በኮቪድ-19 የተያዙ ወላዶች ልጆቻቸውን ማጥባት ይችላሉ ወይ?

በሰሜን አሜሪካ በተለያዩ በሽታዎች የተያዙ ወላዶች በሚወልዱበት ጊዜ፣ የተወለዱትን ሕፃናት አያያዝ በተመለከተ፣ መመሪያ የሚሠጥ የሀኪሞች ወይም የባለሙያተኞች ማህበር (The American Academy of Pediatrics, AAP)፣ ከዚህ ቀደም፣ በኮቪድ-19 የተያዙ ወላዶች በሚወልዱበት ጊዜ ወረርሽኙ እንደተከሰተ የሠጠው መመሪያ፣ ወላዶችና ህፃናትን ለተወሰነ ጊዜ አለያይቶ ማስቀመጥ የሚል ነበር፡፡ ያም የተወለዱትን አዲስ ህፃናት እናቶቻቸው በተያዙበት የኮቪድ በሽታ እንዳይያዙ በሚል ጥንቃቄ ነበር፡፡ በዚያን ጊዘ ብዙም መረጃ ሰላልነበረ ሰዎችም እየሞቱም ጥንቃቄ ያመዘነ መመሪያ ነበር፡፡ ያ ሲመከር፣ ህፃናቱ ከእናቶቻቸው የሚያገኙዋቸውን የተለያዩ ጥቅሞችን ያጓደለ መሆኑ ግልፅ ነበር፡፡ አሁን ግን፣ ሰለ በሽታውና ሥርጭቱ ብዙ ትምህርት ሰለተገኘ፣ የተለያዩ ጥናቶችም በየቦታው እየወጡ ሰለሆነ፣ ከመረጃዎች በመነሳት በኮቪድ 19 የተያዙ ወላዶች በሚወልዱበት ጊዜ ከዚህ ቀደም የተሠጠው ምክርና መመሪያ እንዲቀየር ሆኗል፡፡ እኔም እንደተለመደው ጥናት ተመርኩዞ የቀረበውን መረጃ ላካፍላችሁ አወዳለሁ፡፡

የዚህ ጥናት ውጤት የቀረበው፣ JAMA Pediatrics በተባለ ታዋቂ የህክምና መፅሄት ነው፡፡ የጥናቱ ዋና አቅራቢዎች ማጥናት የፈለጉት፣ በኮቪድ-19 የተያዙ ወላዶችና አዲስ የተወለዱተን ህፃናት አንድ ላይ ማድረግ ሊደርስ የሚችል ችግር አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ነው፡፡

ጥናቴ የተካሄደው በኢጣልያ ሲሆን በተለያዩ የህክምና ማዕከሎች ነው፡፡ በዚህ መሠረትም በኮቪድ-19 ከተያዙ እናቶቻቸው የተወለዱ 62 ህፃናትን ውጤት ነው ያጋሩን፡፡ ወላዶቹ በወሊድ ጊዜ ኮቪድ-19 የተያዙ ሲሆን፣ የኦክስጅን ርዳታ ያላስፈለጋቸው፣ የሰውነት ሙቀት መጠን ከ38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ያልሆነ፣ እናም ልጆቻቸው መያዝ የሚችሉ ማለትም ከባድ የህመም ስሜት የሌላቸው ነበሩ፡፡ ወላዶቹ ከልጆቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት፣ የበሽታ መተላለፍ እንዳይኖር የተደረገው የመከላከያ ዘዴ፣ ያተኮረው፣ እጅን መታጠብና ወላዶቹ አራስ ህፃናቶችን ጡት በሚየጠቡበት ጊዜ፣ ወይም ከጡታቸው ወተት ወደ መያዣዎች በሚሰበስቡበት ጊዜና በማንኛውም ህፃናቱን እንክብካቤ በሚሠጡበት ጊዜ ማስክ (ሰርጂካል ማስክ) እንዲያደርጉ፣ ከተወለዱት ህፃናት ጋር ግንኙነት በማይኖርባቸው ጊዜ ደግሞ በሁሉም ጊዜ የሁለት ሜትር ርቀት እንዲጠብቁ ተደርጎ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ከዚህ በፊት ሲመከር የነበረው ጭራሽ ወላዶችና ህፃናቱ ለተወሰነ ጊዜ በአንድ ክፍል እንዳይቆዩ እንዲደረግ የተለየ መሆኑ ግልፅ መሆን አለበት፡፡

ወላዶች ሰለዚህ ጥንቃቄ ትምህርት የተሠጣቸውና መመሪያው በፅሁፍም የተሠጣቸው ናቸው፡፡

ከዛ በኋላ ሁሉም ህፃናት ጡት እንዲጠቡ ተደርጓል

በዚህ በጥናት ወቅት ጎብኝ ወይመ ጠያቄዎች ከወላዶችና ከህፃናቱ ጋር እንዳይገናኙ ተደርጓል፡፡ (የአገር ቤት ትልቁ ችግር ጠያቂው ነው)

ህፃናቱም፣ በአፍንጫቸው በኩል ለቫይረሱ የምርመራ ክትትል ተደርጓል፡፡ ቢዘህ መሠረት፣ የተወለዱ ዕለት፣ በሰባተኛው እሰከ ዘጠነኛው ቀን፣ ከሀያኛው አስከ ሀያ ሁለተኛው ቀን ላይ ኮቨድ-19 ለሚያስከትለው የሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁ 2 ምርመራ ተደረገ፡፡ ወዲያው እንደተወለዱ በተደረገው ምርመራ አንደኛቸውም ህፃናት ቫይረሱ አልተገኘባቸውም፡፡ በጠቅላላው እስከ መጨረሻው በተደረገው ክትትል ከስልሰ ሁለቱ  ህፃናት ስልሳ አንዱ ላይ ቫይረሱ አልተገኘባቸውም፡፡ አንደኛው ቫይረሱ የተገኘበት ህፃን እናት፣ መጀመሪያ ቀለል ያለ ህመም ቢኖራትም በአምስት ቀናት ውስጥ ህመም እየጠናባት ሄዶ ከቀላል ሳል ወደ ትንፋሽ ማጠርና መድከም ታየቶባታል፡፡ ልጇም በሰባተኛው ቀን ቫይረሱ ተገኝቶበት ቀለል ያለ የትንፋሽ ቸግር የታየበት ሲሆን ከተወለደ በ18ኛው ቀን ምርመራ ሲደረግ ቫይረሱ ተገኝቶበታል፡፡ ነገር ግን ተሸሎት ከሆስፒታል ወጥቶ ከተወለደ በ30ኛው ቀን በተደረገው ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ ተገልጧል፡፡

የዚህ አይነት ጥናት ሲደረግ የመጀመሪያው አይደለም፣ እንዲያውም የዚህ የኢጣልያ ጥናት ውጤት ከዚህ ቀደም በኒው ዮርክ ከተማ በ120 አዲስ የተወለዱ ህፃናት ላይ ከተደረገው ጥናት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በኒው ዮርክ በተደረገው ጥናትም ቢሆን፣ እናቶቹ ወይም ወላዶቹ ሲያጠቡም ሆነ ህፃናቱን ሲንከባከቡ ሰርጂካል ማስክ በማድረግ፣ ንክኪ ከማድረጋቸው በፊትም ቢሆን እጃቸውን እየታጠቡ ነበር፡፡ በተደረገው ክትትልም ከ120 ህፃናት 82 ቫይረሱ አልተገኘባቸውም፡፡

በሌላ በኩል፣ ደግሞ በፈቃደኝነት ከተመዘገቡ የ4ሺ ህፃናት የተገኘው መረጃ የሚያሳያው ደግሞ፣ ከአራት ሺ ህፃናት፣ ስልሳ ፐርሰንት የሚሆኑት እንደተወለዱ ከእናቶቻቸው ጋር በአንድ ክፍል የነበሩ ናቸው፡፡ ለቫይረሱ በተደረገው ምርመራ ደግሞ፣ ሁለት ፐረስንት የሚሆኑት ህፃናት ብቻ ናቸው ቫይረሱ የተገኘባቸው፡፡ ይህ ባጠቃላይ ሲታይ፣ በቫይረሱ ከተያዙት እናቶች ወደ ህፃናት በጣም ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ ነው የተላለፈው፡፡ እንደዚህ አይነት የጥናት ውጤት ሲኖር፣ ለውጤተ ምክንያት የሚሆን የተፈጥሮ ሂደት ይኖር ይሆን ብሎ ይጠየቃል፡፡

አንድ የቀረበ ሳይንሳዊ ጥናት የሚያሳየው ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም በሌሎች ፅሁፎች እንደምጠቁመው፣ የሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁ 2 ወደ ሰውነት ሴሎች ለመግባት፣ ACE-2 and TMPRSS2 የተባሉ ፕሮቲኖች ይጠቀማል፡፡ ሰለዚህ ፅንሱ በሳርስ ኮሮና ቁ 2 ለመያዝ፣ በነብሰ ጡር እናትና በልጅ መሀከል ሁሉም ነገር የሚያስተላለፈው የእንግዲህ ልጅ (Placenta) በቫይረሱ መያዝ አለበት፡፡ የተደረገው ጥናት የሚያሳየው የእንግዲህ ልጁ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የቫይረሱ መግቢያ ፕሮቲኖች በጣም መጠነኛ በሆነ ደረጃ ነው የሚገኙት፡፡ ህም፣ አሁን ሳይንሳዊ ምክንያት አለ ማለት ነው፡፡ በእርግዝና ላይ መያዝ ካልተቻል፣ አደጋ የሚመጣው ልጁ ከተወለደ በኋላ ነው ማለት ነው፡፡

ወደ ማሳረጊያው ስንሄድ፣ መልክቱን መቋጨት አስፈላጊ ነው፡፡

በዚህ መሠረት፣ በኮቪድ-19 የተያዘች ወላድ፣ በየትኛው ጊዜ ቫይሱን ማስተላለፍ እንደምትችል ግልፅ ሰለማይሆነ፣ ህፃኑ ወይም ህፃኗ እንደተወለደች ወዲያውን የመከላከያ ተግባሮች መጀመር አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ ከላይ በኢጣልያው ጥናት እንደታየው በጣም በጠና የታመመቸው ሴትዮ ቫይረሱን ወደ ልጇ ያስተላለፈች ሲሆን፣ የበሽታ ስሜት የማይሰማቸው በቫይረሱ የተያዙት ወላዶችም ቫየረሱም ማስተላለፍ እንሚችሉ መታወቅ አለበት፡፡ ሌላው ነገር፣ ብዙዎች ወላዶች፣ በቫይረሱ ተይዘው ህምመ ጠንከር የሚልባቸው ከወለዱ ከቀናት በኋላ ነው፡፡

ወላጅ እናት፣ በምታጠባበት፣ ልጁን በምትንከባከብበት ጊዜና፣ ከጡት ወተት በምትሰበስብበት ጊዜ ሰርጂካል ማስክ በአግባቡ ማድረግ፣ እጅዋን መታጠብ ይኖርባታል፡፡
ልጁን ካሰተኛች ወይም የህጻን አልጋ ላይ ካሰቀመጠች በኋላ ደግም የሁለት ሜትር ርቀተ መጠበቅ አለባት
ከእናት ውጭ ሌሎቸ የቤተሰቡ አባላትም ቢሆን ህፃኑን የሚንከባከቡ ከሆነ ሰርጂካል ማስክ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ እዚህ ላይ፣ ከህፃኑ ተነስቶ ወደ ሌሎች የቤተሰብ አባላት ቫይረሱ ሊሻገር እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡ ድንገት በቫይረሱ ተይዞ ከሆነ፡፡
በዚህ ሁኔታ ሊኖር የሚችለውን የቫይረሱን መሸጋገር በሚደረጉት ጥንቃቄዎች በመቀነስ፣ ወላዶች ልጆቻቸውን መንከባከብ ይችላሉ፡፡
የጠያቂ ነገር ችግር ነው፡፡ ሰለዚህ ወላጆች ቀጨም ብለው፣ ጠያቂ ወደ ቤት አንዳይገባ መከላከል አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ደግሞ፣ ጠያቂው ራሱ በኮቪድ-19 ከተያዘችው ወላድ በሚመጣ ቫይረስ እንዳይያዝ ይረዳል፡፡
ሆኖም፣ ወላዶ በጣም በጠና ከታመመች፣ ከሀኪሞቻቸው ጋር በመመካከር የሚደረገው ጥንቃቄ ላይ መመካከር ያስፈልጋል

 መልካም ንባብ፡፡ ባካችሁ አካፍሉ፡፡

ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic