Health and History

Community health 

education in Amharic 

ኮቪድ-19 ጉልበቱን በሚያሳይበት ቦታ ከተያዙት 43% ይገድላል      6/03/20

በአሜሪካ በተቀዳሚነት በኮቪድ-19 ከተጠቁት ሶስት ክፍሎች አንዱ ነርሲንግ ሆም (የአዛውንቶች መጦሪያ) ቦታ ነው፡፡ ከዛ ቀጥሎ ቤተሰብ፣ ከዛ ደግሞ የጤና በለሙያተኞች ናቸው፡፡

የነርሲንግ ሆም ጥቃት ከሌሎች የሚለየው፣ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ምን ያህሉ እንደሚሞቱ ነው፡፡ የአሜሪካው CMS (Center for Medicaid and Medicare Services) ሪፖርት ከሠጡት አብዛኞች የነርሲንግ ሆም ተቋሞች ያጠናከረውን አስደንጋጭ መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ በቻርቱ እንደምታዩት፣ በበሽታው ከተያዙት ከ60 439 ሰዎች መሀከል፣ 25 923 ሞተዋል፡፡ በፐርስንት ሲሰላ 43 ነው፡፡ ግማሹን በሉት፡፡ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ምክንያት አለ፡፡ የነርሲንግ ሆም ሰዎች፣ በዕድሜ የገፉና በብዛት ሌሎች ተደራቢ በሽታዎች አንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ ተደጋግሞ እንደታየው፣ በኮቪድ ከተያዙ በኋላ አሰከፊ ውጤት የሚደርስባቸው ሰዎች ናቸው፡፡

ወደ ሀገር ቤት ብንመለስ፣ እንደ አሜሪካ አዛውንቶችን አንድ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚረዱ ተቋማት ብዛት እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን፣ እንደ ባህላችን፣ ወላጆችን በቤታቸው ወይም በየልጆቻቸው ቤት መጦር የተለመደ ነው፡፡ ፍራቻው ደግሞ፣ እነዚህ በየቤቱ የተቀመጡ የዕድሜ ባለፀጎችን፣ ሌሎች አብረዋቸው የሚኖረ ወጣ ገባ የሚሉ ሰዎች ቫይረሱን ሊያቀብሏቸው እንደሚችሉ ነው፡፡ ለዚህ እንግዲህ፣ እንደዚህ አይነት ሰዎች በየቤቱ ያሉባቸው ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ነው፡፡ በጥናት የረዳ ነገር የታየው፣ ወጣ ገባ የሚሉትም፣ አዛውንቱም ማስክ ቢያደርጉ ሠርጭቱን ይቀንሱታል፡፡

በተጨማሪማ፣ ወረርሽኙ አስከሚያልፍ ድረስ፣ እነዚህ በዕደሜ የገፉ ሰዎች ከቤት ውጭ መውጣትና ርቀው መሄድ እንዳይሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ፣ ቤተክርስቲያንና ፀሎት ቤቶችንም ይጨምራል፡፡(ይከብዳል) ነገር ግን አማራጭ ሰሌለም ነው፡፡

መረጃው የሚያሳየው፣ የነርሲንግ ሆም ሠራተኞች በቫይረሱ ከመያዝ አላመለጡም፡፡ ደግነቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በንፅፅር ሲታይ አነስተኛ ነው፡፡ ማለትም ከ34442 ሠራተኞች መሀከል፣ 449 ሞተዋል፡፡

ሌላው አስፈሪ ቁጥር የወጣው ደግሞ፣ የአሜሪካው CDC ይፋ ያደረገው በቫይረሱ የተያዙ የጤና ባለሙያተኞች ቁጥርና በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ነርስና ሀኪሞች ሌሎችንም ጨምሮ ነው፡፡ በቫይረሱ የተያዙት የጤና ባለሙያተኞች ቁጥር 66 770 ሲሆን ከነሱ መሀከል 323 ሞተዋል፡፡

እንደገና ወደ ሀገር ቤት ዞር ብለን ብንመለከት፣ የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ መሄዱን አናያለን፡፡ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎችን ማጨናነቃቸው የሚቀር ነገር አይደለም፡፡ መለስ ብለን የአሜሪካውን ችግር ብናይ፣ በቂ የሆነ ሙሉ የጤና ባለሙያተኞች የሚለብሱት መከላከያ በበቂ ደረጃ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያም ቢሆን ይህ ችግር የከፋ እንደሚሆን ነው፡፡ ሰለዚህ ርዳታችን አንደሚያስፈልጋቸው አስቀድሞ መገንዘብም ያስፈልጋል፡፡

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

የሆስፒታሎች የአካባቢ አየር በሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁ 2 የተበከለ ነው የሚል ጥናት ወጣ

ይህ ነገር እንግዳ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደመም ቢሆን በመጀመሪያው የሳርስ ቫይረስ ጊዜ የሆስፒታል ወይም በሽተኞች ያሉባቸው አካባቢዎች ቫይረሱ እንደሚገኙ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ሆሰፒታል ሲባል ጠቅላላው አየሩ ሳይሆን የኮቪድ-19 ህሙማን ያሉባቸው የሆስፒታሉ ክፍሎችና አካባቢዎች ነው፡፡ JAMA (Journal of American Medical Association) በወጣ መረጃ፣ የኮቪድ ህሙማን ባሉባቸው የአየር አካባቢዎች በተወሰዱ ናሙናዎች 17 ፐረስንት የሚሆኑት በሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁ 2 የተበከሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ትልቁ ጥያቄ፣ የአከባቢው አየር በዚህ ቫይረስ ከተበከለ፣ መልሶ ሌላ ሰው መያዝ ይችላል ወይ ነው፡፡ ይህን ደግሞ የሚወስነው የቫይረሱ መጠን ነው፡፡ በሆስፒታሎችም ቢሆን በተለያዩ ክፍሎች የአካባቢው አየር በቫይረሱ የመበከል መጠን ይለያያል፡፡

በጥናቱ መሠረት የኮቪድ ህሙማን በሚታከሙበት በ ICU (Intensive Care Units) ለምርመራ ከተወሰዱ የአካባቢ አየር ናሙናዎች መሀል 25.2 ፐርሰንት ቫይረሱ ተገኝቷል፣ ከ ICU ውጭ በሆኑ በሌሎች ክፍሎች ግን ቫይረሱ የተገኘባቸው የናሙና መጠኖቸ ወደ 10.7 ፐርሰንት ዝቅ ይላል፡፡ ይህ የሚያሳያው ያው ቫይረሱ በአየር ጠብታ በኩል መተላለፉን ነው፡፡ እንደ ICU ባሉ የህክምና ክፍሎች በሚደረጉ የህክምናና የምርመራ ሥራዎች ምክንያት ጠብታውን ወደ አየር ብናኝ ሰለሚቀይሩ ነው የአካባቢው አየር ላይ በርከት ብሎ ቫይረሱ የሚገኘው፡፡

ሌሎች ቫይረሱ የተገኘባቸው የአካባቢ አየር ጋራ ሲያነፃፅሩ

በሌሎች የህክምና ክፍሎች 8.3 ፐርስንት
መፀዳጃ ቤቶች አካባቢ 23.8 ፐርሰንት
ህዝብ በሚገኝባቸው ቦታዎች ደግሞ ወደ 33 ፐርስንት ነው፡፡

ያም ሆኖ፣ ቫይረሶቹ በአካባቢው አየር ቢገኙም፣ አሁን ባለው ድምዳሜ፣ መልሶ መያዝ የማይችሉ አይነት ወይም መራባት የማየችል አይነት ነው ይላሉ አጥኝዎቹ፡፡ ነገር ግን ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገውም ይጠቁማሉ፡፡

ለዚህ ነው እንግዲህ፣ በህክምና መስጫ ቦታ የምትሠሩ ባለሙያተኞችም ሆነ፣ ለሌላ ህክምና ወደ ሆስፒታል ጎራ የምትሉ ሰዎችም ሆነ ጠያቂዎች፣ ማስኮችን በትክክል ማድረግ የሚገባችሁ፡፡ ያም ሲሆን ከአካባቢው ርቀው ሌሎች ሰዎች በቅርበት የማይገኙበት ቦታ እስከሚደርሱ ማስኩን ማውለቅም ተገቢ የማይሆነው፡፡ አንዱ ችግር የማስኩ ፊት ለፊት ተበክሎ ከሆነስ የሚል ሰለሆነ፣ ማስኩን ያለ አግባብ አሁንም አሁንም መነካካትም ጥሩ አይሆንም፡፡ ከሆነም ቶሎ እጅዎችን በአልኮል ወልወል ያድርጉ፡፡

በጎሽ ድረ ገፅ፣ ከዚህ ቀደም ማስክዎን የሚያወልቁበትን ቦታ ያስተውሉ ብለን መክረን ነበር፡፡ መፀዳጃ ቤቶች አስቸጋሪ ቦታዎች የመሆናቸውን ያህል፣ የጋራ የምግብ መብያ ቦታዎችም የህክምና ባለሙያተኞችን ለኮቪድ እንዳጋለጠ ቀደም ብሎ የሰፈረው ፅሁፍ ያስረዳል፡፡

የዚህን ቫይረስ ሥርጭት በክትባቶቹ እስክንቆጣጠር ድረስ፣ የመከላከያ መንገዶችን አጥብቆ ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ሌላ አልተጠየቀም፡፡ ማስክ፣ የአካል ርቀት፣ ስብስብ ማቆም ነው፡፡ በመንግሥት በኩል ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው ከታወቁ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ወይም የተጋለጡ ሰዎችን ክትትልና ምርመራ ማድረግ ነው፡፡ አሜሪካ በተለይም በካሊፎርንያ እየታየ ያለውን ሁኔታ የተገነዘበ ሰው ይህን ቫይረስ ማክበር ይኖርበታል፡፡ ሞትና ህመሙን ምንም የማይመስለው ካለ ደግሞ ኢኮኖሚውን ማሰብ ይኖርበተታል፡፡ ከመንግሥት ካዝና በሚወጣ የሚደጎም ኢኮኖሜ መልሶ ሁሉንም ይጎዳል፡፡ ሰለዚህ ሥርጭቱ እንዳይሰፋፋ ተገቢውን ጥረት ማድረግ የግድ ነው፡፡