​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

አልማዝን አይቼ  አልማዝን ሳያት
ሶስተኛዋ አልማዝ ብትመጣ ድንገት  (01/04/21)


ከጥላሁን ገሠሠ ዘፈኖች የአንደኛው ማቀንቀኛው ግጥም ላይ የተወሰደ ነው፡፡ ሆኖም፣ አብሬ ሄድኩና መድፊያው ላይ ግን ተለያዬን፡፡ አሱ ያለው፣ ሶስተኛዋ አልማዝ በትመጣ ድንገት፣ ሁለቱን አልማዞች ሰላስረሳችኝ፣ ምርጫዬ በምርጫ ተበላሸብኝ ነበር

ምን ሊል ፈልጎ ነው ሳትሉ አትቀሩም፡፡ ያው የተለመደው ህክምና ነው ብላችሁም የደመደማችሁም ትኖራለችሁ፡፡ ውነት ነው፡፡ ሰለ ኮቪድ ክትባቶች ነው የምገልፀው፡፡ ከአሁን በፊት ፈቃድ ተሠጥቷቸው ሥራ ላይ ስለዋሉት፣ የፋይዘርና የሞደርና ክትባቶች፣ ያለውን መረጃ በመመርኮዝ፣ ሁኔታውን ከማብራራት በተጨማሪ ክትባቶችን እንድትወስዱ ስመክር ሰነበትኩ፡፡ በዚህ ውጥረት መሀል፣ 57 ከሚሆኑት ጥናት ላይ ካሉ ክትባቶች፣ ሶስተኛው በቅርቡ ተፈቀደ፡፡ አሱም አስትራ ዜኔካ የሚባል ካምፓኒ የሚሠራው ነው፡፡ ብዙ የህዝብ ጤና ባለሙያተኞች ፈቃድ መሠጠቱን በፀጋ መቀበል ብቻ ሳይሆን ክትባቱ በርካሽ ዋጋ መቅረቡንና ለሥርጭትም አመቺ መሆኑን በማመስገን ተናግረዋል፡፡

ህም፣ የጥላሁን ገሠሠን ሶስተኛዋ አልማዝ አስታወስኩ፡፡ በኔ በኩል በርግጥ የሶሰተኛዋ አልማዝ መምጣት ምርጫ የሚያበላሽ ነገር ቢሆንም፣ ጥላሁን እንደሚለው፣ ቀድመው የመጡትን ሁለቱን አልማዞች ስላስረሳች አይደለም፡፡ ይልቁንስ፣ አዲስ የመጣው ክትባት፣ ቀድመው ከመጡት ጋር ሲነፃፀር ማስረሳት ሳይሆን የቀደሙትን አጥብቆ መያዝ እንደሚበጅ የሚያሳሳብ ነገርም ሰላለ ነው፡፡ ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡

አንደኛ፤ ጉዳት ኖረው አልኖረውም፣ ይህ ሶሰተኛው ክትባት የሚሠጠው በሌላ አዴኖ ቫይረስ በሚባል ቫይረስ ተሸካሚነት ነው፡፡ አዎ እንደሱም ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም በዚህኛው ክትባት ማለትም በአስትራ ዜኔካው፣ ለክትባት አገልግሎት የሚውለው የኮሮና ቫይረስ የተወሰነ ፕሮቲን ነው፡፡ ያ ፕሮቲን ደግሞ ብቻውን ወይም ሌጣውን መቆየትና መሠጠት ሰለማይችል የግድ ማጓጓዣ ነገር ያስፈልገዋል፡፡

ሁለተኛ፤ በራሳቸው በአስትራ ዜኔካ ጥናትም ቢሆን፣ የመከላከል አቅም በፐርስንት ሲታይና ቀድመው ከመጡት አልማዞች ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ ነው፡፡ የፋይዘርና የሞደርናው ክትባቶች፣ በጥናታቸው ያስመዘገቡት፣ ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች መሀከል ሁለቱም ከ94% በላይ የሆኑቱን ከቫይረሱ ከመያዝ ያስጥላሉ ነው፡፡ አዲስ የመጣው ግን፣ እንደምንም ብሎ 60 ወይም 70% ብቻ ነው፡፡ በተለየ የክትባት መጠን አሰጣጥ ማለትም፣ የመጀመሪያውን ክትባት አነስ ያለ መጠን ሰጥተው በሚቀጥለው መጠን (ዶዝ) መደበኛውን በወሰዱት ሰዎች ላይ የመከላክል አቅሙ 90% ይደርሳል ይላሉ፡፡ የዚያ ምክንያት ግልፅ አይደለም፡፡ ነገር ግን መደበኛ የሆነውን የክትባ መጠን በ28 ቀናት ልዩነት ለወሰዱ ሰዎች ተመልሶ 70% ነው፡፡ ይህ በራሱ አትኩሮት ሠጥተን የምንነጋገርበት ጉዳይ ነው፡፡ አንግዲህ ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገፅ እንደተቀመጠው የህብረተሰብ የጋራ የመከላከል አቅም (Herd Immunity) ለመገንባት ምን ያህል ሰው መከተብ አለበት የሚል ወሳኝ ጥያቄ አለ፡፡ በአሜሪካ የሚታሰበው ህብረተሰቡ አስከ 85% የሚሆነው መከተብ አለበት፡፡ ያ እንግዲህ 94-95% የመከላከል ችሎታ አለው በሚባል ክትባት በኩል ሊታሰብ የሚችል ግብ ነው፡ ማለትም 100% ህብረተሰቡ ሳይከተብ የሚፈለገው ግብ ላይ ሊደረስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን፣ የመከላከል አቅሙ 70% በሆነ ክትባት፣ እንዴት ተደርጎ የሚለውን ስሌት አስቡት፡፡

ሶሰትኛ፡ ይህ አዴኖ ቫይረስ በተሸካሚነት ለሌሎች ክትባት የጥናት አግልግሎት ላይ ውሎም ያውቃል፡፡ ትንሽ ቅር የሚያሰኝ ሪፖረት የተጠቀሰው፣ Lancet በሚባል መፅሄት ነበር፡፡ ያም ኤች አይ ቪ (HIV) ጋር በተያያዘ ባለሙያተኞች የጠቆሙት ነገር አለ፡፡ ነገሩ ቀደም ያለ ነው፡፡ ይህንን ያነሳሁት በሶሻል ሜዲያ ይሆን በግል ሀሳብ ልውውጥ ላይ፣ ክትባቱ HIV ያስይዛል እያሉ ነው ብሎ የነገረኝ ሰው ሰላለ ነው፡፡ ምናልባትም የዚች የክትባና የኤች አይ ቪ ፍንጭ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆን አለበት፡፡ ትንሽ ፍንጭ ከተገኘ እንደተለመደው ሰፋ እያለ ከፍንጩ ርቆ ሌላ ሆኖ ይወራል፡፡ ትዝ ያለኝ ነገር፣ በሬዲዮ መሆን አለበት የሰማሁት፣ በአዲስ አበባ፣ በለገሀር (ላጋር)፣ ሁለት ባዶ ጀንያዎች ጠፉ ተባለ፣ እና ወሬው አዲሱ ገበያ ሲደርስ፣ ጆንያዎች ብር ተሞልቶባቸው ተገኝ፡፡ ሰለዚህ የዚህን የኤች አይቪና የአዲኖ ቫይረስ ግንኙነት ማብራራት ይኖርብኛል፡፡ የሆነው ምንድን ነው፣ አዴኖ ቫይረስ ተሸካሚ የሆነበት ለኤችአይቪ መከላከያ ክትባት ጥናት ላይ ያዩትን አሳሳቢ ነገር ነው ባለሙያኞች የሚያስጠነቅቁት፡፡ በዚያን ጊዜ በተደረገው ጥናት፣ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች፣ ጭራሽ ኤችአይቪ መከላከል ሳይሆን የበለጠ ሲያዙ በመረጃ ስለደረሱበት ነው፡፡ [i] ያ ደግሞ የታየው ከዚህ በፊት በአዴኖ ቫይረስ (የክትባት ተሸካሚው) ተይዘው የነበሩና መያዛቸው ደግሞ በምርመራ ተረጋግጦ በነበረ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ዝርዝሩን ሰፋ አደርገው ማንበብ ለሚፈለጉ ማጣቀሻውን አስቀምጫለሁ፡፡

ነገር ግን ይህንን ችግር ለመወጣት፣ አጥኝዎቹ ያደረጉት ነገር፣ አዴኖ ቫይረሱን ለተሸካሚነት ሲመርጡ፣ ሰዎች ከዚህ በፊት አይተውት የማያውቁ ወይም ያልተጋለጡበት የአዴኖ ቫይረስ ተጠቀሙ፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም ሰዎች ተጋልጠው የነበረው የሰው አዴኖ ቫይረስ ዝርያ ቢጠቀሙ፣ ሰውነት ለተጋለጠው አዴኖ ቫይረሰ መከላከያ አዘጋጅቶ ከነበረ፣ ክትባቱ በቫይረሱ ተጭኖ ሲገባ፣ ሰውነት መከላከያ አንቲቦዲና አጥቂ ሴሎችን በመላክ፣ ተሸሚውን ቫይረስ ከነ ክትባቱ ድራሹን ያጠፋዋል፡፡ ያ ነው አንግዲህ በኤችአይቪ የክትባት ሙከራዎች ላይ የታየው፡፡ በዚህ በአስትራ ዜኔካው፣ የተጠቀሙት ተመልሶ መራባት የማይችል የቺምፓንዚ አዴኖ ቫይረስ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ክትባቱን የተሸከመው መራባት የማይችለው የቺምፓንዚ አዴኖ ቫይረስ በሰው ሰውነት በጠላትነት ስላልተመዘገበ፣ የአስትራ ዜኔካው ክትባት ቸግር አያጋጥመውም፡፡ ይህ ክትባት በኢንግላንድ ጊዜያዊ ፈቃድ ቢሰጠውም፣ በአሜሪካ በጥናት ላይ ነው፡፡ እናም ተስፋ የምናደርገው በዚህ በአሜሪካው ጥናት ውጤት የበለጠ መረጃ እናገኛለን፡፡

አራተኛ፡ ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች ላይ የሚታያው ዳርቻ ጉዳት (Adverse effect) Lancet በሚባለው መፅሄት በዲሴምበር 8 ታትሞ ወጥቷል[ii]፡፡ ዝርዝሩን በሌላ ጊዜ መነጋገርም ይቻላል፡፡

ወደ አልማዞች ስንመለስ፣ እንደ አውነቱ ከሆነ፣ የነዚህ ቀድመው የመጡት አልማዞች ችግር፣ የፋይዘርን ብንመለከት፣ ለማስቀመጥ የሚያስፈልገው የቅዝቃዜ መጠን መጠበቅ የሚችሉ ተጨማሪ ማጓጓዣዎች ወይም ማስቀመጫዎች ተጨማሪ ነገሮች ማስፈለጋቸው ነው፡፡ በሞደርናው ከመጣን ደግሞ የቅዝቃዜ ችግር የለበትም፣ ነገር ግን ሁለቱም ከአዲሷ አልማዝ ጋር ሲወዳደር ዋጋቸው ውድ ስለሆነ ነው እንጂ፣ ምርጫችን ግልፅ ነው፡፡ ከተገኘ ደገኛዋን የፋይዘር አልማዝና የወይናደጋዋን የሞደርና አልማዞችን ጠበቅ ማድረጉ ይበጃል፡፡
[i] Use of Adenovirustype-5 vectored vaccine: a cautionary tale https://www.thelancet.com/journals/lancet/article/PIIS0140-6736(20)32156-5/fulltext
[ii] Oxford-AstraZeneca COVID-19 vaccine efficacy: https://www.thelancet.com/journals/lancet/article/PIIS0140-6736(20)32623-4/fulltext