መካንነት የሚያስከትለው ክትባቱ ሳይሆን ኮቪድ-19 ነው! 01/30/2021


ከመንገድ የተመለሰውን ባለቤቷን “በዛው በጨረሱህ እይሻልም ወይ” አለች ይባላል፡፡

ኮቪድ-19 የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች እየበረከቱ እንጂ እያነሱ አይደለም፡፡ ባጠቃላይ የማይገባበት የሰውነት ከፍል የለም የሚባልለት ይህ በሽታ፣ ሰሞኑን ከወደ ጀርመን በኩል በጥናት የቀረበ ፅሁፍ እንደሚያሳያው፣ በሽታው በወንዶች ላይ ወደመካንነት የሚያመራ ሁኔታ እንደተገኛባቸው ይጠቁማል፡፡ ምንም አንኳን አንድ ጥናትና ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበ ፅሁፍ ቢሆን፣ የዚህን በሽታ ባህሪ የተከታተለ ሰው፣ መካንነቱ ሊፈጠር ይችላል ወደሚለው ድምዳሜ ማድላቱ አይቀርም፡፡


በአንድ በኩል፣ አዲስ በሽታ ሰለሆነ፣ እሳከሁን እንዴት አልታወቀም ብሎ ማማት ያስቸግራል፡፡ በተጨማሪም፣ በአጣዳፊ ሁኔታ ላይ የሚሞቱ ሰዎች ወደ ማዳኑና ሥርጭቱን ወደ መግታቱ ያመዘነ እንቅሰቃሴ ነው ጎላ ብሎ የሚደረገው፡፡ መሆንም ይገባዋል፡፡


ወደ ጥናቱ ውጤት ልውሰዳችሁ፡፡ የጥናቱ ባለቤት ከሆኑት ዶክተሮች አንደኛው የሚሉት፣ የሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር 2 (ሳኮቫ-2) በሰዎች የስፐርም ሴሎች ላይ ሰለሚፈጥረው ሁኔታ ብዙም የሚታወቅ ነገር አልነበረም ነው፡፡ ሰውየው ጀርመን ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ነው የሚሠሩት፡፡ Reproduction በተባለ መፅሄት የሚገልፁት፣ ሳኮቫ-2ና በስፐርም በሚገኙ ጠቋሚ ኮምፓውንዶችና በወንዶች ላይ ዘር የማፍራት ችሎታ ላይ የሚያመጣውን ለውጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘነው እኛ ነን ይላሉ፡፡ ይህ አባባል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ወይም ፈር ቀዳጅ የሆኑ ግኝቶችን የሠሩ ሰዎች የሚኩራሩበት መግቢያ አረፍተ ነገር ነው፡፡ ለማንኛውም ጥናቱ የተካሄደው በኮቪድ-19 ታመው ባገገሙ ሰዎች ላይ ነው፡፡


የክትትል ጥናት ነው የተደረገው፡፡ ይህም ጥሩ ነው ምክንያቱም ነገሩ ካለፈ በኋላ የበሽተኞችን ቻርት በማገላበጥ የሚደረጉ ጥናቶች እንደክትትሉ ጠንከር ያሉ አይደሉም፡፡ በተደረገው ክትትል፣ በቫይረሱ መያዛቸው በላቦራቶር በተረጋገጠ 84 የኮቪድ-19 በሽተኛ የነበሩ ወንዶችና በበሽታው ተይዘው ባልነበሩ 105 ወንዶች ላይ ነው፡፡ ይህም ጥሩ ነገር ነው፣ ምክንያቱም በበሽታው ያልተያዙ ሰዎችን እንደማነፀፃሪያ አድርገዋል፡፡ በጥናቶች ላይ እንዱ ወሳኝ ነገርም ይህ ነው፡፡ ሌላ ማነፃፀሪያ መኖር አለበት፡፡


በጥናቱም የተደረገው፣ የተለያዩ ሰውነት ውስጥ የሚገኙ ኮምፓውንዶችን፣ ACE2 የተባለውን ቫይረሱ ወደ ሰውነት ሴሎች መግቢያ የሚጠቀምበትን ሞሎኪል ወይም ኤንዛይም ጨምሮ፣ የዘር ፈሳሽ (semen) ጥራተን ያካተተ ምርመራ ነው፡፡ ምርመራው በየአስር ቀናቱ እየተደረገ የስልሳ ቀናት ርዝመት ያለው ነበር፡፡


በጥናቱ ከተካቱት ወንዶች አብዛኞች በ30 አመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ናቸው፡፡ የክብደት መጠናቸው ግን የተለያየ ነበር ይላሉ አጥኝዎቹ፡፡ ጥናቱ ከመጀመሩ በፊት፣ የዚህ የፆታ የሰውነት አካልና የዘር መተካት ባለሙያ የሆኑ urologist የሚባሉ ባለሙያተኞች ሰዎቹን በመመርመር ዘር መተካት(fertile)s የሚችሉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በኮቪድ የተያዙት ህሙማኑ ጠንከር ያለ የኮቪድ በሽታም ነበረባቸው፣ ከአንድ ሰው በስተቀር፣ እናም ሰቴሮይድ በተባለ የመድሐኒት አይነትና ቀጥታ ቫይረሱን ሊያጠቃ ይችላል በሚባል መድሐኒት ህክምና ተድረጎላቸዋል፡፡
እንደ አጥኝዎቹ ዘገባ፣ ጥናቱ ሲጀመርና ከዛም በተደረገው ክትትል፣ በኮቪድ,19 ተይዘው የነበሩት ወንዶች፣ በዘር ፈሳሻቸው ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ACE2 ኤንዛይምና ሌሎ ኢንፈላሜሽን የሚያራምዱ የተለያዩ ኮምፓውንዶች ተገኝቶባቸዋል፡፡ በኮቪድ-19 ካልተያዙ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር ሌሎችም ከኦክስጅን ጋር የተያያዘ በሴሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ኮምፓውንዶች በበሸታው ተይዘው በነበሩ ሰዎች ላይ በከፍተኛ መጠን ተገኝተዋል፡፡ በተለይም በስፐርም ሴሎች ላይ ሴሎቹን መጉዳት የሚችሉት ሁኔታዎች በበሽታው ካልተያዙ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር በኮቪደ-19 ተይዘው በነበሩ ሰዎች ከመቶ ዕጥፍ በላይ ከፍ ባለ መጠን ነው የተገኙት፡፡


አንግዲህ ዘር የመተካትን ሁኔታ በተመለከተ የስፐርም ሴሎች ወሳኝ ናቸው፡፡ ዘር መተካት ችሎታቸው የሚቀንስበት ሁኔታዎች ሲኖሩ የሚታዩ ባህሪዎች የመጀመሪያው የስፐርም ሴሎች የእንቅስቃሴ ፍጥነት መቀነስ ሲሆን ሌሎው ደግሞ የራሳቸው የስፐርም ሴሎች መጠን መቀነስ ነው፡፡ በኮቪድ-19 ተይዘው በነበሩ ሰዎች ላይ ሲታይ፣ የስፐርም ሴሎች ቁጥር መጠን በ516% አንሶ የተገኘ ሲሆን፣ የስፐርም ሴሎች የመንቀሳቀስ ችሎታ ደግሞ በ209% አንሶ ታይቷል፡፡ ሌላው ዘር የመተካት ቸሎታ ጋር መቀነስ ጋር ተያይዞ የሚታየው ባህሪ ደገሞ፣ የስፐርም ሴሎች ቅርፅ ነው፡፡ ሥራ መተጓጎል የሚያስከትለውም የሴሎች የተፈጥሮ ቀርፅ ሲቀየር ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ጥናት የታየው ደግሞ፣ በኮቪድ-19 ተይዘው በነበሩ ወንዶች ላይ፣ ካልተያዙት ወንዶች ጋር ሲነፃፀር በ400% የስፐርም ሴሎች ቅርፅ ተቀይሮ ተገኝቷል፡፡ ህም! ምን ቀረ ታዲያ?


ከላይ የተጠቀሱ በስፐርም ሴሎች ላይ የታዩ ባህሪዎች ዘር ከመተካት ችሎታ ማነስ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው፡፡ ማለትም ወደ መካንነቱ የሚወስዱ ማለት ነው፡፡ አጥኝዎቹ የሚሉት፣ ከረዥም ጊዜ በኋላ ይህ የመካንነት ሁኔታ በሌሎች አንዳንድ ጊዘያዊ ይህን አይነት ሁኔታ መፍጠር በሚችሉ ክስተቶች ላይ እንደሚታየው ቀስ ብሎ የመሻሻል ሁኔታ ሊያሳይ የሚችል መስሎ የሚታይ ቢሆንም፣ በኮቪድ-19 በተያዙ ሰዎች ግን መካንነቱ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለና በተለይም በኮቪድ-19 በጠና በታመሙ ሰዎች ላይ የከፋ ደረጃ እንደሚሆን ነው፡፡
የጥናቱን ውጤት ከተግባራዊ ሁኔታ ጋራ ሲያይዙት፣ አጥኝዎቹ የሚሉት፣ ልጅ መውለድ የሚፈልጉ ጥንዶች በጥንቃቄና ተዘጋጅተውበት አንዲሆን፣ ከዛም በኮቪድ-19 ታመው ካገገሙ ባሎቻቸው ልጅ መውለድ የሚፈልጉ ወይም የሚጠብቁ ሴቶች፣ ባሎቻቸው ተመርምረው ዘር መተካት መቻልና አለመቻላቸው በሀኪሞች ተመርመሮ እስኪረጋገጥ ደረስ ረጋ ይበሉ ነው የሚሉት፡፡
ይህን የማቀርበው ለማስደንገጥም አይደለም፡፡ ነገር ግን በጥናት የተረጋገጠ ውጤት ሰለሆነ ወገኖች "ሌላም አለ" ብለው እንዲጠነቀቁ ነው፡፡ ከላይ እንዳያችሁት በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት ሰዎች አብዛኞች በ30 አመት ዕድሜ ክልል ውስጥ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ፣ ባለማወቅም ይሁን ወይም በማን አለብኝነት የኮቨድ-19 የመከላከል ተግባርን ችላ በማለት እንዲያውም አንዳንዶች በማጣጣል ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ ሰዎች የሚገኙበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ ገና አመት የሞላው ይህ በሽታ ብዙ ጉድ አለው፡፡ ቫይረሱም አንደምንከታተለው ባህሪውን እየቀየረ ነው፡፡ ወደ የት? የሚለውን መረዳትም አያዳግትም፡፡ እንግዲህ ጎልማሶቹ የቁጥር መጠናቸው ባይታወቅም ታመው ከሞት ቢተርፉም፣ ዘር መተካት የማይችሉበት ሁኔታ ከተፈጠረ ምን ሊባል ነው፡፡ ይህን ስል አንድ ዕውነት ይሁን ተረት የሚነገር ነገር ትዝ አለኝ፡፡


ያም፣ መንገድ ወጥቶ የተመለሰ ሰው፣ ባገራችን ነው፡፡ በነበረበት አካባቢ የነበሩ ሽፍቶች ይዘርፉታል፡፡ ቤት ባዶ እጁን ነው የገባው፡፡ ለሚስቱ እየነገረ፣ ጦር የት ሄደ? ሰትለው፣ ወሰዱት፣ ጋሻውስ? ወሰዱት፣ ጩቤውስ? ወሰዱት ይላታል፡፡ ሚስትዮዋም፣ ታዲያ ሌላ ምን አደረጉህ? ብላ ጠየቀች፡፡ ባልየውም ሳያቅማማ፣ ሰለቡኝ (ብልቴን ቆረጡት) ይላታል፡፡ እሷም ሳታቅማማ፣ በዛው በጨረሱህ እይሻልም ነበር አለችው ይባላል፡፡ ተረቴን መልሱ ይላሉ ያገራችን ሰዎች


ስለዚህ የኮቪድን መሠራጨት ለመካለከል በተለይም የደቡብ አፍሪካው የቫይረስ ዝርያ በየቦታው በታየበት ወቅት ነገ በእኔ ብሎ ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ ሌላ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ሀላፊ ከሆኑ ሰው የመጣ አንድ ሀሳብ አለ፡፡ 'መ' የሚባለውን ፊደል እንደ መነሻ በመጠቀም እሳቸው የሚሉት፣ በስብሰባ አብሯቸው የነበረ በዚህ በኮቪድ ላይ አብረን የምንሠራ ፕሮፌሰር እንዳካፈለን፣ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
መ------ማስክ በጊዜ፣ ቦታና በአደራረግ ክፍተት ሳይፈጥሩ ማድረግ
መ---- መታጠብ አጅን በውሃና በሳሙና ፣ አለዚያም በተገቢው አልኮል መወልወል
መ---- መራራቅ ሁለት ሜትር ርቀት ጠብቆ
መ-----መስብሰብ ማቆም፣ መቀነስ
ምን እንዳሉ መልክቱ ግልፅ ነው፡፡ ስማቸውን ለመጠቀም ለጊዜው ፈቃድ ሰላላገኘሁ ነው፡፡ ይልመድብን፡፡ የሰውን ሀሳብ ሳይጨልፉ ባለቤቱን እያሳወቁ መጠቀም ማለቴ ነው፡፡

የኮቪድ ክትባትና መካንነት
አዲስ የጥናት ውጤት   08/04/2021


በተለያዩ ቦታዎች ሰለኮቪድ ሆነ ሰለ ኮቪድ ክትባት ውይይት ሲደረግ ተደጋግሞ የምጠየቀው ጥያቄ፣ የኮቪድ ክትባት መካን ያደርጋል ወይ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ጥያቄ መነሻው ከየት እንደሆነ ባይታወቅም፣ ሰለ ኮቪድ ብዙ ነገሮች ሰለሚነገሩ አስገራሚ አይሆንም፡፡ ከዚህ ቀድም በጎሽ ድረ ገፅ፣ የኮቪድ ቫይረስ ወይም በሸታው መካንነት ሊያስከትል እንደሚችል የሚገልፅ የአነስተኛ የጥናት ውጤት አካፍያችሁ ነበር፡፡

አሁን ግን፣ ማን ይሆን ይህን የሚያጠናው ብለን ስንጠብቅ፣ በአሜሪካ ከማያሚ ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ ክትባት መውሰድ በወንዶች ላይ መካንነት ያስከትል ይሆን የሚል ጥናት አጥንተው፣ JAMA በተባለ የህክምና መፅሄት በኩል ለህዝብ አካፍለውናል፡፡ ይህ ከዚህ ቀጥሎ የምገልፅላችሁ የጥናት ውጤትም ከዚህ መፅሄት ነው፡፡ በመረጃ፡፡

ወደ ጥናቱ ዝርዝር ስንሄድ፣ ዕድሜያቸው ከ18 -50 አመት የሆናቸው ወንዶች ለጥናቱ በራሳቸው ፈቃድ እንዲመለመሉ ተደረገ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጥናት ሲመለመሉ የኮቪድ ክትባት ለመውሰድ ቀጠሮ የያዙ ነበሩ፡፡ ጥናቱ፣ እንደማንኛውም ህጋዊ ጥናት (Institutional Review Board, IRB) የተቋሙ ገምጋሚ ቦርድ ካፀደቀው በኋላ ነው የተጀመረው፡፡

ለጥናቱ የተመለመሉት ወንዶች ከዚህ ቀደም የመካንነት ችግር እንደሌለባቸው አስቀድሞ ምርመራ ተደረገ፡፡ በተጨማሪም የኮቨድ ህመም ስሜት ያላቸው ሰዎችና በዘጠና ቀናት ውሥጥ በምርመራ ኮቪድ የተገኘባቸው ሰዎች ከጥናቱ ውጭ እንዲሆኑም ተደረገ፡፡

የመካንነት ምርመራ የሚደረገው የዘር ፈሳሽን በመውሰድ ሰለሆነ፣ የጥናቱ ተሰታፊዎች የመጀመሪያውን ክትባት ከመውሰዳቸው በፊት ከሁለት አስከ ሰባት ቀናት ውሰጥ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከማድረግ ታቅበው የዘር ፈሳሽ እንዲሰጡ ተደረገ፡፡ እንደገና ደግሞ ሁለተኛው ክትባት ከወሰዱ ከሰባ ቀናት በኋላ ድጋሚ የዘር ፈሳሽ እንዲሠጡ ተደረገ፡፡

በተሠጠው የዘር ፈሳሽ ላይ በአለም የጤና ደርጅት መመሪያ መሠረት ለመካንነት የሚደረጉ ምርመራዎች ተካሄዱ፡፡ እነሱም፣ በፈሳሹ ውስጥ ያለው የስፐርም ክምችት መጠን፣ Sperm motility የስፐርም የመንቀሳቀስ ችሎታና የመንቀሳቀስ ችሎታ ያላቸው አጠቃላይ የስፐርም ቁጥር ነበሩ፡፡ ለማብራራት ያክል የስፐርም እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው ምክንያቱም ከሚመረትበት ቦታ ተነስቶ በመጓዝ ወደ ሴት ማህፀን ዘልቆ ከአንቁላል ጋር መገናኘት ካልቻለ ዘር መፍጠር አይችልም፡፡ ሌላኛው መመዘኛ ደግሞ እንደዚህ ተንቀሳቅሰው መጓዝ የሚችሉ የስፐርሞች ቁጥርም ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ጥናት ላይ ከመጀመሪያው የስፐርም መጠኑ ከጤናማ በታች የሆነባቸው ሰዎችም እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡

አነዚህ ምርመራዎች ከክትባት በፊት በተወሰደውና ከዛም ከክትባት በኋላ ከተወሰደው የዘር ፈሳሽ ጋር እንዲነፃፀሩ ተደረገ፡፡ አንግዲህ በዚህ በሁለቱ ንፅፅር ማለትም ከክትባት በፊትና ከክትባት በኋላ የታየው ልዩነት ነው የጥናቱ ዋና ጭብጥ፡፡ ተገቢው የስታቲስቲክ ትንተና መደረጉን ልብ ብለን እንያዝና ወደ ጥናቱ ውጤት እንሂድ፡፡

ምልመላው የተካሄደው ከዲሴምበር 17 2020 ና በጃንዋሪ 12 2021 መሀከል ነበር፡፡ በዚህም 45 አመት በበጎ ፈቃድ የተሳተፉ ሰዎች ነበሩ፡፡ አማካይ ዕድሜ 28 አመት ነበር፡፡ የዘር ፈሳሽ ከተወሰደ በኋላ የወሰዱት ክትባት 21 የፋይዘር ክትባት ሲሆን፣ 24ቱ ደግሞ ሞደርና የተባለውን ክትባት ነበር፡፡ ሁለቱም ክትባቶች mRNA የሚጠቀሙ መሆናቸውን አስተውሉ፡፡ ጥያቄው የሚነሳው በነዚህ ክትባቶች ላይ ነው በአብዛኛው፡፡ ከ JAMA መፅሄት ከተወሰደ ሠንጠረዥ ላካፍላችሁ፡፡ ሠንጠረዡ ወጤቱን በደንብ ያሳያል፡


 በሠንጠረዡ እንደምታዩት የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው፣ በእያንዳንዱ የምርመራ ውጤት ቁጥሩ ከክትባት በፊት ከነበረው የበለጠ ነው የሆነው፡፡ ይህም በስታትሰቲክ ስሌት ተቀባይነት ያለው ውጤት መሆኑን አጥኝዎቹ ግልፅ አድርገውታል፡፡ ሰለዚህ በሁሉም የምርመራ ውጤት እንኳንስ ከሚጠበቀው በታች ወርዶ ለመካንነት ምክንያት መሆኑ ቀርቶ እንዲያውም ቁጥሩ ጨምሮ መታየቱ ግልፅ ሰለሆነ፣ በክትባቱ በኩል መካንነት ይመጣል የሚባለውን፣ አባባል ልበል፣ ውድቅ ያደርገዋል፡፡ መግቢያው ላይ እንደጠቀስኩላችሁ በኮቪድ መያዝ በቫይረሱ መያዝ ነው እናም በኮቪድ የተያዙ ወንዶች መካንነት ሊያስከትል የሚችል ወጤት እንደነበራቸው ተገልጧል፡፡ ክትባቱ ግን ቫይረስ የለበትም፡፡

ለማንኛው ከተሳታፊዎች ውስጥ ከጠዋቱ የስፐርም መጠናቸው ያነሰባቸው ሰዎችስ ምን ለውጥ አሳዩ ለሚለው መልስ፣ እነሱም ቢሆን ከስምነቱ ሰዎች በሰባቱ ላይ ክትትል ሲደረግ ከክትባት በፊት ከነበራቸው ዝቅተኛ ወይም ከጤናማ መጠን በታች የነበረው የስፐርም መጠን ከክትባቱ በኋላ ከፍ በማለት ወደ ጤናማ መጠን ተሸጋግሯል፡፡

ጥናቱ ይህንን ውጤት ማገራቱ በጣም ደስ የሚል ነው፡፡ የብዙ ሰው ጥያቄም ሰለሆነ መልስ አግኘተናል፡፡ በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች ቁጥር በንፅፅር አነስተኛ መሆኑ ከደካማ ጎን ሊቆጠር ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በስታቲሰቲክ ሲታይ ምንም የሚያከራክር ውጤትም ሰላልነበር በፀጋ የምንቀበለው ውጤት ነው፡፡

በቫይረሱ ምክንያት የሚመጣን ነገር ወደ ክትባቱ ማሸጋገርም በተለይ ያለ በቂ መረጃ ጥሩ አይሆንም፡፡ ስንቱን ሰለኮቪድ የሚወራውን መሠረት ያልያዘ ወሬ መከላከል ይቻል ይሆን? በነገራችን ላይ ጥናቱ ያተኮረው በተወሰኑ ክትባቶች ላይ ሰለሆነ ባጠቃላይ ለኮቨድ የሚሠጡ ክትባቶችን አይወክልም፡፡ በተጨማሪም ክትባቶቹ አሰራራቸው ለየት ያለ መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Health and History

Community health 

education in Amharic