ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

ሸጌ የጠቡ ለት የሸሸህ እንደሆን
ሸጌ የዱላው ለት የሸሸህ እንደሆን
እንኩዋን ከንፈር ወዳጅ ጎረቤትም አንሆን

 የከንፈር ወዳጅ ሲነሳ ከንፈር ላይ በብዙ ሰዎች ላይ ብቅ ስለሚል መጠነኛ ሰለሆነ ቁስል ማቅረብ መርጠናል፡፡ መግቢያው ላይ የቀረበው ግጥም የሀገር ባህል ዜማ በመጫወት ታወቂ ከሆነችው ድምፃዊ ዘፈኖች ከአንደኛው የተወሰደ ነው፡፡
ይህ ከንፈር ላይ በአንድ ጎን ብቻ ብቅ የሚል በአብዛኛው ጊዜ በጣም መጠነኛ የሆነ ነው አንደአካባቢው ምቸ ወይም ገረፍታ ነው ተብሎ ይጠራል፡፡ ሆኖም ይህ ቁስል በውነቱ ሔረፕስ በተባለ ቫይረስ አማካኘነት የሚከሰት መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳልን፡፡ አንግዲህ በአማርኛ ለመግባበት እንዲመች ያው በእንግሊዘኛ አጠራሩ ሔርፒስ እያልን ብንቀጥል የሚሻል ይመስላል፡፡
በአሜሪካ ይህ ሔርፒስ ቁስል ከኤች አይ ቪ ባላነሰ መልክ ስሙ ሲከፋ ይታያል፡፡ ይህም የሚሆነው ቫይረሱ አንደአባለ ዘር በሽታዎች ሁሉ በግብረስጋ ግንኙነት ስለሚተላለፍ ነው፡፡ በሸታውን ወይም ቁስሉን የሚያመጣው ይህ ቫይረስ Herpes simplex ባጭሩ HSV ተብሎ ይጠራል፡፡ ቫይረሱ ሁለት አይነት ነው፡፡ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት (Type 1 and type 2) HSV-1 and HSV-2
ቁጥር አንድ በአፍና በክንፈር ላይ ለሚወጣው መቁሰል ምክንያት ሲሆን በሀገር ቤት ምች ወይም የገርፍታ ቁስል እነድምንለው ሁሉ በእንገሊዘኛ ለየት ያለ ስም ለምሳሌ የብርድ ቁስል (cold sore, fever blister) የትኩሰት ቁስልም ተብሎ ይጠራል፡፡
ቁጠር ሁለት ደግሞ በአባለዘር የስውነት ከፍል አካባቢዎች ለሚወጣው ቁስል ምክንያት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመተላለፍ ከፍተኛ ደረጃ አለው ማለትም በግብረስጋ ንክኪ፡፡ ቸግሩ አሁን በግብረሰጋ ግንኙነት ስም በአፍም የሚካሄዱ ሁኔታዎች ስላሉ ከአባለ ዘር ውጭ ሌላም ቦታ ሊታይ ይችላል፡፡ እነዚህ ሁለት ቫየረሶች በህብረተሰቡ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ ናቸው፡፡
ሔርፒስ ቁጥር አንድን ስርጭት ስንመለከት በአሜሪካ ብቻ ከ1999 – 2004 በተደረገ ጥናት 57.7% አሜረካውያን ቁጥር አንድ ያለባቸው መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በአጠቃላይ ከሁለት ሰው አንዱ ማለት ነው፡፡
ወደ ቁጥር ሁለት ስንመለስ በቅርብ የወጣ ዘገባ እንደሚያሳየው ማለትም ከ 2005 – 2008 በተደረገ ጥናት እድሜያቸው ከ 14 -19 እድሜ ክልል ባሉ ሰዎች ከ 6ስቱ በአነዱ ወየም በ 16.2 ከመቶ በሆኑት በቫይረሱ እንተለከፉ ይታወቃል፡፡ በዝርዝር ሲወጣ ደግሞ ሴቶች ከወንዶቸ በላይ 20.9በመቶ ወንዶቸ ደግሞ 11.5 በመቶ፣ በጥቁርና በነጮች ሲወዳደር ደግሞ በጥቁሮች 39.2 በመቶ፣ ነጮች ግን 12.3 በመቶው በቫይረሱ የተለከፉ መሆናቸው ተገልጦአል፡፡ National Health and Nutrition Examination Survey study performed between 2005 and 2008 by CDC.
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ከተደረጉ ጥናቶች ሁለቱን በማቅረብ ስናይ በፋክብሪካ ሠራተኞች እና በከተማ ውስጥ በተደረገ ጥናት የቁጥር ሁለት ሔርፒስ ቫይረስ መለከፍ ምልክት በከፍተኛ ደረጃ ማለትም በተለይ እድሜያቸው 25 አመት ድረስ ባሉ ሰዎች ላይ የታየ ሲሆን ከ25 አመት በሁዋላ 50 በመቶ በሚሆኑ ሰዎች ላይ እንደሚገኝ ነው የሚጠቁመው፡ ከሁለት ሰው አንዱ በቫይረሱ የተለከፉ መሆናቸውን ያሳያል ማለት ነው፡፡ እንደ ጥናቶ አቅራቢዎች በወጣቶች በከፍተኛ ደረጃ መታየት ከሚደረገው ከፍተኛ ያልተጠበቀ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ጋራ የተያያዘ ሊሆን እነደሚችል ነው፡፡

Sex Transm Dis. 2002 Mar;29(3):175-81. Herpes simplex virus type 2 seropositivity among urban adults in Africa: results from two cross-sectional surveys in Addis Ababa, Ethiopia. Mihret W, Rinke de Wit TF, Petros B, Mekonnen Y, Tsegaye A, Wolday D, Beyene A, Aklilu M, Sanders E, Fontanet AL.


በሌላም ጥናት እንዲሁ ሔርፒስ ቁጥር ሁለት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚገኝ ነው የሚያሳየው፡፡ በየትኛውም አለም ክፍል በሰዎች ላይ በከፍተኛ ደረጀ እነደሚኖር የሚገመተው ቫይረስ በተለይ ብዙ ያለተጠበቀ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ብዛት ካለቸው ሰዎች ጋራ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ቢገኝም አያሰገርምም ምክንያቱም በግብረ ሥጋ ንኪኪ ስለሚተላለፍ ነው፡፡
ወደ በሽታው ስንመለስ በተለይ ቁጥር ሁለት ላይ በማተኮር ነው፡፡ ከላይ እንደተገለፀው ግን በሚደረጉ የተለያዩ የግብረ ሥጋ ንኪኪዎች አማካኝነት ቁጥር ሁለት ድሮ ከሚታወቅበት የሰውነት ክልል ወጥቶ ሌላ ቦታ መታየት እንደሚቸል ነው፡፡


  • ስሜትና ምልክቶች


ብዙ ሰዎች በነዚህ ቫይረሶች በሚለከፉበት ጊዜ ምንም ምልክትና ስሜት ላይኖራቸው ይቸላል ካላቸውም ደግም በጣም ቀላል ስለሚሆን ሳይታወቅ ለረዥም ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች መቼ እንደተያዙ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ በሥራ ልምድ አንደሚታየው በሸታው በቁስል መልክ ብቅ ሲል በሁለት ጉዋደኛሞች መሀከል አንተ ነህ አንቺ ነሽ ያመጣኸው ያመጣሽው የሚል ንተርክ ሲሰነዘር እናያልን፡፡ ምልቶች በሚታዪበት ጊዜ ግን በአፍ በከንፈር ወይም በአባለ ዘር አካባቢ መጀመሪያ ቀላ ያሉ ከዛ ውሃ የቁዋጠሩ አንድ ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ሽፍታች በአንድ ላይ እጅብ ብለው ይወጣሉ፡፡ የተቁዋጠረው ፈሳሽ በራሱ ይፈረጥና ክፈት ቁስል ይፈጠራል፡፡ ይህ በራሱ ከ2 – 4 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ይድናሉ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ በሚሉበት ጊዜ አብሮ የሚከሰት ብርድ ብርድ ማለት፤ ራስ ምታት፤ ቁርጥማት እና የንፊፊት የዕጢዎች እብጠት ሊታይ ይችላል፡፡ እነዚህ ክፈት ቁስሎች የህመም ስሜት እናዳላቸውም ማወቅ ተገቢ ነው፡፡

በሴቶች የተመለከትን ከሆን ቁስሎቹ ከአባለዘር ጀምሮ ከወስጥ በማህፀን መግያ፤ በመቀመጫዎች አካባቢ፤ በፊንጢጣ ላይ ሊወጡ ይችላሉ፡፡ በነገራችን ላይ ቁጥር ሁለት (Genital Herpes) ተብሎም ይጠራል፡፡ በወንዶች ደግሞ በአባለዘር፣ በአባለዘር ፍሬ መያዣ፤ በመቀመጫ፤ በፊንጢጣ፤ በሽንት መሽኛ አስከ ሽንት ፊኛ ድረስ ሊዘልቅም ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሽንት በሚሸናበት ጊዜ ህምም ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ቁስሎቹ ቀጥታ የህመም ስሜት ሲኖረቸው በተጨማሪ ቁስሎ ሽሮ አስከሚድን ደርስ በአባለዘር አካባቢ ህመም ሰሜት ሊኖር እነደሚችል ማውቅ ተገቢ
የሔርፒስ ቁስሎቸ ሌላው ፀባይ ደግሞ ተመላልሶ መምጣት ነው፡፡ ቁስሉ አዲስ የወጣ ከሆን ቶሎ ተሎ የመመላለስ ባህሪ ሊያሳይ ይችላል በተለይ ለመጀመሪያዎቹ አምሰት አመታት፡፡ ይህ የመመላለስ ባህርይ (outbreak) ይባላል፡ በአማርኛ የሚስማማው ቃል ምናልባትም ግርሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ግረሻ ቁስሎች እንደመጀመሪያው ቁስል ላይበረቱና ቶሎ ሊከስሙ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ሌላው አብይ ነገር ቢኖር ይህ ባይረስ ከሰውነት ጨርሶ እንደማይጠፋ ማወቅ ነው ለዚህም ነው ግርሻ የሚኖረው፡፡
እንግዲህ እንደሚታወቀው በተለይ ከንፈር ላይ በአንድ በኩል ብቅ የሚለው ይህ መጠነኛ ቁስል እየተመላለሰ መምጣት ወይም ማገርሸት መቻሉ ነው፡፡ በሀገር ቤት ምግብ በልቼ ስወጣ ፀሀይ ምች መቶኝ ነው የወጣው ይባላል፡ ከፀሀይ ጨረር ጋራ ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ባይታወቅም ለግርሻ የሚተወቁ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነሱም

 ጭንቀት (መንፈስ ወይም የአዕምሮ)
 የሰውነት ድካም
 ሌላ ህመም
 ቀዶ ህክምና
 በወር አበባ 


  • መተላለፊያ መንገዶች


ዋናው መተላለፊያ መንገድ በቫይረሱ ከተለከፉ ሰዎች ጋራ በሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ነው፡፡ እንግዲህ ግብረሥጋ ግንኙነት ትርጉሙ ሰፋ እያለ በመምጣቱ የትኛው የሰውነት ክፍል በሚደረገው ንክኪ ምክንያት በሽታውን ማሰተላለፍ ወይም መለከፍ ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ቁስሉ በሚኖርበት ጊዜ የሚታለለፍ ቢሆንም በ ቁጥር ሁለት በተያዙ ሰዎች ግን ቁስል ባይታይባቸውም በገብረሥጋ ግንኙነት ጊዜ ማሰተላለፍ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡
በቁጥር አንድ ከላይ እንደተጠቀሰው በአፍና በከንፍር ላይ ለሚመጣው ቁስል ምክንያት ቢሆንም በአባለዘር የሰውነት ክፍል ሊከሰትም ይችላል በብዛት የሚተላለፈው ግን ቁስሉ በሚኖርበት ጊዜ ነው፡፡ ሌላው ችግር በዚህ በሽታ ምክንያት የኤች አይ ቪ ቫይረስ መሸጋገር በጠም ከፍ እንደሚል ነው፡፡ በሚፈጠረው ቁስል ምክንያት በሰውነት ላይ ክፍተት ስለሚፈጠር እነደ ኤች አይ ቪ የመሰለ ቫይረስ በቀላሉ ወደ ሰውነት ውስጥ መግባት ስለሚቸል ነው፡፡
የሔርፒስ ቫይረስ ከሰውነት ውጭ ከቆየ ቶሎ ስለሚሞት ከሰውነት ንክኪ ውጭ ቫይረሱን በነካ ዕቃ ወይም ቁሳቁስ በመጠቀም አይተላለፍም፡ ከምግብ በአፍ በኩልም አይተላለፍም፡፡

በቫይረሱ ለመለከፍ ከፍተኛ ሰበቦች ወይም ምክንያቶች ቢኖሩ

1. ሴቶች ከወንዶቸ በላይ በቫይረሱ በቀላሉ መለከፍ ይችላሉ፡ ከወንዶች ወደ ሴቶች በቀላሉ ስለሚተላለፍ ሴቶች በብዛት በዚህ ቫይረሰ ተለክፈው ይገኛሉ

2. ከብዙ ሰዎች ጋራ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚያዘወትሩ ሰዎች ደግሞ ለቫይረሱ የመጋለጥና የመለከፍ ዕድሉ ስለሚጨምር


ምርመራ

ሐኪምዎ ቁስሎችን በማየት ማወቅ የሚችሉት ነገር ነው፡፡ ሆኖም ተጨማሪ ምርመራ ካስፈለገ የተላየዩ መንገዶች አሉ

በጣም አስተማማኝ የሚሆነው ቁስሉ በወጣበት ጊዜ ከቁስሉ ላይ ፋሳሹን በመጥረግ

1. ለቫይረስ ካልቸር (Virus culture) ቫይረሱን በላቦራቶሪ በማሰደግ ለማወቅ

2. የቫይረሱን የዘር ሰንሰለት DNA በላቦራቶሪ ለመለየት በሚደረግ ምርመራ፣ ለዚህ ምርመራ ግን ማንኛው ቫይረሱ ሊኖርበት የሚችል የሰውነት ፈሳሽ ከደም ጀምሮ የህብለ ሠረሠር ፈሳሽን ጨምሮ ሊላክ ይቻላል፡፡

3. ከዚህ በፊት ለቫይረሱ የተጋለጡ መሆኑን ለማወቅ በደም ምርመራ የሚካሄድበሰውነት ውስጥ የቫይረሱ አንቲቦዲ መኖሩን ማወቅ ይችላል፡፡


  • ሕክምና


ወደሕክምና ከመሄዳችን በፊት የሔርፒስ በሽታ ሌሎች ከበድ ያሉ በሽታዎች ሊያሰከትል እንደሚችል ልናሰገነዘብ እንወዳለን

 በመጀመሪያ በፊንጢጣ አካባቢ ሰፋ ያለ ቁሰለት ያመጣል በተለይም በግብረ መሰል ፆታ ግንኙነት በሚደርጉ ወነዶች፡ የመከላከያ አቅማቸው በደከመ ሰዎች ኤች አይ ቪን ጨምሮ ከባድና ሰፊ ቁስል በዚህ አከባቢ ያመጣል፡፡
 ከሽንት ፊኛ ጋራ በተያያዘ የሸንት ማጥ ሊያሰከትል ይችላል፤ ውሰጥ በሚፈጠረው ቁሰለት ምክንያት ሽንት መውጣቱ ተደፍኖ በሀኪም እርዳታ በቱቦ እነዲሸና የሚደረግበት ሁኔታ እምብዛም አይሁን እንጂ ሊፈጠር ይችላል

  በአንጎል በሰረሰር ውስጥ በመግባት ደግሞ እነደማጅራት ገትር (Meningitis, encephalitis ) ወይም የአንጎል በሽታም ሊያመጣ ይችላል
 በአይንም ላይ በጣም የህመም ስሜት የሚፈጥር (Keratitis ) የተባለ በሽታ ያመጣል
 ሌላው አሳሳቢ ችግር ደግሞ በሽታው ካለባቸው ወላዶች በወሊድ ጊዜ ወደ አዲስ ወደ ተወለደው ህፃን ከተሸጋገረ ሕፃኑ ላይ(Nenonatal Herpes) የአንጎል ጉዳት፤ የአይነሰውርነት በተጨማሪም የሕይወት ማለፍም ሊያሰከትል ይችላል፡፡

ወደ ሕክምና ስንመለስ መታወቅ ያለባቸው ነገሮች አሉ አንደኛው ቁስሎች በአብዛኛው ጊዜ በራሳቸው እንደሚድኑ በመጀመሪያ ጊዜ የወጡ ከሆን እንደሚበረቱ በተከታታይ በግርሻ መልክ የሚወጡት ግን በብረታትም በቀን ርዝመት ሻል እንደሚሉ ማወቅ ነው፡፡

ሁለተኛው በገልፅ መታወቅ ያለበት ነገር መድሃኒቶች በሽታውን መቆጣጠርና ቶሎ እንዲድኑ ከመርዳት ውጭ ቫይረሱን ጠርገው አያጠፉም፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንግዲህ አንባብያን ሊረዱት የሚገባ ነገር ቢኖር አንኩዋንሰ ኤች አይ ቪ ይህንን ሔርፒስ ቫይረስ እንኩዋን ማዳን እንደማይቻል ነው፡፡

መድሃኒቶቹ በሽታውን ቶሎ እነዲድን በማድረግ የህምም ሰሜቱን መቀነስ፤ የበሸታ ቀኑን ማሰጠር፤ ቁስሉ ቶሎ ስለሚሽርም በቁስሉ ምክንያት ወደ ሌላ ሰው የመሸጋገሩን መጠን መቀነስ፤ በተጨማሪም የግርሻ ቁጥርን መቀነስ ያስችላሉ፡፡ ሀኪምዎ ቁስል በመጀመሪያ በታየበት ጊዜ ቢያንስ ቢያንስ ረዘም ላለ ጊዜ ወደ አስር ቀን ድረስ የሚሆን መድሃኒት ሊያዙልዎት ይችላሉ፡፡ ግርሻ ለሚያሰቸግራቸው ሰዎች በተለይም በአመት ከሰድሰት ጊዜ በላይ ለሚመላለስባቸው ሰዎች ግርሻውን ለመቀነስ በየቀኑ መድሃኒት እንዲወሰዱም የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች በእንክብል መልክ የሚዘጋጁ ሲሆን በሽታው ለሚበረታባቸው ሰዎች ደግሞ በክንድ መርፌ በኩል የሚሰጥ መድሃኒትም አለ፡፡ ቀለል ላለ ግርሻ ግን በአብዛኛው ለአምስት ቀናት የሚሆን መድሃኒት ይወሰዳል፡፡ መድሃኒት በሚታዘዘብት ጊዜ በትክክለ መጨረስ ተገቢ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ባይሆን ይህ ቫይረስ በየጊዜው ለሚታዘዙ መድሃኒቶች የመቁዋቁዋም ምልክት ሲፈጥር ይታያል፡፡

በብዛት የሚታወቁ ወይም የሚታዘዙ መድሃኒቶች የሚከተሉት ናቸው
Acyclovir (Zovirax) አሳይክሎቪር፤ Famciclovir (Famvir) ፋምሳይክሎቪር፤ Valacyclovir (Valtrex) ቫልትሪክስ ከዚህ በተጨማሪ በቅባት መልክ የሚዘጋጁ ቁስሉ ላይ የሚደረጉ ያለሀኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ መድሃኒቶችም አሉ፡፡ እነዚህ ቅባት መድሃኒቶች ሆነ በአፍ የሚወሰዱት ቁስሉ ወዲያው እነደጀመረ ቶሎ መውሰድ ፍጥነት ላለው መሻል ይረዳል፡፡

  • መከላከል

የአባለዘር በሽታ እንደመሆኑ መጠን ለሌች አባለዘር በሽታዎች የሚደረግ የመካለከልን ምክርን መከተል

ቁስሉ በወጣበት ጊዜ ከግብረ ሥጋ ግንኙነት መቆጠብ፤ አንድ ላንደ መወሰን፣ ኮንዶም መጠቀም

ግርሻ ሲኖርም እንዲሁ ከግብረሥጋ ግንኙነት መቆጠብ ያሰፈልጋል

በሔርፒስ ምክንያት ከመከላከል ተግባሮች ትልቅ ትኩረት ሊሠጠው የሚገባ ነገር አለ ይኸውም ነብሰጡር ሴቶች ማድረግ የሚገባቸው ነገር ነው፡፡ ነብሰጡር በሚሆኑበት ጊዜ ከዚህ በፊት የሔርፒስ ቁስል ታይቶብዎት ከሆነ ወይም ለሔርፒሰ ቁስል ህክምና ወስደው ከሆነ ለሀኪምዎ መንገር ያሰፈልጋል በተለይም ለወሊድ ሀኪም ወይም ባለሙያተኞች፡፡ ችግር የሚመጣው በእርግዝና ጊዜ ሳይሆን ልጅ በሚወለድበት ጊዜ በመውላጂያ ሳምነታት በማህፀን አካባቢ ቁስል ከተፈጠር ወደ የሚወለደው ልጅ በቀጥታ በንክኪ ስለሚተላለፍ አና ህፃኑ ከተለከፈም ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች የህይወት ማለፍን ጨምሮ ሊያሰከትል ስለሚችል ነው፡፡ አልፎ አልፎ ሔርፒስ ውርጃም ሊያሰከትል ይችላል፡፡

ስለዚህ በሽታው የሌለባቸው ነብሰጡሮች በሽታው እነዳይዛቸው ማድረግ የመጀመሪያው ተግባር ነው፡፤ የህ ደግሞ የትዳር ወይም የፍቅር ጉዋደኞችን ትብብርና እርዳታ ይጠይቃል፡፡ ድብብቆሽ አደገኛ ነው፡፡

ሀኪምዎ ሔርፒስ ያለብዎት መሆኑን ካወቁ በእርግዝና ጊዜ 36 ወር ጀምሮ አስከወሊድ ድረስ መድሃኒት በማዘዝ በወሊድ ጊዜ ቁስሉ እነዳይከሰት ከዚያም ወደ ልጁ እንዳይታላለፍ ለማድረግ

በምጥ ወይም ወሊድ ሲቃረብ ነብሰጡር ሴቶች ጥንቃቄ የተሞላበት የሰውነት ምርመራ በማድረግ በማህፀንና አካባቢ የሔርፒስ ቁስል ምልክቶች አለመኖራቸው ይረጋገጣል፡፡ ቁስል ከታየ ግን በተለይ በምጥ ጊዜ ህፃኑን ከመለከፍ ለማዳን በኦፐሬሽን (C-section) እነዲወለድ ይደረጋል፡፡

የሔርፒስ በሽታን ስርጨት ስንመለከት ከፍተኛ እነደመሆኑ መጠን(በኢትዮጵያና አካባቢዋ፣ በአሜሪካም) በተለይም በሴቶች ላይ እርግዝና በሚኖርበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግና ከላይ የተጠቀሱትን ምክሮች በመከተል የሚወለዱ ህፃናትን በዚህ በሽታ ከመለከፍ ማዳን ትልቅ ነገር ነው፡ ይህ ደግሞ የሴቶች ሀላፊነት ብቻ ሳይሆን የትዳር ጉዋደኛ ወንዶችንም ይጨምራል፡፡ ይህንን ምክር ከሌሎች ጋራ በማከፈል ዚህ በሽታ ግንዛቤ እነዲጨምር እንዲደርጉም በትህተና እንጠይቃለን፡፡