​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

ሌሎችም ቫይረሶች ዝርያ በመፍጠር ይታወቃሉ  01/10/2021
የተረሳ የሚመስለው የኤችአይቪ ዝርያዎች


 
የቫይረስ ዝርያዎች ሲነሳ በተለይም በአሁኑ በ2020ና 2021 አብዛኛው ሰው ሰለ ኮሮና አዲስ ተከሰቱ ስለተባሉት የእንግሊዝ አገርና (አሁን የእንግሊዝ አትበሉ እየተባልን ነው) የደቡብ አፍሪካ ዝርያዎች ነው የሚያስታውሰው፡፡ ለምናልባት፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት አለምን ውጥር አድረጎ፣ አንደዚሀኛው የሥራ ቦታ ባያዘጋም ጭንቀት የፈጠረ ቫይረስ ነበር፡፡ ይህም ኤች አይ ቪ (HIV) ነው፡፡

ታዲያ የዝርያ ነገር ከተነሳ፣ ኤች አይ ቪ (HIV) የተለያዩ ዝርያዎች እንዳፈራ፣ አንዳንዴም እነዚህ በየጊዜው የሚከሰቱ አዳዲስ ዝርያዎች ምርመራና ህክምና ላይ ጥያቄ እያስነሱ መሆናቸው ቢታወቅ መልካም ነው፡፡ ለሁሉም ቫይረሶች አዲስ ዝርያዎች መፈጠር፣ ከመራባት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መራባት ደግሞ ከሥርጭት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሥርጭት ደግሞ ከሰው ባህሪ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኤች አይ ቪ (HIV) ና ዝርያዎቹን የማጋራችሁ፣ አዲስ ቫይረስ በመጣ ቁጥር ሌላ ትርጉም የሚሠጡ ሰዎች መኖራቸውንም በመገንዘብ ነው፡፡ የተፈጥሮን ባህሪ ዞር ብለው፣ ሰፋ አድርገው ቢመለከቱ፣ ሰውና ቫይረሶች አብረው መኖር የጀመሩበትን ጊዜ የሚያውቅ የለም፡፡ በሽታ ሲያስከትሉና በምርመራ ሲገኙ ነው በይፋ የሚታወቁት፡፡

ወደ ኤች አይ ቪ (HIV) ስንመለስ፣ ይህ ቫይረሰ አንድ ወጥ አይደለም፡፡ የራሱ ክፍፍሎች አሉት፡፡ የቫይረሱ የተለያዩ ዝርያዎች፣ በአለም ዙርያ ተሠራጭተው ቢገኙም፣ አንዳንድ ዝርያዎች በአንድ አካባቢ ደመቅና ጎላ ብለው በመገኘት በሽታ በማስከተል ይታወቃሉ፡፡

ወደ ዘር ቆጠራ እንሂድና፣ በመጀመሪያ ኤች አይ ቪ (HIV) ሁለት ትልልቅ ዝርያዎች እንዳሉት አንመልከት፡፡ እነሱም፣ ኤች አይ ቪ (HIV-1ና፣ ኤች አይ ቪ (HIV-2)፡፡

ሰፋ ያለውን ወይም ድርሻ የሚይዘው ኤች አይ ቪ-1 (HIV-1) በመሆኑ ፣ መጀመሪያ ስለ ኤች አይ ቪ-2 (HIV-2) እንነጋገር፡፡ ይህ ቫይረስ የሚገኘው በምዕራባዊ የአፍሪካ ክፍሎች ነው፡፡ ከዚያ አካባቢ ወጣ በማለት በተለያዩ የአለም ክፍሎች በጣም አነስተኛ በሆነ ደረጃ ይገኛል፡፡ ያም በአብዛኛው ከዚያ አካባቢ በመጡ ሰዎችና ከነሱ ጋር ግንኙነት ባለቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በኢንዲያ፡፡ አንድ የሚታወቅበት ባሕሪ እንደሌላው እንደወንድሙ ኤች አይ ቪ-1 (HIV-1) የከፋ በሽታ አያስከትልም፡፡ አንደገናም ሥርጭት ላይ፣ ከወንድምዬው ከኤች አይ ቪ-1 (HIV-1) በጣም ባነሰ ደረጃ ነው የሚሠራጨው፡፡ በነበረው ግምት በምዕራባዊ የአፍሪካ ክፍል እሰከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ነው የሚገለፀው፡፡ ሆኖም በዚህ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያነሰ ነው የሚሄደው፡፡ መተላለፊያ መንገድ በሁለቱም በኩል ልዩነት የለም፡፡ በሽታ ሲነሳ፣ ኤች አይ ቪ-2 (HIV-2) በጣም አዝግሞ ሰለሚሄድ፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የበሽታ ሰሜትና ምልክት ሳያሳዩ ለብዙ አመታት መቆየት እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ ወደ ኤይድስ ደረጃ በጣም ዘግይቶ ነው የሚሻገረው፡፡ ኤይድስ (AIDS) ማለት፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከጊዜ በኋላ የሰውነት የውስጥ መከላከያ አቅማቸው በመድከሙ ምክንያት የበሽታ ምልክት ሲታይባቸው ነው፡፡ መቼም ብዙ ሰው ይህን ልዩነት ያውቃል ብየ ብገምትም ማብራራት አለብኝ፡፡ በኤች አይ ቪ (HIV) በመያዝ ኤይድስ (AIDS) ደረጃ ሳይደረሱ ህክምና ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ አሁን እንዲያውም ምርመራዎች እንደልብ በየቦታው ሰላሉ፣ በኤች አይ ቪ (HIV) የተያዙ ሰዎች ገና የበሽታ ምልክት ሳይታይባቸው ወይም ኤይድስ (AIDS) ደረጃ ሳይደርሱ ማግኘት ይቻላል፡፡ ሰለዚህ በቫይረሱ መያዝ አንድ ደረጃ ሲሆን፣ ኤይድስ (AIDS) ደረጃ መድረስ ሌላ ሁኔታ ነው፡፡ ኤች አይ ቪ (HIV) ያለበት ሰው ሁሉ ኤይድስ (AIDS) አለበት ማለት አይደለም፡፡ እንግዲህ ኤች አይ ቪ-2 (HIV-2) አዝግሞ ሰለሚሄድ፣ ቫይረሱ የሚያጠቃቸው ነጭ የደም ሴል ክፍል የሆኑት፣ CD4 የሚባሉ ሴሎች ቁጥር በዚህ በኤች አይ ቪ-2 (HIV-2) በተያዙ ሰዎች ላይ ሲለኩ መጠናቸው በአብዛኛው ከፍ ብሎ ነው የሚገኘው፡፡ በነገራችን ላይ፣ የነዚህ ሴሎች ቁጥር በጣም በአነስተኛ ደረጃ መገኘት ነው ወደ ኤይድስ ደረጃ የሚወስደው፡፡ በአሃዝ ለመግለፅ የነዚህ ሴሎች ቁጥር ከ200 በታች ከሆነ፣ አሁን ባለው የአጠራር ወይም ስያሜ ደረጃ ኤይድስ ይባላል፡፡

በምርመራ ሲመጣ፣ አሁን ያሉ መመርመሪያዎች፣ ኤች አይ ቪ-2 (HIV-2) መኖሩን ወይም አለመኖሩን ያሳውቃሉ፡፡ በአሜሪካ የምናየው ችግር፣ በሥራ ላይ፤ የዚህን ኤች አይ ቪ-2 (HIV-2) መጠን በቁጥር ለመለካት ብዙ መመርመሪያዎች የሉም፡፡ ቢኖሩም በምርምር ቦታዎች ነው፡፡ የንግድ ላቦራቶሪዎች፣ ይህ ቫይረስ በብዛት አለመኖሩን ሰለሚያውቁ፣ ትርፍ የለውም በማለት ይመስላል፣ ምርመራውን አያካሂዱም፡፡

ወደ መድሐኒቶች ስንመጣ፣ ለኤች አይ ቪ (HIV) ከሚውሉ መድሐኒቶች መሀከል፣ ከአንድ ወገን የሚመደቡ መድሐኒቶች በዚህ ቫይረስ ማለትም ኤች አይ ቪ-2 (HIV-2) ሰለማይሰሩ አንጠቅምባቸውም፡፡ ከዚህ በላይ ብዙም ተጨማሪ ማብራሪያ ሰለማያሰፈልገው ወደ ሌላኛው ቫይረስ እንሂድ፡፡

ኤች አይ ቪ-1 (HIV-1)

ይህ ቫይረስ፣ አለምን በስፋት ወጥሮ የያዘ ሲሆን፣ እሱ ብቻውን በአራት ክፍሎች የተከፈለ ነው፡፡ ክፍሎቹ በእንግሊዝኛ ፊደላት ነው የሚጠሩት፡፡

እነሱም፡ Group M, N, O and P ተብለው ይጠራሉ፡፡ የመጨረሻው Group P ዘግይቶ፣ ከምዕራብ አፍሪካ ወደ ፈረንሳይ አገር በተጓዘች መንገደኛ ላይ ነው የተገኘው፡፡ ከነዚህ መሀል Group M የተባለው በስፋት በአለም የተሠራጨው ቫይረስ ወገን በመሆኑ ለማስታወስ እንዲመች በማለት (M Major) በማለት እንጠራዋለን፡፡ ከነዚህ ከአራቱ ትልልቅ ክፍሎች ቀጥሎ ደግሞ፣ Group M በራሱ የራሱ ንዑስ ዝርያዎች(Sub types) አሉት፡፡ የዛሬ አራት አመት ስፅፍ፣ የንዑስ ዝርያዎች ብዛት አስር አካባቢ ነበር አሁን ግን እየጨመረ መጥቷል፡፡ ሥርጭቱና መራባቱ አስከቀጠለ ድረስ አዳዲስ ዝርያዎቸ መፈጠራቸው ይቀጥላል፡፡

Group M    – A  B  C  D  F  G  H  J  K  CRF

ችግር እየተፈጠረ ያለው፣ ከሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የ ኤች አይ ቪ (HIV) ቫይረሶች ሲገናኙ በመዳቀል የሚፈጥሯቸው አዳዲሰ ቫይረሶች ናቸው፡፡ እነዚህ በአንድ ወገን CRF (Circulating Recombinant Forms) ተብለው ይጠራሉ፤ እነሱም ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመረ ሰለሚሄድ አዳዲስ ሰሞች በየጊዜው ይታያሉ፡፡ ከሀያ በላይ እንዳሉም ይታወቃል፡፡ መለያቸው በ CRF ነው የሚጀምረው ከዛም ፊደል ቁጥር በመጨመር ከየትኛው የቫይረስ ንዑስ ምድብ እንደተነሱ ለማወቅ ይጠቀሙበታል፡፡፡፡ እዚህ ላይ አዲስ የሚከሰቱት የቫይረስ ዝርያዎቸ ባህሪያቸው በውል አይታወቅም፣ ከምርመራ ጀምሮ፣ ህክምና ላይና የበሽታ መጠንከር ላይ ምን እንደሆኑ ፈጥኖ ማወቅ አይቻልም፡፡ ዋናው ነገር፣ እነዚህ አዳዲስ ዝርያዎች እንዳይከሰቱ፣ የኤች አይ ቪ መተላለፊያ መንገዶችን በመገንዘብ፣ መከላከያዎችን በተግባር ማዋል ነው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ፣ አንድ ሰው ከአንድ ወይም ከሁለት በላይ በሆኑ የ ኤች አይ ቪ (HIV) ቫይረሶች ሊያዝ ይችላል፡፡ ድርብ ወይም ተደራራቢ ማለት ነው፡፡ ያ ሁኔታ ነው አንግዲህ፣ በመራባት ላይ አንዱ የቫይረስ ወገን ከሌላው ጋር በመዳቀል አዲስ ቫይረስ የሚወለደው፡፡ ይህ ሁኔታ ከ ኤች አይ ቪ (HIV) ቫይረሶች ውጭ በጣም አሳሳቢ ወይም አስከፊ ገፅታ አለው፡፡ በቀላሉ የሰው ኢንፍሉዌንዛ ቫይረሰ፣ ከሌሎች የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ፣ ማለትም ከአዕዋፍ ወይም ከአሳማ ዘር ጋር ተዳቅሎ ሌላ ምንነቱ ያልታወቀ አስከፊ ቫይረስ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ለዚህ ነው፣ የቫየረስ ሥርጭት ላይ ሁሉም ሰው ሊጠነቀቅ፣ ሊመክርና ሊያስተምር የሚገባው፡፡ እንደታየው ከሆነ፣ በአንድ የአለም ክፍል የታየ ቫይረስ ሳይውል ሳያድር አጠገባችን ድረስ ብቅ ይላል፡፡ ተላላፊ በሽታዎች የሌላ ሀገር ወይም የሌላ ሰው ችግር ብቻ አይደሉም፡፡ ከማንኛውም በበለጠ ጊዜ፣ በወቅቱ በሚታየው የኮሮና ቫይረስ ላይ ፈላስፋዎቸና ነቢዮች በዝተዋል፡፡ ድሮም ይኖሩ ይሆናል፡፡ አሁን ግን የሶሻል ሜዲያ መድረኩን ሰለሚያገኙ መሰማት ሰለጀመሩ ነው፡፡ ሰለ ኤችአይቪ ዝርያም ለማቅረብ የተገደድኩት፣ የቫይረሶችን የተፈጥሮ ባህሪ ለማስረዳት፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ መሆናቸውን ለመግለፅ ነው፡፡ እንግዳ ቫይረስ ከአራዊቶች ዘሎ ተሸግሮ ወደ ሰዎች በገባ ቁጥር፣ የአለም መጨረሻን መስበክ የሚጀምሩ ሰዎችም አሉ፡፡ ኤችአይቪም ቢሆን ከእንስሳት ዘሎ ወደ ሰው ገባ ነው የሚለው መላ ምቱ፡፡ ከተከሰተ አመታት አስቆጥሮ፣ አሁን ባለው ህክምና፣ መድሐኒት በደንብ ለሚውሰድ ሰዎች እምብዛም ችግር አልሆነም፡፡ የዕደሜ ጣሪያቸውም ከሌሎቹ ጋር በጣም እየተጠጋ ነው፡፡ እንደማንም ሰው፣ ተምረው፣ ሠርተው፣ አግብተው፣ ወልደው ይኖራሉ፡፡ ብቻ መድሐኒቱን ያለማሰለስ በትክክል መውሰድ ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡ መድሃኒቶቹም በየጊዜው በመሻሻል፣ በአሁኑ ጊዜ፣ በአብዛኛው በቀን አንድ እንክብል ብቻ ነው የሚወሰደው፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ፡፡ መድሐኒቱን በመውሰድ በደማቸው ውስጥ ያለውን የቫይረስ ዝውውር ከተቆጣጣሩ ወደ ሌላ ሰው የማያሳልፉ ወይም የማያሻግሩ መሆኑም ተረጋግጧል፡፡ የቀረው ጠርጎ ማዳን ብቻ ነው፡፡ ኤችአይቪ መጣ ሲባል የአለም መጨረሸ መጣ ብለው፣ መከላከያ መንገዶችን መተግበር ላይ እንቅፋት የነበሩ ሰዎችም ነበሩ፡፡ የአለም መጨረሻው የት ሄደ?

በ ኤች አይ ቪ (HIV) ቢሆን አንዳንድ ዝርያዎች፣ ቶሎ ወደ በሽታ የማሸጋገር ችሎታ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት አንዳንድ ንዑስ ቫይረሶች፣ በከፍተኛ ደረጃ የሚሠራጩባቸው የአለም ክፍሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከሰሃራ በታች በሚባሉ የአፍሪካ አገሮች፣ በጉልበት ርስቱን ይዞ በስፋት የሚሠራጨው ከ Group M ወገን የሆነው subtype or clade C የሚባለው ቫይረስ ነው፡፡ ተከሳሽ ቢሆን፣ ለብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ይህ ቫይረስ ነው፡፡ በአሜሪካ በኩል ደግሞ ለጊዜው ተቆጣጥሮ በስፋት የሚሠራጨው Group M ወገን የሆነው subtype or clade በ ቫይረስ ነው፡፡ አስካሁን ደጋግሞ የሚታወቀው ቁጥር፣ በአሜሪካ በኤይድስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ ማለት ነው ከእምስት መቶሺ በላይ ነው፡፡ አስተውሉ፣ በ2021 መጀመሪያ ላይ፣ በውል የሚታወቀው በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ስስት መቶ ሰባ ሺ ተሻግሯል፡፡ ስሌቱን ለናንተ እንተወው፡፡

መልካም ንባብ፣ ለሌሎችም አካፍሉ ሰለ ቫይረሶች ያለውን ግንዛቤ በመጨመር በተለይም በኮሮና ወይም ሰለኮሮና ቫይረሶች ያለውን የተሳሳተ አመለካካት ያስተካክላል ብዬ አምናለሁ፡፡