​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

ከሚጠበቀው በላይ ሞት ሲከሰት ትርፍ ሞት የሚባል ነገር አለ ወይ? 10/20/2020

ይህንን ጉዳይ ለህብረተሰቡ ማድረስ ተገቢ ነው፡፡ በቴሌቪዢን ወይም በደረ ገፅ በሚነገሩ ወይም በሚታዩ ቁጥሮች ብቻ በመመርኮዝ ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ማየት ያስከትላል፡፡

በኮቪድ-19 ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርና ከዚያም ጋር ተያይዞ የሚሰላው ስሌት በትክክል የሞቱን ቁጥር ይገልፃል ወይ ብሎ መጠየቅ አግባብ ያለው ነገር ነው፡፡ የምንያቸው አሃዞች ትክክል ናቸው አይደሉም፣ ቁጥሮች ትክክል ናቸው፣ ግን ሁኔታውን በደንብ ይገልፃሉ ወይ፡፡ ይህ ዝርዘር አመለካከት፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የመሰሉ ሀገራት ላይ ወሳኝነት የሚኖረው ነገር ነው፡፡

የምናያቸው ቁጥሮች በቂ አይደሉም ለሚለው ክርክር

  1. እንደ ህክምና ባለሙያተኛ የምናውቀውም ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ሁሉ በምን እንደሞቱ ምርመራ አይደረግም፡፡ ሰለዚህ በኮቪደ-19 ይሙቱ ወይም በሌላ ምክንያት ግልፅ አይሆንም፡፡ ሰለዚህ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎችን አጠቃላይ ቁጥር ማወቅ አይቻልም፡፡ እንደ ቦታው ይብዛ ይነስ እንጂ፣ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሚነገረውና ከሚታወቀው በላይ ነው፡፡ በተለይም በቂ የኮቪድ-19 ምርመራ በማይደረገበት አካባቢ ወይም አገር ትክክለኛውን ቁጥር ቀርቶ ግምቱን ማግኝት ይከብዳል፡፡
  2. በሌላ በኩል፣ በኮቪደ-19 ከተያዙ ሰዎች መሀል ይህን ያህል ሞተዋል ብሎ የወጣውን ስሌት ማቅረብም ትክክለኛውን መጠን አይገልፅም፡፡ በሰሌት ከመጣ፣ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች በሙሉ ተመርምረው ሪፖርት ውስጥ ካልገቡ በስተቀር፣ ስሌቱ ከሚገባው በላይ ከፍ ሊልም ይችላል፡፡ ስሌት ስል፣ በፐርስንት ሲገለጽ ነው፡፡
  3. ይህ ቫይረስ ግን ተቀበልንም አልተቀበልንም፣ ሕይወታቸው የሚያልፉ ሰዎችን ቁጥር የሚያገኘው በፐርሰንት ሳይሆን በብዛት በመሠራጨት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ሊቀየር ይችላል፡፡ ሰለዚህ የሁሉም ሰው አትኩሮት መሆን ያለበት ሥርጭቱን ለመግታተ በመረባረብ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ ዞሮ ዞሮ የሚገለው ሰው ያገኛል፡፡ የራሴ አባባል ነው፡፡


 በዚህ መሀል የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ብዛት ለመገመት ሌላ አቀራረብ ወይም አመለካከት አለ፡፡ ያም በየአመቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ግምት የታወቀ ሲሆን፣ አሁን ከዚያ ከሚታወቀው ግምት በላይ ብዙ ሰው ከሞተ (Excess Death)፣ ምን ያህል ሰው ሞተ፣ ከሆነስ ደግሞ ምክንያቱ ምንድነው ተብሎ በመጠየቅ የሚቀርብ ሪፖርት አለ፡፡ ወጥቷልም፡፡

 ይህንን አስመልክቶ የአሜሪካው ሲዲሲ ባወጣው መረጃ፤ ከሚጠበቀው በላይ ብዙ ሰዎች እንደሞቱ ይነገራል፡፡ ምን ያህሉ ትርፍ ሞት ነው፣ ምን ያህሉስ በኮቪድ ምክንያት ነው፣ ከሞቱስ እነማናቸው እየሞቱ ያሉት ለሚሉ ጥያቄዎች፡

በኦክቶበር 20፣ 2020 አስቀድሞ በተለቀቀው ሪፖርት መሠረት፣ ከጃንዋሪ 26 አስከ ኦክቶበር 3 ባለው ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ

በግልፅ የሚጠቀሰው ቁጥር 216 025 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ቢሆንም፣ ይህ ቁጥር ግን በወረርሽኙ ምክንያት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር አሳንሶ ነው የሚነግረው፡፡

ከጃንዋሪ እሰክ አክቶበር 3 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ባጠቃላይ በየአመቱ ከሚጠበቀው በላይ 299 028 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከነዚህ መሀል ሁለት ሶስተኛው በኮቪድ-19 ምክንያት ነው የተባለው፡፡ ከማርች አስከ 1፣ አስከ ኦገስት 1 ባለው ጊዜ ውስጥ በወጣው ሪፖረት ባጠቃላይ፣ 1 336 561 ሰዎች መሞታቸው ሲታወቅ፣ ይህ ቁጥር ያሳየው፣ የሞቱትሰ ሰዎች ቁጥር ከሚጠበቀው በላይ በሀያ 20 ፐርስንት ከፍ ያለ ነበር፡፡ እንግዲህ በሁለቱም ሪፖረት ብትመለከቱ፣ በዚህ አመት ብዙ ሰዎች ከሚጠበቀው ቁጥር በላይ እንደሞቱ ነው፡፡ በዚህኛው ሪፖረትም፣ ትርፍ ሞት ተብሎ ከተመዘገበው መሀል ሁለት ሶስተኛው ትርፍ ሞት በኮቪድ-19 ምክንያት ነው፡፡

በወራት ለይተን ብንመለከት፣ ከፍተኛ የሆነ ከሚጠበቅ በላይ የሰዎች ሞት የተመዘገበው በአፕሪል 11 አካባቢ በትርፍ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 40ፐርስንት፣ እና ደግሞ በኦገስት 8 አካባቢ ትርፍ ሞት በ23.5 ፐርስንት ነበር፡፡ በነዚህ ወራትም ሁለት ሶስተኛው ትርፍ ሞት ምክንያት ኮቪድ-19 ነበር፡፡

በዕድሜ ሲታይ ማነው እይሞተ ያለው ለሚለው ጥያቄ፣ ከፍተኛው የሞት ቁጥር የታየው ዕድሜያቸው ከ75-84 አመታት በሆኑ ሰዎች ሲሆን አነስተኛው ደግሞ ዕድሜያቸው ከ25 አመት በታች በሆኑ ሰዎች ነው፡፡ እንደዛ ሆኖ ግን በጥልቀት ሲታይ፣ ካለፉት አመታት ጋር ሲነፃፀር በዚህ አመት፣ ከሚጠበቀው ቁጥር በላይ በመሞት ከፍተኛውን ልዩነት ያሳዩት ዕድሜያቸው ከ25-44 አመታት ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ በፐርስንት 26.5 ዘንድሮ በብዛት ሞተዋል ነው ነገሩ፡፡ በዕድሜ ሲታይ ባጠቃለይ

ዕድሜ ገደብ            ሞት በፐርሰንት
< 25                           2.0              
25-44                        26.5
45-64                        14.4
65-74                        24.1
75-84                        21.5
> 84                           14.7

በዘር ተለይቶ ሲታይ፣ ከሚጠበቀው በላይ የሞቱ ነጮች ቁጥር ከፍተኘውን ደረጃ ይዞ 171 491 ነው፡፡ ከ2015 እሰከ 2019 ባሉት አመታት ጋር ሲነፃፀር ትርፍ የሞት ቁጥሩ ለነጮቹ በ11.9 ፐርስንት ከፍ ብሏል፡፡ በጣም መጠነኛ ቁጥር ሆኖ የተገኘው፣ በአሜሪካን ኢንዲያንስና በአላስካ ኔቲቮች ነው፡፡
ነገር ግን በሞት ቁጠር ከመጣ ካላቸው  የህዝብ ብዛት ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ የሞት ቁጥር ያስመዘገቡ ሌሎች አሉ፡፡

ዝርያ                                        ከሚጠበቀው በላይ የሞት መጠን በፐርሰንት
ሂሰፓኒክ                                                  53.6
አሜሪካን ኢንዲያን አላስካ ኔቲቭ                     28.9
ጥቁር                                                      32.9
ዝርያ ያልታወቀ                                          34.6
ኤስያውያን                                               36.6

ይህ ሪፖርት የወረርሽኙን ክፋት ለመገመት ወደሚያስችል ውነታ ያስጠጋናል፡፡ ነገር ግን፣ ታዳጊ በሚባሉ አገሮች፣ ለኮቪደ-19 የሚደረገው ምርመራ በቆሙባቸው አካባቢ ወይም ከአቅም በላይ በሆነበት ቦታ፣ በየአመቱ የሚሞተውን ሰው ቁጥርና፣ ኮቪድ-19 ከመጣ በሁዋላ እየሞተ ያለውን ሰው ቁጥር ማግኘትና ማነፃፀር ተገቢ ነው፡፡ ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ ይታወቃል፣ ነገር ግን ምርመራ ካልተደረገ በስተቀር በወረርሽኙ ይሁን በሌላ ምክንያት መሆኑ አይታወቅም፡፡ ምናልባትም የቅርብ ቤተሰብ ሊያውቅ ወይም ሊገምት ይችላል፡፡ በዕድሜ የገፉ ሰዎች በየትኛውም የአለም ክፍል፣ የዚህ ወረርሽኝ ሰላባ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ በአደባባይ ከሚነገረው ቁጥር ወጣ ብሎ ሰፋ አድርጎ ማሰብም ያስፈልጋል፡፡ መልክቱ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ ወደነዚህ ተጠቂ ሰዎች አንዳይደርስ ጥረት፣ ርብርብ መደረግ አለበት፡፡ በጣም ቀላሉ፣ ማስክ በእግባቡ ማድረግና የስድስት ጫማ ወይም የሁለት ሜትር ርቀት መጠበቅ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ይህንን ለማድረግ እንኳን በቂ ሰው አልሞተም በማለት ትንተና በማድረግ መከላከሉ ላይ የሚደረገውን ርብርብ ላይ ከፍተኛ አትኩሮት እንዳይኖር የሚያደርግ ትንተና የሚያቀርቡ ፊደል የቆጠሩ ሰዎች እንዳሉ መስማቱም ያሳዝናል፡፡

ትርፍ ወይም ከሚገባው ቁጥር በላይ ሰዎች ሞተዋል፣ ከነሱ መሀል ሁለት ሶሰተኛው በኮቪድ-19 ነው የሚል ተከታታይ መረጃ ወጥቷል፡፡ የቀረው አንድ ሶስተኛው የሟች ቁጥር፣ በበራሱ በኮቪድ-19፣ እናም ደግሞ በወረርሽኙ ምክንያት በቂ ከትትል ባለማግኘት በሌላ በሽታ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ይጨምራል፡፡ ሰለዚህ በኮቨድ-19 የሞተውን ሰው ብቻ ስንቆጥር፣ የህክምናው አቅም ባነሰበት ሁኔታ ወይም በወረርሽኙ ምክንያት የህክምና ባለሙያተኞችም ሆነ የመታከሚያ ቦታው መታወክ የሚየስከትለውን ቸግር መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡ የህክምና ባለሙየተኞች ተጋልጠው ለአስራ አራት ቀናት የሚገለሉ ከሆነ፣ የሆስፒታል አገልግሎት መስጫዎች በኮቪድ-19 የሚጥለቀለቁ ከሆኑ፣ በቀጥታ ባይሆንም በህክምና ዕጥረት ምክንያት ኮቪድ-19 እየገደለ ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ በግንባር ለሚሰሩ ሠራተኞች ትኩረት ተሠጥቶ፣ በቂ መከላከያ እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ የሆነው፡፡ አለ የሚባለውን የግላቭ ዕጥረት መስማትና የሚቻለውን መርዳት ጥሩ ነው፡፡

 ከመዝጋቴ በፊት ሰለ ግድየለሾቹ ወይም በውነት የአኮኖሚው ችግር ከፍቶባቸው አደጋ ላይ ሊወድቁ በሚችሉበት ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን አመለካከት ማሰተዋል ተገቢ ነው፡፡ ጭፈራ ቤት እዚህ ውስጥ መግባትም የለበትም፡፡ ሰለ ኢኮኖሚ የሚጨነቁ ሰዎች፣ መጀመሪያ ማድረግና መተባበር ያለባቸው ሥርጭቱ እንዲቀንስ ማድረግ ነው፡፡ ያንን ሳያደርጉ ለበሽታው በከፍተኛ መሠራጨት ምክንያት መሆን፣ ከዛም ወደየቤቱ እየወሰዱ ለደጋጎቹ ህይወት ህልፈት ምክንያት መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ራሳቸው በሚያደርጉተ ነገር ኢኮኖሚውን መልሰው እየጎዱት መሆኑን ቢገነዘቡ፡፡ ሠርቶ ለማደር በሚጥረው ሰው እንጀራ ላይ አመድ እየነሰነሱ መሆኑን ቢረዱ ጥሩ ነበር፡፡ በቫይረሱ ተይዘው ወደ ሥራ ቦታ መሄድ፣ የሥራ ቦታው የግድ ቢዘጋ የማን ያለህ ሊባል ነው፡፡ እንዳየነው ከሆነ፣ የዚህን ቫይረስ ሥርጭት ፊት ለፊት ተጋፍጠው የመከላከያ መንገዶችን የተጠቀሙ ሀገራት ወደነበሩበት የኢኮኖሚ ሁኔታ እየተመለሱ ነው፡፡ መስማት እየተቸገርን ነው፡፡ የውቅቱ ፈርኦኖች በቫይረሱ ሲያዙ እያየን ነው፡፡ ለሌላ ጊዜ፡፡

የ1918 የህዳር በሽታም ቢሆን፣ በሚያዝያ ታይቶ በህዳር ተመልሶ ነው የመጣው፡፡ ያስከተለውን ችግር እንደታሪክ ማወቅ ከፈለጋችሁ ድረ ገፁ ላይ ያለውን ትረካ አዳምጡ፡፡ ይህ ቫይረስ ሁሉንም ነገር ተክኖታል፡፡ የቀረው ነገር ቢኖር የመገደል ችሎታውን መጨመር ነው፡፡ ከዚያ ግን ሁላችንም ፈጣሪ ይጠብቀን፡