Community health 

education in Amharic 

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Health and History

  • ኮቪድ-19 የተስፋ ጮራ


የሶሰተኛ ደረጃ የሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር ሁሉት (ሳኮ2) ክትባት በ30 ሺ ሰዎች ላይ በሀምሌ ሊጀመር ነው 

መረዳት አንደምንችለው፣ እንደዚህ አይነተኛ ሞገደኛ ቫይረሰ (ሳኮ2) ሥርጭትን መግታት የሚቻለው በክትባት ነው፡፡ ሳይንቲስቶቹ መራወጥ ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ፣ የጠፋ ገንዘብ ይጥፋ ተብሎ በጀት ተመድቦ እይተሠራ ነው፡፡

ክትባት ለመስራት ከመሰረቱ የተለያዩ የጥናት ደረጃዎች ተሸግሮ መምጣት አለበት፡፡ እነዚህ ደረጃዎች በእንግሊዘኛው Phase 1, Phase 2, Phase3 ወዘተ. ይባላሉ፡፡ ክትባቱ የግድ በእያንዳንዶቹ ደረጃዎች አልፎ መሄድ አለበት፡፡ ለህዝብ አገልግሎት ለመቅረብ የመጨረሻውን Phase ማለፍ አለበት፡፡ ችግሩ ምንድንነው፣ ጊዜ ነው፡፡ የጥናቶቹን አይነት ከመግለፄ በፊት፣ ጥሩውን ዜና ላከፍላችሁ፡፡

በአሜሪካው (National Institute of Health) የተሠራ ክትባት አሁን በቅርቡ በጁላይ መጀመሪያ ላይ የ Phase 3 ጥናት ሊጀመር ነው፡፡ ጥናቱ በአሜሪካና በመላው አለም ባሉ ቦታዎች ነው፡፡ የሚገርመው ነገር፣ እኔም ብሆን የሥራ ቦታየ በዚህ ጥናት አንዲሳተፍ፣ ከሌላ ኩባንያ በኩል ጥሪ ደርሶኛል፡፡ ክትባቱ ለጥናት የሚቀርበው ባዮቴክ ሞደርና በሚባል ካምፓኒ ሲሆን፣ ለዚህ ጥናት 30 000 ሰዎች እንደሚሳተፉ ነው፡፡

በጣም አስፈላጊው ነገር፣ የጥናቱን ክትባት የሚወስዱ ሰዎች፣ የቫይረሱ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ ባለበት አካበቢ ቢኖሩ ነው የሚመረጠው፡፡ እና አጋጣሚው ጥሩ ነው ማለት ነው፡፡ ይሀ ደገሞ ወደ ጥናቱ ውጤት ቶሎ መድረስ ይቻላል፡፡ ሁለቱን የጥናት ደረጃ ተሻግሮ እዚህ መድረሱ በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡

ነገር ግን፣ ሁለት አቢይ ነገሮችን መነጋገር አለብን፡፡

አንደኛ፣ ከዚህ ቀድም እንደምናየው የኮሮና ቫይረሶች ለሰው ልጅ እንግዳ አይደሉም፡፡ ተራ ጉንፋን የሚያስይዙን አራቱ የኮሮና ቫይረሶች፣ በቀላል ህምመ ከሰው ጋር ይገላገላሉ፡፡ በነዚህ ተራ ጉንፋን በሚያስይዙ የኮሮና ቫይረሶች የተጋለጡ ሰዎች አገግመው ብዙም ሳይታመሙ ኑሯቸውን ይቀጥላሉ፡፡ የሚታመነው፣ ሰዎች ለነዚህ ቫይረሶች መከላከያ አንቲቦዲ እንደሚኖራቸው ነው፡፡ ችግር የሆነው፣ ይህ የተፈጥሮ መከላከያ አንቲቦዲ ረዥም ዕድሜ የለውም፣ በአብዛኛው ከስድስት ወራት አያልፍም፡፡ እናም፣ ይህ አዲሱ ቫይስም የኮሮና ዘር ሰለሆነ፣ ክትባቱ የሚሠራ ቢሆን፣ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አይታወቅም፡፡ በልባችሁ፣ ምነው በመጡና አፈር በበሉ ሳትሉ አትቀሩም፡፡ እኔም እስማማለሁ፡፡

ሁለተኛው ነገር፣ አሁንም ቢሆን ክትባቱ ይሠራ ይሆን መጠነኛም ባይሆን ፍራቻ አለ፡፡ ከሠራ ደግሞ ሥርጭት ላይ እንዲት ይሆናል የሚል ጥያቄም አለ፡፡ ባለሥልጣኖቹ የሚሉት፣ የከሰረ ገንዘብ ይክሰር ተብሎ ብዙ ወጭ ወይም ኢነቭስትሜንት ተደርጎበታል፡፡

ሁላችንም ቢሆን ይህንን ተስፋ የሚሠጥ ዜና በፀጋ ብንቀበለውም፣ በተስፋ ብንጠባበቅም፣ እስከዛ ድረስ ግን ይህንን የቫይረስ ሥርጭት ለመግታት መደረግ የሚገባውን ነገር አጥበቅን ተግባራዊ ማድረግና ሌሎችንም መምከር ተገቢ ነው፡፡

ይህንን የመከላከል ተግባር ባናደርግና፣ እንዲያው ክትባት ደርሶ ብዙ ቢረዳን፣ በቫይረሱ መክንያት አሁን መሞት የማይገባቸው ሰዎች ቢሞቱ ፀፀቱ የጋራ ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ተመሳሳይ የሶስተኛ ደረጃ ጥናት በሌላ አሰትራ ዜኔካ በሚባል ካምፕኒ ወይም የላይኛውን ጥናት ተከትሎ አለዚያም ጎን ለጎን ሊካሄድ እንደሚችል ተገልጧል፡፡ ሌላ ጥሩ ዜና ነው፡፡

ቀደም ብዬ ቃል እንደገባሁት የጥናት ደረጃዎችን ላካፍል፡፡ እነዚህ ደረጃዎች ለክትባት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች መድሐኒቶች በሙሉ ነው፡፡

Phase I፡ የዚህ ጥናት አላማው፣ ለአግልግሎት ሊውል ያቀደው ኮምፓውንድ ጉዳት የማያደርስ መሆነና፣ መወሰድ የሚቻለውን መጠን ለማወቅ ነው፡፡ ጥናቱ የሚካሄደው ከ20 እስከ 80 በሚሆኑ በሽታ በሌለባቸው ጤናማ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ጥናቱ የሚካሄደው በታሳታፊዎች መልካም ፈቃድ ነው፡፡

Phase 2፡ በዚህ ደረጃ፣ ጥናቱ የሚካሄደው መድሓኒቱ አገልግሎት ላይ የሚውልበት በሽታ በተያዙ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ቁጥሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ፡፡ አሁንም በበጎ ፈቃድ የተመሠረተ ነው፡፡ የዚህ ጥናት አላማ የመደሐኒቱን ፍቱንነትና የሚኖረውን ዳርቻ ጉዳት ለማወቅ ነው፡፡ (efficacy and adverse effects)

Phase 3: ይህ ጥናት በሽታው ባለባቸው ከሶስት መቶ እሰከ ሶስት ሺ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ይህም ቢሆን የበሽተኞቹ በጎ ፈቃድ በኩል ነው የሚደረገው፡፡ የዚህ ጥናት አላማም የመድሐኒቱን ፍቱንነት ለማየትና፣ ሌሎች ወይም ተጨማሪ የዳርቻ ጉዳት መኖሩን ለመከታተል ነው፡፡

Phase 4፣ ደግሞ አለ፡፡ ይህ ግን ብዛት ባላቸው በሽታው ያለባቸው ሰዎች መደሐኒቱን ሲወስዱ በተጫማሪ ፍቱንነቱና ዳርቻ ጉዳቱን ለመከታተል ነው፡፡ በጥናቱ የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥር በሺዎች ደረጃ ነው፡፡

አብዛኞች ኮምፓውንዶች ወይም መድሐኒቶች ከዚህ በኋላ ለፈቃድ ማመልከት ይቻላሉ፣ ፈቃድ ሰጭውም የሁሉንም ጥናቶች ውጤት ተመልክቶ ይፈቅዳል፡፡

Phase 5፡ ይህ ጥናት እንኳን መድሐኒቱ ተፈቅዶ አገልግሎት ላይ አየዋለ በብዛት ታማሚዎች ሲጠቀሙት ሊከስት የሚችሉ ጉዳቶች ካሉ ክትትል ማድረግ ነው፡፡ አልፎ አልፎ አንዳንድ መድሐኒቶች፣ ተፈቀደው አግልግሎት ላይ እየዋሉ፣ ነገር ግን በስፋት ጥቅም ላይ ሲውሉ፣ ከዚህ በፊት ባለፉት ጥናቶች ያልታዩ የዳርቻ ጉዳቶች ማሳየት ጀምረው ከፈቃድ የወጡ ወይም የተከለከሉ አሉ፡፡

ልብ ካላችሁ ጥናቶች ከጤናማ ሰዎች ጀምሮ በታማሚዎች በኩል አልፎ ነው ለአገልግሎት የሚቀርቡት፡፡ ታዲያ አንዳንዴ በመልካም ምኞትና ስሜት፣ በተለይም የሀገር ባህል መድሐኒቶች ሥራ ላይ እንዲውሉ ግፊት ሲደረግ ይታያል፡፡ ገና እኮ ያልተሞከረውን ነው፡፡

​​ስለ አዲሱ የኮቪድ ክትባት ማወቅ የሚገባዎት

በወቅቱ በአለማችን በፍጥነት እየተሠራጨ ያለው፣ በአብዛኛው የአለም ክፍሎች በሁለተኛው ዙር ወረርሽኝ በሚገኙበት ሁኔታ፣ በተለይም በአሜሪካና በአውሮፓ በበሽታው ምክንያት ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች አንዲሁም በበሽታው ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በጨመረበት ጨለማ መሀል ተስፋ የሚሠጥ ነገር የታየው ለዚሁ በሽታ መከላከያ ክትባቶች መገኘታቸውና በአገልገሎት ላይ መዋል መጀመሩ ነው፡፡ ነገር ግን በማወቅም ባለማወቅ ሰለ ክትባቶቹ የተሳሳቱ መረጃዎች በህብረተሰቡ መሀከል መዛመታቸው ይታወቃል፡፡ እንደ ሀይማኖት አድርገው ፀረ ክትባት አቋማቸውን የሚያንፀባርቁ፣ አዲስ ባይሆኑም፣ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እዚህ ላይ የህክምና ባለሙያ ነን የሚሉ በጣም ጥቂት ሰዎች መታየታቸው ያስገረመን ነገርም ነው፡፡ የሳይንስን ውጤት እያዳሉ ወይም እየመረጡ መጠቀሙ ግራ ያጋባል፡፡ ሰለዚህ ለአንባብያን ሰለ ኮቪድ ክትባት የሚታወቁት እውነታዎች ማከፈል የግድ ነው፡፡

ለኮቪድ መከላከያ የሚሆኑ ክትባቶች ጥናት በብዛት ይካሄዳሉ፡፡ የአለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ በአሁኑ ወቅት 52 የሚሆኑ የክትባት ጥናቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ አንግዲህ ጥናቶች በተለያዩ ደረጃዎች አልፈው መሄድ የግድ ነው፡፡ ያ ደግሞ ከደረጃ (phase) አንድ ጀምሮ እሰከ ደረጃ አራት ድረስ ባሉት ውስጥ ነው፡፡ ደረጃ አንድ ሳይሠራ ወደ ደረጃ ሁለት መሄድ የማይሞክር ነገር ነው፡፡ በሳይንሱ አለም፡፡ ደረጃዎችን አልፈው በደረጃ ሶስት የሚገኙ አምስት ጥናቶች አሉ፡፡

በቅርቡ ሁላችንም እንዳየነው፣ ደረጃ ሶስትን ጨርሰው፣ የመንግሥት ፈቃድ ከጠየቁት ከሁለቱ አንደኛው ተፈቀዶለት፣ በምሰሎች አንደምታዩት በየቦታው እየተሠራጨ ነው፡፡ በእንግሊዝ አገር ክትባቱ መሠጠት ከጀመረ ሰንበት ብሏል፡፡ ይህ ክተባት ፋይዘር የሚባለው ኩባንያ የሚያመርተው ነው፡፡

አዚህ ላይ አንድ ትልቅ ጥያቄ አለ፡፡ አሱም፣ እንዴት በፍጥነት ለአገልግሎት ደረሰ በማለት፣ በችኮላ እንደነገሩ የተሠራ ሊሆን ይችላል የሚል ፍራቻ ያለባቸው ሰዎች አሉ፡፡ ፖለቲከኞቹ ኮቪድ ላይ ያሳዩን ባህሪ የተመከለተ ሰው በነዚህ ሰዎች መፍረድ አይችልም፡፡

ቶሎ ሊደርስ የቻለበትን ምክንያት ለመግለፅ

1ኛ. ለክትባት አገልግሎት የሚውለውን ኢላማ የሚሆነውን የቫይረሱን ክፍል ማግኘት ጊዜ የሚወሰድ ነገር ነበር፡፡ ያም እንግዲህ የቫይረሱን የዘር ሰንሰለትና የተለያዬ የቫይሱን ፕሮቲኖች፣ የትኛው የቫየረስ ክፍል ምን አይነት ሥራ እንደሚሠራ ማወቅም ሰለሚያሰፈልግ ነው፡፡ በኮቪድ የሆነው፣ የቫይረሱ የዘር ሰንሰለት ኮድ ወዲያውኑ ለሁሉም ባለሙያተኞች በመለቀቁ ነው፡፡ ቻይኖቹ አንድ የሚመሰገኑበት ነገር ይህ ነው፡፡ ሚስጥር አድርገው ሳይዙ የቫይረሱን የዘር ሰንሰለት ኮድ በመልቀቃቸው፣ በአለም ዙርያ ያሉ ላቦራቶሮችና ሳይንቲሰቶች በዚህ ላይ መድከም አልነበረባችውም፡፡

2ኛ፡ ካላይ እንደተጠቀሰው፣ የክትባትም ሆነ የመድሀኒት ጥናት በደረጃዎቸ ተራ በተራ ማለፍ አለበት፡፡ በኮቨድ ክትባት ጥናት ላይም አንድም የተዘለለ ደረጃ የለም፡፡ በአብዛኛው ጊዜ የሚወስደው ነገር፣ ክትባቱ ወይም መድሐኒቱ ደረጃ ሶስት አልፎ ከተፈቀደለት በኋላ ነው ወደ ማምረት የሚኬደው፡፡ ለምን፣ መፈቀዱን ሳያወቁ ወይም የጥናቱን ውጤት ሳያውቁ አስቀደመው ማማረት ኪሳራ ላይ ሰለሚጥል ነው፡፡ በኮቪድ ጊዜ የተደረገው፣ ጊዜውን ያሳጠረው ነገር፣ ጥናቶቹ በየደረጃው እየተካሄዱ፣ በተለይም ደረጃ አንድና ሁለትን ሲያልፍ ጥሩ ውጤት ካሳየ፣ ደረጃ ሶስት ጥናት ላይ ሆነው የፈለገው ኪሳራ ይምጣ በማለት በስፋት ማምረት ጀመሩ፡፡ እዚህ ላይ፣ መንግሥታቱና የግል ኩባንያዎችም የፈለገው ኪሳራ ይምጣ በማለት ገንዘብ ሰለመደቡም ነው፡፡ ይህ የፋይዘሩ ክተባት ከአሜረካ መንግሥት ሳንቲም ሳይቀበል በራሱ ገንዘብ ነው ደፍሮ ጥናት ያካሄደው ክትባቱን ማምረት የጀመረው፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ክትባቱ ፈቃደ ባገኘ በነጋታው የክትባቱ ሥርጭት የተጀመረው፡፡ ደፍረው ቢያመርቱም፣ የደረጃ ሶስት ውጤት ታይቶ ፈቃድ ካልተሠጠ በስተቀር ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡

3ኛ የክትባቱ ጥናት ሲካሄድ፣ ጥናቱን የሚሳተፉ ሰዎች መመልመልና፣ ከዛም ለበሽታው የሚጋለጡበት ሁኔታ መኖር አስፈላጊ ነበር፡፡ በኮቪድ የታየው፣ የህብረተሰቡ አንዳንድ ክፍሎች በጥናቱ ለመሳተፍ ቢያመናቱም፣ ምስጋና ይግባቸውና ብዙ ፈቃደኞች ለጥናቱ ተሳታፊ ሆነው በመቅረባቸው የምልመላ ጊዜውን አሳጥሮታል፡፡ በተጨማሪም፣ የቫይረሱ ሥርጭት ከፍተኛ ደረጃ በሆነበት ጊዜ ሰለሆነ፣ ሰዎች አስከሚጋለጡ ድረስ መጠበቅም አላስፈለገም፡፡ ምክንያቱም በሚኖሩበት አካባቢ የመከላከያ ዘዴ ካልተጠቀሙ በስተቀር ተጋላጭ ናቸው፡፡ ያ ደግሞ ጥናቱን ለማፋጠን ከፍተኛ አስተወፅኦ አደርጓል፡፡ በመሠረቱ፣ ጥናት የሚሳተፉ ሰዎች ከሁለት ተከፍለው፣ አንደኛው ወገን የውነተኛው የሚጠናው ክትባት ሲሠጠው ሌላኛው ወገን ደግሞ ማስመሰያ (placebo) ምንም የክትባት ወይም መድሀኒትነት ባህ የሌለው ነገር ይሠጣል፡፡ እንግዲህ በጥናቱ ተሳታፊ የሆኑት ሰዎች ምን እንደተሠጣቸውም አያውቁም፡፡ ይህ መሰወር (Blinding) ይባላል፡፡ ይህ ደግሞ ተሳታፊዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ በተሳታፊዎች ላይ የሚደርሰውን ውጤት የሚከታተሉ ባለሙያተኞችም ማንኛው ምን እንደተሠጠው አያውቁም፡፡ አለበለዚያ የማጋደል ስሜት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በዚህ ሁኔታ ሲገኙ ድርብ ስውር (Double blinding) ይባላል፡፡ ትክክለኛ የሚባለው የሳይንስ ጥናት በዚህ መልክ ነው የሚካሄደው፡፡ ጥናቱን የበለጠ ጠንካራ የሚያደርገው ደገም፣ ክትባት ወይም ማስመሰያው የሚሠጣቸው ሰዎች አመራረጥ ላይ፣ አጥኝዎቹ እንደፈለጉ እንዳይመድቡ፣ አብዛኛው በኮምፒተር አማካኝነት ምድባ ይደረጋል፡፡ ይህ አሠራር Randomization ይባላል፡፡ ይህ የሚደረገው ሰዎች ወይም አጥኞዎች የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ለማስወገድ ነው፡፡ ይህ አይነት ጥናት ነው እንግዲህ ክፍተኛ ዕምነት የሚጣልበትና ውጤት በሳይነሳዊ ስሌት ተሰልቶ ይጠቅማል አይጠቅምም የሚባለው፡፡ ለመናገር ያህል፣ እንዲህ አይነት ነገር የወሰዱ ሰዎች ድነዋል እና ያ የተወሰደው ነገር መድሐኒት ነው ማለት ምን ያህል ከሳይንስ እንደሚርቅ መገመት አያስቸግርም፡፡ የታመሙና መድሐኒቱን የወሰዱ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በጥናቱ ውስጥ የታመሙ ግን መድሐኒት የተባለውን ነገር ያልወሰዱ ሰዎች ተካተው የሚታየው ውጤት ተወዳድሮ ነው፣ ይረዳል የሚባለው ነገር የሚነገረው፡፡ ይህ ወደኋላ የተጠቀሰው ነገር በአብዛኛው የሚታየው ለዚህ በሽታ የሚሆን የባህላዊ መድሀኒት ተገኘ  እየተባለ ሲነገር ነው፡፡ በርግጥ መድሀኒትነት ሊኖረው ይችላል ግን ምን ያህል የሚለውና ሌላው ትልቁ ነገር ደግሞ ጉዳቱ ይታወቃል ወይ የሚለውን ጥያቄ አይመልስም፡፡ በዘመናዊ ጥናት መጀመሪያ መታወቅ የሚገባው ነገር ቢኖር ለጥናት የቀረበው ነገር በሰው ላይ ጉዳት ያስከትላል ወይስ አያስከትልም የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ ወደ ደረጃ ሶስት ብቅ አይላትም፡፡ በርግጥ የጉዳቱ መጠን ታይቶ ነው እንጂ ሁሉም ነገር ዳርቻ ጉዳት (Side effect) አለው፡፡

ጥናቶቹ ሲካሄዱ ከፍቱንነት ጥያቄ በፊት ምን ያህል ጉዳት ያስከትላል የሚለው ላይ ከፍተኛ ትኩረት ስለሚሠጥ፣ በጥናቱ ላይ ገለልተኛ የሆኑ አይኖች አተኩረው እንዲከታተሉ ህግም ያስገድዳል፡፡ አጥኝዎቹ በየጊዜው የተገኘውን ውጤት ለነዚህ ገለልተኛ ወገኖች ማቅረብ አለባቸው፡፡ ህግ ነው፡፡ ገለልተኛ አይኖች የሚባሉት ከሚያጠናው ካምፓኒ ጋር በገንዘብም ሆነ በሌላ ነገር ንክኪ የሌላቸው ሰዎች የተሰባሰቡበት ቡድን ነው፡፡ የሚገርመው በጥናት ላይም አንድ ሁለትም ሰለምንል፣ አይደለም አጥኝው፣ የአጥኝው ባለቤት ከካምፓኒው ጋራ ንኪኪ ይኑር አይኑር የምንሞላው ፎርም ላይ አንገልፃለን፡፡ ገለልተኛው ቡደን በአንግሊዝኛ Data Safety Monitoring Board (DSMB) ይባላል፡፡ በጣም ትልቅ ሥልጣንም አለው፡፡ ለሰዎች አደጋ ያስከትላል የሚባል ነገር ከታየ ቦርዱ ጥናቱን ባለበት የማሰቆም ችሎታ ብቻ ሳይሆን ጥናቱ ከነጭራሹ እንዲቆም ማድረግ ይችላል፡፡ ጥናቱ ገና ሲጀመር የጥናቱን ንድፈ ሀሳብ አይቶ በትክክል መነደፉን፣ ሰዎች የሚጎዱ አለመሆናቸውን፣ እንደገናም ደግሞ በገንዘብም ይሁን በሌላ መልክ ሰዎቸን አባብሎ ወይም አስገድዶ እንዳይመለመሉ የሚጣራና ጥናቱን እንዲካሄድ የሚፈቅድ ሌላ ገምጋሚ ቦርድ አለ፡፡ ባጭሩ IRB (Institution Review Board) ይባላል፡፡ ይሀ ቦርድም ገለልተኛነቱን መጠበቅ አለበት፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው፣ ከዚህ ቀድም አጥኝዎች በሰዎች ላይ በማንአለብኘነትም ይሁን በማባበል ለሚደርሱባቸው ጉዳት ደንታ ሳይሠጡ የተካሄዱ ጥናቶች ሰለነበሩ ነው፡፡ በጣም የሚታወቀው በጥቁር አሜሪካውያን ላይ የተሠራው፣ ሰዎቹን ውርዴ (syphilis) እንዲይዛቸው አድርገው ግን መድሐኒት ሳይሰጡ ያደረጉት ጥናት ነው፡፡ በአንግሊዝኛ Tuskegee experiment ተብሎ ይታወቃል፡፡ ሌሎችም አሉ፣ የጀርምን ናዚ ሀኪም የነበረው መንጌሊ የሚባል ሰው ያደረገው ኢሰብአዊ ጥናትም ሌላ ነው፡፡ እያስረዘምኩት ነው ግን አጋጣሚውን በማለት ሰለሆነ ታገሡኝ፡፡ እንግዲህ ከዚህ ቀደም በተደረጉ  ኢሰብአዊና ግብረገብ በጎደላቸው ጥናቶች ምክንያት የተለያየ ህጎች ፀድቀው እየተተረጎሙ ነው፡፡ በአጥኝ ደረጃ የሚሳተፍ ሰው፣ በአመት እስከ አራት ሰአታት ድረስ የሚወስዱ ህጎችን በተመለከተና፣ ጥናቶ የሰውን ስብዕና እንዳይፃረሩ የሚያሰተምሩ ኮርሶችን እንድንወስድ እንገደዳለን፡፡


​ወደ ኮቪድ ክትባት እንመለስ

አሁን የወጣው ክትባት mRNA የተመረኮዘ ነው ሲባል ሰምታችኋል፡፡ ሰለሱም ማብራራት የግድ ነው፡፡ ክትባቶች ሲዘጋጁ በአጠቃላይ በሁለት ደረጃ ይከፈላሉ፣ ሶስትም ማለት ይቻላል፡፡ እንደኛው የክትባት አይነት፣ በሽታ የሚያመጣውን ቫይረስ በመጠኑ ለተከታቢው በመስጠት የተከታቢው ሰውነት መከላከያ (Antibody) እንዲፈጥር ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የኩፍኝ ክትባት (varicella) ማለት ነው፡፡ ሌላኛው ዘዴ ደግሞ፣ ሙሉ ቫይረስ ሳይሆን፣ የቫይረሱ ወሳኝ የሆነውን ፕሮቲን ብቻ በመስጠት መከላከያ እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ በየአመቱ የምንወሰድው የኢንፍሉዌንዛ ክትባት በተለይ በመርፌ በኩል የሚሠጠው አይነት ማለት ነው፡፡ በርግጥ በአፍንጫ በኩል የሚረጭ ሙሉ ቫይረስ ያለበት የኢንፍሉዌንዛ ክትባት አለ፡፡ በብዛት አገልግሎት ላይ አይውልም፡፡ እዚህ ላይ፣ ሙሉ ወይም ደከም ያለ ቫይረስ ያለበት ክትባት በሽታ ሊያስከትል ይችላል፤ ሆኖም በጣም አልፎ አልፎ ነው የሚታየው፡፡ የቫይረሱ ፕሮቲን ግን በሽታ አያስከትልም፡፡ አራት ነጥብ፡፡ ሰዎች ሰሜት ይሰማቸዋል ያ ግን የራሳቸው ሰውነት መከላከያ ሲፈጥር በመወራጨት የሚፈጥረው ነገር ነው፡፡ በህክምናው በኩል፣ የሰውነት መከላከያ አቅማቸው ለደከመ ሰዎች አብዛኞቹ ሙሉ ቫይረስ ያላቸው ክትባቶች አይሠጡም፡፡ ለምሳሌ ኤይድስ፣ ካንሰር፣ የካንሰር መድሀኒት ላይ ያሉ ሰዎቸን ለመጥቀስ ያህል፡፡

ይህ ከላይ የተጠቀሰው mRNA ክትባት በሥራ ላይ ሲውል ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ አዲስ ሆኖ አይደለም፣ ከ1990ዎች ጀምሮ ይህንን ዘዴ ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ሲደረግ ነበር፡፡ ለምሳሌ ዚካ የሚባለው ቫይረስን በዚህ አይነት ክትባት፣ ሌላም CMV የሚባል ቫይረስን በዚህ ዘዴ ክትባቱን ለመስራት እየተሞከረ ነበር፡፡ አሁን ኮቪድ መጣ፣ ብርም እንደልብ ተገኘ፣ ሳይንሱም አደገና ሥራ ላይ ዋለ፡፡

ይህንን mRNA ክትባት ለመረዳት፣ ወደ ባዮሎጂ ዞር ብሎ የፕሮቲን አሠራርን መመልከት ይረዳል፡፡ mRNA በመሠረቱ ፕሮቲን እንዲፈጠር ወይም ለመሥራት ትዕዛዝ የሚሠጥ በተፈጥሮ በየሴሎቻችን ውስጥ የሚገኝ ኮድ ነው፡፡ የ mRNA ቅንብር ነው እንገዲህ የትኛውን ፕሮቲን መሠራት እንዳለበት የሚወስነው፡፡ ይህን ቴክኖሎጂ አስደናቂ እምርታ የሚያደረገውን ነገር እንመልከት፡፡ የኮቪድ ቫይረስ ወደ ሰው ሰውነት ወይም ወደ ሴሎች ለመግባት በሽፋኑ ላይ የሚገኝ ሰፓይክ ፕሮቲን (Spike Protein) የሚባለውን ክፍሉን ነው የሚጠቀመው፡፡ በየምስሉ የምታዩት በቫይረሱ ላይ እንደ ጌጥ ቁጭ ቁጭ ብለው የሚታዩት ይህ ስፓይክ ፕሮቲን የሚባሉ ክፈሎች ናቸው፡፡ ሚስጥሩ ይህ ከሆን፣ ሰውነት ማድረግ ያለበት፣ ይህንን ስፓይክ ፕሮቲን በጠላትነት መዝግቦ የመከላከያ አንቲቦዲ ከፈጠረ፣ ቫይረሱ ወደ ሰውነት በዘለቀ ቁጥር እንቲቦዲው ይህንን ፕሮቲን ከጥቅም ውጭ ያደርገውን ቫይረሱ ወደ ሴሎችም አይገባም፣ ካልገባ ደግሞ ዘልቆ መራባትና በሽታ መፍጠር አይችልም፡፡ ልብ በሉ፣ ዋናው ሚስጥር ይህ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ለማድረግ፣ ሙሉ ቫይረሱን ሳይሆን ይህንን ፕሮቲን ብቻ ለሰዎች መሥጠት እንደ ክትባት ያገለግላል፡፡ ጥያቀውና ችግሩ ይህንን ስፓይክ ፕሮቲን በገፍ ለማምረት፣ ቫይረሱን በገፍ ማሳደግ ይኖርባቸዋል፡፡ የምታወቁ ከሆነ፣ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ በእንቁላል አስኳል ወስጥ እንዲያድግ ተደርጎ ነው ከዛ በኋላ የሚፈለገው ለክትባት የሚውለው ፕሮቲን ተለይቶ የሚመረተው፡፡ ህም፣ ማን ኮቪድን ያሳድጋልስ ማንስ ያመርታልስ፣ አደጋውስ፡፡ እንዲሁ በተገኘ ላቦራቶርም የሚያሳድጉት ነገር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ሳይንስ ላይ ሲያተኩር መላ ማግኘቱ አይቀርም፡፡ እናም ተገኘ፡፡ የተደረገው ነገር፣ ሰፓይክ ፕሮቲን አንዲሠራ የሚያዘውን የ mRNA ሰንሰለት ማወቅ ብቻ ነው የተፈለገው፡፡ ከዛ በኋላ፣ የተፈለገውም ሰፓይክ ፕሮቲኑ ብቻ እንጂ ቫይረሱ ሰላልሆነ፣ ይህን mRNA ስንሰለት ከውጭ አርቲፈሻል በሆነ መንገድ ማምረት ነው፡፡ አስተውሉ፣ ፕሮቲን እንዲሠራ የሚያዘውን  የmRNA ሰንሰለት ከውጭ ማምረት ከቫይረሱ ጋር ጭራሽ አይገናኝም ሰለዚህ ክትባቱ ቫይረስ የለውም፡፡

ይህን ካገኙ በኋላ የmRNA ሰንሰለቱን ናኖ ፓርቲክል በሚባል መንገድ ማዘጋጀት ነበረባቸው፡፡ ይህ የተዘጋጀው ነገር በክትባት መልክ ለሰዎች ሲሰጥ፣ ወደ ሰዎች ሴሎች በተለይም የጡንቻ ሴሎች ውስጥ ይዘልቅና፣ የጡንቻ (muscle) ሴሉን፣ ስፓይክ የተባለውን ፕሮቲን እንዲሠራ ትዛዝ ይሠጣል፡፡ ሰፓይክ ፕሮቲኑ ከተሠራ በኋላ ከጡንቻው ሴል ገና ከመውጣቱ፣ የሰውነታችን የመከላከያው ክፍል፣ ፀጉረ ልውጥ ፕሮቲን መኖሩን ይገነዘባል፡፡ ረቂቅ ነው፡፡ መታወቂያ ይጠይቅ ወይም የጣት አሻራ፣ ብቻ ሰውነት ውስጥ መገኘት የማይገባው ፕሮቲን መሆኑን ያውቅና፣ በሴሎች አማካኝነት ተቀባብሎ፣ አዲሱን ወይም ፀጉረ ልውጡን ፕሮቲን ደራሹን ያጠፋዋል፡፡ ግን በዛ አያቆምም፣ ሁለተኛ ተመልሶ ሲመጣ በተገኘበት እንዲመታ፣ በጠላትነት ይመዘግብና የተለየ ለዚህ ፕሮቲን ብቻ የሚሆን ማጥፊያ እንቲቦድ ያዘጋጃል፤ ይከዝናል፡፡ እንገዲህ በዚህ መንገድ የተዘጋጀ ሰውነት፣ ከላይ እንደገለፅኩት እውነተኛው ቫይረስ ሲመጣ ወደ ሴሎችም የሚገባስ ያንን ሰፓይክ ፕሮቲን ተጠቅሞ ሰለሆነ፣ ባይረሱ ሰፓይክ ፕሮቲኑን ገና ከማሳየቱ በተጠንቀቅ የተዘጋጀው ሰውነት፣ በሴሎች አማካኝነት ያ ፀጉረ ልውጡ ፕሮቲን ገብቷል ብሎ መልክት ከማሳወቁ፣ ተከዝኖ የነበረው አንቲቦዲ ይለቀቃል፡፡ በዚህ መክል እንቲቦዲው የገባውን ፕሮቲን በማምከን ቫይረሱን መግቢያና መራቢያ ያሳጠዋል፤ በኮቪድ መያዝም ይቀራል፡፡ ይህ ነው ሚስጥሩ፡፡ ከአንቲ ቦዲ ውጭ አጥቆ ሴሎችም ይረባረባሉ፡፡ ታዲያ የተሠጠው የmRNA ማስመሰያ ፕሮቲን መስሪያ መንገድ ነው እንጂ ጭራሽ ቫይረስ ሰላልሆነ፣ ኮቪድ በሽታ አያመጣም፡፡ አራት ነጥብ፡፡

በጣም ጠለቅ ብለው ይህንን ጉዳይ የሚያውቁ ሰዎች በክትባት የተሠጠው የmRNA ሰንሰለት ወደ ሴል ኑክለስ ከገባ የሰውን የዘር ሰንሰለት ያዛባ ይሆን ይላሉ፡፡ ለሱም መልሱ የmRNA ሰንሰለቱ ወደ ጡንቻ ሴል አይገባም፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን፣ ሥራው ከሠራ በኋላ የmRNA ጭራሽ ይወገዳል እናም ወደኋላ ቀርቶ ስፓይክ ፕሮቲን ሲሰራ አይከርምም፡፡

ወደ ቀረቡት ጥናቶች ስንመለስ በተለይ የፋየዘሩ ክትባትን በሚመለከት፣ ተደጋጋሚ ጥናቶች ተደርገው፣ ማለትም ዋናው ነገር ጉዳት ማድረስ እና አለማድረስ በመሆኑ፣ ለሰዎች በጣም አስጊ ነው የሚባል ነገር አልታየም፡፡ ክትባቱ የተፈቀደ ዕለት ኒው ኢንግላንድ ጆርናል በተባለው ታዋቂ የህክምና መፅሔት ሰለዚህ ክትባት ጉዳትና ፍቱንነት የሚገልፅ የጥናት ውጤት ታትሟል፡፡ በጥናቱ የተገለፀው፣ ክትባቱ ከመቶው በዘጠና አምስት ፐርስንቱ ላይ የሚፈለገውን ውጤት አሳይቷል፡፡ ማለትም ለቫይረሱ ተጋልጠው ክትባቱ ሳይሆን ማሰመሰያው ከተሠጣቸው ሰዎች ጋር ሲወዳደር፣ ክትባት ከወሰዱ መሀከል 8 ሰዎች በኮቪደ ሲያዙ፣ ካልወሰዱት መሀከል 162 ሰዎች በኮቪድ ተይዘዋል ይላል፡፡ ሰታቲስቲኩን መፅሔቱ ላይ ተከታለሉ፡፡  ይህ አንግዲህ 43 ሺ548 ሰዎች የጥናቱ ተሳታፊዎች ከሁለት ተከፍለው በተደረገው ጥናት ነው፡፡ ጉዳቱን በሚመለከት፣ ጎላ ብለው የታዩ ነገሮች ቢኖሩ፣ አንደኛ የድካም ስሜት፣ ሁለተኛ የራስ ምታትና ሶስተኛ ደግሞ መርፌ የተሠጠበት የሰውነት ክፍል የህመም ስሜት መሰማት ነው፡፡ እነዚህ ጎላ ብለው የታዩት ከሁለተኛው ክትባት በኋላ ነው፡፡ ክትባቱ በ21 ቀናት ልዩነት ሁለት ጊዜ ነው የሚሠጠው፡፡

እዚህ ላይ የኮቪድ ሥርጭትን ለመግታት በህብረተሰቡ ውስጥ በክትባቱ አማካኝነት የመከላከያ አንቲቦዲ ያላቸው ሰዎች ቁጥር እንደ ስሌቶ ከሰባ ፐርስነት ወይም ከዛ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዛም የወረደ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ያ ማለት፣ ያን ያህል ሰው አስኪከተብ ድረስ የኮቪድ መከላከያ ተግባራት አይቆሙም፡፡ አሁን አንዲያውም በተናከረ መልክ ተተግብረው፣ የቫይረሱን ሥርጭት መግታትና በዚሁ ምክንያት የሚመተውን ሰው መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

ክትባቱ በስፋት ለህዝብ መሠጠት ከተጀመረ፣ ድንገት በጥናቱ ላይ ያልታዩ ነገሮች ይኖሩ ይሆን ለማለት ወደ ሰላሳ ሺ የሚሆኑ ሰዎች ክትባቱን ወሰድው ክትትል ማድረግ ያሰፈልጋል፡፡ ሰለዚሀ ክትባቱን እወስዳለሁ አልወሰድም፣ ጉዳቱን አላውቅም የሚሉ ሰዎች፣ መልስ ያገኛሉ፡፡ መጀመሪያ እንዲወሰዱ ከተመደቡ ወገኖች የጤና ባለሙያተኞች የመጀመሪዎቹ ናቸው፡፡ እስከ ታህሳስ ማለቂያ አርባ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ይከተባሉ ሰለሚባል፣ ተራዎ ሲደርስ ሰለ ክትባቱ የበለጠ መረጃ ይኖረዎታል፡፡

መልካም ንባብ አካፍሉ

ዋቢ Safety and Efficacy of the BNT162b2 mRNA Covid-19 Vaccineere.