​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

የኤች አይ ቪ (HIV) መከላከያ ክትባት ተፈቅዷል በሚል የሚሠራጭ ሀሰተኛ ዜና

 ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ (የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ)​
07/31/2022


ይህንን ርእስ ከዚህ በፊት መጠነኛ ገለፃ ለመስጠት ሞክሬ፣ ነገር ግን በየጊዜው ለውጦች ሰለመጡ ፋታ ልስጥ ብይ ሰጠብቅ፣ አንድ ወዳጄ ከአዲስ አበባ የፌስ ቡክ ርዕስ ላከልኝና ሰመለከት በጣም አዘንኩኝ፡፡ የፌስ ቡክ ለጣፊው፣ ትንሽ በደንብ ቢያነቡ እንዲሕ አይነት መረጃም ባለጠፉ ነበር፡፡ ይህ ፖለቲካ አይደለም፣ ሳይንስ ነው፡፡ በኮቪድ በሀሰት የምንታመሰው ይበቃል፡፡ እናም፣ ጉዳዩን ላስተካክል ብዬ ይህን ፅሁፍ አቅርቤያሁ፡፡

ለምን ብላችሁ ብትጠይቁ

1ኛ. የኤች አይ ቪ (HIV) መከላከያ የሚባል ነገር ጭራሽ የለም፡፡ ቢኖርም ገና ጥናት ላይ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ተሞክረው ያልተሳኩ በርከት ያሉ ምርመሮች አሉ፡፡ ከዚህ እንጀመር፡፡ ይህ የሀሰት መረጃ ወይም ያላዋቂ ማለት ይቻላል፡፡ ሰዎችን ሊያዘነጋ ሰለሚችልም ነው በርግጠኝነት ውነቱ መነገር ያለበት፡፡

2ኛ. ሰዎች በኤች አይ ቪ (HIV) እንዳይያዙ የተለያዩ መከላከያ መንገዶች አሉ፡፡ በተግባር የሚሠሩ፣ እንደባለሙያ እኛም የምናዛቸው፡፡ ትንሽ ጨመር ለማድረግ፣ ሰዎች በኤች አይ ቪ (HIV) እንዳይያዙ ካሉ አቀራረቦች፡

የመጀመሪያው፣ በቫይረሱ እንዳያዙ የሚደረጉ በእንግሊዝኛ Pre exposure Prophylaxis (PrEP) የሚባለው አቀራረብ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ፣ አንድ ሰው አውቆም ሆነ ሳያውቅ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሚኖረው ከሆነ፣ ገና ከመጋለጡ በፊትና እየተጋለጠም መውሰድ የሚችለው መድሐኒት ነው፡፡ ከዚህ ቀድም፣ ይህ መከላከያ የሚደረገው፣ በቫይረሱ ላልተያዘ ሰው በየቀኑ የሚወሰድ መድሐኒት በመስጠት ነው፡፡ መጀመሪያ ትሩቫዳ የሚባል መድሐኒት፣ ከዛም ዴስኮቪ የሚባል መድሐኒት ተፈቅዶ አገልግሎት ላይ ከዋለ ቆይቷል፡፡ እኛም መድሐኒቱን እይሰጠን፣ ሰዎችን በመደበኛ ጊዜ እየተከታተልን ነው፡፡ ነገር ግን፣ በየቀኑ እንክብል መውሰዱን ሰዎችም ሰለተሰላቹ፣ በመርፌ መልክ የሚሠጥ መደሐኒት መመረት ተጀምሮ፣ ጥናቱ ተፈቅዶ አግልግሎት ላይ እየዋለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ክትባት አይደለም፡፡ በመሠረቱ ቫይረሱ ላላባቸው ሰዎች ከሚሰጡ መድሐኒቶች ሁለት ተመርጠው ለመከላከያ ብቻ እንዲሠጡ ነው የሚረገው፡፡

እነዚህ መድሐኒቶች በትክክል ከተወሰዱ ከቫይረሱ የመከላከል አቅማቸው 99 ፐርስንት ነው፡፡ በተጨማሪም፣ መድሐኒቱ ከመጀመሩ በፊት በቂ ምርመራና፣ ከዛም ደግሞ፣ መድሐኒቱ ሰዎች ላይ ጉዳት የማያደርስ መሆኑ ተረጋግጦ ነው የሚሠጠው፡፡

በማህበራዊ ሜድያ የተለቀቀው ግንዛቤ የጎደለው፣ ከዚህ በፊት ከተፈቀደ አመት ያለፈው በመርፌ መልክ ለኤችአይቪ መከላከያ የተፈቀ መድሐኒት ነው፡፡ መድሐኒቱ በመርፌ ሲሠጥ ፕሮቶኮል ተክትሎ ይጀመርና ከዛም በየሁለት ወሩ ይሠጣል፡፡ ይህንን የሚወስዱ ሰዎች ክኒኑን አይወሰዱም፡፡ እንግዲህ ይሕንን ነው፣ ክትባት ተፈቀደ ብለዎ የለጠፉት፡፡

ሌላው ነገር፣ እንዲህ አይነት ነገር ሲፈቀድ፣ የየሀገሩ የመድሐኒት መቆጣጠሪያ ማዕከሎች ጥናቱን አይተው ካረጋገጡ በኋላ ነው፡፡ እንጂ የአለም ጤና ድርጅት ከመሬት ተነስቶ መፍቀድም አይችልም፡፡ ሀገሮች መጠቀም ከጀመሩ በኋላ፣ በርግጥ በመመሪያ ወይም እንደ መመሪያ ውሳኔ ይሠጣል፡፡

ይህ በየሁለት ወሩ በመርፌ መልክ የሚሰጠው መድሐኒት Apretude (cabotegravir extended-release injectable suspension) ይባላል፡፡ አፕረቱድ፡፡ በመርፌ ውስጥ ሰውነት ከገባ በኋላ፣ ለሁለት ወራት መቆየት ሰለሚችል ነው፡፡ ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ሌላ መርፌ መደገም አለበት፡፡ ባጭሩ ረዥም ጊዜ ሰውነት ውስጥ መቆየት የሚችል መድሐኒት እንጂ ክትባት አይደለም፡፡ https://www.fda.gov/news-events/press-announcements/fda-approves-first-injectable-treatment-hiv-pre-exposure-prevention

እንግዲህ በአችአይቪ ላለመያዝ አንዱ ትልቅ ዘዴ ሆኖ የተገኘው፡፡ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች፣ መደሐኒቶቻቸውን በትክክል እይወሰዱ፣ ቫይረሱን በደማቸው ውስጥ በቁጥጥር ስር የሚያውሉ ከሆነ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በላቦራቶ የቫይረሱ ቁጥር ሲለካ፣ ላቦራቶሪው፣ ቫይረሱን መቁጠር አልቻልኩም የሚል መልስ ይሠጣል፣ እናም በአንግሊዝኛ Undetectable የሚባል ሪፖርት ይሠጣል፡፡ እነዚህ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች፣ ግን መድሐኒታቸውን በትክክል እይወሰዱ ቫይረሱን በቁጥጥር ሥር ካዋሉ፣ ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው እንደማያሰተላልፉ ካወቅን ከርመናል፡፡ ለዚህ ነው በአንግሊዝኛ (Undetectable = Untransmitabl U=U) የሚሉ ማስታወቂያዎችን የምታዩት፡፡ ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ ልንገራችሁ፡፡ ከሙያና ከተግባር በመነሳት፡፡

የኤች አይ ቪ ቫይረስ ያለባት ሴት፣ ስትፀንስ (እርግዝና)፣ ቀድመን የምናደርገው ነገር በሰውነቷ ውስጥ ያለው የቫይረስ መጠን ለማውረድና ለመቆጣጠር መደሐኒት እንጀምራለን፡፡ የሚሠጠው መድሐኒት፣ ለእርግዝና ተስማሚ የሆነ መደበኛ የኤች አይ ቪ መድሐኒት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሴትዮዋ ቫይረሱን ስለምትቆጣጠር፣ ሕፃኑ በቫይረሱ ሳይያዝ ይወለዳል፡፡ ክትትልም ተደርጎ ከአንድ አመት ተኩል በኋላ ከቫይረስ ነፃ የሆኑ ልጅ መሆኑ ይረጋገጣል፡፡ ይህ አሠራር ቆይቷል፡፡ በደንብ ይሠራል፡፡ የብዙ ሕፃናትን ሕይወት ታድጓል፡፡ በዚህ የምንረዳው፣ ኤች አይ ቪ ያላባቸው ሴቶች፣ ማርገዝና ልጅ መውለድ፣ ልጁም በቫይሩሰ እንዳይያዝ መደረግ እንደሚቻል ሲሆን፡፡

ሁለተኛው ነገር ደግሞ፣ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች፣ የተሠጣቸውን መድሐኒት በትክክል በመውሰድ፣ ቫይረሱን ከተቆጣጠሩ፣ እንኳንስ በግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ በማሕፀናቸው ውስጥ የነበረ፣ የነሱን ደም የሚጋራ ፅንስ በቫይረሱ እንዳይያዝ ማድረግ መቻላቸው ነው፡፡ ሰለዚህ ቫይረሱ ያለበት ሰው በሙሉ፣ በክትትል መድሐኒት እንዲወስድ ብሎም ቫይረሱን እንዲቆጣጠር ማድረግ፣ ቫይረሱ ያለበት ሰው ብቻ ሳይሆን፣ ጉደዩን የሚያውቅ፣ የትዳር ጓደኛን ጨምሮ ቤተሰብ ሰዎችን ማበራታት አለባቸው፡፡ የኤች አይ ቪ ቫይረስ በቁጥጥር ሥር ሲውል፣ የሚጨመረው የጤንነት መጠንና የዕድሜ ጣራ ከታወቀ ከርሟል፡፡ የቀረን ነገር ቢኖር ቫይረሱን ጠርጎ የሚያጠፋ ህክምና ነው፡፡ ከዚህም ከዚያ ከቫይረሱ ድነዋል የሚባሉ ሰዎች አሉ፡፡ ያ በጣም የተለየ ሁኔታ ለማንም በቫይረሱ ለተያዘ ሰው የማይሆን ነው፡፡ ወደፊት ይገለፃል፡፡

ወደ ኤች አይ ቪ መከላከያ ስንመለስ፣ ይህ አቀራረብ ብዙ ጊዜ የሚመከረው፣ የግብረሥጋ ግንኙነት ላይ በተወሰነ ደረጃ የማይቆጠቡና በተከታታይ የሚጋለጡ ሰዎች፤ በክንድ መርፌ በኩል አደንዛዥ የሚወስዱና ከሌሎች ጋር መርፌውን የሚጋሩ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ከማያወቁት ሠው ጋር የግብረሥጋ ግንኙነት ወይም ረዘም ያለ የአካል ግንኙነት ማድረግ፣ ኤች አይ ቪ ጨምሮ፣ አሁን እንደ አዲስ የሚሠራጨው ሞንኪ ፖክስ ቫይረስም ያገልጣል፡፡

መልክቱ ምንድነው፣ ተቆጠቡ ነወው፡፡ ትልቁ መከላከያ ይኸው ነው፡፡

ከመዝጋቴ በፊት፣ አንድ ሰው ሳያስበው ድንገት ለቫይረሱ ቢጋለጥ፣ ማድረግ የሚችለው ነገር ደግሞ ድህረ መጋለጥ መከላከያ የሚባል ነገር፡፡ ይህ እንግዲህ፣ ተጋላጩ በርግጠኛነት ለኤች አይ ቪ ከተጋለጠ በኋላ የሚደረግ ህክምና ነው፡፡ በእንግሊዝኛ Post Exposure Prophylaxis (PEP) ይባላል፡፡ ይህም በሥራ ላይ ያለ ነገር፡፡ ለምሳሌ በህክምና ቦታ ላይ፣ የጤና ባለሙያው ኤች አይ ቪ ያለበት ሰው ደም በነካው መርፌ ድንገት ቢወጋ በርግጥ ህክምና ካላደረገ በቫይረሱ ሊያዝ ይችላል፡፡ ይህ በሙያ በኩል የሚመጣው አደጋ Occupational Exposure የሚባል ሲሆን፣ ከሙያ ውጭ በሌላ መንገድ ተጋላጭ ሲሆኑ ደግሞ  non Occupational Exposure nPEP ይባላል፡፡ ለሁለቱም ተመሳሳይ አቀራረብ ነው፡፡ ዋናው ነገር መድሐኒት በሁለት ሰአታት ውስጥ መጀመር ነው፡፡ የሚሠጠው መድሐኒት መደበኛ የኤች አይ ቪ መድሒኒት ሲሆን፣ የሚወሰደውም ለአንድ ወር ብቻ ነው፡፡ በርግጥ አስፈላጊ መርመራዎች ይደረጋሉ፣ ክትትልም ይደረጋል፡፡ ዋናው ነገር፣ ተጋላጩ ከዚህ በፊት በኤች አይ ቪ አለመያዙ መረጋገጥ አለበት፡፡ ምንም እንኳን መድሐኒቱ ቶሎ መጀመር ቢኖርበትም፣ ዘግየት ብለው 72 ሰአታት ወይም በሶስት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ተመርምረው መድሐኒት መውሰድ ይችላሉ፡፡ ይህንን አቀራረብ፣ መንገደኞች ወይም ወጣ ወጣ የሚሉ ሰዎች ማስተዋል አለባቸው፡፡ በመጠጥ ሞቅታና በጓደኛ ግፊት ሊጋለጡ ሰለሚችሉ፣ ድምፅን አፍኖ ቀን ከመቁጠር፣ መጋለጣቸውን ካወቁበት ሰአታት ጀምሮ፣ ወድ ህክምና ዘልቆ፣ የአንድ ወር መድሐኒት ወሰድ መገላገሉ ታላቅ እፎይታ ነው፡፡ የአንድ ቀን ስህተት በህይታቸው ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ መረደት ጥሩ ነው፡፡ በተለይም የትዳር ጓደኛ፣ ዕጮኛ፣ ወዘተ ላላቸው ሰዎች፣ ይህን መከላከያ በሰአቱ ማድረግ፣ በነሱ ምክንያት ሌላ ሰው እንዳይያዝ ሰለሚያደረጉ ሌላው ቢቀር ከህሊና እስረኝነት ነፃ ያወጣቸዋል፡፡

አመሰግናለሁ

አካፍሉ