​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

ቢሲጂና ኮቪድ-19 (BCG and COVID-19) 5/3/20

ከዚህ ቀደም፣ በጥናት መልክም የተለቀቀ፣ ያንንም ተከትሎ በማህበራዊ ሜዲያ BCG ቢሲጂን በሚመለከት የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ታይቷል

ቢሲጂ BCG በነገራችን ላይ ለሳንባ ነቀርሳ መከላከያ እንዲሆን በክትባት መልክ ሲሰጥ የኖረና አሁንም የሚሠጥ ነገር ነው፡፡

ጥያቄው፣ ይህንን ክትባት መውሰድ በኮቪድ በሽታ በተያዙ ሰዎች ላይ ቀለል ያለ ህመም አንዲኖራቸው ያደርጋል ወይ ነው፡፡ የአለም የጤና ደርጅት፣ በይፋ በሰጠው መግለጫ ቢሲጂን መውሰድ በኮቪድ-19 ቫይረስ ከመያዝ ለማስጣሉ መረጃ የለም ይላል፡፡ (WHO scientific brief, 12 april, 2020)

በዚህ መግለጫው፣ የአለም ጤና ድርጅት፣ ከዚህ በፊት በድረ ገፅ የወጡ ሶስት ጥናቶችን በመገምገም፣ አንደኛ፣ አነዚህ የወጡ ጥናቶች፣ እንደ መደበኛ ሳይንሳዊ ጥናቶች በአቻ ባለሙያተኞች ሳይገመገሙ ነው ለህዝብ የቀረቡት፡፡ በተጨማሪም፣ የወጡት ፅሁፎች ባለቤቶች ያወዳደሩት፣ ቢሲጂ ለህፃናቶች በሚሠጥበትና በማይሠጥባቸው አገሮች መሀል፣ ክትባት የተሠጠባቸው አገሮች በኮቪድ-19 ብዙም አልተጠቁም ነው የሚሉት፡፡ ያ ነው እንግዲህ ስሜት የፈጠረው፡፡ ነገር ግን፣ ጥናቶቹ ሲካሄዱ የጥናቱን ውጤት ከማጠቃለል በፊት፣ የታየውን ውጤት ወደ አንድ አቅጣጫ ወይም ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚወሰዱ በጥናቱ ያልተካተቱ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህ በደንብ ካልተጠኑ በጥናቱ ላይ መደምደሚያ መስጠት አሰቸጋሪ ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ፣ ለኮቢድ-19 በቂ ምርመራ አልተደረገምና ምርመራ በበቂ ሳይደረግ፣ ክትባቱን የወሰዱ አገሮች ትንሽ ኮቪድ ነው ያለባቸው ማለት ይከብዳል፡፡ ሌሎች የጥናቱን ውጤት ድምዳሜ ብቃት ሊያውኩ የሚችሉ ተጨማሪ ሁኔታዎች አሉ፡፡

ለመሆኑ BCG ( Bacille Calmette-Guerin) ክትባት በዚህ ደረጃ ሊጠና ያበቃው ለምን ይሆን

አንደኛ፡ ይህ ክትባት በመደበኛነት አገልግሎት ላይ የሚውለው የሳንባ ነቀርሳን (Tuberculosis) ለመከላከል ነው፡፡

ሁለተኛ፡ ከዚህ ቀድም በተደረጉ ጥናቶች፣ BCG የሽንት ፊኛ ካንሰር ላይ ርዳታ መሥጠቱ የታየ ነገር ነው፡፡

ከነዚህ በተጨማሪ BCG መውሰድ የመተንፈሻ አካላት ላይ የሚደርሱ ህመሞችን እንደሚከላከል ወይም እንደሚቀንስ በተለያዩ አገሮች የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ (በጊነ ቢሳዎ፣ በደቡብ አፍሪካ)

ሌላ የታየ ነገር ቢኖር BCG፣ የሎው ፊቨር Yellow Fever, ክትባት የወሰዱ ሰዎች በክትባቱ ምክንያት የየሎው ፊቨር ቫይረስ መባዛትን ይቀንሳል የሚል መረጃ አለ፡፡

በመሠረቱ፣ የ BCG ክትባት ሊሠራ የሚችለው፣ የሰውነት የመከላከያ አቅም (Immunity) ላይ ለውጥ በማድረግ ወይም የማጠናከር ሁኔታ ስለሚፈጥር ነው፡፡

ማስታወስ ያለብን፣ ሰውነት፣ ተላላፊ በሽታ የሚያሰክትሉ ቫይረሶችና ባክቴሪያዎችን፣ በራሱ በሚያደርጋቸው ሴሎችና ሌሎች ፕሮቲኖች፣ ኬሚካሎቸን በመጠቀም ጠርጎ በማጥፋት ነው ከበሽታ የሚያድነን፡፡ እና ይህን የመከላከያ አቅም በውጭ በሚሠጡ ነገሮች፣ ማነቃቃት ወይም ማጠናከር ሰውነት በራሱ ለሚያደርጋቸው የበሽታ መከላክል ተግባሮች ርዳታ መስጠት ይቻላል ነው፡፡

ሀሳቡን ትልቅ ግንዛቤ በመሥጠት በአሁኑ ወቅት ሁለት ጥናቶች በኔዘርላንድና በአውስትራሊያ አይተካሄዱ ነው፡፡ የአለም የጤና ድርጅትም፣ የነዚህ ሁለት ጥናቶች ውጤት አስኪወጣ ድረስ መጠበቅ አለብን ይላል፡፡

አንግዲህ BCG ክትባት ይከላከላል ተብሎ ስለተወራ፣ በዚህ ምክንያት ከሚከሰቱ ችግሮች አንዱ፡፡ ለተጠቃሚዎች መድረስ የሚገባው ክትባት በዕጥረት ምክንያት ላይደርስ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ አንደተወለዱ ይህንን ክትባት ማግኘት የሚገባቸው ህፃናት ለቱበርኩሎሲስ አደጋ እንዲጋለጡ ያደርጋል፡፡

ሁለተኛው ነገር ደግሞ፣ ገና ባልተረጋገጠ በዚህ አይነት የዜና ሥርጭት ምክንያት መዘናጋት ይፈጠራል፡፡ እንደውነቱ ከሆኑ፣ በኢትዮጵያ የተወለደና ያደገ ሰው፣ ይህንን ክትባት ሊያገኝ እንደሚችል ነው፡፡ እናም ይህ ከአመታት በፊት የተወሰደ ክትባት የኮቪድ-19 በሽታን መከላከል ወይም ማለሳለስ መቻሉ የሚታወቅ ነገር አይደለም፡፡

ሰለዚህ ሁላችንም ቢሆን፣ በተባራሪ ወጥተው፣ ሳይገመገሙ ለአንባቢ የሚቀርቡ ፅሁፎችን ስለ ጥንካሪያቸው መጠየቅ መልመድ አለብን፡፡ የተፃፈ ሁሉ እውነት አይደለም፡፡

ይህንን BCG ክትባትና ኮቪድ-19 በሚመለከት፣ ጥናት መደረጉ ራሱ አንድ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የሚረዳ ቢሆን ሁሉም ሰው በምሰጋና የሚቀበለው ነገር ነው፡፡ የጥናቱን ውጤት እሰክምናውቅ ድረስ በትግሥት እንጠብቅ፡፡ አሰከዚያ ድረስ፣ BCG ክትባት ኮቪድ-19ን በሚመለከት የሚረዳው ወይም የሚጎዳው የተረጋገጠ ነገር ሰለሌ፣ ሥርጭቱን በመከላከል እንቆይ፡፡