ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

አስፕሪንና ኮቪድ-19
 አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ አወጣ

መቼም ኮሮና ወይም ኮቪድ ከተከሰተ ወዲህ፣ እርስ በርስ አትነጋጋሩ የሚል የባቢሎን ግንባታ አይነት ርግማን ሳይወርድብን አልቀረም፡፡

በመሠረቱ፣ ኮሮና ቫይረስ ቁ 2 ነው አዲሱ ነገር፣ የሚያሰከትለው በሸታም እንግዳ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ያ ግን ከሙያ ውጭ ለሆኑ ሰዎች ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሳርስ የሚባል በሽታ ለተወሰነ ጊዜ አለምን ሲያሸብር፣ እንዳሁኑ ፖለቲከኛውም ሆነ፣ አንድ ቀን አንኳን በእጁ በሽተኛ ነክቶ የማያውቀው ምሁር ሃሳብ ሲሠጥ አላየንም፡፡

ይሕ ግን የተለየ ነው፡፡ ያላዋቂው የሚሰነዝረው ሀሳብ ሌላ አላዋቂ ላይ ሲደርስ ጉዳት እየታየ ነው፡፡ ከታወቁ ጆርናሎች ወይም የጤና መፅሔቶች ተነበው የማያልቁ፣ ሰለዚህ ቫይረስና በሽታ የሚወጡ ፅሁፎችን ሳያነቡ፣ ለሚፅፉትም ነገር መረጃቸውን ሳይጠቅሱ፣ አንዳንድ ሰዎች ለአንባቢ የሚያቀርቧቸውን ፅሁፎች መመልከት እየከበደ መጥቷል፡፡ እንደ ፖለቲካው፣ የራሳቸው ጉዳይ ነው ብሎ ማለፍ የሚቻልም አይደለም፡፡

ያላዋቂ ሀሳብ ሲሰጥ የደረሰውን ጉዳት እናስታውስ፤

ክሎሮኩዊን ያድናል ተብሎ ሲነገር የሰሙ ባልና ሚስት፣ በውሥጡ ክሎሮኩዊን ፎስፌት ያለበት የአሳ ገንዳ ማፅጃ ኬሚካል  አይተው፣ ከጭማቂ ጋር ደባልቀው በመጠጣት፣ ባልየው በግማሽ ሰአት ወስጥ ሲሞት፣ ሚስትየዋ ለወሬ ነጋሪ ተርፋለች፡፡

ክሎሮኩዊን ወይም በተሻለ መንገድ የተሠራው ሀይድሮክሲ ክሎሮኩዊን፣ ለኮቪድ ህክምና አይተሰጠ ነው፡፡ ውጤቱ አጥጋቢ ቢሆን ኖሮ፣ መደበኛ መድሀኒት ይሆን ነበር፡፡ ግን ገና ነው፡፡ አማራጭ በማጣት ነው የሚሰጠው፡፡ እንደዛም ሆኖ የልብ ትርታ መዛባት ሰለሚያሰከትል፣ አሁን፣ ክሎሮኩዊን ዚትሮማከስ ከተባለ ፀረ-ህዋስ መድሀኒት ጋር እንዳይሠጥ ሆኗል፡፡ ማስታወስ ያለብን እነዚህ መድሀኒቶች በጠና ታመው ሆስፒታል ለገቡ ሰዎች የሚሠጡ ናቸው እንጂ አንደመከላከያነት ለመጠቀም ገና ጥናት ላይ ነው፡፡ ገና ያልታመመ ሰው ይህንን ለምን እንደሚወስድ ሁላችንም መጠየቅ የሚገባን ነገር ነው፡፡

ሰሞኑን ደግሞ፣ ቫይረሱን በዕቃዎች ላይ ለማፅዳት ያገለግላሉ ከተባሉት ኬሚካሎች አንዱ አልኮል ነው፡፡ ለማፅጃ ሲሆን ሰባ ፐርሰንት ይሆናል፡፡ ይህንን የሰማ አንድ የአሜሪካ ዜጋ፣ ሰባ ፐረስንት አልኮል በመጠጣት ቫይረሱን ለማጥፋት ሞከረ፡፡ ገና አልተያዘም፡፡ ነገር ግን ይህ ሙከራው ሆስፒታል በራፍ ነው ያደረሰው፣ በፀና ታሞ ድንገተኛ ክፍል ነበር፡፡ አግዚአብሔር ይርዳው፡፡

በነገራችን ላይ ወደ አፍ የምናሰገባው ነገር ቀጥታ ወደ ደም እንደማይሻገር ማወቅም ተገቢ ነው፡፡ አልኮሉ እንደሌሎች ኬሚካሎች ሁሉ በጉበት በኩል አልፎ ተጣርቶ ነው ወደ ሰውነት የሚደርሰው፡፡ ችግሩ፣ እግረ መንገዱን ጉበቱን ያቃጥላል፡፡ ሰውነት አንደ መኪና አይደለም፡፡ በፈለግን ሰአት በብዙ ውሀ የምናጥበው ወይም በሌላ መድሀኒትም ሆነ ኮምፓውንድ የምናጠራው ነገር አይደለም፡፡ ረቂቅ የሥራ ውጤት ነው፡፡ ከልክ በላይ መቀበል አይችልም፡፡ ውሀም ቢሆን፡፡ እዚህ ላይ ቫይታሚኖችን እንደልባቸው የሚቅሙ፣ ከመጠን በላይ ከወሰዱ ደግሞ ጥቅም የሚያገኙ የሚመስላቸው ብዙ እንደሆኑ አይካድም፡፡

ሰለ ቫይታሚኖች አንድ ልበላችሁ፡፡ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ በውሀ ወይም በቅባት የሚሟሙ እንበል፡፡ በውሃ የሚሟሙትን ከመጠን በላይ ብንወስድ፣ ሰውነት የተረፈውን ያስወጣዋል፡፡ ሰው እንደልቡ ከመጠን በላይ ለሚወስደው ቫይታሚን ሰውነት መካዝን የለውም፡፡

በቅባት የሚሟሙትን ቫይታሚኖች ከመጠን በላይ መውሰድ ችግር ይፈጥራል፡፡ በቀላሉ ከሰውነት ማስወጣት ሰለማይቻል፣ ትርፍ ቫይታሚኑ ቶክሲሲቲ ማለትም በሰውነት ላይ ጉዳት ያደርሳል፡፡ የነዚህ ቫይታሚን ወገኖች፡ ቫይታሚን ኤ፣ ዲ፣ ኢ ይገኙበታል፡፡

ሰለዚህ ከመጠን በላይ በመወስድ ጠቀሚታ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ጉዳት አለው፡፡ በርግጥ በፍሪጅ የከረረ ምግብ በሚበላበት አገር፣ ተመጣጣኝ ምግም በማይገኝበት ቦታ፣ በየቀኑ ለሰውነት የሚያሰፈልጉ ቫይታሚንና ንጥረ ነገሮች ጉደለት ይኖራል፡፡ ያንንም በቀን አንድ ጊዜ ብቻ በሚወሰዱ በልክ የተሠሩ ቫይታሚንና ንጥረ ነገሮች መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ በየቫይታሚን መያዣዎች ጀርባ፣ በጥቃቅን የተፀፉትን ብታነቡ፣ Daily requirement የሚል ነገር ታያላችሁ፡፡ ሰለዚህ ሰውነት በቀን ለቀኑ የሚያሰፈልገውን መጠን መወስድ ነው፡፡ እንደ ግመል ሻኛ፣ ከመጠን በላይ የምንወስደውን ነገር ማካማቻ የውስጥ ሰውነት የለውም፡፡

ሰለ ኮቪድ ለመግለፅ፣ ያልታመመ ወይም ያልተያዘ ሰው አለ፤ የተጋለጠ ቫይረሱ ያልያዘው ሰው አለ፤ የተያዘ ምንም የበሽታ ምልክት የማሳይ ሰው አለ፤ የተያዘ ግን ቀለል ያለ ህመም ይዞት የሚድን ሰው አለ (ወደ ሰማንያ ፐረስንቱ በዚህ ምድብ ውስጥ ነው ያለው)፤ ከዚያ ደግሞ ተይዞ በሽታው የሚጠናበት አለ (በጥናት የታየው ወደ 14 ፐረስንት)፣ ተይዞ በሽታው መጥናት ብቻ ሳይሆን ለህይወት አስጊና ለሕይወት ማለፍ ደረጃ የሚደርስ አለ (በጥናት ወደ 6 ፐርሰንት)

አሁን በሽታው የጠናባቸው ሰዎች ላይ፣ ኮቪድ የሚገለጥባቸው ስሜትና ምልክቶች አሉ፡፡

ይህ ቫይረስ፣ እንዳየነው ከሆነ፣ ከአንጎል ጀምሮ፣ የአንጀትና ጨጓራን በመውረር ይታወቃል፡፡ ሳምባ ዋና መግቢያና መውጫው ነው፡፡ ትልቁ ችግር የመጣው፡፡ ይህ ቫይረስ ወደ ሰውነት በሚዘልቅበት ጊዜ፣ ሰውነት ሌላ ጊዜ ወራሪ ቫይረስ ሲመጣ አንደሚያደርገው ሁሉ፣ ቫይረሱን ለማጥቃት የተለያዩ ሴሎችን ይጠቀማል ከነዚህ አጥቂ ሴሎች የሚለቀቁ የተለያዩ ኬሚካሎችን ይጠቀማል፡፡ እንግዲህ የዚህ የሰውነት መካለክል፣ ከመካለክል አልፎ ቁጣ በመሰለ መንገድ ከመጠን በላይ የሚለቃቸው ኬሚካሎች ናቸው ችግር የፈጠሩት፡፡ ባጠቃላይ የነዚህ ኬሚካሎች መለቀቅ ኢንፍላሜሽን ይባላል፡፡ ይህ ሁኔታ ሲከፋ፣ ራሱን የሰውነት ክፍሎች ማጥቃት ይጀምራል፡፡ በዚህ መልክ ሳንባ ራሱ ጥቃት ይደርስበታል፣ ጉበት፣ ኩላሊትም አንዲሁ፡፡ በዚህ በሚፈጠረው ቅጥ ያጣ የሰውነት ቁጣ ምክንያት፣ ከዚህ በፊት በስርእት በቁጥጥር የሚካሄዱ የሰውነት ሥራዎች ይዛባሉ፡፡ አንዱ የሚታየው ነገር፣ የደም መርጋት ነው፡፡ የደም መርጋት ደግሞ፣ እንደሚከሰትበት የሰውነት ክፍል አደጋው ከፍ ያለ ነው፡፡ ኮቪድ ኖረም አልኖርም፣ የረጋ ደም ተቋጥሮ ወደ ሳምባ በሚሻገርበት ጊዜ፣ ለሳምባ ክፍሎች ደም የሚያደርሱ የደም ሥሮችን ሲዘጋ፣ ሳምባ ሥራውን ያቆማል፡፡ እንደተዘጋው የደም ሥር ትልቅነት የህይወት ህልፈት ያስከትላል፡፡ ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

 ታዲያ ማንኛውም አይነት ከፍተኛ ጥቃቅ ሳምባ ላይ በሚደርስበት ጊዜ፣ ሳምባ ሙሉ በሙሉ መሥራት ካልቻል፣ ሰውነት አኮስሰጅን አያገኝም፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ በአፍና ባፍንጫ በኩል ኦክስጅን ሲሠጥ የምታዩት፡፡ ሳምባ በጣም ከተጎዳና በሽተኛው በራሱ መተንፈስ ካቃታው፣ አርቴፊሻል መተንፈሻ (Ventilator) ላይ ይደረጋል፡፡ ቪንቴሌተሩ፣ ሰውየወን በመተካት አየር ማስወጣትና ማስገባት ነው ሥራው፡፡ ቪንቲሌተር መድሐኒት አይደለም፣ ቪንቴሌተር መጠቀም ማለት ብቻውን ማዳን ማለት አይደለም፡፡ ሰውየው ካለበት በሸታ አገግሞ፣ ሰውነቱ ጠንከር ብሎ በራሱ በቂ መተንፈስና በቂ ኦክስጅን ማስወጣትና ማስገባት አስኪጀምር የተውሶ ሳምባ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለኮቪድ ብቻ አይደለም የሚደረገው፡፡ በመኪና አደጋ ራሱን ለሳተ ሰው፣ አንጎል ወደ ሥራው እሰኪመለስ ድረስ በተውሶ ሳምባ ይቆያል፡፡ አስብን የምንተነፍስ አታድርጉት፣ በፕሮገራም ነው፡፡ አስብን የምንተነፍስ ቢሆን፣ ስንተኛ በዛው ነበር የምንሄደው፡፡ በድሮ የግሪክ አፈታሪክ መሰለኝ፣ አንድ ርግማን ነበር፡፡ ርግማኑም ትንፋሹን አስቦ እንዲተነፍስ የሚል ነበር፡፡ የተረገመው ሰው መተኛት አይቸልም፡፡

በኮቪድ ጊዜ ቪንቲለተር የተፈለገው ዋናው ነገር፣ የበሽታው ዋና መግደያ መንገድ ትንፋሸ በማሣጣት በመሆኑ ነው፡፡

አንግዲህ ከላይ ካስታወሳችሁ በጣም በቁጥራቸው አነስ ላሉት ለነዚህ ሰዎች፣ ኢንፍላሜሽን የሚባለው ነገር አደጋ ላይ የጣላቸው መሆኑ ስለሚታወቅ፣ የኢንፍላሜሽን ምልክት ናቸው የሚባሉና የደም መርጋት ምልክት የሚባሉ የተለያዩ ብዛት ያላቸው በደም የሚሠሩ ምርምራዎች ይደረጋሉ፡፡ ይህ ኢንፍላሜሽን ገና ከጥዋቱ የታወቀ ነገር ነው፡፡ በአብዛኛው ኢንፍላሜሸን (የሰውነት ቁጣን) ረገብ ለማድረግ፣ ሰቴሮይድ የሚባሉ የመድሐኒት ወገኖች መጠቀም ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ የቻይኖችን የህክምና ዘገባ ያነበበ ካለ፣ ይህንን በሚገባ መረዳት ይችላል፡፡

የተለያዩ የመድሐኒቶች አይነቶችም ይሠጣሉ፡፡ ከሚሰጡት የመድሐኒት ወገኖች ጥቂቶቹ፣ የሰውነት የመከላከያ አቅም ወይም ኢሙየኒቲ (Immunity) ለማለዘብ የሚሠጡ ናቸው፡፡ ደምበኛ ፍቱን የተባለ መድሐኒት እስከሚገኝ ብዙ የሚደረጉ ነገሮች አሉ፡፡ ይህን በባለሙያዎች በውል የሚታወቅን ነገር፣ አደባባይ ማውጣቱ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ ለብዙ ሰዎች በሚገባቸው መንገድ መግለፁ አስቸጋሪ ነው፡፡

ይህንን ቆንፀል አድረጎ አውጥቶ፣ በሙያው ላይ ያሉ ሰዎች የሚያደርጉትን አያውቁም አይነት አቀራረብ በጣም የሚገርም ሳይሆን የሚያሳዝንም ነው፡፡ አንድ ቀን ኢንተንሲቪስትና ሌሎች ሀኪሞች የሚያደርጉትን ኮንፈረንስ ገብተው ቢከታተሉ፣ ሀኪሞቹ በሥራቸው ላይ የሚያደርጉትን ነገር፣ የሚጥሩትን ነገር፣ የሚሄዱበትን ሳይንሳዊ አቀራረብ መመልከት ያስችል ነበር፡፡ በማያውቁት ነገር ጠበብት ለመምሰል መሞከርም ተገቢ አይደለም፡፡ ዝም ተብሎ ማለፍ ይቻላል፣ ነገር ግን፣ እነዚህን ሰዎች የሰሙ ወይም ፅሁፋቸውን ያነበቡ ሌሎች ሰዎች አደጋ ላይ እየወደቁና ሲወድቁም ሰለሚታይ የግድ መግለፅ አስፈላጊ ነው፡፡

 ኮቪድን ለመከላከል ተብሎ ስለሚፃፉ ነገሮች አስኪ አንድ እንበል፡፡ በሽታን ለመከላከል፣ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ በኩል፣ ወራሪ ባክቴሪያ ወይም ቫይረሱን የሚደመስስ እንቲ ቦዲ መፍጠር ነው፡፡ ሰው ሠራሽ ሲሆን ክትባት ይባላል፡፡ በተረፈ ሰው በበሽታው ተጠቅቶ ሲያገገም ለአንዳንድ በሽታዎች እንቲ ቦዲ ይፈጥርና ተመልሶ እንደማይያዝ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ሄፒታይትስ ኤ (የወፍ በሽታ)፣ ጉድፍ፣ ሄፓታይተስ ቢ፣ የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡

እንግዲህ ለኮቪድም ክትባቱ ጥናት ላይ ነው፡፡ የሚጠናው ኮምፓውንድ ከተገኘ ሰንብቷል፡፡ ታዲያ ይህ ኮምፓውንድ መስራትና አለመስራቱ በምን ይታወቃል? መጀመሪያ፣ እንደማናቸው የመድሐኒት ጥናቶች፣ ሰውነት ላይ ጉዳት አለማድረሱ ይጠናል፡፡ ያንን ካለፈ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ይሄዳል፡፡ ልብ በሉ በዚህኛው ደረጃ፣ ሰዎች በሁለት ወገን ይመደባሉ፡፡ ማለት ለጥናት የተመለመሉት፣ አንዱ ወገን ትክክለኛ ለክትባት የተዘጋጀውን ኮምፓውንድ እንዲወሰዱ ይደረጋል፡፡ ሌላኛው ወገን ደገም፣ ክትባት የሌለው ማስመሰያ መድሐኒት ይሠጣቸዋል፡፡ በነገራችና ላይ ሁለቱም ወገኖች ምን እንደተሠጣቸው አያውቁም፡፡ ክትባቱ ወይም ማስመሰያው፡፡ አሁን ሁለቱም ወገኖች አኩል በሆነ ደረጃ ለቫይረሱ ይጋለጣሉ፡፡ ክትትልም ይደረጋል፡፡ ይህ ሲሆን፣ በሚወጣው ውጤት ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ፣ ሁለቱም ወገኖች፣ በዕድሜ፣ በጾታና በሌሎችም ነገሮች አኩል በሆነ ደረጃ ነው የሚከፈሉት፡፡ እንግዲህ ክትትል እየተደረገ፣ በነገራችን ላይ፣ በደንበኛ ጥናት፣ መርማሪዎች ወይም አጥኝዎች የትኛው ወገን ክተባቱን፣ የትኛው ወገን ማስመሰያ እንደተሠጠው እንዳያውቁ ሊደረግ ይቻላል፡፡ ታዲያ በክትትሉ ወቅት፣ በቫይረሱ ሰው መያዝ ሲጀምር፣ ፋይሉ ይታይና ክትባቱን ወይስ ማስመሰያው መውሰዱ እንዲታወቅ ይደረጋል፡፡ በቁጥር በሰታቲሰቲክ በተደገፈ፣ ክትባቱን ያልወሰዱ ሰዎች ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች በበለጠ በቫይረሱ መያዛቸው ከታወቀ፣ ጥናቱ ከመሀል ተቋርጦ ክትባቱ ለሁሉም እንዲሠጥ ይደረጋል፡፡ እንግዲህ በዚህ መልክ ነው፣ ክትባቱ ያስጥላል የሚባለው፣፡፡

አሁን አንግዲህ ከነጭ ሽንኩርት ጀምሮ፣ ቃሪያ፣ አረቄ፣ ማር፣ ሎሚ፣ ይከላከላሉና ተመገቡ ሲባል፣ መከላከላቸው አንዴት ታወቀ ብሎ መጠየቅ ለምን ያስቸግራል፡፡ የሚያስጥሉ ቢሆን ዘጠኝ ሺ የአሜሪካ ሀኪምና ነርሶች ራሳቸውን ከኮቪድ ያስጥሉ ነበር፡፡ እኛ የጤና ባለሙያተኞች ሞኝ ሆነን መሆን አለበት፣ እንደዚህ የሚከላከል ነገር እያለ አደጋ ወዳለበት የህክምና ቦታ የምንሄደው፡፡ የሌሎቹስ መቼም፣ አረቄ ሰልፍ ውስጥ መግባቱ ነው የሚገርመው፡፡ አልኮል የመከላከያ አቅም እንደሚያደክም ካወቅን ሰንብተን፣ ተው በምንልበት ጊዜ የኮቢድ መከላከያ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ ይገርማል፡፡

ከመድሐኒቶች ወገን ደግሞ አሁን አስፒሪን ሰልፍ ውስጥ ገብቷል ብሎ እንድ ሰው አጫወተኝ፡፡ የመካሪው ሎጂክ፣ የኮቪድ ህሙማን በደም መርጋት ሰለሞቱ አስፒሪን ይረዳል ነው፡፡ በኮቪድ ከሞቱ ሰዎች ስንቱ ደም መርጋት እንደደረሰበትም የተገነዘቡም አይመስልም፡፡ እሺ ይሁን፣ የታመሙት ደም መርጋት ሲታይባቸው የሚሠጥ መድሀኒት አለ፡፡ እንግዲህ ገና በቫይረሱ ያልተያዙ ሰዎች፣ የታመሙ ሰዎች የሚወስዱትን አይነት መድሀኒት ለምንድን ነው የሚወስዱት ብሎ መጠየቅ ተገቢ አይሆንም ወይ፡፡ ወይስ ድንገት በቫይረሱ ብንያዝ የደም መርጋቱን ሰለሚካለክል እንወሰድና አንጠብቅ ነው፡፡ ከቪድ በደም መርጋት ብቻ አይደለም የሚገድለው፡፡ የሚገድለው ሰው ቁጥር በንፅፅር ከሌሎቹ ዘመዶቹ ቫይረሶች አነስ ያለ ቢመስልም፣ በፈለገው መንገድ ሰው እየጠለፈ ነው፡፡

ሌላው ነገር፣ እንዲያው፣ ላስተዋለ ሰው፣ ለስትሮክና ለሌላም ተብሎ አስፒሪን ይሠጣል፣ የሚወስዱም አሉ፣ እስኪ ሚሊግራሙን አስተውሉ (ከነስሙ ቤቢ አስፕሪን ነው የሚባለው) 81 ሚሊግራም ነው፡፡ ሀኪሞች ስስታም ሆነው ነው 81ሚሊግራም ብቻ የሚያዙት? አይደለም፡፡ አስፕሪን ከመጠን በላይ ከሆን፣ ራሱ ይገድላል፡፡ አንደኛው መንገድ የጨጓራ አልሰር መፍጠር፣ አልሰር ካለም በደም መፍሰስ ነው፡፡ አንግዲህ በተራ አነጋገር አስፒሪን ከህመም ማሰታገሻነት የተነሳበት ዋናው ምክንያት ይህ በደም ማቅጠን ምክንያት የሚያሰከትለውን ደም መፍሰስ በማስተዋል ነው፡፡  ማርና ቅቤውን እንደፈለጋችሁ፣ አስፒሪንን ግን ተውት፡፡ አሁን ሆስፒታል በተጨናነቀበት ዘመን፣ በጨጓራ አልሰርና በደም መፍሰስ ሁኔታ መገኘት ምን እንደሚያስከትል ማወቅ ጥሩ ነው፡፡

እንዳው በነገራችን ላይ፣ ኮቪድ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተሠራጨም (ባደረገልን) እየተባለ፣ ለቫይረሱ መቼ ተጋልጦ ነው፣ ይህ ምግብ ያ መድሐኒት ያስጥላል ተብሎ የሚነገረው፡፡ ገና ጦር ግንባር ሳይደርሱ፣ ሳይዋጉ አሸናፊ መሆን ማለት እኮ ነው፡፡

መደምደሚያ፡፡ እያንዳንዳችን፣ እንደ አጅ አሻራችን፣ በመከላከያ አቅማችን የተለያየን ነን፡፡ ይህ ደግሞ በሌሎች በሸታዎች የታየም ነገር ነው፡፡ ለማንኛውም የመከላከያ አቅምን ከሚያድክሙ ነገሮች አንዱ ተመጣጣኝ ምግብ በበቂ መጠን አለመመገብ ነው፤ የሰውነተ እንቅስቃሴ አለማዘውተርም ሌለው ነው፡፡ ከዚያ ውጭ አልኮል የመከላከያ አቅም ያደክማል፤ የአእምሮ ጭንቀትም የመከላከያ አቅም ያደክማል፣ ሰውነት ከሚጎዱ ነገሮች፣ ሲጋራና ዕፅ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ መወፈር፣ ሌሎች ተደራቢ በሽታዎች መኖርም ችግር ያስከትላሉ፡፡ አንድን ነገር ከመጠን በላይ በትርፍ መመገብ ጉዳት እንጂ ትርፍ የለውም፡፡

ይልቁን፣ ተመጣጠኝ ምግብ፣ በቀን አንድ የሚወሰድ ቫይታሚንና ሜኒራሎች፡፡ አሱም እኮ የምንመገበው ምግብ በቂ አይኖረውም ተብሎ ነው፡፡ ወደኋላ ብንመለስ፣ ቫይታሚን የሚባል አንክብል አልነበረም፡፡ የሰውነት እንቅስቃሴ፣ የአእምሮ ጤንነት ላይ አተኩረን፣ ሌሎች መደረግ የሚገባቸው መከላከያ ማድረግ ነው፡፡ ሌላ ሚስጥር እኮ የለውም፤ ይህ ቀን እሰከሚያልፍ ከሰው ራቁ ነው መልክቱ፡፡ ቫይረሱን ሰው አይደለም እንዴ የሚያመላልሰው፡፡

መልካም ንባብ