​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Health and History

Community health 

education in Amharic 

ኮቪድ-19 በግብረ ሥጋ ይተላለፋል…

 ከዚህ ቀደም በተለየዩ ቃለ መጠይቆች፣ ኮቪድ-19 የሚያሰከትለው ቫይረስ ሳርስ ኮሮና ቁ 2 (ለምን ሳኮ2 አንለውም ከአሁን በኋላ) ከሽንት በሰተቀር በሰውነት ፈሳሾች በሁሉም ይገኛል ብዬ ነበር፡፡ አሁን ግን ጥናቶች የሚያሳዩት በሽንትም እንደሚገኝ ነው፡፡

ዋናው ጥያቄ በዘር ፈሳሽ (semen) ውስጥስ ይገኛል ወይ? ከተገኘስ ምን ማለት ነው? ሌላ መተላለፊያ መንገድ መታወቁ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች በአዕምሯችን እንደሚላለሱ ርግጠኛ ነኝ፡፡ ለዚህም ቢሆን ጥናቶች የሚጠቁሙት ነገር አለ፡፡ በሜይ 7 ዕትም፣ የአሜሪካው JAMA የሚባል መፅሄት ያወጣው ነገር መልስን እንድናስብ አድርጎናል፡፡

ሳኮ2፣ በዘር ፈሳሽ ሰለመገኘቱ ከመግለፄ በፊት፣ ይህ ቫይረስ ወደ ሰውነት ውስጥ እንዴት እንደሚገባ በመጠኑ ልግለፅላችሁ፡፡ ከዛ በኋላ አብረን እንፈርዳለን፡፡

ከዚህ ቀደም እንደተገለፀው ሳኮ2፣ ሰውነትን በሚወርበት ጊዜ የሚመርጣቸው ሴሎች አሉ፡፡ አነዚህ ሴሎች፣ በላያቸው ላይ ACE2 (Angiotensin Converting Enzyme 2)  የተባለ ሞሎኪል አለባቸው፡፡ ይህን ነገር ቫይረሱ እንደመግቢያ በር ይጠቀምበታል፡፡ በቅርብ ጊዜ የወጡ ጥናቶች የሚገልፁት ነገር ቢኖር፣ ሳኮ2፣ ከሳርስ ኮሮና በበለጠ ከሰው ወደ ሰው መሻገር ችሎታው ምክንያቶች አንዱ፣ ሳኮ2 ከዚህ ACE2 ከተባለው ሞሎኪል ጋር፣ ከዛኛው ሳርስ ኮሮና ቫይረስ ከአስር እሰከ ሀያ ዕጥፍ በሆነ መጠን የመለጠፍ ባህሪ ስላለው ነው፡፡ ማለትም በፍጥነትና በቀላሉ ከዚህ ሞሎኪል ጋር መለጠፍ ከቻለ፣ ወደ ሰውነት ውስጥ ለመግባት በጣም ቀላል ይሆንለታል ማለት ነው፡፡

አስካሁን እንደሚታወቀው፣ የመተንፈሻ አካላት፣ ሳምባን ጨምሮ ሴሎቻቸው ACE2  የተባለውን ሞሎኪል በላያቸው ላይ ያንፀባርቃሉ፡፡ የነዚህ አይነት ክፍሎች ትክክለኛ አጠራር Receptors ነው፡፡ በአማርኛ፣ ተቀባይ ወይም መግቢያ ሊባሉ ይችላል፡፡ መግቢያ ሳይመች አይቀርም፡፡ ወደ ሴሎች ውስጥ የሚዘልቅ ማናቸውም ነገር፣ መድሐኒቶችንም ጨምሮ ለየራሱ የእንደዚህ አይነት የተለዩ መግቢያዎች አሉት፡፡ ኤች አይ ቪን ብትውሰዱ ወደ ሴሎች ውስጥ የሚገባበት የተለየ መግቢያ አለው፡፡ ከመተንፈሻ አካለት ውጭ፣ ACE2 የተባለውን መግቢያ በብዛት የያዙ ሴሎች የሚገኙት በጨጓራና በእንጀት ነው፡፡ አይገርምም፡፡ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም ቢሆን ይህ ACE2 የተባለ መግቢያ አላቸው፡፡

 ወደ ዘር ፈሳሽ ውስጥ ወደ ተኘበት ሁኔታ ልመልሳችሁ፡፡ ጥናቱ የተጠናው በቻይና ሲሆን፣ ከጃንዋሪ 26 እሰከ ፌብሩዋሪ 16 ባለው ጊዜ ውስጥ በኮቪድ-19 መያዛቸው በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ዕድሜያቸው ከአስራ አምስትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች፣ በጥናቱ እንዲገቡ ከተደረጉ በኋላ፣ የዘር ፈሳሽ አንዲሠጡ ተደረገ፡፡ ከጠቅላላው ለጥናቱ ይሆናሉ ከተባሉት ሃምሳ ሰዎች፣ አስራ ሁለቱ በተለያዩ ምክንያቶች የዘር ፈሳሽ መሥጠት አልቻሉም፡፡ ለጥናቱ የቀሩት 38 ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡

አነዚህ የዘር ፈሳሽ የሰጡት 38 ሰዎች መሀከል፣ 23 (60.5%) ከበሽታው ያገገሙ ነበሩ፡፡ አስራ አምስት የሚሆኑት ደግሞ በበሸታው በትኩሱ እንደተያዙ ነበር፡፡ የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው፣ በስድስት በሽተኞች ላይ ከተወሰደው የዘር ፈሳሻቸው ውስጥ ቫይረሱ መገኘቱን ነው፡፡ ከስድስት ውስጥ አራቱ በበሽታው በትኩሱ ታመው ከነበሩት ሲሆን፣ ሁለቱ ደግሞ ከበሽታው ካገገሙት መሀከል ነበር፡፡ ካገገሙት መሀል መገኘቱ ጉዳዩን ትኩረት ያሠጠዋል፡፡

እንግዲህ በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች ቁጥር አነስተኛም በመሆኑ፣ በዘር ፈሳሽ ውስጥ የተገኘው ቫይረስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ፣ በምን ያህል መጠን እንደሚወጣም ማውቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰፋ ያለ ጥናት ቢያስፈልግም፣ ሁለት ነገሮች ለመጠቆም ያህል፡፡ ባገገሙ ሰዎች ላይ ዘግይቶ መገኘቱ አንድ ትኩረት የሚሠጠው ነገር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሌላ ጥናት እንደታየው፣ ሰዎች አገግመው በመተንፈሻ አካላቶቻቸው ውስጥ ያለው ቫይረስ የለም ከተባለ በኋላ በአይነ ምድር በኩል ቫይረሱ ሳይጠራ ቀርቶ ዘግየት ብሎ መገኘቱ ይታወቃል፡፡

ሁለተኛው ነጥብ፣ በዘር ፈሳሽ ውስጥ ከተገኘ፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ይተላለፋል ወይ ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ እንግዲህ ከመግቢያው ላይ ሆን ብዬ የቫይረሱን ወደ ሰውነት መግቢያ የገለፅኩት ከዚህኛው ነጥብ ጋር ለማዛመድ ነው፡፡ ጥያቄው አንግዲህ ምን አይነት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ነው ወደሚለውም ይወሰድናል፡፡ ከአፍ ጀምሮ በመተንፈሻ አካላት ላይ ቫይረሱን ወደ ሴሎች ወደ ወስጥ የሚያዘልቅ መግቢያ ACE2 በብዛት የሚገኝ ከሆነ፣ ለየት ባለ ሁኔታ ከሚደረጉ እንደ (Oral sex) የሚባለው ድርጊቶች አያጋልጡም ወይ? በድሮፕሌት በኩል ይምጣ፣ በተነካካ እጅ በኩል ይምጣ, በዘር ፈሳሽ በኩል ይምጣ, ቫይረሱ መተንፈሻ አካላት አካባቢ ካረፈ መግባቱ አይቀርም፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ይህ ACE2 የተባለ መግቢያ በጨጓራ፣ በአንጀትና በሠገራ መውጫ (rectum) ሴሎች ላይ በብዛት ይገኛል፡፡ እንግዲህ ይህ አካባቢም ወደ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ጎራ ከገባ ስንብቷል፡፡ ከዚህ በኋላ፣ አንድ ሲደመር አንድ፣ ሁለት ነው ማለቱ የናንተ ሥራ ይሆናል፡፡

ይህ ሁኔታ በስፋት ተጠንቶ ተጨማሪ መረጃ እሰከሚመጣ፣ ለመጠንቀቅ ሲባል፣ ኮንዶም መጠቀም አስፈላጊ ነው ይላሉ አጥኝዎቹ በማጠቃለያቸው፡፡ እኔም ይህን ሀሳብ እጋራዋለሁ፡፡ ምንም አንኳን የኮሮና ቤተሰቦች በዚህ መንገድ ይተላለፋሉ ወይም ተላልፈዋል የሚል መረጃ አስካሁን ባይኖርም፡፡

አሁን ሙግቱ ያለው፣ አንደኛ ብዙ ቫይረሶች በወንዶቸ የዘር ፈሳሽ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ በግብረሥጋ ግንኙነት ይተላለፋል ተብሎ መመሪያ የተጻፈበት ቫይረስ አንድ ሰሞን ብቅ ብሎ የነበረው ዚካ የሚባለው ቫይረስ ነው፡፡ በኢቦላ ቫይረስ የተያዙና የተረፉ ሰዎችም ቫየረሱ በዘር ፈሳሻቸው ውስጥ ካገገሙ በኋላ ለረዥም ጊዜ መገኘቱ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ቫይረሱ መገኘቱ ብቻ በቂ አይደለም የሚሉ ባለሙያተኞችም አሉ፡፡ በፈሳሹ ወስጥ የተገኘውን ቫይረስ በላቦራቶሪ ማደግ መቻሉን (ካልቸር) ማረጋገጥ ከተቻለ በርግጥ መውረርና በሽታ ማስከተል ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ በላቦራቶሪ ቫይረሶችን ማደግ መቻላቸውን ማወቅ እየቀረ የመጣ ዘዴ ነው፡፡ አንደኛ አደጋ አለው፣ ሁለተኛ ጊዜም ይወስዳል፡፡

ለማንኛውም ያገሬ ሰው “በኋላ ከማዘን…. “ የሚለው አባባል አለው፡፡ መጠንቀቅን የሚያክል ነገር የለም፡፡

JAMA Netw Open. 2020;3(5):e208292. doi:10.1001/jamanetworkopen.2020.8292
Gastroenterology 2020;158:1831–1833