Health and History

አዲስ የኮሮና ቫይረሶች መከሰት ምን አደጋ አለው? 12/26/2020

በቅርቡ በብዙሀን መገናኛ የኮሮና ቫይረስ ቁጥር 2 አዲስ ዝርያዎች በኢንግላንድና በደቡብ አፍሪካ መከሰታቸው ሲገለፅ ከመልስ ይልቅ ብዙ ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በባለሙያተኞቹ በኩል፣ ርዕሱ ወይም ጉዳዩ በብዙሀን መገናኛ መገለፁን የወደድነው ቢሆንም ለብዙ ትርጉም መጋለጡን ስናይ ደግሞ አሳሳቢነቱ የሚጨምር ነገር አድርጎታል፡፡ ሰለዚህ፣ ትክክለኛውን ማብራሪያ መሥጠት የግድ ነው፡፡ የብዙ ሰዎች ጥያቄም ነው፡፡ አንድ ትልቅ ሰውም፣ ይህ ነገር ማለትም፣ በሥርጭት በኩል አዳዲሶቹ ቫይረሶች ከድሮዎች ከሰባ ከመቶ በላይ ነው ማለት ምንድን ነው ብለው ጠየቁ፡፡ አስከትለው የተናገሩት ነገር ደግሞ ፈገግ እንድንል ቢያደርገንም ማብራራት እንዳለብን ግዴታውን ጨምሮታል፡፡ ምን እንዳሉ በኋላ ልመለስበት፡፡

በቃላት እንጀምር፣ አዲስ እንበላቸው፣ የተከሰቱት ቫይረሶች የጋራ መጠሪያ በአንግሊዝኛ በተለያዩ የቃላት ስያሜያቸው variants, strains or lineage ተብለው ይጠራሉ፡፡ በአማርኛ ዝርያ በማለት ለመጥራት እንስማማ፡፡ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ይህ ቫይረስ (ሳርስ ኮሮና ቁ 2) ሳኮ-2፣ ዝርያውን እየቀየረ እንደሚሄድ ለማስገንዘብም ለማስጠንቀቅም ሞክረናል፡፡ በታህሣስ መጨረሻ የተከሰተው አባት ቫይረስ መሠራጨት ከጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በተለያዩ የአለም ክፍሎች የተለያዩ ከዚሁ አባት ቫይረስ የሆኑ ግን በዝርያ በመጠኑም ለየት ያሉ ቫይረሶች ተከስተዋል፡፡

ለምንድን ነው አዲስ ዝርያ የሚከሰተው ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት፣ ወደኋላ ወደ ፕሮቲን አሠራር መመለስ የግድ ነው፡፡ ፕሮቲኖች ባጠቃላይ የአንድ አካል፣ የሰውም ይሁን የእንሰሳ፣ የቫይረስም ይሁን የባክቴርያ መሠረታዊ የግንባታ አካል ናቸው፡፡ ፕሮቲኖች ሲሰሩ ግን፣ እያንዳንዱን ፕሮቲን የተለየ አድርጎ እንዲወጣ የሚያደርጉት የዘር ስንሰለት ኮዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በሰዎች ላይ ብንመለከት፣ ዋናው የሰው የዘር ሀረግ በሴሎች አስኳል (Nucleus) ውስጥ የሚቀመጠው (ዲ ኤን ኤ DNA)  ነው፡፡ ይህ የዘር ሀረግ ኮድ፣ እንደ አንገት ሀብል ሰንሰለቶች የተቀጣጠሉ ወይም የተያያዙ ንጥሮች በድርብ መስመር ተጠቅለው ይገኙበታል፡፡ ሁሉም የሰውነት ክፍላችን ከሴሎች ጀምሮ ሌሎቹም ምን መምሰል እንዳለባቸው ትዕዛዙ የሚመነጨው ከዚህ የዘር ሀረግ ነው፡፡ እንግዲህ አንድን ፕሮቲን መስራት ሲያስፈልግ፣ ከዘር ሀረጉ የተወሰነ ክፍል፣ የሚሠራውን ፕሮቲን አይነት ትዛዝ የሚሠጥ ኮድ ይመረጣል፡፡ ነገር ግን ይህ የዘር ሀረግ ከአስኳሉ ሰለማይወጣ፣ ሌላ ኮድ ተሸካሚ መልክተኛ ነገር ያስፈልጋል፡፡ ያ መልክተኛ፣ ከዘር ሀረጉ የሚያስፈልጉትን ኮዶች ብቻ ይገለብጥና ወደ ሴሎች ዋና አካል ለመሄድ ከአስኳሉ ይወጣል፡፡ ገምታችሁ ከሆነ፣ ያ የኮዱን መልክት ይዞ የወጣው ነገር መልክተኛው አር ኤን ኤ messenger RNA(mRNA) ይባላል፡፡ ክትባቶችንም ለማብራራ እንዲመች ጠለቅ ማለት ነበረብኝ፡፡

የኮዱን መልክት የያዘው መልክተኛው mRNA ነጠላ ሰንሰለት ነው፣ በሴሎቹ ክፍል፣ ከአስኳሉ ውጭ፣ ኮዱን በመተርጎም የተባለውን ፕሮቲን እንዲሠራ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ፕሮቲኖቸ ሲሰሩ ደግሞ በውስጣቸው እንደ ግንባታ መሠረት የሚሆኑት በኋላም ተቀጣጥለው የፕሮቲኑን ምንነት የሚወስኑት አሚኖ አሲድ የሚባሉ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህ አሚኖ አሲዶች በአይነትና በተራ ቁጥር በሥነ ሠርአት ተቀጣጥለው መቀመጥ አለባቸው፡፡ አንዱ አሚኖ አሲድ በተራ ቁጥሩ ላይ በሌላ አሚኖ አሲድ ሲተካ፣ ፕሮቲኑን ከመሠረታዊ ግንባታው ባያናጋውም የተለየ ሊያደርገውና የተለየ ባህሪም ሊፈጥርበት ይችላል፡፡ ይህ በተራ ቁጥር የተቀመጡ አሚኖ አሲዶች አንዱ በሌላው ሲተኩ በእንግሊዝኛ mutation ይባላል፡፡

እያንዳንዱ ፕሮቲን የራሱ የሆነ የተለየ ተልዕኮ ወይም መገለጫ አለው፡፡ መገለጫም ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ወይም ሥራው ለራሱ የብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ቫይረሶችም ቢሆን ከተለያዩ ፕሮቲኖች የተገነቡ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ የቫይረሱ አካልም የተለያዩ ፕሮቲኖች ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌ የሳኮ ቁ 2 ቫይረስ፣ በምስሎች ላይ የምታዩዋቸው በአካሉ ላይ ቁጭ ቁጭ ብለው የሚታዩት ነገሮች ስፓይክ ፕሮቲን Spike protein ተብለው ነው የሚጠሩት፡፡ እነዚህ የቫይረሱ ክፍሎች ላይ የምናተኩረው፣ ቫይረሱ ወደ ሰውነት ለመግባት የሚጠቀምባቸው ፕሮቲኖች ሰለሆኑ ነው፡፡ በርግጥ ቫይረሱ በዙ ሌሎች ፕሮቲኖች አሉት፡፡ አሁን ክትባትም ሆነ፣ የሰውነት የውስጥ መከላከያ ኢላማ ያደረጉት የቫይረሱ አካል ይህ የተጠቀሰውን ሰፓይክ ፕሮቲን ነው፡፡ ለምን ከተባለ፣ ቫይረሱ አንደ መግቢያ ቁልፍ አድርጎ የሚጠቀምበት አካሉ ከሆነ፣ ይህንን ቁልፍ ማሰናከል ወይም ማምከን፣ ቫይረሱ ወደ ሰውነት ሴሎች እንዳይዘልቅና እንዳይራባ ያደርገዋል፡፡ አንደዛ ከሆነ ደግሞ በሽታ መያዝ ቀርቶ፣ ተራብቶ መልሶ ሌላ ሰው መያዝ የሚችል ቫይረስ ሰለማይኖር ሥርጭት ይቆማል ነው፡፡ ይህ ነው ትልቁ የክትባትም ሆነ የተፈጥሮ መከላከያ ሚስጥር፡፡

ከዚህ ቀደም ሳኮ ቁ 2 ቫይረስ የተለያዩ ዝርያዎችን እየፈጠረና አዲስ የተፈጠሩት ቫይረሶችም እየተባዙና እየተሠራጩ እየሄዱ እንደሆን እየገለፅንም ነበር፡፡ አዲስ ዝርያ ቫይረስ የሚፈጠረው፣ ፕሮቲኖች እንዲሠሩ የሚያዘው ኮድ በመጠኑ ለወጥ ካለ፣ ቀደም ተብሎ የተጠቀሱት የፕሮቲኑ መሠረታዊ የግንባታ አካላት የሆኑት አሚኖ አሲዶች በተወሰነ የሰንሰለት ቁጥር ላይ አንዱ በሌላው ሲተካ፣ የተሠራው ፕሮቲን ከመጀመሪያው ቫይረስ ፕሮቲን እየተለወጠ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ይህ በመሠረቱ የዝርያ ለውጥ እንደሆነ ነው የሚያሳየው፡፡ አንግዲህ በዘር ወይም በኮድ ለየት ያለ ፕሮቲን ያለው ቫይረስ አዲስ ዝርያ ነው የሚሆነው፡፡ አዲስ ዝርያዎችም የየራሳቸው ስም ይሠጣቸዋል፡፡ ሌላው ወሳኝ ጥያቄ፣ አዲሱ ቫይረስ ላይ በመጠኑም ይሁኑ በስፋት የተለወጠው የቫይረሱ የትኛው ፕሮቲን ነው የሚለው ነው፡፡ ቫይረሱ ወደ ሰውነት ለመግባት፣ ከዛም በሰውነት ውስጥ በሰዎች ውስጥ ካለው የተለየ ሞሎኪል ጋር የሚገናኝበት ፕሮቲን፣ ለቫይረሱ ወሳኝ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሰው የሰውነት መከላከያ ይህን ሳኮ ቫይረሰ ቁ 2ን የሚያውቀውና ዘግቦ የሚያስቀምጠው፣ ከዛም ወደ ማጥቃት የሚሄደው ይህንኑ የመግቢያ ፕሮቲኑን (ስፓይክ ፕሮቲን) ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ በውጭ የተሠራው ክትባት ደግሞ ኢላማ አድርጎ የተሠራው፣ ይህንን ስፓይክ ፕሮቲን ለሰው ሰውነት ተለይቶ እንዲታወቅ በማድርግ ሰውነት የራሱን መከላከያ እንዲያበጅ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ስፓይክ ፕሮቲን ላይ የመከሰት ለውጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ማለት ነው፡፡

ቫይረሶች ከአንድ ሰው ዘለው ወደሌላ ሰው ከተሻገሩ በኋላ፣ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር መራባት ነው፡፡ የሚራቡትም በሰው ሰውነት ሴሎች ኪሳራ ነው፡፡ ይህ ባጠቃላይ RNA Virus ተብለው የሚጠሩ ቫይረሶች ባህሪ ነው፡፡ በቀላሉ ሲነገር፣ በሰው ጎጆ ሌጣውን ወይም ብቻውን ገብቶ ልጆቹን እንደመውለድ ማለት ነው፡፡ አዚህ ላይ ቫይረሶቹ፣ mRNA በመጠቀም ኮዱን እያሰተረጎሙ የተለያዩ የቫይሱን ፕሮቲኖች ሲገነቡ፣ ከብዛት የተነሳ፣ ኮድ ግልበጣው ላይ ስህተት ይፈጠራል፡፡ ሰህተቱ ትርጉሙ ላይ፣ ወይም የሚሠራው ፕሮቲን ላይ ነው የሚከሰተው፡፡ የፕሮቲኑ ለውጥ ከመጀመሪያው ፕሮቲን ምን ያህል በጥልቀት ወይም በርቀት መቀየሩ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ ልብ ማለት ያለብን፣ የተለያዬ የቫይረሱ ፕሮቲኖች በመጠኑ መቀየር ቫይረሱን እንዳለ በትልቅ ዝርያ ወደ ሌላ ቫይረስ አይቀይረውም ግን ከተነሳበት ወይም ከመጣበት ለየት ያለ ያደርገዋል፡፡ ይህ ለየት ያለው ቫይረስ ነው እንግዲህ አዲስ ዝርያ ተብሎ የሚጠራው፡፡

አሁን አዲስ የተከሰተው ቫይረስ፣ በውስጡ ባሉ ፕሮቲኖች መጠነኛው ወይም ስፋት ያለው ለውጥ ካለው ምን ይሆናል የሚል ጥያቄም አለ፡፡ ባይገርማችሁ፣ እንዲህ ለወጥ ያለ ፕሮቲን ያለው ቫይረስ፣ ሰንካላ በመሆኑ መቀጠልና መራባት ሳይችል ሲቀር በዛው ይከስማል፡፡ ሰለዚህ የፕሮቲን ለውጥ ማድረጉ ለቫይረሱም የማይበጅበት ሁኔታ አለ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ለወጥ ያለው ቫይረስ፣ ከሁኔታው ጋር ተስማሚ ከሆነ፣ ያደረገው ለውጥ ደግሞ እንዲቀጥልና እንዲባዛ የሚያስችለው ከሆነ፣ እንደምትገምቱት፣ መራባቱን ይቀጥላል፣ እንዳውም አዲስ የፈጠረው ፕሮቲን ጠንከር የሚያደርገው ከሆነ፣ ከመጀሪያው ቫይረስ በበለጠ ይራባል ይባዛል፣ አንደዛ ሲሆን፣ ርስቱን የሚይዘው አዲሱ ዝርያ ይሆንና የቀድሞው ቫይረስ እየከሰመ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ በቫይረስ አለምም ቢሆን ጉልበተኛው ያሸንፋል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ፣ በታሕሣሥ የተከሰተው አባት ቫይረስ እየከሰመ ሲሄድ አዳዲሶቹ ሥርጭቱን እየተቆጣጠሩት የሚሄዱት፡፡ አስተውላችሁ ከሆነ፣ ለአዳዲስ ጉልበተኛ ቫይረሶች መከሰት ምክንያቱ ቫይረሱ መራባት ወይም መባዛት ሲቀጥል ነው፡፡ መዋለድ ካልጀመረ አዲስ ልጅ ከየት ይመጣል? ይህ ደግሞ የሚሆነው፣ ሰዎች፣ ቫይረሱን ከአንዱ ሰው ወደሌላው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሲያሻግሩት ነው፡፡

የለንደንም ሆነ የደቡብ አፍሪካው ቫይረስ በዚህ መንገድ ነው የተከሰቱት፡፡ ለምን አሁን ጉልህ ሆነ ብትሉ፤ በሥርጭት ላይ ያሉ ቫይረሶችን የዝርያ ጥናት በስፋትና በጥልቀት ሰለሚመመረምሩ ነው፡፡ ኢንግላንድ፣ ንብረቷን ወጣ አድርጋ ብዙ ቫይረሶችን በመመርመሯ ምክንያት በህብረተሰቡ ውስጥ እየተሠራጨ ያለውን ቫይረስ ቶሎ ማወቅ ችላለች፡፡ በአንፃሩ፣ አሜሪካ ይህንን ነገር የጀመረችው በቅርብ ጊዜ ሲሆን፣ ይሀ ፅሁፍ እስከወጣበት ጊዜ 57ሺ ቫይረሶችን ብቻ ነው የመመረመረችው፡፡ ሰለዚህ አሜሪካ ውስጥ ምን አይነት የቫይረስ ዝርያ እንደሚሠራጭ በውል ማወቅም አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያም ቢሆን፣ እኔ እሰከ አሁን እሰከማውቀው ድረስ ምን አይነት የቫይረስ ዝርያ ነው ለሚለው የቀረበ ጥናት አልሰማሁም፡፡

ወደ አሳሳቢው ክፍል እንሂድ

ከዚህ ቀደም ይህን ጉዳይ፣ ማለትም ቫይረሱ በስፋት መሠራጨት ከቀጠለ ወደፊት ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች አንዱ ነው በማለት ምክር ስንሠጥ ሰንብተናል፡፡ ትልቁ ጥያቄ፣ አዲሱ ቫይረስ ወይም ዝርያ፣ በውስጡ በተደረገው የፕሮቲን ለውጥ ምክንያት የባህሪ ለውጥ አሳይቷል ወይ ነው፡፡ ከፕሮቲኖቹስ የትኞቹ ናቸው ለውጥ እየታየባቸው ያለው የሚለው ቀደም ያለውን ጥያቄ ያጠናክረዋል፡፡ ባህሪን በሚመለከት አንድ ሁለት ልበል፡፡

አንደኛ፡ የመራባት ችሎታ፡፡ ይህ ሳኮ ቁ 2፣ ከጠዋቱም ቢሆን፣ ከዘመዶቹ ከመጀመሪያው ሳርስና (SARS) ከሚድል ኢስት ኮሮና ቫይረስ (MERS Co virus) በበለጠ መራባት ይችላል፣ ለዚህም ጥናቶች አሉ፡፡ የጎሽ ድረ ገፅም ላይ ቢሆን ተቀምጧል፡፡

መራባት ሲባል፣ ቫይረሱ ወደ ሰውነት ሲዘልቅ በሰውነት ውስጠ ከሚገኝ ACE 2 ከሚባል ሞሎኪል ጋር በመጣበቅ ነው ወደሌላ የሚስፋፋው፡፡ ሰለዚህ ከዚህ ሞሎኪል ጋር በቀላሉና በፍጥነት ከዛም ጠንከር ያለ የመጣበቅ ሁኔታ ካለው ወደ ሰውነት ወስጥ ቶሎ የመዝለቅ ባህሪ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ፣ ከሰው ወደ ሰው ለመሻገር አስፈላጊ የሚሆነው የቫይረስ መጠን ያንሳል ማለት ነው፡፡ ማለት ለመጠነኛ የቫይረስ መጠን መጋለጥ ወደ ኢንፌክሽን ይቀየራል ማለት ነው፡፡ ሌላው ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ አዲስ ባገኘው ባህሪ ምክንያት ቫይረሱ በመተንፈሻ አካላት ላይ ከመጠን በላይ የሚራባ ከሆነ፣ በተለይም የላይኛው የመተንፈሻ ክፍሎች፣ ሰዎች በሚያስሉበት፣ በሚያስነጥሱበት፣ ጮክ ብለው በሚናገሩበት፣ በሚዘምሩበት፣ ከባድ ትንፋሽ በሚተነፍሱበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ በመደበኛ ንግግር በሚወጣው ትንፈሻቸው ክምር ክምር ቫይረስ ያዘልቃሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ነው አንግዲህ በፐርስንት እየተጠቀሰ እነዚህ አዳዲስ ዝርያዎች ቀድሞ ከተከሰቱት ቫይረሶች በዚህ መጠን ከፍ ባለ ሁኔታ ይተላለፋሉ የሚባለው፡፡ ለቫይረሶች የከፋ ጉዳት ለማስከተል አንዱ ባህሪ ይህ በፍጥነትና በብዛት መሸጋገር መቻል ነው፡፡ የመተላለፍ ችሎታን በተመለከተ፣ ለምሳሌ ለመጥቀስ፣ አንደኛ ደረጃነቱን የያዘው ቫይረሰ ሚዝልስ ወይም ኩፍኝ ነው፡፡ በኩፍኝ ቫይረስ ከተጋለጡ አስር ሰዎች፣ ዘጠኙ ይያዛሉ (ዘጠና ፐርስንት መተላለፍ)፡፡

መግቢያ ላይ የጠቀስኳቸውትልቅ ሰው የነገሩንን ነገር እዚህ ላስገባ፡፡ ስውየው የተናገሩት የሰሙትን ነው፡፡ እናም ቫይረሱ በአይን ይተላለፋል፤ ሰለዚህ ትክ ብለህ አትየኝ እሰከማለተ ተደርሷል ነው የሚሉት፡፡ ይህ አባባል ትክክለኛ ክፍልም አለው፣ የተሳሳተ ክፍልም አለው፡፡ ቫይረሱ በአፍ፣ በአፍንጫ በአይን ላይ ካረፈ እንደሚተላለፍ ይታወቃል፡፡ ይህ የሚሆነው፣ እነዚህ የሰውነት ክፍሎች፣ የአፍንጫ ውስጥ፣ የአፍ ውስጥና አይን በመደኛው የውጭ ቆዳ ስላልተሸፈኑ መከላከል አይችሉም፡፡ እናም አውነት ነው በአይን ይተላለፋል፤ ለዚህም ነው ህክምና ቦታ ላይ ተደራቢ የፊት መሸፈኛ ፕላሰቲክ የሚለበሰው ወይም የአይን መሸፈኛ መነፀርም የሚደረገው፡፡ ትክክል ያልሆነው በአይን በኩል መግቢያ እንጂ መውጫ አይደለም፣ አፍና አፍንጫ ግን የተለየ ታሪክ ነው፡፡ በውስጥ የተከመረው ቫይረስ፣ በተነፈስንና በተናገርን ቁጥር ወደ ውጭ ይወጣል፣ በአይናችን በኩል ግን ቫይረስ አይወጣም፡፡ ትክ ብሎ ማየቱ ሳይሆን፣ አፍና አፍንጫውን ካልሸፈነ፣ ምን ለማድረግ እንጠጋለን፡፡

የሚፈጠሩ የባህሪ ለውጦችን በሚመለከት ተጨማሪ

ሁለተኛ፡፡ በባህሪ ለውጥ ምክንያት ሀይል ከጨመረ፣ ከፍተኛ ደረጃ ህመም ወይም የመግደል ችሎታው ይጨምር ይሆን የሚል ትልቅ ፍራቻ አለ፡፡ ይህ ደግሞ መላ ምት ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በሌሎች ቫይረሶች፣ ለምሳሌ የ1918 የስፓኒሽ ፍሉ፣ በአገር ቤት አጠራር የህዳር በሽታን ያስከተለው ቫይረስ፣ ሲለዋወጥ ከርሞ ነው መግደል የጀመረው፡፡ አሁን ታዩ በተባሉት አዲስ ቫይረሶች፣ የበሽታ መክፋትና ተጨማሪ ሞት አልታየም ተብሏል፡፡ ነገር ግን ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ለምን? በሰውነት ውስጥ የቫይረሱ መጠን በጣም ከፍ ባለ ቁጥር ህመም እንደሚከብድ የሚታወቅ ነገር ስላለ ነው፡፡

ሶሰተኛ፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያሉት ክትባቶች ላይሠሩ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖር ይሆን የሚልም አሳሳቢ ጥያቄ አለ፡፡ እንግዲህ ከላይ ሳብራራ፣ በኮድ ለውጥ ምክንያት የቫይረሶች ፕሮቲኖች የሚቀየሩ ከሆነ፣ የትኛው ፕሮቲን ነው ይህን ለውጥ ያሳያው፣ ካሳየስ የባህሪ ለውጥ አለ ወይ ነው፡፡ በዚህ ቫይረስ ወሳኝ ፕሮቲን ሆኖ የተገኘው ሰፓይክ ፕሮቲን ነው፡፡ በርግጥ በዚህ ፕሮቲን ላይ፣ 23 ቦታዎች የአሚኖ አሲድ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ለውጡም ቫይረሱ ከሞሎኪል ጋር የሚገናኝበት ቦታን ነካክቷል፡፡ ነገር ግን እሰካሁን በመጠኑ ነው፣ እናም በፕሮቲኑ ላይ የታያው የኮድ ለውጥ ክትባቱን እንደማይሠራ አያደርገውም ነው የሚባለው፡፡ ያ ግን አስከመቼ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ እናም ከዚህ ቫይረስ ጋር የግድ መሽቀዳደም ይኖርብናል፡፡ ሌላ ዝርያ ከመፍጠሩ በፊት፣ በቁጥጥር ሥር ማድረግ ይኖርብናል፣ ያ ደግሞ ሥርጭቱን ለመግታት የሚደረጉ ተግባራትን መከተል ነው፡፡ አለዚያ ሁሉም በሚገባ ቢከተብ ግን ክትባቱን ማምለጥ የሚችል ፕሮቲን ያለው ቫይረሰ በቀላሉ እንደገና ይሠራጫል ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ የሰውነት መከላከያ አቅም፣ የቫይረሱ መታወቂያ አድርጎ ዘግቦ የያዘው ይህንን የስፓይክ ፕሮቲን ከሆነ፣ ቫይረሱ ደግሞ የሰፓይክ ፕሮቲኑን ቀይሮ አዲስ ካደረገው፣ የመከላከያ አቅሙ ዘግቦ ከያዘው ፕሮቲን የተለየ ከሆነ፣ የተሠራው የተፈጥሮ አንቲቦዲ አግልጎሎት ላይ አይውልም፡፡ በቀላል አማርኛ፣ ፖሊስ ክትትል የሚያደርገው በፀጉር ቀለም፣ በመታወቂያ ከሆነ፣ ይህንን መቀየር የቻለ ተፈላጊ ያመልጣል ማለት ነው፡፡ ይህም እንዱ አደጋ ነው፡፡

በነገራችን ላይ፣ ይህን የፕሮቲን መሥሪያ ኮድ መቀየርና ፕሮቲኖችን (የቫይረሶች) ማለቴ  ነው ባህሪያቸውን መቀየር መቻል፣ ለተላላፊ ባለሙያኞች የእለት ከእለት ክትትል የሚያደርጉበት ነገር ነው፡፡ ያም እንደ ኤች አይ ቪ፣ ሄፓታይትስ ሲ ና ቢ የተባሉ ቫይረሶችን የምናክም ሰዎች፡፡ Mutation and mutation codes የሚባሉ ነገሮች በሥራ ላይ የምንጠቅምባቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው፣ የተሠሩት መድሃኒቶች የቫይረሱን አንድ ክፍል ፕሮቲን (ኤንዛይም) ኢላማ ሰለሚያደርጉ ነው፡፡ ቫይረሱ ያንን ፕሮቲን ሲቀይር መድሐኒቱ አይሠራም ሰለዚህ አስቀድመን ማወቅና መቀየር አለብን፡፡ እናም በቀላሉ ጂኖታይፕ የሚባሉ የላቦራቶር ምርመራ በማድርግ ቫይረሱ መድሐኒቱ ኢላማ ያደረገውን ፕሮቲን መቀየርና አለመቀየሩን ለማወቅ እንሞክራለን፡፡ መድሐኒቱ በቫይረሱ ላይ የማይሠራበትን ቫይረስ (Resistance virus) እንለዋለን፡፡ እናም በዚህ ቫይረስም፣ ለህክምና የሚውሉት መድሐኒቶችም አደጋ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ ነው፡፡

አራተኛ፡ እምብዛም የማይነገረው አደጋ ደግሞ፣ የላቦራቶር ምርመራ ነው፡፡ ቫይረሶችን ለይቶ ለማወቅ የተለዩ የቫይረሱን አካላት በምርመራ ተለይተው እንዲታወቁ ይደረጋል፡፡ እናም ለቫይረሱ እንደመለያ የሆኑት የቫይረሱ አካሎች (ፕሮቲኖች) ከተቀየሩ፣ መመርመሪያው መንገድ ሳያውቃቸው ይቀርና፣ ቫይረሱ እያለ፣ የላቦራቶሪው ውጤት ቫይረሱ የለም የሚል ይሆናል፡፡ (False negative)፡፡ እሰካሁን ድረስ በሳርስ ኮ ቫይረሰ ቁ2 በኩል ይህ ሥጋት የለም፡፡ ምክንያቱም ቫይረሱን ለመለየት እንደመታወቂያ ተጠንተው በላቦራቶሪ በኩል የሚፈለጉት የቫይረሱ የፕሮቲን መጠኖች ብዛት ያላቸው ናቸው፡፡ በተወሰኑ ብቻ አየደለም፡፡ ሰለዚህ ቫይረሱ ከላቦራቶሪ ምርመራ ለማምለጥ ብዙ ፕሮቲኖችን መቀየር ወይም ብዛት ያላቸው mutation ማድረግ አለበት፡፡ አስካሁን አልሆነም፡፡ ያም ሆኖ ሥጋቱ ሰላለ፣ የዚህን ቫይረስ ሥርጭት በፍጥነት ማድከምና ማስቆም ይኖርብናል፡፡ እዚህ ላይ ግን ሁሉም ተባባሪ መሆን አለበት፡፡ ሰለዚህ ቫይረሰ፣ መከላከያ፣ መመርመሪያ መንገዶች አዲስ አይደሉም፡፡ አዲስ የሆነው ቫይረሱና ባህሪው ነው፡፡ ሰለዚህ ትንሽም ቢሆን ማብራራቱን ጉዳዩን ለሚያውቁ ሰዎች በማድረግ ትክክለኛው መረጃ ማግኘት ጥሩ ነው፡፡ የጓደኛና የጎረቤት ኤክስፐርቶቸን፣ አንድ ላይ እናንብብ ብሎ መልካም ምክር መለገስም ጥሩ ነው፡፡

ከመዝጋቴ በፊት፣ ሰለ አዲሶቹ ክትባቶች አንድ ልበል፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩላችሁ፣ ፕሮቲን ሲመረት፣ ከጀርባው ትዛዙን የያዘውን ኮድ ይዞ የሚመጣው mRNA መልክተኛው ነው፡፡ መልክተኛው፣ የተወሰኑ ኮዶች ለተወሰነ የፕሮቲን አይነት ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ ይህ እንግዲህ ሰውነታቸን በህይወት ዘመኑ በየቀኑ የሚያደርገው የተፈጥሮ ሂደት ነው፡፡ ሂደቱ እንግዳ አይደለም፡፡ ሀኪሞቹና ሳይንቲሰቶቹ እየጣሩ ያሉት በተፈጥሮ የሚታዩትን የመከላከያ መንገዶች በመኮረጅ ለመጠቀም ነው፡፡ እንጂ አንዳንዶቸ በስፋት እንደሚያወሩት የተለየ ፀረ- ሰው ባሕሪ ያለው ነገር ለመሥራትም አይደለም፡፡

እንግዲህ ክትባቶቹ፣ ከውጭ የሚዘጋጁት ሰውነት ውስጥ ከገቡ በኋላ፣ ሰፓይክ የተባለውን ፕሮቲን ብቻ እንዲመረት የሚያደርግ ትዛዙን የያዘ mRNA ለመሥጠት ነው፡፡ በሴሎች በተለይም በጡንቻ ሴሎች ውስጥ፣ ይህ ከውጭ የተዘጋጀው mRNA በሴሉ ውስጥ ይሆንና ትዛዝ በመሥጠት ስፓይክ ፕሮቲን እንዲሠራ ያደርጋል፡፡ ልብ ብሉ፣ ያ የሚሠራው ስፓይክ ፕሮቲን አሁን በመዘዋወር ላይ ያሉ ቫይረሶች ወደ ሰውነት ለመግባት የሚጠቀሙበት ስፓይክ ፕሮቲን ቅጅ ወይም አምሳያ ነው፡፡ ፕሮቲኑ ከተሠራ በኋላ፣ ከውጭ በክትባት በኩል የተሠጠው mRNA ወዲያውኑ ከሴሉ ይወገዳል፡፡ ሴሎቹ ራሳቸውን የማፅዳት ችሎታ አላቸው፡፡ ሰለዚህ የሚቀር ነገር የለም፡፡ ሌላው ጠቀሜታ፣ ሰውነት የራሱን መከላከይ ለማበጀት ስፓይክ ፕሮቲኑን ኢላማ ለማድረግ አንድ ሰው በቫይረሱ መያዝ አለበት፣ ነገር ግን በዚህ የክትባት መንገድ ያ አስፈላጊ አይደለም፣ ፕሮቲኑን ብቻ ማዘጋጀት ነው፡፡ ፕሮቲኑ ብቻውን ደግሞ መራባት የሚችል ቫይረስ ቀርቶ ቫይረስም አይሆንም፡፡ ሰለዚህ ለቫይረሱ ሳይጋለጡ በአቋራጭ የቫይረሱን መታወቂያ ማግኘት ነው፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ፣ mRNA ወደ ሴሉ አስኳል አይገባም፡፡ የሴል አስኳል፣ የተከበረ ቦታ ነው፣ ለምን? የዘር ሀረጋችን የሚተረጉመው DNA የሚባለው የዘር ስንሰለት እዛ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሰለዚህ በክትባት በኩል የተሠጠው mRNA በጣም ውሱን ሥር ብቻ የሚሠራ ከመሆኑ ባሻገር ወደ አስኳሉ ሰለማይገባ ከዘር ሀረጋችን DNA ጋር ንክኪ የለውም፡፡

ቀጥሎ የሚመጣው ነገር፣ ሰፓይክ ፕሮቲኑ ከተሠራ በኋላ ገና ከጡንቻ ሴሎች ብቅ ከማለቱ፣ የሰውነታችን የስለላ ክፍልና መከላከያ ክፍሉ ይህንን አዲስ ፀጉረ-ልውጥ ፕሮቲን ይመዘግብና መደመስሻ አንቲቦዲ ያዘጋጅለታል፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን፣ በደንብ በጠላትነት ፈርጆ ሰለመዘገበው፣ በሚቀጥለው ይህንን ፕሮቲን የያዘው ውነተኛው ቫይረስ ብቅ ሲል፣ ለዚህ ጉዳይ የተመደቡ ሴሎችና አንቲቦዲዎች በፍጥነት ተንቀሳቀሰው ፐሮቲኑን ከነቫይረሱ ያመክኑታል፡፡ በዚሀ መንገድ በቫይረሱ ከመያዝ ከዛም አስተላለፊ ከመሆን እንድናለን ማለት ነው፡፡ አንግዲህ ክትባት ማለት ሚስጥሩ ይሀ ነው፡፡ የተፈጥሮ መከላከያን ማንቃትና ማዘጋጀት ነው፡፡ ዘዴው ነው ዋናው፡፡ ይህ ዘዴ፣ mRNA ለክትባት መጠቀም ወይም የክትባት አሠጣጥ አሁን ተሳክቶ ሥራ ላይ ዋለ እንጂ ከ1990 ጀምሮ ጥናት ላይ የነበረ ነው፡፡

ለማንኛውም በዚህ ላቁም

አካፍሉ

ከምሰጋና ጋር

Community health 

education in Amharic 

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ