ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

አዲሱ ኮሮና ቫይረስ በአየር ላይና በዕቃዎች ላይ የመቆየት ችሎታ አዲስ ጥናት ውጤት ሰብሰብ ብሎ ለመቆየት በቂና ተጨማሪ መረጃ 03/21/2020 

ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገፅ፣ ከዚህ በፊት የተደረጉ፣ ማለትም ሌሎች ቫይረሶችን፣ ጥናቶች ተመርኩዞ አዲሱ ቫይረስ ምን ያህል ቀናት ከሰው ሰውነት ውጭ እንደሚቆየ አስገንዝበን ነበር፡፡
       አሁን ግን፣ አጥኝዎች ይህንን ወሳኝ ጥያቄ ለመመለስ ያደረጉትን ጥናት በስመ ጥሩ የኒው ኢንግላንድ ጆርናል መፅሔት አካፍለውናል፡፡ እንደተለመደው፣ አዲሱን ነገር ለወገኖቹ በትኩሱ ላከፍል በሚል፣ በተለይም የህክምና ቃላትና አተረጓጎም ጤና ባለሙያ ላልሆኑ ሰዎች እንደሚሆን አደርጌ ዘገባ አቅርቤያለሁ፡፡
     ይህ ርዕስ፣ እንደ ህክምና ባለሙያና፣ በተለይም በዚህ በተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ እንደመሆኔ፣ ወዲያውኑ ወደ ሥራ እንድንተገብራቸው የምናደረጋቸው ነገሮች የረዳን ነው፡፡
      ወደ ጥናቱ ልውሰዳችሁ፡፡ የአዲሱ ቫይረስ ሳይንሳዊ ስሙ SARS-CoV-2 መሆኑን እንድተገነዘቡ ያስፈልጋል፡፡ ቁጥር ሁለት የተባለው፣ ከዚህ ቀደም በዝርያው ከዚህ ከአዲሱ ጋር የተዛመደ SARS-CoV-1 የሚባል ቫይረስ ሰለነበረ ነው፡፡ የነዚህ ቫይረስ አያታቸው የሌሊት ወፍ ነው፡፡
      የዚህ ጥናት አትኩሮት የሆነው፡፡ ሁለቱ ቫይረሶች በአየር ላይና በዕቃዎች ላይ ምን ያህል ጊዜ ይቆያሉ ብሎ ማወዳደር ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ በአየር ላይና በተለያያ ዕቃዎች ላይ፣ ከሆነም በየትኛዎቹ ዕቃዎች ላይ፣ ሰዎችን መልሶ መልከፍ የሚችል ቫይረስ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፣
      በዝርዝር ወደ ቴክኒክ አሠራሩ ሳልገባ፣ እነዚህን ሁለት ቫይረሶች በአይን በማይታይ ጠብታ በሚመስል ሁኔታ፣ አየር ላይ መርጨት በሚችል መሣሪያ አማካኝነት፣ በደንብ በተዘጋ ሣጥን ውሥጥ የሁለቱ ቫይረሶች ያሉበት ፈሳሽ ልክ ከሰው ማስነጠስ ጋር አየር ላይ እንደሚወጣው አይነት አንዲሆን ተደርጎ ተረጨ፡፡ በነገራቸን ላይ ይህ አዲሱ ቫይረስ፣ አንድ ወጥ ብቻ አይደለም፣ በመጠነኛ መንገድ የሚለያዩ ግን ካንድ የዘር ግንድ የወጡ የተለያዩ ዝርያዎች አሉት፡፡ ከነዚህ መሀከል ከእያንዳንዳቸው አንድ የቫይረስ ዘር ተመርጦ ነው ለዚህ ጥናት የተጠቀሙት፡፡ በዚህ መንገድ ወደዚህ ሣጥን ውስጥ የተረጨው አየር (የተበከለው) ሳምፕል ተወስዶ ሲለካ የፈጠረው ሁኔታ ከሰዎች የመተንፈሻ አካላት ከሚወጣው ቫይረስ መጠን ጋር ተመሳሳይ ነው የሆነው፡፡
      አጥኝዎቹ በፅሁፋቸው እንደ ገለፁት፣ አስር ሙከራዎች ማድረጋቸውን፣ በነዚህ አስር ሙከራዎች፣ (በአየር ላይ፣ በፕላስቲክ ላይ፣ በብረት ላይ፣ በመዳብ ላይና የወረቀት ካርድ ቦርድ ላይ) ጥናት አደረጉ፡፡ በነዚህ በተጠቀሱት ነገሮች ላይ ያረፈውን ቫይረስ መጠን በመለካት ነው ውጤቱን ያካፈሉት፡፡
      አዚህ ላይ በጣም መገንዘብ ያለብን የሚከተውን ውጤት ነው፡፡ በጥናታቸው መሠረት፣ SARS-CoV-2 (አዲሱ ኮሮና፣ ኮቪድ) በተበከለው አየር ላይ፣ ለሶስት ሰአታት viable (ከነነብሱ ልበል) መቆየት እንደሚችል ተመልከተዋል፡፡ viable የሚለው ቃል የሚገልጠው፣ ተመልሶ ሌላ ሰው የመያዝ አቅም አለው ማለት ነው፡፡ ከሶሰት ሰአታት በኋላ ግን፣ የቫይረሱ መጠን በሊትር (በሂሳብ መለኪያው)፣ ልክ እንደዛኛው ቫይረስ ማለትም SARS-CoV-1፣ እኩል በሆነ ደረጃ የቫይረሱ መጠን እየቀነሰ ሲሄድ አስተውለዋል፡፡
ወደ ሌሎቹ ዕቃዎች ስንሻገር፣ አጥኝዎቹ የተመለከቱት፣ አዲሱ ቫይረስ፣ SARS-CoV-2፣ በፕላሰቲክና በብረት ላይ (stainless steel) ከመዳብና ከካርድ ቦርድ ላይ በበለጠ ሁኔታ ተደላድሎ መቆየት መቻሉን ተመልክተዋል፡፡ በነዚህ ዕቃዎች ላይ፣ ከ72 ሰአታት ወይም ሶሰት ቀናት በኋላም ሲለኩ፣ ከላይ እንደገለጥኩት፣ viable (ያልሞተ) ቫይረሰ መገኘቱን ይገልጣሉ፡፡ ነገር ግን፣ የቫይረሱ መጠን ከነበረበት የቀነስ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ የቫይረሱ በፕላሰቲክና በብረት ላይ ከ72 ሰአታት በኋላ የመቆየት ችሎታውና እያደረ የብዛቱ መጠን መቀነስ ተመሳሳይ ሆኖ ነው ያገኙት፡፡
      በመዳብ ላይ ግን፣ ከአራት ሰአታት በኋላ ምንም አይነት viable የሆነ SARS-CoV-2ቫይረስ ያልተገኘ ሲሆን፣ ከስምንት ሰአታት በኋላ ሲለካ ደግሞ ምንም SARS-CoV-1 አልተገኘም፡፡
      በወረቀት (ካርድ ቦርድ) የወረቀት ካርቶን ላይ፣ ከ24 ሰአታት በኋላ viable የሆነ SARS-CoV-2 አልተገኘም፡፡ ከስምንት ሰአታት በኋላ ደግሞ ምንም አይነት SARS-CoV-1 አልተገኘም፡፡
        የዚህ ጥናት አንዱ አላማ ደግሞ፣ ይህ አዲሱ ቫይረስ በፍጥነት እንዲህ የተዛመተው፣ በአየር ላይና በዕቃ ላይ ከድሮዎቹ ቫይረሶች በተለየ ሁኔታ ሰለሚገኝ ነው ወይ የሚለው ጥያቄ ላይ በማተኮር ነው፡፡ ለዚህም ነው ጥናቱ፣ SARS-CoV-1 ና SARS-CoV-2 በማወዳደር የተደረገው፡፡ ልብ ብሉ፣ እንደዚህ አይነት ጥናቶች በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡ የቫየረሱን ስርጭት ለመቀነስ የምንወስዳቸው ርምጃዎቸ በነዚህ ጥናት ውጤቶች የተመረኮዙ ናቸው፡፡
       ሁለቱም ቫይረሶች በአየር ላይም ሆነ በሌሎቹ በተጠኑ ዕቃዎች ላይ የነበራቸው መጠን ጊዜው በጨመረ ቁጥር እያሽቆለቆለ እንደሚሄድ ተመልክተዋል፡፡
       አዲስ አባባል የግድ ማስረዳት ያለብኝ (half-live) የሚለውን ነው፡፡ ቫይረሶቹ ከነበራቸው ከመጀመሪያው ሙሉ መጠን፣ ወደ ግማሹ የሚወርዱበት የጊዜ መጠን ነው፡፡ ማለትም ከምን ያህል ጊዜ በኋላ መጠኑ በግማሽ ይወርዳል፡፡ ይህ የመጠን መለኪያም በቫይረስ ብቻ ሳይሆን በሰውነት ውስጥ መድሃኒቶች ምን ያህል ጊዜ ይቆያሉ ተብሎ እንደመለኪያ ይቆጠራል፡፡
       በዚህ መሠረት፣ በአየር ላይ ሁለቱም፣ SARS-CoV-1 ና SARS-CoV-2 እኩል የሆነ half-live ላይ አላቸው፡፡ አየር ስል እዚህ ላይ፣ ቫይረሱ የተረጨበትን (የተበከለውን) ማለት እንደሆነ እንድተገነዘቡ፡፡ የ half-live ጊዜው መጠን፣ በአማካይ ከ1.1 አስከ 1.2 ሰአት ነው፡፡ አማካዩ ያ ይሁን እንጂ፣ በሙከራው የታየው፣ በ SARS-CoV-2 በኩል፣ ከ0.64 ሰአት እሰክ 2.64 ሰአታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፣ ለ SARS-CoV-1 ደግሞ ከ0.78 እሰክ 2.43 ሰአታት ጊዜ ነው፡፡ አማካይ የሚለው ቃል የሚገልጠው በአብዛኛዎቹ ሙከራዎች የታየውን ነው፡፡ አለዚያ ግን በአንደኛው ሙከራ 0.64 ሰኣት ቢሆን በሌላኛው ሙከራ ደግሞ 2.64 ሰአት ድረስ ታይቷል ነው፡፡ ስታቲስቲክ በመጠቀም ነው፣ እንግዲህ ሊያስማማን ወደ ሚችል ቁጥር የምንመጣው፡፡
       የላይኛው በተበከለው አየር ሲሆን፣ በመዳብ ላይ፣ የሁለቱም ቫይረሶች half-live እኩል ሆኖ ነው የተገኘው፡፡

በካርቶን ወረቀት ላይ ግን፣ የ SARS-CoV-2 half-live ከ SARS-CoV-1 የበለጠ ሆኖ የተገኘው፡፡

ረዘም ያለው half-live በሁለቱም ቫይረሶች በኩል የታየው በፕላስቲክና በብረት ላይ ነው፡፡ በቀላሉ ረዥም ጊዜ ይቆያል ለማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ በብረት ላይ 5.6 ሰኣታት ሲሆን፣ በፕላሰቲክ ላይ ግን 6.8 ሰአታት ነው፡፡
በዚህ ግኝታቸው ማጠቃለያው፣ በሁለቱ ቫይረሶች መሀከል በተበከለ አየርም ይሁን ከላይ በተጠቀሱት ዕቃዎች ላይ የቫይረሶቹ የመቆየት ችሎታ ልዩነት የሌለው ወይም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰለዚህ በሁለቱ መሀከል የመዛመት ፍጥነት ልዩነት የመጣው በሌሎች ምክንያቶች ሊሆን ይችላል ነው፡፡ ከነዚህ መሀል ያነሷቸው ምክንያቶች፡፡ የ SARS-CoV-2 በፍጥነት መዛመት፣ በሰዎች መተንፈሻ አካላት ላይ በጣም ከፍተኛ የሆነ የቫይረስ መጠን ሰለሚገኝና፣ ሌለው ደግሞ የበሽታው ስሜት የሌላቸው ሰዎች ቫይረሱን ሰለሚያዛምቱ ነው ይላሉ፡፡
       በመቀጠልም፣ የተበከለ አየርና ቫይረሱ ያረፈባቸው ዕቃወዎች ከዚህ በፊት በ SARS-CoV-1 እንደታየው ሁሉ፣ ቫይረሱን ማዛመት የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ያሳስባሉ፡፡ ዋቢ N ENGL J MED
       ይህ ቫይረስ ብቅ እንዳለ፣ ባለሙያተኞቹ፣ የድሮዎችን ቫይረስ የሥርጭትና ሌሎች ባህሪዎችን በመመልከት ነው እንግዲህ፣ የቫይረሱን መሠራጨት ለመግታትና እንዳንያዝም መከላከያዎችን እንድናደረግ መመሪያዎች ያወጡት፡፡ አብረን በዚህ ጥናት እንዳየነውም፣ ትክክል ነው ያደረጉት፡፡ ሰለዚህ ከዚህ ቀደም የተሠጡና የሚሠጡ ምክሮችን መፈፀም የግድ ነው፡፡ በዚህ ገፅ በተለያዩ ጊዜ የቀመጡትን ፅሁፎች ብታነቡ ግንዛቤ ይጨምራል፡፡

      ተጨማሪው ምክር ደግሞ፣ እንዳያችሁት፣ ሰዎች ተሰብሰበው ወደ ነበሩባቸው አካባቢዎች ብትሄዱና፣ ባጋጣሚ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሲስሉና ሲያነጥሱ ከነበረ፣ የተበከለው አየር ለሶስት ሰአታት ሌላን ሰው መልሶ መያዝ የሚችል መጠን እንደሚኖረው ነው፡፡ ይህ በተለይ ጠበብ ባሉ ክፍሎች፡፡ በተለይ፣ በተለይ በኢሊቬተሮች ውስጥ፣ ስብሰባ ካለቀ በኋላ ቢሄዱም አደጋው ሊኖር እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ እኮ ነው፣ ባካችሁ በጣም አስፈላጊ ካልሆነ ሰብሰብ በሉ የሚባለው፡፡ እኔም ብሆን፣

ዕቃዎችን ላለመንካት እጅን ሰብሰብ
አይን፣ አፍንጫን፣ አፍንም ሳይታጠቡ ከመንካት ጣቶችን ሰብሰብ
ድንገት ተይዘው ከሆነ ደግሞ፣ ቫይረሱን ላለመርጨት ሳልዎን ሰብሰብ
ወጣ ወጣ በማለት፣ ከተበከለ አየር ወይም ከተበከለ ዕቃ ጋር ላለመገጣጠም እግርዎን ሰብሰብ ያድርጉ አላለሁ፡፡​​​


የሱን ኮቪድ ለኔ፣ የኔን ኮቪድ ላንቺ የሚያመላልሰው
የታለ ደሞዙ ሱፉን የለበሰው 5/12/2020


 እንደ ኮቪድ-19 የመሰለ አሰቸጋሪ በሸታ ታይቶም አይታወቅም፡፡ በዚህ ሲሉት በዚያ፣ እየተቀያየረ እየሄደ ነው፡፡ ወዴት እንደሚሄድ መቼም እግዚአብሔር ይጠብቀን፡፡

ሰሞኑን በአሜሪካ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የተጠቃው የኒው ዮርክ ስቴት አስተዳደሪ በሠጡት መግለጫ አንድ እንግዳ የሆነ መረጃ አየን፡፡ እነሱ ያደረጉት ምንድን ነው፣ በኮቪድ-19 ምክንያት ማነው ወደ ሆሰፒታል የሚሄደው ብለው ከተወሰኑ ሆሰፒታሎች መረጃ ሰበሰቡ፡፡ ውጤቱ የማስደንገጥም ያህል ነው የሆነው፡፡

ምክንያቱም በአሀዝ ሲታይ በኮቪድ ምክንያት ሆሰፒታል የሚገቡ ሰዎች፡

ከነርሲነግ ሆም (18 ፐርስንት)

ከሌሎች ክፍሎች፣ ማደሪያ የለሾችን ጨምሮ ከ4 ፐርስንትና ከዚያ በታች ነው

ትልቁ  ድርሻ የመጣው፣ ከቤታቸው ከሚመጡ ሰዎች ነው፡፡ ያም 66 ፐርስንት ነው፡፡

እንዴ፣ ቤታችሁ ቆዩ ተብለው ቤት ውስጥ የቆዩ ሰዎች እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ ብለን ሁላችንም ጠየቅን፡፡

ነገሩ የሚገርም አይደለም፡፡ ባንድ ቤት ውስጥ ካንድ ሰው በላይ የሚኖርበት የቤት አኗኗር ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሰዎቹ ታመው ከሚወጡበት ቤት ሌሎች ወጣ ገባ የሚሉ ሰዎች አብረዋቸው እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ እንግዲህ ከዚህ መሀል ለሥራም የሚወጡ ሰላሉበት ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ወጣ ገባ የሚሉት ቢታመሙ ኖሮ ያው በቤታቸው ይቆያሉ፣ እንደዛም ሆነው ያጋልጣሉ፡፡ የበሽታው ስሜት ካልተሰማቸው ደግሞ፣ መውጣት መግባታቸውን አያቆሙም፣ ቫይረሱም ካለባቸው ቤት ለሚቆዩት ሰዎች እያቀበሉ ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ ወጣትና ጎልማሶች፣ ግድ የለሽ በሆነ መንገድ ወጣ ገባ ሲሉ፣ እቤት አብረዋቸው ያሉትን ሰዎች ማሰብ ያለባቸው፡፡

ይህ ቫይረስ (ሳርስ ኮሮና ቁጥር ሁለት፣ ሳኮ2) ቤት ውስጥ ከገባ አስቸጋሪ ነው፡፡ በህክምና ቦታዎች ካንዱ ወደ ሌላው ወደ ጤና ባለሙያተኛው ጨምሮ ለመተላለፍ ጥቂት ደቂቃዎች ቢበቃውም፣ ከህክምና ቦታ ውጭ ከሆነ ከአስር ደቂቃ በላይ ከታማሚው ጋር አብሮ መቆየትም በቫይረሱ ለመያዝ በቂ ነው፡፡ አንድ ጣራ ስር አብረው የሚኖሩ ከሆነ ግን፣ ራሳችሁ አስቡት ለምን ያህል ጊዜ የመጋለጥ ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ፡፡ በተጨማሪ በብዙ መኖሪያ ቤቶች በቂ ርቀት መጠበቅም አይቻልም፣ ሰለዚህ ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር በሁለት ሜትር ክልል ውስጥ መቆየቱ ተጨማሪ መጋለጥ ነው፡፡ ሌላው የምንረሳው ነገር ደግሞ፣ ቫይረሱ ካለበት ሰው የሚወጣው ቫይረስ አካባቢውን አንደሚበክለው ነው፡፡ በህክምና ቦታ አንድ የምርመራ ክፍል ከተጋለጠ፣ ወዲያው ተዘግቶ ለተወሰኑ ሰአታት አግልግሎት እንዳይሠጥ ይደረጋል፡፡ አገልግሎት ከመሥጠቱ በፊት ደግሞ በደንብ ይፀዳል፡፡

ሌላው አሠራር፣ በተለይ አሁን፣ የሥራ ቦታዎች ይከፈቱ በሚባልበት ጊዜ፣ አንድ የሥራ ቦታ በኮቪድ-19 ከተጋለጠ፣ መንግሥት (ሲዲሲ) የሚመክረው፣ ያንን የተጋለጠ ክፍል ለሀያ አራት ሰአታት ዝጉት ነው፡፡ ምክንያቱም ሌላ ያልተጋለጠ ሠራተኛ ወደ ክፍሉ ገብቶ እንዳይጋለጥም ነው፡፡

ታዲያ መኖሪያ ቤት እንዴት አድርጎ ይዘጋል? ማጽዳት በርግጥ መደረግ የሚገባ ነገር ነው፡፡

ዋናው ነገር፣ ይህ ቫይረስ፣ ሳኮ2፣ ወደቤት እንዳይገባ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ቫይረሱን የሚያመላልሱ ሰዎችን ባካችሁ እያልን የምንማፀነው፡፡

ወደ ኒው ዮርክ ሪፖርት ልመልሳችሁና፣ ይህ መረጃ የመጣው ከ113 ሆስፒታሎችና በነዚህ ሆሰፒታሎች ውስጥ ከተረዱ 1269 ህሙማን መሀከል ነው፡፡

ዝርዝሩን በደንብ ከተመለከትን፣ በብዛት ሆሰፒታል የገቡት፣ ጥቁሮች፣ በእድሜ የገፉ ሰዎች መሆናቸውን እናያለን፡፡ በእድሜ መግፋት ለማንኛውም ህብረተሰብ የጋራ አደጋ የሚፈጥር ሁኔታ ነው፡፡

ጥቁሮች በብዛት ገቡ የሚለው፣ ጥቁር ሰለሆኑ ቫይረሱ በተለየ መንገድ ይይዛቸዋል ማለትም አይደለም፣ እስካሁን እሰከምናውቀው ድረስ፡፡ ነገር ግን፣ የቤትና የቤተሰብ አኗኗርን ከተመለከተን፣ በአንድ ቤት ውስጥ ብዙ ሰው ተጋርቶ የሚኖርበት ሁኔታ ሰላለ ነው፡፡

መልክቱ ግልፅ ነው፡፡ ሳኮ2 ወይም ኮቪድ፣ ሰዎች ሰብሰብ ሲሉ ሰለሚወድ ነው፡፡ የዚህ ቫይረስ ሥርጭት በኢትዮጵያ ውስጥ ጠነከርም አልጠነከርም፣ የቤተሰብ አኗኗሩ እዚህ እየተጎዳ ካለው ማህብረሰብ የተለየ አይደለም፡፡ ሰለዚህ ወጣ ገባ የሚሉ ሰዎች ደጋግመው ሊያስቡበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ በአሜሪካም ቢሆን፣ በቫይረሱ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሊወድቁ የሚችሉ የቤተሰብ አባላት በቤት ውስጥ ካሉ፣ ወጣ ገባ የሚሉ ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡ የቫይረሱን ሥጦታ ማንም አይፈልገውምና አደራ አላለሁ፡፡ 

ማስክዎን የሚያወልቁባቸው ቦታዎች ያጋልጡዎት ይሆን? 4/18/20

 ሀሉም ሰው ማሰክ እንዲያደርግ ሲመከር፣ ዋናው ምክንያት፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በሚተነፍሱበት፣ በሚያስነጥሱበት ወይም በሚያስሉበት ጊዜ፣ ከትንፈሻቸው የሚወጡትን ቫይረስ የተሸከሙ ጠብታዎችን ለመገደብ ነው፡፡ አሁን እንግዳ የመሰለው፣ ግን ከመጀመሪያው የታወቀው ነገር፣ በቫይረሱ ተይዘው የበሽታ ምልክት የማያሳዩ ሰዎች ለቫይረሱ መተላለፍ ብቻ ሳይሆን በፍጥነት ለመሠራጨት ምክንያትም መሆናቸው ነው፡፡

ጥሩ ምክር ነው፣ እርስዎም ምክሩን ሰምተው ማስክ አድርገው ሲወጡ ለሌሎቹም ምሳሌ ሰለሚሆኑ፣ ማሰብ ያለብዎት፣ ቫይረሱ ባይኖርብዎት አንኳን፣ ሁሉም ሰው እንደስዎ ማሰክ ካደረገ፣ ካለባቸው ሰዎች የሚወጣው ቫይረስ ሰለሚገደብ በምሳሌ ያደረጉት ነገር፣ አስዎንም ሆነ ሌሎችን ከመያዝ እንዲከላከል የረዱ መሆኖዎን በማሰብ በሚችሉት መንገድ ሥርጭቱን ለመግታት ከሚታገሉት ወገኖች ራስዎን ይመድቡ፡፡

አሁን፣ ሁላችንም ለተወሰነ ሰከንዶች ቆም ብለን ብናስብና ብንጠይቅ፣ የጤና ባለሙያ ሆኑ ሌላም፣ ማስክዎ  ከፊትዎ የሚያውልቁባቸው ቦታዎችን ይቁጠሩ፡፡

አንደኛው በግልፅ ለብቻዎ ሲሆኑ፣ በመኖሪያ ቤትዎ ወይም በመኪናዎ ውስጥም ሊሆን ይችላሉ

ሁለተኛ፣ ግልፅ የሚሆነው፣ ምግብ ወይም መጠጥ በሚወስዱበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይም ምግብ ሊበሉ ሲሉ ነው፡፡ ጥያቄው ደግሞ የት ነው የሚበሉት ነው፡፡ በሥራ ቦታ ከሆነ የት ክፍል?

ሶሰተኛ፤ ብዙ ሰዎች ወደ መፀዳጃ ክፍሎች ሲገቡ፣ ብዙ ጊዜ የሚያደርጉት ነገር፣ ከአጅ መታጠብ ጋር አፋቸውን ፊታውን መጥረግ አክታ ወይም ምራቅ መትፋትን ይጨምራል፡፡ በዚህኛውም ላይ፣ ጥያቄው፣ መፃዳጃ ቤቱ የት ነው የሚለው ነው፡፡

ከዚህ ቀደም፣ በዚህ በጎሽ ገፅ እንደተገለፀው የሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2፣ በአየርና በዕቃዎች ላይ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል ለሚለው ጥያቄ፣ አጥኝዎች ያካፈሉን ነገር አለ፡፡ ከነሱ አንደኛው፣ ቫይረሱ በተዘጋ ክፍል ወይም አየር እንደልብ በማይዛወርበት ክፍሎች፣ ቫይረሱ ለሶስት ሰአታት ያህል ተንሳፎ ሊቆይ እንደሚቸል ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ በየጊዜው የሚተገበር አዲስ ያልሆነ ነገር፣ በህክምና ተቋሞች ውስጥ፣ እንደዚህ አይነት ተላላፊ በሽታዎች ያላባቸው ወይም የሚጠረጠሩ ሰዎች የሚቆዩበት ክፍል፣ በአንግሊዝኛው Isolation room ተብለው የሚጠሩ፣ በክፍሉ የሚገኘው አየር በዛው በክፍሉ ብቻ እየተዛወረ እንዳይቆይ፣ አየሩን ወደ ውድ መሳብ የሚችሉ መሳሪያዎች የተጠመዱበት ክፍል ነው፡፡ አሁን አንደ የዚህ አይነት ነገር የሌለው ክፍል፣ ደንገት አፍና አፍንጫውን ባልሸፈነ ህሙም ሳልና ንጥሻ ተጋለጠ ቢባል፣ ክፍሉን ለሌላ በሽተኛ ከመጠቀም በፈት፣ ክፍሉ እንደ አየሩ ዝውውር፣ ለአንድ ሰአት ግፋ ሲልም ለሶሰት ወይም አራት ሰአታት ተዘግቶ ይቆያል፣ ለማፅዳት የሚገቡ ሠራተኞች አንኳን ሙሉ መከላከያ ልብስ አድርገው ነው የሚገቡት፡፡ እንግዲህ ወደ ሆስፒታል የዘለቃችሁ ሰዎች፣ የምርመራ ክፍሎችን ስፋት ማስታወስ ትችላላችሁ፡፡ ይህ የሚሆነው፣ ከጥዋቱም ቢሆን በአየር ላይ ተንሳፎ የሚቆይ ቫይረስ መኖሩ ስለሚታወቅ ነው፡፡

ወደ ማስክ ማውለቂያ ቦታዎች ስንመለስ፣ ሥንሠራ ውለን ግን ለምሳ ሰአት ማስኩን ስናወልቅ፣ በተለይ በሥራ ቦታዎች፣ ጠበብ ያሉ የምግብ ቦታዎችን ከሌሎች የሥራ ባልደሮቦች ጋር በመጋራት ነው፡፡ እዚህ ላይ፣ ሰሜት አልባ የሆነ በቫይረሱ የተያዘ ሠራተኛ ቢኖር፣ መጋለጥ ይመጣል፡፡ የቻይና ሆስፒታሎች ይህንን የተገነዘቡት ቀድም ብለው ሰለነበር፣ የጤና ባለሙያ ብቻውን በአንድ ጠረጴዛ እንዲበላ እንጂ ከባልደረባ ጋር እንዳይቀመጥ ይከልክላሉ የሚል መረጃ አይቻለሁ፡፡ ለዚህ ነው፣ ከዚህ ቀደም ምክር ስሰጥ፣ ከቻላችሁ ከነማስካችሁ ወጣ በሉና፣ መኪና ያላችሁ በመኪናችህ ውስጥ ብቻችሁን፣ አለዚያመ ከሌች ሰዎች ራቅ ባለ ሰፋ ያለ ቦታ መመገብ ይመረጣል፡፡

ወደ መፀዳጃ ቤት እንመለስ፣ በአብዛኛው በአንድ ህንፃ ወስጥ ጠበብ ያሉ ክፍሎች መፀዳጃ ቤቶች ናቸው፡፡ ፅሁፌን ሳልጨረስ፣ ነገሩን የደመደማችሁ እንደምትኖሩ ይገባኛል፡፡ መፀዳጃ ቤቶች ደግሞ ሁሉም ሰው ነው የሚገለገልባቸው፡፡ በነዚህ ክፍል ጉሮሮውን የሚያጠራ የሚያስነጥስ ሰውም ይኖራል፡፡ የተያዘም ያልተያዘም፡፡ ወደኋላ መለስ ብላችሁ ካያችሁ፣ ቫይረሱ በአየር ላይ ምን ያህል ሰአት ሊቆይ እንደሚችል፣ በህክምናው አለም ተብክሏል የተባለን ክፍል መልሶ ከመጠቀም በፊት የሚወሰደውን ርምጃ ካስተዋላችሁ፣ መፀዳጃ ቤቶች አደገኛ ሰልፍ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በጋራ የምንጠቅምባቸውን መፀዳጃ ቤቶች ማለቴ ነው፡፡

ሰለዚህ፣ በነዚህ ቦታዎች፣ ማስክዎን ከማውለቅ ይቆጠቡ፡፡ ሌላው እዚህ ላይ መጨመር የምፈልገው፣ የማስኩ የፊት ለፊት በኩል፣ የተጋለጠ በመሆኑ፣ በእጅዎ ከመነካካት ይቆጠቡ፣ ሲያወልቁም በጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡ዋናው ምክር ደግሞ፣ ሁላችንም ቢሆን ቫይረሱ ኖረንም አልኖረንም የምናደርገው ጥንቃቄ ቫይረሱ እንዳለበት እንዲሆን ነው፡፡ አንድ ላይ ተጋግዘን መስራት መቻልና አለመቻላችን የሚፈትን ነገር ነው የመጣብን፡፡

​​የኮቪድ-19 ድብቅ ምንጮ


4/14/20


 ከዚህ ቀደም፣ በኮቪድ-19 የተያዙ የህመም ስሜት ያላቸው ሰዎች፣ ቫይረሱን እንደሚያስተላልፉ የታወቀ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን፣ የዚህን ቫይረስ ፍጥነት የተሞላበትና ስፋት ያለውን ሥርጭት ምክንያት ለማወቅ ባለሙያተኞቹ የተለያዩ መላ ምቶች ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡ ለዚህ በፍጥነት መሠራጨት ምክንያት ናቸው የሚባሉ ሰዎች ደግሞ፣ በቫይረሱ ተይዘው የስሜት ምልክት የሌለባቸው፣ ወይም ዘግይተው የበሽታ ሰሜትና ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች ናቸው፡፡

አንግዲህ አነዚህ ሰዎች ለይቶ ማወቅ ካልተቻለ የበሽታውን ሥርጭት ለማርገብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቀደም ብሎ፣ እዚህም እዚያም በወጡ ፅሁፎች፣ እንዲያውም በአንድ በጣም ቀለል የህመም ስሜት ያለው ሰው፣ ለዛውም ቫይረሱ ለ18 ቀናት የተገኘበት ሰው ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች በቫይረሱ ሳይያዙ ሰለተገኙ፣ ያንን ሪፖርት ያቀረቡ ሰዎች፣ ያሉት ቀለል ያለ ስሜት ያላቸው ወይም ስሜት የማይሰማቸው ሰዎች አያስተላልፉም ብለው ድምድም አድርገው ነበር የተናገሩት፡፡ ከቻይና በኩል አራት አጥኝዎች ደግሞ፣ የለም ይህማ ስህተት ነው አሉ፣ አስጠነቀቁም፡፡ ለነገሩ በአንድ ሰው ተመርኩዞም መመሪያ አይሰጥም በማለት የራሳቸውን አሀዝ ያለበት ፅሁፍ ይዘው ቀረቡ፡፡ መቼም ቢሆን አሀዝ ያለበትን መረጃ የሚያክል የለም፡፡ ቁጥሩን የፃፈው ሰው ይዋሽ እንደሆን እንጂ ቁጥር አይዋሽም፡፡

ወደ ነገሩ ልመልሳችሁ፡፡ ለነገሩ በጣም ወሳኝ ነገርም ነው፡፡

በማርች 28፣ የቻይና ጆርናል ኦፍ ኤፒደሚዮሎጂ የሚባል መፅሄት አትሞ ያወጣው ጥናት የሚያሳየው፣ የክትትል ጥናት በማድረግ፣ 2147 ስሜት የነበራቸውና ሰሜት ያልነበራቸው በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎችን ጋር ቅርበት ያለው ግንኙነት የነበራቸውን ወይም የተጋለጡ ሰዎችን በመከታተል ያገኙትን ውጤት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከተያዙት ሰዎች ጋር በቅርብ ተገናኝተው የተጋለጡ ሰዎች ተለይቶ ሲታይ፣ በቫይረሱ ተይዘው የበሽታ ስሜት ከነበራቸው ሰዎች ጋር የተገናኙ በፐረሰንት 6.3 በቫየረሱ መያዛቸው ሲታወቅ፡፡ በቫይረሱ ተይዘው የበሽታ ሰሜት ካልነበራቸው ሰዎች ጋር የተጋለጡት ደግሞ በፐርሰንት 4.11 የሚሆኑት በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ ይህንን ጥናት ያቀረቡት ሰዎች የሚሉት፣ እውነትም ነው፤ በቫይረሱ ተይዘው የበሽታ ስሜት የሌለባቸው አያሰተላልፉም ተብሎ መዘነጋት አያስፈልግም ነው፡፡

አንዱ ችግር የሆነው፣ የበሽታ ሰሜት አለኝ የለኝም የሚሉት ሰዎች ላይ፣ አንዳንዶቹ፣ ቀለል ያለ የተለየ ስሜት ቢሰማቸው፣ ከበሽታ ስሜት ላይቆጥሩት ይችሉና፣ የለኝም ወይም አልነበረኝም የሚል መልስ ሊሰጡ ይችላሉ ነው፡፡ ይህ እንደ ሰዎች ይለያያል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ፣ በወቅቱ፣ ቫይረሱን ተሸክመው የሚገኙ ሰዎች ምንም የበሸታ ሰሜት የለኝም ቢሉ፣ ከትንሽ ቀናት በኋላ ግን፣ ግልጥ ያለ የበሽት ሰሜት ይታይባቸዋል፡፡ እነዚህ እንግዲህ በአንግሊዝኛው presymptomatic የሚባሉት ናቸው፡፡ በነዚህ አይነት ሰዎች ቫይረሱ ከነሱ ዘሎ ወደሌሎች መሻገሩን የሚገልፅ ጥናትም በይፋ ወጥቷል፡፡ እነዚህም ቢሆን ያስተላልፋሉ ማለት ነው፡፡

ሌላው ነገር፣ እነዚህ የበሽታ ስሜት የሌለባቸው ነገር ግን ቫይረሱን ማስተላለፍ የሚችሉ ሰዎች ለመሆኑ ምን ያህል ይሆናሉ የሚለው ነው፡፡ ይህ በሽታ እንደመጣ፣ እኔም ራሴ የነዚህ ሰዎች ቁጥር መጠነኛ ነው ብለው የሚናገሩ ሰዎችን ተቀብዬ ነበር፡፡ ነገሩ ግን ሌላ ሆኖ ነው የተገኘው (ከውሸቱ ሰላምና መረጋጋት መልክት ጋር የተያያዘም መሰለኝ)፡፡ በሌሎች ሪፖርቶች እንደቀረበው ከሆነ፣ ቫይረሱን ከሚያዛምቱት መሀከል፣ እነዚህ ሰሜት የሌላቸው ሰዎች በፐርሰንት ሲታይ ከ30 አስከ 60 ድረስ ይሆናል ነው የተባለው፡፡ ይህ በጣም ትልቅና አስፈሪ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም፣ እነዚህ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘናል የሚል ሀሳብም ሰሌላቸው ጥንቃቄም ሰለማያደርጉ ማስተላለፉን ይቀጥላሉ፡፡ የመከላከል ርምጃ መውሰድ ቢያሰፈልግ አንኳን፣ አነዚህን ሰዎች አንዴት አድርጎ መለየት ይቻላል? አንድ ወሳኝ ነገር ቢኖር፣ ስሜት ያለውና የሌለውን ምርመራ ማድረግ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ምርመራ ያደረጉ ጥቂት አገሮች፣ ተሳክቶላቸው፣ ሥርጭቱን ጋብ አድርገውታል፡፡ ሰለዚህ በስሜት ብቻ ተመርኩዞ ሰዎችን መለየት፣ አደጋ ይኖረዋል ይላሉ ፀሀፊዎቹ፡፡ እኔም ይህንን ፍራቻ እኩል ወይም በበለጠ ደረጃ እጋራዋለሁ፡፡

አስቡት እንግዲህ፣ በስሜት ብቻ ሰው የሚለይ ከሆነ፣ እነዚህ ቫይረሱ እያለባቸው ነገር ግን ሰሜት የሌለባቸው ሰዎች ከማን ጋር ይደባለቃሉ? ከሌለባቸው ሰዎች ጋር ነው፡፡ በዚህ መንገድ የውነት ቫይረሱ የሌለባቸው ሰዎች ከነዚህ ስሜት አልባ አሰተላላፊዎች ጋር ሰለሚሆኑ፣ በቫይረሱ ይያዛሉ፣ በሽታውም በዛ ህብረተሰብ ውስጥ ይዛመታል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ በርዕሱ እንደተጠቀሰው፣ ድብቅ የኮቪድ-19 ምንጮች የሚሆኑት፡፡ የታመሙትማ ይታወቃሉ፡፡

ታዲያ ምርመራ በማይደረግበት አካባቢ፣ ማድረግ የሚቻለው፣ ዋናው አማራጭ፣ ሰው ከሰው ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት ማቆም ወይም መቀነስ ነው፡፡ እንግዲህ ተከተት የሚለው መፈክርም የመጣው ከዚህ ነው፡፡ ለማስታወስ ያህል፣ ይህ ቫይረሰ በአፍንጫ ውስጥ ከመጠን በላይ እንደሚከማች መረጃዎች ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ነው ፈንጠር በል የሚለው ምክርም የመጣው፡፡ በርግጥ የሚያስሉና የሚያስነጥሱ ሰዎች፣ በአፍንጫቸው ውስጥ ያለውን ቫይረስ ወደ አየር በደንብ መርጨት እንደሚችሉ ከዚህ በፊት ገልጫለሁ፡፡ ከበድ ከበድ ያሉ ቫይረሱን በብዛት የተሸከሙት በአይን የማይታዩ ጠብታዎች፣ ከንጥሻው ባለቤት ሁለት ሜትር ክልል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አሁን ፍራቻው፣ ሰሜት አልባዎቹም፣ ቫይረስ እንደጉድ በተመላበት በአፍንጫው በኩል ሲተነፍሱም ቫይረሱን አብረው እየረጩት ሰለሆነ፣ እነዚህ ሰዎች በዚህ መንገድ የሁለት ሜትር ክልላቸውን አየር ሊበክሉ ሰለሚችሉ፣ ሁሉም ሰው ማስክ አድርግ ቢባል፣ እነሱም ሲያደረጉ፣ ከነሱ የሚወጣው ቫይረስ በማስኩ ተገድቦ ይቀራል፡፡ ለዚህ ነው፣ ሁሉም ሰው ማስክ አድርጎ ይዘዋወር የተባለውም፡፡ ዋናው ምክንያት ይህ ነው፡፡

አሁን፣ ማን ቫይረስ እንዳለበት ወይም እንደሌለበት ማወቅ አይቻልምና፣ ራቅ ራቅ በሉ ባካችሁ ቢባል መተባበር ነው እንጂ መልሶ መጋፋት ወይም ያልሆነ ምክንያት መሥጠት አግባብ አይደለም፡፡ ሰሜት አልባዎቹ ምንም ባይሆኑም፣ ለሌሎች አቀባይ ወይም አሻጋሪ ስለሚሆኑ፣ በዚህ ቫይረስም የሚሞቱ ሰዎች ሰላሉና ሰለሚኖሩ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ሌሎቻችንም ቢሆን፣ አነዚህ ሰብሰብ የማይሉና ለቫይረሱ መሠራጨት ምክንያት የሚሆኑ ሰዎችን፣ “አይሰሙም” ብሎ መተው አይቻልም፡፡ ሰለዚህ ሁሉም ሰው አስተማሪና መካሪ መሆን አለበት፡፡ እንደዚህ አይነት ሰሜት አልባ የሆኑ ሰዎች ሲያሰተላልፉት ሰንብተው፣ በበሽታው የሚጎዱ ሰዎች እስኪደረስ ድረስ፣ የተወሰነ ፀጥ ያለ ወይም የሚመስል ጊዜ እንደሚወስድ አይተናል፡፡ በአሜሪካ፣ የኒው ዮርክ ስቴት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ሰለዚህ፣ የታመሙ ሰዎች፣ የሞቱ ሰዎች ካላይን አናምንም ለሚሉ ሰዎች፣ እነ ስሜት አልባን ማስታወስ የግድ ነው፡፡

ለምንጭ ከተጠቀምኩበት ፅሁፍ ዋነኛው መረጃ

Asymptomatic and Presymptomatic Infectors: Hidden Sources of COVID-19 Disease
Guanjian Li, Weiran Li, Xiaojin He and Yunxia Cao

በሚያስነጥሱበት ጊዜ፣ ከአፍንጫ ወይም ከአፍ የሚወጣው በአይን የማይታየው ጠብታ ምን ያህል ርቀት ይሄዳል? 4/9/2020 

ይህን ማወቅ፣ ተላላፊ በሽታዎች፣ አንደ ኢንፍሉዌንዛ፣ አሁን ደግሞ እንደ ሳርስ ኮቪ-2 የመሳሰሉትን ለመከላከል የሚወሰደውን ርምጃ ያጠናክራል፡፡ በባለሙያተኞቹ በኩል የምናውቀው ነገር ቢኖር፣ ስድስት ጫማ ርቀት ወይም ሁለት ሜትር ነው፡፡ አሁን በኮሮና ጊዜ፣ የተለያዩ ርቀቶች ሲነገሩ መስማት ብቻ ሳይሆን በዛ ተመሠርቶ ምክር ሲሰጥም አይተናል፡፡

ለመሆኑ የስድስት ጫማ ርቀት ዙሪያ ለአመታት አንደ መከለያ ሆኖ ሲወሰድ የነበረው መረጃ ይኖረው ይሆን ለሚሉ ሰዎች፣ ከዚህ ቀደም ከወደ ቦስተን አጥኝዎች ያገኙትን ውጤት፣ ኒው ኢንግላንድ የተባለ መፅሄት አካፍሎናል፡፡ የጥናቱ ውጤት የታተመው እኤአ በ2016 ነው፡፡

አጠገባችን ሰው ቢያስነጥስ ከሰውየው የሚወጡ ለአይን የማታዩ ጠብታዎችና droplet ብናኞቹ ምን ያህል ርቀት ይሄደሉ በሚል፣ በቪዲዮ የተደገፈ ጥናት አደረጉ፡፡ ይህም አንድ ሰው ሲያሰነጥስ ነው፡፡ ማሰነጠሱም ምንም ሌላ የሚያባብስ ወይም የሚያጠናክር ነገር ሳይደረግበት ሰው በተፈጥሮ እንደሚያስነጥሰው ባለበት ሁኔታ ነው የተለካው፡፡

በጥናቱ መሠረት፣ በየ2 ሚሊ ሰከንድ ፎቶ እየተነሳ፣ ከጤነኛው ሰው ንጥሻ የሚወጡትን ጠብታና ብናኞች እየተከታተሉ ነበር፡፡ በዚህ በከፍተኛ ፍጥነት ቪዲዮ በሚቀርፅ ካሜራ በመጠቀም በየጊዜው፣ ከሰውየው ንጥሻ የወጣውን ጉም የመሰለ ነገር እየተከታተሉ ያዩትና የዘገቡት ነገር፣ ከበድ ከበድ ያሉት ጠብታዎቸ (droplet) ከሰውየው አንድና ሁለት ሜትር ርቀት አካባቢ ሲቀሩ፣ በጣም ትንንሾቹ ደግሞ፣ እንደ ብናኝ በመሆን በአየር ላይ ከሰከንዶች አስከ ደቂቃዎች ድረስ ዘግየት ብለው ከተንሳፈፉ በኋላ በክፍሉ ውስጥ ከስድስት አስከ ስምንት ሜትር ርቀት ድረስ መጓዛቸውን ዘግበዋል፡፡ (ምንጭ New England Journal of Medcine)

እንግዲህ በአይን የማይታይ ጠብታ ወይም በ droplet ይተላለፋል ሲባል፣ በቪዲዮው የተቀረፁት ከበድ ከበድ ያሉት ከሰውየው ሁለት ሜትር ዙሪያ አካባቢ የሚቀሩትን ለማለት ነው፡፡

ተላላፊ በሽታም ኖረም አልኖረም፣ አፍና አፍንጫውን ሳይሸፍን የሚያሰነጥስ ሰው፣ አካባቢውን እንደሚያዳርሰው ከተረዳን፣ እንደ ባህል አድርገን፣ የግድ ማድረግ የሚገባን ነገር፣ ንጥሻና ሳልን ቢቻል በሌላ ነገር አለዚያ በክንዳችን መሸፈን የግድ ነው፡፡

አሁን እያሰባችሁት ያለውን ነገር መገመት ብችል፣ የሚሆነው፣ እነዛ ቀለል ያሉ ብናኞች እስከ ስምንት ሜትር ርቀት ድረስ ከሄዱ፣ እንዴት ነው አደጋ አለው ወይ የሚል ጥያቄ ነው፡፡

ቫይረስም ሆነ ባክቴሪያ በተለያዩ መንገድ ወደ ሰዎች ሲዘልቅ ወደ ኢንፌክሽን ለመቀየር የሚያሰፈልገው አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም አየሩን ወይም ዕቃንም ሆነ ምግብን የበከለው ቫይረስ መጠን ምን ያህል ነው የሚለው ነው፡፡ በእንግሊዝኛ load ይባላል፡፡ ያ ማለት በጠብታም ሆነ በብናኙ ውሥጥ የቫይረሱ መጠን ምን ያህል ነው? እንደተረዳነው፣ ከበድ ባሉት፣ ርቀት መሄድ ባልቻሉት ጠብታዎቸ ውስጥ ከፍተኛ የቫይረስ መጠን አለ፡፡ ያን ያህል መጠን በሰው የውስጥ ሰውነት አልፎ ሲገባ እንደገና ተራብቶ ብዛቱን በመጨመር በሽታ ወይም ተሸካሚ የማድረግ ችሎታ አለው ማለት ነው፡፡ የዚህ የቫይረስ መጠን በራሱ ልኬታ አለው፡፡ ቫይረሶች ወይም ባክተሪያው እንደ ሀይለኝነቱ፣ በሽታ ሊያስከትል የሚችለው መጠን ይለያያል፡፡ ሰለዚህ እነዚያ ራቅ ብለው የሚሄዱት ብናኞች በቂ የቫይረስ መጠን ላይዙ ስለሚችሉ ለአደጋ አያጋልጡም ይሆናል፡፡ ይልቅስ በሰውየው ሁለት ሜትር ዙሪያ በሰከኑት ከበድ ያሉት droplet ላይ እናተኩርና፣ ኮሮናን ለመከለካል፣ ስድስት ጫማ ወይም ሁለት ሜትር ራቅ በል የሚለውን ምክር ተግባራዊ እናድርግ፡፡ ከዚህ ሁሉ፣ አለመውጣትና አለመጋለጥ አይበልጥም ወይ? ሥርጭቱን ያቀዘቀዝው የተረጋገጠው መንገድ ደግሞ ይሀ አለመገናኘቱ ነው፡፡ የሰዎች እንቅስቃሴ ከተገታ፣ ቫይሱን ከሰው ወደ ሰው ወይም ከቦታ ወደ ቦታ ማሻገሩ ይቀንሳል፡፡ ሰለዚህ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ከሌሉ፣ የተያዙት ባብዛኛው በማገገም፣ ከሰውነታቸው ውስጥ ቫይረሱን ሰለሚያስወግዱ፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በአብዛኛው ለሥርጭት የሚሆነው የቫየረስ ምንጭ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ አሁን የሁሉም ጥረት ሌላ አዲስ ሰው እንዳይያዝ ጥረት ማድረግ ነው፡፡

 የሚያስነጥስ ወይም የሚያስል ሰው ደግሞ፣ ይህንን መልክት ካነበበ፣ ካልሸፈነ በሰተቀር አካባቢውን እንደሚያልበሰው ተገንዝቦ፣ ሳልና ንጥሻውን ሸፈን ያድርግ፡፡ ካሁን በኋላ፣ ሳይሸፍኑ መሳል ወይም ማስነጠስ የሚያሳፍር ነገር ይሆናል ማለት ነው፡፡ 


በሌላ የደረሰው እንዳይደርስ… አዲስ ምክር 4/8/2020

ሱቅና የተለያዩ ስቶር ባለቤቶች ኮሮናን ለመከላከል አስፈላጊ ምክር 

ከዚህ ቀደም በድረ ገፁም ሆነ በተለያዩ መገናኛዎች ሰለ ሳርስ ኮቪ ቫይረስ ቁጥር ሁለት (SARS-CoV-2) ፣ ወይም ሰለሚያስከትለው በሽታ ኮቪድ-19 (COVID-19 ኮሮና ቫይረስ ዲዚዝ በ2019)፣ አጠቃላይ ምክርና ትምህርት ለመሥጠት የሚቻለው ተደርጓል፡፡ ምክሩን ሰምተው በቂ ጥንቃቄ ያደረጉ ዜጎች እንዳሉም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
     ዋናው ነገር፣ በዚህ ጉዳይ ከሚገባው በላይ መሸበርና መጨነቅ አስፈላጊ አይደለም፡፡ መሸበር ወይም መጨነቅ የሚመጣው፣ አንደኛ፣ ሰለ ቫይረሱ በቂ ግንዛቤ ወይም ዕወቀት ሳይኖር ሲቀር፤ ሁለተኛ ደግሞ፤ ምን ማድረግ እችላለሁ ወይስ ምን እንናድርግ ለሚለው በቂ ዝግጅት ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡
     ይህንን ሁሉ በማየትም፣ በዚህ ፓንደሚክ በኩል በተለያዩ ተቋማት የደረሰውን ወይም እየደረሰ ያለውን ችግር በመመልከት፣ ከአጠቃላይ ምክር ገባ በማለት ዘርዘር ያለና ጠለቅ ያለ ምክር መሥጠት የግድ ነው፡፡
     በዚህ ቁጥር አንድ ምክር ርዕሱ በሌሎች የደረሰው እንዳይደርስ የሚል ነው፡፡
    ይህ ምክር በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የደረሰውን ችግር ከማየት የመነጨ መሆኑንም እንድትገነዘቡ ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው ይህንን ፓንደሚክ ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ፣ አሳዛኝ የሆኑ የተለያዩ አመለካከትና ሀሳቦቸ ሲሠጡ ከርመዋል፡፡ ያም በሽታውን እንደሌለ ወይም አንደማይመጣ አድርጎ ከሚሠራጨው ሃሳብና ከመጠን በላይ ፍርሃትና ሽብር የሚያስከትሉ ዜናዎች መለቀቅን ጨምሮ ነው፡፡

አንድ ነገር ሹክ ልበላችሁ

በሽታን መከላከል በእንግሊዝኛ (Infection Control) የሚባል ራሱን የቻለ ከህክምናው ጋር በተጓዳኝ የሚተገበር፣ በሳይንስ የተመረኮዘ ሙያ ነው፡፡ ለአመታት፣ ለእያንዳንዱ ተላለፊ በሸታ ምን አይነት መከላከያ ዘዴ ነው መተላለፉን የሚያስጥለው ተብሎ፣ በተግባር ሲፈጸም የኖረ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ አይነት አስከፊ ሥርጭት አምብዛም አለመከሰቱ፣ ይህን በጀርባ የሚካሄድ ወሳኝ ሙያ ህዝቡ፣ ባለሥልጣናቱ ቀርቶ፣ መሰል ሌሎች የህክምና ባለሙያኞች በውል ሳያውቁት የከረመ ነገር ነው፡፡

እንድ ሌላ ነገር ልናገር፣ ሆስፓታል ገብተው ታክመው የወጡ ህሙማን፣ ለሌላ ጉዳይ ቢገቡም፣ ሆሰፒታሉ ውስጥ የሚዘዋወር ተላላፊ በሽታ በመኖሩ፣ በገቡበት ምክንያ ሳይሆን በተላላፊ በሽታ ምክንያት ታመው ህይወታቸው ማለፉ የአደባባይ ሚሥጥር ነው፡፡ ሌላው ቢቀር፣ የጤና ባለሙያተኞቹ፣ ከህሙማኑ በሚመጣው በሽታ እንዳይያዙ አስፈላጊ ምክርና፣ አንዳንዴም መደርግ የሚገባቸው የመከላከያ ተግባራት በግድ እንዲደረጉ ሰለሚደረግ፣ የሕክምና ባለሙያተኞች በበሽታ ሳይያዙ፣ ወደ የቤታቸውም ተሸክመው ሳይሄዱ መቆየት ቸለዋል፡፡ የሰነበቱትም ለዚህ ነው፡፡፡ ስንት ነብሰ ገዳይ ባክቴሪያና ቫይረስ ያለ ይመስላችኋል?

አሁን ኮቪድ-19 የሚባል ነገር ሲመጣ፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ሰለሙያው አንዳችም ልምድ የሌላቸው ሰዎች እየወጡ ከመናገራቸው በተጨማሪ፣ ክፋት ያስከተለው ነገር ቢኖር፣ የቁሳቁስና የሰው ሀይል ዕጥረት በመከሰቱ፣ ለአመታት ስንገለገልባቸው የነበሩ የመከላከያ ዘዴዎች፣ ከደረጃ በታች በሆነ መንገድ እየተቀየሩ በመመሪያ መልክ ሲወጡ አስተውለን፣ ተንገሽግሸናል፡፡ የህክምና ባለሙያተኞችም፣ ለዚሁ አደጋ በሚጋለጡበት ደረጃ ሥራ እንዲሠሩ እየተደረገም ነው፡፡ ባለሙያተኞቹ፣ ሰው ለመርዳት ባላቸው፣ የውስጥ፣ ከልብ የመነጨ ሰብአዊነት ምክንየት፣ እያወቁ አደጋ ላይ የወደቁ ህይወታቸውም ያለፈ ብዙ ናቸው፡፡ ሌላው፣ ቫይረሱንና በሸታውን እንደ አመጣጡ ከማየት ይልቅ፣ ለሚያሰከትለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግር ቅድሚያ የተሠጠበት ነገር በገሀድ የታየ ነው፡፡

ምን ለማለት ነው፡፡ ሰለ ቫይረሱና ሰለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ካለ፣ ሰለመከላከያና ስለሚደረገው ጥንቃቄ፣ ምክርና መመሪያ ከሚያወጡ ወገኖች ወይም አመራሮቸ ከሚሠጡት በላይ አስፈላጊውን መከላከል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ሰፊ መግቢያ ነው የሆነው ወደ ምክሩ እንሂድ

በሌላ የደረሰው እንዳይደርስ

በዚህ ግብግብ ለአደጋ በጣም ከተጋለጡ ወገኖች መሀል አንዱም በመሆኔ፣ ከአንድ ሁለት ወይም ሶሰት ጊዜ ሊደርስ ከሚችል ችግር በመትረፌ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ ተመልከቱ፣ የህክምና ባለሙያተኛቸ (ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ረዳቶች፣ ሌሎችም በኤክስ ሬይ፣ በሌላም ተግባር ከበሸተኛ ጋር የሚሠሩ ባለሙያተኞች በሙሉ) የኮቪድ አደጋ የሚመጣባቸው ከተለያየ አቅጣጫ ነው፡፡

1ኛ. እንደማንም የህብተሰቡ አባል፣ ከቤት፣ ከዘመድ ከጓደኛ በኩል

2ኛ. በሥራ ምክንያት፣ በኮቪድ-19 የተያዙ ወይም የሚጠረጠሩ ህሙማን

3ኛ. በቫይረሱ መያዛቸው ያልታወቀ፣ ጤናማ የሚመስሉ ግን ለሌላ ህክምና ርዳት ወደ ህክምና ተቋማት የሚዘልቁ ሰዎች

4ኛ. በጣም አሳሳቢ የሆነውው ደግሞ፣ የራሳቸው የሥራ ባልደረቦች፣ የስሜት ምልክት እያላቸው ግን ሳያገናዝቡ ወደ ሥራ የሚመጡ

5ኛ› የሥራ ባልደረቦች፣ ባቫይረሱ ተይዘው ግን ስሜት የሌለባቸው ወደ ሥራ የሚዘልቁ ናቸው፡፡

በቁጥር 4ና 5 ያሉት፣ አደጋውን የሚጨምሩት፣ እነሱ ይያዙ አይያዙ በቂ የቁጥጥር ዘዴ ባለመተግበሩና፣ የለባቸውም ተብሎ ስለሚታሰብም፣ ከውስጥ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ያለ መከላከያ ተቀላቅለው ስለሚሰሩ ነው፡፡ የማካፍላችሁ ነገር፣ የህክምና ባለሙያተኞች በቫይረሱ መያዛቸው፣ የተወሰኑትም ህይወታቸው ማለፉ፣ በሥራ ላይ ያሉትም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ጭንቀት የፈጠራባቸው መሁኑን ነው፡፡

እዚህ ላይ ትንሽ ቆም እንበልና እናስብ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ወይም አደጋ ውነት በህክምና ሠራተኞች አካባቢ ብቻ የሚከሰት ነገር ነው ወይ?

አይደለም፡፡ ማንኛውም፣ ለሌሎች ሰዎች አገልግሎት የሚሠጥ ድርጅት ወይም ተቋም ከዚህ ወገን በምንም መንገድ አይለይም፡፡ የመለየው ነገር ቢኖር፣ የታወቁ ታማሚዎች ጋር አለመጋለጥ ነው፡፡ ነገር ግን፣ በጣም በፀና ከታመሙት ይበልጥ፣ በጣም ያልታመሙ፣ እንዲያውም የበሽታ ምልክት የሌለባቸው ቫይረሱን የሚያስተላልፈ ሰዎች ናቸው ሥርጭቱን ያባባሱት፡

 በዚህ ሁኔታ ባላቸው የሥራ ፀባይ ልክ እንደ ጤና ተቋሙ ሊጋለጡ የሚችሉ ወገኖች፣ ሰፊም ሆነ መጠነኛ ሱቆች፣ ወይም ሌላ አገልግሎት የሚሠጡ ናቸው፡፡ ሰለዚህ ነው፣ ሱቆች ያላችሁ ወይም በተመሳሳይ ሁኔታ የንግድ ሥራ ያላችሁ ሰዎች በጥሞና ማንበብ የሚገባችሁ፡፡ እንደ ህክምና ባለሙያተኞቹ ሁሉ፣ ተመሳሳይ ሁኔታ አለ፡፡ በተለይ፣ ለአግልግሎት የሚገባውን ደንበኛ ለይቶ ማወቅ አለመቻሉና፣ እንደ ህክምና ባለሙያተኞቹ በቫይረሱ ላላመያዝ ሙሉ ትጥቅ መልበስ አለመቻሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥል፡፡

ምክሩ በተራ ቁጥር የሚከተለው ነው፡፡

1ኛ. እንደ ማንኛውም የህብረተሰቡ አባል መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ማድረግ

2ኛ፡ በሥራ ቦታችሁ፣ ደንበኛው በቂ ርቀት አንዲኖረው (ስድስት ጫማ) አድርጎ መገበያየት፣ ይሉኝታ አይሠራም

3ኛ. ቢቻል፣ ወደ ሱቅ የሚገባው ደንበኛ፣ ሳልና ማስነጠስ ካለው፣ ማስክ ሊለበስ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር፡፡ ይህም ከውጭ በኩል በበቂ ማስታወቂያ በማሳየት ወደ ሱቅ ከመግባቱ በፊት፡፡ ችግሩ የማስክ ዕጥረት ነው፡፡ አሁን ግን፣ ይሀ አሠራር፣ በተለይ፣ ሁሉም ሰው ማስክ ማድረግ እንዳለበት ሰለተነገረ ችግር አይፈጥርም፡፡

4ኛ. ደንበኛው በእጆቹ ያመላለሳቸውን ዕቃዎች ደጋግሞ ከመንካት መቆጠብ፣ ከነኩም (ለሽያጭ ሲባል) በአልኮል መወልወል፡፡ ዋናው ግን፣ ሠራተኛው፣ እጁን ካልታጠበ ወይም በአልኮል ካልወለወለ በስተቀር፣ አፍንጫ፣ አፍና አይን እንዳይነካ ወይም እንዳትነካ ማድረግ

5ኛ. ዋናው ደጋግመን ማስታወስ የሚገባን ነገር፣ የዚህ ቫይረስ መተላለፊያ መንገድ፣ ዋነኛው በመተንፈሻ አካል የወጣው በአይን የማይታይ ቫይረሱን የተሸከመው ጠብታ፣ ወደ ሌላ ሰው አፍ፣ አፍንጫ አይን ሲዘልቅ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ተገልጋዩ ደንበኛ ማስክ ካደረገ፣ ከፍተኛው አደጋ ቀነሰ ማለት ነው፡፡

ከላይ በህክምና ባለሙያተኞች ካስተዋላችሁ፣ አብዛኛው አደጋ የተከሰተው፣ ካልጠረጠሯቸው ከራሳቸው የሥራ ጓደኞች ነው፡፡ በተለይም በተመላላሽ ህክምና ከፍል ለሚሠሩ ባለሙያኞች በስፋት መጋለጥ የመጣው ከስራ ባልደረቦቻቸው ነው፡፡ የታመሙ አሉ፣ በብዛት ግን፣ መጋለጣቸው ሲታወቅ፣ ገለል ብለው እንዲሰነብቱ ስለሚደረግ፣ ለአስራ አራት ቀናት፣ የሠራተኛ ዕጥረት መፈጠሩም ሌላው ችግር ነው፡፡ የሥራ ጓደኞቻቸው ደግሞ፣ በቫይረሱ የተያዙት ከሥራ ቦታ ሳይሆነ፣ ከቤታቸው ወይም ከህብረተሰቡ መሆኑ ነው፡፡

ሰለዚህ፣ በሱቆችና በሌሎች ለደንበኞቸ አገልግሎት የሚሠጡ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በተመሳሳይ ሁኔታ የሥራ ባልደረቦቻቸውን ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡ ከልምድ እንዳየነው፣ የበሸታ ስሜት ምልክት እየተሰማቸው፣ ነገር ግነ፣ ገቢውንና ሥራዬን አጣለሁ በሚል ፍራቻ ዝም ብለው ወደ ሥራ ቦታ የዘለቁ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ባለሙያተኞች ማየት ችለናል፡፡

ስለዚህ በዚህ በኩል የሚጣውን አደጋ ለመቀነስ

1ኛ. ከቤትም ሆነ ከህብረተሰቡ ለቫይረሱ ተጋልጦ መጠነኛ ሰሜት ያለው ሰው፡፡ ከሥራ ሃላፊዎች ጋር ተነጋግሮ ወደ ሥራ አለመዝለቅ

2ኛ› ድንገት ከዘለቀም፣ የዚሀህ ሰው ቫይረስ ወደ ሌላ እንዳይሻገር በከፍተኛ ደረጃ ሊከልክል የሚችለው ማስክ ሰለሆነ፣ ወደ ሥራው ከመግባቱ በፊት ማስክ ማድረግ

3ኛ. ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሰዎች የበሽታ ስሜት ሳያሳዩ፣ ቫይረሱን ማስተላለፍ መቻላቸው የተረጋገጠ በመሆኑ፣ ሁሉም ወደ ሥራ የሚመጣ ሰው ማስክ እንዲያደርግ ማድረግ

4ኛ. ማስኩ፣ ካለቆሸሸ በሰተቀር፣ ለረዥም ጊዜ መደረግ ይችላል፡፡ ሰለዚህ ማስኩ መውለቅ የሚገባው፣ ወይም ከሱቁ ወይም ከሥራ ቦታው ወጣ ተብሎ መሆን አለበት፡፡ ማስኩ በውጩ በኩል ሊጋለጥ ሰለሚችል (ለመጋለጡ ጥናት አለ) ማስኩን በየጊዜው መነካካት አያስፈልግም፡፡ ከነኩ ግን እጅን ለሀያ ሰክንድ በሳሙናና በውሀ መታጠብ፣ አለዚያም 60 ፐረስንት አልኮል ባለው እጅቻውን መወልወል ነው፡፡ ይህ አሰራር፣ ሁለተኛውን የመተላለፊያ መንገድ መቀነስ ይችላል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ከአሰሪ ጀምሮ እስከ ሠራተኛ፣ ሙሉውን ገዜ ማስክ መልበስ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ደንበኛው፣ ማን እንደያዘው ማን እንዳልያዘው ስለማይታወቅም ነው፡፡ በዛው ልክም የሥራ ባለደረባም ቢሆን ማን እንዳለው ወይም እንደሌለው አይታወቅም፡፡

5ኛ. ሠራተኞች፣ ለእረፍት ሲወጡና ምግብም የሚበሉ ከሆነ ብቻቸውን እንዲቀመጡ ማድረግ፣ ከፊት ለፊት፣ ሌላ ባልደረባ አብሮ እንዳይቀመጥ ማድረግ፡፡ ምግብ ሲበሉ ማስክ ሰለሚያወልቁ፣ በሥራ ቦታው ውስጥ ለምግብ በቂ ቦታ ሰለማይኖር፣ መኪኖቻቸው ውስጥ ተመግበው ቢመለሱ፣ ለነሱም ሆነ ለሌላው ሠራተኛ ጥሩ ነው፡፡

6ኛ. በሥራ ቦታው እያሉ፣ በየትኛውም ቦታ ማስኩን ማውለቅ የለባቸውም፡፡ በተለይም መፀዳጃ ቤቶች ወይም ሌሎች ጠበብ ያሉ የሥራ  ክፍሎች፡፡ ለዚህም፣ ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገፅ እንደተቀመጠው፣ ከመተንፈሻ አካል በእንጥሻ የሚወጣው ቫይረስ፣ ጠበብ ባለ ወይም በተዘጋ ክፍል፣ ለሶስት ሰአታት በአየር ላይ ይቆያል፡፡ ሰለዚህ ተጠቃሚዎቸ፣ ከነሱ በፊት መፀዳጃ ቤቱን ማን እንደተጠቀመ ሰለማያውቁ፣ ማስካቸውን ሳያወልቁ መገልገል አለባቸው፡፡ እነሱም ድንገት ቢኖራቸው፣ ከማስነጠስና ክፍሉን በቫይረስ ከማጋለጥ ይቆጠባሉ ማለት ነው፡፡

7ኛ. ሥራቸውን ጨርሰው ሲወጡ፣ ማስኩ መውለቅ የሚገባው ከመሥሪያ ቦታው ወጣ ወይም ራቅ ብለው መሆን አለበት፡፡ በር አካባቢ ምን እንዳንዣበበ ማወቅም ሰለማይቻል ነወ፡፡ ነገር ግን ከቤት ውጭ ማስክ መልበሱም ሰለሚደገፍ፣ ማውለቁ ተገቢም አይደለም፡፡

8ኛ› ሲገቡም ሆነ፣ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት እጅ መታጠብ በዛው ልክም ሥራ ጨርሰው ሲወጡ እጅ መታጠብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም፣ መኪና የሚያሽከረክሩ ሰዎች፣ ወደ መኪናቸው ምንም ነገር ይዘው ላለማስገባት መጣር አለባቸው፡፡ መኪናቸውን በ70 ፐርስንት አልኮል መወልወል፡፡ በተለይም በእጅ አዘውትውረው የሚነኩ ነገሮችን ማለት ነው፡፡

9ኛ. ወጭ በዛ ካላላችሁ፣ የቀረው ነገር ልብስ ነው፡፡ በኛ ሙያ ልብሳችን በጣም ተጠንቀቀን ነው የምንይዘው፡፡ አብዛኛው የህክምና ባለሙያ የለበሰውን ለብሶ ወደ ቤት፣ ወደ ውስጥ አይገባም፡፡ የህክምና ባሙያኞች የሚለብሱትን አይታችኋል፡፡ ታዲያ፣ ያንን ልበሱ ሳይሆን፣ በሥራ በታ ብቻ የሚለበስ እንደ ካፖርት የመሰለ፣ ወይም ሀኪሞች የሚለብሱት አይነት ጋወን ማዘጋጅትና በሥራ ቦታው እሰካሉ ድረስ አሱን መልበስ፣ ከሥራ ሲወጡ ማውለቅ ይረዳል፡፡ ለአእምሮም እረፍት ነው፡፡ ነጭ የሀኪም ኮት እኮ ለመለያ ብቻ አይደለም የሚለበስው፡፡ መከለያም ነው፡፡

10ኛ› ይህ ሁሉ ሆኖ፣ ድንገት የተጋለጡ ከመሰለዎት፣ ራስዎን አዳምጡ፣ የበሸታ ስሜት ካለብዎት፣ ወደ ሥራ አይሂዱ፣ ርግጠኛ ነኝ፣ አሠሪዎ ያመሰግንዎታል፡፡ ከሄዱ ግን፣ ጓደኛም ይጋለጣል፡፡ ሱቅም ይዘጋና ሥራዎን መልሰው ያጣሉ ማለት ነው፡፡ ድንገት ከተገኘብዎት ደግሞ፣ ሥራ ጓዶችዎን ደውሎ መንገር ጥሩ ነው፡፡ መቼም እነሱ ተጋልጠው ቢሆን እንኳን፣ ወደሌላ የቤተሰብ አባል፣ በቫይረሱ ከተያዘ አደጋ ላይ ሊወድቅ ወደሚችል ሰው እንዳያዳሻግሩት ነው፡፡ በአሜሪካ ከሆነ፣ የምትኖሩበት ሰቴት፣ ይህንን ነገር አጣርቶ መጠየቁ አይቀርም፡፡ የመንግሥት ህግም ነው፡፡


የፊት ማስክ አጠቃቀምን በተመለከተ አዲስ ምክር                          (04/03/2020) 

እንደ ተለመደው በዚህ ኮቪድ-19ን በተመለከተ ሁኔታዎች በየጊዜው እየተቀያየሩ፣ ከዚህ በፊት ይሠጡ የነበሩ ምክሮች እየተለወጡ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ከዚህ በፊት የሚለገሱ ምክሮች በነበረው መረጃ ተመርኩዘው ቢሆንም፣ በቁሳቁሶች ዕጥረት ምክንያት ፣ ቅድሚያ ሲሰጥ የነበረው ቁሳቁሶች ለባለሙያተኞች አገልግሎት እንዲውሉ ነበር፡፡
ከነዚህ አንዱ ሲሠጥ የነበረው ምክር፣ የፊት ማስክን በሚመለከተ ነበር፡፡ በዚህም የበሸታ ስሜት የሌለባቸው ሰዎች ማስክ እንዳያደርጉ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ሆኖም በሚከተሉት ሁኔታዎች ምክንያት፣ ያንን ምክር መቀየር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

1ኛ. ቫይረሱ የበሽታ ስሜት በሌለባቸው ሰዎች አማካኝነት እየተሠራጨ በመገኘቱ፣ ለሥርጭቱ መጠንከር  ምክንያት በመሆኑ

2ኛ. የበሽታው ምልክት የሌለባቸው ሰዎች፣ ሳያስነጥሱና ሳያስሉ በመተንፈስ ብቻ ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ሰለሚችሉ

ማንኛውም ሰው ከቤቱ ወጥቶ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ፊቱ ላይ ማስከ እንዲያደርግ ምክር እየተሠጠ ነው፡፡
እንግዲህ ማስክ ሲደረግ፣ አፍንጫና አፍ በደንብ መሸፈን አለበት፡፡ ትንፋሽ በጎን በኩል የሚወጣ ከሆነ፣ ጠቀሜታው ሙሉ በሙሉ አይደለም፡፡
ሁሉም ማስክ እንዲለብስ የሚመከረው፣ ድንገት በቫይረሱ የተያዘ ሰው ቢተነፍስ፣ ቢያስነጥስ ወይም ቢያስል፣ ከሰውየው የሚወጣው ቫይረስ በማስኩ ተሸፍኖ ሊቀር ሰለሚችል ወደ ሌላ ሰው የመሻገሩን ወይም የአካባቢ ቁሳቁስ ላይ የማረፉን ዕድል ሰለሚቀነሰው ነው፡፡ ቢዘህ ወቅት ማን እንደተያዘ ማወቅም ሰለማይቻል፣ ሁሉም ሰው ማስክ እንዲያደርግ የተሠጠውን ምክር እንደግፋለን፡፡ በመሆኑም፣ ከቤት ሰትወጡ ማስክ ማድረግ እንደምትችሉ እናስገነዝባለን፡፡

መታወስ የሚገባው ይህ ምክር ድንገት የተያዘ ሰው ሊያስተላልፍ እንዳይችል ለማድረግ ነው፡፡ ሆኖም፣ አፍንጫና አፋቸውን የመነካካት ልማድ ያላቸው ሰዎችን ሊከላከል ስለሚችል፣ በንክኪ የሚመጣውን መተላለፍ ሊቀንሰው ይችላል፡፡ በኔ በኩል አንድ የምጨምረው ነገር ቢኖር፣ በማስክ ቢሸፈኑም፣ አይን ክፍት ሰለሚሆን፣ የአይን መከለያ መነፀር ማድረግ ሊረዳ ይችላል፡፡ በዚህ ላይ ግን ያንን ያደረጉትን መነፀር ማፅዳት አንደሚኖርብዎት እመክራለሁ፡፡ መነፀርዎ በሰባ ፐርስነት አልኮል መፅዳትም ይችላል፡፡ ይችላል፡፡ አሁንም ቢሆን፣ ማስክ ማድረጉ፣ ከሚደረጉት መከለከያዎች ተደራቢ እንዲሆን ነው ምክሩ፡፡ ሰለዚህ፣ መዘናጋት ሳይኖር

ላለመያዝ ጥረት ማድረግ፣ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር በየቤታችሁ እንድትገደቡ
ከወጣችሁም፣ የስድስት ጫማ ርቀት (ሁለት ሜትር) እንድትጠብቁ
በአጃችሁ ዕቃዎችን ከመነካካት መቆጠብ፣ ከነካችሁም ፣ወይም ወጥታችሁ ከገባችሁም በደንብ በውሃና በሳሙና ለሀያ ሰክንዶች መታጠብ፡፡ አለዚያም ከስልሳ ፐርስነት አልኮል ባለው መወልወያ እጃችሁን መወልወል፡፡ አለዚያም ፊታችሁን (አፍ፣ አፍንጫ፣ አይንን ከመነካካት መቆጠብ)
የምትነኳቸውን ዕቃዎችና መኖሪያ ቤታችሁን በተገቢው ኬሚካል ማፅዳት
የእጅ ስልክዎን፣ የሚገለገሉበትን ቁሳቁስ፣ ኮምፒተር፣ ላፕቶፕ የመሳሰሉትን በ70% አልኮል መወልወል፡፡
የሚያሽከረክሩትን መኪና መሪና ሌሎች ክፍሎችን በተደጋጋሚ ማፅዳት
ቤትዎም ውስጥ፣ የበር እጀታ፣ ማብሪያና ማጥፊያዎችን፣ ባጠቃላይ ሰዎች አዘውትረው የሚነካኳቸውን ዕቃዎች ማፅዳት 
ድንገት የተጋለጡ ከመሰለዎት፣ ራስዎን በቤትዎ አግልለው መቀመጥ
የህምመም ስሜት ከተሰማዎት ደግሞ፣ ከቤተሰብ ተነጥለው መቆየት
ከታመሙ፣ የቤት እንስሳትን ከመነካካት ወይም ከማቅረብ መቆጠብ አለብዎት፡፡

​​​የእናት ሆድ ዥጉርጉር
አዲሱ ኮሮና ቫይረስ አንድ ወጥ አይደለም 03/26/2020 


የተላላፊ በሽታ ባለሙያተኞችንና ሌሎችን የጤና ባለሙያተኞችን እንቅልፍ የሚነሳ ነገር ልነገራችሁ፡፡ በተለይም በቫይረሶች በኩል ነው ይህ ትልቅ ፍራቻ የሚታሰበው፡፡ ቫይረሶች አንደማንኛው ህይወት አለው እንደሚባል ፍጥረት፣ መኖር፣ መቆየት መራባት ባሕሪዎች ይታይባቸዋል፡፡ ይፈልጉታልም፡፡ አንድ ቫይረስ ከጥዋቱ ጀነቲክ መሠረት አለው ማለትም የዘር ግንድ ወይም የዘር ሰንሰለት አለው፡፡ በዚህ የዘር ስንሰለት አማካኝነት የቫይረሱ ባህሪ ይመሠረታል፡፡

አንዳንድ ቫይረሶች እንደ ሜርስ ኮሮና ቫይረስ አይነት በከፈተኛ ደረጃ ሰው ይገላሉ፤ ነገር ግን የሚጎላቸው ባህሪ ቢኖር፣ በሰው፣ ላይ ከሰው ወደ ሰው የመሻገር ችሎታቸው ደካማ ነው፡፡ (በዚሁ ያስቀርልን)፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የወፍ ኢንፍሉዋንዛ የሚባለውም አንዲሁ ከሰው ወደ ሰው እንደ ልቡ አይሸጋገርም፡፡ መደበኛው የሰው ኢንፍሉዌንዛ ደግሞ፣ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ይሻገራል፡፡ እንደ ሌሎቹ ራቅ እንዳሉት ዘመዶቹ ባይሆንም ለሰዎች ህልፈት ምክንያት ነው፡፡ ይሀ ሁሉ የተለያየ ባህሪ እንግዲህ ባላቸው የዘር ግንድ አማካኝነት ነው፡፡

እንቅልፍ ወደ ሚነሳው ፍራቻ ልመልሳችሁ፡፡ እነዚህ ቫይረሶች የዘር ሀረጋቸውን ማለትም ጀነቲክ ኮዳቸውን በትንሹ መቀየር ይችላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ አንግዲህ በአንግሊዝና ሙቴሽን(Mutation) ይባላል:: ይህንን በሚያደርጉበት ጊዜ አዲስ ባህሪ ያሳያሉ፡፡ በአብዛኛው ይህ የጀነቲክ ኮድ ላይ መጠነኛ ለውጥ ማድረግ፣ ለቫይረሱ የሚመች ባሕሪ እንዲያገኝ ያደርገዋል፡፡ ወይ መድሐኒትን የመቋቋም ችሎታ፣ ወይም በፍጥነት የመዛመት ችሎታ አና ሌሎችም ጠቃሚ ነገሮች እንዲያገኝ ያደርገዋል፡፡ ባህሪው ይቀየራል ማለት ነው፡፡ ሌላው፣ አነዚህ የተለያዩ ቫይረሶች፣ ለምሳሌ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች አንድ ላይ በሚገናኙበት ጊዜ፣ አንደኛው ከሌላኛው ጀነቲክ ኮድ በመዋስ፣ እንዲያውም በእንግሊዝኛ (viral sex) በሚበል ሁኔታ አዲስ ቫይረስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ይህ በተለይ በኢንፍሉዌንዛ ደጋግሞ የሚታይ ነገር ሲሆን፣ በኤች አይ ቫይረሶች ላይም የምናየው ነገር ነው፡፡ አሁን ለሰው ዘር፣ አስፈሪው፣ አዲስ ተቀይጦ የተፈጠረው ቫይረስ፣ ከተለያዩ ቫይረሶች ሀይለኛ የሚባሉ ባህሪዎችን ይዞ ሊመጣ ይችላል ነው፡፡ ለምሳሌ ገዳይ የመሆን ባህሪውንና፣ በሰው ላይ በፍጥነት የመዛመት ባሕሪውን ይዞ ብቅ ቢልስ፡፡ (ፈጣሪ ይጠብቀን)

ትንሽ ሰለ(Spanish flu) ስፓኒሽ ፍሉ ሰለሚባለው ከወፍ ዝርያ ሰለመጣው ኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ እንመልከት፡፡ እኤአ በ1918 ባንድ ጊዜ የአለም አንድ ሶሰተኛ ህዝብ (500 ሚሊዮን በዛን ጊዜ) በመልከፍ፣ ለ50 ሚሊዮን ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑን፣ ማሰብ ባንፈለግም የግድ፣ ሰለ ቫይረሶችና ወረረሽኝ ሲወራ አእምሮ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ ለነገሩ ስፓኒሽ ይሉታል እንጂ፣ ከየት እንደተነሳም አይታወቅም፡፡ የዚሀ ቫይረስ ያልተለመደ ባሕሪው፣ በብዛት የሞቱት ጤናማ የሆኑ ዕድሜያቸው ከ15-34 አመታት የሆኑትን ነው፡፡ ህም፣ ምን አይነት ነገር ነው፡፡ ይህ ቫይረስ የአሜሪካ ሰዎችን የዕደሜ ጣራ ገደብ በ12 ሰመታት ነው የጎረደው፡፡ እንዴት አይጉረድ፣ በአሜሪካ ብቻ 675 ሺ ሰዎችን ሲገድል፡፡

ታዲያ ተመራማሪዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ እንዴት ይህን ያህል ገዳይ ሊሆን ቻለ? ከየትስ ነው የመጣው? ወደፊትስ እንዲህ አይነቱን ነገር እንዴት መከላከል ይቻላል? የሚሉ ነበሩ፡፡ ይህንን ለመመለስ ደግሞ የዚህን ቫይረስ የዘር ግንድ፣ ጀነቲክ ሜካፕ መመርመር ነበረባቸው፡፡

ሲያፈላልጉ ከረሙና፣ በ1918 በ21 አመቱ በስድስት ቀናት ውስጥ የሞተ ወታደር ሳምባ ለወደፊት ለምርመራ ይጠቅማል ተበሎ የተቀመጠ ያገኛሉ፡፡ ሌሎችም ተጨማሪ በዚህ ቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች የሰውነት ክፍል አገኙና፡፡ የዘር ግንዱን እንደገና ሙሉ ምርመራ በማድረግ፣ በ1999 ማስታወቅ ችለዋል፡፡ በነሱ ግኝት መሠረት፣ ቫይረሱ ምንም እንኳን በ1918 ፓንደሚክ ወረረሽኝ ቢያስከትልም፣ ከ1900 እሰከ 1915 ባለው ጊዜ ሰዎችን ይዞ እንደነበር ነው፡፡ አንግዲህ ጨምረው የገለጡት፣ ያ ቫይረስ የመጀመሪያ መነሻው የአጥቢ እንስሳት ቫይረሶች ነው የነበረው፡፡ ከአጥቢ እንስሳት ደግሞ የአሳማ ኢንፍሉዌንዛ (swine flu)ዝርያ ነበር፡፡ እንግዲህ ከመሠረቱ ይህ የአጥቢ እንስሳቶ ቫይረስ፣ የሰውም ይሁን የአሳማ የነበረው፣ ከወፍ ዝርያ ቫይረስ የተወሰነ ጂን በመውሰድ የተዳቀለ ቫይረስ ነው የነበረው፡፡ ይህ መዳቀል ነው እንግዲህ የተለየ ሀይል የሰጠው ተብሎ የሚታመነው፡፡

አዲሱ ኮሮና ቫይረስ ደግሞ፣ በዝርዘር ሲመረመር፣ ምንም እንኳን መሠረቱ ኮሮና ቢሆንም፣ እያንዳንዳቸው መጠነኛ በሆነ ለውጥ የጀነቲክ ግንዳቸው ላይ በማድረግ፣ ልክ ከአንድ አባትና እናት የተለያዩ መልክና ባሕሪ ያላቸው ልጆች እንደሚወለዱት፣ አዲሱ ኮሮና ቫይረስም በዝርያቸው በመጠኑ የተለያዩ ዘሮችን ይዞ ብቅ ማለቱን በቅርቡ ለይፋ ባልቀረበ፣ ግን የጥናት ውጤቶች ቶሎ እንዲሠራጩ ሲባል፣ እንደዚሀ አይነት ጥናቶች ሰብሰብ አድርጎ ለባለሙያተኞችም ሆነ ለተጠቃሚ በሚያቀርበ ጆርናል ላይ አስፍሯል፡፡ አዲሱ ኮሮና ቫይረስ ስሙ SARS-CoV-2 የሚባለው፡፡ የሚያሰከትለው በሸታ ደግሞ COVID-19 ይባላል፡፡ ይህ ቫይረስ አምስት የተለያዩ ዝርያዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ በቫይረሶች አለም፣ እንደዚሀ አዲስ ዝርያዎች(strains) የሚፈጠሩት ቫይረሱ በየጊዜው በጀነቲክ ኮዱ ላይ በሚያደርገው መጠነኛ ለውጥ (mutation) ምክንየት ነው፡፡ ከግሩፕ 1 እሰከ ግሩፕ አምስት ድረስ ደርሰዋል፡፡

ዋናው ፍራቻ እነዚህ በmutation ምክንያት የሚፈጠሩ ዝርያዎች፣ አዲስ ቫይረስ ይዘው ብቅ በማለት ባህሪያቸውን ቢለውጡስ ነው፡፡ እንደተስተዋለው ከሆነ፣ ቫይረሱ በፍጥነት የመዛመት ችሎታውን ተክኖታል፡፡ ግን በጣም ሀይለኛ ቢሆንስ፡፡ ሌላው ደግሞ፣ የክትባት ሙከራ ላይ ናቸው፣ እናስ አዲስ የተፈጠረው ዝርያ ክትባቱ የማይመለከተው አይነት ቢሆንስ የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ አስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ሙከራ ላይ ያለውን ክትባት አያሰጋውም በማለት ባለሙያተኞቹ እየገለጡ ነው፡፡ ሌላው ከባሕሪ ጋር አብሮ የሚጠቀሰው፣ አሁን ያለው ቫይረስ ወደ ሰውነት ሴሎች ሲገባ ACE II የተባለ ሞሎኪል ያላቸውን ሴሎች እየፈለገ ነው፡፡ ለዛ ነው መተንፈሻ አካላትና የጨጓራና አንጀት ላይ እንደ ልቡ የሚርመሰመው፡፡ ሌላ መግቢያ ቢፈጥርና ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ቢሄድሰ ነው፡፡ በየአገሩ እየዘለለ ሲሄድ ዝርያውን እየቀየረ mutate እያደረገ ከመጀመሪያው ቫይረስ በዘር እየራቀ ይሄዳል፡፡ እንግዲህ ወይ ሀይለኝነቱ ይጨምራል፣ ወይም ደግሞ ደካማ ሆኖ ይሠወር ይሆን ነው ጥያቄው፡፡

ለዚህ ሁሉ ሥጋት መከላከያው፣ በቫይረሱ ላላመያዝ ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ በማድረግ በተጨማሪም ቫይረሱ እንዳይዛመትም እንዲሁ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ባላበት ቦታ ቆም ማድረግ ከተቻለ፣ በየጊዘው mutation ውስጥ እያለፈ አዲስ ዝርያ ከመፍጠር ማቀዝቀዝ ይቻላል፡፡

የስፓኒሽ ፍሉን ታሪክ ካያችሁ፣ የበረታው ወጣቶች ላይ ነበር፡፡ ይኼኛውስ ቢሆን ባሕሪው ቀይሮ አንደዛ ቢያደርግስ? ሰለዚህ፣ ወጣቶች፣ ነገ በኔ በማለት በሽታው እንዳይዛመት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግደየለሽነቱ ይብቃ፡፡ በዚህ ጉዳይ መግተርተር ነው እንጂ አልበገር ባይነት የሚባል ነገር የለም፡፡ ቫይረሱ የሚበቃውን ያህል እየገደለ ነው፡፡ በቻይና ሊያቀዘቅዙት የበቁት፣ እንቅስቃሴ በመገደብ ነው፡፡ በየቤታችሁ ሰብሰብ በሉ፡፡ መፅሐፍ የሚነበብበት ጊዜ ካለ አሁን ነው፡፡ አልፎ ሊሄድ ይችላል፡፡