Health and History

ማስክ 

 የኮቪድን ሥርጭት ለማቀዝቀዝ አይነተኛ ከሆኑ መንገዶች አንደኛው፣ አፍና አፍንጫን መሸፈን ነው፡፡ ይህ ለምን እንደሚጠቀም ወይም ለምን እንዳሰፈለገ ሰዎች በትክክል መገንዘብ አለባቸው፡፡

1ኛ. ቫይረሱ ለመሠራጨት አንዱ ትልቁ ምክንያት በቫይረሱ ተይዘው የበሽታ ስሜት የሌለባቸው ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ ይህ ቁጥር አሰቃቂ በሆነ ደረጃ አስከ ስልሳ ፐርሰንት ድረስ ሊወጣ ይችላል፡፡ ጉዳዩ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አያውቁም፡፡ ሰለዚህ ከሰው ጋር መቀላቀልና ቫይረሱን የማሰተላለፍ አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ከነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ የበሽታ ስሜት ይጀምራቸዋል፤ ግን ቫይረሱ መተላለፍ ከጀመረ ቆይቷል፡፡

2ኛ. ይህ ቫይረስ በትንፋሽ አማካኝነት እንደሚተላለፍ ይታወቃል፡፡ ዋናው መተላለፊያ መንገድም ይኸው ነው፡፡ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ሲየስሉ ወይም ሲያነስጥሱ፣ በመተንፈሻ አካላቸው ውስጥ የተሰገሰገውን ቫይረስ ወደ አየር ይበትኑታል፡፡ በተለይም እርጥበት አዘል በሆኑት በ5 ማይክሮን መጠን በሚሆኑት ጠብታዎች ውስጥ የቫይረሱ መጠን በጣም ከፍተኛ በሆነ ደረጃ ነው የሚገኘው፡፡ ለምሳሌ በአንድ ጠብታ (ድሮፕሌት) ከ700ሺ በላይ የቫይስ ኮፒዎች ወይም ከዛ በላይ እንደሚገኙ የታወቃል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ይህን ያህል ቫይረስ የተሸከመው ድሮፕሌት የሌላ ሰው፣ አፍ፣ አፍንጫና አይን ላይ ሲያርፍ በቀላሉ ዘልቆ በመግባት (ኢንፌክሽን) የሚፈጥረው፡፡ በክብደታቸው ምክንያት በአብዛኛው ከስድስት ጫማዎቸ ወይም ሁለት ሜትር በላይ ርቀው የማይሄዱት እነዚህ ለአይን የተሠወሩ ጠብታዎች (ድሮፕሌት) በአስቀያሚው ክልላቸው ውስጥ ያልጠረጠረ ሰው ከተገኘ፣ ተያዘ ማለት ነው፡፡ ራቅ በሉ የሚለው መልክትም የመነጨው ከዚህ ነው፡፡

ችግሩ፣ ማስነጠስም ማሳልም ሳይኖር በተራ ንግግር፣ እነዚህ ቫይረሱን የተሸከሙ ጠብታዎችን ማመንጨት እንደሚቻል ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ታዲያ በቫይረሱ መያዙን ያላወቀ ሰው አጠገቡ ሆነው የቤተ ዘመድም ይሁን የጓደኛ ወሬ እያወራ ቫይረሱን ወደስዎ እያቀበለዎ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡
ለዚህ ነው፣ ሁሉም ሰው ማስክ ያድርግ የሚለው ወሳኝ ምክር የመጣው፡፡
አፍና አፍንጫውን ሳይሸፍን የሚጠጋዎት ሰው ካለ፣ ወይም መልክቱ አልገባውም፣ ወይም አልደረሰውም፣ አለዚያ ግን የወዳጅነት መቀራረብ ለመሆኑ ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡
ዋናው መንገድ፣ ሁሉም ሰው በቫይረሱ እንደተያዘ አይነት በማሰብ፣ ለሌላ ሰው ላለማስተላለፍ በማለት በሰብአዊነት ስሜት አፍና አፍንጫን መሸፈን የዘመናዊነት አስተሳሰብ ምልክት ነው፡፡ ከታናሽ ወንድሜ ጋራ በዚህ ጉዳይ ስንወያይ አንድ የነገረኝ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ወደ ሆነ መስሪያ ቤት ለመግባት አንድ ላይ የመጡ ሁለት ወንዶች፣ አንደኛው ማስክ ያለው ሲሆን፣ ማስከ የሌለው ባለጉዳይ ሰለነበር፣ ወደ መስሪያ ቤቱ መግባት ነበረበት፡፡ አብሮት የመጣው ሰው በለጋስነት አፉ ላይ የነበረውን ማስከ አውልቆ፣ ይህንን አድርገህ ግባ ብሎ ሲያውሰው እንደተመለከተ በመገረም ነገረኝ፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር ይሏል ይች ነች፡፡
የከተማው ሰው ማሰክ ለማድረግ ይተራመስ እንጂ፣ የገጠሩ ያገሬ ሰው፣ አፍና አፍንጫውን በጋቢ ከሸፈነ ይበቃዋል፡፡ ለዛም ሁለት ሜትር በላይ ርዝመት ያለውን ዱላውን ወይ በትሩን ይዞ የሚጠጋውን ሰው እየመተረ ራቅ ካለ፣ ከመያዝ ያመልጣል፡፡ ይህ ደግሞ ለገጠሬው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሰለዚህ የገጠር ዘመዶቻችን ማስክ ከማደል ድነናል ማለት ነው፡፡ በፎቶው እንዳያችሁት፣ አፍና አፍንጫቸውን ሸፈን እንዲያደርጉ መምከር ተገቢ ነው፡፡
ተራው ማስክ የበለጠ አገልግሎት ያለው በቫይረሱ ከተያዘ ሰው የሚወጣውን ቫይረስ ገድቦ ለማስቀረት ሰለሆነ፣ በእንግሊዝኛው አጠራር Universal masking የሚለው ምክር ወሳኝ ነው፡፡

ችግሩ፣ በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች ጋር የሚሠሩት የጤና ባለሙያተኞች ላይ ነው፡፡ እያቃሰተና እያሳለ ከሚወራጭ በሽተኛ አጠገብ ሆነው ርዳታ ለመስጠት የሚታገሉት የጤና ባለሙያተኞች፣ እንደ አውነቱ ከሆነ በቂ መከላከያ ካላደረጉ፣ በቫይረሱ ለመያዝ፣ ባሉበት ከበሽተኛው ጋራ ባላቸው ቅርበት፣ ሁለት ደቂቃ ይበቃል፡፡

ልብ በሉ፤ አንድ የጤና ባለሙያተኛ፣ ነርስ ወይም ሀኪም ከተጋለጠ፣ መጋለጡም ከታወቀ፣ ለአስራ አራት ቀናት ከሥራ ይገለላል፡፡ እንደዚህ የተጋለጡ ሰዎች ደግሞ በብዛት የሚወጡ ከሆነ፣ የሠራተኛ ዕጥረት መፈጠሩ ግልፅ ነው፡፡ በርግጥ ይህን የሠራተኛ ዕጥረት በማየት የተጋለጡ ወይም በቫይረሱ የተያዙ ባለሙያተኞች በሰባት ቀን ወደ ሥራ እንዲመለሱ የሚለው ህግ ተሸሮ ወደ አስር ቀን ተራዝሟል (በአሜሪካ)፡፡ እሱም ቢሆን፣ የቀሩትን አራት ቀናት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲሠሩ ተደርጎ ነው፡፡ ሰለዚህ ጤናማው መንገድ አስራ አራት ቀናት ከሥራ መገለል ነው፡፡ እንግዲህ የተጋለጡትንም የተያዙትንም በቀላሉ ምህረቱን ይላክላቸው ካልን በኋላ ግን፣ መልሰን ብናስበው፣ በነዚህ ባለሙያተኞች የሥራ ቦታቸው አለመገኘት፣ አይደለም በኮቪድ-19 የተያዘውን ህሙም ቀርቶ፣ ሌላውን ህሙም መርዳት የሚችል ሰው ላይኖር ነው፡፡ ፍራቻው፣ በኮቪድ ከተያዙት በላይ፣ በቂ ርዳታ ማግኘት ሳይችሉ በሌላ ህመም የሚሰቃዩ ሰዎች የሞት ቁጥር ሊጨምር ይችላል ነው፡፡

ለነዚህ ባለሙያተኞች፣ ከሌላው አብሮ ከሚለበሰው መከላከያ ልብስ በተጨማሪ፣ ተራ ማስክ ሳይሆን፣ N95 የተባለ፣ ኮሮና ቫይረስ ሾልኮ ሊሄድበት የማይችል ማስክ መጠቀም የግድ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ባለሙያተኞቹ አደጋ ላይ ናቸው፡፡ በቅርቡ በሚያሰቅቅ ሁኔታ፣ ከኢትዮጵያ፣ በጎንደር ሆስፒታል፣ በኮቪድ መያዙ ከተረጋገጠ ሰው ጋር በመጋለጣቸው ከመቶ በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች ከሥራ መገለላቸውን ሰማን፡፡ ባለሙያተኞቹ አስፈላጊው ማስክ ቢኖራቸው ኖሮ ያን ያህል ሰው ሆስፒታልን ከመሰለ የሥራ ቦታ አየገለልም ነበር፡፡ ያወቅነውና ያረጋገጥነው ነገር፣ በቂ ማስከ አለመኖሩን ነው፡፡ አሜሪካን በመሰለ አገር ከስለሳ ሰባት ሺ በላይ የጤና ባለሙያተኛ በቫይረሱ መያዙ በተረጋገጠበት አገር፣ ሶስት መቶ ሀያሶስት ነርስና ዶክተር ህይወታቸው አልፏል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ትችላለች ወይ?

የማስክ ዕጥረት በግልፅ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ አደጋው ደግሞ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚሆንም አይደለም፡፡ ቆም በሉና አስቡ፣ ምን ማድረግ ይችላሉ፡፡ አንዱ ቀለል ያለው ነገር ቢኖር፣ የሚቻልዎትን በመለገስ፣ ማስክ ተገዝቶ በቀጥታ ለጤና ባለሙያተኞች አንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡ የጎንደር ሆሰፒታል፣ የኮቪድ ሆሰፒታል ተብሎ መወሰኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለሱዳን አዋሳኝ ከሆነው ከመተማ በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎችም ርዳታ እንዲሠጥ በመደረጉ፣ በተአምር ካልሆነ በስተቀር ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው፡፡ 


በኮቪድ ሥርጭት ቤተሰብዎን ለማዳን የሚረዳ ታላቅ ግኝት “የጨነቀ ዕለት” አለ ድምፃዊው 5/31/20

የሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁ2 (ሳኮ2) ከሰው ወደ ሰው በመሸጋገር አደገኛነቱን ወይም የተዋጣለት መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ታዲያ በጣም የሚሸጋገርባቸው ቦታዎችን ካየን፣ አንዱና ትልቁ በቤተሰብ መሀል በቤት ውስጥ ነው፡፡
ለምን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው

አንደኛ፤ ቅርበት፣ ማለትም በስድስት ጫማ (ሁለት ሜትር) መቀራረብ ሰላለ
ሁለተኛ ደግሞ፡፡ የመጋለጫ ጊዜ ረዥም ሰለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ በሆስፒታል፣ አንድ በኮቪድ የተያዘ ሰው ምንም ማስክ ሳያደርግ ማሰክ ካላደረገ የጤና ባለሙያተኛ ጋር በቅርበት ግንኙነት ቢያደርግ፣ በቫይረሱ ለመያዝ ሁለት ደቂቃ በቂ ነው፡፡ ታዲየ ቤት ውስጥማ፣ እራሳችሁ ገምቱት፡፡

አንዱ ትልቅ ችግር የሆነው፣ በሳኮ 2 ተይዘው ስሜት አልባ የሆኑ ሰዎች ብዛት ነው፡፡ ሰሜት አልባዎቹ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ በቫይረሱ ቢያዙም የስሜት ምልክት ሳይኖራቸው አስከ መጨረሻው የሚዘልቁ ሲሆን፡፡ ቀሪዎቹ ግን፣ በቫይረሱ ተይዘው፣ መጀመሪያ ሰሜት ባይኖራቸውም ቆየት ብለው የበሽታ ሰሜት፣ ከመጠነኛ እሰከ ለህይወት አስጊ የሚሆን ድረስ ይታይባቸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች፣ የበሽታ ሰሜት ከመጀመሩ ከአራት ቀናት በፊት(በአብዛኛው ደግሞ ከ48 ሰኣታት በፊት) ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው ያስተላልፋሉ ማለት ነው፡፡ እነዚሀ ሰዎች በጣም አደገኛ የሚያደርጋቸው ነገር ደግሞ፣ እንደታወቀው፣ የበሽታ ህመም ከመጀመሩ በፊት፣ ቫይረሱ በአፍንጫ ውስጥ ከመጠን በላይ ሰፍሮ ሰለሚገኝ ነው፡፡

አሁን ይሀንን በመረዳት ሁሉም ሰው ከቤት ውጭ ማስክ (የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርግ ተደርጓል)፡፡ ማን ቫይረሱ እንዳለበት ወይም እንደሌለበት የሚታወቅ ነገር አይደለም፡፡ ቆየት ብለው የሚታመሙ በወቅቱ የበሽታ ስሜት የሌላቸው ሰዎች ቫይረሱን ቢያስተላልፉም፣ እነሱ ራሳቸው መያዛቸውን አያውቁም፡፡ ሰለዚህ ጣት መቀሰር አያስፈልግም፡፡

ቸግር የሆነው በቤት ውስጥ ነው፡፡ እንደ ምኞታችን ቫይረሱ ከአካባቢው አልፎ እስኪሄድ ሁሉም ሰው በቤት ውስጥ ቢከተት ደስታውን አንችለውም፡፡ ነገር ግን፣ የኑሮ ጉዳይ አለ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ህብረተሰቡን የሚያገለግሉ እንደሌላው በየቤታቸው መቆየት የማይችሉ የጤና ባለመያተኞች፣ ፀጥታ አስከባሪዎች፣ የውሃ የመብራት አገልግሎት ሠራተኘቾ፣ ምግብኛ ሸቀጥ አቅራቢዎች የግድ ከቤት መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡

ከነዚህ ውጭ ግን፣ በቤታቸው መቆየት እየቻሉ፣ የሞተ ሰው ካላዩ በስተቀር ኮሮና አልገባም የሚሉ፤ አኛን አይነካንም የሚሉ ወይም ብለው የሚያስቡ፤ ሌላውን ምክር ከቁብ የማይቆጥሩ ባሉበት ሁኔታ ምን ማድረግ ይቻላል፡፡

ከውጭ ማስክ ማድረግ ይቻላል ቤት ውስጥ ግን በተለይ፣ በቫይረሱ ከተያዙ ከፍተኛ የህመም ደረጃ ብሎም ህይወታቸው ሊያልፍ የሚችሉ ሰዎች ያሉበት ቤተሰብ ውስጥ ምን ማድረግ ይቻላል የሚለው ጥያቄ በማንም በዚህ ጉዳይ የሚጨነቅ ባለሙያም ሆነ ቅን ዜጋ አዕምሮ የሚብሰለሰል ነገር ነበር፡፡

አሁን አተገባበሩ ግራ የሚያጋባ ቢመስልም አንድ አዲስ ጥናት ወጥቷል፡፡ እንደ ሌሎቹ “ሰበር ዜና” ብዬ ባላጋራችሁም፣ ደስተኛ ከሆንኩባቸው ጥናቶች አንዱ በመሆኑ፣ በሰንበት፣ ጣቶችን ከታይፕ ጋር አገናኝቼ፣ ዜናው ለናንተ አስኪደርስ በጉጉት በመተክተክ ላይ ነኝ፡፡

እንደተለመደው በመረጃ ነው፡፡ ጥናቱ ከቻይና በኩል ነው የመጣው፤ የፅሁፉን ምንጭ በዚህ ፅሁፍ መጨረሻ ላይ አስቀምጫለሁ፡፡

መግቢያው ላይ የሚጠቁሙትም፣ በቤት ወስጥ መደረግ ሰለሚገባው ጥንቃቄ ከዚህ በፊት በጥናት የታየ መረጃ የለም ነው የሚሉት፡፡ ውነት ነው፡፡ በውጭ በኩል የሚደረጉ የመከላከያ እርምጃዎች ውጤት እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡

በጥናቱ መሠረት፣ ከ124 ቤተሰብ (ቤቶች) 335 ሰዎችን ያካተተ ጥናት ነው የተመለከቱት፡፡ በየቤቱ ቢያንስ ቢያንስ አንድ በኮቪድ መያዙ የተረጋገጠ ሰው አለበት፡፡ የጥናቱ ጊዜ ከየካቲት ማለቂያ እሰክ መጋቢት ማለቂይ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

የጥናቱ ውጤት የሆነው ደግሞ፣ በኮቪድ ከተያዘው በመጀመሪያው ሰው ምክንያት ምን ያህል የቤተሰቡ አባለት በኮቪድ ተያዙ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ሰው ተነስቶ ወደሌሎቹ ሲሻገር ሁለተኛ ሥርጭት ይባላል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘው ቤቶች ውስጥ የተደረጉትን የመከላከል ባሕሪዎችንም ተመልክተዋል፡፡

በውጤቱ የታየው፤ ከመጀመሪያው በኮቪድ ከተያዘው የቤተሰብ አባል ተነስቶ ወደ ሌሎቹ የመሻገር ማለትም ሁለተኛ ደረጃ ሥርጭቱ 23% ነበር (ከ335 ሰዎች 77 ተይዘዋል ማለት ነው)፡፡ ይህ ቁጥር አስተውላችሁ ከሆነ፣ ሌላ ጊዜ ካየነው ቁጥር በጣም ያነሰ ነው፡፡ እንዴት ከ335 ከተጋለጡ ሰዎች መሀከል፣ ያውም በቤት ውስጥ፣ 77 ሰዎች ብቻ ተያዙ? ጥሩ ነገሩም የመጣው ከዚህ ቁጥር ማነስ ጋር ተያይዞ ነው፡፡

ይሀ ቁጥር ማነስ የታየው፣ በኮቪድ ቫይረስ የተያዘው ሰውና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት፣ ሰውየው የህመም ስሜት ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ ሁሉም በቤታቸው ውስጥ ማስክ በማድረጋቸው፣ የበሽታው ወይም የቫይረሱ ሥርጭት በ79% እንዲቀንስ ነው ያደረገው፡፡ በጣም ጠቃሚ ትልቅ መረጃ ነው፡፡ ከማስኩ በተጨማሪ፣ በየቀኑ በአልኮልም ሆን በክሎሪን ቤቱን ማፅዳት፣ እንደ አጥኝዎቹ ስሌት፣ ሥርጭቱን በ77% መቀነስ እንደሚችል ነው፡፡

እዚህ ላይ፣ እንደተጠበቀው፣ የበሽታ ምልክት ወይም ሰሜት ከጀመረ በኋላ፣ ማስክ ማድረጉ ጠቀሚታ አልታየበትም፡፡ እንዳያችሁት ወይም እንደምትገነዘቡት፣ ጉዳቱ የደረሰው ገና የበሽታ ሰሜት ሳይጀመር ነው፡፡ እንግዲህ በቀናት ሲታይ ወደኋላ ከአራት ቀናት በፊት በርግጥም ከ48 ሰአታት በፊት መከላከል ካልተደረገ፣ ቫይረሱ ተሻግሯል፡፡

በቤት ውስጥ አብሮ በመኖር ብቻ፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር በሚደረገው ቅርበት ያለው ግንኙነት ተደጋጋሚ መጋለጥ የቤተሰቡን አባላት በ18 ዕጥፍ የመያዝ አደጋ ላይ ይጥላቸዋል፡፡ ይህ እንግዲህ በትንፋሽ ከሚመጣው አደጋ ነው፡፡ በኮቪድ የተያዘው ሰው ተቅማጥ ቢኖረውስ፤ በዚህ ሁኔታ ደግሞ የቤተሰቡ አባለት በአራት ዕጥፍ በቫይረሱ የመያዝ አደጋ ላይ ናቸው፡፡

ሰለዚህ፣ ምን መደረግ እንደሚኖረበት ሁላችንም አኩል ሃሳብ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ አሳዛኝ ሆኖ ቤተሰብ ውስጥ ሀይለኛ ሥርጭት ሰለሚፈጠር፣ እንደቤተሰብ አብረን የምናደርጋቸው ነገሮች ላይ ነው የመጣብን፡፡

ምክሩ
1ኛ. ከቤት ወጥተው የሚሠሩ ከሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ መራራቁ የሚመክረው፣ ካልተገደዱ በስተቀር እንዳይወጡ ነው፡፡
2ኛ. በቤት ውስጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር አብረው የሚኖሩ ከሆነ፣ እስዎ በመውጣትዎ ምክንያት በቫይረሱ ለመያዝ የሚጋለጡ ከሆነ፣ የግድ ሊሆን ነው፣ ቤት ውስጥ ማስክ ማድረግ ሊኖርብዎት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ አዛውንቶች ካሉ፣ ሌላ በኮቪድ ከፍተኛ የህመም ሁኔታ ሊፈጥርባቸው የሚችል ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሰዎች በቤትዎ ወስጥ ካሉ የግድ ማሰክ ማድረግ ይኖርብዎታል፡፡
3ኛ› ከቤተሰብ አባላት ጋር በሚገናኙበት ጊዜ ማስክ የሚያስወልቅ ሁኔታ አብረው እንዳይሆኑ ያስፈልጋል፡፡ ይቅርታ፣ አብረው አይበሉም ማለት ነው፡፡ በተለይ አዛውንቶችና ታማሚዎች በቤትዎ ውስጥ ካሉ፡፡
4ኛ፡ ድንግት ከታመሙ፣ ራስዎን ሙሉ በሙሉ በማግለል (Isolation) ፣ ከሌሎቹ ጋር ያለዎትን ግንኙነት ያቆማሉ፡፡ ግን የግድ የመኖሪያ ሁኔታው ለማግለል የማይመች ከሆነ፣ ከዚህ ቀድም ታማሚው ብቻ ማስክ ያድርግ ከሚለው ምክር በተጨማሪ፣ አሁን በጥናት እንዳያችሁት የቤተሰብ አባላቱም ማስክ ያድርጉ፡፡ ይህ እንግዲህ ታማሚው መቆየት የሚችልበት የተለየ ክፍል በማይኖርበት ሁኔታ ነው፡፡
5ኛ. ታማሚው ተቅማጥ ካለበት፣ ተገቢው ንፅህና በየቀኑ፣ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ በተደጋጋሚ መደረግ አለበት፡፡
6ኛ. አይውጡ፣ ከወጡ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ ይህን ቫይረስ የሚያመላልሰው ሰው ነው ያውም ምንም የበሽታ ስሜት የሌለበት፡፡ ሰለዚህ ማንንም ማመን ይከብዳል፡፡ ለብዙዎቻችሁ ይህ ነገር ከባድ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ለኮቪድ-19 በሽተኞች በየቀኑ ርዳታ የሚሠጡ የጤና ባለሙያተኞች ቤተስብ እንደ ተለመደው የሚደረገው የቤተሰብ አኗኗር ከተቀየረ ከርሟል፡፡ አሁን ጥረቱ ሌሎች የቤተሰብ አባላቶችዎችን ማዳን ነው፡፡
በቤተሰብ በኩል የሚካሄደው ሥርጭት ከቀነስ፣ በአብዛኛው ሥርጭት የሚመጣው ከዚህ በኩል ሰለሆነ፣ የበሽታው መዛመት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል፡፡
ያም ሆኖ ቫይረሱን ወደ ቤት ይዘው እንዳይመጡ ከቤት ውጭ መደረግ የሚገባቸውን ምክሮች ተግባራዊ አድርጉ፡፡ 

ምንጭ
Wang Y, Tian H, Zhang L, et al
Reduction of secondary transmission of SARS-CoV-2 in households by face mask use, disinfection and social distancing: a cohort study in Beijing, China
BMJ Global Health 2020;5:e002794.

Community health 

education in Amharic 

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ