የፈሩት ይደርሳል! 01/25/2021

ከዚህ ቀድም የኮሮና ቫይረስ ቁ 2 ያለ ገደብ መሠራጨት ከሚያስከትላቸው ውጤቶች አንዱ ቫይረሱ በየጊዜው አዳዲስ ዝርያዎችን እየፈጠረ መሄድ ብቻ ሳይሆን በባህሪው ለውጥ እያመጣም እንደሚሄድ ነው፡፡ በታህሣስ መጨረሻ ላይ የተከሰተው ይህ የኮሮና ቫይረስ ቁጥር 2፣ አሁን ብዙ ለየት ያሉ ዝርያዎች እንዳሉት እየታወቀ ነው፡፡ እንደመጣ ዝርያ ሳያፈራ ቀርቶ አይደለም እሰካሁን እንዳሁኑ በአደባባይ ያልታወቀው፡፡ ይልቁንስ የቫይረስ ዝርያዎችን ሆን ብሎ በስፋት ማጥናቱን አቅም ያላቸው መንግሥታት ሲያደርጉት ሰላልነበር ነው፡፡ ኢንግላንድ፣ ጨከን ብላ ባጀት መድባ የዚህን ባይረስ ዝርያዎች መከታተል ስትጀምር ነው በደቡባዊ ኢንግላንድ አካባቢ አዲስ ቫይረስ መከሰቱን ለአለም ያስተወቀችው፡፡ ከዛ በኋላም አሜሪካም ሆነ ሌሎች አገሮች በስፋት ምርመራውን ጀመሩ፡፡ በአንግሊዝኛ Genomic study ይባላል፡፡

ቫይረሱ ከተሰተበት ቀን ጀምሮና መጀመሪያ የታየው ቫይረስ የዘር ሀረግ ለሳይንቲሰቶቹ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ፣ እሰከ አሁን ጃንዋሪ 2021 መባቻ ድረስ ባጠቃላይ 300ሺ የዝርያ ጥናቶች ነው የተደረጉት፡፡ ሰለዚህ በዚያ መጠን ብቻ ዝርያውን የቀየረውን ቫይረስ በወቅቱ መከታተል ይቸግራል፡፡ ለጠመንጃና ለጥይት የሚያወጡትን በጀት ያህል በዚህኛው ቢደፍሩና ሳይንስን ቢቀበሉ፣ አደጋውንም ቢረዱ ነገሩ ቀላል ነበር፡፡

ለማንኛውም የቫይረስ ዝርያ ሲቀየር፣ ድሮ ከነበረው የቫይረስ ዝርያ በባህሪ ለውጥ እየታየ ነው፡፡ መጀመሪያ ደጋግሞ እየታየ ያለው ባህሪ ደግሞ በፍጥነትና በብዛት በመራባት ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው መሸጋገር መቻል ነው፡፡ ይህም ታየቷል፡፡ ሌላው የምንፈራው ነገር ደግሞ የከፋ በሽታ ያመጣ ይሆን የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ ለሱም ቢሆን፣ ሰሞኑን የእንግሊዙ መራሄ መንግሥት፣ ራሳቸው ከኮቪድ በተአምር የተረፉት ሰው፤ መድረክ ይዘው፣ ይህ በኢንግላንድ የታየው አዲስ ቫይረስ በጣም እያሳመመ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ሲዘዋወሩ ከነበሩ ቫይረሶች ጋር ሲነፃፀር ህመም የማጠንከርና የመግደል ችሎታው በ30 ፐርስንት አድጓል ብለው ተናገሩ፡፡ ይህ ቫይረስ ባገራቸው መገኘቱ እንደታወቅ ጠበቅ ያለ የኮቪድ ሥርጭት መከላከያ ርምጃዎችን መውሰዳቸውን ያስታወሰ ሰው፣ ምንም አሁን ወጥተው ቫይረሱ በጣ ያሳምማል የበለጠ ይገድላል ቢሉም ቀደም ብሎ ጥርጣሬ ወይ መረጃ ሊኖራቸው እንደሚችል ነው፡፡ ታዲያ ይህ የኢንግላንድ የሚባለው ቫይረስ ፈትለክ ብሎ ወጥቶ በሌላው አለም ተገኝቷል፡፡

በኢንግላንዱ ስንገረም፣ የደቡብ አፍሪቃው ብቅ አለ፡፡ አሱም ቢሆን በፍጥነት መራባትና መሠራጨቱን ተክኖታል፡፡ ገና የዚህኛውን ቫይረስ ባህሪ መረዳት ሳንችል ከብራዚል ሌላ ብቅ አለ፡፡ ከአሁን በኋለ ሌሎች ዝርያዎች ተገኙ ቢባል መገረም የለባችሁም፡፡ ጥያቄው ምን አይነት ባህሪ ለውጥ አደረጉ ነው፡፡ የባህሪ ለውጥን እንደገና ስንመለከት፣ ተጨማረ ህመምና ሞትን ከማስከተል ተደምሮ፣ የተፈጥሮን ሆነ፣ በክትባት የሚመጣውን መከላከያ ማምለጥ ይችል ይሆን የሚል ሌላ አሳሳቢ ጥያቄ አለ፡፡ የኢንግላንዱን ቫይረስ፣ ቀደም ብሎ የወጣው የፋይዘር ክትባት ይሸፍነዋል በማለት የካምፓኒው ሰዎች በተዘዋዋሪ መንገድ የተጠናውን ጥናት አካፍለዋል፡፡ ሌላው ባልንጀራ የሆነው የሞደርና ክትባትም ቢሆን የኢንግላንዱን ቫይረስ ይሸፍናል ተብሎ በመረጋጋት ላይ ነበርን፡፡

ሆኖም፣ የደቡብ አፍሪካው ቫይረስስ? ሲባል፣ ለተወሰነ ጊዜ ዝም ጭጭ ሆነ፣ በተስፋ አንዳንዶቹ ክትባቱ ሊሠራ ይችላል በማለት ይናገሩ ነበር፡፡ እሱም ለማረጋጋት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ግን ያለ መረጃ፣ ያለ ጥናት ማንም ደፍሮ ፈርጠም ያለ አረፍተ ነገር መናገር አይችልም፡፡ ውሎ አደሮ፣ አሁን ባለንበት ጊዜ፣ ክትባቱ ሊሰራ ይችላል ግን በሌሎቹ ቫይረሶች ከሚሰራበት አቅም ባነሰ ነው አሉ፡፡

አስተውሉ እንግዲህ፡፡ እንደምንም ተብሎ አብዛኛው ሰው ክትባት አግኝቶ በወቅቱ የሚሠራጨውን ቫይረስ መግታት ቢቻልም፣ ይህ አዲስ ዝርያ የሆነው ቫይረስ ከክትባቱ ኢላማ ወጣ ያለ ወይም መታወቂያውን የቀየረ ቫይረስ ይዞ ብቅ ቢል፣ ክትባቱ የፈጠረው መከላከያ ሰላማያውቀው እንደገና ችግር ላይ ልንወድቅ ነው፡፡ ያም ሆኖ እነዚህ የክትባት መሥሪያ ዘዴዎች የአዲሱን ዝርያ ቫይረስ ፕሮቲን የሚያጠቃ ክትባት መሥራት ይችላሉ፡፡ ግን፣ አይታችሁ ከሆነ ክትባቱ መሠራት ብቻ ሳይሆን የሰዎች ክንድ ላይ ማረፍ አለበት፡፡ ያን ለማድረግ ደግሞ የማምረትና የማሠራጨት አቅሙ እንደምታዩት አስቸጋሪ ነው፡፡ የብራዚሉ ቫይረስም ቢሆን የደቡበ አፍሪቃው ቫይረስ አይነት ባህሪ አለው ተብሎ ተፈርቷል፡፡

ከኋላ የመጣ አይን አወጣ እንደሚባለው፡፡ ወደ ኋላ የሚከሰቱ ቫይረሶች የግድ በሥርጭት ሀይለኛ መሆን አለባቸው፡፡ ለመኖር ከፈለጉ እሱኑ ነው የሚያደርጉት፡፡ ማለትም የባሰ እንጂ የተሻለ አይመጣም፡፡ የኢንግላንዱ ቫይረስ የማሳመምና የመግደል ሀይሉ በ30 ፐርስንት ቢጨምርም፣ በንፅፅር ሲታይ በጣም ወደ ከፋ ደረጃ አልሄደም፡፡

በአለማችን በዚህ ቫይረስና በሽታ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንደየአካባቢው የተለያየ ነው፡፡ አንዱ መላ ምት፣ በአካባቢው የሚሠራጨው ወይም እየተዛመተ የሚገኘው ቫይረስ ገራም ሰለሆነ ይሆን ይባላል፡፡ የአካባቢ አየር ልዩነትን ከሂሳብ እናውጣው፡፡ እንዳየነው ከሆነ፣ በረሃና ደጋ ሳይል በተገኘው ቦታ እየተሠራጨ ነው፡፡ ሌላው መላ ምት ደግሞ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ትንሽ በተፈጥሮ መከላከያ አቅም ሰላላቸው ይሆን የሚል ነው፡፡ እሱንም ቢሆን በጥናት የተደገፈ መረጃ እሰከምናገኝ መላ ምት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ስናተኩር፣ ቫይረሱ እየተሠራጨ ለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም፡፡ ሌላው ቢቀር በኮቪድ በጠና ታመው ወደ ህክምና ጣቢያዎች የሚዘልቁ ሰዎች ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን በጣም አሳሳቢና አደገኛ ደረጃ መድረሱ ግልፅ ነው፡፡ ካላመናችሁ ወደ ኢትዮጵያ ስልክ ስትደውሉ የሚሰማውን መልክት አዳምጡ፡፡ አሁን ባንድ በኩልም ሰውን እያዘናጋ ያለው፣ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በውል አለመታወቁ ነው፡፡ በኮቪድ የሚሞቱ ማለት ነው፡፡ ሆኖም ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ይመስላል፡፡

አንግዲህ የትኛው ቫይረስ ነው ሀላፊነቱን የወሰደው ለሚለው ጥያቄ አስካሁን መልስ የለም፡፡ የማውቀው ጥናት የለም፣ ወደፊት ግን እንደሚጠና ፕሮግራሞች እንሚዘረጉ ሰምቻለሁ፡፡ የሀገራችን ሰው፣ በቀላሉ ያዝ ያደረገውን ይህን ቫይረስ በንቀት አይን ያየው ይመስላል፡፡ የመከላከያ መንገዶች አይከበሩም፡፡ ማስክ ነውር ይመስላል፡፡ ለዛውም ባለሥልጣኖቹም ቢሆን አሁን ትንሽ ሻል አሉ እንጂ ማሰክ ሳያደርጉ በአደባባይ ይታያሉ፡፡ ማስክ የማይወዱት የአሜሪካው መሪ በምርጫ ከቤተመንግሥት መውጣታቸውንና፣ ሳይንስና ማስክ የሚያከብሩ መሪዎች መተካታቸውን አላስተዋሉም መሰለኝ፡፡ ከዚህ ቫይረስ ጋር ድብብቆሽ መጫወት ትርፉ ሀዘን ነው፡፡ በካሊፎርንያ በየስድስት ደቂቃው በኮቪድ ምክንያት አንድ ሰው በሚሞትበት፣ በጠቅላላው በአሜሪካ በየሀያ ስድስት ደቂቃዎች አንድ ሰው የሚሞትበት ጊዜ ደርሰናል፡፡ ስንት ሰው ቢሞት ነው ሰው የሚደነግጠው? ጥንቃቄ የሚያደርገው ብሎ መጠየቅም አግባብ ነው፡፡

እንግዲህ፣ ተመስገን እንበልና ኢትዮጵያ በሞት ሲታይ የከፋ ደረጃ አልታየም፣ ቫይረሱም ገራም ነው ብሎ ለሚዝናኑ ሰዎች የምመክረው ነገር ቢኖር፣ አዳዲስ ቫይረሶች ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ከሆነ አደጋው ሊጨምር ይችላል፡፡ ሰለዚህ አንበሳን ለማዳ አድርጌያለሁ ብሎ ከጫካ አንበሳ ጋራ የወዳጅነት ቅርርብ የሚያደርግ አይኖርም፡፡ እናም አዲስ የሚመጡ ቫይረሶችን ባህሪ ስለማናውቅ አዲስ ቫይረሶች እንዳይፈጠሩ መታገል ነው፡፡ ያ ደግሞ ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ ማስክ በአግባቡ ማድረግ፣ ርቀት መጠበቅ፣ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸውን ቦታዎች ለጊዜው መተውና፣ እጅን በውሀ አለዚያም በአልኮል ማፅዳት ነው፡፡

በሰዎች ስብስብ አማካኝነት የሚተዳደሩ ሰዎች፣ ለጊዜው ሌላ መፈለግ ነው ያለባቸው፡፡ በባዶ ስታዲዮም እግር ኳስ ጨዋታ መካሄዱን እየለመድነው አይደለም ወይ? እነሱ ሲጫወቱ መዘንጋት የሌለብን፣ ማስክ የማያደርጉት በየጊዜው ለኮቪድ ምርመራ ሰለሚያደርጉ ነው፡፡ በዚያ ሰሞን ግብፃዊው ታዋቂ ተጫዋች ኮቪድ ተገኝቶበት አገሩን ወክሎ ለአፍሪቃ ማጣሪያ ግጥሚያ ላይ አልተሰለፈም፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የሪያል ማድሪዱ አሠልጣኝ ፈረንሳዊው ዚነዲን ኮቪድ ተገኝቶበት ወደ ስታዲዮም ብቅ አላለም፡፡ ግብፃዊው በኮቪድ የተያዘው ሠርግ ቤት ሄዶ መሆኑን ልብ በሉ፡፡ ለማንኛውም ባለፈው ፅሁፍ የኤች አይቪ ዝርያዎችን እንዳሳየኋችሁ ሁሉ፣ በዚህ ምስል የምታዩት ደግሞ የኮሮና ዝርያዎች ናቸው፡፡

መልካም ንባብ

ሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic