​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

በከፍተኛ ቁጥር የሚገኘው የአባለ ዘር በሽታ??

 
ከማንበብዎ በፊት የራስዎን ግምት ይያዙ፡፡

 በሥራ ላይ፣ ይህ ስሙን ያልጠቀስኩት በሽታ በአሮጊቶች ወይም በዕድሜ በልፀግ ያሉ ሴቶች ላይ ሲታይ በመገረም ነበር የምንከታተለው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሴቶች በአብዛኛው ባለትዳር የሆኑ፤ የወር አበባ ያቆሙ በመሆናቸው በርግጥም ደግሞ ከትዳር ውጭም ውስልትና ያደርጋሉ የማይባሉ ስለሆነ እንዴት ነው ይህ  በሽታ ወይም ልክፍት የሚገኝባቸው በሚል ጥያቄ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ በወጣ መረጃ፣ ይህ በሽታ ዕድሜያቸው ከ47 እስከ 53 አመታት በተቆጠረ ሴቶች ላይ በክፍተኛ ደረጃ መገኘቱ ተገልፆአል፡፡ ለዚህ ሁኔታ ባለሙያተኞቹ የተለያየ መላ ምት አቅርበዋል፡፡ ከሌሎች የአባለ ዘር በሽታዎች ጋር ሲነፃፀር፣ ይህ በወጣት ሴቶች ላይ ይታይና ተመልሶ ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው የእድሜ ክልል ባሉ ሴቶች ላይ ይታያል፡፡ ይህ እንግዲህ በአሜሪካ ነው፡፡

በኢትዮጵያስ እንዴት ይሆን ብዬ መረጃ ሳፈላልግ፣ አንድ ለህዝብ የቀረበ ጥናት አየሁ፡፡ ይህ እኤአ በ2013 በጅማ ዩኒቨርሰቲ በነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ በተደረገው ጥናት፣ አጥኝዎቹ ደ/ር አብዱረህማን መሀመድ፣ አህመድ ዘይነዲንና ዘለቀ እሽቴ እንደዘገቡት ከ361 ነፍሰጡሮች መሀከል በ18 የዚህ በሽታ መንስኤ የሆነው ተባይ ተገኝቷል፡፡ በርፐስንት ሲቀመር 4.98 መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ጥናቱ ባለቤቶች አባባል በወጣት ነፍሰጡር ሴቶች ላይ ከፍተኛ ፐርሰንት ነው፡፡

ከቫይረስ መንስኤ ውጭ ይህ በአለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ ወይም ቁጥር የሚገኘው በሽታ ትሪኮሞናስ ቫጂናሊስ በሚባል ተባይ ወይም ህዋስ አማካኝነት የሚከሰተው ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ስሙ Trichomonas Vaginalis (T. Vaginalis ወይም TV) ይባላል፡፡

እንደ አለም የጤና ድርጅት መረጃ፣ እኤአ 2008 በአለማችን 276.4 ሚሊዮን በሚሆኑ ሰዎች ላይ እንደሚገኝ ነው የተገመተው፡፡ ከዚህ ውስጥ ዘጠና በመቶው በታዳጊ አገሮች በሚኖሩ ሰዎች ላይ ነው የሚገኘው፡፡ አንግዲህ የአባለዘር በሽታ ሲባል በግብረሥጋ ግንኙነት መተላለፉን መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ የሚታወቁት የጨብጥ (Gonorrhea ) የክላሚዲያና (Chlamydia) የውርዴ (syphilis)አንድ ላይ ቢደመሩም የዚህ የ T. Vaginalis ቁጥር ይበልጣል ማለት ነው፡፡ በብዛት ከመቶ 8.1 ፐርሰንት በሴቶች ላይ የሚገኝ ሲሆን በወንዶች ደግሞ መጠኑ ወደ አንድ ፐርሰንት ይወርዳል፡፡ ለበሽታው በየጊዜው ምርመራ ሰለማይደረግ ነው እንጂ መጠኑ ከዚህ በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

ይህን በሽታ የሚስከትለው T. Vaginalis ጥገኛ ህዋስ ነው፡፡ተባይ ማለትም ይቻላል፡፡ በምስሉ እንዳያችሁት፣ እሰከ አራት ጅራፍ የመሰሉ ጅራቶች ያሉት ይህ ህዋስ በሽንትና በአባለዘር የሰውነት ክፍሎች ላይ መኖር የሚችል ነው፡፡ለመኖር ኦክስጅንም አያስፈልገውም፡፡ በሴቶች በታችኛው የአባለዘር ክፍል ግድግዳዎች ላይ ሲኖር፣ በወንዶች ደግሞ በሽንት ቧንቧና ፕሮሰቴት በተባለ ወንዶች ላይ ብቻ በሚገኝ ዕጢ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ህዋስ ከሰው ወደ ሰው በግብረሥጋ ግንኙነት አማካኝነት ይተላለፋል፡፡ የሚታወቀውም ሰዎችን ብቻ በመልከፍ ስለሆነ በእንስሳት ላይ አይገኝም፡፡

ይህ ህዋስ በሴቶች ላይ ለረዥም ጊዜ አመታትም ድረስ መቆየት የሚችል ሲሆን፣ በወንዶች ላይ ግን ከአስር ቀናት በላይ አይቆይም፡፡

 የበሽታ ምልክቶች

 የሚገርመው 85 በመቶ በሚሆኑ ሴቶችና 77 በመቶ የሚሆኑ ወንዶች በ T. Vaginalis ቢለከፉም ምንም የበሽታ ምልክት ወይም ስሜትም አይኖራቸውም፡፡ ከነዚህ ስሜት ያልተሰማቸው መሀከል አንድ ሶሰተኛው በስድሰት ወራት ውስጥ ምለክቶች ይሰማቸዋል፡፡ በወንዶች ከሆነ፣ በሽንት መውጫ በኩል ፈሳሽ መታየትና ሸንት ሲሸኑ የህመም ስሜትን ይጨምራል፡፡ በሴቶች ደግሞ የማህፀን ፈሳሽ በብበዛት መታየት፣ ፈሳሹም ሽታ የሌለው ቀለሙ ግን በብጫና አረንጓዴ የተቀላቀለ ነው፡፡ ከሱም ጋር አያይዞ የማሳከክ ስሜት፤ የታችኛው ሆድ ህመምና፣ የጾታ ብልት የውጭ ክፍል የመለብለብ ስሜት ይኖራል፡፡ በሴቶች በኩል ተባዩ ወደ ውስጥ ወደላይ ከዘለቀ ግን ተጨማሪ የሰውነት ክፍሎችን በመልከፍ ይታወቃል፡፡በወንዶችም ቢሆን እስከ ፕሮሰቴት መለከፍ ድረስ ያመጣል፡፡

ተደራቢ ችግሮች

ይህ ህዋስ ካለይ የተጠቀሱት የሰውነት ክፍሎችን በመልከፍና የበሽታ ስሜት ከመፍጠር በተጨማሪ ሌሎች ቸግሮች ያስከትላል፡፡

በሴቶች ላይ በሰውነት ክፍላቸው በሚከሰተው በሽታ ምክንያት ሌሎች የአባለዘር በሽታዎች እንደ ጨብጥ፣ ውርዴ፣ ክላሚዲያና ሔርፒስ አብረው የሚገኙ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡ ይህ ማለት እነዚህ ተጨማሪ የአባለዘር በሽታዎች በቀላሉ እንዲይዛቸው ያመቻቻል ማለት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በእርግዝና ላይ ቸግር ያሰከትላል፡፡ ይህም ያለጊዜ መወለድን፤ የሚወለደው ህፃን ክብደት ማነስ፤ የእንጥሽት ውሀ ያለወቅቱ መፍሰስን ሁሉ ያካትታል፡፡ የሚወለደው ህፃን ላይም በሽታ ሊያስከትል እንደሚችልም ተዘግቧል፡፡ በወንዶች በኩል ከሆነ ደግሞ የስፐርም ሴል እንቅስቃሴን የሚቀነስ በመሆኑ መካንነትን ሊያሰከትል ይችል ይሆናል፡፡

ሌላው አሳሳቢ ተደራቢ ችግር ደግሞ በዚህ ህዋስ በመለከፋቸው ምክንያት በኤች አይ ቪ የመለከፍ ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህም T. Vaginalis ከሌለባቸው ሰዎች ጋር ሲወዳደር ነወ፡፡ በዚህ በኤች አይ ቪ የመለከፍ አጋጣሚው ከፍ የሚልበት ምክንያቶቸ ውስጥ አንዱ ያው በግልፅ በዚህ ህዋስ ምክንያት በሰውነት ክፍሎቹ ላይ ቁስለት ሰለሚፈጠር በዚህ በቁስለቱ ምክንያት በተጎዳው የሰውነት ክፍል የኤች አይ ቪ ቫይረስ በቀላሉ ወደ ውስጥ መዝለቅ ሰለሚችል ነው፡፡

 ምርመራ

 በቀላሉ የሚሠራው ከማህፀን ከሚወጣው ፈሳሽ ናሙና በመውሰድ በቀጥታ በማይክሮስኮፕ በማየት ነው፡፡ ይህ ርካሽና በቀላሉ ሀኪሞች ሊያደርጉት የሚቸሉት የምርመራ ዘዴ ነው፡፡ ሆኖም ህዋሱን የማግኘት ወይም የማየት ጉልበቱ አነስ ያለ ነው ያም ከ50-70 ፐርሰንት ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ውድ ይሆናሉ እንጂ ቀጥታ ከማሕፀን ግደግዳ ወይም መግቢያ ላይ ፈሳሽን በመጥረግ ፒሲ አር (PCR) በተባለ ቴክኒክ ህዋሱን የማግኘት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከ95-100 ፐርሰንት፡፡ ከሽንትም በተመሳሳይ መንገድ ምርመራ ማድረግ ይቸላል፡፡ ይህ አይነቱ ምርመራ ግን በታዳጊ አገሮች በስፋት መለመዱን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

 ህክምና

ለዚህ በሽታ ህክምና መድሐኒት የሚሠጥ ሲሆን በብዛት ለአንድ ቀን ብቻ የሚወሰድ መድሀኒት ነው የሚሠጠው፡፡ ሆኖም ኤች አይ ቪና ሌሎች ችግሮች ላለባቸው ሰዎች በተለይም ሴቶች መድሐኒቱ እሰከ ሰባት ቀን ድረስ እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ እንግዲህ ማስተዋል የሚገባው፣ ይህ በሽታ በግብረሥጋ የሚተላለፍ እንደመሆኑ፣ ታካሚው ብቻውን ቢታከም ካልታከመው የትዳር ጓደኛም ይሁን ሌላ በሽታውን መልሶ መቀበል ሁኔታ ስለሚፈጥር የፆታ ግንኙነት ጓደኛም የግድ መታከም አለበት ወይም አለባት፡፡ ይህም ሲሆን በአንድ ላይ በአንድ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የህክምና ባለሙያተኛን እንዲያማክሩ እያሳሰብኩ፣ ለዚህ በሽታ የሚሠጠው መድሀኒት ሜትሮናይዳዞል የሚባለው ነው፡፡ ይህ መድሀኒት ለጃርዲያና ለአሜባም ይሠጣል፡፡

ወደ መግቢያው ልመልሳችሁና፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ዕድሜያቸው ከ47-53 ሆኑ ሴቶች ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሚገኝ መሆኑን ጠቁሜ ነበር፡፡ በዚህ ዕድሜ ክልል ባሉ ሴቶች የዚህ በሽታ መገኘት በትዳር ላይ ጥያቄ ሲያስነሳም ታዝበናል፡፡ የተለያዩ መላ ምቶች ቢሠጡም በተለይም ከሰውነት የሆርሞን ለውጥ ጋር በተያያዘ፣ ጠንከር ያለው ምክንያት ግን፣ ሴቶች ከዚህ ቀደም ተለከፍው ምንም የበሽታ ስሜት ሳይኖራቸው ይህ ጥገኛ ተባይ በሰውነታቸው ውስጥ ለረዠም ጊዜ በፀጥታ በመቆየቱና አሁን በሚከሰተው የሆርሞን ለውጥ ምክንያት የበሽታ ስሜት መፍጠሩ ነው፡፡ የሰባ አምስት አመት ዕድሜ ባለፀጋ ሴት ላይም ያየንበት ሁኔታ አለ፡፡ስለዚህ በዚህ ዕድሜ ክልል(47-53) ባሉ ሴቶች ይህ በሽታ ቢከሰትና በምርመራ ቢገኝ ምንም እንኳን የአባለዘር በሽታ ቢሆንም ከዚህ ቀደም ተጋልጠው ስሜት ሳይፈጥር አብሮ የኖረ ነገር መሆኑን በመገንዘብ፣ ባልየውን “ተረጋጋ” ማለት ያስችላል፡፡  

 መልካም ንባብ