Health and History

በኮቪድ ተይዘው የነበሩ ሰዎች፣ መልሰው በኮቪድ ይያዛሉ ወይ?

መውደድ እንደገና 08/29/2020

 የፍቅር አይደለም፣ የፈረደበት ኮቪደ-19 ነው፡፡

ከዚህ ቀደም እኔም ራሴ ብሆን በማውቀው ሰው በህክምና፣ በኮቪድ-19 ተይዞ ካገገመ በኋላ እንደገና በተመሳሳይ ሁኔታ ሲታመም ታዝቤያለሁ፡፡ ሰውየው አንደገና የታመመው፣ የቤተሰብ አባል የሆነ ሰው ከታመመ በኋላ ነበር፡፡ ያን ጊዜ፣ ጥያቄው፣ አንደገና ወዲያውኑ ከተያዘ፣ መጀመሪያ ከያዘውና ከዛም ካገገመ በኋላ ምንም አይነት የመከላከያ ዘዴ አልነበረውም የሚል ነበር፡፡ እንደዛ ከሆነ ደግሞ፣ ሰዎች መልሰው ተመላልሰው ሊያዙ ይችላሉ ማለት ነው(Reinfection)፡፡ የዚህን ሚስጥር ማወቅ  ብዙ መልስ የሚሠጥ ነገር አለው፡፡

እንግዲህ በጥርጣሬ ላይ እያለን፣ ወደ መጠንቀቁ እየመከርን ባለንበት ወቅት፣ ከሆንግ ኮንግ በኩል በመረጃ የተደገፈ ዘገባ ይቀርባል፡፡፡ የ33 አመት የሆነው ሰው በማርች 26 ታሞ ከዳነ በኋላ፣ እንደገና በኦገስት 15 ይያዛል፡፡ በሁለቱም ጊዜ ሰውየውን የያዘው ቫይረስ በመወሰድ(ፈይሎጀነቲክ) የሚባል ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ ባጭሩ የቫይረሱን ዝርያ ማጥናት ነው፡፡

ይህ ቫይረስ ወደ 30ሺ የሚሆኑ የዝርያው አይነት ወይም የዘርገ ሀረጉን የሚወስኑ ኮዶች አሉት፡፡ የዝርያ ለውጥ የሚመጣው ከነዚህ ከ30ሺ ኮዶች ሁለቱ ወይም ሶስቱ ከተቀየሩ፣ ዋናው ሀረጉ ኮሮና ቢሆንም፣ ለየት ያለ አዲስ የኮሮና ቫይረሰ ትውልድ ይሆናል፡፡

ታዲያ በሁለቱም የህመም ጊዜ  ሰውየውን የያዙት ቫይረሶች ጥናት ሲደረግ፣ ሁለቱም ቫይረሶች በመጠኑ የተለየ ዝርያ ያላቸው ሆነው ይገኛሉ፡፡ ማለትም ሰውየው በኦገስት ሲታመም መጀመሪያ በያዘው ቫይረስ ምክንያት ያገረሸ በሽታ ሳይሆን፣ በሌላ ቫይረስ በመያዙ ነው፡፡ እረፉት፣ አንዱ ትልቁ ሥጋት ይህ ነው፡፡ ሁለት ሥጋት በሉት፡፡

አንደኛ፣ በቫይረሱ የተያዘ ሰው በቂ መከላከያ በሰውነቱ ውስጥ አለመኖሩ በመጠኑ ለየት ባለ ሌላ የኮሮና ቫይረስ መያዙ ነው፡፡

ሁለተኛ፤ የኮሮና ቫይረስ ቁ2 (ኮቪድ-19ን የሚያመጣው) በተራባ ቁጥር አዳዲስ ልጆች እየፈጠረ መሄዱ ነው፡፡ አዲስ የተፈጠረው ቫይረስ ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም ያልተያዙ ሰዎችን፣ ተይዘው የነበሩ ሰዎችንም መያዝ ከቻለ ሥርጭቱ ማባሪያ የለውም፡፡ ለዚህ መፍትሄው ላለመያዝ፣ ከዛም ቫይረሱን ላለማዛመት የሚገባውን ጥንቃቄ ሳይሰላቹ ማድረግ ነው፡፡

ሌለው፣ ሶስተኛ ሥጋት ደግሞ፣ ይህ እየተቀየረ የመጣው አዲስ የቫይረሱ ዝርያ፣ ባህሪውን ይቀይር ይሆን ነው፡፡ ባህሪውን መቀየር ማለት ደግሞ፣ አስከፊ በሽታ ማምጣት፣ ሰዎችን የመግደል ችሎታ መጨመር ነው፡፡

በሆንግ ኮንግ ሰውየ ስንገረም፣ ከአውሮፓ በኩል ሌላ ዘገባ ወጣ፡፡ ይህም፣ ሁለት ሰዎች እንደገና በኮሮና ቫይረስ ቁ 2 መያዛቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

መልክቱ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ያገገሙ ሰዎች፣ እንደገና እንያዝም ብለው እንዳይዘናጉ ነው፡፡ እንዲያውም ከመጀመሪያው በኮሮና ቫይረስ እንዲያዙ ያደረጋቸውን ሁኔታ መልሰው በመገምገም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዝ፣ ይህ ቫይረሰ ብዛት ያላቸው አዳዲስ ዝርያዎችን እየፈጠረ መሄዱ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚፈጠረው፣ ቫይረሱ ራሱን ለማባዘት ወይም ከመጠን በላይ በሚራባበት ጊዜ በሚፈጠር ስህተት አንድ ወይ ሁለት ወይም ከዛ በላይ የዘር ሀረጉን የሚፈጥሩት ኮዶች መሳሳት ነው፡፡ አንግዲህ አዲስ የተፈጠረው በመጠኑም ቢሆን ሳት ያለ ኮድ ያለው ቫይረስ መራባት ከቻለ የራሱን ዘር እያስፋፋ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

ከወደ ቦሰትን በዘለቀ መረጃ፣ ወደ ቦስተን ወደ ስምንት ጊዜ የኮረና ቫይረስ የገባ ሲሆን፣ በቦሰተን ተስፋፍቶ ከዛም አልፎ አስከ አላስካና ሲንጋፖር ድረስ የተዛመተው ግን የአንድ የተለየ ቫይረስ ዝርያ ብቻ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ የተነሳው የአንድ ካምፓኒ አመታዊ ስብሰባ ላይ በተገኝ አንድ ግለሰብ አማካኝነት ነው፡፡ በየካቲትም ሰለነበር፣ ምንም ያልጠረጠሩት የካምፓኒው ሰዎች ሲተቃቀፉ፣ ሲዝናኑ ከርመው፣ ተስብሳቢዎች ወደ የቤታቸውና አገራቸው ሲመለሱ ቫይረሱን ይዘውት ሄዱ፡፡ ቦሰተንም ቆየት ብሎ ይህ ቫይረስ በመጠለያ ቦታዎች ድረስ ዘልቆ በመሄድ ብዙ ሰዎች መያዙን ባወጡት ጥናታዊ ፅሁፍ ገልጠዋል፡፡

አንድ ሰው፣ አንደ የቫይረስ ዝርያ ከአንድ ቦታ ብቻ ተነስቶ ተሰብሳበዊንም ከዛም አልፎ ሌሎችንም ሲይዝ በምስክርነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው  Super spreading event የሚባለውም ይህ ነው፡፡

ከዚህ መማር የምንችለው፣ በቂ ጥንቃቄ ካልተደረገ በስተቀር ለማሠራጨት አንድ ሰው ይበቃል፡፡ ይህንን ቫይረስ የሚያመላልሰው ሰው ነው፡፡ ሰውና ሰው ከተገናኘ ደግሞ ችግር ይፈጠራል፡፡ ችግሩ፣ አስተላላፊው ሰው የህመም ስሜት ላይኖረው ይችላል፡፡ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በዚህ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለ ከሆነ ከፍ እያለም ከሄደ፣ ለጊዜውም ቢሆን ከሰዎች ጋር የሚደረገውን ግንኙነት መቆጠብ ያስፈልጋል፣ በተለይም በቤቶች ወይም በአዳራሾች ውስጥ መሰባሰብ ካለ፡፡

መረዳት የሚገባን፣ የምናደርገው ሰርጂካል ማስከ፣ በቫይረሱ ከተያዘው የሚወጣውን ቫይረሰ ይገድበው እንደሆነ እንጂ፣ ላልተያዘ ሰው ሙሉ በሙሉ የመከላከል ችሎታው ርግጠኛ አይደለም፡፡ ለመጋለጥ ዋና ምክንያቶች ቫይረሱን ከሚተነፍሱ ሰዎች አጠገብ መገኘት፣ ከተገኙም ቆይታው ረዥም ጊዜ በሆነ ቁጥር አደጋው እየጨመረ እንደሚሄድ ነው፡፡

ማስክ አድርጉ ሲባል ብትክክል መሆን አለበት፡፡ አፍና አፍንጫ በደንብ ተሸፍኖ፣ ትንፋሽ በጎን የማየወጣበት ሁኔታ መሆን አለበት፡፡ አንዳንድ ሰው ማስክ ሲያደርግ፣ በጎን በኩል ጣት ማሾልክ የሚያስችል ክፍተት ይታያል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ፣ አፋቸውን ብቻ ዘግተው፣ አፍንጫቸውን አይሸፍኑም፡፡ ዋናው የቫይረሱ መዘጋጃ ቦታ አፍንጫ ነው፡፡

በጤና መስኩ፣ እንደምታውቁት፣ ሰርጂካል ማስክ ሳይሆን፣ N95 የተባለ ማስክ ነው የሚደረገው፡፡ እሱም ቢሆን በትክክል መሸፈን መቻሉን ለማረጋገጥ እያንዳንዱ ጤና ሙያተኛ Fit testing አድርጎ ነው፡፡ ማስኩ በተለያየ መጠን ሰለሚመጣ ባለሙያተኛው የሚስማማውን መጠን ካደረገ በኋላ፣ ማሰኩ ላይ የሚረጭ ነገር አለ፡፡ የተረጨበት ሰው ምንም ስሜት ካልተሰማው፣ ማስኩም አደራረጉም ትክክል ነው፡፡ አለበለዚያ የተረጨውን ነገር መቅመስ ከቻለ፣ ማስኩ ወይ በትክክል አልተደረገም ወይም ትክክለኛው መጠን አይደለም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ላይ እንግዲህ ፌስ ሺልድ የሚባል መስታውት ነገር አይንን እንዲሸፍን ተደርጎ ነው የጤና ባለሙያተኞች የሚሠሩት፡፡ እንደዛም ሆኖ፣ በአሜሪካ ከ130ሺ በላይ የጤና ባለሙያተኞች በዚህ ቫይረስ መያዛቸው ይታወቃል፣ ከነዚህ መሀል ወደ 662 ነርሶች፣ ሀኪሞችና ሌሎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ (የሲዲሲ መረጃን ይመልከቱ)

ይህን ቫይረስ መናቅም፣ መዳፈረም ጉዳት አለው፡፡ እያወቁ ቫይረሱን የሚያሻግሩ ሰዎች በሰማይ ሳይሆን በምድር የሚጠየቁበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም፡፡ በቫይረሱ ሥርጭት ምክንያት ኢኮኖሚው የተዘጋበት ህብረተሰብ ክፍል እነዚህን ሰዎች በክፉ ቢያያቸው የሚገርም አይሆንም፡፡ መንግስት፣ የንግዱና የሌላው ኢኮኖሚ፣ በትግስት የሚጠብቀው ነገር ቢኖር፣ የአካባቢው ሥርጭት ከ1 ቁጥር በታች እንዲሆን ነው፡፡ ማለትም አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ከአንድ ሰው በላይ አለማስተላለፍ ማለት ነው፡፡ የዋሸንግተን፣ ዲሲ ከተማ፣ ይህ ቁጥር ከ1 በታች ሰላልሆነ፣ ከphase 2  ወደ phase 3 መውረድ አልቻለም፡፡ ሥርጭቱ በቀጠለ ቁጥር፣ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎችም፣ ሰዎች እንዲሰባበሰቡ የሚያደርጉ ጥሪ የሚያቀርቡ ሰዎች ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ የጠራናቸው ሰዎች ባህሪ ነው ብሎ ዝም ማለትም አይቻልም፡፡ እያመመው የሚመጣ ሰው መኖሩ ከታወቀ፣ ወይ አለመጥራት ወይ ደግሞ ይህ ሰው እንዳይመጣ አስፈለጊውን ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ ነው፡፡ በማህበረሰባችን ውስጥ ቫይረሱ ከሚገባው ቁጥር በላይ መኖሩን መገመት አያዳግትም፡፡ በደንብ ከማውቀው፣ በዲሲ፣ የቫይረሱ ሥርጭት መጠን ከሌሎች የዲሲ ክፍሎች በላይ በአፍሪካን አሜሪካውን ላይ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከዲሲ አማካይ በላይም ነው፡፡ በዚህ ቫይረስ ሥርጭት መቀጠል ማን እየተጎዳ መሆኑን መግለፅም አያስፈልግም፡፡


መልካም ንባብ፣ አካፍሉ

በኮቪድ-19 ተይዘው የነበሩ ሰዎች ለምን ያህል ጊዜ መከላከያ ይኖራቸዋል?

በኮቪድ-19 ተይዘው የነበሩ ሰዎች በበሽታው ተመልሰው ይያዛሉ ወይ? 01/19/2021

በአለማችን የዚህ በሽታ ሥርጭት እየጨመረ፣ እንደቦታው ደግሞ ብዙ ሰዎች እየገደለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሀል በአሜሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት አራት መቶ ሺ ሰዎች መሞታቸውንና፣ በካሊፎርንያ ደግሞ በየስድስት ደቂቃዎች በኮቪድ ምክንያት አንድ ሰው እየሞተ መሆኑን ዘንግተን የምናልፈው ነገር አይደለም፡፡

አሁን ጥያቄ እየሆነ የመጣው፣ ብዙ ሰዎች በምርመራ ታወቀም አልታወቅም በሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር 2 መያዛቸው በሚታወቅበት ሁኔታ በቫይረሱ ተይዘው የነበሩ ሰዎች ሁኔታ፣ መልሰው ይያዙ ይሆን፣ መልሰው ያስተላለፍ ይሆን፣ መልሰው ይታመሙ ይሆን የሚሉ ጥያቄዎች ከሰዎችም ከባለሙያተኞችም እየቀረበ ነው፡፡ ከተከሰተ አንድ አመት ያለፈው ይህ ቫይረስና በሽታው በተከሰተበት ጊዜ ውስጥ የታየውና የተጠናውን ነው ማወቅ የምንችለው፡፡

በቫይረሱ ተይዘው የነበሩ ሰዎች፣ በመያዛቸው ብቻ ለስድስት ወራት መከላከያ ሊኖራቸው እንደሚችል በተደጋጋሚ የወጡ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ የስድስት ወሩ ግምትም ነበረን፡፡ ለምን ብትሉ ከዚህ ቀደም መጥተው ተላምደውን በየጊዜው ጉንፋን የሚያስዙን አራቱ ቀደምት የኮሮና ቫይረሶች ጉንፋን ሲያስዙን የመከለከያ አንቲቦዲው ለስድስት ወራት ብቻ እንደሚሠራ ሰለሚታወቅ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ በተለይ በአፍሪካ፣ ጉንፋን አመት እስከ አመት ድረስ የሚከሰተው፡፡

የመከላከል አቅሙ ለስድስት ወራት ከቆየስ ምን ያህሉ ሰው ነው ለዚያን ያህል ጊዜ መከላከያ የሚኖረው የሚል ጥያቄ አለ፡፡ በህክምናው አለም መቶ ፐርስንት የሚባል ነገር አንድ እንቁ ውድ ነው፡፡ ከአንድ በእንግሊዝ አገር በተደረገ ጥናት፣ ከሰኔ እስከ ህዳር ባደረጉት ጥናት፣ በቫይሱ ተይዘው ከነበሩ ሰዎች 83 ፐርስንቱ ለአምስት ወራ መልሰው ከመያዝ የሚያስጥል አንቲቦዲ መጠን ነበራቸው የሚል መረጃ ለህዝብ ቀርቧል፡፡ ችግር ሰለማይጠፋ፣ እዚህ ላይ አንድ ችግር ታይቷል፡፡ በበሽታው ተይዘው የነበሩት ሰዎች፣ ሰውነታቸው በፈጠረው አንቲቦዲ ምክንያት መልሰው የመያዙ ዕደሉ በጣም ያነሰ ቢሆንም፣ የተወሰኑ ሰዎች መልሰው መያዝ እንደሚችሉም ታይቷል፡፡ ለውጡ የታየው፣ ጥቂትም ቢሆኑ፣ መልሰው የተያዙት ሰዎች፣ መጀመሪያ ሲያዙ አንደነበረው የበሽታ ስሜት አይታይባቸውም፡፡ ይህም ከእንቲቦዲ ጋር በተያያዘ፣ ክትባትን ጨምሮ የሚጠቀስ ነገር ነው፡፡ ባያስጥልም በሽታውን ያቀለዋል የሚባል ነገር አለ፡፡ ይህንን በሌሎች ክትባቶች ላይ ያሰተዋልነው ነገር ነው፡፡ በአዲሶቹ ክትባቶች ጥናትም ላይ ቢሆን፣ ክትባቱን ወሰድው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በጣም በጠና እንደማይታመሙ ተዘግቧል፡፡ ሰለዚህ የክትባትም ሆነ የተፈጥሮ መከላከያ ሲፈጠር ሁለተኛው ጠቀሜታ መሆኑ ነው፡፡

ሌላው ነገር ይህን ቫይረስ የርግማን የሚስመስለው ግን፣ እነዚህ በቫይረሱ ተይዘው የነበሩና ያገገሙ፣ ለአምስትም ሆነ ለሰድስት ወራት የሚከላከልላቸው እንቲ ቦዲ ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ባይታመሙም ከፍተኛ መጠን ያለው ቫይረስ በሰውነታቸው ይዘው፣ ሳይታመሙ ቫይረሱን ማስተላለፍ ይችላሉ የሚለው መረጃ መቅረቡ ነው፡፡ ለነገሩ ነው እንጂ ከጥዋቱም ቢሆን እኮ የበሽታ ምልክት ሳይሰታይባቸው፣ ቫይረሱን የሚያስተላልፉ ሰዎች በብዛት መኖሩ ነው የዚህን ቫይረስ ሥርጭትም ያገነነው፡፡ አነዚህ ሰዎች ራሳቸው ባይታመሙ ሌሎችን ማሳመም የሚችል ቫይረስ ተሸካሚ ናቸው ማለት ነው፡፡ ለምን ሁሉም ማስክ ያድርግ እንደምንል አሁን ግልፅ ሆነ ወይ?

በአንግሊዝ አገር ተጠንቶ British Medical Journal በተባለው መፅሄት የቀረበውን አሃዛዊ መረጃ ላካፍላችሁ፡፡ በመረጃ የተደገፈ ዕውቀት ጥሩ ነው፡፡ የአገሪቱ የጤና ሠራተኞች በበጎ ፈቃድ የተሳተፉበት ጥናት ነበር፡፡ ተሳታፊዎቹ በሁለት ጎራ ተከፈሉ፡፡ አንደኛው ወገን ኮቪድ የሌለባቸው፣ ማለትም በምርመራ በኩል ከዚህ በፊት ለኮቪድ-19 አለመጋለጣቸው የታወቁ ሰዎች፡፡ ሁለተኛው ጎራ ደግሞ፣ ከዚህ ቀድም በኮቪድ-19 ለመያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ናቸው፡፡ ጥናቱ የተደረገው ከሰኔ እስከ ህዳር ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ክትትል የተደረገውም፣ ሁለቱም ወገኖች በሁለት እሰከ አራት ሳምንት ውስጥ በድግግሞሽ ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ ምርመራውም መደበኛው PCR የሚባለውና እንቲቦዲ ምርመራ ነበር፡፡ በየሁለት ሳምንት ደግሞ፣ ለቫይረሱ መጋለጥና አለመጋለጣቸውን እንዲሁም የበሽታ ሰሜትና ምልክት መኖሩና አለመኖሩነ የሚገልፁበት መጠይቅ እንዲሞሉ እየተደተረገ ነበር፡፡

ቁጥራቸው ሲታይ 14፣173 (68%) የሚሆኑት በኮቪድ ካልተጋለጠው ወገን፣ 6614 የሚሆኑት ደግሞ በኮቪድ ተይዘው ከነበሩት ወገን ነበሩ፡፡ ከጠቅላላ ተሳታፊዎች መሀከል የተሳታፊዎቹ አማካይ ዕድሜ 45.9 አመት ሲሆን፣ 84% ሴቶች ነበሩ፡፡ በህዳር 24፣ ሲታይ በኮቪድ ካልተጋለጡት መሀከል 409 አዲስ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ይገኛሉ፡፡  ከነዚህ መሀል አብዛኞቹ 249 የመሆኑት የበሽታ ሰሜት ነበራቸው፡፡ 40 የሚሆኑት የበሽታ ስሜት ያልነበራቸው ሲሆነ ወደ 28 የሚሆነት ደግሞ መጠይቁን አልሞሉም፡፡

በሌላ በኩል፣ ከዚህ ቀደም በኮቪድ ተይዘው ከነበሩት መሀከል፣ 44 እንደገና የተያዙ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መሀል 15ቱ የበሽታ ሰሜትና ምልክት ነበራቸው፡፡

ከዛኛው ቡድን ጋር ማለትም በኮቪድ ተይዘው ያልነበሩ ተሳታፊዎች ጋር ሲወዳደር፣ በኮቪድ ተይዘው የነበሩ ሰዎች ላይ 83% የሚሆኑት በቫይረሱ ተመልሰው አልታያዙም፡፡ በጣም ቁጥራቸው ካነሰው በቫይረሱ ተመልሰው የተያዙት፣ ጊዜው ሲታይ ተመልሰው የተየዙት በአማካይ 160 ቀናት ካለፉ በኋላ ነው፡፡ ለዚህ ነው ለአምስት ወራት ይከላከላል የሚለው ሃሳብ የቀረበው፡፡ እንግዲህ ከዚህ በፊት ተይዘው የነበሩት ሰዎች ተመልሰው ቢያዙም፣ ባደረጉት ስሌት ከዚህ ቀደም ሲያዙ ህመም ሰሜት የነበራቸው ሰዎች ደግሞ ተመልሶ የመያዝ ዕደላቸው በዘጠና ፐርስንት የቀነሰ ነው፡፡ ወይም በዘጠና ፐርሰንት መልሰው አይያዙም ለማለት ነው፡፡

አጥኝዎቹ በመደምደሚያቸው የሚሉት፣ የዚህ ጥናት ውጤት አሁን ያለውን የክትባት ሁኔታና አሁን እየተከሰተ ያለውን አዲስ የኮሮና ቫይረስ ሁኔታ የሚያስረዳ ወይም የሚጠቁም መረጃ የለም ነው፡፡

ዋነው ነገር፣ መቼም ሁሉንም መከላከል ካልተቻለ፡፡ በቫይረሱ ቢያዙ ከፍተኛ የህመም ደረጃና የህይወት ዕልፈት ደረጃ የሚደርሱ ተጠቂ ሰዎች እንዳሉ ሰለሚታወቅ፣ ቫይረሱ ወደነሱ እንዳይሄደ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነው፡፡ በሀገር ቤት ደረጃ በተለይ እነዚህን የዕደሜ ባለፀጋ ሰዎች ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ርቀት መጠበቅ፣ ማስክ ማድረግ፣ ከታመሙ ወይም ከተጋለጡ ራስን ማግለል ወይም ከነሱ መራቅ ነው፡፡ ትዝ ይለኛል፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን ለዕጩነት ሁሉም በየፓርቲያቸው ሲወዳደሩ፣ የሚኒሶታ ክፍለ ሀገር ሴናተር የሆነቸው ክሎባቸር፣ ገና በጊዜ፣ ባለቤቷ በኮሮና ተይዞ ነበር፡፡ እናም እሷ፣ ሰውየውን ትታ የጓኛዋ ቤት ስትሰነበት አስታውሳለሁ፡፡ ይሄም አለ ለካ፡፡ አዛውንቶችን ጠብቁ፡፡

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic