​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

የኮቪድ ክትባት ለተከተቡ ሰዎች ጥሩ ዜና 02/11/2021

የኮቪድ ክትባት እንደሚታወቀው ባለው ዕጥረት ምክንያት ቅድሚያ የተሠጣቸው ወገኖች አሉ፡፡ አሁን ግን ሰፋ እያለ ለሌሎችም እየተዳረሰ ነው፡፡ ዕድሜ ከ65 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ ክትባቱ ሲወሰድ ለተከተቡ ሰዎች የሚሠጠው ጥቅም በጥናቶቹ መሠረት የሚያሳያው የበሽታ ስሜት ያለበት በኮቪድ መያዝን የማስጣል ሁኔታ ነው፡፡ እንደ ክትባቱ አይነት 95 (ፋይዘር)፣ 94 ፐርሰንት (ሞድርና) ነው፡፡

ሆኖም፣ ክትባቱን ከወሰድን በኋላ ምን ማድረግ እንደሚገባን ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው፣ ክትባት ከወሰድን በኋላ፣ መከላከያ ይኖረናል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛውን ክትባት ከወሰድን ከሁለት ሳምነታት በኋላ ነው፡፡ እናም ክትባት ወሰድን ድንገት ከኮሮና ወይም ኮቪድ ብንጋለጥ ምን ማድረግ ይኖርብናል ለሚለው ጥያቄ፣ የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) የመለሰው መልስ አለ፡፡

ክትባቱን በትክክል ወሰድው የጨረሱ ሰዎች በኮቪድ-19 ከተያዘ ሰው ጋር ቢጋለጡ ራሳቸውን ወደ ኳራንቲን ማስገባት የለባችው

ከላይ የተጠቀሰው የሲዲሲ መመሪያ ነው፡፡ እንግዲህ የዚህ ምክር ትርጉም ተሰፋ የሚሠጥ ነው፡፡ በተለይም በሥራ ምክንያት ራሳቸው ከኮቪድ በሽተኞች ጋር የሚጋለጡበት ሁኔታ ለሚሠሩ ሰዎች፣ ባለሙያተኞች ከጭንቀት የሚያድን ሁኔታ ነው የፈጠረው፡፡ ይህ ምከር ቢወጣም፣ የተከተቡ ሰዎች የኮቪድ ሥርጭት ለመከላከል ሌሎች ማድረግ የሚገባቸውን፣ ማስክ ማድረግ፣ ስድስት ጫማ ርቀትና ስብስብን ማቆም አለባቸው፡፡

ወደ ኳራንቲን ስንመለስ፣ ክትባቱን ወስደው ነገር ግን፣ ኮቪድ ከያዘው ሰው ጋር ቢጋለጡ ራሳቸውን ማግለል የለባቸውም የሚለው የሚከተሉትን ሶሰት መመዘኛዎች በሙሉ ካሟሉ ነው፡፡

ከትባቱን በትክክል የወሰዱ ማለትም ሁለተኛውን ክትባት ከወሰዱ 2 ሳምንት ካለፋቸው፡፡ አንድ ክትባት ብቻ የሚሠጥ ከሆነም ያንን ከወሰዱ ከሁለት ሳምንት ካለፋቸው
ክትባቱን ማለትም የመጨረሻውን ከወሰዱ በሶስት ወራት ውስጥ ከሆነ፡፡ እዚህ ላይ፣ በክትባቱ አማካኝነት የተፈጠረው የመከላከያ አንቲቦዲ ሊቆይ የሚችለው የጊዜ ገደብ ሶስት ወራት ብቻ ሊሆን ይችላል ከሚል ከመረጃ የመነጨ ነው፡፡ ሆኖም ይህንን በሚመለከት ጥናቶች ሰለሚካሄደ የተፈጠረው የመከላከያ አንቲቦዲ ምን ያህል ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል ማወቅ ይቻላል፡፡
ከተጋለጡ በሁዋላ ምንም የበሽታ ስሜት የማይሰማቸው ወይም ምልክት የሌላቸው ከሆነ፡፡ይህ በራሱ ትልቅ ዜና ነው፡፡ ኳራንቲን ከመግባት ጋር የሚፈጠሩ የአእምሮ ጭንቀተ፣ ሥራ ማቋረጥ የመሳሰሉ፣ እንደገናም ሌሎችንም አጋልጨ ይሆን ብሎ መጨነቅም ሰለሚኖር፣ ከላይ ከተሰጠው መመዘኛ በመነሳት ክትባት የወሰዱ ሰዎች ቢጋለጡም ራሳቸውን ኳራንቲን ማስገባት የለባቸውም ሲባል ትልቅ ዕፎይታ ነው፡፡ ለወደፊት ይህ ምክር ክትባት ከተወሰደ ከሶስት ወራት በላይን ይጨምራል እንደሚል ተስፋ ይኖራል፡፡ ምናልባትም ለሰድስት ወራት፡፡ አስከዛ ድረስ ግን ሥርጭቱን ማገድ መቀነስ ተገቢ ነው፡፡


ቤተ ክርሰቲያን መሪዎች ክትባቱን እየወሰዱ ነው


የሮማው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከቀዳሚው ጳጳስ ጋር በመሆን የኮቪድ ክትባት እንደወሰዱ ቫቲካን ኒውስ የተባለው በመግለጫው አካፍሎናል፡፡


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤክርሰቲያን አቡን ደግሞ ራሳቸው ክትባቱን ሲወስዱ የተነሱትን ፎቶግራፍ “አስተምርበት” ብለው ፈቃድ ሰጥተውኝ እያካፈልኳችሁ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከልብ የመነጨ ምስጋናየን በአደባባይ ማቅረብ እወዳለሁለ፡፡


ሀይማኖትን ተመርኩዘው ሰለ ክትባቱ ብዙ የሚናገሩ፣ ከዛም አልፎ፣ አትከተቡ የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ለኔም እንዳልከተብ ምክራቸውን ለግሠዋል፡፡ መነሻ ምክንያታቸው በግልፅ ሰፋ ያለም አይደለም፡፡ ክትባት መሠራት ከተጀመረ ጀምሮ ፀረ-ክትባት አቋም ያላቸው ሰዎች መኖራቸው እንግዳ አየደለም፡፡ እናም አነዚህ ሰዎች በተገኘው መገናኛ ተቃውሟቸውን ማሰማት ብቻ ሳይሆን፣ ማስፈራራትም ጀምረዋል፡፡ የሀገራችን ሰዎችም ተጠንቀቁ እያሉ ይመክራሉ፡፡ ሀይማኖትን ተመርኩዘው ከሆነ፣ ህክምናውን ልተወውና፣ እኔ የምሰማው የሀይማኖት መሪዎችን ነው፡፡ የናንተን ባለውቅም፡፡


ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ፣ ኮሮና ቫይረስና የኮቪድ በሽታን መከላክል ሰብአዊ ግዴታ ነው፡ ለሌሎች ሲባልም የሚደረግ ነገር ነው እያልኩ ነው፡፡ ለማንኛውም የሮማው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲሰ ሰለ ክትባቱ የተናገሩትን አንብቡ፡፡


“An ethical action, because you are gambling with your health, 
you are gambling with your life, but you are also gambling with the lives of others.”


Pope Francis

The Vatican News

የኮቪድ ክትባት ከህመም ብቻ ሳይሆን ከመያዝም ያስጥላል 04/06/2021

ቸር ያሰማን እንደሚባለው ሁሉ፣ የኮቪድ ክትባት ውጤት መስማት ተስፋ የሚሠጥ ነገር ነው፡፡ ወደኋላ ትንሽ ልመልሳችሁና ሰለ ክትባቶች አሰራርና ኢላማ ላካፍላችሁ፡፡ ክትባቶች ሲጠኑ ኢላማ ያደረጉት በቫይረሱ መያዝ ሳይሆን ለቫይረሱ ከተጋለጡ በኋላ የበሽታ ስሜት የሚሰማቸውን ሰዎች ምን ያህሉን ያስጥላል ነው፡፡ እንደምትሰሙት እንግዲህ የጥናት ውጤት ተብሎ በአሃዝ በፐርስነት የሚገለፀው ክትባቱን በወሰዱና ባልወሰዱ ሰዎች መሀክል ንፅፅር ሲደረግ፣ የኮቪድ የበሽታ ስሜት ያለባቸው ሰዎች ክትባቱን ባልወሰዱ መሀል ቁጥሩ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ክትባቱን ከወሰዱት መሀከል እንደክትባቱ አይነት በጣም መጠነኛ ነው፡፡

ነገር ግን ሁላችንም እናውቃለን ብዬ እንደምገምተው፣ በኮሮና ቫይረሱ የተያዙ ግን የበሽታ ስሜት የማይታይባቸው ሰዎች ብዙ እንደሆኑ ነው፡፡ እንዳውም ለቫይረሱ ሥርጭት አብይ ሚና የሚጫወቱት እነዚህ ቫይረሱ ያለባቸው ግን የበሽታ ስሜት የሌለባቸው ሰዎች ናቸው፡፡

ታዲያ ክትባቶቹ እንደወጡ፣ ከበሽታ ማስጣላቸውን በፀጋ የተቀበልነው ነገር ቢሆንም፣ በቫይረሱ ከመያዝ ያስጥሉን ይሆን ብለን እየጠየቅን ነበርን፡፡ ለምን ክትባቱን ወስደን በሽታ ስሜት ባይኖረን፣ ነገር ግን ቫይረሱን ይዘን ለሌላ ሰው የምናስተላልፍ ከሆነ ደግሞ ለሥርጭት መቀጠል ምክንያት ልንሆን ነው፡፡ ሰለዚህ እነዚህ ክትባቶች በቫይሱ ከመያዝ ማሰጣላቸውን በጥናት የተደገፈ መረጃ ለማግኝት በጉጉት ስንጠብቅ፣ የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል MMWR በሚባለው መግለጫቸው ተስፋ የሚሠጥ ቸር ወሬ አካፈሉን፡፡

ይህም ከዲሴምበር 14 2020 ጀምሮ አስከ ማርች 13፣ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ በስምንት ቦታዎች በሚካሄድ ፕሮገራም፣ ሰዎች የበሽታ ምልክት ኖራቸውም አልኖራቸውም በየሳምንቱ ለኮሮና ቫይረስ ምርመራ ያደርጉላቸው ነበር፡፡ ክትባቶች ሲመጡ ደግሞ፣ ከነዚህ ሰዎች መሀከል ከዚህ በፊት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ከማያወቁ ከ3950 ሰዎች መሀከል፣ 2479 (62.8%) ሁለት ጊዜ ክትባት ይወሰዳሉ፣ ቀሪዎች 477 ደግሞ በጊዘው አንድ ክትባት ብቻ ነበር የወሰዱት፡፡ ቀደም ብሎ እንደተገለፀው፣ በየሳምንቱ ለኮሮና ቫይረስ የሚደረገው ምርመራ ሰያቆም ቀጠለ፡፡

በዚህ ምርመራ ያገኙት ውጤት የሚያሳያው፣ በክትትሉ ከሚሳተፉ ሰዎች፣ እናም ክትባት ባልወሰዱት መሀከል፣ 161 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ሲታወቅ፣ ሙሉ ክትባት ወሰዱ ከተባሉት መሀከል፣ (ማለትም ሁለተኛውን ክትባት ከወሰዱ ከሁለት ሳምንት በኋላ) በምርመራ በኮሮና መያዛቸው የተረጋገጠ ሶስት ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ያልተከተቡት ላይ፣ ማለትም፣ የመጀመሪያውን ክትባት ከወሰዱ 14 ቀናት ያለፋቸው ነገር ግን ገና ሁለተኛውን ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች መሀከል፣ አምስት በኮሮና መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ሲገኙ፣ የመጀመሪያውን ከወሰዱ ሁለት ሳምንት በላይ ሆኗቸው ሁለተኛውን ክትባት የወሰዱ ግን ሁለተኛውን ከወሰዱ ሁለት ሳምንት ያላለፋቸው ሰዎች መሀከል ሶስት በኮሮና መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ነበሩ፡፡ ሰለዚህ ሁለተኛውን ክትባት ከወሰዱ ሁለት ሳምንት ያላላፋቸው ሰዎች መሀከል ባጠቃላይ ስምንት በኮሮና መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ነበሩ፡፡

አንግዲህ የስሌቱን ዘዴ ልዝለልና በአሃዝ በፐርስነት ሲገለፅ፣ የታየው ነገር የሚያስረዳው፤ ክትባቱን አሟልተው ወሰደዋል ከሚባሉ ሰዎች ላይ በቫይረሱ ያለመያዝ ሁኔታው በፐርሰንት ሲገለፅ 90 ከመቶ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ በቀላል አማርኛ፣ በቫይረሱ መያዝ በዘጠና ፐርስንት ይቀንሳል ወይም በዘጠና ፐርሰንት ያለመያዝ ሁኔታ ታይቷል ነው፡፡ በሌላ በኩል ክትባት ቢወስዱም ገና ያልተሟላ ማለትም ሁለተኛውን ክትባት ከወሰዱ ሁለት ሳምንታት ያላለፋቸው ሰዎች መሀከል ደግሞ፣ በቫይረሱ ያለመያዝ ሁኔታ የታየው ወረድ ብሎ በ80 ፐርሰንት ነው፡፡ አንግዲህ አንዳንዶች እንደሚያደርጉት፣ ገና ክትባት እንደወሰዱ መከላከያ ዘዴዎችን ማቆም በመጠኑም ቢሆን በቫይረሱ ለመያዝ ይዳርገናል፡፡

የዚህ ጥናት ተሳታፊዎች የጤና ባለሙያተኞች፣ የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞችና ሌሎች (Essential) ሠራተኞች ናቸው፡፡ የወሰዷቸው ክትባቶች ደግሞ፣ በአሜሪካ ፈቃድ ያገኙትን የፋይዘር ወይም የሞደርና ክትባት ነው፡፡ አንግዲህ የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው፣ የበሽታ ምልክት ኖረም አልኖረም በቫይረሱ የመያዝ ዕድሉን መቀነሱን ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ቸር ወሬ የሚሆነው፣ ክትባቱን ለወሰደው ግለሰብ ብቻ ሳይሆን በቫረሱ የመያዝ ዕድሉ በመቀነሱ፣ ለሥርጭቱ መቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሰለሚያደርግም ነው፡፡ በዚህ ጥናት የተሳተፉ ሰዎች ደግሞ በሥራ ፀባያቸው ምክንያት ለኮሮና ቫይረስ ሊጋለጡ የሚችሉ ሰዎች በመሆኑ፣ ይህንን ያህል በቫይረሱ ከመያዝ መቀነስ መታየቱ በጣም ጥሩ ያደርገዋል፡፡

የዚህ ጥናት ውጤት ከዚህ በፊት በተለያዩ ጥናቶች ከታዩት ውጤቶች ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ይህ ጥናት የሁለቱ ማለትም የሞደርናና የፋይዘር ክትባቶች በወሰዱ ሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት እንደመሆኑ፣ የጥናቱን ውጤት ወደ ሌሎች ክትባቶች ማጠቃለል አይቻልም፡፡ ጥነት ሲካሄድ ደግሞ አንዳንድ ያላሟቸው ነገሮች ስለሚኖሩ የጥናቱን ውጤት እንደ አስርቱ ትዕዛዛት ህግ ሙሉ መቀበል አይቻልም፡፡ ሆኖም የጥናቱ ጠንካራ ጎን ስለሚያመዝን እንደገና ቸር ወሬ ነው በማለት መቀበል ያስችላል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ከትባት በወቅቱ ማግኘት የማይችሉ ወገኖቻችን እያሰብን መሆን አለበት፡፡

ስለዚህ ክትባት መወሰድ ለግለሰብ በኮቪድ በሽታ ከመያዝ ብቻ ሳይሆን በቫይረሱ ከመያዝ የሚረዳ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በተጨማሪ ግን በቫይሱ የመያዝ ዕድሉም ስለሚቀንስ የቫይረሱን ሥርጭት በመቀነስ፣ ቤተሰብ፣ የሥራ ባልደረባንና በስፋትም ህብረተሰቡን ይጠቅማል ማለት ነው፡፡ ይህንን ጠቀሜታ እያዬ አለመከተብ ማለት ፍርዱን ለናንተ እተዋለሁ፡፡ ወደፊት ስለከትባቶች ልዩነት ሰለምገልፅ ተከታተሉ፡፡

መልካም ንባብ፣ አካፍሉ

የመጀመሪያው የሞደርና ክትባት የኮቪድ ተወሰደ፣ ከወር በኋላ ለሁለተኛው ዝግጁ ነን፡፡ 01/08/2021


ተከተቡ እያልን ስንሰብክ ከርምን፣ ባንከተብ እንታማ ነበር፡፡ እንደ ሌሎቹ የሥራ ባልደረቦቼና ጓደኞቼ ሁሉ፣ የሞደርናን ክትባት የመጀመሪያውን ተከተብኩኝ፡፡ ለአስራ አምስት ደቂቃዎች ቁጭ ብዬ ራሴን ማዳመጥ ነበረብኝ፡፡ ፕሮቶኮሉም እንደዛ ነው፡፡ አምስት ደቂቃዎች ይሆናሉ፣ ትንሽ ሞቅ የሚል ስሜት ተሰማኝና፣ ክፍሉ ነው ወይ ብዬ አሰብኩ፡፡ ሌላ ምልክት እስኪመጣ ድረስ፣ የአቦይን መያዝ የሚገልፁ ዜና አውታሮችን ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡ ምንም ተጨማሪ ስሜትም አልነበረም፡፡ መሄድ ትችላለህ ተባልኩና ወደ ቤት አዘገምኩ፡፡

ይህን ክትባት ስወስድ በአእምሮዬ፣ የኢንግላንድና የደቡብ አፍሪካውን ዝርያ እያስታወስኩ ነበር፡፡ ሰምታችሁ ወይም እየተከታተላችሁ ከሆነ፣ እነዚህ አዲስ የቫይረሱ ዝርያዎች ያሳዩት ባህሪ፣ ከሰው ወደ ሰው በፍጥነት መሸጋገርና በፍጥነትና በብዛት መራባት ነው፡፡ መጀመሪያ ከተከሰቱበት አገር ወጥተው በሌላው የአለም ክፍል እየታዩ ነው፡፡ በአሜሪካም መታየታቸው ተዘግቧል፡፡ እሰካሁን ድረስ የተረጋገጠው ነገር፣ በፍጥነት መሻገሩን ቢካኑትም የተለየ ከባድ ህመም የመፍጠር ወይም የመግደል ችሎታቸው አለመጨመራቸው ነው፡፡

ታዲያ ክትባት ከወሰድክ ምን አስጨነቀህ ሳትሉም አትቀሩም፡፡ መጨነቁ አግባብ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ቫይረሶች አዲስ ዝርያ ሲሆኑ፣ የሆኑበትም ምክንያተ ስፓይክ ፕሮቲን ተበሎ የሚጠራው ቫይረሱ ወደ ሰው ሰውነት እንደመግቢያ ቁልፍ የሚጠቀምበት አካሉ ላይ ለውጥ በማድረጋቸው ነው፡፡ ታዲያ ክትባቶቹ የተሠሩት ይህንን ፕሮቲን ኢላማ በማድረግ ነው፡፡ ኢላማ ያደረጉት ቀድመው የታዩትን የቫይረስ ዝርያዎች ስፓይክ ፕሮቲኖቸን ነው፡፡ ችግሩ ወይም አሳሳቢነቱ የሚመጣው፣ እነዚህ በፍጥነት እየተሠራጩ ያሉት አዲሶቹ ዝርያዎች፣ ለውጥ ያደረጉት የስፓይክ ፕሮቲኑ ላይ ከሆነ፣ ፕሮቲኑን ደግሞ ክትባቱ የሚፈጥረው እንቲቦዲ (የመከላከያ ሀይል) የማያወቀው ከሆነ፣ አገልግሎቱን ይስታል ማለት ነው፡፡ ባጭር አማርኛ፣ የተሠራው ክትባት አዲሶቹን ቫይረሶች ላይሸፍን ይችላል ማለት ነው፡፡ ታዲያ እንደዚህ ከሆነ፣ መጨነቁ አግባብ ነው፡፡ ለማንኛውም፣ ክትባትም ተወስዶ በቂ የህብረተሰቡ ክፍል እስኪከተብ ድረስ፣ የመከላከያ መንገዶች መቀጠል አለባቸው፤ ይቀጥላሉም፡፡ እንዲያውም አዳዲስ ቫየረሶችን ከመፈጠር የሚያግደው ወይም የሚቀንሰው፣ ቫይረሶቹ ከሰው ወደ ሰው እየዘለሉ መራባታቸውን ስንከላከል ነው፡፡ በተለይም አሁን፣ ክትባቱ እስሚዳረስ ድረስ፣ የመከላከያ መንገዶቹን ጠበቅ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

አሳሳቢነቱ ጠንከር ባለበት በዚህ ሁኔታ፣ አንደኛውን የmRNA ክትባት የሠራው የፋይዘር ካምፓኒ፣ ጥሩ ቸር ወሬ አካፈለን፡፡ በጃንዋሪ 6 ባወጣው የጥናት ውጤት፣ የፋይዘሩ ክትባት አዲስ የተከሰተውን ቫይረስም ይሸፍናል ይላል፡፡ ትርጉሙ ክትባቱ በዚህ በአዲሱ፣ ከኢንግላንድ በታየው ዝርያ ላይ ይሠራል ነው፡፡ ገና በአቻዎች ባልተገመገመው ባቀረቡት ጥናት የገለፁት፣ ከዚህ ቀደም የነሱን ክትባት የወሰዱ በጥናት ላይ ከነበሩ ሀያ ሰዎች በተሰበሰበ ደም ላይ፣ ከክትባቱ በኋላ በሰዎቹ ሰውነት ውስጥ የተፈጠረውን አንቲቦዲ በመውሰድ፣ ከዚህ ከአዲሱ ቫይረስ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ቫይረሶች ላይ ሊሠራ እንደሚችል በአሃዝ በተደገፈ መረጃ አቅርበዋል፡፡ ሞደርናም ቢሆን (ሌላኛው የmRNA ክትባት የሠራው ካምፓኒ) የነሱ ክትባትም አዲሱ ዝርያ ላይ ሊሠራ ይችላል ብለው ቀና ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን በመረጃ ለማስደገፍ ጥናት እንደሚያደርጉ ነው የተገለፀው፡፡

አሜሪካ፣ የነዚህን አዲስ የቫይረስ ዝርያዎች ሥርጭት ለማጥናት ዘግየት ብትልም አሁን በሙሉ ጉልበት እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ አሳሳቢነት ባለበት ሁኔታ፣ ደግሞ ደጋግሞ የሚታወቅ ነገር ቢኖር፣ አሁን ባሉት መከላከያ መንገዶች ሥርጭቱን መግታት ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን እየተሠራጩ ያሉትን ቫይረስ ዝርያዎች ክትባቶቹ ይሸፍናሉ እንበል፣ ግን ሥርጭቱ ከቀጠለ ደግሞ ቫይረሶቹ ፕሮቲናቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ቢያደርጉ የሚከተለውን ችግር መገንዘብ ትችላላችሁ፡፡ በዚህ መሀል ጥሩው ነገር፣ ይህ የmRNA ክትባት ቴክኖሎጂ፣ አዲስ የሚታዩ የቫይረስ ዝርያዎችን መሸፈን የሚያስችል ሌላ ክትባት በፍጥነት መሥራት የሚያስችል መሆኑ ይነገራል፡፡ ነገር ግን አስከዛ ድረስ ደግሞ ስንት ሰው ይለቅ? እናም መከላከያ መንገዱን ጠበቅ አድርጉ ብለን ብንማፀን የምትረዱን ይመስለኛል፡፡

ምናልባትም፣ በአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር፣ መጪው ፕሬዚዳንት ቃል የገቡት፣ በመቶ ቀናት ውስጥ መቶ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለመከተብ ነው፡፡ ትንሽ አከራካሪ የሆነው፣ የመጀመሪያውን ክትባት ለወሰድን ሰዎች፣ ሁለተኛው ክትባት መኖሩ መረጋገጥ አለበት ተብሎ በተከተቡ ሰዎች ልክ የሚሆን የተቀመጠው ክትባት ይውጣና ይሰጥ በማለታቸው ነው፡፡ ሞደርናም ሆነ ፋይዘር ምርቱን ጨምረው፣ የጀመሩ ሰዎች በሥርአቱና በታየው ጥናት መሠረት ሁለተኛውን ክትባት መውሰድ እንዲችሉ ካደረጉ፣  በመጀመሪው ዙር ብዙ ሰዎች መከተባቸው ጠቃሚ ነው፡፡ ልብ በሉ፣ በ2020 መጨረሻ ላይ እናደርጋለን ብለው የተናገሩት፣ ሀያ ሚሊዮን ሰዎች ለመከተብ ነው፡፡ አንኳን ሀያ ሚሊዮን ሊከትቡ፣ የተቀረበው ክትባት መጠን አስራ ሁለት ሚሊዮን ነው፡፡ እሱም ሆኖ አስካሁን የተከተቡ ሰዎች ቁጥር ከአምስት ሚሊዮን አልተሻገረም፡፡፡ ይህ ግን የመንገደኛው አስተዳደር ፕሮግራም ነው የነበረው፡፡ በክትባት ዕጥረት ምክንያት በመጀመሪያ የህክምና ባለሙያተኞች፣ ከዚያ ደግሞ የነርሲንግ ሆም ኗሪዎች እንዲሠጣቸው ነው የተተለመው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ዕደሜያቸው ከ75 አመት በላይ ወይም ከ65 በላይ ለሆኑ ሰዎች ነው፡፡ ሌሎች እንግዲህ ዘግየት ብሎ ይደርሳቸዋል፡፡ የሞደርናው ክትባት አንድ ብልቃጥ አስር ሰው ብቻ ነው የሚከትበው፣ ብልቃጡ ከተከፈተ አስከ ስድስት ሰአታት ባለው ጊዜ ወስጥ አስር ሰዎች ካልወሰዱት ይደፋል፡፡ ህም፣ የሰማሁትን ላካፍላችሁ፣ ከሚደፋ ተብሎ፣ ፕሮግራሙ ውስጥ የለሉ ሰዎች ከተገኙ በሞተ ከዳ እየተሰጣቸው ያላሰቡት ሲሳይ አግኝተዋል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ የራሳቸውን ሠራተኞች ለዚህ ሲሉ በተንጠቀቅ እያስጠበቁ ድንገት ለመከተብ ፕሮግራም የያዘው ሰው ቢቀር ተጠባባቂዎቹ እንዲወሰድ እያደረጉ ነው፡፡

ክትባቱን ቶሎ ያላገኙ ሰዎች አንድ ያልታሰበ ጠቀሜታ አግኝተዋል፡፡ ምክንያቱም፣ ክትባቶቹ በስፋት ሲሰጡ በጥናት ላይ ያልታዩ ዳርቻ ጉዳቶች (Side effects) ይከሰታሉ፡፡ ይህ ደግሞ በመድሐኒቶችም ቢሆን የተለመደ አሠራር ነው፡፡ እናም ከነሱ በፊት ወደ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ሲከተቡ ትልቅ ክፉ ነገር ወይም ጉዳት ቢኖር እስካሁን ይታወቅ ነበር፡፡ ባለመኖሩ ክትባቱን የሚጠራጠሩ ወይም የሚፈሩ ሰዎች መጀመሪያ በወሰዱት ሰዎች በመመርኮዝ መረጋጋት ይችላሉ፡፡ እስካሁን የታየ ነገር ቢኖር፣ ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ የሚወድቁ ሰዎች ቁጥር ነው፡፡ ያም ከአንድ ሚሊዮን መሀል ወደ አስራ አንድ ሰዎች ላይ ነው፡፡ እስካሁን በሚታወቀው፡፡ ይህ ድንገተኛ መውደቅ በአንግሊዝኛ Anaphylaxis ይባላል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በሌሎች ክትባቶች፣ መድሐኒቶችም ላይ የሚታይ ነገር ነው፡፡ በህክምናም መዳን የሚችል ነገር ነው፡፡ በቀላሉ ኢፒነፍሪን የተባለ መድሐኒት በመርፌ መልክ መስጠት ነው፡፡ እንደዚህ መድሐኒት ወይም ክትባት ወስደው ይህ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች፣ አዲሶቹን ክትባት እንዲወስዱ ተደርጎ፣ ለሰላሳ ደቂቃ እዛው አንዲታዩ ይደረጋል፡፡ ከነበረዎት ይናገሩ፡፡ የተከለከለ ሁኔታ ቢኖር፣ የመጀመሪያውን የኮቪድ ክትባት ሲወስዱ ይህ Anaphylaxis የታየባቸው ሰዎች ሁለተኛውን ክትባት እንዳይወሰዱ ይደረጋል፡፡

ሁላችሁም መከተብ የምትችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ተስፋው አለ፡፡ ጥያቄው፣ መቼ ነው የሚለው ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ላለመያዝ መደረግ የሚገባውን እናድርግ፡፡ ይህ ቫይረስ በትንሽ ፐርሰንት ለአመል ያህል የመግደል ችሎታውን ከጨመረ፣ ምን አይነት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ገምቱ፡፡ ተይዛችሁ የዳናችሁ ወይም የበሽታ ስሜት ያልታየባችሁ ሰዎች በተለይ በደንብ አስቡበት፡፡ ለምንና እንዴት እንደተያዛችሁም ከናንተ በላይ የሚያውቅ የለም፡፡ በዚሁ ይማረን ብሎ ጥንቃቄውን መቀጠል፣ ሌሎችንም መምከር ሰብአዊ ግዴታ ነው፡፡
መልካም ንባብ