​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

የቫይታሚን ዲ (Vitamin D) ዕጥረትና እና ኮቪድ-19

ኮቪድ-19 ከተከሰተ ወዲህ፣ አሁን ረገብ አለ እንጂ፣ ይህን ብሉ፣ ይህን ጠጡ፣ ይህን አጭሱ፣ ይህን ቆርጥሙ እየተባለ እየተመከረ ብዙ ጉዳትም ሲደርስ አይተናል፡፡ ክሎሮኪዊን ያለበትን የአሳ ገንዳ ማጠቢያ ኬሚካል ጠጥተው የሞቱና የታመሙም አሉ፡፡ ለእጅ መታጠቢያ የሚሆነውን አልኮል ጠጥቶ ድንገተኛ ክፍል ድረስ የደረሰ ሰው አለ፡፡ ወደ አሪዞና ደግሞ፣ ለእጅ ንፅህና የሚዘጋጅ ሳኒታይዘር ተጠቅመው የታመሙ፣ የአይን ብርሃን ያጡ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ እንኳን አደጋው የደረሰባቸው፣ ለእጅ መፅጃ የሚዘጋጀው አልኮል፣ ኤቲል አልኮል (Ethyl alcohol)  መሆን ሲገባው፣ ሰዎቹ የተጠቀሙት ግን ሜቲል አልኮል (Methyl alcohol)  የሚባል፣ ያልተፈቀደ የአልኮል ዝርያ የሆነ ኮምፓውንድ በሳኒታይዘሩ ውስጥ መገኘቱ ነው፡፡ አንባቢዎች፣ ለእጅ ማፅጃ የምትጠቀሙበት አልኮል (Ethyl alcohol) ኤትል አልኮል መሆኑን አረጋግጡ፡፡ ድንገት በግርግር ትርፍ ለማግኘት ያሰበ ሜቲል (Methyl alcohol) አልኮል ያለበት ሳኒታይዘር ሊያቀርብ ስለሚችል፣ ሜቲል አልኮል ያለበት ማፅጃ እንዳትጠቀሙ አደራ እላለሁ፡፡

ወደ ርዕሱ ስንመለስ፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት ለብዙ በሽታዎች ምክንያት ይሆናል ተብሎ ያልተበረበረ ጥናት የለም፡፡ አንድ ሰሞንማ በህክምናው አለም፣ ቫይታሚን ዲ ወሳኝ ነብስ አድን አይነት መድሀኒት ሊሆን ምንም አልቀረውም፡፡ በመረጃ ወይም በጥናት የተደገፈ ምንጭ ሲኖር፣ በባዶ የሚወራውም ነገር እየከሰመ ይሄዳል፡፡ ቫይታሚን ዲ ከኮቪ-19 ጋር በተያያዘም ቀደም ብሎ የወጡ አመለካከቶች ነበሩ፡፡ አሁን ግን፣ የአሜሪካ የአጥንትና የሚኔራል ምርምር ቡድን በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ፣ በአካል አይደለም፣ ያው ቨርቹዋል (virtual) ያቀረቡት ነገር፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት ያለባቸው በኮቪድ-19 የተያዙ ህሙማን፣ ህመሙ ጠንቶባቸው ወደ ICU እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል የሚል ነው፡፡ ወደ ICU ለመግባት ዋናው ምክንያት ሳምባ ላይ የሚደርሰው አጣዳፊ የሆነ የሳምባ ሥራ መታወክ ብቻ ሳይሆን ሥራውን ማከናወን የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ ነው፡፡ በአንግሊዘኛ Acute Respiratory Distress Syndrome (ARDS) ይባላል፡፡ ለብዙ በኮቪድ-19 ለተያዙ ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያትም ይህ የተገለፀው የህመም አይነትና ደረጃ ነው፡፡ በዚህ ህመም፣ ሰዎች በራሳቸው በመተንፈስ በቂ አኮስጅን ወደ ሰውነት ማድረስ ሰለማይችሉ ወደ ICU እንዲገቡ ተደርጎ ቬንቲሌተር (አርቲፊሻል መተንፈሻ) ላይ  ይሆናሉ፡፡

ጥናቱ የቀረበው በኢጣልያ ሀኪሞች በኩል ነው፡፡ እንደነሱ አገላለፅ፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት ያለባቸው ሰዎች ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ARDS ውሰጥ የሚገቡ ሲሆን፣ እንደ ሀኪሞቹ ገለፃ ደግሞ፣ በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኘው የቫይታሚን ዲ መጠን ከ20ng/ml በታቸ ከሆነ ደግሞ ህሙማኑ ወደ ሕይወት ማለፍ ደረጃ መድረስ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡ ሳትጠይቁ፣ ጤናማ የቫይታሚን ዲ መጠን ስንት እንደሆነ ላካፍላችሁ፡፡ ጤናማ መጠን የሚባለው ከ30 ng/ml በላይ ሲሆን ነው፡፡ ገደቡ ትንሽ ይለያያል፣ ከ20 እሰከ 40 ጤናማ ነው የሚሉም አሉ፣ ከ30 እሰከ 50 ጤናማ ገደብ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በዕለት ከዕለት ሥራችን ከ30 በታች ከሆነ፣ ያነሰ ነው እንላለን፡፡

ሰለ ቫይታሚን ዲ፣ ከሚታወቀው ከአጥንት ጥንካሬ ጋር ካለው ግንኙነት በተጨማሪ፣ ሰውነታችን በህዋሳት በሚወረርበት ጊዜ (ኢንፌክሽን)፣ ሰውነት ራሱን ለመከላከል በሚለቃቸው ኬሚካሎች አማካኝት የሚከሰተውን ኢንፈላሜሽን የተባለ ሂደት ይቆጣጠራል፡፡ ካስታወሳችሁ፣ ኮቪድ-19፣ አንዱ ትልቁ ችግሩ ይህ ኢንፈላሜሽን የሚባለው ሂደት ከመጠን በላይ በመሆን መልሶ ሰውነትን ይጎዳል፡፡ በተለይም ከዚህ ጋር በተያያዘ በልጆች ላይ የሚከሰት በሽታም አለ፡፡ (Mutlisystem Inflammatory Syndrome in Children, MIS-C) ይባላል፡፡ እንደ ሳይንቲሰቱ አገላለፅ፣ ቫይታሚን ዲ፣ ሰውነት ቫይረሱን ለማጠቃትነገር ግን ከመጠን በላይ የሚለቃቸው ኬሚካሎችን በመቀነስ፣ የደም ሥሮች ግድግዳ ላይ ያሉ ሴሎችን ጤናማ እንደሆኑ እንዲቆዩ ማድርግና፣ ከዛም በብዛት በኮቪደ-19 ላይ እየታየ ያለውን በደም ሥሮች ውስጥ የደም መርጋትን ሁኔታ እንዲቀነስ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሌላ አገልግሎት ያለው መሆኑ ተገልጧል፡፡ እንግዲህ እንዲህ አይነት ሥራን ለማከናውን፣ በሰውነት ውስጥ የቫይታሚን ዲ መጠን ጤናማ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ሁላችንም እንስማማለን፡፡

ከዚህ በፊት የተጠኑ ጥናቶች የሚጠቁሙት፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት መኖር፣ ባጠቃላይ በመተንፈሻ አካላት ላይ ኢንፊክሽን እንዲኖር አደጋውን እንደሚጨምር ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ቫይታሚን ዲ መውሰድ በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚደርሰውን ኢንፌክሽን ይቀንሳል የሚሉ ናቸው፡፡

አስታውሳችሁ ከሆነ፣ የፀሀይ ብርሃን በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የቫይታሚን ዲ መጠን አንዲጨምር የሚረዳ ሲሆን፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ባጠቃላይ በክረምት ወራት አነስ ብሎ ሲታይ፣ በበጋው ወራት ደግሞ መጠኑ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ይህ እንግዲህ በሰዎች ደም ውስጥ ሲለካ ነው፡፡ እንደምንኖርበት አካባቢም የቫይታሚን ዲ መጠን የተለያየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ውዝግብም ነበር፡፡ ጤናማ መጠን የትኛው ነው የሚል፡፡ ምክንያቱ ግልፅ ባይሆንም፣ በአውሮፓ ካሉ አገራት የኢጣልያ ሰዎች፣ በከፍተኛ ደረጃ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት አለባቸው ተብሎ ይታወቃል፡፡ ኢጣልያዊው ዶክተር የሚሉት በኢጣልያ በተለይ በክረምቱ ወራት፣ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለ ነበር፣ በጋው ሲመጣ ግን የሞቱ ቁጥር ቀነሰ፡፡ በበጋው ወራት በፀሀይ ብርሃን ምክንያት የቫይታሚን ዲ ዕጥረት እንደ ክረምቱ ወራት አይከፋም፡፡

ይህንን እየፃፍኩ፣ አፍሪካ ትዝ አለኝ፡፡ እንደምታውቁት በኮቪድ-19 ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅ ያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ እስካሁን ድረስ፡፡ ህም፣ ቫይታሚን ዲ መላ ምት፣ በመላ ምት ደረጃ ይቻል ይሆን?

ወደ ጥናቱ ስንመለስ፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት ያስከትላል የተባለውን ችግር ለመመርመር፣ በኢጣልያ በኮቪድ -19 በከፍተኛ ደረጃ የታመሙ በሚላን፣ ሳንታ ሉካ ሆስፒታል የገቡ 103 ሰዎችን ለጥናቱ መለመሉ፡፡ ከማርች 9 አስከ አፕሪል 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ እነዚህን ሰዎች ደግሞ 52 በኮቪድ የተያዙ የበሽታ ስሜት ወይም ምልክት የሌላባቸው ወይም ቀለል ያለ ህመም ከታየባቸው ሰዎች ጋር ለማነፀፀር ጥናቱ ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ፣ 206 ሰዎች፣ በእድሜና በፆታ ከህሙማኑ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ነገር ግን በኮቪድ-19 ያልተያዙ፣ በመደበኛ ጤና ምርመራ ጊዜ የቫይታሚን ዲ መጠን የተለካላቸውን ሰዎቸ ከህሙማኑ ጋር ማነፃፀሪያ አደረጉ፡፡ በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች አማካይ ዕድሜ 66 ነበር፡፡ ከሌሎቹ ጋር ሲወዳደር፣ በዕድሜያቸው የገፉ፣ ወንዶች እና በኮቪድ-19 ህመም የጠናባቸው ሰዎች የነበራቸው የቫይታሚን ዲ መጠን በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡  በተደረገው ምርመራ፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ዝቅ ባለ ቁጥር፣ ኢንፈላሜሽን ለመኖሩ ምልክት የሚሠጡ ሁለት ኮምፓውንዶች መጠን ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡

ወደ ሆስፒታል ሲገቡ፣ በጠና የታመሙ ሰዎች የቫይታሚን ዲ መጠን ዝቅ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፣ 18.2ng/ml፡፡ በኮቪድ -19 ቀለል ያለ ህመም የታየባቸው ሰዎች ደግሞ የቫይታሚን ዲ መጠን 30.3ng/ml ሲሆን፣ በሌሎቹ ለማነፃፀሪያ ጥናቱ ውስጥ የተካተቱ ግን በኮቪድ-19 ያልተያዙ ሰዎች የቫይታሚን ዲ መጠን 25.4ng/ml ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በስታቲሰቲክሰ ሲታይ፣ ይህ ልዩነት ትክክለኛ ልዩነት ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ማለትም የቁጥር ልዩነት ብቻ አልነበረም፡፡

ARDS ደረጃ ደርሰው ወደ ICU የገቡት 54 ሰዎች፣ በጠና ታመው ማለት ነው፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ሲለካ 14.4ng/ml ሆኖ ተገኝቷል፡፡ እነዚህ ሰዎች፣ ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሲሆን፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ዝቅ ብሎ መገኘት ብቻ ሳይሆን፣ የኮቪድ በሽታ መበርታት ምልክት ነው የሚባለው IL-6 የኢንፍላሜሽን ጠቋሚ ኮምፓውንድ ከፍ ብሎ ተገኝቷል፡፡ 19 ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ የሞቱትም በ ARDS ነበር፡፡ በህይወት ከተረፉት ጋር ሲወዳደር፣ የቫይታሚን ዲ መጠን 13.2 ng/ml ነበር፣ የተረፉት ደግሞ የቫይታሚን ዲ መጠን 19.3 ng/ml ሆኖ ተገኝቷል፡፡

እንደ ሀኪሙ ማጠቃለያ፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ዝቅ ማለት በራሱ ብቻውን ከከፍተኛ ህመም ደረጃ በመድረስ ወደ ICU ለመግባትና የህይወት ማለፍ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡

እንግዲህ በሳይንሳዊ ጥናት የተሳታፊ ቁጥር ማነስ ለጥናቱ ጥንካሬ ባይሰጠውም፣ ሀኪሞቹ የሚሉት፣ ተጨማሪ ቫይታሚን ዲ መስጠት በኮቪደ-19 ምክንያት የሚደርሰውን የመተንፈስ ችሎታ መድከም ይቀንስ እንደሆን ተጨማሪ ሥራ ይሠራ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ጤናማ መጠን እንዲሆን ማድረግ ወደፊት በኮቪድ-19 ምክንያት የሚከሰተውን የበሽታ መበርታት ለመቀነስ አስተዋፅኦ ያደርጋል ይላሉ፡፡

ዋናው መልክት የቫይታሚን ዲ ዕጥረትን ማስተካከል ነው እንጂ ከሚገባው በላይ ቫይታሚን ዲ መውሰድ ተገቢ እንደማይሆን ነው፡፡ ይህ ጥናት ከመውጣቱም በፊት፣ ዕጥረት አስተካክሉ ነበር መልክቱ፡፡ በአብዛኛው በሥራ ቦታ የቫይታሚን ዲ መጠን ስንለካ፣ በጣም ጥቂት ሰው ነው ጤናማ መጠን ያለው፡፡ በአሜሪካ፣ ለፀሀይ ብርሃን የምንጋለጥባቸው ወራቶች በጣም ጥቂት ሆነው፣ ለሱም ቢሆን ከቤት ወጥቶ ወደ መኪና፣ ከመኪና በአብዛኛው የፀሀይ ብርሃን ማግኘት ቀርቶ ማየት ወደማይቻልባቸው የሥራ ቦታዎች ነው የምንገባው፡፡ በምግብ በኩል፣ ቫይታሚን ዲ በበቂ መጠን አለባቸው የሚባሉ እንደ አሳ (በተለይ ሳልመን) ቱናን ጨምሮ፣ በመጠኑም ቢሆን በአይብ፣ በእንቁላልም፣ በወተትም ይኖራል፡፡ ይህንን ስዘረዘር ከይቅርታ ጋር ነው፡፡ ለምን እንዳልኩ ይገባችኋል፡፡

ሰለዚህ ቢቻል የቫይታሚን ዲ መጠን መለካትም ጥሩ ነው፡፡ ኮቪድ ባይኖም ለአጥንት ጥንካሬ ይፈለጋል፡፡ ዕጥረት ካለ፣ ዕጥረቱን ለማስተካከል የሚሰጥ ቫይታሚን ዲ መጠን ይለያያል፡፡ ከዛ ውጭ ግን በቀን አስፈላጊ መጠን የሚባለው የቫይታሚን ዲ መጠን መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡ አቅም ላለው አጥኝ፣ አፍሪካ ወይም በኢትዮጵያ ይህንን ጉዳይ በጥናት ቢመለከቱት ጥሩ ነበር፡፡ ድህነት የሚጎዳው በብዙ መልኩ ነው፡፡ ከመጨረሴ በፊት ግን፣ ቫይታሚን ዲ ከመጠን በላይ ከተወሰድ ጉዳት ያስከትላል፣ የሆድ ህመም፣ ማስታወክና ሌሎችን ጨምሮ በተገላቢጦሽ አጥንት እንዲሳሳ ያደርጋል፡፡ 13 ወራት የፀሀይ ብርሃን ጥቅሙ ይኸው፡፡ ለአጥንት ጥንካሬ ቫይታሚን ዲ የሚወስዱ ከሆን ከካልሲየም ጋር መውሰድ ይረዳል፡፡ ከአፍሪካ ውጭ ለሚኖሩ ሰዎች በቀን መወሰድ የሚገባው የቫይታሚን ዲ መጠን እንደ ዕደሜያችን ስለሆነ የሚከተለውን ሠንጠረዥ ይመልከቱ፡፡ ምንጭ (National Institute of Health office of Dietary Supplements) ይህንን እንኳን በደንብ አካፍሉ፡፡ መልካም ንባብ፡፡