መሸፈኛዎችን ከቀየሩ በሁዋላ እጅዎን ከላይ እንደተጠቀሰው መታጠብ አስፈላጊ ነው፡፡
  • የግል መፀዳጃዎችን አይጋሩ፡ የግል መገልገያዎች እንደ ፎጣ፤ መላጫዎች፤ ልብሶች፤ መሳሰሉትን ከቁስልዎ ጋራ የተነካኩ ማንኛውንም አይነት ነገሮችን አይጋሩ፡፡ ፎጣ፤ አንሶላዎችን፤ ልብሶችዎን በልብስ ሳሙናዎች በደንብ ማጠብና ማድረቅ ተገቢ ነው፡፡
  • በቤትዎ ውስጥም ሆነ በሌላ ቦታዎች ከቁስሉ ጋራ የተነካኩ ማንኘውንም ቁሳቁሶች ማፅዳትና በንፅህና መጠበቅ
  • ወደ ህክምና ቦታ ሲሄዱ በመርሳ መለከፍወን ካወቁ ለህክምና ባለሙያዎች አስቀድሞ መንገር በሽታው ወደ ሌላ ሰው እንዳይጋባ ለሚያደርጉት መከላል ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ትክክለኛውን መድሃኒት ለማዘዝም ይረዳል፡፡ 


መልካም ንባብ