ሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

       ቡናና መጠጣትና የጉበት በሽታ 

በአብዛኛው የምንመገበውና የምንጠጣቸው ነገሮች በሰውነት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ለሰውነት ጠቀሜታ ያላቸው ነገሮች እንዳሉ ከዚህም ከዚያም የሚወጡ ጥናቶች ይዘግባሉ፡፡
       ሰዎች በብዛት ከሚያዘወትሯቸው መጠጦች አንዱ ቡና ነው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች አንደሚያሳዩት፣ ከዚህ ቀደም በሰውነት ላይ ጥሩ ውጤት ያመጣል ተብሎ ነው ማጠቃለያው የሚወጣው፡፡ ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር እየቀለድንም ቢሆን ይህን ጥናት ያካሄደው ሰታርባክስ ነው ወይ እያልን ነበር፡፡ አሁን ግን ጠንከር ባለ ሁኔታ ቡና በተለይም የጉበት በሽታ ያላቸው ሰዎች ላይ ያለው ከፍተኛ ጠቀሚታ በጥናት እየታየ ነው፡፡ በቀን ከሁለት ኩባያ በላይ ቡና መጠጣት ያለውን ጠቀሜታ በዝርዝር ለማሰቀመጥ ሰለ ጉበት በሸታዎች በመጠኑም ቢሆን መግለፅ ጥሩ ነው፡፡
   የጉበት በሽታ በሔፓታይትሰ ቢ(Hepatitis B)፣ በሔፓታይትስ ሲ (Hepatitis C) ቫይረሶች አማካኝነት ይከሰታል፡፡ መጥፎ ውጤቱም ጉበቱን በማቁሰል የጉበት ጥብሰት (ሲሮስስ cirrhosis of the liver)፣ የጉበት መድከም (liver failure) እና የጉበት ካንሰር ናቸው፡፡ የጉበት መድከም አስኪከሰት ድረስ በጉበት ውስጥ የሚካሄደው ጥብሰት ምንም ምልክት የማይሰጥ መሆኑን አንባብያን ሊረዱት ይገባል፡፡ በጎሽ ድረ ገፆች ስለነዚህ በሽታዎች ሰፋ ያሉ ፅሁፎችን ያንብቡ::
        ከቫይረስ ልክፍቶች ውጭ ደግሞ በአልኮሆል አማካኝነት ተመሳሳይ የጉበት በሽታ የሚከሰት ሲሆን ሌላ እምብዛም በህብረተሰቡ የማይታወቅ በአልኮሆል ያልመጣ በጉበት ውስጥ ከመጠን በላይ ጮማ መከማቸት የሚያስከትለው (Non Alcoholic Fatty liver disease ) የሚባል በሽታ አለ፡፡ ይህ (fatty liver disease) የሚባል ሁኔታ በአልኮል አማካኝነትም ይከሰታል፡፡
     እንግዲህ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆን ከሁለት ኩባያ ወይም ከዛ በላይ በየቀኑ ቡና መጠጣት የሚከተሉትን ለውጦች ሲያስከትል ታይቷል፡፡
1. በጉበት በሽታ ምክንያት በደም ምርመራ የሚታዩ ሶሰት ነገሮችን ማለሳለስ
 2. ከዚህ ጋር በተያያዘም የጉበት ጥብሰት መፈጠርን ማዘግየት
 3. የጉበት ጥብሰት በመዘግየቱ ምክንያት ደግሞ የጉበት መድከምን ማዘግየትና መከላከል
 4. ተያይዞም የጉበት ካንሰር የመከሰት ሁኔታን መቀነስ
 5. በዚህም ምክንያት ደግሞ በጉበት በሽታ ምክንያት የሚከሰት ሕይወት ማለፍን ማዘግየት
 6. የሔፓታየትስ ሲ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ላይ ደግሞ ቡና በመጠጣታቸው ምክንያት ለሔፓታይትስ መድሀኒቶች ጥሩ ምላሽ መስጠት ናቸው፡፡


​​​እነዚህ ጥናቶች ከዚህ በፊት የታዘገቡም ቢሆን፤ የዚህ መልክት ፀሀፊ በቅርቡ በኒው ኦርሊንስ ከተማ በተደረገው በአሜሪካ የተላላፊ በሽታ ስፔሽያሊስቶች ስብሰባ በመገኘት ከባለሙያተኞ የቀረበውን መረጃም አዳምጦአል፡፡ እንደ መረጃ አቅራቢዎች በቀን የቡናው መጠን በጨመረ ቁጥር ጠቀሚታው እየጨመረ አንደሚሄድ ነው ያስገነዘቡት፡፡
    በዚህ ምክንያት ለጉበት በሽታ መከሰት አደጋ ላይ ያሉ ሰዎች ቡና እንዲያዘወትሩ ምክር እንዲሠጥ ነው የተሰማማነው፡፡ ለዚህም ነው ይህ ፅሁፍ የቀረበው፡፡
ቡና በመጠጣት የሚከተለውን ሌላ አደጋ ማሰተዋል ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የደረት ቃር(Gastro esophageal reflux disease, GERD) ላለባቸው ሰዎች ቡና እንዳይጠጡ ምክር ይሠጣል፡፡ የጨጓራ (ulcer) ያለባቸው ሰዎችም እንዲሁ፡፡ ከሙያ አንፃር የምመክረው፤ ለጉበት በሽታ የተጋለጡ ሰዎች የጨጓራ መድኃኒቶችን እየወሰዱ ቡና እንዲያዘወትሩ ነው ምክሩ፡፡ ምክንያቱም አንድ ጊዜ የጉበት ጥብሰት ከተከሰተ ወይም የጉበት ካንስር ከተከሰት አካሄዱ ወደ ከፋ ደረጃ ማለትም ወደ ሕይወት ማለፍ የሚያሽቆለቁል ሰለሆነ ነው፡፡
   እንደኔ ከሆነ የኢትየጵያ ቡና ሳይሻል አይቀርም (እየቀለድኩ ነው)፡፡ ነገር ግን አዲስ አባባ የታሸጉ ቡናዎች በከረጢት ለመግዛት ስንሞክር የተሠጠን ምክር አሁን ድረስ ይከነክነኛል፡፡ ይሄን አይነት አትግዙ ምክንያቱም ቡናው ውስጥ ምናምን ይጨምሩበታል ተብለን አንድ ቦታ ብቻ ሄደን ገዝተናል፡፡ ስሙን አልናገረም፤ ግን ቡና ጠጭዎች የትኛው ንፁህ እንደሆን ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ፣ ኩባያ ሲባል እዚህ አውሮፓና አሜሪካ ያለውን መጠን መገንዘብ ነው፡፡


​ዋቢ

Impact of coffee on liver diseases: a systematic review.
Saab S, Mallam D, Cox GA 2nd, Tong MJ.
Liver Int. 2014 Apr;34(4):495-504. doi: 10.1111/liv.12304. Review

Coffee and non-alcoholic fatty liver disease: brewing evidence for hepatoprotection?
Chen S, Teoh NC, Chitturi S, Farrell GC.
J Gastroenterol Hepatol. 2014 Mar;29(3):435-41. doi: 10.1111/jgh.12422. Review

Coffee has hepatoprotective benefits in Brazilian patients with chronic hepatitis C even in lower daily consumption than in American and European populations.
Machado SR, Parise ER, Carvalho Ld.
Braz J Infect Dis. 2014 Mar-Apr;18(2):170-6. doi: 10.1016/j.bjid.2013.09.001

Association of coffee and caffeine consumption with fatty liver disease, nonalcoholic steatohepatitis, and degree of hepatic fibrosis.
Molloy JW, Calcagno CJ, Williams CD, Jones FJ, Torres DM, Harrison SA.
Hepatology. 2012 Feb;55(2):429-36. doi: 10.1002/hep.24731.