ፕሌግ (Plague) ተላላፊ በሽታ

ሰሞኑን በመገናኛ ከማደጋሰካር በኩል አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ይህ ፕሌግ የተባለ ተላላፊ በሽታ አለ፡፡ ይህ በሽታ በተለያየ መንገድ ነው የሚገለጠው፡፡ እስከዛሬ ድረስ በማደጋሰካር በየአመቱ ይከሰት የነበረው ቡቦኒክ ፕሌግ(Bubonic Plague) የሚባለው አይነት ነበር፡፡ ይህ አይነቱ የአካል ዕጢዎችን በማሳበጥ የሚታወቅ ነው፡፡ ሆኖም ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ባህሪ የለውም፡፡ ይህ በዕጢዎች የሚታየው በሽታ በጊዜ ህክምና ካላገኛ ወደሳምባ ይዘልቅና የሳምባ ምች ወይም ኒሞኒያ ያስከትላል (Plague Penumonia)፡፡ ይህ እንግዲህ ከበሽታው መክፋት በተጨማሪ፤ በበሽታው የለከፉ ሰዎች ሳል በሚስሉበት ጊዜ ባክቴሪያው ከሳምባቸው ከሳሉ ጋር ስለሚወጣ በትነፋሽ አማካኝነት ወደ ሌላ ሰው ይተላለፋል፡፡ ለዚህ ነው የማዳጋሰካር የአሁኑ ሁኔታ አሳሳቢ የሆነው ምክንየቱም የሳምባ ምች አይነቱ ከዋና ከተማው ከአንታናናሪቮና ሌሎችም ከተሞች መታየት በመጀመሩ ነው፡፡  ይህን በሚመለከት የአለም የጤና ድርጅትም ሆነ የአሚሪካው የበሽታ መከላከያና መቆጠጠሪያ ማዕከል ሁኔታውን በቅርብ በመከታተል ላይ ናቸው፡፡

ከዚህም ከዚያም ሰዎች ሰለዚህ ጉዳይ መልክት ሲቀያየሩ ሰለታየ ሰለዚህ ፕሌግ ስለተባለው በሽታ መጠነኛ ማብራሪያ መስጠት ይጠቅም ይሆናል በማለት ይኸው ይህን ፅሁፍ አቅርበናል፡፡

ለመሆኑ ፕሌግ (Plague) ምንድን ነው?

ፕሌግ ቀደም ብሎ የሚታወቅ ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ በሽታው የሚመጣው በባክቴሪያ አማካኝነት ነው፡፡ ቸግሩ ይህ ባክቴሪያ የሚተላለፈው በቁንጫ አማካኝነት ስለሆነ ነው፡፡ በባክቴሪያው የተለከፉ ቁንጮች ሰው በሚነክሱበት ጊዜ ባክቴሪያውን ወደ ሰውነት ሰለሚያዘልቁት ሰዎች በባክቴሪያው ይለከፋሉ፡፡ በዚህ በመጀመሪያ ደረጃ መለከፍ፣ ሰዎች ከሁለት አስከ ስድስት ቀን ባሉት ጊዜያት ህመም ምልክት ይጀመራቸዋል፡፡ ያም ከፍተኛ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ራስ ምታት የድካም ስሜት መሰማትና በሰውነት የሚገኙ ዕጢዎች ማበጥ ጋር ነው፡፡

ቶሎ ህክምና ካልተደረገ በሽታው ከዕጢዎች ተነስቶ በመላ ሰውነት ይሠራጭና ሰውነትን የመመረዝ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ይህ ሁኔታ በእንግሊዝኛ (Septicemic Plague) ይባላል፡፡ ማለትም ባክቴሪያው በደም ዝውውር ውስጥ ሲገባና በየቦታው መሠራጨት ሲጀመር ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች፣ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ከፍተኛ የሰውነት ድካም፣ የሆድ ህመም፣ በቆዳና በሰውነት ክፍሎች የመድማት ሁኔታና ሲከፋ ደግሞ ሾክ ውስጥ መግባት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በበሽታው የተለከፉ ሌሎች እንስሳቶችን በመነካካትም ይመጣል፡፡

ሽታው ቶሎ ህክምና ካልተደረገለት፣ ባክቴሪያው ወደ ሳንባ ይዘልቅና የሳንባ ምች ያስከትላል፡፡ በዚህ ደረጃም ሰዎች፣ ትኩሰት ብርድ ብርድ ማለት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ ትንፈሽ እጥር እጥር ማለት፣ የደረት ህመም፣ ሳል ይጀምራል፡፡ እየከፋ ሲሄድ ደግሞ ሾክና ጠቅላላ መተንፈስ አለመቻል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በሚሰሉበት ጊዜም አክታው ደም ሊኖረው ይችላል፡፡ አንግዲህ ሰዎች በሚስሉበት ጊዜ በአይን መታይት በማይችሉ ጠብታዎች አማካኝነት ባክቴሪያው ወደ ሌሎች ባካባቢ ወዳሉ ሰዎች ይሻገራል፡፡ ይህ አይነቱ ፕሌግ ነው እንግዲህ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው፡፡ በትነፋሽ አማካኝነት በበሽታው የሚለከፉ ሰዎች ቀጥታ የሳንባ ምች አይነቱ ነው የሚከሰትባቸው፡፡ ይህ ደግሞ በአብዛኛው ጊዜ ከሁለት እስከ አራት ቀናት ባሉት ጊዚያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡

ፕሌግን በመድሐኒት ማከም ይችላል፡፡ ሆኖም ህክምናው ቶሎ ካልተደረገ በሽታው የከፋ የሚሆንና ለህይወት ማለፍም የሚዳርግ ይሆናል፡፡

ዋናው ጥያቄ እንዴት መከላከል ይቻላል ነው

ክትባት የለውም ነገር ግን ሰዎች በግላቸው ማድረግ የሚችሏቸው ነገሮች አሉ፡፡

በቁንጫ ላለመነከስ አስፈላጊ ተባይ መከላከያ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የሚጠቀሙት መከላከያ ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

በበሽታው የተለከፉ ወይም በበሽታው የሞቱ እንስሳትን ከመነካካት መቆጠብ

በበሽታው ከተለከፉና በጠና ከታመሙና ሳል ከሚስሉ ሰዎች ጋር ቅርበት ከማድረግ ይቆጠቡ

በሽታው አለበት ወደሚባል ቦታ ተጉዘው ከሆነ ደግሞ እናም በበሽታው ከተለከፉ ሰዎችና እንስሳት ጋራ ንክኪ ካላቸው፣ ለሀኪም ወዲያውኑ መንገር ይኖርባቸዋል፡፡ በሽታው ባይዛቸውም እንኳን ሰለተጋለጡ ብቻ በሽታው እንዳይነሳ ለማድረግ የመከላከያ ፀረ ህዋስ(antibiotics)  መድሀኒቶች መውሰድ ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ወደ ማደጋሰካር የሚጓዙ ወይም ተጉዘው ከሆነ ይህንን ምክር ልብ ይበሉ፡፡

በሽታው አለበት በሚባለው ቦታ፣ እንስሳትነ ከመነካካት ይቆጠቡ፡፡ በመኖርያ ቦታዎ ወይም በስራ ቦታዎ እንስሳቶቹ ነካክተውት ወይም ታክከውት ሊሆኑ የሚችል ነገሮችን ከመነካካት ይቆጠቡ፡፡ የግድ መንካት ካለበዎት ጓንት ማድረግ ይኖርብዎታል፡፡

ውሻ ወይም ድመት ካለዎት ደግሞ ቁንጫ እንዳይራቸው መከላከያ መርጨት፣ በተጨማሪም እንስሳቶችዎችን ልቅ ከመስደድ ይቆጠቡ፡፡

መልካም ንባብ

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History