ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

ልጆችና ኮቪድ -19፣ ቫይረሱን ያስተላልፋሉ ወይስ… 9/12/2020

 ኮቪድ-19 የጤና ችግር ከመሆን አልፎ ህብረተሰቡን በተለያየ ክፍል የሚነካ ችግር ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ኮቨድ -19 በልጆች ላይ ወይም በልጆች በኩል፣ የዳበረ መረጃ እስኪወጣ ድረስ፣ በማወቅም ባለማወቅ ብዙ ሲባል ነበር፡፡ ከጥዋቱ ግልፅ የሆነው ነገር፣ በቁጥር ሲነፃፀር፣ ልጆች በቫይረሱ ቢያዙም ብዙ እንደማይታመሙ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ልጆች ቫይረሱን ያስተላልፋሉ ወይ፣ ካሰተላለፉስ ምን ያህል ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ፣ ከእውነታው ይልቅ፣ ሊደረግ በታሰበው ጉዳይ ላይ በመመርኮዝ አስተያየት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ዋናው ቸግር፣ ትምህርት ቤት ይከፈት አይከፈት በሚሉ ወገኖች መሀከል የሚደረገው ሙግት ነው፡፡ ት/ቤት ይከፈት ብለው የሚያስቡ ወገኖች፣ ከፖለቲከኞቹ በኩል ስለ ኢኮኖሚ በማሰብ፣ ሌሎች ደግሞ አርቲፊሻል የሆነ ሰላምና መረጋጋት ያለ እንደሚስል በመጣር፣ ከዛም ደግሞ ለሳይንስ ደንታ የሌላቸውን ጨምሮ ልጆች ኮሮና አያስታላልፉም በማለት በግልፅ በአደባባይ ሲናገሩ ከርመዋል፡፡ በወላጆች በኩል ደግሞ፣ በአብዛኛው፣ ይከፈት የሚሉት በተለይ በአሜሪካ፣ ልጆቻቸውን በቤት መጠበቅ የማይችሉ፣ ምክንያትም የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ከቤት ወጥተው መሥራት የሚኖርባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከነሱ ጋር ግን፣ ኮቪድ የለም ብለው የሚያምኑ፣ ወይም ኮቪድ የለም የሚሉ የፖለቲካ መሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ የሀይማኖት መሪዎችን የሚከተሉ ሰዎች አሉበት፡፡

ይህንን ልጆችና ኮቪድ-19 በሚመለከት፣ ከኮርያ በኩል የመጣ የጥናት ውጤት ለማጋራት እየተዘጋጀሁ እያለሁ፣ የአሜሪካው የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል፣ (CDC)፣ MMWR በተባለው ሳምንታዊ ሪፓርት መረጃ ይዞ ቀርቧል፡፡

ልጆችን በሚመለከት፣ ከዚሀ በፊት የሚታወቀው፣ ዕድሜያቸው ከ10 አመት በላይ የሆኑ ቫይረሱን እንደሚያስተላልፉ የተዘገቡ መረጃዎች አሉ፡፡ ጥያቄው፣ ዕድሜያቸው ከአስር አመት በታች የሆኑት ላይ ነው፡፡ በኮቪድ-19 ከመጣ፣ ከመከላከያ መንገዶች አንዱ ወይም ዋናኛው ማለት ይቻላል፣ አፍና አፍንጫን ለመሸፈን የሚለበሱ መከላከያዎችን ህፃናቱ ማድረግ የሚችሉት ነገር አለመሆኑ ነው፡፡

ወደ  ጥያቄው ስንመለስ፣ ከሚያዝያ እስከ ሀምሌ 2020፣ ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በአሜሪካ፣ ዩታህ በተባለ ሰቴት፣ በተለይም ሶልት ሌክ በተባለ ካውንቲ፣ በሶሰት ህፃናት ማቆያ ቦታዎች(child care centers) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የተደረገውን የክትትል ጥናት ውጤት ነው የማጋራችሁ፡፡

እንዲህ አይነት ጥናት ሲጠና፣ ዋናው ቁልፍ ነገር፣ በቫይረሱ ተይዘው ከተገኙት ልጆች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ወይም የተጋለጡ ሰዎች ክትትል ማድረግ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው አጠራር ይህ Contact Tracing የሚባለው አሰራር፣ የቫይረሱን ሥርጭት አካሄድ ማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ ምን ያህል ሰዎች እንደተጋለጡ፣ የተጋለጡትም መልሰው ለሌሎች ሰዎች ማሳለፋቸውን ማወቅ የሚቻልበት መንገድ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ አሠራር፣ የነበረ፣ በተላላፊ በሽታዎች ክትትል ዋነኛ መሳሪያ የሆነ ነው፡፡ ይህንን የተጋለጡ ሰዎች ከትትል በወግ ሳያደርጉ የቫይረሱን ሥርጭት አጋኖም ሆነ አቅልሎ ማቅረብ ትልቅ ስህተት ነው፡፡

በሶልት ሌክ ካውንቲ በተደረገው ክትትል፣ በድምሩ 184 ሰዎች ከነሱ መሀል 110 ልጆች ኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተባቸው ከሶስት የህጻናት ማቆያ ቦታዎች ከአንደኛው ጋር የመጋለጥ አጋጣሚ ነበራቸው፡፡ በዚያን ጊዜ፣ ከ184 ሰዎች መሀከል፣ 31 ሰዎች በላቦራቶሪ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከነዚሀ መሀል 13ቱ ልጆች ነበሩ፡፡ በህፃናት ማቆያ ቦታዎች በቫይረሱ የተያዙት ህፃናት ቀለል ያለ የበሽታ ስሜት አለዚያም ምንም የበሽታ ስሜት አልነበራቸውም፡፡ በቫይረሱ ከተያዙት የበሽታ ስሜት ወይም ምልክት ካልነበራቸው ሁለት ህፃናት አማካኝነት፣ ቫይረሱ ወደሌሎች ሰዎች መተላለፉን ማወቅ ተችሏል፡፡ መረጃውን በጥልቀት ሲመለከቱት የታየው ነገር፣ በህፃናት ማቆያዎች በቫይረሱ የተያዙት ህፃናት፣ ቫይረሱን ወደ ቤት በመውሰድ ወደ ሌሎች ሰዎች ማስተላለፍ መቻላቸውን ነው፡፡ ህም፣ ልጄ ወይም ልጆቼ ምን ይዘው ሊመጡ ይችላሉ? የበሽታ ስሜት ወይም ምልክት ከሌላቸው ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸውንስ እንዴት ማወቅ ይቻላል?

መጋለጥ ሲባል፣ ሲዲሲ የሚያሰቀምጠው መመዘኛ የሚከተለው ነው፡፡ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር በሰድስት ጫማ ቅርበት ለአስራ አምስት ደቂቃዎቸ መቆየት ነው፡፡ እንግዲህ በቫይረሱ የተያዘ ህጻን ወይም ልጅ ወደ ቤት ሲመለስ፣ ቤት ውስጥ አብሮ ውሎ ማደር ባለበት ሁኔታ፣ የቅርበትና የመጋለጫ ጊዜው መመዘኛም አስፈላጊ አይሆንም፡፡

የጥናቱን ዝርዝር፣ በስፋት ለማንበብ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች እንተውና፣ የጥናቱን ማጠቃለያ ብንመለከት፣

አንደኛ፤ ዕድሜያቸው ከአስር ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ልጆች ከት/ቤት ጋር በተያያዘ ቫይረሱን እንደሚያስተላልፉ የታወቀ ነው፡፡

ሁለተኛ፤ በዚህ ጥናት፣ 12 ልጆች በህፃናት ማቆያ ቦታ በቫይረሱ መያዛቸው፣ ከነዚህ 12 ልጆች ተነስቶ ወደ ሌሎች ሰዎች በቁጥር 46፣ የተላለፈ መሆኑ፡፡ በቫይረሱ ከተያዙት ወላጆች፣ አንደኛው ሆስፒታል የገባ መሆኑን፡፡ የበሽታ ስሜትና ምልክት ካልነበራቸው፣ በቫይረሱ ከተያዙ ህፃናት ወደ ሌሎች ሰዎች ቫይረሱ መተላለፉ ተዘግቧል፡፡ እንግዲህ እድሜያቸው ከአስር አመታች በሆኑ ልጆች፣ በህፃናት ማቆያ ቦታዎች በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ ወደ ቤተሰብ ይዘው መሄድና ማስተላለፍ መቻላቸው ነው የተዘገበው፡፡

ከደቡብ ኮርያ በኩል ይህንን በሚመለከት የቀረበውን ጥናት ላጋራችሁ፡፡ በነገራችን ላይ እንደዚህ አይነት ወሳኝ መረጃዎችን ለማካፈል የወሰንኩት፣ ለማሸበር ወይም ለማስፈራራት ሳይሆን፣ በቤት ሆነ፣ ከቤት ውጭ በዚህ ጉዳይ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር፤ የአካባቢዎ በላሥልጣናት ይህንን በሚመለከት በተለይም፣ በትምህርት ቤት ጉዳይ የሚወስኑት በቂ መረጃ ተመርኩዘው መሆኑን ለመጠየቅ እንዲያስችል፣ ራስዎም ቢሆን ልጆች ካሉዎት እናም የቤትዎን ሁኔታ በማየት ት/ቤትን በተመለከተ ለሚወስኑት ውሳኔ እንዲረዳ ነው፡፡

የኮርያው ጥናት ሰፋ አድርጎ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር፤ በሳረስ ኮቪ 2 (ኮቪድ-19ን የሚያሰከትለው ቫይረስ) በተያዙ ልጆች፣ ቫይረሱ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል የሚለውን ጥያቄና በኮቪድ-19 የተያዙ ህጸናትን በበሽታ ስሜትና ምልከት ለይቶ ማወቅስ ይቻላል ወይ የሚለውን ጥያቄ መልስ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የሚታወቀው፣ በኮቪድ-19 የተያዙ አዋቂ ሰዎች መሀከል ከ 20% እሰክ 45% የሚሆኑት የበሽታ ስሜት ወይም ምልክት የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ ከአዋቂዎች ጋር ሲነጻጸር፣ ልጆች በጣም የማይታመሙ ሰለሆነ፣ ቫይረሱን ምን ያህል እንደሚያሠራጩም ግልፅ አልነበርም፡፡ ምንም እንኳን ፖለቲከኞቹ፣ አያስተላልፉም ብለው በአደባባይ የተናገሩ ቢሆንም፡፡

የደቡብ ኮሪያውን ጥናት ማጠቃለያ ብንመለከት፤

አንደኛ፣ ባደረጉት ክትትል፣ በኮቪድ-19 መያዛቸው በላቦራቶሪ ከተረጋገጠ በ91 ልጆች፣ ተደጋጋሚ በተደረገው በአፍንጫ ወይም በጎሮሮ በኩል በሚወሰድ ምርመራ፣ መጀመሪያ ቫይረሱ ተገኘባቸው ከተባለው ቀን ጀምሮ፣ በአማካይ አስከ 17.6 ቀናት ድረስ ቫይረሱ የተገኘባቸው መሆኑን ነው፡፡ ይህ እንግዲህ፣ የተከታተላችሁ ሰዎች እንምትረዱት፣ በነዚህ ልጆች ላይ፣ ቫይረሱ ከሚታወቀው ከሁለት ሳምንት በላይ ለረጅም ጊዜ በጎሮሮና በአፍንጫቸው መገኘቱን ነው፡፡

ሁለተኛ፤ በዚህ ጥናት ውስጥ ከተካተቱት 91 ልጆች መሀከል፣ 20ዎች ምንም አይነት የበሽታ ስሜት ወይም ምልክት ያልነበራቸው ሲሆን፣ መጀመሪያ ቫይረሱ መኖሩ ከተረጋገጠበት ቀን ጀምሮ በአማካይ ለ14 ቀናት፣ ቫይረሱ የተገኘ ሲሆን፣ ከነዚህ መሀል አራቱ ከሶስት ሳምንቶች በኋላ እንኳን ቫይረሱ የተገኘባቸው መሆኑን ዘግበዋል፡፡

ልጆች፣ ምንም እንኳን በቫይረሱ ምክንያት ብዙ የማይታመሙ ቢሆንም፣ በላይኛው የመተንፈሻ አካላቸው ውስጥ ከአዋቂዎች በበለጠ ብዛት ያለው ቫይረስ እንደሚሸከሙ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ 86 ልጆች ወይም ቀለል ያለ በሽታ ምልክት ነው ያላቸው አለዚያም ምንም አይነት የበሽታ ምልክት አልነበራቸውም፡፡ ሰለዚህ፣ ልጆችን በተመለከት፣ በቫይረሱ ተይዛዋል ወይም አልተያዙም ለማለት በበሽታ ስሜትና ምልክት መመዘኛ መጠቀም የማያዋጣ ነገር ይሆናል፡፡ ይህን ያህል ልጆች፣ እንግዲህ በፀጥታ ቫይረሱን ለቤተሰባቸው ያስተላልፋሉ ማለት ነው፡፡ በዚህ ጥናት የሚገርመው ነገር ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ልጆቹ ቫይረሱን ለረዥም ጊዜ በመተንፈሻ አካላቶቻቸው በመያዝ ማስተላለፉን ለተራዘመ ጊዜ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው፡፡ የበሽታ ምልክት በነበራቸው ህጻናት መሀከል፣ ቫይረሱ በልጆቹ ላይ ለ21 ቀናት እየተገኘም ነበር፡፡

ደቡብ ኮርያ በወሰዱት ጥብቅ ኳራንቲን ርምጃዎች፣ የቫይረሱን ሥርጭት በደንብ ማጥናት ከሚችሉ ከጥቂት አገሮች አንዱ ነው፡፡ በዚህም እንዲህ አይነት መረጃ ሲያቀርቡ፣ ተቀባይነትና ታማኝነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡

እኔም ሆነ ሌሎች በኮቢድ-19 ላይ ያለንን ፍራቻ ለማጋራት የምንቀሳቀስ ሰዎች፣ ከጥዋቱ፣ በኮቪድ-19 ምክንያት፣ ከ80ፐርስንት በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቀላሉ የሚወጡት ነገር እንደሆኑ ስንናገር ከርመናል፡፡ አልታመምንም ወይም እንታመምም ከሚሉ ሰዎች ጋር ልዩነት የለንም፡፡ ዋናው ፍራቻ፣ ይህ ቫይረስ በኔ አባባል “ይህ ቫይረሰ ዞሮ ዞሮ የሚገለው ሰው ያገኛል”፡፡ ቫይረሱ ከያዛቸው ከፍተኛ ህመም ወይም የህይወት ህልፈት ደረጃ የሚደርሱ ሰዎች አሉ፣ ታይተዋልም፡፡ ስለዚህ ዋናው ጥረት ይህ ቫይረስ እነዚህ ሰዎችን እንዳያገኝ ነው፡፡ ሰሌት በማስላት የሞቱ ሰዎችን በፐርስንት ወይም በቁጥር በማየት ከፍተኛ ጉዳት አያደርስም የሚሉ ሰዎች በሀገር ቤትም እየታዩ እንደሆነ ጥቆማዎች አሉ፡፡ በርግጥ በኢትዮጵያ፣ በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥጥር ከሌሎች ቦታዎች ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ይመስላል፡፡ እዚህ ላይ ግን የመረጃ አሰባሰብና ሪፖርትን ጥራት ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው፡፡

የሚገርመው ነገር፣ ኮቢድ-19 በሚመለከት፣ ይህ ቢሆን ይሻላል ለሚሉ ሰዎች፣ የተለያየ ሀገሮች የተለያየ አቀራረብ ተጠቅመው የደረሰውን መመልከት እንችላለን፡፡ በህዝብ ጭነትም ይሁን በሌላ ምክንያት፣ ጥብቅ ቁጥጥሩን ላላ ያደረጉ አገሮች፣ የቫይረሱ ሥርጭት እንደገና ሲያገረሽባቸው ታይቷል፡፡ እነዚህ አገሮች ደግሞ የቫይረሱን ሥርጭት ካረገቡ በኋላ ነው ላላ ለማድረግ የሞከሩት፡፡ በሌላ ጉዳይ፣ በተለይም የተያዘው ይያዝና የማህበረሰብ የመከላከያ አቅም ሲፈጠር የቫይረሱን ሥርጭት መቆጣጠር ይቻላል ብለው፣ በየቤትህ ቆይ የሚለውን አቀራረብ ሳይጠቀሙ የወሰዱት ርምጃ ያሰከተለውን ውጤት አለም በታዛቢነት ያየበት አገር ስዊድን ነው፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲወዳደር፣ በኮቪድ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በሰዊድን፣ ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች መሀል (561/million) የሞቱበት አገር ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ደግሞ በበሽታው በጣም ከተጠቁት አገሮች በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኛው ከኢጣልያ ቀጥሎ ነው (581/million)፡፡ ይህ ቁጥር በኖርዌይ (47/million) ነው፡፡

የስዊድን ቁጥር ስንመለከት፣ በኢትዮጵያ በኮቪድ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ትንሽ ነው ብለን ለመደምደም ይከብዳል፡፡ አስከ ዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ በዳሽ ቦርዱ እንዳስቀመጡት በቫይረሱ ከተያዙ 58,672 ሰዎች መሀከል፣ 918 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል፡፡ ዝም ብሎ በቀላሉ ቢታይ፣ ይህ ቁጥር በፐርስንት ቢታይ ከስዊድን በላይ ነው፡፡ ፍራቻው ምንድን ነው፣ በኢትዮጵያ በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል የሚባሉ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መምሰሉ የሚያፅናና ቢመስልም፣ ቫይረሱ በስፋት ከተሠራጨ፣ በመጠነ ስፋቱ ብቻ የሟቾች ቁጥር ከፍ ያለ እንዳይሆን ነው፡፡ ለዚህም፣ ኢትዮጵያውያን ባለሙያተኞች ሊሞት የሚችለውን ሰው ቁጥር ያቀረቡበት የስሌት ሞዴል አለ፡፡ ሰለዚህ በተቻለ መጠን፣ በተለይም ህብረተሰቡ  ሥርጭቱ ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡

ሌላው በስፋት የማይነገረው ነገር፣ እናም በጣም አሳሳቢው፣ በኮቪደ-19 ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ሳይሆን፣ ሌሎች በሽታዎች ያሉባቸው ህሙማን ሞት ቁጥር ከፍ እንደሚል ነው፡፡ ይህም በዘመቻ መልክ ሁሉም ነገር ወደ ኮቪድ-19 ከሆነ፣ የጤና ባለሙያተኞች በተጋለጡና፣ ከሥራ ቦታ በተገለሉ ቁጥር፣ ያሉት የህክምና መስጫ ቦታዎች በኮቪድ ህሙማን በተጥለቀለቁ ቁጥር፣ ለሌሎች ህሙማን መገልገያ ቦታ ዕጥረት ስለሚፈጠርም ነው፡፡ 

ሰለዚህ ሰለ ኮቪድ-19 መከላከል ስንነጋገር፣ ኮቪድ-19 ብቻ አለመሆኑን መገንዘብ ጥሩ ነው፡፡

የኮቪድ-19 ሥርጭት በቀጠለ ቁጥር ደግሞ ኢኮኖሚው እየተጎዳ እንደሚሄድ ግልፅ ነው፡፡ ለሰው ጤንነት፣ ህይወት እምብዛም ግድ ለማይኖራቸው ሰዎች፣ ሥርጭቱ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ከሆነ፣ ኢኮኖሚውን እየጎዱ መሆናቸውን ቢገነዘቡ መልካም ነው፡፡ አይክፋ እንጂ፣ ይህ ቫይረስ ፈንቅሎ በመውጣት፣ ዩኒቨርሰቲዎችን፣ ቤተከርሰቲያችን፣ ትምህርት ቤቶችን ሲያዘጋ እያየን፡፡ ተደባብቀው የሚያልፉትም ነገር አይደለም፡፡

የግድ በሥራ ምክንያት መውጣት እንዳለብን የሚታወቅ ነው፡፡ አሱም ቢሆን ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጎ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ለምናደርገው ስብስብ እያስበንና እያስተዋልን ቢሆን ይመረጣል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ ሥራየ ብለው ወደ ኢትዮጵያ ሰልክ እየደወሉ መምከሩ የግድ ነው፡፡ በተለይም በዕድሜ የገፉ የቤተሰብ አባላቶችን፡፡ በአሜሪካም እንደታየው፣ በዚህ በሽታ በጣም ተጠቂ የሚሆነው በብዛት መጠነኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ከአኗኗር ጀምሮ፣ በተለይ በኢትዮጵያ፣ በቂ ህክምና ለማግኘት አቅም ማነስ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ በማለት ነው እባካችሁ አያልን የምንማፀነው፡፡

 የመረጃ ምንጭ፡ JAMA Pediatrics 2020; DOI: 10.1001/jamapediatrics.2020.3988