ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

​​ዚካ ቫይረስ አዲስ ዜና

የመጀመሪያው ከሴት ወንድ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የዚካ ቫይረስ መተላለፍ ተዘገበ
ነገሩ የተጀመረው የኒው ዮርክ የጤና ቢሮ ከሴት ወደ ወንድ ዚካ ተላልፏል የሚባል ጥርጣሪ ያለበት ሁኔታ ባቀረበው ሪፖርት፣ ዚካ ቫይረስ ይተላለፍበታል ከሚባል አካባቢ የመጣች ሴት ኒው ዮርክ የገባች ለት ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ያለ መከላከያ ወይም ኮንዶም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ታደርጋለች፡፡ በኋላ ሲመረመር በደሟ ሆነ በሽንቷ የዚካ ቫይረስ ይገኛል፡፡ ከሴትዮዋ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ያደረገው ወንድ ጓደኛዋ ካደረገ ከሰባት ቀን በኋላ በዚካ ቫይረስ የመለከፍ ስሜትና ምልክት ያሳያል፡፡ በሰውየው በተደረገው ምርምራ በሽንቱ ውስጥ የዚካ ቫይረስ ይገኛል ሆኖም በደም ውስጥ በተደረገው ምርመራ አልተገኘም፡፡ እንደዚህ አይነት የመተላለፍ ሁኔታ ሲከሰት ወይም ሲጠረጠር እንደሚደረገው ሁሉ፣ ሰውየው በጣም ጠለቅ ያለ ቃለ መጠየቅ ይደረግለታል፡፡ በቃለ ጥያቄውም ሰውየው ከመታመሙ በፊት ለአንድ አመት የሚሆን ከአሜሪካ ወጥቶ አያውቅም፤ በቅርብ ጊዜ ቢሆንም ሌላ የግብረ ሥጋ ግንኙነት አላደረገም፤ ከመታመሙ ከአንድ ሳምንት በፊት በሞስኪቶ ተነክሶም አያውቅም፡፡ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ መደበኛ የሆነ ግብረ ሥጋ ያደረገ ሲሆን ምንም ደም የመፍሰስ ምልክት አላየም፡፡ ሴትዮዋ ወደ ኒው ዮርክ ሰትመለስ በደሟ ውስጥ የዚካ ቫይረስ ነበረባት፡፡
ይህ ዘገባ የሚያሳየው ለመጀመሪያ ጊዜ ዚካ ቫይረስ ከሴት ወደ ወንድ ባልተጠበቀ ግብረሥጋ ግንኙነት መተላለፉን የሚጠቁም መረጃ መሆኑን ነው፡፡
ከእንደዚህ አይነቱ ሁኔታ ለመከላከል ቢቻል ግብረሥጋ ግንኙነት አለማድረግ፣ ካልሆነም ደግሞ ኮንዶም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ግብረሥጋ ግንኙነት ሲባል ደግም በአፍ የሚደረገውንም ይጨምራል፡፡ በአፍ ለሚደረጉ ወሲባዊ ግንኙነቶች መከላከያ የአፍ ኮንዶም እንዳለ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡
ለተጨማሪ መከላከል ግንዛቤ ድረ ገፁ ውስጥ ስለዚካ የተፃፈውን ያንብቡ፡፡
በነገራችን ላይ ይህ ቫይረስ በጣም አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡


ዚካ ቫይረስ (Zika virus)
 ከዚህ ቀደም ኢቦላ የሚባል ቫይረስ በተለይም በምዕራባዊ የአፍሪካ አህጉር ያደረሰውን ችግር ተመልክተናል ወይም ተከታትለናል፡፡ አንግዲህ አዲስ ዚካ የሚባል ቫይረስ ደግሞ ጉዳቱ የኢቦላ ቫይረስን ያህል ባይሆንም ከፍተኛ አሳሳቢ ሁኔታ በተለይም በነብሰ ጡር አናቶች በፅንስ ላይ የሚያሰክትለው ጉዳት እየታወቀ መጥቷል፡፡
ሰለ በሽታው ከመነጋገራችን በፊት ይህ ቫይረስ እንዴት እንደሚተላለፍ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ቫይረሱ በሞስኪቶ ንክሻ አማካኝነት የሚተላለፍ ሲሆን፡፡ ይህንን ቫይረስ የሚያሰተላልፈው የሞሰኪቶ ዝርያ ኤዲስ(Aedes) ተብሎ የሚጠራ ነው፡፡ ነገራችን ላይ ይህ የሞስኪቶ ዝርያ ሌሎች ቫይረሶችንም ያስተላልፋል ደንጌ እን ቺኩንጊኒያ የተባሉትን፡፡
የበሽታውን ሥርጭት በሚመለከት ሲዲሲ(CDC) የአሜሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ያወጣው ካርታ ላይ ከሰዎች ላይ በተወሰደው ደም ምርመራ መሠረት ለዚህ ቫይረስ ወይም ለሌላ ተመሳሳይ ቫይረስ የተጋለጡ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት በኢትዮጵያም ውስጥ መገኘቱን ይጠቁማል፡፡ ከ2015 በፊት ቫይረሱ በአፍሪካ በደቡብ ምስራቅ ኤስያ አና በፓሲፊክ አይላንድስ የታየ ሲሆን ከግንቦት 2015 ወዲህ ግን መጀመሪያ በብራዚል አሁን ግን በተለያዩ ቁጥራቸው እየጨመረ ከመጣው የደቡብ አሜሪካ አገሮች እየታየ ነው፡፡

ወደ መተላለፊያ መንገድ ስንመለስ ከሞሰኪቶ ንክሻ በተጨማሪ በመጠኑም ቢሆን በቫይረሱ ከተለከፈች ነብሰ ጡር ወዳልተወለደው ፅንስ የመተላለፍ ሁኔታ አለ በተለይም በወሊድ ጊዜ፡፡ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውም ይህ ሁኔታ ነው፡፡

በደም ዝውውር አማካኝነት ቫይረሱ ለመተላለፉ ዘገባ ሲኖር በግብረ ስጋ ግንኙነትም ለመተላለፉ አንድ ሪፖረት ያለ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የበሽታው ስሜትና ምልክቶች
ባቫይረሱ ከተለከፉ ሰዎች ከአምስቱ አንዱ የበሽታ ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ በአብዛኛው የሚታየው ስሜትና ምልክቶች ትኩሳት፤ ሽፍታ፤ የመገጣጠሚያዎች ህመም ወይም ቁርጥማት፤ አይን መቅላትን ይጨምራል፡፡ ራስ ምታትና የሠውነት ወይም የጡንቻዎች ህመም ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ አንግዲህ ለራሱ የተለየ የበሽታ ስሜት ምልክት አለመኖሩን ነው የሚያሳየው፡፡  በቫይረሱ ከተለከፉ በሁዋላ በምን ያህል ጊዜ በሽታው እንደሚከሰት ( )ርግጠኛ መረጃ ባይኖረም በጥቂት ቀናት አስከ አንድ ሳምንት ባለው ጊዜ ወስጥ ሊከሰት አንደሚችል ነው፡፡

ይህ በሽታ ከፍተኛ ደረጃ የሆነ ሆስፒታል ውስጥ የሚያሰተኝ ደረጃ አይደርስም፡፡ በዚህ በሽታ ምክንያትም ህይወት ማለፍ በጣም ያልታየ ነገር ነው፡፡ በሽታው ቀለል ያለ ሲሆን ሰዎችም ካገገሙ በሁዋላ ቫይረሱ በእንዳንድ ሰዎች ላይ በደማቸው ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል ነው
፡፡


​ስለ ዚካ (Zika Virus) ቫይረስ ተጨማሪ መረጃ

ዚካ ቫይረስ ትልቅ ችግር የሚያስከትለው በማህፀን ውስጥ ባለ ፅንስ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ዚካ ቫይረስና ሲወለዱ ጭንቅላታቸው ከመጠን በታች(microcephaly) ያነስ ህፃናት ጋር ግንኙነት እንዳለው ይጠቀስ ነበር፡፡ ነገር ግን እሰከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቫይረሱ ለዚህ የጭንቅላት ማነስ ትክክለኛ መንስኤ ለመሆኑ መረጃ አልነበረም፡፡
አንባብያንን ለማስታወስ ግንኙነት አለ መባልና መንስኤ ነው መባል ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ መንስኤ ነው ብሎ በርግጠኝነት ለመናገር መረጃ ያስፈልጋል፡፡
ወደ ጉዳዩ ስንመለስ በዚህ በሽታ ከባድ ችግር የደረሰበት አገር ቢኖር ብራዚል ነው፡፡ በብራዚል ወደ 4700 ጭንቅላተቸው ከመጠን በላይ ያነሰ ህፃናት አንዳሉ ሪፖርት ቀርቧል፡፡  ያም ሆኖ በፊብሩዋሪ 9 2016፣ ቫይረሱ በ26 ሀገሮች በሞስኪቶ አማካኝነት እየተላለፈ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የጭንቅላት ከመጠን በላይ ማነስና ቫይረሱ ግንኙነት መኖሩ ጥናት እንዲደረግ ተደርጎ የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያ ማእከል(CDC) ለዚሁ ባዘጋጀው ምርምራ ከአራት ማለትም ሁለት በ36 እና በ38 ሳምንት ውሰጥ ተወልደው ግን በ20 ሰአታት ውስጥ የሞቱ ህፃናትና ሁለት ደግሞ በ 11 አና በ13 በውርጃ የወጡ ፅንሶች ላይ የተገኙ የሰውነት ክፍሎች ላይ ምርምራው ይደረጋል፡፡ የነዚህ አራት ነብሰጡሮች የዚካ ቫይረስ በሽታ ምልክት በመጀማሪያዎቹ የእርግዝና ሳምንቶች ውስተ የታባቸው መሆኑ ይረጋገጣል፡፡ የነዚህ አራት ፅንሶች የሰውነት ክፍል ላይ በተደረገው ምርመራ አራቱም ላይ የዚካ ቫይረስ መገኘቱ ተረጋግጧል፡፡ ይህም የቫይረሱ የዘር ሰንሰለት በሚመረምር (RT-PCR ) በተባለ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ነው፡፡ ይህ ቫይረስ የተገኘው በፅንሶች አንጎል ነው፡፡ ተያይዞም በአንጎል ውስጥ የተለያዪ የበሽታ ምልክቶች መገኘታቸውን ምርመራው ይዘግባል፡፡በተደረገው ምርመራም በአንጎል ላይ ተመሳሳይ ጉዳት የሚያሰከትሉ ሌሎች በሽታዎች ለምሳሌ ሄርፒስ፤ ኤችአይቪ፤ እና ሌሎች ተጨማሪ ቫይረሶች እና ቶክሶፕላስማ የሚባል ተባይ አለመኖሩ ይረጋገጣል፡፡ እንግዲህ ከዚካ ቫይረስ በአንጎላቸው ውስጥ መገኘቱ፤ አንጎልም ውስጥ የመጎዳት ምልክት መታየቱ በተጨማሪ ለዚህ የእንጎል መጎዳት ሌሎች ምክንያቶች አለመኖራቸውን ወይም አለመገኛታቸውን አንባቢ መረዳት ይኖርበታል፡፡
በዚህ ግኝት መሠረት ዚካ ቫይረስና የአንጎል መጎዳት ተያይዞም ትንሽ ጭንቅላት ይዞ መወለድ ቀጥታ ግንኙነት እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡

አዲስ ተጨማሪ ነገር ቢኖር ዚካ ቫይረስ በሞስኪቶ ብቻ ሳይሆን በግብረ ሥጋ ግንኙነት ከሰው ወደ ሰው እንደሚታላለፍ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ቫይረሱ አለ የሚባል አካባቢ የተጉዋዙ ወይም የሚኖሩ ወንዶቸ ከነብሰ ጡር ሴቶች ጋር የሚያደርጉት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፅንሱን አደጋ ላይ ስለሚጥል ወይም እርግዝናው እስከሚጨረስ መቆጠብ አለዚያም መከላከያ ኮንዶም መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡


​ሕክምና
እንደ ብዙዎች በቫይረስ አማካኝነት ለሚከሰቱ በሽታዎች ሁሉ የራሱ የሆነ መድሃኒት እሰካሁን የለም፡፡ ነገር ግን የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ ሊረዳ ይችላል፡፡
በቂ እረፍት ማድረግ
በቂ ፈሳሽ መውሰድ በተለይም የሰውነት ድርቀት እንዳይፈጠር ለመከላከል
የህመም ማሰታሻ መድሀኒቶችን መውሰድ (ለዚህ ደግሞ የሚመረጠው ታይለኖል ወይም ፓናዶል ወይም ፓራሲታሞል ተብሎ የሚጠራው መድሃኒት ነው፡፡ ሌሎች እንደ አስፒሪን፤ አድቪል ወይም አይቡፐሮፌን ወይም ሞትሪን እና አሊቭ ወይም ናፐሮሲን የሚባሉ መድሀኒቶችን ሀኪምዎች ሳያማክሩ መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቶም የበሽታው ምልክቶች ሌሎች እንደ ደንጌ የተባሉ በሽታወች ጋራ ተመሳሳይነት ስላለው ድንገት በደንጌ የተለከፉ ሰዎች እነዚህን መድሃኒቶች ቢወስዱ ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ ችግር ስለሚፈጠርባቸው ነው፡፡

ነብሰ ጡር የሆኑ ሴቶች
ነብሰ ጡር የሆኑ ሴቶች በቫይረሱ ለመለከፍ የተለየ ሁኔታ ባይኖረባቸውም መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በቫይረሱ ከተለከፉ ነብሰጡሮች የተወለዱ ህፃናት ላይ ጭንቅላት ከመጠን በላይ ወይም ከጤናማ መጠን በታች ያነሰ ሁኔታ መከሰቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በእንግሊዘኛ (Microcephaly) ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ምክንያት ነብሰጡር ሴቶች ይህ ባይረስ ወዳለባቸው ሀገሮች ወይም አካባቢዎች እንዳይጓዙ ምክርና መመሪያ የሚሠጠው፡፡

ለጊዜው ዋናው አሳሳቢ ችግር ይህ ስለሆነ በሽታውን መከላከያ ክትባት ወይም መከላከያ መድሃኒት ሰለሌለ ነብስ ጡሮች ምክሩን መከተል ይኖረባቸዋል፡፡

የግድ መጓዝ ካለባቸው ደግሞ በሞስኪቶው እንዳይነከሱ  ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም እጅጌ ረጅም ልብስ ከመልበስ ጀምሮ ጤና ላይ ጉዳት የማያሰከትሎ የሞስኪቶ መከላከያ የሚረጩ ኬሚካሎችንና ሰውነት ላይ እንደመከላከያ የሚደረጉ ኬሚካሎችን ይጨምራል፡

መከላከያ መንገዶች
ለእንደዚህ አይነት መድሃኒት ወይም ክትባት ለሌላቸው በቫይረስ አማካኝነት ለሚከሰቱ በሽታዎች መከላከያ አብይ መንገድ ነው፡፡ የሚያተኩረውም ቫይረሱን ከሚያሰራጩ ሞስኪቶዎች ንክሻ ራስን ማስጣል ነው፡፡  ይህ ኤዲስ የተባለ የሞስኪቶ ዝርያ ደግሞ ሰዎችን የሚነከሰው በቀን ወይም በብርሃን ጊዜ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ከዚካ በሽታ በተጨማሪ ደንጌ እና ቺኩንጊኒያ በዚህ ሞስኪቶ ዝርያ አማካኝነት እንደሚተላለፍ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ከሞስኪቶ ንክሻ ለመከላከል 
የሚረጩ ጤና ላይ ጉዳት የማያሰከትሉ ኬሚካለሎችን መርጨት
ሞስኪቶ እንዳየነክስ ሰውነት ላይ የሚቀቡ ወይም የሚረጩ ኬሚካሎችን መጠቀም፡፡ ነገር ግን ለህፃናት ተገቢ መሆኑን ማጣረት አስፈላጊ ነው፡፡
የሚለብሱት ልብስ ፐሪሜትሪን የተባለ ኬሚካል የተቀባ ከሆነ ወይም 

ራስዎ ልብሱ ላይ ሊያደርጉብት የሚችሉ ከሆነ ያድርጉበት
አጅጌ ረጅም ልብስ መልበስ
የቤትዎ በርና መስኮተች ሞስኪቶ ወደ ውስጥ እንዳየገባ የሚካለከሉ ስክሪኖች ማድረግ
ሞሰኪቶ እንዳይረባ የተጠራቀሙ ወይም የተቋቱ ውሃዎችነ ማፍሰስና ማፅዳት በተለይም የአበባ ማሳደጊያ ቤትዎ አካባቢ ጎድጎድ ያሉ ውሀ ሊጠራቀምባቸው የሚችሉ ቦታወችን መድፍን


ድንገት በቫይረሱ ከተለከፉና የበሽታው ስሜት ካለብዎት ለመጀመሪያው ሳምንት ሞስኪቶ እንዳይነክስዎት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም በደምዎ ውስጥ ቫይረሱ ስላለ ሞስኪቶ አርስዎ ከነከሰ በሁዋላ ቫይረሱን በመሸከም ወደ ሌላ ወዳልተከለፈ ሰው በንክሻ አማካኝነት ሊያስተላልፍ ስለሚችል ነው፡፡

ዚካ ቫይረስን በማስተላለፍ የሚታወቁት የሞስኪቶ ዝርያወች

እነዚህ ቫይረሶች ከዚካ ተጨማሪ ሌሎች በሽታዎችን ደንጌ፣ ቹኩንጊኒያ የተባሉትንም ያስተላልፋሉ
ለመራባትም በጣም ትንስ የተጠራቀመ ውሃ ነው የሚበቃቸው፡፡ የጠርሙስ ክዳን ወይም ቆርኪ ላይ ያለ ውሃ በቂ ነው፡፡
በቤትና ከቤት ውጭ መኖር ይችላሉ፡፡ አይነተኛ ባሕሪያቸው ደግም በብዛት የሚናከሱት በቀን ነው፡፡
ሰዎቸን መንከስ ይመርጣሉ፡፡  እነዚህ ሁለት የሞስኪቶ ዝርያዎቸ በተፈጥሮ በሰሜን አሜሪካ ይገኛሉ፡፡ ከስር ምስሉን ይመልከቱ፡፡
 ዋናው ቸግር በቫይረሱ የተለከፈ ሰው አግኝተው ከነከሱ ቫይረሱን ማራባት ይጀምራሉ፡፡

በዚህ ምክንያት
ሞስኪቶዎች በአካባቢዎ እንዳይራቡ እስፈላጊውን ጥረት ማድረግ የሁሉም ሰው ግዴታ መሆን አለበት
በተለይም ከውጭ ውሀ እንዳይጠራቀም ማድረግ
ውጭ የሚወጡ ከሆነ ከላይ እንደተጠቀሰው የሞስኪቶ መከላከያ ቅባቶችን መጠቀምና ረዥም እጅጌ መልበስ አስፈላጊ ነው፡፡

Countries where active transmission of Zika virus is reported, CDC