​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

ሙከራው በንግግር ብቻ በአፍ በኩል በቂ የአየር ጠብታዎች እንደሚወጡ ያሳያል

የኮሮና ቫይረስ (SARS-CoV-2) በስፋት ሊሠራጭ የቻለበት አንዱ ምክንያት በቫይረሱ ተይዘው ግን ስሜት አልባ በሆኑ ሰዎች አማካኝነት ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች ቁጥር በዚሁ በጎሽ ድረ ገፅ በሌላ ርዕስ እንደተጠቀሰው ከ30-60 ፐርሰንት ሊሆኑ ይችላሉ ነው፡፡ ሲዲሲ ራሱ 25 ፐርስንቱን ተቀብሏል፡፡

ታዲያ እነዚህ ሰዎች፣ ካላሳላቸው ወይም ካላስነጠሳቸው፣ በመተንፈሻ አካላቸው ያለውን ቫይረስ እንዴት አድርገው ነው የሚያስወጡት፣ ከወጣስ፣ ለአይን የማታይ ጠብታዎች በንግግር ይወጡ ይሆን የሚል ጥያቄ ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ሁሉም ሰው ማሰክ ያድርግ ሲባል፣ ዋናው አላማ፣ ከእነዚህ ስሜት አልባ ከሆኑ ሰዎች ትንፋሽ የሚወጣውን የአየር ጠብታ በዛውም ቫይረሱን ለመግታት ነው፡፡ እናስ፣ ማስክ ማድረጉ ምን ያህል ያሰቀረዋል የሚል ጥያቄም አለ፡፡

ለዚህ ጥያቄ መልስ፣ በኒው ኢንግላንድ ጆርናል፣ ሰዎች ያደረጉትን ሙከራ አካፍለዋል፡፡ በሙከራቸው፣ ማሰነጠሥ ሳይሆን በንግግር ብቻ ከአፍ በኩል የአየር ጠብታዎች ሲወጡ የሚቀርፅ ካሜሪ በመጠቀም፣ በሚገርም ሁኔታ ሰውየው ሲናገር አሳይተዋል፡፡ ሰውየው ድምፁን ደመቅ ሲያደርግም በርከት ያሉ ጠብታዎች ሲወጡ ይታያል፡፡ እንዲሁም ለስለስ አድርጎ ቢናገርም የተወሰነ መጠን ይወጣል፡፡

እነሱ ሰውየው እንዲናገር ያደረጉት አረፍተ ነገር፣ “Stay home” የሚል ነበር፡፡ እራሳችንም ቢሆን መስታውት ፊት ቆመን የተለያዩ ቃላትን እየተጠቀምን እንሞክርና፣ መስታውቱ ላይ ምን ያህል ጉም እንደሚያርፍ እንመልከት፡፡ እኔ ያገኙት “አሁን” የሚለውን ቃል ነው፡፡ ሌሎቹም ይኖራሉ፡፡ እስዎም ይሞክሩት፡፡

ከዚህ ቀደም እንደተጠቀሰው፣ ከበድ ያሉት የአየር ጠብታዎች፣ በእንጥሻና በሳል ሲወጡ፣ ከሁለት ሜትር ወይም ስድስት ጫማ በላይ ርቀው እንደማይሄዱ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ ከበድ ያሉት በቫይረስ ጢም ብለው የተሞሉ ሰለሆኑ በተጋለጠው ሰው ወደ ወስጥ በመዝለቅ ቫይረሱ እንደገና ተራብቶ በሽታ የማምጣት ወይም ተሸካሚ የማድረግ መጠን አላቸው፡፡ በሌላ ጥናት እንደታየው፣ ከበድ ያላሉ ብናኞች እሰከ ስምንት ሜትሮች ርቀት ድረስ ይሄዳሉ፡፡

እንግዲህ ሰው ሲናገር፣ በአፍ በኩል በቂ መጠን የአየር ጠብታዎች ከወጡ፣ በአጠገብ ያለ ሰው ላይ ቫይረሱን የሚያስተላለፍ አቅም ወይም መጠን ያላቸው ጠብታዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ በተፈጥሮ አንዳንድ ሰው ሲናገር፣ ከአፉ፣ አይደለም በአይን የማይታይ፣ በአይን የሚታዩ ፍንጣሪዎች ይታዩበታል፡፡ ቀልድ ለመቀለድ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም አንድ ሰው እንዲሁ ሲናገር ምራቁ ሲረጭ ይታይ ሰለነበረ፣ ጓደኞቹ “ዝናቡ” የሚል ቅፅል ስም ሠጠተውት ነበር፡፡ ዝናቡን, ኮሮና ባይዘው ይሻላል፣ አለዚያ አገር ይጨርሳል፡፡ ካልሆነም አፉን በጨምብል ወይም ማስክ መሸፈን ይኖርበታል፡፡

አሃ፣ ተመራማሪዎቹ. ቀጥለው ያደረጉት ነገር፣ ሰውየውን ማስክ አልብሰው ያንኑ አረፍተ ነገር እንዲናገር አደረጉት፡፡ ከዚህ ሁሉ ለምን ቪዲዮውን አታዩትም፡፡  

ምንም ጠቃሚ ነገር ሲወጣ አልታየም፡፡ እንግዲህ የታመመውም፣ ሰሜት አልባውም ማስክ የሚያደርግ ከሆነ፣ መተላለፉን ረገብ ያደርገዋል፡፡ ይህ ሲባል ግን ርቀት መጠበቅን፣ እጅ መታጠብን፣ ከሰዎች ጋር የማይፈለግ ግንኙነት ወይም መቀራረብን ማቆምና በየቤቱ መከተተን ይጨምራል፡፡ ዋናው የገደበው በየቤቱ ሰብሰብ ማለቱ ነው፡፡ መልክቱ ግልፅ ነው፡፡ አፋችሁን ሸፈን አድርጉ፡፡ ለአሁኑ ትውልድ እንግዳ ቢሆን ነው እንጂ፣ የድሮዎቹ እኮ አፋቻውን በጋቢ ሸፈን አድርገው ነበር የሚስሉት፡፡


https://www.nejm.org/doi/full/10.1056/NEJMc2007800?query=featured_coronavirus


መልካም ንባብ