Health and History

ያልነበረው እንደነበረ!

ስመ ጥሩ የሆነው ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን በጥናት ሲታይ የረዳውም የጎዳውም ነገር የለም፣ እንዳውም… 5/18/2020

    በተስፋም ይሁን ህዝቡን ለማረጋጋትም ይሁን፣ ገና መረጃ በሌለበት ሁኔታ፣ ይህን ለዎባና ለሌሎች በሽታዎች አገልግሎት የሚውል ክሎሮኩዊን ወይም ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን ለኮቪድ-19 መድሐኒት እንደሆነ ተደርጎ መነገሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ብዙዎቻችን፣ ባለሙያተኞች ይህ ነገር የችኮላ ነው፤ የሚታወቅ ነገር የለም፤ በማለት ለመከራከር ሞክረን ነበር፡፡
     ሲጀመር፣ አንድ መድሐኒት ሲሠጥ ጉዳት አለው ወይ ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን በራሱ ብቻውን ሳይሆን ዚትሮማክስ ከተባለ መድሐኒት ጋር ሲሠጥ ይረዳል ተብሎ፣ ለህሙማኑ ሲሰጥ ነበር፡፡ ከዚያም፣ እነዚህ ሁለቱ መድሐኒቶች አንድ ላይ፣ ሆስፒታል ለማይገቡ ከውጭ ሆነው መታከም ለሚችሉ ሰዎች ይሠራ ይሆን ተብሎ፣ በጀት ተመድቦ ጥናቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ እኔ ራሴ የማውቀው፣ ሁለት የዚህ አይነት ጥናቶች አሉ፡፡
     ነገር ግን፣ የታወቀ ነገር ቢኖር፣ ከላይ የተጠቀሱት ሁለት መድሐኒቶች አንድ ላይ ሲሠጡ የልብ ትርታ መዛባት በማምጣት፣ ህመምተኞቹን አደጋ ላይ ሰለጣሉ፣ ሁለቱም አንድ ላይ እንዳይሠጡ ተብሎ፣ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን ብቻውን እየተሠጠ ነው፡፡
     በዚህ በኮቪድ-19 ወቅት፣ እሰካሁን ድረስ ይህ ነው ተብሎ ያድናል ተብሎ ፈቃድ የተሠጠው መድሐኒት የለም፡፡ ግን የተለያዩ መድሐኒቶች ይሞከራሉ፡፡ አማራጭ በማጣትና በጥናት መልክ ነው የሚሠጡት፡፡ ሰሞኑን በወጣ ጥናት፣ የኢቦላ መድሐኒት፣ ረምደሰቪር የሚባል፣ ፍንጭ አሳይቷል ተብሎ፣ ማለትም የህሙማኑ የሆስፒታል ቆይታ አነስ ብሏል ተብሎ ጊዜያዊ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡ ችግሩ፣ አሱም ቢሆን ዕጥረት ሰላለ ሁሉም ሆስፒታሎች ውስጥ አይገኝም፡፡ ያገኙ ቦታዎች በጥናቱ የሚሳተፉ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ በጥናት መልክ ሲሰጥ፣ በሽተኛው ወይም የበሸተኛው ቤተሰቦች መስማማታቸው ወይም ፈቃድ እንዲሠጡ የሚጠየቀው፡፡
       ወደ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን እንመለስና፣ በቅርቡ፣ በታወቂው የህክምና መፅሄት፣ በኒው ኢንግላንደ ጆርናል፣ የወጣውን ይህንን መድሐኒት በሚመለከት የተዘገበውን ጥናት እንመልከት፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በኒው ዮርክ ከተማ ነው፡፡ አጥኝዎቹ ማወቅ የፈለጉት፣ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊንን መጠቀም፣ በህሙማኑ ላይ አርቴፊሻል መተንፈሻ (ቬንቲሌተር) መጠቀም ወይም ከሞት ጋር ለውጥ አምጥቷል ወይ ነው፡፡

ይህ ጥናት፣ የነበሩትን መረጃዎች በመሰብሰብ የተካሄደ ነው፡፡ ያደረጉት ነገር፣ በድንገተኛ ክፍል በኩል ከመጡት በኮቪድ-19 ከተያዙ ህሙማን መሀከል፣ በ24 ሰአት ውስጥ ቪንቴለተር ላይ እንዲሆኑ የተደረጉ ወይም የሞቱትን ሰዎች መረጃ አልጨመሩም፡፡ ለጥናቱ በቂ ጊዜ ለመስጠትም ነው፡፡ ተከትለው ያደረጉት ከማርች 7 አስከ አፕሪል 8፣ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ጥናቱን፣ በኒው ዮርክ ከተማ፣ ማንሀተን፣ ኒው ዮርክ ፐርሰባይተሪያን ሆስፒታል (ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አርቪንግ ሜዲካል ሴንትር) ነው፡፡ በኮቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ ከተረጋገጠ አዋቂዎች፣ ከሁሉም ናሙና ወሰዱ፡፡ ጥናቱንም እሰከ አፕሪል 25 ድረስ ቀጠሉ፡፡ ጥናቱም፣ አንደ አግባቡ፣ በጥናት ገምጋሚ ቦርድ ተፈቀደ፡፡ መረጃዎችን ከተለያዩ ክፍሎች ሰበሰቡ፡፡  በድንገተኛ ክፍል ከገቡ ከሀያ አራት ሰአታት በኋላ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊንን በማንኛውም መንገድ የተሠጣቸው ህሙማን ጥናቱ ውስጥ አካተቱ፡

የጥናቱ ዋና መገምገሚያው፣ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን ከተሠጣቸው ከመነሻው ጀምሮ በተደረገው ክትትል፣ በሽተኞቹ ምን ያህሉ ቪንቴሌተር ላይ ሆኑ ወይም ምን ያህሉ ሞቱ ነው፡፡ ይህን ሲመለከቱ፣ አንደኛ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን ካልተሠጣቸው ህሙማን ጋር በማነፃፀር፣ ሁለተኛ ደግሞ፣ ሌሎች ምክንያት ወይም ሰበቦች፣ የጥናቱን ውጤት ወደ አንድ እቅጣጫ እንዳይገፉት፣ በሁለቱም በሚነፃፀሩት ወገኖች በኩል አኩል በሆነ ደረጃ እንዲታዩ ነው፡፡

የስታቲሰቲካል ቋንቋውን ለጊዜው ተወት አድርገን፣ ውጤቱ ላይ ስናተኩር፣ ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ፣ 1446 በኮቪድ-19 የተያዙ ህሙማን፣ በተለያየ ጊዜ ወደ ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፣ በጥናቱ መመዘኛ መሠረት፣ 70 የሚሆኑት ከጥናቱ እንዲገለሉ ተደረገ፡፡ ስለዚህ በቀሩት 1376 ህሙማን ከተሰበሰው መረጃ ትንተና ወይም ግምገማ ተካሄደ፡፡

የጥናቱ ማቆሚያ በነበረው በአፕሪል 25፣ 232 ሰዎች ሞተዋል፡፡ የቀሩት 1025 አገግመው ከሆስፒታል ወጥተዋል፤ በዚያን ጊዜ  በሆስፒታል ከቀሩት 119 ሰዎች መሀል 24 ብቻ ነበሩ ቬንቲሌተር ላይ ያልነበሩት፡፡

ከ1376 ህሙማን መሀከል፣ 811 ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን ተሠጥቷቸዋል፡፡ 565(41.1%) መድሐኒቱ አልተሠጣቸውም፡፡ በታየው ውጤት፣ የጥናቱ ግብ የሆኑት፣ ቪንቴለተር ላይ መሆንና ሞትን በተመለከተ፣ ከ346 ሰዎች መሀከል፣ 180ዎቹ ቪንቲሌትር ላይ ሲሆኑ፣ 166 ደግሞ ቪንቲሌተርe ሳይደርሱ ሞተዋል፡፡

አጥኝዎቹ የሚነግሩን ነገር፣ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን የወሰዱ ሰዎች ካልወሰዱት ይልቅ ከላይ የተጠቀሱት ግቦች ውስጥ ሲገኙ ታይተዋል፡፡ ነገር ግን፣ የተለያዩ ሰበቦችና ምክንያቶቸን በማካተት በተደረገው ስሌት፣ የጥናቱ ድምዳሜ፣ በዚህ ጥናት፣ ህሙማ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን ሰለወሰዱ ቪንቴለተር ላይ በመሆን ወይም ውጤቱ ሞት በሆነበት ሁኔታ ምንም የቀነሰው ወይም የጨመረው ነገር የለም፡፡ ማለትም ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን መውሰድ ህሙማኑን ቪንቴለተር ላይ ከመሆን ወይም ከመሞት የረዳቸው ነገር የለም ነው፡፡ ያም ካልወሰዱ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር ነው፡፡ ከዚህ ውጤት በመነሳት፣ አጥኝዎቹ በሆስፒታላቸው ውስጥ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን ከህክምና ሰልፍ እንዲወጣ ተደርጓል ይላሉ፡፡ እንዳውም በደንብ በመደበኛ ጥናት ካልቀረበ በስተቀር ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊንን መጠቀም የጥናቱ ውጤት አይደግፈውም ነው፡፡

እረፉት እንግዲህ፡፡

ያም ሆኖ፣ ይህ አንድ ጥናት ብቻ በመሆኑ፣ መደበኛ የሆነውን አይነተኛ ሳይንሳዊ ጥናት ተከትሎ የተሠራ ባለመሆኑ፣ አይነተኛው ጥናት የግድ መጠናት ይኖርበታል፡፡ አስካሁንም ይህ መድሐኒት ለታማሚዎች እየተሠጠ ነው፡፡ ጉዳቱ እያመዘነ ከመጣ ግን፣ ያው ከሰልፍ ውጭ ይሆናል፡፡ ስለ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን አጠቃቀም፣ ከጀርባው የተለያዩ በቁጥር ትንሽ ከሆኑ ህሙማን የታዩ ጥናቶች አሉበት፡፡ ችግሩ በጥቂት ሰዎች ብቻ ተመርኩዞ ጠንከር ያለ መደምደሚያ መስጠት እንደማይቻል የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን ሳይሆን ክሎሮኩዊንን በሚመለከት፣ 440 ሰዎች የተካተቱበት ጥናት ተጀምሮ፣ 81 ሰዎቸ መድሐኒቱ ከተሠጣቸው በኋላ፣ ጥናቱ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ይህም የሆነው፣ ክሎሮኩዊን 600 ሚሊግራም በቀን ሁለት ጊዜ ከተሠጣቸው መሀል፣ አደገኛ የሆነ የልብ ትርታ መዛባት ብቻ ሳይሆን መቆምም የሚችልበት ሁኔታና ከህይወት ማለፍ ጋር የሚያያዝ ደረጃ የሚያደርስ ምልክት ስለታየ ነው፡፡

እንግዲህ መመልከት የምንችለው፣ መድሐኒት ተገኘ ሲባል፣ ምን ያህል ፍተሻ እንደሚደረግ ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ፣ የተባለው መድሐኒት ጉዳት ያደርሳል ወይ? ጉዳቱስ ምን ያህል ነው? እንዳያችሁት፣ ጉዳት ያለው ከሆነ፣ ጥናቱም፣ መድሐኒቱም ይቆማል፡፡ የባህል መድሐኒትም ቢሆን፣ ጉዳት ማምጣቱና ፈዋሽነቱ መፈተሸ አለበት፡፡ ያልተፈተሸን ነገር፣ ወይም የህሙማንን ደጅ ያልረገጠን ነገር፣ “ያድናል” ሲባል፣ ሰምቶ ወደሌላ ከማሳለፍ በፊት፣ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንጀመር፡፡

አካፍሉ



​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic