​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

አጠገባችሁ ያለ ሰው በሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 መያዙን ማወቅ ከቻላችሁ…. 4/6/2020

የበሽታ ስሜት የማይታይባቸው ሰዎች ቫይረሱን ማስተላለፋቸው የተረጋገጠ ነገር ነው

ከዚህ ቀደም ፈራ ተባ እያሉ፣ የበሽታ ምልክት የማያሳዩ ሰዎች ቫይረሱን ያስተላልፉ ይሆን የሚል ጥያቄና መልሶች ነበሩ፡፡

እንግዲህ ይህ ሳርስ-ኮቪ-2 የተባለው አዲሱ ቫይረስ፣ ለምን እንዲህ በፍጥነት አለምን አዳረሳት ለሚለው ጥያቄ መልስ ፍለጋ ከተጀመረ ቆየት ብሏል፡፡ አንዱ ጥናት፣ ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገጽ እንዳካፈልኳችሁ፣ የተመለከተው ነገር ቢኖር፣ በሁለቱ ቫይረሶች መሀከል በቁጥር 1 እና በዘህኛው በቁጥር 2 መሀከል፣ ቫይረሶች በአየር ላይና በዕቃዎች ላይ የሚቆዩበት ጊዜ የተለያየ ይሆን የሚል ነበር፡፡ ጥናቱ፣ በሰታቲሰቲክ ደረጃ በሁለቱ ቫይረሶች መሀከል ልዩነት አላሳየም፡፡ የጥናቱን ውጤት ማየት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይም ለመከላከል ለሚደረገው ርምጃ፡፡ ታዲያ ምን ይሆን ተብሎ ሲገመት፡፡ አንደኛው ምክንያት፣ ቫይረሱ ከመጠን በላይ በአፍንጫ ውስጥ ሰለሚገኝ ነው፡፡ ሌላኛው ምክንያት ደግሞ፣ በቫይረሱ የተያዙ፣ ገና ምልክት ያልታየባቸው ጤናማ ሰዎች ቫይረሱን ሰለሚያስተላልፉ ነው ብለው ገመቱ፡፡

ነገሩ ግምት ብቻ አይደለም፡፡ እውነት ነው፡፡ የተለያዩ መረጃዎችም እየወጡ ነው፡፡ ከነዚህ ከወጡ መረጃዎች አንድ ሁለቱን ላካፍላችሁ፡፡

የመጀመሪያው፣ በአሜሪካ ኮቪድ ተገኝቶባቸው፣ ለብዙ ህሙማን ህይወት ማለፍ ምክንያት ለሆነው፣ በዋሽንግተን ሰቴት፣ ኪንግ ካውንቲ፣ ውስጥ የሚገኘው የአዛውንቶችና ህሙማን መኖሪያ ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቦታ፣ ሀኪሞቹም ሆነ፣ የአሜሪካው የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ሰዎች አጥንተው፣ በሳምንታዊ መግለጫቸው የወጣው ነው፡፡ በመረጃ የተደገፈ ነገር ማንበብና ማካፈል እንልመድ፡፡ መረጃ ሰለተፃፈ ብቻ ሳይሆን፣ እነማናቸው የፃፉት ማለትም ተገቢ ነው፡፡

በዚህ መረጃ መሠረት፣ በዚህ ነርሲንግ ሆም (ወይም የኣዘውንቶች የህክምና ርዳታ እየተደረገላቸው በሚኖሩበት ቦታ)፣ አንድ የጤና ሠራተኛ ኮቪድ-19 ስለተገኘበት፣ በዚህ መኖሪያ ቦታ ከሚኖሩ ከ82 አዛውነቶች በ76 ላይ ምርመራ ይደረጋል፡፡ የግድ ነው፡፡ በዛው በመኖሪያው ውስጥ ሰለሚኖሩ፣ አንደኛው ሰው ከተያዘ ለሁሉም ሰለሚሻገር ነው፡፡ እንግዳ ነገርም አይደለም ምክንያቱም በሌሎች ተላላፊ በሽታዎችም ላይ የሚደረግ አቀራረብ ነው፡፡ ምርመራው ከተደረገላቸው አዛውንቶች መሀከል፣ በዚያን ጊዜ ከመቶ 30 ፐርሰንቱ፣ በዚሁ በሳርስ-ኮቪ-2 መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ አሁን ዋናው ነገር፣ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው ሰዎች መሀከል፣ ምን ያህሉ የበሽታ ስሜት ነበራቸው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ከሆነስ፣ በበሽታው ሥርጭትና፣ በሽታውን ለመከላከል በሚወሰደው ርምጃ ላይ የሚያሰከትለው ወይም የሚለውጠው ነገር አለ ወይ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ወሳኝ የሚሆነው፣ ለምን ይመስላችኋል፡፡ ለኮቪድ በሸታ መያዝ ማጣሪያ ጥያቄው (ስክሪኒንግ) በበሸታ ስሜት ያተኮረ ሰለሆን፡፡ የበሽታ ስሜት የለበትም የተባለ አዛውንት በመሀሉ ማጣሪያውን አልፎ የለባቸውም ከሚባሉ ሰዎች ጋር ሰለሚቀላቀል፣ ቫይረሱ መዛመቱ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

በዕድሜ ገፋ ያሉ ኣዘውንቶች፣ ባቫይረሱ ከተያዙ በዕድሜያቸው ብቻ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ህመም እንደሚሄዱም ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ ቫይረሱ ወደ ነሱ እንዳይገባ አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ የተያዙትን ካልተያዙ መለየት፣ ተያዙ ከተባሉት ጋር የሚሠሩ የጤና ባሙያተኞች ደግም፣ አስፈለጊውን መከላከያ ለብሰው እንዲሠሩ ማድረግን ይጨምራል፡፡

ነገሩ የመጣው፣ የጤና ባለሙያተኘው፣ እያመመው ሥራውን የቀጠለው ይህ ሠራተኛ፣ ሁለት ቀናት ብቻ ነው የሠራው፡፡ ምርመራ ሲደረግለት፣ በቫይረሱ እንደተያዘ ይረጋገጣል፡፡ እሱ የሠራው፣ በፌብሩዋሪ 26ና 28 ነው፡፡ በማርች 6፣ ሰባት የሚሆኑት አዛውንቶች ይታመማሉ፣ ምርመራው ሲደረግ በቫይረሱ መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ በማርች 13፣ CDC ለኗሪዎቹ ምርመራ ያደርጋል፡፡ ምርመራው የበሽታ ምልክት ማሳየትና አለማሳየታቸው፣ ከዚህም ጋር ደግሞ የላብራቶሪ ምርመራ በማድረግ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ከ82 ኗሪዎች መሀከል፣ 76 ላይ ነው ምርመራ የተደረገው፡፡ በዚህ መሠረት የበሽታ ምልክቶች (ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ ማጠር ስሜትና ሌሎችን ጨምሮ) የሌለባቸውና ያለባቸው ተብለው ተከፈሉ፡፡ ከ76 ሰዎች መሀከል፣ 23 ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆኑ፣ ከነዚህ ከ23 መሀከል ደግሞ፣ አስሩ የበሽታ ምልክት ሲገኝባቸው፣ ምርመራው በተደረገበት ጊዜ ከ23 ወስጥ 13ቱ ምንም የበሽታ ስሜት አልነበራቸውም፡፡ እንግዲህ አስተውሉ፣ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች፣ 57% የሆኑት፣ ምርመራው በተደረገው ወቅት ምንም አይነት የበሽታ ምልክት አልነበራቸውም፡፡ እንግዲህ፣ ሰዎችን ለመለየት፣ የላብራቶር ምርመራ ሳይጨመር፣ ዝም ብሎ በበሸታ ምልክት ብቻ ማጣሪያ ቢደረግ፣ እነዚህ አስራ ሶስት ሰዎች፣ የለባቸውም ተብለው ከሌለባቸው ሰዎች ጋር ሲቀላቀሉ የሚከተለውን ጉዳት መገመት አያደግትም፡፡ ከዚህ ቫይረስ ባህሪዎች አደገኛው ይህ ነው፤ በተለይም ሥርጭቱን ለማባባስ፡፡

ሌላው የታየው ነገር፣ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ምንም ምልክት ሳያሳዩ ቫይረሱን ተሸክመው አሻጋሪ ሆነው ቢቆዩም፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን፣ የበሽታውን ምልክት ማሳየት ይጀምራሉ፡፡ ያ ግን ጉዳት ከደረሰ፣ ማለትም ቫይረሱን ካሻገሩ በኋላ ነው፡፡ እነዚህ ዘግየት ብሎ የበሽታ ምልክት የሚታይባቸው (ቅድመ ሰሜት አሻጋሪዎች ወይም አስተላላፊዎች) ናቸው፡፡  ማጠቃለያው፣ በበሽታ ስሜትና ምልክቶች ብቻ እከሌ ይዞታል እከሌ አልያዘውም ብሎ መለየት፣ ፈተና የማያልፍ አሰራር ነው፡፡ እንግዲህ ተጧሪዎች እንድ ላይ የሚኖሩበት ቦታ፣ ወይም ሰዎች ሰብሰብ ብለው የሚኖሩበት ቦታ፣ የግድ የላብራቶሪ ምርመራ አስፈላጊ ነው፡፡ ያም በቫይረሱ የተያዘውን ለይቶ ለማስቀመጥ፡፡ ሰፋ ወዳለው ህዝብ ስንመጣ ደግሞ፣ በተለይም ሥርጭቱ ገፋ ባለበት ጊዜ፣ ማን በቫይረሱ እንደተያዘ፣ ማን እንዳልተያዘ መለየት አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው ከሰው ጋር የሚደረገውን ግንኙነት አቁሙ፤ አሁን ደግሞ፣ የተያዘውና ያልተያዘው ሰለማይለይ፣ ሁሉም ሰው ጭምብል (ወይም ማስክ) ማድረግ እንደሚኖርበት የተነገረው፡፡ ድሮም ቢሆን የማሰክ ዕጥረት ተፈርቶ ነው አንጂ፣ ማስክ መልበሱ ብዙውን ሰው ከመያዝ እንደሚያድነው ሳይታወቅ ቀርቶ አየደለም፡፡ ማሰክ ሲደረግ ግን፣ አፍና አፍንጫ በደንብ ተሸፍኖ፣ ትንፋሽ በማፈኛ ማስኩ በኩል እንዲወጣና እንዲገባ ተደርጎ ነው እንጂ ለይስሙላ አፍ ላይ ጣል አድርጎ መዞሩ አግባብ አይደለም፣ አያስጥልም፡፡ እንደ ነገሩ ማስክ አድርጎ የሚዞር ሰው ካያችሁ፣ ስድስት ጫማ ወይም ሁለት ሜትር ሳይሆን አራት ሜትር መራቅ ይሻላል፡፡ አራት ሜትር ራቁ ማለቴም አይደለም፣ ነገር ግን ሰውየው ሰለ ኮሮና የገባው ሰለማይመስል፣ ሌላስ ሰዎችን ለቫይረሱ የሚያጋልጥ ነገር ምን ያደርግ ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ መምከር ግን ጥሩ ነው፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ማስተማር ነው፡፡

አሁን የዚህን ቫይረስ ሥርጭት ያገነነውን አንዱን ትልቁን ምክንያት ተገንዘበናል፡፡ ወደኋላ መለስ ብላችሁ ካያችሁ፡፡ ይህ ቫይረስ በአፍንጫ ውስጥ በብዛት የሚገኝ ከሆነ፣ ስሜት የሌለባቸው የሚያስተላልፉ ከሆነ፣ ሳያስላቸው ወይ ሳያሰነጥሳቸው በሚያወሩበትና በሚተነፈሱበት ጊዜ ቫይረሱን ወደ ውጭ እየረጩት ነው ማለት ነው፡፡ ሰለዚህ ሁሉም ሰው ጭምብል ሲያደርግ እነዚህ ሰዎችም ሰለሚያደርጉ ከነሱ የሚወጣው ቫይረስ በጭምብሉ ተከልክሎ ይቀራል፡፡ በዚህ መንገድ ሥርጭቱ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ሰለዚህ አፍና አፍንጫን በጭምብል አፍኖ መውጣት ፋሽን መሆን አለበት፡፡ ይሁን፡፡ ምናለበት እነዚህ ዘፋኞች ይህን እያደረጉ እየወጡ ቢያሳዩ መልካም አርኣያ ይሆኑ ነበር፡፡ ፖለቲከኞቹን አንኳን ወይ ፀበል መንከር፣ ወይ አንድ ላይ ሰብስቦ ሶላት ካላደረጉላቸው የህዝብ ችግር የገባቸው አይመስሉም፡፡ በዚህ ላይ ቢረባረቡ ጥሩ ነበር፡፡

በሠርግ ዕለት ያልተጠራው ተጋባዥ ኮቪድ-19 ሠርገኞችን … 5/25/20202

 ሰው ከሰው ጋር ከተገናኝ መተላለፍ መቻሉን ያስመሰከረው ሳርስ ኮሮና ቁ 2፣ (ሳኮ2) በተለያዩ አጋጣሚዎች መሠራጨቱን አይተናል፡፡ እንግዲህ፣ በልደት፣ በሀዘን፣ በቤተክርሰቲያን ስብስብ ተላለፈ፡፡ ትልልቅ የሚባሉ የህዝብ በአላት ላይ፣ ሠርጭቱ ከመጠን አልፎ የሚሄድበት መሆኑ ታውቋል፡፡ በውሀን ከተማ፣ የቻይኖቹን አዲስ አመት ለማክበር የሄደ ህዝብ ነው ሥርጭቱን ከቁጥጥር ውጭ ያደረገው፡፡ የዛሬ መቶ አመት የታየው የስፓኒሽ ኢንፍሉዌንዛ፣ በኢትዮጵያ የህዳር በሽታ፣ በጣም የገነነው የህዳር ሚካኤል በተከበረ በሳምንቱ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የህዳር በሽታና የኮቪድ አካሄድ ተመሳሳይ ነው ማለት ያስደፍራል፡፡ ለማንኛውም የዚህን ታሪክ ትረካ ክፍል አንድና ሁለትን ብታዳምጡ ብዙ መገንዘብ ትችላላችሁ፡፡

እስካሁን ስለ ሠርግና ኮቪድ ወግ ባለው የፅሁፍ ምንጭ ሰላልቀረበ፣ ማካፈልም አልተቻለም ነበር፡፡ አሁን ግን በአርቲክል መልከ ከጤና ባለሙያኞች በኩል የቀረበ ፅሁፍ ላካፍላችሁ፡፡

ነገሩ የሆነው በጆርዳን ነው፡፡ በማርች 2020፣ በሠርግ የተነሳ፣ ሰፋ ያለ የኮቢድ-19 ሥርጭት ይከሰታል፡፡ እንግዲህ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር፣ የመንግሥት መደበኛ ሥራ መሆን የሚገባው፣ በሠርጉ ለት የተገኙ ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት፣ መጠየቅና መመርመር ነው፡፡ ጆርዳንም ይህንን አደረጉ፡፡ የሚገርመው ነገር የዚህ የሠርጉ ሥርጭት እሰኪፈነዳ ድረስ፣ ማለትም አስከ ማርች 15፣ በጆርዳን አንድ በላቦራቶሪ የተረጋገጠ በኮሮኖ የተያዘ ሰው ብቻ ነበር የሚታወቀው፡፡

በማርች 13፣ 2020 ሁለት ሰአታት በወሰደ ሠርግ ላይ ሥርጭት ይከሰታል፡፡ ሠርጉ፣ ለአራት መቶ ሰዎች ተብሎ የተዘጋጀ ነበር፣ የተገኙት ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም፣ ወደ 360 የሚሆኑ ሰዎች እንደታደሙ ይገመታል፡፡ ከአካባበዊ የጤና ቢሮ ጋር በመሆን፣ አጥኝዎቹ፣ ታመሙ አልታመሙም 360 ሰዎች ላይ ምርመራ ያደርጋሉ፣ በአፍንጫ በኩል በሚደረግ ቫይረሱ መኖሩን የሚያረጋግጥ ምርመራ ነው፡፡ ሠርጉ ላይ የተገኙ ሰዎች ብቻ ሳይወሰን፣ ከነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ወይም የተጋለጡ ሰዎችም ጥናቱ ውስጥ ተካተዋል፡፡ ተጨማሪ መረጃዎችም ተሰበሰብዋል፡፡

ቫይረሱን ይዞ የመጣና ለመተላለፍ ምክንያት የሆነው ሰው፣ ሌላ ቢሆን ጥሩ ነበር፣ ነገር ግን የሙሽራዋ አባት ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ሰውየው ከሠርጉ ሁለት ቀናቶች በፊት፣ ሳል፣ ትኩሳትና፣ ንፍጥ (ይቅርታ) ነበረው፡፡ ከሠርጉ ከሁለት ቀን በኋለ ወደ ድንገተኛ ክፍል ሄዶ ሲመረመር በኮቢድ-19 ወይም ሳኮ2 መያዙ ይረጋገጣል፡፡ ሰውየው ከስፔይን ነበር የተጓዘው፣ በስፔይን፣ ኮቪድ ካለው ሰው ጋር ለመገናኘቱ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ከሠርጉ ከአራት ቀናት በፊት ጆርዳን ሲመጣ ሙሽራውን ጨምሮ ከቅርብ ቤተሰብ ጋር ተገናኝቷል፡፡

ምርመራው የተደረገው ከሠርጉ አራት ሳምንታት በኋላ ሲሆን፣ ከሙሽራዋ አባት ጋር 85 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ከነዚህ መሀል 76 በሠርጉ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ ዘጠኙ ግን በሠርጉ ላይ ያልነበሩ፣ ነገር ግን ወደ ሠርጉ ከሄዱ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የሚገርመው፣ በጆርዳን ብሄራዊ ፖሊሲ መመሪያ መሠረት ሁሉም በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሆስፒታል ገብተው ክትትል ተደረገላቸው፡፡

ከ76ቱ ሠርጉ ላይ ከተገኙት እና በሳኮ2 መያዛቸው ከተረጋገጠው ሰዎች መሀል፣ 40ዎች (52.6%) የበሽታው ስሜት ነበራቸው፡፡ 36ቱ (47.4%) የበሽታ ስሜት አልነበራቸውም፡፡ ከተያዙት መሀከል አንደኛዋ ነብሰ ጡር ነበረች፣ ነገር ግን በሰላም ተገላግላለች፡፡ ከ48 ሰኣታት በኋላ አዲሱ ልጅ ምርመራ ተደርጎለት ቫይረሱ አልተገኘበትም፡፡ አነዚህ ሰዎች ሁሉ ክትትል ያደረገው የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ነው፡፡

አብዛኛዎቹ ስሜት የነበራቸው ሰዎች፣ በብዛት የታየባቸው ምልክት ትኩሳት፣ መናፈጥና፣ ራስ ምታት ነበር፡፡ ሌሎችም ተጨማሪ ምልክቶች እንደ ጉሮሮ መከርከር፣ ድካምና ጡንቻ ህመም፣ ትንፋሽ ማጠር ስሜትም ነበሩ፡፡ ከሁለት ሰዎች በስተቀር በሌሎቹ ቀለል ያለ ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ አንድ የ80 አመት የጡት ካንሰር የነበራት አሮጊት፣ እየከፋ የሚሄድ የሳምባ ምች (ኒሞኒያ) ይዟት፣ ሆስፒታል በገባች ከሁለት ሳምንት በኋላ ሞተች፡፡ በዚህ ሥርጭት፣ ከተጋለጡ በኋላ የበሽታ ስሜት ለመከሰት የወሰደው ጊዜ አምሰት ቀናት ነበር፡፡ አማካይ ነው፣ ገደቡ ከ2 አስከ 13 ቀን ድረስ ነበር፡፡

እነዛ ድግስ ሳይበሉ በኮቪድ የተያዙ ዘጠኝ ሰዎች ሁሉም፣ ወደ ሠርግ ሄደው ቫይረሱን ይዘው የተመለሱ ሰዎች ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ማመላለስ ይሏችኋል ይህ ነው፡፡ ከዘጠኙ መሀል፣ አራቱ የበሽታ ሰሜት ነበራቸው፡፡ አምስቱ ግን አልነበራቸውም፡፡

ይህ ሪፖርት ብዙ ምክሮች ልናገኝበት የምንችል ነው፡፡
1ኛ. ግልፅ እንደሆነው የሰዎች ስብስብ መፈጠሩ
2ኛ. በሁለት ሰአታት ውስጥ ያን ያህል ሥርጭት መፈጠሩ፣
3ኛ› በአንድ ሰው አማካኝነት ብቻ መሆኑ፡፡ ሰዎቹ ከሰውየው ጋር የነበራቸው ርቀት ወይም ቅርበት አይታወቅም፡፡ ነገር ግን የሙሽራዋና የሙሽራው ወላጆች በር ላይ ቆመው የሚመጡ ሰዎችን ሲቀበሉ ነበሩ ይላል ሪፖርቱ፡፡ እንደዛ ከሆነ ደግሞ፣ በጣም አጭር ጊዜ ነው የነበረው፡፡ ግን መተቃቀፍ መሳሳሙም አለ፡፡
4ኛ. ቫይረሱ ቤት ድረስ ሄዶ ሠርግ ላይ ያልተገኙ ሰዎችን መያዙ
5ኛ. ቁጥራቸው ከፍ ያለ ስሜት አልባ ሰዎች መኖራቸው
6ኛ. መደበኛ ክትትልና፣ የተያዙትን ለይቶ ማወቅና ማግለል፣ እንደ ሪፓርት አቅራቢዎች ዘገባ፣ በቀጠለው ክትትል ሌላ ሰው አለመያዙ ሌላ ትምህርት ነው፡፡
7ኛ. በዚህ ዘገባ በተደረገው ስሌት፣ 1 በቫይረሱ የተያዘ ሰው ከ2 አስከ 3ት ለሚሆኑ ሰዎች እንዳስተላለፈ ነው፡፡ ይህ ስሌት በሽታን ለመቆጣጠር በሚደረግ ዝግጅት ወሳኝ ነው፡፡ ይሀ ቁጥር ግን፣ በጣም በተጣበበ ብዛት ያላቸው ሰዎች ባንድ ላይ በሚኖሩበት ቦታ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ በአሜሪካ ሰሌት አስር ነው ሲባል ነበር፡፡
8ኛ. ቫይረሱ እንደምንም ብሎ የሚገለው ሰው እንዳገኘ መገንዘብ ወሳኝ ነው፡፡

መልካም ንባብ፡፡

በኮቪድ-19 የተያዘው ዶክተር ፀፀቱን ገለፀ 7/27/2020 

ባልና ሚስት ዶክተሮች፣ በሥራ ቦታቸው በኮቪድ ላለመያዝ መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ሲያደርጉ የከረሙ ሲሆን፣ በቤታቸውም ቢሆን ከተወሰኑ ቅርብ ጓደኞቻቸውና ቤተሰብ ጋር ብቻ ነበር የሚገኙት፡፡ ጓደኞቻቸውም ሆነ ሌሎች የቤተሰብ አባለት ሁሉም መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ሲያደርጉ ነው የከረሙት፡፡ ባልና ሚስቱ በሀምሌ ወር በቀጠሮ ይዘውት የነበረውን የዕረፍት ጊዜ ይሰርዛሉ፡፡ ምክንያቱም ፕሮግረሙ የነበረው ፍሎሪዳ ነው፡፡ ፍሎሪዳ ደግሞ የኮቪድ-19 ሠርግና ምላሽ ቦታ ሆኗል፡፡

ታዲያ በሚኖሩበት በአለባማ ሰቴት በሚገኝ ሀይቅ አካባቢ ከሰው ራቅ ወዳለ ቦታ መሄድ ወሰኑ፡፡ ለዕረፍት፡፡ የቅርብ ጓደኞቻቸውንና የቤተሰብ አባላትንም ይጋብዛሉ፡፡ ከነሱም ጋር የባልና ሚስቱ ወላጆችም ተጠሩ፡፡ እንደዘገባው ወላጆቻቸው በ60 አመታት ዕድሜ ክልል ውስጥ ናቸው፡፡ ሁሉም የተጋበዙት ሰዎች፣ በኮቪድ ከመጣ ጠንቃቆች ነበሩ፡፡ በሀይቁ አጠገብ ውጭ ሜዳው ላይ ነው መገናኘትና ጊዜ ማሳለፈ የፈለጉት፡፡

እንደዛም ሲሆን የሚገባውን የርቀት ጥንቃቄ አድረገው፣ ወደ ዘጠና ፐርስንት የሚሆነውን ጊዜ ውጭ ነበር ያሳፉት፡፡ አንድ ላይ የተጠጋጉበት ጊዜም አልነበረም፡፡
ነገር ግን ማሰክ አላደረጉም፡፡
እናስ?
ለመዝናናት ከተገናኙት 11 ሰዎች፣ ባልና ሚስቱን ጨምሮ፣ ስምንት ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ ሁለት አመት የሆናት ልጃቸውም ቢሆን ባላት የበሽታው ምልክት ምክንያ በኮቪድ-19 እንደተያዘች ጥርጣሬ አላቸው፡፡

ባጭሩ ባልና ሚስቱ የሚሉት፣ ቤተሰብና ጓደኞች ጋር ስለሆን፣ ተዘናጋን እናም ማስክ አላደረግንም ነው፡፡ ባልየው፣ የደረሰባቸውን ቸግር በትዊት አካውንቱ ወዲያውኑ ለቀቀው፡፡ ሀሳቡም እኛ የደረሰብን እይደረስባችሁ ነው፡፡ ሰለዚህ ሌሎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለመምከር ነው፡፡

ዶክተሩ የሚለው፣ ክርስትና፣ ሠርግ፣ ቡናቤት የመሳሰሉት ቦታዎች አልሄድንም፣ እናም ገለል ያለ ቦታ ሰለተገናኘን አደጋ የሚደርስብንም አልመሰለንም፡፡ እናም ሌሎቹ ከኛ ትምህርት እንደሚያገኙ ተስፋ አለን ይላል፡፡

እንግዲህ፣ የኮቪደ-19 ዋናው መተላለፊያ በትንፋሽ መሆኑን ሁላችንም የተረዳን ይመስለኛል፡፡ ተራርቃችሁ የሚባለው መተላለፊያው በትንፋሽ ሲሆን ቫይረሱን በተሸከሙ በአይን የማይታዩ ርጥበት ጠብታዎች (ድሮፐሌት) አማካኝነት ሰለሆነ፣ እነዚህ ርጥበቶች ደግሞ በክብደታቸው ምክንያት ከስድስት ጫማ በላይ ርቀው ስለማይሄዱ ነው፡፡

የለም የለም፣ የሰሞኑን ሙግት የተከታተላችሁ ካለችሁ፣ በድሮፕሌት ብቻ ነው የሚለው ሀሳብ ግፊት እየደረሰበት ነው፡፡ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ሳይንቲስቶች፣ ለአለም የጤና ድርጅት(የኛ ሰው አለቃ የሆነበት መሥሪያ ቤት) ደብደቤ በመፃፍ፣ ይህ ቫይረስ በድሮፕሌት ብቻ ሳይሆን በአየር ብናኝ (ኤር ቦርን) አማካኝነት ይተላለፋልና፣ ድርጅቱ ይህንን ተቀብሎ ህዝቡን ያስታውቅ ይላሉ፡፡ ዱላና ግፊት የበዛበት ድርጅቱም፣ የኤር ቦረን መተላለፉን ሀሳብ በመቀበል፣ ሊሆን ይችላል ነገር ግን የተረጋገጠ ነገር የለም በማለት መግለጫ ያወጣል፡፡

ህም፣ ኤር ቦርን ሲባል፣ ከድሮፕሌት የሚለየው፣ ቫይረሱን የያዘው ከትንፋሽ የወጣው ነገር በአየር ላይ ተንሳፎ መቆየት ብቻ ሳይሆን ከስድስት ጫማ አልፎ በርቀት ይሄዳል፡፡ በዚህ መንገድ የሚተላለፉ ምናልባትም ከምታውቋቸው በሽታዎች አንዱ፣ ስመጥሩው ሳንባ ነቀርሳ ነው( ቲቢ)፡፡

በርግጥ ኮቪድ-19 በኤርቦርን ተላልፏል የሚል ጥናት አልወጣም፡፡ ለመሟገት ከሆነ ግን፣ በኤርቦር የማይተላለፍ ቢሆን ነው የሚገርመው፡፡ ምክንያቱም፣ ከዚህ ቀደም የመጡት የሳርስ ኮሮና ቫይረስ 2 (ኮቪድ-19 የሚያመጣው) ታላላቅ ወንድሞቹ፣ ሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር አንድና፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው ሜርስ ኮሮና ቫይረስ በኤርቦርን ይተላለፋሉ፡፡ በተለይም በ2002-3 ታይቶ የነበረው ሳርስ ኮሮና ቁጥር አንድ፣ በሆቴሎች ጎን ለጎን ባሉ ክፍል በአየር አማካኝነት ተላልፏል፡፡ ጥናቶች የሚሉት፣ የአይነምድርና የሽንት መውረጃ ቱቦዎች ሙሉ በሙሉ ዝግ ያልነበሩ ሲሆን፣ አይነ ምድር ያለበትን ፈሳሽ ወደ አየር እንዲበተን በማድረግ ነው ይላሉ፡፡ የትንፈሹ ላይበቃ ደግሞ በዚ በኩል፡፡ ነገሩ ምንድን ነው፣ ወደ አየር ብናኝ አትቀይሩት ነው፡፡ በዚህኛው በኮቪድ-19ኝም ቢሆን፣ ከተፀዳዱ በኋላ ውሀ ከመልቀቅዎ በፊት ክዳኑን ይዝጉት የሚል ምክር አለ፡፡

በሆስፒታልም ውስጥ ቢሆን ያ ሁሉ ጥንቃቄ እየተደረገ፣ ከመቶ ሺ በላይ የጤና ባለሙያተኞች በዚህ ቫይረስ መያዛቸው፣ ከነሱም ውስጥ ከ560 በላይ ነርሶች፣ ዶክተሮችና ሌሎቸ ባለሙያተኞች ህይወት ማለፍ ከማሳዘኑም በላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነገር ነው፡፡

ዋናው ነገር፣ ከባልና ሚስት ሀኪሞች የምንማረው አንዱ ነገር መዘናጋት እንደማይስፈልግ ነው፡፡ በትንፋሽ ከሆነ የሚተላለፈው፣ ትንፋሽን መከወን ነው፡፡ ያም የትም ቦታ ቢሆን ነው፡፡ ማንም ሊታመን አይችልም፡፡ በተለይም በቫይረሱ ተይዘው የበሽታ ስሜት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር በግልፅ እየታወቀ በመጣበት ጊዜ፡፡ ለነገሩ ከታወቀ እንኳን ቆይቷል፣ ዕድሜ ላላዋቂ ፈትፋች በይፋ ለመቀበል ተቸግረው ነበር፡፡ ባለፉት ፅሁፎች ባንዱ እንደገለጥኩት፣ ማስክ በቤትም ውስጥ ማድረግ የግድ ነው፡፡ በተለይም፣ ግድ የሌላቸው፤ የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ በማየት፣ ወጣ ገባ የሚሉ፣ በሽታው አይነካንም የሚሉ ሰዎች ባሉበት ቤት፣ መከላከል የግድ ነው፡፡ በርግጥ 80 ፐርስንቱ ከበድ ያለ ህመም የማይታይበት ቢሆንም፣ ይህ ቫይረስ ከደረስና ካገኛቸው ግን ሕይወታቸው የሚያልፉ ሰዎች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ ቫይሱን በግድ የለሽነት ማስተላለፍ፣ የሰው ህይወት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውን እንደሚጎዳ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ዋናው ተማፅኖ፣ ባካችሁ ለሌሎች ሰዎች ስትሉ ቫይረሱን ከማስተላለፍ፣ ለሌሎች ሰዎች አደጋ ከመፍጠርም ተቆጠቡ ነው፡፡ የጤና ባለሙያተኞች በዚህ መጠን መጎዳት ከቀጠሉ፣ ሌላውን በሽታ ማን እንደሚያክመው ሁላችንም መጠየቅ አለብን፡፡

እኔ እንደማየው ከሆኑ፣ በትክክለኛው መንገድ፣ ወገን ተጎዳ በማለት የሚችሉትን ሁሉ የሚያደርጉ ሰዎች እንዳሉ ግልፅ ነው፡፡ እያየንም ነው፡፡ ነገር ግን እንደዛ አይነቱ ስሜታዊ እንቅስቃሴ በፖለቲካ ላይ ብቻ ተወስኖ ሲቀር፣ የወገን ወይም የሰው ዘር መጎዳት ማለት የተለየ ትርጉም ያለ ይመስላል፡፡ ያውም እኮ ይህ ቫይረስ አሁን እያጠቃ ያለው ማንን እንደሆነ ግልፅ በሆነበት ጊዜ፡፡ ለነዚህ ሰዎች እኮ ነው ሰዎች የሚታገሉት፡፡ ነገር ግን በቫይረስ ከሆነ፣ ምንም አለመጣር ምን ይባል ይሆን፡፡ ይሄ ነገር የሰው ዘር ጠላት ነው፡፡ ሰለዚህ ጎራችሁን ለዩና ሥርጭቱን ለመቀነስ ከሚጥሩ ሰዎች ወገን ሁኑ፡፡

ዋናው ነገር፣ ተራርቀን ቁጭ ብለን እንተርፋለን የሚል ሃሳብ ካለ፣ እንገደና ተከልሶ መታየት አለበት፡፡ በትንፋሽ ነው፣ በትንፋሽ ነው፡፡ ሰለዚህ ትንፋሻችሁን ገድቡ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የሀኪሞቹና የቤተሰቦች በኮቪድ መያዝ የሚያሰተምረን ነገር አንዱ በግል ማስክ አለማድረግ የሚያመጣው ነገር ሲሆን፤ ሌላው ግን፣ አደጋ ያለው በቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ በክፍት አየር ባለበት ቦታ መሆኑ ነው፡፡ ሰለዚህ በቤት ውስጥ አብሮን ከሚኖር ሰው ውጭ ከሌሎች ጋር በምንገናኝበት ቦታ ሁሉ፣ ማስክ ማስክ ማሰክ፡፡ ማን አለበት ማን የለበትም የሚታመን ነገር አይደለም፡፡ መርሳት የሌለብን፣ ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገፅ እንተጠቀሰው፣ ቫይረሱን የያዝ ትንፋሽ በመደበኛ ንግግር እንደሚወጣ ነው፤ እንኳን ሳል፣ ንጥሻ፣ ጮክ ብሎ መናገር፣ መዘመር ተጨምሮበት፡፡

ወጣቶችም ቢሆን በኮቨድ-19 መያዛቸው ያውም በከፍተኛ ቁጥር መሆኑ ከታወቀ ቆይቷል፡፡ አዲስ ነገር የሆነው፣ በኮቪድ-19 ተይዘው ከታመሙት መሀል አስከ ሶስት ሳምንት ድረስ ወደሙሉ ጤንነት እንዳልተመለሱ በዘገባ ቀርቧል፡፡ ያም ቁጥር ወደ ሀያ ፐርስነት የሚሆኑት መሀል ነው፡፡

ከተከሰተበት ከ2019 ማለቂያ ጀምሮ፣ ይህ ቫይረስ ራሱን በመጠኑም ቢሆን እየለወጠ፣ ሁለት ነገሮችን ተክኗል፡፡ አንደኛ፣ ከሰው ወደ ሰው በመሸጋገር፣ ወደር የሌለው ችሎታ መፍጠር

ሁለተኛ፤ የሰው ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ከመጠን በላይ የመራባት ችሎታ፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት ስንጠይቅ የነበረውን፣ ማለትም የቫይረሱ መጠን በሰውነት ውስጥ በጣም ከፍ ካለ የተለየ ችግር ይፈጥራል ወይ የሚለውን መልስ አግኝተናል፡፡ መረጃው የሚያሳየው የቫይረሱ መጠን በከፍተኛ ደረጃ የሆነባቸው ሰዎች በጣም ታማሚዎች መሆናቸውን ነው፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ፣ ይህ ቫይረስ ከዚህ ቀደም የመጡ ዘመዶቹ ያላሳዩትን ችሎታዎች ተክኗል፡፡ የቀረው ነገር፣ እንደነሱ ገዳይ መሆኑ ነው፡፡ ለማስታወስ ያህል ሳርስ ኮሮና ቁጥር አንድ ከያዛቸው ሰዎች አስር ፐርስንት ይገላል፡፡ መካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው ቫይስ ደግሞ ከያዛቸው ሰዎች አስከ ሰላሳ አምስት ፐርስንት ይገላል፡፡ ፈጣሪ ይጠብቀን፡፡


በማሰክም መመለሱ እኮ ተመስገን ነው፡፡ ማሰክ ካደረገን ደግሞ ቦታና ሰው መምረጥ የለብንም፣ ካደረግንም በትክክል መሆነ አለበት፡፡ አላማው ትንፈሽ ለመገደብ ነው፡፡

ግም ለግም አብረህ አዝግም
በአሜሪካው ምክር ቤት ላይ በተደረገው የአመፅ ወረራ ላይ የታየችው ዶክተር


መቼም ይህ መከረኛ ኮቪድ ከመጣ ወዲህ ያላየነው ያልሰማነው ጉድ የለም፡፡ ሰለ ህከምና፣ ሰለ ቫይረስ፣ ሰለ በሽታ ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ሰለ ቫይረሱና በሽታው አሉታዊ ነገር ቢያወሩ የሚገርም አይሆንም፡፡ በዚህ ነገር ላይ “ነብዮችም” አሉበት፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፣ ህብረተሰቡን ግራ ያጋቡና የሚያጋቡት፣ በህክምና ሙያ ተመርቀው ዶክተሮች ተብለው ሰለ ኮቪድ የተሳሳተ ወሬ ሲነዙ የከረሙ ሰዎች ናቸው፡፡ ምኑም አይቀራቸውም ሲቃወሙ፣ ክትባቱን፣ የመከላከያ መንገዱን በሙሉ፡፡ እኛም ግራ ግብት እስኪለን ድረስ ነበር፡፡ አሁን በቅርቡ ቢሯቸውን ለሚለቁት ፕሬዜዳንት አማካሪ የነበረ ሀኪም፣ ስሙ አትላስ ይባላል፡፡ ያላለው ነገር አልነበረም፡፡

ከነዚህ ሁሉ በጣም የሚታወቁት በአንግሊዝኛ አጠራር ስማቸውን አሳምረው America’s Frontline Doctors በመባል ባለፈው በጋው ወራት፣ በአሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ሰለፍ በማድረግ፣ ሰለ ሀይደሮክሲ ክሎሮኪን የተባለ መድሐኒት ያልተረጋገጠ ወሬ ማናፈስ፣ ማስክ አይሰራም፣ በየቤታችሁ ቆዩ የሚለውን የመከላከያ መልክት ሲቃወሙ ታይተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ስለ ኮቪድ ክትባት ህብረተሰቡን ለማሸበር የተሳሳተ መልክት በማሠራጨት ሙከራ ሲያደርጉ ነበር፡፡

ለምን ይህን አመጣህ ብትሉኝ፡፡ ይህንን የተሳሳተ ወሬ ከመነሻው የሚያሠራጩ ሰዎች፣ ከህክምናው የራቀ ሌላ ተልኮ አላቸው፡፡ ተቀባዩና አዳማጩ  በውል ሳይረዳ እየተቀባበለ በስፋት ሲያሠራጨው ማን እንደጀመረው ሳይታወቅ፣ ጀማሪዎቹ ያሰቡትን ውጤት ያሳካል፡፡ እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ዶክተር የሚባሉ ሰዎች በየቪዲዮው ያደረጉት ሆን ተብሎ የሚሠራጭ የተሳሳተ ወሬ ብዙዎችን ግራ ቢያጋባ እንዳውም ለአንዳንድ ሰዎች እንደ መረጃ ሆኖ ቢቀርብ አይገርምም፡፡ የሚገርመው ብዙ አዳማጭ ያለው የዚህ አይነቱ ወሬ መሆኑ ነው፡፡ በቪዲዮ የተለቀቀ፣ ዶክተር የተባለ ያለውን ሁሉ ትክክል አድርጎ የሚወሰድ ሰው እንዳለ ሁላችንም እንረዳለን፡፡

ባለፈው ረቡዕ፣ በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ ያልታወቀ አመፃ ተነስቶ፣ ምክር ቤቱን በመውረር፣ የህዝቡ ድምፅ ውጤት እንዳይቆጠር ሙከራ መደረጉን ተከታትላችኋል፡፡ በዚህ አመፃ ላይ ብዙ ሰዎች የተሳተፉ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ታዲያ በታላቅ አክብሮት የሚታየውን የአሜሪካውን ምክር ቤት የወረሩ ሰዎች ቀንደኞቹን በመለየት፣ የአሜሪካው የፌዴራል ምርመራ ቢሮ፣ ፎቶግራፎችን ይበትናል፡፡

ከዚህ ከተሠራጨው ፎቶ መሀል በቁጥር 21 የምታተይ ሰው አለች፡፡ ፎቶ ለህዝብ በይፋ እንደወጣ፣ እንደተደረሰባትም ስላወቀች ይሆናል፣ በሰልፉ ቦታ መገኘቷን ራሷ አምና ዋሽንግተን ፖስት ለተባለው ጋዜጣ ትናገራለች፡፡ ይች ሰው ማን መሰላቻችሁ፣ ከላይ በማህበር ተደራጅተው ስለ ኮቪድ የተሳሳተ ወሬ ሲያሰውሩና ደፍረውም በከፍተኛው ፍርድ ቤት ፊት ለፊት የተሰለፉት በስም ቆንጆ የሆነው America’s Frontline Doctors የተባለው ድርጅት መሥራች ነች፡፡ አንግዲህ በደንብ አስተውሉ፣ በሙያዋ የገባቸውን ቃል ኪዳን፣ አዎ መሀላ እኮ አለብን- ሰውን አልጎዳም የሚል፡፡ ሰውን አልጎዳም ሲባል በተሳሳተ መድሀኒት ብቻም አይደለም፣ እንደዚህ በማደናገርና ሳይንስን አጣሞ ሰውን የሚረብሽ ነገር መንዛትን ይጨምራል፡፡ የሙያ ግዴታዋን አውልቃ ወርውራ ከሰውየው ጋር በመተባበር ሰልፍ ድረስ የሚያስኬድ ሆን ተብሎ የተሳሳተ መረጃን አቀናብራ ስተዘምት ከርማ ነበር፡፡ አሁን በምስሉ እንደምታዩት፣ (በነገራችን ላይ ምስሉ የአሜሪካ መንግሥት ካሠራጨው “እነዚህን ሰዎች ካያችሁ” ከሚለው ፎቶግራፎች ፖስተር ነው የተወሰደው፡፡ ሴትዮዋ ዶክተሯ፣ በአመፃው መሰለፍ ብቻ ሳይሆን የድምፅ ማጉያ ይዛ ስተቀሰቀስ የነበረች ናት፡፡ ራሷም ፎቶው ላይ ያለችው ሰው እኔ ነኝ ብላለች፡፡ ምን ትላላችሁ? ዕውነት ለሰው ሕይወት ደንታ አላት? ቢኖራትስ ለነማን ነው? በአመፁ ላይ የተሳተፉት ሰዎች ምን አይነት አርማ ይዘው እንደታዩ ታውቃለችሁ፡፡ እናንተና እኔን ለሚመስል ሰው ደንታም የላቸውም፡፡ በዚህ መሀል፣ ቀድም አድርጌ ለማሳሰብ የሞከርኩት አንድ ነገር ነበር፡፡ ያም በዚህ በኮቪድ በዛን ጊዜ በብዛት እየተጠቃ የነበረው አሁንም ቢሆን ከድርሻው በላይ የሚሞት የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ እናም ይችን የመሰለች ዘረኛ ሰውና መሰሎቻቸው …. ልተወው፡፡


መልክቱ፣ ከሳይንሱ ወጣ ያለ የማይመስል ነገር ሲወራ፣ እንዴት? ወዴት? መረጃ? ማነው ያለው? ዕወቀት አለው ወይ? ልምድስ አለው ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ከፉ ሰዎች አንደሆነ እንኳን ሙያ፣ አገርም ይሸጣሉ፣ የአባታቾቻቸውን አደራም ይበላሉ፡፡ በቪዲዮ የተለጠፈ፣ በሜዲያ የቀረበ ነገር ሁሉ ውነት አይደለም፡፡ እነዚህን የመሰሉ ሰዎች ይሰሙና እኛን መልሰው የሚሞግቱ ሰዎችም አይተናል፡፡ አሃ! ስሟን ልናገር እንጂ፤ ሲሞኔ ጎልድ ትባላለች፡፡ እሷ አንደመከላከያ ያቀረበቸው፣ በዚያን ቀን የነበሩ ሰዎች ምክር ቤቱን ጥሰው እንደሚገቡ አላወቅሁም የሚል ነው፡፡ ባገራችን አባባል “ለማያውቅሽ ታጠኝ” ይባላል፡፡

በህዝብ በኩል የሚደረጉ መከላከያዎች የኮቪድ-19 ሥርጭትን ማቀዝቀዛቸውን የሚገልፅ ጥናት 4/23/2020

ይህ ፅሁፍ፣ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ይገታሉ ወይም ይቀንሳሉ የሚባሉ የመከላከያ ተግባራትን ውጤት በጥናት መልክ ያቀረበ ነው፡፡ የተሠሩ ሥራዎችን ውጤት መገመት ቢቻልም፣ በርግጠኛነት መናገር የሚቻለው ግን፣ እንደዚህ በጥናት ወጥቶ በአሃዝ ተደግፎ ሲቀርብ ነው፡፡

ይህንን በሚመለከት፣ የአሜሪካ የህክምና መፅሄት አንዱ ከሆነው JAMA (Journal of Medical Association) በአፕሪል ዕትሙ ጥናት አውጥቷል፡፡

የኮቪድ-19 ሥርጭት በቻይና በውሃን ከተማ ነው የጀመረው የሚለውን ዘገባ ብዙዎቻችን ተቀብለነዋል፡፡ በዚህ ከተማ ሲጀምርም፣ ዘግይተዋል ይባል እንጂ፣ ቻይኖቹ የወሰዷቸው ርምጃዎች ነበሩ፡፡ ከነዚህ ርምጃዎች በኋላ፣ ሥርጭቱ በጣምና እንደዘገባው ከሆነ አንደምሳሌ ሊጠቀስ የሚገባው አቀናነስ ነው የታየው፡፡ ታዲያ የጥናቱ ጥያቄ፣ ውነት እነዚህ የተወሰዱ ርምጃዎች፣ ሥርጭቱን ከመቀነሱ ጋር ግንኙነት አላቸው ነው ወይ፡፡

ይህን ጥያቄ ለመመለስ፣ አጥኝዎቹ፣ በኮቪድ-19 መያዛቸው በላቦራቶሪ የተረጋገጠ የ32 583 ሰዎችን ዝርዝር መረጃ ተመለከቱ፡፡ ጥናቱ ያተኮረው ከታህሳስ 8 አስከ መጋቢት 8 ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች መረጃ፣ ከከተማው የተለላፊ በሽታዎች ሪፖርተ ተሰበሰበ፡፡ መረጃው፣ የልደት ቀን፣ዕድሜን፣ ፆታን፣ መኖሪያ አካባቢን፣ የሥራ ቦታን ያካተተ ሲሆን፣ የበሽታውን ጥናት በደረጃ መከፋፈልንም ይጨምራል፡፡ የበሽታው ሰሜት መጀመሪያ የተሰማበትን ቀንና፣ በላቦራቶሪ የተረጋገጠበትን ቀንም ይጨምራል፡፡

የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት በህዝብ ደረጃ የተወሰዱ ርምጃዎች ደግሞ፡ አካባቢን በማገድ ሰው እንዳይወጣ እንዳይገባ ማድረግ፣ የትራፊክ ዕገዳ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር በርቀት መሆን፣ በቤት ውስጥ ብቻ ተወስኖ መቀመጥ፣ ከዚያ በተጨማሪ ደገም፣ ማዕከላዊ የሆነ የመገለያ ቦታ ማስገባት፣ እንዲሁም አጠቃላይ የሆኑ በበሽታው ስሜት የተመረኮዘ አሰሳ ማድረግ ነበሩ፡፡

የታዩ ውጤቶችና የተወሰዱት ርምጃዎች፡ የሥርጭቱን ጊዜ፣ ማለትም ከታህሳስ 8 አስከ መጋቢት 8 ያለውን በአምስት ወቅቶች እንዲከፈሉ ተደረገ፡፡ በነዚህ ወቅቶች፣ በኮቪድ መያዛቸው በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ሰዎች በአሃዝ ለማስቀመጥ፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በቀን በአንድ ሚሊዩን ህዝብ እንዲሰላ ከተደረገ በኋላ፣ ይህ ስሌት በዕድሜ፣ በፆታ፣ በሠፈር ወይም የመኖሪያ ቦታን በመጨመር አንድ ላይ እንዲሰላ ተደረገ፡፡

አንግዲህ በነዚህ በአምስት ወቅቶች የነበረውን ሁኔታ አንመልከት

ከታህሳስ 8 እሰከ ጥር 9 ባለው ጊዜ ውስጥ ምንም አይነት ከላይ የተገለጡን በህዝብ ደረጃ የሚደረጉ የመከላከያ ርምጃዎች አልተወሰዱም፡፡ ይህ ወቅት የመጀመሪያው ወቅት የተባለ ሲሆን፣ የቻይኖቹን አዲስ አመት ለማክበር ብዛት ያለው የህዝብ አንቅስቃሴም ነበር

ከጥር 10 እሰከ ጥር 22 ባለው ጊዜ፣ የቻይኖቹን አዲስ አመት ለማክበር የህዝብ እንቅስቃሴ በገፍ ነበር የታየው፡፡ በዚህ ሁለተኛው ወቅት በሚባለው ጊዜ፣ ያን ያህል የህዝብ እንቅስቃሴ በመካሄዱ የኮቪድ-19 ሥርጭትን እንደሚያፋጥነው ይጠበቅ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ጠንከር ያለ በህዝብ ደረጃ የተደረገ መከላከያ አልነበረም፡፡ በዚህ ጊዜ፣ የመጀመሪያው ከሰው ወደ ሰው መተላለፉ ከተነገረ በኋላና፣ የጤና ባለሙያተኞች በበሽታው መያዛቸው ከታወቀ በኋላ፣ ሆሰፒታሎች፣ ትኩሳትና የመተንፈሻ አካለት ህመም ሰሜት ባላቸው ሰዎች መጨናነቅ ጀመሩ፡፡

ከጥር 23 አስከ የካቲት 1 ባለው ጊዜ፣ አካባቢን ከልሎ መዝጋት፣ በቤት ውስጥ ገለል ብሎ መቆየት፣ እና የትራፊክ እገዳ ተደረገ፡፡ በዚህ በሶሰተኛው ወቅት፣ ከውሀን ከተማ የሚወጣ ማኘውም ትራንስፖርተ እንዲዘጋ ተደረገ፤ ከዛ ቀጥሎም የህዝብ መመላለሻ አገልግሎት ታገደ፣ ተከትሎም በከተማው ውስጥ ምንም አይነት የትራንስፖረት እንቅስቀሴ እንዳየደረግ ተወሰነ፡፡ በዚህ ጊዜ፣ በሰዎች መሀል መራራቅ፣ ከቤት ውጨ ወይም ሰዎች ባሉበት አካባቢ ማስክ መልበስ ማስገደድና፣ ማንኛውም የሰዎች መገናኛ የሆኑ ቦታዎች ወይም ሁኔታዎች አንዲሰረዙ ተደረገ፡፡ በቻይናም ቢሆን፣ በዚህ ወቅት፣ የህክምና ቁሶች ከፍተኛ ዕጥረት ስለነበር፣ ብዙ የታመሙ ሰዎች በቤታቸው ሆነው እንዲገለሉ ተደረገ፡፡

ከየካቲት 2 አስከ የካቲት 16 ባለው ጊዜ፣ ማዕከላዊ ማግለያ ቦታና ህክምና ተካሄደ፡፡ የህክምና መገልገያዎች ዕጥረት ሰለተስተካከለ፣ አጠቃለይ የማግለያ (ኳራንቲን) ቦታ ተዘጋጅቶ፣ የህመም ስሜት ያላቸው ሰዎች ህክምና እንዲያገኙ ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜም፣ ለሁሉም የከተማው ኗሪዎች በየቤታቸው እንዲቀመጡ የሚል ፖሊሲ ተግባራዊ ተደረ፡፡

ከየካቲት 16 አስከተ መጋቢት 8 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ፣ አጠቃላይ የሆኑ የኮቪድ-19 የበሽታ ስሜቶችን የተመረኮዘ አሰሳ ተደረገ፡፡ በዚህ ወቅት፣ መንግሥት፣ ለሁሉም ነዋሪዎች፣ ከቤት ወደ ቤት በመዘዋወር፣ ግለሰቦችን የበሽታው ስሜት ያላቸው ወይም የሌላቸው መሆኑን የሚዘግብ አሰሳ ተደረገ፡፡ ለዚህ አንግዲህ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ዕገዛም ነበረበት፡፡

ከዚህ ጋርም፣ የሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 የመባዛት መጠን ከላይ በታዩት ወቅቶች ውስጥ እንዲሰላ ተደረገ፡፡ ይህ የቫይረሱ የመራባት መጠን የሚጠቁመው፣ በሌሎች ተጋልጠው በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ መልሰው ለሌሎች ማዛማታቸውን ነው፡፡

 ከላይ የተጠቀሱት ዕገዳዎች መሥራታቸውን አለመሥራታቸውን መለኪያ ያደረጉበት ስሌት፣ በቀን፣ በአንድ ሚሊዮን ሰዎች መሀል፣ ምን ያህል በበሽታው መያዙ የተረጋገጠ ሰው ተገኘ ለሚለው ቁጥር፣ በፆጻ፣ በዕደሜ፣ በሥራ ቦታ፣ ጤና ባለሙያተኞችን ጨምሮ፣ በሚኖሩበት አካባቢ እንዲመዘን ተደረገ፡፡

ይህ ስሌተ በጀርባው፣ ቀናትን፣ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር፣ በአካባቢው ያለውን ህዝብ ቁጥር ያካተተ ነው፡፡ ሰለሱ ብዙም ሳንነጋገር፣ ወደ አሃዞቹ አንግባ፡፡ ለእንደዚህ አይነት ጥናት መግለጫነት በሳይንስ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ስሌት ነው ብለን እንቀበለው፡፡ አለዚያ አይታተምም ነበር፡፡

 ብዙ ዝርዝር መረጃዎች ቢኖሩበትም፣ ለዚህ ፅሁፍ እንዲተኮርበት የተፈለገው፣ የሥርጭቱን ግራፍ ነው፡፡

አብዛኛው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር የተከሰተው ከጥር 20 አስከ የካቲት 6 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያሰመዘገበውም በየካቲት 1 ነበር፡፡ ሥርጭቱ ከመሀል ከተማ ተነስቶ ወደ ዳር ዳር ቦታዎች አንደሄደም፣ በዳር ቦታዎችና በመሀል ከተማ የሥርጭት መጠን ልዩነት ያለው ሲሆን፣ የመሀል ከተማው በብዛት በበሽታው የታያዙ ሰዎች የታዩበት ክፍል ነው፡፡ በየቀኑ የሚታየው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥረ በእያንዳንዱ ሚሊዮን ሰዎች ሲሰላ፣ ከጥር 10 በፊት 2.0 የነበረው ቁጥር፣ በቀጥታ ወደ 162.6 ከፍ ያለው ከጥር 23 እስከ የካቲት 1 ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ መቀነስ ጀመረ፡፡ ከየካቲት 2 አስከ የካቲት 16 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ 77.9 ወረደ፣ ከየካቲት 16 በኋላ ደግሞ ወደ 17.2 ወረደ፡፡

ጥናቱ፣ የዚህን ስሌት ቁጥር አወራረድ በተለያየ ገፅታዎች ተመልክቷል፡፡ ዝርዝሩን ማስፈርም አልተፈለገም፡፡ ዋነው መልክት ግልፅ ነው፡፡ ቻይኖቹ ያንን የሚያህል ህዝብ ባለበት ከተማ የወሰዱት ርምጃ፣ ምን ያህል ሥርጭቱን እንደገታው መመልከት ይቻላል፡፡ ይህንነ በማድረጋቸው፣ ወደ መላው ቻይና ሥርጭቱን መግታት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውጭ ሊወጣ የሚችለውን የሥርጭት መጠን በ80ፐርስን ቀንሰውታል ይላል ከሌላ በኩል የተገኘው መረጃ፡፡ ሥርጭቱን መቀነስ ብቻ ሳይሆን የቀናት ፋታ እንዲኖርም እድረገዋል፡፡

ያንን ያህል የመከላከያ ተግባር በተለያየ መንገድ ፖሊሲ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በተግባር መፈፀሙ፣ አቅም የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ፣ መንግሥት አለም አላለም፣ ከዚህ መማር የሚቻለውን ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ከላይ ከጠቀሱት ተግባራት፣ ህዝቡ በራሱ ማድረግ የሚችለው፣ በየቤተ መከለልን፣ ማህብረሰባዊ ርቀትን መጠበቅ ይገኙበታል፡፡

ማስታውስ ያለብን ቫይረሱን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚወስደው ራሱ ሰው ነው፡፡ ሰለዚህ የሰው እንቅስቃሴ መገታት የቫይረሱን በፍጥነት መዛመት ያሳንሰዋል፡፡

ሌለው ትምህርት ደግሞ፣ ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች መሀል በቀን በበሸታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ በነበረበት ጊዜ፣ ቁጥሩ 2.0 ነው፣ ድንገት ወደ ላይ አንዲነሳ ያደረገው፣ ቁጥር ስፍር የሌለው ሰው፣ የቻይኖቹን አዲስ አመት ለማክበር በዚያው በውሀን ሲርመሰመስ ሰለነበረ ነው፡፡

በኢትዮጵያ እንግዲህ በየቀኑ በመጠኑ ዝቅተኛ የሆነ ሰው ቁጥር በበሽታው ሊያዝ ይችል ይሆናል፡፡ ይህንን ቁጥር ግን ልክ በቻይኖቹ እንደታየው ወደ ላይ ከፍ ሊያደርገውና ስፋት ያለው ሥርጭት እንዲከተል ሊያደረጉት የሚችሉተ ድርጊቶች ሰዎች በአንድ ላይ በብዛት መገናኘት ነው፡፡ የአምልኮ ወይም የፀሎት ቤቶች በዚህ ይካተታሉ፡፡

ሰለዚህ፣ እያንዳንዱ ግለሠብ ወደ ነዚህ ቦታዎች በመሄድ ስብሰቡን ሲያደምቅ በዛው ልክ ደግሞ የበሽታውን ሥርጭት ሊያፋፍም ወይም ሊያደምቅ አንደሚችል መገንዘብ አለበት፡፡

በየቀኑ የምንከታተለው የአለም አቀፍ ሥርጭት የሚያስተምረን ነገር አለ፡፡ አሱም፣ ቫይረሱ አንድ ሀገር ወይም አካባቢ ሲዛመት፣ ሌላ ቦታ አለ ወይስ የለም በሚባልበት ደረጃ ፀጥ ያለ ይመስልና፣ እነዚህ ፀጥ ያሉ የሚመስሉ አገሮች ሥርጭቱ እየጨመረ እየሰፋ ሲሄድባቸው ይታያል፡፡ ፀጥታ የሚመስለው ነገር፣ ብዙ ጊዜ፣ ለበሽታው ከሚደረገው ምርመራ ጋር መያያዙ ግልፅ ነው፡፡ ሌላ ተጨማሪ ነገር ቢኖር፣ የበሽታውን ምልክት የማሳዩ ግን በቫይረሱ የተያዙና ቫይሱን ወደ ሌላው የሚያስተላለፉ ሰዎች ነው፡፡ ካልታመሙ በሸታው መኖሩ አይታወቅም፡፡ ነገር ግን፣ እንደልቡ የሚሆንበት ሰፈርና ሰዎች ቤት ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ የቻይኖቹ የውሃን ሁኔታ የሚያሳየን፣ ከመሀል ከተማ ወደ ዳር ዳር መውጣቱን ነው፡፡ ከተሜዎች ልብ ቢሉ ምናለበት፡፡

እንግዲህ አያድርስ ነው፣ ሌሎች በአፍሪካ ሊደርስ ይቻላል ብለው የሚተነብዩትን ነገር መስማት ባንፈልግም፣ ማስተዋልና ለሚደረገው ዝግጀት አስፈላጊውን ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ እነሱ አንደሚሉት፣ አሁን በአፈሪካ የሚታየው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር፣ ማዕበል ከመምጣቱ በፊት ቀደም ብለው እንደሚታዩት የዝናብ ጠብታዎቸ ነው፡፡ባይሆን መልካም ነበር፡፡ እንግዲህ የበሽታውን ሥርጭት ለማቀዝቀዘ የሠራውነ ነገር አንድ ላይ ተመልከተናል፡፡ ይህ መልክት፣ ለግለሰቦች፣ በአስተዳደር ሥራ ላይ ላሉ፣ ለፖሊሲ አውጭዎችም ጭምር ነው፡፡

የህንዱ ኮሮና ቫይረሰ አሳሳቢ ነው ተባለ

በቀን 25 ሺ ሰዎች እየሞቱ ነው ተብሎ ይገመታል

ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገፅ ሆነ በሌላ መንገድ ቸግር ሊሆን ይችላል በማለት በተደጋጋሞ የምጠቅሰው ነገር ቢኖር፣ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በጨመረ ቁጥር ቫይረሱ አዳዲስ ዝርያዎችን መፍጠር መቻሉ ነው፡፡ አዲስ የቫይረሱ ዝርያዎች ሲፈጠሩ በሁሉት ምድብ ይከፈላሉ፡፡ አዲስ የመጡት አትኩሮት የሚሠጣቸው የሚባሉ በአንድ ወገን ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ አሳሳቢ ዝርያዎች የሚባሉ በሌላ ወገን ይመደባሉ፡፡ እንደ አለም የጤና ደርጅት በአሀኑ ጊዜ አስር የሚሆኑ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች በአሳሳቢነት ደረጃ የተመደቡ አሉ፡፡

አሳሳቢ እንዲባሉ የሚያደርጋቸው አዲስ ዝርያ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ በሚያሳዩት ባህሪ ነው፡፡ የመጀመሪያው የባህሪ ለውጥ ቀድሞ ከታየው የኮሮና ቫይረስ በበለጠ ከሰው ወደ ሰው የመሻገር ችሎታቸው ሲጨምር ነው፡፡ ሁለተኛና ሶስተኛ ባህሪዎች ደግሞ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ከድሮው በበለጠ ለከፋ ህመም መዳረግና በዚህም ምክንያት የመግደል ችሎታ መጨመር ነው፡፡

አዲስ ቫይረሶች የአካላቸው ክፍል ከሆነው ወሳኝ ፕሮቲን ላይ የዘር ሀረግ ለውጥ ሲያደርጉ ፕሮቲኑን የመለወጥ ሁኔታ ሰለሚከተል በዘር ደረጃ ከቀደመው ቫይረስ ይለያሉ፡፡ አንዳንድ ቫይረሶች ደግሞ አንድ ቦታ ብቻ ሳይሆን የተለያያ ተጨማሪ ቦታዎች ለውጥ በማድረግ ለየት ያለ ፕሮቲን ይኖራቸዋል፡፡

የህንዱ ቫይረስ አንድ ብቻ ሳይሆን ሶስት ለውጥ ቦታ ሰላለው (Triple mutant) ብለው እየጠሩት ነው፡፡ በኮድ ቁጥሩ B.1.617 ተብሎ የሚጠራው ይህ አዲስ ዝርያ፣ በአለም የጤና ድርጅት በኩል አሳሳቢ ከሚባሉ ቫይሶች ወገን ተመድቧል፡፡ እነሱ አሳሳቢ ነው ሲሉ፣ ቫይረሱ ከህንድ ወጥቶ ሌላ ቦታ ሊዛመት ይችላል በሚል ስጋት ነው፡፡ ለነገሩማ በእንግሊዝ አገር መጀመሪያ የታየው ቫይረስ አሁን አለምን እየተቆጣጠረ በአንዳንድ አገሮች ለአራተኛ ዙር ማዕበል ወረርሽኝ አብቅቷቸዋል፡፡

የህንዱ ቫይረስ በፍጥነት መሠራጨት መቻሉ ተረጋግጧል፡፡ የሳይንስና የመረጃ ጉዳይ ሰለሆነ በሽታ በማምጣት ጉልበት መጨመሩና ደግሞ የመግደል ችሎታው መጨመሩ በጥናት ይቅረብ በማለት ቁርጥ ያላ ሀሳብ ከመስጠት ገሸሽ ብለዋል፡፡

ለተከታተለ ሰው ግን፣ በህንድ በአሁኑ ጊዜ ከመንግሥታቸው በሚሰጠው ሪፖርት በቀን አራት ሺ ሰው እየሞተ ነው ይላሉ፡፡ ያ ግን ከሚታወቀው፣ ሆሰፒታል ገብቶ በምረመራ በኮሮና ቫይረስ መያዙ ለተረጋገጠ ሰው ነው፡፡ ሰለዚህ ይህ አራት ሺ ቁጥር ዝቅተኛው ነው ማለት ነው፡፡ በሜድያ፣ ዝርያቸው ህንዳዊ የሆኑ ግን የአሜሪካ ፕሮፌሰር እንደሚሉት ከሆነ፣ አራት ሺ ሞት በየቀኑ የሚባለው ትክከለኛ ጣራው አይደለም ይሉና ቀጥለውም የሳቸው ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ትንተና ወይም ጥናት፣ በህንድ በአሁኑ ጊዜ በቀን 25ሺ ሰው እየሞተ እንደሆን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም እንደገለፅኩላችሁ፤ በየቀኑ የሚሞተው ሰው ቁጥር ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ በሳቸው አባባል በየቀኑ ምናልባትም ከ25ሺ ሰዎች በላይ እየሞቱ ነው፡፡ ጥያቄው ታዲያ ከነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ በኮቪድ ምክንያት ሞተ ነው፡፡ ትርፍ ሞት ወደሚባለው የቅመራ መንገድ እየወሰድኳችሁ ነው፡፡

እንግዲህ በኢትዮጵያም ቢሆን፣ የሚሞተውን ሰው ቀጥር በቀላሉ ማወቅ ይቻላል፡፡ በተለይም እምነት ቤቶች በየደብሩ አለዚያም በመስጊድ አማካኝነት በየቀኑ የሚሞተው ሰው ቁጥር አላቸው፡፡ ያ የሚሞተው ሰው ሁሉ ለኮቪድ ምርመራ ቀርቶ ሆስፒልም ያልገባ ነው፡፡ ትርፍ ሞት ማለት አምናና ታች አምና በዚህ ወቅት ሲሞት የነበረው ሰው ቁጥር ግምቱ አለ፡፡ አሁን ግን ሰው በብዛት ከሚገመተው በላይ እየሞተ ነው ከተባለ፡፡ በብዛት ከሚገባው በላይ እየሞተ ያለው ሰው በምን ምክንያት ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ በወቅቱ ሰው መግደል የሚችል ወረርሽኝ ባለበት ሰአት ሌላ የሞት ምክንያት ቢኖርም ይህን ያህል ሰው እንዲሞት የሚያደርገው እንግዲህ ኮቪድ መሆኑ ነው፡፡

አዲስ ቫይረሶች ሲከሰቱ ሌላ ፍራቻ እንዳለም መዘንጋት የለብንም፣ እነሱም ክትባት የማምለጥ ችሎታና ያሉትን መድሀኒቶች የማምለጥ ችሎታዎች ናቸው፡፡ በክትባት ከመጣ የደቡብ አፍሪካ ዝርያው አሁን በአገልግሎት ላይ ካሉ የኮቪድ ክትባቶች አንደኛውን ከጥቅም ውጭ ሰላደረገው፣ ያ ክትባት በደቡብ አፍሪካ እንዳይሠጥ ተደርጓል፡፡

ታዲያ ከዚህ መማር የሚገባን ነገር ቢኖር፣ ወረርሽኙን በክትባት ብቻ ማምለጥ እንደማይቻል ነው፡፡ ያውም በቂ የሆነ የህብረተሰቡ ቁጥር ባልተከተበበት ሁኔታ፡፡

ሌላው ችግር በሌሎቹ ቫይረሶች እንደታየው በህንድም ይሁን በሌላ አገር የተከሰተው ቫይረስ አገሪቱ ውስጥ ዘልቆ መግባት አንደሚችል ሰለሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን፣ ሥርጭቱን ለመቆጣጠር የመከላከያ ዘዴዎች  ተግባራዊ ካልሆኑ፣ ቫይረሱ ራሱ በኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን አዲስ ዝርያ መፍጠር እንደሚችል ማወቅ ነው፡፡ ይህንን ለማወቅ፣ ጀኖሚክ ጥናት የሚባል፣ የቫየረሱን የዘር ሀረግ የሚያጠና  ጅምር በኢትዮጵያ አለ፣ ግን የገንዘብ አቅም ሰለሚጠይቅ ብዛት ያላቸውን የኮሮና ቫይረሶች ባንድ ጊዜ ማጥናት አልተቻለም፡፡ ከበርቴዎችና መንግሥት (አየር መንገድ) እዚህ ላይ ፈታ ብለው ጥናቱ ጠንከር ባለ ሁኔታ እንዲደረግ ቢያደርጉ ለሁላችንም ጥሩ ነው፡፡

ዞሮ ዞሮ ዋናው ክትባት፣ በቫይረሱ አለመያዝ ነው፡፡ የተጠየቀው ማስክ ማድረግና ስብስብን ማቆም ነው፡፡ ግን አሁን እየተሸሉ መጡ እንጂ ባለሥልጣናቱ ሲያደርጉ የከረሙት ነገር ወደኋላ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ነው፡፡ መልካም አርአያ መሆን አቅቷቸው ነበር፡፡ ክትባት ወስደውም ከሆነ፣ ሰበር ኮቪድ ሰለሚባል ነገር ቢሰሙ ጥሩ ነው፡፡ መጠኑ አነስ ይበል እንጂ ክትባት የወሰዱ ሰዎችም በቫይረሱ ሊያዙና ወደሌሎቹ ሊያቀብሉ እንደሚችሉ መረጃ አለ፡፡ መረጃ፡፡ ሲጀመር እኮ የትኛውም ክትባት መቶ ፐርሰንት የሚል ነገር የለውም፡፡ ማለቴ ከበሽታ በመስጣልም ሆነ በቫይረሱ ከመያዝ፡፡ አንድ በሉ፡፡ ሁለተኛ ክትባቶቹ፣ በጎልማሳ ሰውና በዕድሜ በገፉ ሰዎች መሀከል እኩል ምላሽ የላቸውም፡፡ ሰለዚህ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን፣ ክትባት ወሰዱም አልወሰዱም በቫይረሱ እንዳይያዙ ማድረግ የቤተሰብ አባላት ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡም ሀላፊነት ነው፡፡

ብዙ ክፉ ወሬም እየሰማን፣ የምናውቃቸው ሰዎችም ሆነ ዘመዶቻችን እየሞቱ ነው፡፡ ነብሳቸውን በገነት ያኑርልን፡፡ ነገር ግን አስከ መቼ ድረስ ከዚ ቫይረስ ጋር ድብብቆሽ እንደምንጫወት ሊገባን አልቻለም፡፡ ማሰክ ሳያደርጉ በቂ ርቀት ሳይጠብቁ በቴሌቪዢን ባይታዩ ምናለበት፡፡ ስማቸውን መጥቀስ የማልፈልገው አንድ መሪ ጭራሽ የማስክ አለርጂ ያለባቸው ይመስላል፡፡ ሳታውቋቸው አትቀሩም፡፡

በነገራችን ላይ፣ በኮቪድ ለታመሙ ህሙማን በኢትዮጵያ ደረጃ አይነተኛ የህክምና ርዳታ የሚሆነው አንዱና ዋናው ኦክስጅን ነው፡፡ ነገር ግን በሲሊንደር እየተሞላ የሚቀርብ ኦክስጅ በቂም አይደለም፡፡ አሁን በአሜሪካ የሚኖሩ ህንዶች እያደረጉ ያሉት፣ ገንዘብ እያዋጡ concentrator የሚባል ማሽን እየገዙ ወደ ህንድ እየጫኑ ነው፡፡ በአጋጣሚም ከአንደኛው የነሱ ሰው ጋር የመነጋገር ዕደሉ ነበረኝ፡፡ በጀምላ ከሆነ ከገበያ ዋጋ ወረድ ብሎ ይሸጣል፡፡ ችግሩ ህንዶቹ በገፍ እየገዙት ሰለሆነ በበቂ መጠን ገበያ ላይ አይገኝም፡፡ በጋራ ተሰባስብን ማድረግ የምንችለውም ነገር አንዱ ይህ ነው፡፡ እሰከዚያ ግን ለቤተሰብ ቢሆን አንዳንደ እየገዛችሁ መላክ ትችላላችሁ፡፡ ለጊዜው በደቂቃ አምስት ሊትር ኦክስጅን መስጠት የሚችለው በቂ ነው፡፡ ይህ መሣሪየ ተፈላጊ የሆነው፣ የአካባቢውን አየር ወደ ከፍተኛ መጠን ወደ ሆነ ኦክስጅን መቀየር ሰለሚችል፡፡ ኤሊትሪክ ባላበት ቦታ ሆሉ አገልግሎት መሥጠት ይችላል፡፡ በተለይም ከሆስፒታል አገግመው የወጡ ግን ኦክስጅን መውሰድ ለሚገባቸው ሰዎች ትልቅ ርዳታ ይሠጣል፡፡ ይህም በመረጃ የተደገፈ ነው፡፡

መልካም ንባብ

አካፍሉ

ከኮሮና እንድናለን ብለው ያልተፈቀደ መድሐኒት የወሰዱ
 ባልየው ሲሞት ባለቤቱ በጠና ታማለች፡፡


ይህ መልክት ለሁሉም ነው፡፡ ከዚህ ቀድም በተለያዬ ሜድያዎችም ሆነ በጎሽ ድረ ገፅ ለማሰተማርም ለማንሰጠንቀቅ ተሞክሯል፡፡ ይህ ይሠራል ወይም አይሠራም የሚለው ነገር፣ ከጀርባው በመረጃ የተደገፈ መሆን አለበት፡፡
    በዛሬው ዕለት ሜድያው እየተቀባበለ ያቀረበው አሳዛኝ ክስተት አለ፡፡ ለኮሮና ቫይረስ ከሚሞከሩ መድሓኒቶች አንዱ የዎባ መድሐኒት ክሎሮኪን የሚባል ነው፡፡(chloroquine phosphate)፡፡ ይህ መድሀኒት ለኮሮና ህክምና ጥናት ላይ ነው፡፡ ፍቱህ መሆኑም አልታወቀም፡፡ የሙያ ባልደረቦቻችን በየሆስፒታሉ የሚያደርጉትን ጥረት ብትመለከቱ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ይህ ነው የሚባል መድሐኒት አስካሁን አልተገኘም፡፡ የመድሐኒቶቹን ዝርዝር በጎሽ ድረ ገፅ አሰቀምጫለሁ፡፡ ጎብኙ አንብቡ፡፡
    ወደ ዜናው ስንምለስ የአሜሪካው መራሄ መንግሥት፣ የዚህን መድሐኒት ስም እየጠሩ ልክ እንደተረጋገጠ የሚሠራ ነገር አድርገው ሲገልፁ የተመለከቱ የአሪዞና ነዋሪ የሆኑ ባልና ሚሰት፤ የመድሐኒቱን ስም፣ የአሳ ገንዳ ማፅጀው ኮምፓውንድ ላይ ተፅፎ ያዩታል፡፡ የአሳ ማፅጃው ውስጥ የሚገኙ ተባዮችን ነው የሚገለው፡፡
     ባልየው ምን ብሏል፣ ይሕ ኮምፓውን በቴሊቪዢን የሚያወሩት አየደለም እንዴ፡፡ ታዲይ ሁለቱም ብድግ ያደርጉና ከጨማቂ ጋር ደባልቀው መጠጣት፡፡ በ30 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለቱም በጠና ታመው ሆሰፒታል ይገባሉ፤ ባልየው ይሞታል፣ ሴትዮዋ በጠና አንደታመመች ነው፡፡
        ብዙ መማር አለብን፡ ኮምፓውንዱ ተመሳሳይ ቢሆንም የጉልበት መጠኑ ይለያያል፡፡ ለሰው የሚሰጠው የጉልበት መጠን ለአሳ ገንዳ ማፅጃው መጠን ጋር የሰማይና ምድር ነው፡፡ሁለተኛ ለኮሮና ፍቱንነቱም አልተረጋገጠም፡፡
        እንግዲህ ባራኪና ለማፅጃነት ያገለግላል ብየ ስፅፍ፣ ለማጽዳት እንኳን መጠኑ ተበርዞ ወደ አንድ አምስተኛ መውረድ አለበት፡፡
      አንደኛ ለኮሮና የሚሞከሩ መድሐኒቶች ኮምፓውንዶች የታወቁ አሉ፣ ከዚህ በፊት የጠቀስኩላችሁ ሎፒናቪር ሪቶናቪር የሚባል ለኤች አይ ቪ ህክምና የምንጠቀመበት መድሐኒት ለኮሮና አይሠራም ተብሎ ከምርምሩ ገለል ተደርጓል፡፡
         ሰለዚህ ሰዎች፣ ተስፋ በመቁረጥም ይሁን፣ ባለማወቅ፣ ወይም ከሰው የበለጡ መስሏቸው የማይታወቅ ነገር ወስደው ለአደጋ እንዳይጋለጡ ለመምከር ነው የምጥረው፡፡ በበአሁኑ ሰአት፣ የህክምና ሙያ ቀርቶ ሰለ ህክምና አንዳች ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች የሚፅፉትነ አታንብቡ፣ ሼርም አታደርጉ፡ ሼር ያደረጋችሁት ነገር፣ ያልታሰበ ሰው ላይ ደርሶ ተግባራዊ ሊሆንና አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ አንድ ነገር ብቻ ወይም አንድ በሽተኛ ብቻ አየተው ሰለ ሁኔታው በሶሻል ሜድያ የሚለጥፉ ባለሙያ የሚመስሉ ሰዎችም አሉ ከነሱም ተጠንቀቁ፡፡
       አንድ የተሠራጨ ነገር ቢኖር፣ ቫይረሱ በጨጓራ አሲድ ይሞታል ነው፡፡ ጎሽ ላይ ይህንን በሚመለከት በአጥኝ ሀኪሞች የተፃፈውን ተመልከቱ፡፡ በሠገራ ይገኛል በሚል፡፡ እንዲያውም አሜሪካ ውስጥ እየታየ ያለው፣ በዛ ያሉ ሰዎች ተቅማጥ እንደለባቸው ነው፡፡ ምነው አሲዱ በገደለው፡፡
        ሰለዚህ ሰለኮሮና የምታገኙትን ዜና ምንጭ አረጋግጡ፡፡ አታራቡት፡፡ ለዝናና ለገቢ ሲባል፣ ሰዎች ምን ያህል አሳዛኝ ነገር እንደሚፅፉ መረዳት አለባችሁ፡፡ ባለፈው ሰሞን፣ ድፍን የአሜሪካ የኤይድስ ህሙም ግማሹ ኢትዮጵያው ነው ብለው እየተቀባበሉ ሲያናፍሱ አይተናል፡፡ አግባብ ያለው የሰከነ ምላሽ ሠጥተናል፡፡ በዘህ ጉዳይ፣ ባለሙያ ባልሆን ደፍሬ አልፅፍም ለመምከርም አልሞክርም ነበር፡፡ ግን ሁሉም ነገር፣ እንደ ፖለቲካ ማንም እንደፈለገ እየተናገረና እየፃፈ የሚያስክትለውን አደጋ እያየሁ ዝም ማለትም አልችልም፡፡ ሰዎች ሰከኑ በሉ፣ ይህ ነገር በሽታ ነው፡፡ እየተደማመጥን የሚቻለንን እናድርግ፡፡ በዚህ ወቅት ትልቁ ግብ፣ አለመያዝና ከተያዙም አለመሠራጨት ነው፡፡ ሆስፒታል ውስጥ የሚደረገው ግብግብ እያወጣን ብንነግራችሁ፣ የሚመች አይደለም፡፡ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ነው፡፡ ለዛውም እኮ እኛም ራሳችን አደጋ ላይ እየወደቅን ነው፡፡
      የዛሬ ስንት አመት፣ አንድ የወንድሜ ልጅ ካሊፎርንያ እንደመጣ የማያደርገው ነገር አልነበረም፡፡ ታዲያ የክፍል ደባሉ የሆነ ልጅ ሲመክረው፤ “አንተ ልጅ የማታወቀውን መርዝ ውጠህ እንዳትሞት” ብሎ ነበር፡፡ ያ አባባል አሁንም ትዝ ይለኛል፡፡ ተመርምሮ ተጠንቶ በሰው ልክ ይሆናል ተብሎ የሚሠራ መድሐኒት እንኳን ሰው ላይ ዳርቻ ጉዳት(side effect) ያስከትል ይሆን ብለን በምንጨነቅበት አለም፣ ያገኘውን መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡
      አንዲየው ኮሮኖ በሜዲያ ሰለተነገረ፣ የመንግሥት ባለሥልጣኖችም እናውቃለን እያሉ እንደሌላ ጉደይ ለመሸፋፈን የሞከሩት ነገር ያስከተለውን ጣጣ ተመልከቱ፡፡ 

አሳዛኝ ዜና፣ በኮቪድ-19 ምክንያት የመጀመሪያው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ህይወት ማለፍ  (3/30/20)
       
            ወሳኝ መልክት ሰላለው ባካችሁ አካፍሉ 
በተለይም በዲሲ፣ ቨርጂኒያና፣ ሜሪላንድ አካባቢ የምትኖሩ

የ57 አመት ጎልማሳ የነበረ ሰው በዚህ በኮቭድ-19 ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ መሆኑን ጓደኞቹና ቤተዘመዶቹ አስታወቃል፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ኑዋሪ የነበረው ትውልደ ኢትዮጵያዊን ሞት አስመልከቶ፣ ከቤተሰቦቹ በኩል ዜናው እንዲነገርና ለሌሎች ማስገንዘቢያ እንዲሆን ፈቃድ መሠጠቱ ምስጋና የሚያሰጥ ነገር፡፡ ያም ሲሆን ማንነታቸው በተጠበቀ መልክ እንዲቆይም አሳስበዋል፡፡ ከሁሉም በፊት በሰውየው ህይወት ማለፍ ሀዘን የተሰማን መሆኑን እየገለጠን፣ ለቤተሰቦቹም ብርታቱንና መፅናናቱን ፈጣሪ እንዲሰጣቸው እንመኛለን፡፡

ተጨማሪ ሁኔታ ደግሞ፣ ባለቤቱና ልጁም በዚሁ በኮቪድ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ እነሱንም ከበሽታው እንዲያገግሙ በፀሎት እንርዳቸው፡፡ ሕይወቱ ያለፈው ይህ ኢትዮጵያዊ፣ ከአውፕላን ማረፊያ መንገደኞችን የሚያመላለስ የታክሲ ሥራ ላይ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም፣ ተጨማሪ ምክሮች መሥጠት የግድ ነው፡፡ በመሠረቱ እንዲዚህ ያልተለመደ አዲስ ተላላፊ በሽታ ቀርቶ፣ ሌሎች ብዛት ያላቸው በሽታዎች፣ በአንድ ሰው ላይ በሚገኙ ጊዜ፣ ሀኪሙ ለአካባቢው መንግሠት ወዲያውኑ እንዲያስታውቅ የሚያስገድድ ህግ አለ፡፡ ሰለዚህ ሀኪሞች ሪፖረት ያደርጋሉ፡፡ ከቆዩት በሽታዎች አንዱ የሳንባ ነቀርሳ ነው፡፡ ሌለችም የአባለ ዘር በሽታዎች ሲከሰቱ፣ ሪፓርት እንዲደረጉ ህጉ ያስገድዳል፡፡ ሪፓርት ከተደረገ በኋላ፣ በሽታው የተገኘበት ሰው የሚኖርበት መንግሠት የጤና ቢሮ ክፍል፣ በሽታው የተገኘበትን ሰው በመጠያቅ፣ የንክኪ ምርመራ ይጀምራል፡፡ በአንግሊዝኛ (Contact Investigation) ይባላል፡፡ ሰለዚህ የመንግሥት ሠራተኞች በር ቢያንኳኩ እንዳይገርማችሁ፡፡ ህግ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሀኪሞች የበሽተኛን ስም ሆነ ሌላ መረጃ አሳልፈው አይሰጡም፡፡ የሚሰጡ ከሆነ ከበሸተኛው ፈቃድ ተቀብለው ያውም በፊርማ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ፣ ለበሽተኛው ተከታይ ህክምና ወይም የስፔሻሊሰት ምክር ሲያስፈልግ ግን ሰለ በሸተኛው ያለው መረጃ ምክር ለተጠየቀው ይነገራል፡፡

ይህን የምጠቅሰው፣ በቅርቡ ሕይወቱ ያለፈው ወንድማችን በቫየረሱ መያዙ እንደታወቀ፣ የሚኖርበት አካባቢ መንግሥት፣ የንክኪ ምርመራ አድርጓል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን፣ በአሁን ጊዜ በጤናው መስክ ያሉ ሥራዎች ሰለተወጣጠሩ፣ ይህ ባይደረግስ ብየም አሰብኩ፡፡ አንግዲህ ልብ ማለት ያለብን፣ ሰውየው ከነማን ጋር፣ በምን መልክ ለምን ያህል ጊዜ፣ በምን ያህል ቅርበት ግንኙነት አድርጓል ተብሎ ይጠየቃል፡፡ በተለይም የህመም ስሜት ከጀመረው ጊዜ ጀምሮ፡፡ ይህ ሲደረግ ከሰውየው ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ይታወቁና እያንዳንዳቸው ራሳቸውን እንዲያገሉና ሰውነታቸውን እንዲያዳምጡ ይደረጋል፡፡ ይህ የሚደረገው፣ የተጋለጡት ሰዎች ድንገት ተይዘው ከሆነ እነሱም በተራቸው ወደ ሌላ ሰው እንዳያስተላለፍ ለመግታት ነው፡፡ እንደሰማነው፣ ባለቤቱና ልጁ በዚህ ቫይረስ መያዛቸው ግልፅ ተደርጓል፡፡ ይህ ሌሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ያሉ የጤና በላሙያኞችን ለመርዳት፣ በቡድን ከሚንቀሳቀሱ የህከምና ባለሙያዎች በኩል የተገለጠ ነው፡፡ የንክኪ ምርመራው ደግሞ፣ ሰውየው ከማን ተገናኘ ተብሎ ሲመረመር እርሱ ራሱም ከማን እንዳገኘው ለማወቅ ጥረት ይደረጋል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው በሸታው በስፋት ከመሠራጨቱ በፊት የተጋለጡ ሰዎችን በማግለል ወደሌሎች እንዳይዘመት ለመከላከል ነው፡፡

ከዚህ ጋር አያይዞ፣ ከሰውየው ጋር በተለይም የህመም ስሜት እየተሰማው አያለ በቅርበት ከሱ ጋር ጊዜ ያሳለፋችሁ የቅርብ ጓደኞችና የቤተሰብ አባለት፣ የመንግሥት ምክር ሳትጠብቁ፣ ራሳችሁነ በማግለል ሥርጭቱን ለመግታት ሞክሩ፡፡ አዚህ አካባቢ በሚኖሩ ኢትዮጵያውን፣ ከሟቹ ቤተሰቦች በተጨማሪ ሌሎች የተያዘሁ መሆናቸው የታወቀ ሶሰት ሰዎች መኖራቸውን እኔ ራሴ የማውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በኛ አኗኗር ሁኔታ፣ ምክርን ቸል የማለት ባህሪ፣ ቫይረሱ በፍጥነት በመሠራጨት ብዛት ያለቸው የህብረተሰቡን አባላት ሊይዝ እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡ ራሳችሁ ከሰውየው ጋር ግንኙነት ባይኖራችሁ፣ ሌሎች ከሱ ጋር ተገናኝተው ሊሆኑ ይችላሉ ለምትሏቸው ሰዎች ይህንን ምክር አካፍሉ፡፡

አንግዲህ ጥርጣሬው ያላቸው ሰዎች፣ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር ራስን ማግለል (self-quarantine)ነው፡፡ ያም ለአስራ ቀናት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ከቤት አካበቢ ተውስነው በመቀመጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያደርጉትን ግንኙት ማቆም አለባቸው፡፡ ወደ ቤታቸውም ሌላ እንግዳ እንዳይመጣ መከልከል አለባቸው፡፡

ራሳቸውን አግልለው በሚቆዩበት ጊዜ፣ በአንድ ክፍል ይወሰናሉ ማለት አይደለም፡፡ ራሳቸውን አዳምጡ ሲባል፣ በቀን ሁለት ጊዜ የትኩሳት መጠን መለካት፡፡ ሳል መከሰቱን ማወቅ፣ ራስ ምታትም እየታዬ ነው፣ የጉሮሮ መቁሰልም እይታየ ነው፡፡ ባጠቃለይ ከነበራቸው ሁኔታ ለየት ያለ ነገር ሲከሰት፣ ምልክት እንደጀመራቸው በመገንዘብ፣ ከዚህ በኋላ ራስን ከማግለል ራስን (self-isolation) መለየት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን፣ በአንድ ክፍል በመወሰን፣ ከሌሎች የቤተሰብ አባላት ጋር በማይገናኙበት ሁኔታ ነው፡፡ የህምም ስሜቱ ጠንከር በማለት፣ ትንፋሽ የማጠር ስሜት፣ ትንፋሽ መፈጠን ሲጀምር፣ ስልክ ደውለው ሰለ ሁኔታው በመግለፅ ወደ ህክምና ቦታ እንዲሄዱ ይመከራል፡፡

ሆስፒታል በማያደርስ ደረጃ ቤት ከቆዩ፣ ምልክት ከጀመራቸው ከሰባት ቀን በኋላ፣ ትኩሳቱም ምንም የትኩሳት ማብረጃ መድሐኒት ሳይወሰዱ በራሱ ከወረደ ከ72 ሰዓታት በኋላ፣ ከማግለያ ይወጣሉ፡፡ ይህ በወቅቱ ያለ አሠራር ነው ወደ ፊት ግን ሊለወጥ ይችላል፡፡ በተለይም ምርመራው ለሁሉም የሚደርስ ከሆነ፣ ከአፍና ከአፍንጫ በሚወሰድ ምርመራ ቫይረሱ አለመኖሩ ሁለት ምርመራዎቸ በ24 ሰኣት ልዩነት ከተደረጉ በኋላ ከተረጋገጠ፤ አገግመዋል ከቫይሱም ነፃ ሆነዋል ሰለሚባል ከመለያ ክፍላቸው መውጣት ይችላሉ ማለት ነው፡፡

ከሌሊት ወፍ አምጥቶ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር ሁለትን ወደ ሰዎች አሻገረ የሚባለው ተጠርጣሪው እንስሳ ይህ ሳይሆን አይቀርም

 ከዚህ ቀደም ሰለ ሳርስ ኮሮና ቫይሶች ሲገለጥ፣ ሶስቱም አደገኛ የሆኑት የኮሮና ቫይሶች መነሻቸው የሌሊት ወፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም፣ ከሌሊት ወፍ ተነስቶ በቀጥታ ወደ ሰው እይሻገሩም፡፡ ያ ማለት አሻጋሪ ሌላ እንሰሳ ያስፈልጋቸዋል፡፡

በ2002-2003 የተነሳው የሳርስ ኮሮና ቫይረስ አሻጋሪ እንሰሳ ሲቬክ ድመት የሚባል እንሰሳ መሆኑ ከታወቀ ቆይቷል፡፡ ከሳውዲ ተነስቷል የሚባለው፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ኮሮና ቫይረስ በምህፃር ሜርስ ኮሮና የሚባለው፣ አሻጋሪ እንሰሳው ግመል መሆኑ ታወቋል

ይህ፣ በታህሳስ ድንገት ብቅ ብሎ አለምን እያስጨነቀ ያለው ሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር ሁለት፣ በዝርያው ከሌሎቹ ቀደም ካሉት ጋር የሚመሳሰል ቢሆንና ከሌሊት ወፍ መነሳቱ ቢገለጥም፣ እንዴት ብሎ ወደ ሰው እንደደረሰ ከመላ ምት በላይ ብዙም የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡ ቻይናም ቢሆን በዚህ በኩል፣ ፈታ ብላ የገለጠቸው ነገር የለም፡፡ ለነገሩ፣ በሽታው የተከሰበት በውሃን ከተማ፣ የአሳና የሌሎች የጫካና የቤት እንስሳት የሚሸጡበት ገበያ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በቅርብ ጊዜ ሹልክ ብሎ የወጣ ጥናት የሚጠቁመው፣ ፀሀፊዎቹ፣ ከላይ በምስሉ የምታዩት ፓንጎሊን የሚባል እንሰሳ ነው የሚል ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

ለምን ግን ይህ እንስሳ ሊሆን ይችላል? ማለትም ምን ያህል ከሰዎች ጋር ግንኙነት አለው ለሚለው መልሱ ቀላል ነው፡፡ ይህ ዕንስሳ በጣም የሚፈለግና በብዛት በተለያየ መልክ ለገበያ የሚቀርብ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሰውነቱ እንደምታዩት ቅርፊት በመሰሉ ብዛት ባለቸው ጠጠር ወይም ጠንከር ባሉ መደረቢያዎች የተሸፈነ ነው፡፡ ለካስ፣ እነዚህ ቅርፊቶች ናቸው፣ ይህንን እንስሳ ተፈላጊነቱን የጨመሩት፡፡ ቅርፊቶቹ ከምግብነት በላይ ለመድሐኒትነት ያገለግላሉ ሰለሚባል ይህንን እንሰሳ ፈላጊና አዳኙ እንዲበዛበት አድርጓታል፡፡ እንግዲህ ከዚህ በላይ ከሰው ጋር ንክኪ የት አለ፡፡

በጥያቄና መልስ ጊዜ ከአንባቢ ወይም ከአዳማጭ አንድ ሰው፣ ሰለ ኮሮና ቫይረሶች ተጨማሪ መግለጫ ይሰጠን ብሎ መጠየቁን ሰለተመለከትኩ፣ እነሆ ስለ ኮሮና ቫይረሶች

በመጀመሪያ ኮሮና የሚለው ስም የመጣው፣ (ኮሮና ማለት ዘውድ ማለት ነው)፣ ቫይረሱን በኤሌክትሮኒክ ማይክሮስኮፕ ሲመለከቱት የዘውድ ቅርፅ ስላለው ነው፡፡ ከዘውድ ጋር የተያያዘ ስም ያላችሁ ሰዎች ይቅርታ፣ ትንሽ ለመቆጠብም አስቤ ነበር፡፡

የኮሮና ቫይረሶች በጣም ስፋት ያለው የቫይረስ ቤተሰብ አባላት ናቸው፡፡
ባላቸው የዘር ስንስለት ልዩነት ምክንያት ከአራት ምድብ ይከፈላሉ፡

አልፋ ኮሮና ቫይረስ
ቤታ ኮሮና ቫይረስ
ጋማ ኮሮና ቫይረስ
ዴልታ ኮሮና ቫይረስ

የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ፣ አልፋና ቤታ ኮረና ቫይረስ የሰውና የእንስሳት ሲሆኑ
ተከታዮቹ ጋማና ዴልታ የአእዋፍ ቫይረሶች ናቸው፡፡

በዝርያ በተጨማሪ መከፋፈል ከተፈለገ፣ የቤታ ኮሮና ቫይረሶች አንደገና በአራት ይከፈላሉ፡፡ ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ፡፡

አሁን የምናተኩረው የሰው ኮሮና ቫይረሶች በሆኑት በአልፋና በቤታ ቫይረሶች ነው፡፡

እሰካሁን ድረስ፣ የሰው ኮሮና ቫይረስ ተብለው የሚጠቀሱ ወይም የሚታወቁ ሰባት ኮሮና ቫይረሶች አሉ፣ አዲሱን ጉልበተኛ ጨምሮ ነው፡፡

ቀደም ብለው የተነሱ አብረውን ተላምደው ቀለል ያለ በሸታ፣ ጉንፋን የሚያሰከትሉት አራቱ፣ ከሁለቱም ወገን ይመጣሉ ማለትም ከአልፋና ከቤታ ቫይረስ ወገን፡፡ እነዚህ ቫይረሶች ቀደም ብለው የሚታወቁ ሲሆን፣ ከነዚህ አንደኛው ገና በ1960፣ ጉንፋን ከያዘው ሰው አፍንጫ ተገኝቶ ማንነቱ ከታወቀ ሰንብቷል፡፡ ግምቱ ምንድነው፣ እነዚህ፣ አራቱ ቀለል ያለ ጉንፋን ብቻ እያሰከተሉ ከሰው ጋር አብረው ቢኖሩም፣ ከመጀመሪያ ሲነሱ ሌሎች ከነሱ ጋር የመጡ ቫይረሶች ገዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እና ይህን አባባል ሰፋ ብናደርገው፡፡ ገዳይ ቫይረሶች ከነበሩ ለምን አሁን የሉም ብሎ አንድ ሰው መጠየቅም ይችላል፡፡ መላ ምቱ ምንድን ነው፣ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎቸ ከነቫይረሱ አብረው ሰለጠፉ ነው፣ እነዚህ በአንፃራዊ አነጋገር ለማዳ የሆኑት አራቱ፣ ተራ ጉንፋን የሚያስይዙት የቀሩት፡፡ (የዳርዊንን ነገር ካስታወሳችሁ)፡፡ እንግዲህ ገዳይና ሟች አብሮ ሰለጠፋ፣ የቀረው ህዝብ ደግሞ ከዛ የተረፈ በመሆኑ፣ የቀረው ቫይረስም ደግሞ እንደ አጥፍቶ አጥፊ አብሮ በመጥፋቱ የቀሩትን አራቱን ቫይረሶ ይዘን ኖረናል፡፡

ያ ግን እሰከ አውሮፓ አቆጣጠር 2002-03 ድረስ ነበር፡፡ ምን ብቅ አለ? የመጀመሪያው ሳርስ ኮሮና ቫይረስ፡፡ ይህ ቫይረስ እራሱ መነሻው ከቻይና ጉዋንዶግ ከሚባል ፕሮቪንስ ነው፡፡ (2002)፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ አለምን አናውጦ፣ ወደ 8ሺ ሰዎች መያዛቸው የተረጋገጠ፣ ካዳረስ በኋላ፣ (10%) አስር ፐረስንቱን ገድሎ፣ ጥፍት አለ፡፡ ለሱ የተዘጋጀው ክትባትም ጥቅም ላይ ሳይውል ቀረ፡፡ እኔ ራሴ አስታውሳለሁ፣ በዚያ ጊዜ የተላላፊ በሽታዎች ስብሰባ በሙሉ በአብዛኛው ሰለ ሳርስ ነበር፡፡ ለእንደኔ አይነቱ ባለሙያተኛ ገና የሳርስ ስም ሲጠቀስ ብዙ የምናስታውሰው ነገር አለ፡፡ ይህ ቀዳማዊ ሳርስ በዝርያው ከቤታ ኮሮና ቫይረሶች ነው የሚመደበው፡፡

ሁሉም ሰላም መሰለ፣ ዝም ዝም ተባለና፣ ከአስር አመት በኋላ በ2012 ደግሞ ሌላ ኮሮና ቫይረስ ከሳውዲ በኩል ብቅ አለ፡፡ ይሀ ቫይረስ የሚያስከትለው በሸታ ለየትም አለ፡፡ ሁሉም ቫይረሶች ዋና የበሸታ ማዕከል ያደረጉት የመተንፈሻ አካለትን ሲሆን፣ ይህ ግን ዘሎ ኩላሊት ላይ ጉብ በማለት የኩላሊት ድክመት ወይም ውድቀት ያስከትላል፡፡ አስከፊነቱም የታየው፣ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች፣ ከሶስቱ አንዱን በመግደል ነው (34 ፐረስንት)፡፡ ይህ ቫይረስ የሚድል ኢስት ኮሮና ቫይረስ ተብሎ ይታወቃል፡፡ ሜርስ ኮሮና፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ መሽጎ፣ አንዳንዴ በመንገደኛ ምክንያት ሾለክ እያለ አውሮፓም ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በ2015 በደቡብ ኮርያ በኩል ብቅ ብሎ 186 ሰዎችን መያዙ ይታወቃል፡፡ እስከ የካቲት 2020 ድረስ፣ ባጠቃላይ፣ 2500 መያዛቸው በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ሰዎች ይታወቃሉ፣ ከነዚህ መሀል 34.4 ፐርስነቱ በበሸታው ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፡፡ ለዚህ ነው ይህ ቫይረስ በነብሰ ገዳይነተ ቀዳሚውን ደረጃ የሚይዘው፣ ከኮሮና ማለት ነው፡፡ ይህ ቫይረስም ከቤታ ኮሮና ቫይረሶች ወገን ነው፡፡ ይህ ቫይረስ ያነሰው ነገር ቢኖር፣ ከሰው ወደ ሰው እንደልቡ ወይም በበቂ መንገድ አለመተላለፉ ነው፡፡ እንዳው በዛው ይቅር ሳትሉ አትቀሩም፡፡ ለሱም፣ አሜን ነው መልሱ፡፡ ይህ በጠመንጃና በገንዘብ አቅም ራሱን ከፍ ከፍ ያደረገ አለም፣ በኮቪድ ሲንበረከክ ስላየን፣ ያኛውን እዛው በቤቱ ያስቀረው ማለት የግድ ነው፡፡

ከቤታ ወገኖች፣ ሶሰተኘው ቫይረስ ደግሞ ይህ አዲሱ ጎረምሳ ነው፡፡ እንደ አዲስነቱ ያስመዘገበው ልዩ ባህሪ ምንድነው ቢባል፣ ከሰው ወደ ሰው በፍጥነትና በቀላሉ መሸጋገር መቻሉ ነው፡፡ የሚገለውም ሰው ቁጥር እንደ ዘመዶቹ ከፍ ያለ ባይመስልም፣ መግደል ከፈለገ፣ በአሜሪካ የነርሲነግ ሆምስ (አሮጊትና ሽማግሌዎች መጦርያና የህክምና ርዳታ መስጫ ማዕከል) ሲገባ የሚያደርሰው ጉደት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ አስካሁን ድረስ በአሜሪካ በጠቅላላ በኮቪድ ምክንያት ከሞቱ ሰዎች ሀያ ፐርሰንቱ ከነርሲነግ ሆም ነው፡፡ ይህ ግን በአሜሪካ ብቻ አይደለም፣ በአውሮፓ፣ በኮቪድ ምክንያት ከሚሞቱ ሰዎች ግማሹ ከነዚህ ነርሲንግ ሆም ካሉ ሰዎች መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት ገልጧል፡፡ አዲስ እንደመሆኑ ሁሉም ሰው በዚህ ቫይረስ የመያዝ ዕድል አለው፡ አነሰ ቢባል፣ ዕድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑት ላይ መጠኑ አነስተኛ ነው፡፡ እንደዛ ሆኖ ይዘልቅ ይሆን የሚታወቅ ነገር አይደለም፡፡ ዕድሜያቸው ከ19-44 አመት የሆኑት፣ “አይነካንም” ብለው የሚያስቡ በጣም ተሳሰተዋል፡፡ በአሜሪካ ዳታ እንዳየነው፣ በቫይረሱ ከሚያዙ ሰዎች አንድ ሶሰተኛውን የሚይዙት እነሱ ናቸው፡፡ ሰለዚህ ሥርጭቱ እንዳይሰፋ ማድረግ የሚገባቸውን ነገር ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡ ይህ ቫይረስ አፍሪካ፣ ከገባ ምን አይነት ባህሪ እንደሚያሳይ የሚያውቅ የለም፡፡ አፍረካ፣ በኤች አይ ቪ፣ በሳንባ ነቀርሳ ብዛት የሚታወቅ ከፍተኛ ቁጥር እንዳለ ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቢያዙ ምን እንደሚያሳዩ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ሰለዚህ ለራስም፣ ለህብረተሰብም፣ ለደጋጎቹም በማሰብ፣ ወጣቱና ጎልማሳው ቢጠነቀቅ መልካም ነው፡፡

ለማጠቃለል፣ አንደዚህ አይነት የቫይረስ ወረረሽኝ ሲነሳ፣ ቫይረሱን ብቻ ነጥሎ ማየትም ጥሩ አይሆንም፡፡ የአካባቢ አየር ለውጥ፣ የሰው ባህሪ እራሱ (ማለትም በምስሉ አንደተጠቀሰው አይነት አንስሳና ሌሎችም አሻጋሪ ሊሆኑ ከሚችሉ አንስሳት ጋር የሚደረገው ግንኙነት ሊታሰብበት ይገባል)፡፡ በአለም በአንድ ጠርዝ በኩል የሚደረግ ነገርና የሚያሰከትለው ውጤት በሌላው አለም ጫፍ መድረሱን ተመልከተናል፡፡

ኮሮና ቫይረስ የሚያሰተምረን አንድ ትልቅ ነገር ነገር ቢኖር፣ የሰው ልጅ አንድ ዘር፣ ቫይረስ ሌላ ዘር መሆኑን ነው፡፡ በሌላ መንገድ፣ በትንሹም በትልቁም ሰውን የሚያክል ፍጡር መከፋፈሉን ቆም ብለን ማሰብ ይገባናል፡፡ ይኸው ጥቃት ሲመጣ፣ ቫይረስ የሰው ዘር ነው እያጠቃ ያለው፡፡ ይልቁንስ፣ አንድ ላይ እየተጋገዝን ወደ ዕደገቱ መራመድ፣ በተጨማሪም፣ መንግሥታቱ እንደ አንጀራ ልጅ የሚያዩትንና በቂ በጀት የማይመድቡለትን የጤናውን ዘርፍ ወይም መስክ ቅድሚያ እንዲሰጠው ማድረግ የግድ መሆኑ ታይቷል፡፡ የሲንጋፖር ሰዎች አንዳደረጉት፣ የምታወቋቸውንም ሆነ፣ የማታውቋቸውን የጤና ባለሙያተኞች ባገኛችሁበት አጋጣሚ አመስግኑ፡፡ የቀራቸው ነገር ቢኖር የህዝቡ ከበሬታ ነው፡፡



መልካም ንባብ