ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

ይህ በምስሉ የሚታየው እንስሳ አርማዲሎ (ዮ) ይባላል፡፡ ያለ ነገር አይደለም የተለጠፈው፡፡ በአማርኛ አጠራር ቁምጥና (Leprosy) ተብሎ የሚጠራ በሽታ አለ፡፡ የዚህ በሽታ ሥርጭት በአብዛኛው በታዳጊ በሚባሉ አገሮች ነው የሚገኘው፡፡ ይህንን በሽታ የሚያመጣው ባክቴሪያ ማይኮባክተሪየም ሌፕሬ ተብሎ ይጠራል፡፡ የሳንባ ነቀርሳ ከሚያመጣው ባክቴሪያ ጋር ቤተ ዘመድ ናቸው፡፡ በሽታው በነዚህ በታዳጊ አገሮች በሰዎች ላይ ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ የሚተላለፈውም በባክቴሪያው ከተለከፉ ሰዎች ጋር በጣም በቅርበት በመኖር፣ ንክኪን ጨምሮ ነው፡፡ በሽታው ያለባቸው ሰዎች ባክቴሪያው ከአፍንጫቸው በኩል በመውጣት ነው ሌሎቹን የሚያጋልጠው፡፡ አንዳንድ በሽተኞች ባክቴሪያን በብዛት በመሸከም ሊያሰተላልፉ ይችላሉ፡፡ ሁሉም የተጋለጠ ሰው በባክቴሪያው ተለክፎ በሽታው ሊከሰትበት አይችልም ምክንያቱም በዚህ ባክቴሪያ ለመለከፍና በበሽታው ለመያዝ በተፈጥሯቸው አመቺ ሆነው የሚገኙት አምስት ከመቶ(5%) የሚሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡

በአለማችን በሽታው በብዛት ከሚገኝባቸው አገሮች ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በአለም አዲስ ተለከፉ የሚባሉ ሰዎች ቁጥር ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆነው ሪፖርት የሚደረገው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአስራ አራት አገሮች ነው፡፡ እነሱም ባንግላዴሽ፣ ብራዚል፣ ኮት ዲቯር፣ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ማደጋስካር፣ ማይናማር፣ ኔፓል፣ ናይጄሪያ፣ ፊሊፒንስ፣ ሰሪላንካና ታንዛንያ ናቸው፡፡ ሆኖም ከነዚህ ውስጥ አብዛኛው 59 ከመቶ የሚሆነው ከህንድ ነው፡፡

በአደጉ አገሮች እንደ አሜሪካ (ዩናይትድ ሰቴትስ) ይህ በሽታ ብርቅ ቢሆንም በአንዳንድ ስቴቶች ሪፖርት ይደረጋል፤ ከነዚህ አንዱ ፍሎሪዳ የሚባል ስቴት ነው፡፡ በታዳጊ አገሮች፣ እንደተጠቀሰው የዚህ በሽታ ተሸካሚ ሰዎች ብቻ ሲሆኑ፣ በምዕራባዊ ክፍለ አለም ግን ከሰዎች በተጨማረ አንድ አንስሳ በዚህ ባክቴሪያ የተለከፈ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በ 2005 አም በተደረገ ምርምራ፣ ከአምስት ሺ በላይ የሚሆኑ አርማዲዮዎች በበሽታው መለከፋቸው ተረጋግጧል፡፡

በዘገባዎች መሠረት በአሜሪካ 70 በመቶ የሚሆኑት ይህ በሽታ የተገኘባቸው ሰዎች ውጭ ሀገር ቁምጥና ወይም ሌፕሮሲ ባሉባቸው አገሮች መኖራቸውን ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን የቀሩት ግን ሌላ በቂ ምክንያት አልተገኘባቸውም፡፡ ሆኖም ከዚህ ባለ ዘጠኝ ድርብ ሽፋን ካለው እንስሳ ጋር የመጋለጥ ሁኔታ እንዳለባቸው ነው የሚገመተው፡፡ ስለዚህ ቁምጥና ከዚህ አንሰሳ ወደ ሰዎች በመተላለፍ ሰዎች ላይ እንደሚከሰት ነው፡፡ በተጨማሪ በአሜሪካ ይህ በሽታ ተገኘባቸው የሚባሉ ሰዎች በባህር ዳርቻ በደቡብ ክፈለ ሀገራት የሚኖሩና እነዚህን እንስሳት የሚያድኑ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡በማደን፣ ለምግብነት በማዘጋጀት፣ በመብላት ለዚህ መጋለጥ ሁኔታ ያበቃል፡፡ አንዳንድ ኗሪዎችም ቢሆን አነዚህ አንስሳት በቤታቸው አካባቢ ጉድጓድ እየቆፈሩ ስለሚያስቸግሩ በማጥመድ ወይም በመግደል ለእንስሳቱ በመጋለጥ በዛውም ለባክቴሪያው ይጋለጣሉ ማለት ነው፡፡