ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Athlete's Foot  ጭቅቅት ወይም ጫቆ (የእግር  ቆዳ ፈንገስ)
 
የፈንገስ በሽታ በቆዳ ላይ በየትኛውም የሰውነት ክፍል ሊከሰት ይችላል ሆኖም በእግር ላይ በአብዛኛው ጊዜ ይታያል፡፡ ይህም የሚሆነው ፈንገስ በተፈጥረው ሙቀትና እርጥበት ያለበት ቦታ ስለሚሰማማውና ስለሚያድግ ነው፡፡ እንግዲህ በእግር ላይ ሲከሰት በእንግሊዝና የህክምና አጠራር ቲኒያ ፔዲስ (Tinea Pedis) በተለምዶ ግን የሚጠራበት ቃል Athlete’s foot ይባላል፡፡ በአማርኛ ደግሞ ጭቅቅት ወይም ጫቆ ተብሎ ይታወቃል፡፡ ይህ ቃል በብዛት መታወቁን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ በብዛት ሚታየው በወንዶች ላይ ነው፡፡

ይህ የእግር ቆዳ በፈንገስ በሚያዝበት ጊዜ የሚያሳክክ የሚረግፍ በእግር በመረገጫ በኩል የሚታይ ሲሆን በእግር ጣቶች መሀከልም ይታያል፡፡ እየከፋ ሲሄድ ደግሞ በእግር ጣቶች መሀከል ውሃ መቁዋጠርና መሠንጠቅ ያሳያል፡፡ በተለይም በእግር ጣቶች መሀከል ነጭ የረጠበ ሲነኩት የሚረግፍ ሽፍታ ያሳያል፡፡ ይህ በብዛት የሚከሰተው ሙቀት በሚኖርበት ጊዜ ነው፡፡ አንዳንዴም ከመረገጫ በኩልና ከጣቶች መሃከል ካለው ቆዳ በተጨማሪ በእግር በላይኛው ቆዳ ላይ የሚያሳክክ ደረቅ የሚፈረፈር ምልክት ያሳያል የውሀ መቁዋጠር ምልክትም ይኖራል፡፡ ይህ በእግር ላይ የሚታየው ፈንገስ የቆዳ በሽታ ወደ ሌላ የሰውነት ክፍልና ወደ የእግር ጥፍሮችም ሊዛመት ይችላል፡፡ በፎቶግራፉ ላይ የሚታየው የእግር ጥፍሮች ላይ ፈንገስ ከተዛመተ በሁዋላ የሚያሳየው ምልክት ነው፡፡ ይህ በእግር ጥፍር ውስጥ የሚታየው በሽታ በህክምና አጠራር onychomycosis ተብሎ ይታወቃል፡፡ ይህ ፈንገስ በአካባቢያችን በብዛት የሚገኘው ሞቀትና እርጥበት ባሉባቸው ቦታዎች ነው ለምሳሌ ገላ መታጠቢያ ቤት፤ መዋኛ ቦታዎች፤ በተጨማሪም ሰፖርተኞች ልብስ የሚቀይሩባቸው ክፍሎች (Locker rooms) የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ወደ ህክምና ከመሄዳችን በፊት ይህንን ለመከላከል ምን ማድረግ ይቻላል?  ለዚህም የሚሰጡ ምክሮች

  • ·ባዶ እግር መሄድ ማቆም በተለይ ብዙ ሰዎች በሚያዘወትሩዋቸው ቦታዎች እንደ ሆቴሎች የመሳሰሉ ቦታዎች
  • ·         ከቤትዎ ውጭ ሻወር የሚወስዱ ከሆነ ጫማ ማድረግ
  • ·         ጫማዎችዎ ቀለል ያሉና አየር ማስገባት የሚችሉ ቢሆን
  • ·         እግርዎን በየቀኑ በሳሙና መታጠብ
  • ·         ሻወር ከወሰዱ ወይም እግርዎን ከታጠቡ በሁዋላ እግርዎን በተለይ በእግር ጣቶችዎ መሃከል በደንብ ማድረቅ፡፡ ለዚሁ ሲሉ የተለየ ፎጣ ማዘጋጀትም ይረዳል፡፡

·         ካልሲ ከማድረግዎ በፊት እግረዎ በደንብ ማድረቅ እግረዎን የሚያልብዎት ከሆነም ደግሞ ቢችሉ ካልሲ ቶሎ ቶሎ መቀየር ወይም ካልታጠበ በሰተቀር አለመድገም (የሚቻል ከሆነ)

ከላይ የተዘረዘሩት ምክሮች እነዳይያዙ የሚረዳዎት ሲሆን ተይዘውም የሚያውቁ ከሆን እንዳይመላለስብዎ ይረዳዎታል፡፡ መድሃኒት ብቻ መጠቀም ከመመላለስ ሊያሰጥልዎት አይችልም፡፡ ሰዎች መድሃኒት ከተጠቀሙ በሁዋላ ሲመለስ መድሃኒቱ ያልረዳቸው ይመስላቸዋል ችግሩ ግን ጥንቃቄ ባለማድረግ የተነሳ እንደገና ስለሚያዙ ነው፡፡

በእግር ጣቶች ላይ የመሰንጠቅ ወየም የመከፈት ሁኔታ ከፈንገስ ውጭ ሌላ ችግር ያስከትላል ይኸውም በተከፈተው ቦታ ባክቴሪያ በመግባት እግር ላይ የቆዳ ወይም ከበድ ያለ ከቆዳ ስር የሚገኙ የሰውነት ክፍሎችን የሚጨምር በሽታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የስኩዋር በሽተኞች ላይ ከበድ ያለ ችግር ያስከትላል፡፡


ህክምና
በአብዛናው ጊዜ ያለሀኪም ትዕዛዝ የሚገዙ በቅባትነት የሚዘጋጁ መድሃኒቶች አሉ፡፡ የሚጠቀሙ ከሆነም ለመድሃኒቱ አለርጂ የሌለብዎት መሆኑን ያረጋግጡ፡፡ መድሃኒቱን ከመጠቀምዎ በፊት እግረዎን በተለይም በእግር ጣትዎ መሀከል ያሉትን ቦታዎች በደንብ መታጠብና በደንብ ማድረቅ ከዚያም መድሃኒቱን መቀባት ከቀቡም በሁዋላ እጅዎን በሳሙና በደንብ መታጠብ፡፡ ሀኪምዎ ካልመከሩዎት በሰተቀር የተቀባውን ቦታ በምንም ነገር አለመሸፈን ይመረጣል፡፡ የመሻል ወይም የመዳን ምልክት ቢታይም መድሃኒቱ ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት ጥዋትና ማታ  መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

መድሃኒቶች በተለያየ እነደቅባት፤ የሚረጭ ነገር ወይም እንደ ዱቄት የሚነሰነሱ በሆነ መልክ ይገኛሉ፡፡ ያለሀኪም ፈቃድ የሚገኑ መድሃኒቶች እንደአሉበት ቦታ ስማቸው ሊለያይ ይችላል ከዚህ በታች ያለው ዝርዘር በአሜሪካ የሚገኙ ናቸው

  • ·         Butenafine (Lotrimin Ultra) ሎትሪሚን አልትራ
  • ·         Terbinafine (Lamisil AT)  ላሚሲል (ይህ በአፍ የሚዋጥ የእንክብል አይነትም አለው)
  • ·         Clotrimazole (Lotrimin AF) ሎትሪሚን
  • ·         Miconazole (Desenex,)
  • ·         Tolnaftate (Tinactin)


በሀኪም የሚታዘዙት መድሃኒቶች ከላይ የተጠቀሱት ሊሆኑ ይችላሉ ሆኖም በሀኪም የሚታዘዙት በጉልበት ጠንከር ያለ ደረጃ ያላቸው ይሆናሉ ብርታቱ የሚገለፀው በፐርሰንት ነው፡፡ እነግዲህ ራሰዎ ገዝተው ተጠቀምው ካላሻለዎት ሀኪምዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ይህ በሽታ በምስሉ እነደሚታየው ወደ እግር ጥፍሮች ከተዛመተ ግን በአፍ የሚወሰዱ መድሃኒቶች ሀኪምዎ ሊያዝልዎት ይችላሉ፡፡ ዋናው ነገር መድሃኒቱንም እየተጠቀሙ ከተሻለዎት በሁዋላም ከላይ የተዘረዘሩትን ምክሮች ማሰታወስና መከተል ጠቃሚ ነው፡፡