ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

ምርመራ

ሐኪሞች በሽታው በብዛት ባለበት አካባቢ በሽተኞች በሚነግሩዋቸው ምልክቶችና ስሜቶ በመነሳት በሽተኛው በጃርዲያ መለከፉን መጠርጠር ይችላሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን የሠገራ ምርመራ በማድረግ በአይነምድር ውስጥ ተባዪን በማየት ወይም በማግኘት ሲሆን፡፡ በተጠናከረ መንገድ ተባዪን ለማየት በተለያዩ ቀናት አይነምድርን መመርመር ይረዳል፡፡ ይህም በሽተኞች አንዳንድ ጊዜ ተባዩን በአይነምድራቸው አልፎ አልፎ ስለሚያስወጡ ነው፡፡
ተባዪን በማይክሮስኮፕ ከማየት የተሻለ መንገድ ደግሞ አይነምድሩ ላይ ኢሚዩኖአሴይ የተባሉ ምርመራዎችን ማድረግ ነው፡፡
በአሜሪካ ከዚህ በተጨማሪ በደም በኩል የሚደረግ ምርመራም ይደረጋል፡፡

 ሕክምና

የተለያዩ መድሓኒቶች ለዚህ በሽታ አገልገሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በአገር ቤት ስሙ ሚዝል ተብሎ የሚጠራው ሜትሮናይደዞልን (metronidazole) ጨምሮ ቲኒዳዞል (tinidazole) ፤ ኒታዞክሳናይድ(nitazoxanide) ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት በሽታውን በደንብ የማከም ችሎታ አላቸው፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ ፓሮሞማይሲን፤ ኩዊናክሪን እና ፉራዞሊዶን (paromomycin,quinacrine, and furazolidone) የተባሉ በተቀያሪነት አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ መድሃኒቶች እንደ ሀገሩ ሊኖሩም ላይኖሩም ይችላሉ፡፡ለማንኛውም እነዚህን መድሀኒቶች ከሀኪምዎ ጋር በመካከር የሚታዘዙ መሆናቸውን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

በሽታውን መከላከል 

አንግዲህ ወደ አፍ የሚገባ መጠጥና ምግብ በበሽታው ከተለከፉ ሰዎች በሚወጣው አይነምድር አማካኝነት መበከል ስለሆነ የመፀዳጃ ቤቶች መሠራት ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ ይህ በሁሉም ህብረተሰብ መደገፍ የሚገባው ነገር ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በግል መደረግ የሚገባቸው ነገሮች ቢኖር
የግል ንፅሕናን መጠበቅ
ያልተጣራን ውሃ በተለይም የመዝናኛ ቦታዎች ውሃን አለመጠጣት
በተባዩ ሊለከፉ የሚችሉ ምግቦች አለመመገብ
በግብረመሠል ፆታ ግንኙነት ጊዜ በተባዩ ከተለከፉ ሰዎች ጋር ግንኙነት አለማድረግን ይጨምራል፡፡

የግልንፅሕናን በሚመለከት ዋናው ተግባር እጅ መታጠብ ነው፡፡ እጅን በሳሙና በደንብ አድርጎ ለሀያ ሰከንዶች መታጠብ፡፡ ይህም ምግብ ከማዘጋጀት በፊትና ምግብ ከማቅረብ በፊት፡፡ ከመመገብዎ አስቀድሞ፤ የታመመን ሰው ከመንካትዎ በፊትና ከነኩ በሁዋላ፤ ከተፀዳዱ በሁዋላ፤ የተፀዳዳ ህፃንን ከነኩ ወይም ልብስ ከቀየሩ በሁዋላ፤ የሚጣሉ ቆሻሻዎችን ከነኩ በሁዋላ፡፡ ልጆችዎንም ሆነ ሌሎች ልጆችን እንዲታጠቡ ማሰተማርና ማገዝ፡፡

በአጠቃላይ እርስዎ ወይ ልጅዎ በበሽታው ከተለከፈ መዋኛ ቦታዎችን ኩሬና ወንዞች ውስጥ ከመዋኘት መቆጠብ ሌሎች እንዳይያዙ ይረዳል፡፡ የታመመ ልጅ ካለም እስከሚድን ድረስ ትምህርት ቤት እንዳይሄድ ማድረግ በተለይ መዋዕለ ሕፃናት፡፡

መዋኛ ቦታዎችና ኩሬ ወይም ወንዞች ከዋኙ ውሃውን ላለመጠጣት ይሞክሩ፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው በሽታው በብዛት ወደሚገኝባቸው ክፍለ አለማት ኢትዮጵያን ጨምሮ የሚጓዙ ከሆነ የሚጠጡትን ውሃ በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብዎታል፡፡
የታሽገ ውሀ መጠጣት
ከቡዋንብዋ ውሀ የሚጠጡ ከሆነ ለአንድ ደቂቃ በማፍላት መጠቀም፡፡

ፊልተር የሚጠቀሙ ከሆነ ደግሞ ለዚሁ ጉዳይ የተፈተነ ወይም የተፈቀደ አይነት መጠቀም ተገቢ ነው፡፡

ሌሎች ጥንቃቄ መደረግ የሚገባቸው ነገሮች ቢኖሩ በበሽታው የተለከፈ ሰው ወይም ህፃን አይነምድር ያረፈባቸውን እቃዎች መጫወቻዎችን ጨምሮ ጓንት በመልበስ በተገቢ ማጠቢያ ማጠብ፡፡ በጨርቅ የተሠሩ ቁሳቁሶች እንደሶፋ የመሳሰሉትን ደግሞ በእንፋሎት ማጠብ ተገቢ ነው፡፡ ማንም ሰው መያዝ ሰለሚችል ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ በግልዎ ማድረግ የሚገባዎትን ማድረግና ማሰተማር ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ድረ ገፅ ሁልጊዜ እንደምንጠቅሰው ተላላፊ በሽታዎች የግለሰብ ችግር ብቻ አይደሉም፡፡

ጃርዲያ (Giardia)

ጃርዲያ (Giardia) በአይን የማይታይ ጥገኛ ተባይ ሲሆን የሚያሰከትለው የተቅማጥ በሽታ ደግሞ ጃርዲያሲሰ ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ተባይ በየቦታው ሊገኝ ይችላል ማለትም በዚህ በሽታ የተለከፉ ሰዎች አይነ ምድር ወይም ሠገራ በተነካካ ቦታ አፈር ላይ፤ ምግብ፤ ውሀ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ተባይ በተፈጥሮው ራሱን የሚከልልበት ሽፋን ስላለው ሳየጎዳ ለረጅም ጊዜ በአንድ ቦታ መቆየት ከመቻሉ በላይ በክሎሪንና በሌሎችም ማፅጃ ኬሚካሎችን የመቋቋም ችሎታ አለው፡፡

ጃርዲያ በሽታ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰት በሽታ ነው፡፡ በታዳጊ አገሮች 2 ከመቶ የሚሆኑ አዋቂዎችን የሚለክፍ ሲሆን በልጆች ደግሞ የልክፍቱ መጠን ከ6 እሰከ 8 በመቶ ይደርሳል፡፡ በዚሁ በታዳጊ አገሮች ከጠቅላላው ህዝብ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው በጃርዲያ ተለክፎ ያውቃል፡፡ ይህ በሽታ ግን በታዳጊ አገሮች ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም፡፡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በአሜሪካ ሰዎችን በማጥቃት ከሚታወቁ የአንጀት ጥገኛ ተባዮች ጃርዲያ የመጀመሪያ ደረጃን ይዟል፡፡
ሰዎች በጃርዲያ የሚለከፉት በተበከለ ውሃና ምግብ ውስጥ የሚገኘውን በራሱ ሽፋን ውስጥ የተደበቀውን ተባይ በሚውጡበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ተባይ በማይክሮሰኮፕ አንጂ በአይን እንደማይታይ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ በዚህ በሽታ ለመለከፍ ከአስር ያልበለጡ በሽፋን ውስጥ ያሉ ተባዮች በአፍ በኩል ወደ ሰውነት ሲገቡ ነው፡፡ በበሽታው የተለከፈው ሰው ደግሞ በአይነ ምድር አማካኝነት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ተባዮችን እንደሚፀዳዳ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ለወራት ሊቆይ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ እንግዲህ ተባዩ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከእንስሳት ወደ ሰው በሌላ በኩል ደግም በአፍ በሚደረግ የግብረ ስጋ ግንኙነት አማካኝነት እንደሚተላለፍም ይታወቃል፡፡

 የበሽታው ስሜትና ምልክቶች


ስሜትና ምልክቶች የሚጀምሩት ሰዎች በተባዩ ከተለከፉ ከአንድ አስከ ሶሰት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

ማንም ሰው በጃርዲያ መለክፍ የሚችል ሲሆን በተለይ በዚህ ተባይ ለመለከፍ ከፍተኛ ሁኔታ ላዩ ያሉ ሰዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡፡

ጃርዲያ በብዛት ወደሚገኝባቸው የአለም ክፍሎች የሚጓዙ መንገደኞች

መዋዕለ ሕፃናት ቦታ የሚሠሩ ሰዎች

በጃርዲያ ከተከለፈ ሰው ጋራ በቅርበት ወይም አብረው የሚኖሩ ሰዎች

በጃርዲያ የተለከፈን ውሃ የሚጠጡ ሰዎች

ካምፕና ጫካ መውጣት የሚወዱ ሰዎች ከወንዝ ወይም ከኩሬ ወይም ከሀይቅ ውሃ የሚጠጡ ሰዎች

በበሽታው ከተለከፉ እንስሳት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች

ግብረ መሠል ፆታ ግንኙነት የሚየደርጉ ሰዎች

ከድመትና ከውሾች ወደ ሰው የመተላለፍ እድሉ መጠነኛ ነው ምክንያቱም ድመትና ውሾችን የሚያጠቃው የጃርዲያ ዝርያ የተለየ በመሆኑ ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች በተባዩ ቢለከፉም የበሽታ ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ፡፡

 አንዳንድ ጊዜ የበሽታው ስሜትና ምልክቶች ረገብ ያሉ ይመስላሉ ሆኖም ከሳምንታት በሁዋላ ተመልሶ የመምጣት ሁኔታ ያሳያሉ፡፡ ይህ በሽታ በቅማጡ ምክንያት የክብደት መቀነስ ከዚህም ተያይዞ አንጀት ጠቃሚ የምግብ ክፍሎች እንደ ቫይታሚን ኤ ና ቢ12፤ ጮማና ላክቶስ ወደሰውነት እንዳይገቡ ያደርጋል፡፡ በልጆች ደግሞ ይህ በሽታ ሲከፋ የሰውነትና የአእምሮ እድገት መግታትን ያስከትላል፡፡