​​​​​​​​​​እየጨመሩ የመጡት በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሊኖሯቸው የሚችሉ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች 

በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የሚኖሯቸው የበሽታ ሰሜትና ምልክቶች እየጨመሩ ነው፡፡ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሁሉም አንድ አይነት ሁኔታ አይታይባቸውም፡፡ ማለትም በቀላሉ ከሚለቃቸው ጀምሮ በጠና የሚታመሙና ህይወታቸው የሚያልፍም ድረስ ነው፡፡
ሰሜቶች በቫይረሱ ከተጋለጡ ከ2-14 ቀናት ባሉት ጊዜ ውስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ሁሉም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሰሜቶች አንድ ላይ ላይገኙ ይችላል፡፡

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ስሜቶች ያሉባቸው ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘውም ሊሆን ይችላል፡፡

 1. ብርድ ብርድ ስሜትና ትኩሳት
 2. ሳል
 3. የትንፈሽ ሰሜት ማጠርና ለመተንፈስ መቸገር
 4. የድካም ስሜት
 5. የጡንቻና የሰውነት ህመም
 6. ራስ ምታት
 7. ድንገተኛ የማሽተትና የመቅመስ ችሎታ ማጣት
 8. የጉሮሮ መቁሰል
 9. አፍንጫ መታፈንና ንፍጥ መውረድ
 10. ማቅለሽለሽና ማስታወክ
 11. ተቅማጥ

 
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ይሁኑ እንጂ ሰዎች ሌሎች ተጨማሪ ስሜቶችና ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ቫይረሱ የማየድርስበት የሰውነት ክፍል ሰለሌለ፣ በቆዳ፣ በአይንም በኩል የበሽታ ምልክት እያሳየ ነው፡፡ ስትሮክና የልብ ህመም ታይቷል፡፡ ልጆች ላይ የተከሰተው በኢንፍላሜሽን አማካኝነት የሚመጣው በሽታም ሌላ መገለጫ ነው፡፡


​​ኮቪድ-19 ጉልበቱን በሚያሳይበት ቦታ ከተያዙት 43% ይገድላል    6/03/20

በአሜሪካ በተቀዳሚነት በኮቪድ-19 ከተጠቁት ሶስት ክፍሎች አንዱ ነርሲንግ ሆም (የአዛውንቶች መጦሪያ) ቦታ ነው፡፡ ከዛ ቀጥሎ ቤተሰብ፣ ከዛ ደግሞ የጤና በለሙያተኞች ናቸው፡፡

የነርሲንግ ሆም ጥቃት ከሌሎች የሚለየው፣ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ምን ያህሉ እንደሚሞቱ ነው፡፡ የአሜሪካው CMS (Center for Medicaid and Medicare Services) ሪፖርት ከሠጡት አብዛኞች የነርሲንግ ሆም ተቋሞች ያጠናከረውን አስደንጋጭ መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ በቻርቱ እንደምታዩት፣ በበሽታው ከተያዙት ከ60 439 ሰዎች መሀከል፣ 25 923 ሞተዋል፡፡ በፐርስንት ሲሰላ 43 ነው፡፡ ግማሹን በሉት፡፡ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ምክንያት አለ፡፡ የነርሲንግ ሆም ሰዎች፣ በዕድሜ የገፉና በብዛት ሌሎች ተደራቢ በሽታዎች አንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ ተደጋግሞ እንደታየው፣ በኮቪድ ከተያዙ በኋላ አሰከፊ ውጤት የሚደርስባቸው ሰዎች ናቸው፡፡

ወደ ሀገር ቤት ብንመለስ፣ እንደ አሜሪካ አዛውንቶችን አንድ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚረዱ ተቋማት ብዛት እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን፣ እንደ ባህላችን፣ ወላጆችን በቤታቸው ወይም በየልጆቻቸው ቤት መጦር የተለመደ ነው፡፡ ፍራቻው ደግሞ፣ እነዚህ በየቤቱ የተቀመጡ የዕድሜ ባለፀጎችን፣ ሌሎች አብረዋቸው የሚኖረ ወጣ ገባ የሚሉ ሰዎች ቫይረሱን ሊያቀብሏቸው እንደሚችሉ ነው፡፡ ለዚህ እንግዲህ፣ እንደዚህ አይነት ሰዎች በየቤቱ ያሉባቸው ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ነው፡፡ በጥናት የረዳ ነገር የታየው፣ ወጣ ገባ የሚሉትም፣ አዛውንቱም ማስክ ቢያደርጉ ሠርጭቱን ይቀንሱታል፡፡

በተጨማሪማ፣ ወረርሽኙ አስከሚያልፍ ድረስ፣ እነዚህ በዕደሜ የገፉ ሰዎች ከቤት ውጭ መውጣትና ርቀው መሄድ እንዳይሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ፣ ቤተክርስቲያንና ፀሎት ቤቶችንም ይጨምራል፡፡(ይከብዳል) ነገር ግን አማራጭ ሰሌለም ነው፡፡

መረጃው የሚያሳየው፣ የነርሲንግ ሆም ሠራተኞች በቫይረሱ ከመያዝ አላመለጡም፡፡ ደግነቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በንፅፅር ሲታይ አነስተኛ ነው፡፡ ማለትም ከ34442 ሠራተኞች መሀከል፣ 449 ሞተዋል፡፡

ሌላው አስፈሪ ቁጥር የወጣው ደግሞ፣ የአሜሪካው CDC ይፋ ያደረገው በቫይረሱ የተያዙ የጤና ባለሙያተኞች ቁጥርና በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ነርስና ሀኪሞች ሌሎችንም ጨምሮ ነው፡፡ በቫይረሱ የተያዙት የጤና ባለሙያተኞች ቁጥር 66 770 ሲሆን ከነሱ መሀከል 323 ሞተዋል፡፡

እንደገና ወደ ሀገር ቤት ዞር ብለን ብንመለከት፣ የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ መሄዱን አናያለን፡፡ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎችን ማጨናነቃቸው የሚቀር ነገር አይደለም፡፡ መለስ ብለን የአሜሪካውን ችግር ብናይ፣ በቂ የሆነ ሙሉ የጤና ባለሙያተኞች የሚለብሱት መከላከያ በበቂ ደረጃ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያም ቢሆን ይህ ችግር የከፋ እንደሚሆን ነው፡፡ ሰለዚህ ርዳታችን አንደሚያስፈልጋቸው አስቀድሞ መገንዘብም ያስፈልጋል፡፡


በኮቪድ ሥርጭት ቤተሰብዎን ለማዳን የሚረዳ ታላቅ ግኝት “የጨነቀ ዕለት” አለ ድምፃዊው 5/31/20

በሠርግ ዕለት ያልተጠራው ተጋባዥ ኮቪድ-19 ሠርገኞችን … 

In 2020 

የድረ ገፁ ጉብኝት ቁጥር

429,612

የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ! 
የሚያልፍ ኮቪድም አይያዝህ፣ በሚያልፍ ኮቪድ ሰውን አታስይዝ

የኮቪድ-19 ክትባቶች  11/17/2020
ሰሞኑን ተስፋ የሚሠጡ ግኝቶች የተከሰቱበት የኮቪድ ክትባቶችን በተመለከተ በተከታታይ ዜና ማሠራጫዎች ሲያቀርቡ ታይቷል ወይም እይታየ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ክትባት መከላከያ እንጂ በበሽታው ከተያዙ በኋላ ለህክምና የሚሠጥ ነገር አይደለም፡፡ ሰለ ክትባት ከመግለፄ በፊት ግን ሰሞኑን፣ Herd Immunity የሚባል ነገር ተነስቶ አከራካሪና አስቆጪ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ ይህንን Herd Immunity ይካሄድ ብለው የመከሩ ሰዎች፣ ሰብዕና የጎደላቸው ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ በመሠረቱ Herd Immunity ማለተ፣ የህብረተሰብ የጋራ የመከላከያ አቅም ማለት ነው፡፡ በዝርዝር ሲታይ፣ እንደ ኮቪድ-19 አይነት ወረርሽኝ ሲከሰት፣ ምንም የመከላከያ ዘዴ ሳይሰተገበር፣ የታመመው ታሞ፣ የሞተው ሞቶ፣ ቀሪው ሰው ለበሽታው መከላከያ የሚሆን አንቲቦዲ ሲኖረው በሽታው መዛመት አቁሞ በዛው ይከስማል ነው፡፡ ምክንያቱም አዲስ የሚያዝ ሰው ከሌለ፣ የሚጋለጠውም ሰው እንቲቦዲ ወይም መከላከያ ካለው በበሽታው ሰለማይያዝ ነው፡፡

ይህ Herd Immunity የማህበረሰብ የመከላከያ አቅም፣ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው፣ ከህብረተሰቡ ውስጥ ምን ያህሉ ሰው ለበሽታው ሲጋለጥና በሰውነቱ ውስጥ የመከላከያ አቅም ወይም እንቲቦዲ መፍጠር መቻሉ በአሃዝ ግብ ሲኖረው ነው፡፡ በአብዛኛው እንደ በሽታው ቢሆንም፣ ከስልሳ አስከ ሰባ በመቶ የሚሆነው ሰው ለበሽታው መጋለጥ ይኖርበታል፡፡ እዚህ ላይ ግን፣ የበሽታው የመሠራጨት አቅምም ወሳኝ ይሆናል እንደ ኮቪድ-19 ያለ በሽታ ከአንድ ሰው ተነስቶ ስንት ሰው ላይ ይሻገራል የሚለው ጥያቄም ይታያል፡፡ እንደምናየው ከሆነ፣ በመሠራጨት አቅም ባለ ዝናና ሪኮርዱን የያዘው ሚዝልስ ወይም ኩፍኝ የሚባል፣ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት በሽታ ነው፡፡ ከተጋለጡ ሰዎች ዘጠና ፐርስንቱ መከላከያ ከሌላቸው (በክትባት ወይም በተፈጥሮ) በስተቀር በሚዝልስ ቫይረስ እንደሚያዙ ነው፡፡

ይህ አዲሱ ጎበዝ፣ ኮቪድ-19፣ በደረጃ ማለትም በመሠራጨት አቅም ከሚዝልስ ቀጥሎ ይገኛል፡፡ አትጠራጠሩ ከሰው ወደ ሰው የመሸጋገር ችሎታውን ተክኖታል፡፡ እና በዚህ ደረጃ፣ Herd Immunity ለመፈጠር በበሽታው መጋለጥ ያለባቸው ሰዎች እሰከ ሰማንያ ዘጠና ፐርሰንት ድረስ ይሄዳል፡፡ እንግዲህ፣ አኮኖሚው ሞተ ወይም ሊሞት ነው የሚሉ ሰዎች፣ በሽታውን እንዳመጣጡ አንልቀቀውና የዳነው ድኖ ወደ ሥራችን እንመለስ ብለው፣ ያውም ሳይንቲሰት ተብየዎች ፕሮፖዛል አቅርበው፣ አሁን ሽኝቱን አልቀበልም ያሉት የአሚሪካው ፕሪዚዳንት አማካሪ ሳይቀር ይህንን ሀሳብ ከወደቤተ መንግሥት በኩል አሰምተው ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ቁጣ ያሰነሳው ያለ ነገረ አልነበረም፡፡ ልብ በሉ

1ኛ፡ በሽታው እንደልቡ ይሠራጭ የሚሉ ሰዎቸ፣ በማስክ የማያምኑ ለመሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ዋናው ነገር፣ ለምሳሌ የአሚሪካ ህዝብ ሶስት መቶ ሚሊዮን ነው ቢባል፣ አስከ ዘጠና ፐርስንቱ ይጋለጥና Herd Immunity ይፈጠር ሲባል፣ በዚህ ምክንያት የሚሞተውን ሰው ቁጥር እንደ ሂሳብ ማወራረጃ ነው የቆጠሩት፡፡ ገምቱ፣ ከአስር ሚሊዮን ሰው ዕሩብ ሚሊዮን የሚሞት ከሆነ፣ በቀላሉ ከሁለት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ሰው ምን ያህል ይሞታል?

2ኛ፡ አስቀያሚው ነገር፣ አስካሁን በድርሻ ሲታይ ከሚገባቸው ከህብተሰቡ ቁጥር ውክልና ወይም ፐርስንት መጠን በላይ እነማን እንደሚሞቱ ገልፅ ነው፡፡ ይህንን ፅሁፍ ማንበብ የቻላችሁ በሙሉ በዚህ በሚጎዱት ሰዎች ወገን ነው የምትመደቡት፡፡ እነዚህ ሰዎች አንግዲህ ጥቁሮች፣ ሂስፓኒኮች ወይም የነጭ ዠርያ ያልሆኑ ናቸው፡፡ ይሀ ሁኔታ ግልፅ ሆኖ እያለ በሽታው እንደልቡ ይራወጥ ማለት፣ በፖሊሲ ደረጃ፣ አጠያያቂ ነው፡፡

3ኛ፤ በሽታው ያለ ገደብ ከተለቀቀ፣ ኢኮኖሚውን መጉዳቱስ ይቀራል ወይ? ሰው አልባ ኢኮኖሚስ አለ ወይ?

4ኛ፤ Herd Immunity ይፈጠር ሲባል፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ለቫይረሱ የተፈጥሮ መከላከያ ማበጀት አለባቸው፡፡ ያ የመከላከያ አቅም ወይም እንቲቦዲ መጀመሪያውኑ መልሶ ከመያዝ ያስጥላል ወይ? የሚያስጥል ከሆነ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል? የሚሉ ጥያቄዎች መልስ ግልፅ ባልሆነበት ሁኔታ፡፡ በሽታውን ልቀቁተን የፈጠረው ይፈጠር ማለት አደጋው ቢጨምር እንጂ አያንስም፡፡

አንግዲህ በHerd Immunity በሚመለከት የተነሳውን ውዝግብ ተከታተላችሁ፡፡ በዚህ ላይ እያወቁ በፖሊሲ ደረጃ መተግበር፣ ወይም አቅም አንሶ መከላከያው መተግበር አለመቻል አለዚያም አገራችን ላይና እዚህም ስፋት ባለው በፖለቲካው የተጠመደ ህብረተሰብ ክፍል በምን ግዴ የመከላከያ መንገዶችን አለመተግበር ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡

ይልቁንስ ወደ ሁለተኛው የHerd Immunity መፍጠር ወደሚቻልበት ሁኔታ እንመለስ፡፡ ይኼኛው ደግሞ፣ በሽታውን ልቅ በመስደድ ሳይሆን፣ በክትባት በቂ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል በመከተብ፣ ቫይረሱ እንዳይሠራጭ ወይም እንዳይዛመት ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ የሁለቱ ክትባቶች ውጤት ሲገለፅ የተስፋ ስሜት የሠጠው፡፡ የሁለተኛው ክትባት ውጤት ሲነገር፣ ገበያ ደርቶ እንደነበር፣ ወል ስትሪት የሚከታተሉ ሰዎች ያዩት ነገር ነው፡፡

በዚህ ክትባት አሠራር ላይ ከስድስት በላይ የሚሆኑ ካምፓኒዎች እየሠሩ ነው፡፡ ሁለቱ ቀድመው ቢወጡም፣ ሌሎች አሉ ማለት ነው፡፡

ከዚህ በፊት ክትባቶች ሲሠሩ፣ ለህብረተሰቡ ከመቅረባቸው በፊት ከጥንስስ እስከ መጨረሻው ውጤት ድረስ ተሸግረው የሚያልፉባቸው ደረጃዎች አሉ፡፡ እነሱም ፌዝ (Phase) 1 – 4 ድረስ ናቸው፡፡ ለውጤት ለመብቃትና አገልግሎት ላይ ለመዋል ረዥም ጊዜ ይወስድባቸውል፡፡ አሁን የብዙዎች ጥያቄ የሆነው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክትባቶች ውጤታቸው እየተገለፀ ነው ሲባል፣ እንዴት ሆኖ፣ የትኛውን ደረጃ ቢዘሉ ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጤት የበቁት የሚል ነው፡፡ አግባብ ያለው ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ለሰዎች የሚሠጥ ክትባትም ሆነ መድሓኒት ከሁሉም በፊት የሚያደርሰው ጉዳት መታወቅም ሰላለበት ነው፡፡ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ከሆነ፣ አንዴት ተደርጎ ለህዝብስ ይቀርባል፡፡ ይህንን በሚመለከት፣ ጥናቶች በሚካሄዱበት ጊዜ፣ ጥናቱን ከሚያካሂዱት ሰዎች ብሎም፣ ከጥናቱ ጋር የተያያዘ ሳይነሳዊም ይሁን ወይም የገንዘብ ንክኪ የሌላቸው፣ ነፃ የሆኑ፣ በአበዛኛው ባላሙያተኞች፣ ጥናቱ ከመጀመሪየ ተነስቶ በየደረጃ የሚያሳያውን ጉዳት የሚከታተሉ ይመደባሉ፡፡ ህግ ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች ቡድን በምህፃረ ቃል DSMB (Data Safety Monitoring Board) ይባላል፡፡ አደጋ ካዩ ጥናቱን የማስቆም መብት አላቸው፡፡ ታስታውሱ ከሆነ፣ በአንደኛው ጥናት ላይ፣ ክትባቱን የወሰደ ግለሰብ ታሞ፣ በዚያ ግለሰብ ምክንያት ብቻ ጥናቱን የሚያጠናው ካምፓኒ፣ ጥናቱን ለማቆም ተገዶ ነበር፡፡

ሁለተኛ፣ አነዚህ ካምፓኒዎች የጥናታቸውን ውጤት ቢያቀርቡም፣ ሌላ መንግሥታዊ ድርጅት፣ ጥናቱን በዝርዝር ተመልከቶ ፈቃድ ካልሠጠ አገልግሎት ላይ አይውሉም፡፡ ይህ የመንግሥት አካል ደግሞ በምህፃረ ቃል FDA ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ የዚሀ መሥሪያ ቤት ሠራተኞቸ ደግሞ፣ ከዚህ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች መድሐኒት፣ ክትባት፣ የህክምና መሣሪያ ከሚያመርቱ ኩባንያዎች ጋር ልክልክ እንዳይኖራቸው ጥብቅ ቁጥጥር አለባቸው፡፡ ሰለዚህ ነፃ ናችው ማለት ይቻላል፡፡

የጥናቱን ሂደትና ውጤት የሚከታተሉ ነፃ የሆኑ ሰዎች ቡደኖች መኖራቸውን ከተመለከትን፡፡ የክትባቱ ውጤት ቶሎ እንዴት ለህዝብ ይደርሳል ለሚለው ጥያቄ፤ መታወቅ ያለበት፣ እነዚህ ጥናቶች ቶሎ ለመድረስ ተብሎ አንዱን ደረጃ ዘለው ወደ ሌላኛው እንደማይሄዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ፌዝ አንድን ሠርቶ ፌዝ ሁለተን ሳያጠናቅቁ ወደ ፌዝ ሶስት መሄድ አይችሉም እያደረጉም አይደለም፡፡ በአብዛኛው ጊዜ የሚወስደው ነገር፣ ፌዝ አራት ውስጥ የተካተተው፣ ክትባቱን በስፋት ማምረትና ለህዝብ ማድረስ ነው፡፡ ይህም የፌዝ ሶስትን ውጤት ጠብቆ ነው፡፡ አሁን የሆነው፣ ፊዝ ሶስት እየተሰራ እያለ ፌዝ አራት በተደራቢ መሠራቱ ነው ሊያፈጥነው የቻለው፡፡ የፌዝ ሶስት ውጤት ሳያልቅ ወደ ማምረቱ መሄድ አደጋው የገንዘብ ኪሳራ ነው፡፡ ምክንያቱም የፌዝ ሶስት ውጤት የሚያሳየው ክትባቱ ሰው ላይ ጉዳት አለውና ለአግልግሎት አይውልም ቢባል፣ ያ ሁሉ የተመረተ ክትባት ይደፋል ማለት ነው፡፡ እዚሀ ላይ ነው እንገዲህ ባለሀብቶችና መንገሥት በመተባበር፣ ኪሳር ከመጣ ይምጣ በማለት በሚሊዮኖች የሚቀጠር ብር አውጥተው ለሥራ ይዋል በማለታቸው፣ ደረጃ ሶስትና ደረጃ አራት እኩለ አብረው በመሄዳቸው ክትባቱ ለህዝብ የሚቀርበብተን የጊዜ ገደብ በጣም ያሣጠሩት፡፡

ባጭሩም ቢሆን ሰለ ክትባቶቹ እንነጋገር፡፡ የመጀመሪያው ፋይዘር የሚባል ኩባንያ ያቀረበው ክትባት (በነገራችን ላይ ፋይዘር የክትባቱን ጥናት በራሱ ገንዘብ ነው ያካሄደው፣ ማለትም ከመንግሥት አስቀድሞ የወሰደው ነገር የለም)፣ ውጤቱ መቶ ሰዎች ለባይረሱ ቢጋለጡ ዘጠናው ሳይያዙ ቀርተዋልና ስለዚህ ዘጠና በመቶ በሚሆኑ ሰዎች ላይ በሽታውን መከላከል ወይም ማስጣል ይችላል ነው፡፡ አስተውሉ፣ ክትባቱን ወስደው ግን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አሉ፡፡ አነሱም ከመቶ አስሩ ማለት ናቸው፡፡

ይህ ክትባት የሚሠጠው በሶስት ሳምነታት ልዩነት ሁለት ጊዜ ነው፡፡ ሁለተኛው ክትባት ከተሠጠ ከሳምነት በኋላ ዘጠና ፐርሰንት የመከላከል ችሎታ አሳይቷል፡፡ ክትባቱን ከጀመሩ ከውር በኋላ ማለት ነው፡፡  ትልቅ ችግር የሆነው፣ ክትባቱን ለህዝብ ለማድረስ፣ ክትባቱ ማይነስ 70 በሆነ ዲግሪ ሲንቲግሬድ ቀዝቃዘ ሁኔታ መቀመጥ አለበት፡፡ ያ ማለት የአንታርቲካ ክረምት ወራት ማለት ነው፡፡ ይህንን ያህል ቅዝቃዜ መፍጠር የሚችል ማቀዝቀዣ ደግሞ በየቦታው ቀርቶ ትልልቅ ማዕከሎች ላይ የማይገኝ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ ታዳጊ አገሮችን ማሰብ ነው፡፡ ያም ሆኖ የሚደረገው ተደርጎ ቅድሚያ በማውጣት ክትባቱን አስቀድመው የሚወሰዱ ሰዎች እንዲያገኙት ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የቅድሚያ ሁኔታ የመጣው ሁሉንም መከተብ የሚገባውን ሰው ለመክተብ በቂ ክትባት ማምረት አለመቻሉ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ አያለ፣ ሌላው የክትባት ጥናት የሚያካሂደው ሞደርና የተባለ ኩባንያ፣ የኔ ክትባት ጥናት ውጤት፣ ከመቶ ዘጠና አምስቱን (94.5) ያስጥላል በማለት የተሻለ ውጤት ይዞ ቀረበ፡፡ ይህ ክትባት እንደ ፋይዘሩ ሁለት ጊዜ የሚሠጥ ነው፡፡ ትልቅ ጠቀሚታ የታየው ግን፣ ክትባቱን ለማስቀመጥ ሆነ ለማጓጓዝ እንደ ፋይዘሩ ክትባት በረዶ ቤት የማያስፈልገው መሆኑ ነው፡፡ ክትባቱ ከ 36 ዲግሪ አስከ 46 ዲግሪ ፋራናይት በሆነ ቦታ መቀመጥ ይችላል፡፡ ያ ማለት የተለመዱ ክትባት በምናገኝባቸው ቦታዎች ሁሉ ክትባቱ መሠጠት ይችላል፡፤ ለታዳጊ አገሮች፣ ክትባቱን በጊዜ ማግኝት ከቻሉ፣ የትራንስፖርት ችግር የለም፡፡ ሆኖም የማምረት ችሎታው መላውን ህዝብ ማዳረስ የማየቻል በመሆኑ ቅድሚያ ክትባት መውሰድ የሚገባቸው ሰዎች በቅድሚያ እንዲያገኙ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለቀሪው ህዝብ ከመዳረሱ በፊት ወራቶች መጠበቅ ሊኖርብን ነው፡፡ ይህ ወሳኝ ነገር ነው፡፡

ዋናው ነገር ደግሞ የጥናቶቹ ውጤት የሚያሳዩት፣ ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች ላይ የታየ አሳሳቢ ችግር የለም ነው፡፡ የሞደርናው ክትባት ያሳያው (No safety concern) የሚል ማጠቃለያ እንዲሠጥ አድረጎታል፡፡ የቀደመው አገላለጥም በፋይዘር የተጠናው ክትባት ላይመ የታየ ነው፡፡ የፋይዘሩ ክትባት፣ ዕደሜያቸው ከ12 አመታት በታች ለሆኑ ልጆች ገና ጥናት ሊያደርግ አቅዷል፤ አስከዛ ድረስ ግን ለነዚህ ልጆች አይሠጥም ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ተስፋው፣ በክትባት አማካኝነት፣ ህዝቡ መከላከያ አበጅቶ በቫይረሱ እንዳይያዝ፣ መልሶም እንዳየሠራጭ ለማድረግ የመጠውን ወረርሽኝ ለመመለስ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ይህን ጥቁር ደመና መሻገር የምንችልበት ሁኔታ ይመጣል ማለት ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው የሚያልፍ ወረርሽኝ አይያዝህ ያልኩት ነው፡፡

ነገር ግን ልብ ካላችሁ፡፡ ክትባቱ ባንድ ጊዜ ለመላው ህዝብ መዳረስ አለመቻሉ፣ ጊዜው እየረዘመ ሰለሚሄድ ብዙ ሰዎች አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ ለዚህ ነው ክትባቱ ቢጀርም፣ ኮቪድ -19 ለመከላከል ማድረግ የሚገባንን ጥንቃቄዎች መቀጠል ያለብን፡፡ ክትባቱን የወሰደ ሰውም ቢሆን፣ በሽታው ባካባቢው በቁጥጥር ስር ውሎአል ቢባልም ጥንቃቄውን ማቆም አይኖርበትም፡፡ ክትባቶች መቶ ፐርስነት የሚከላከሉ አለመሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡ ትልቁ ጥያቄ ደግሞ፣ በክትባቱ አማካኝነት በሰውነት ውስጥ የተፈጠረው በቫይረሱ እንዳንያዝ የሚረዳን አንቲቦዲ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አለማወቃችን ነው፡፡ ውሎ አድሮ መታወቁ አይቀርም፡፡ 

እናም አልፎ የሚሄድ ከሆነ፣ አልፎ በሚሄድ ባይረስ መያዝ ከዛም ለሌሎች አሳልፎ መሰጠቱ በብዙ መልክ ተገቢ አይደለም፡፡ ከመከላከያዎች ሁሉ ዋነኞቹ ማስክ ማድረግና የአካል ርቀት መጠበቅ ነው፡፡ የሰዎች ስብስቦችን ማስቀረት፡፡ በቤትዎ ውስጥ በአንድ ጣራ አብሮት የማይኖር ከሆነ፣ ቤተሰብም ሆነ ጓደኛ ጋር አለመገናኘት፤ በተለይ በቤቶች ወይም በክፍሎች ውስጥ፡፡ በአሜረካ ለምትኖሩ፣ የዘንድሮ የምስጋና ቀን (Thanks Giving) በቤቱ ውሰጥ አብረው ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ብቻ እንዲሆን ነው የሚከረው፡፡ ህዝቡን ለማረጋጋት በማለት፣ ግድየለም ሁለት ወይም ሶስት ቤተሰብ፣ ከአስር ሰው ያልበለጠ የሚባለው ምክር ትክክልም አይደለም፡፡ ይልቁንስ ቁጥር ሳይጎድል ለመጭው ምስጋና ቀን መገናኘት አይሻልም ወይ?  

ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጋር ያገናኘን ነገር

ነብሳቸውን በገነት ያኑረውና በቅርቡ ያረፉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ የተደበቀው ማስታወሻ የተባለውን በእኔና በአቶ ደሳለኝ አለሙ ለህዝብ የቀረበውን መፅሐፍ እንዳነበቡና፣ መፅሐፉን ብዙ ቦታዎች ላይ ምልክት እንዳደረጉበት አንድ ሰው ሹክ ብሎኝ ነበር፡፡ ቆየት ብለው ግን፣ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ፣ የሚከተለውን አስተያየት ፅፈው አነበብኩ፡፡ መፅሐፉን ያነበበ ሰው፣ ፕሮፌሰሩ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ብዙ ቦታ ምልክት ማድረጋቸው የሚያስገርመው አይመስለኝም፡፡ ያላነበባችሁ ብታነቡት ይመከራል፡፡ በማንበባችሁ እንደምተደሰቱ እርግጠኛ ነኝ፡፡ 

_________________________________

A post from Professor Mesfin's page
Mesfin Wolde-Mariam
December 9, 2015 ·


የወኔ ተስፋ

በኢጣልያ ወረራ ጊዜ በደጃዝማች አያሌው ብሩ የጦር ሰፈር አንድ አማርኛን አቀላጥፎ የሚናገር ስዊድን ሀኪም አብሮ ነበረ፤ ትዝብቱን ጽፎ የተተረጎመውን ሳነብ አንድ ልብን በኩራት የሚያሳብጥ ታሪክ አነበብሁ፤ ስለደጃዝማቹ ጦር ሲናገር በከፊል እንደሚከተለው ነው፤--

‹‹በግምት ከየመቶው ሰው ሰባቱ ጎራዴ ብቻ ወይም በትር የያዙ ናቸው፤ በተለይ የማስታውሰው የአሥራ ስምንት ዓመት ወጣት ልጅ በኩራት መንፈስ ዱላውን በቀኝ ትከሻው ላይ አድርጎ ይንጎራደድ ነበር፤ ዱላው የእንጨት ሲሆን ቀይ ቀለም ያለው ሆኖ እላዩ ላይ ጌጥ ተቀርጾበታል፤ የዚህ ወጣት ልጅ የተለየ ኩራትና አካሄድ የሰዎችን ዓይን የመሳብ ችሎታ ፈጥሯል፤

ደጃዝማች አስጠሩትና
ዕድሜህ ስንት ነው?
አባቴ የሚነግረኝ በንጉሥ ሚካኤልና በሸዋ ገዢዎች መሀከል በተደረገው የሰገሌ ጦርነት ወር ነው የተወለድኩት፤
መልካም በዚህ በሚያምር ዱላህ ምን ልታደርግበት ነው?
በዚህ ዱላ ነጭ ልገልበት ነው፤
እንደሱ እንኳን ማድረግ አትችልም፤ በምትኩ ጠመንጃ ልስጥህ፤
የለም አመሰግናለሁ፤ ለአባቴ የማልኩት ቃለ መሐላ ጣልያን ገድዬ ጠመንጃውን ወስጄ አሳያለሁ፤ አለዚያ በዚህ በጦር ሜዳ እቀራለሁ፤››


የተደበቀው ማስታወሻ ከሚል መጽሐፍ፡፡


እኔ መስሎኝ የነበረውና የማምነው ኢትዮጵያውያን

ምርጫ ካላቸው ቀላሉን እንጂ ከባዱን አይመርጡም

የሚል ነበር፤ ይህ ወጣት የቆየ እምነቴን አነከተው!

አንዳንድ ኢጥዮጵያውያን ከባዱን የመምረጥ ወኔ

አላቸው ማለት ነው፤ አምላክ ዘሩን ያበርክተው!

ልቤን በኩራት አሳበጠው፤ የኢትዮጵያዊነት

ክብሬንም አደሰው! የዚህ ወጣት ወኔ በብዙ

መልኩ የሚታይ ነው፤ የዛሬ ወጣቶች አባባሉን

እንዲመረምሩት እተውላቸዋለሁ፡፡


መስፍን ወልደማርያም 

የቫይታሚን ዲ (Vitamin D) ዕጥረትና እና ኮቪድ-19

ኮቪድ-19 ከተከሰተ ወዲህ፣ አሁን ረገብ አለ እንጂ፣ ይህን ብሉ፣ ይህን ጠጡ፣ ይህን አጭሱ፣ ይህን ቆርጥሙ እየተባለ እየተመከረ ብዙ ጉዳትም ሲደርስ አይተናል፡፡ ክሎሮኪዊን ያለበትን የአሳ ገንዳ ማጠቢያ ኬሚካል ጠጥተው የሞቱና የታመሙም አሉ፡፡ ለእጅ መታጠቢያ የሚሆነውን አልኮል ጠጥቶ ድንገተኛ ክፍል ድረስ የደረሰ ሰው አለ፡፡ ወደ አሪዞና ደግሞ፣ ለእጅ ንፅህና የሚዘጋጅ ሳኒታይዘር ተጠቅመው የታመሙ፣ የአይን ብርሃን ያጡ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ እንኳን አደጋው የደረሰባቸው፣ ለእጅ መፅጃ የሚዘጋጀው አልኮል፣ ኤቲል አልኮል (Ethyl alcohol)  መሆን ሲገባው፣ ሰዎቹ የተጠቀሙት ግን ሜቲል አልኮል (Methyl alcohol)  የሚባል፣ ያልተፈቀደ የአልኮል ዝርያ የሆነ ኮምፓውንድ በሳኒታይዘሩ ውስጥ መገኘቱ ነው፡፡ አንባቢዎች፣ ለእጅ ማፅጃ የምትጠቀሙበት አልኮል (Ethyl alcohol) ኤትል አልኮል መሆኑን አረጋግጡ፡፡ ድንገት በግርግር ትርፍ ለማግኘት ያሰበ ሜቲል (Methyl alcohol) አልኮል ያለበት ሳኒታይዘር ሊያቀርብ ስለሚችል፣ ሜቲል አልኮል ያለበት ማፅጃ እንዳትጠቀሙ አደራ እላለሁ፡፡

ወደ ርዕሱ ስንመለስ፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት ለብዙ በሽታዎች ምክንያት ይሆናል ተብሎ ያልተበረበረ ጥናት የለም፡፡ 

​For more reading

ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

የኮቪድ-19 ሥርጭትን በተሳካ ሁኔታ ያሰቆመ አገር አለ ወይ? 08/09/2020

 እንዴታ፣ በደንብ፡፡ ግን ያልተጠበቀ፣ ትንሽ አገሮች ከሚባሉት አንዱ ኒውዚላንደ፣ የኮቪድ-19 ሥርጭትን አስቆመናል ሲሉ በቅርቡ በታወቂው የኒው ኢንግደላንድ መፅሔት ገልፀዋል፡፡
ኒውዚላንድ የማስታወሰው፣ የአጼ ቴዎድሮስ ባለሟል የነበረው ባሻ ፈለቀ (ካፒቴን ሰፒዲ)፣ ከቴዎድሮስ ተለይቶ ከሄደ በኋላ፣ ቅጥር ወታደር በመሆን፣ በኒወዚላንድ የማኦሪወች ጦርነት መካፈሉን ነው፡፡ ማአሪዎች በርግጥም፣ የኒውዚላንድ ቀደምት ኗሪዎች ናቸው፡፡

የ1918 ስፓኒሽ ፍሉ በኢትዮጵያ ደግሞ የህዳር በሽታ ተብሎ

የሚጠራው ወረርሽኝን አስገራሚ ታሪክ ያዳምጡ

በዋሽንግተንና አካባቢው ለምትኖሩ 
በኮቪድ-19 ተይዘው ከሆነ፣ ዕድሜዎ ከ18 አስከ 80 አመታት ባለው ውስጥ ከሆነ 
በኮቪድ -19 ለመያዝዎ የተረጋገጠው ባለፉት 28 ቀናት ውስጥ ከሆነ፣

በ Bethesda በሚገኘው የ National Institute of Health (NIH) ሰለ ኮቪድ-19 በሽታ ጥናት የሚካሄድና ጥናቱም በሽታው ወይም ኮቪድ-19 በሰዎች ላይ የሚያሰክትለውን ሁኔታ በጥልቀት ለማጥናት በመሆኑ ፈቃደኛ ከሆኑ ከሥር በተጠቀሱት ቁጥሮች ደውለው ማነጋገር ይችላሉ፡፡


አስቀድመው ከኔ ጋር መገናኘት ከፈለጉ ደግሞ፣ በኤሜይል goshinfo@goshhealth.org ሊያገኙኝ ይችላሉ፡፡ ጥናቱ በነፃ ስለሆነ፣ ኢንሹራንስ አያስፈለግዎትም፡፡ በተጨማሪም፣ ድንገት ህመሙ ከጠናብዎት አስፈላጊው ህክምና በ NIH ይደረግልዎታል፡፡ ይህ ጥናት የክትትል ጥናት እንጂ ምርምር ወይም experiment አይደለም፡፡ በኮቪድ-19 ተይዘው የተለየ ስሜት የሚሰማዎት ከሆነ ወይም የበሽታ ስሜቱ የቀጠለብዎት ከሆነ፣ በዚህ ጥናት መሳተፉ በሚደረገው ሰፋ ያለ የላቦራቶሪና ተጨማሪ ምርመራዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ

ቀጥታ ራስዎ የሚደውሉ ከሆነም፣ ማስታወቂያውን ያገኙት ከዚህ ከጎሽ ገፅ ወይም ከዶክተር ተፊሪ ነው ብለው መናገር ይችላሉ፡፡

ዶክተር ገበየሁ ተፈሪ
የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያተኛ

በምግብ መብያ ቦታ (Break room) ማሰክ ማውለቅ ያስከተለው ጣጣ 11/10/2020

 በኮቪድ መሰላቸት የብዙ ሰው ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ የጤና ባለሙያተኞችንም ይጨምራል፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ቸልተኝነት የሚያሰከትለው አደጋ እየታየ ነው፡፡ የተወሰኑ ሰዎች፣ ወይ ራሳቸው ካልታመሙ፣ አለዚያም የቤተሰብ አባልና የቅርብ ጓደኛ ታሞ ካላዩ፣ ኮቪድ-19 እንደሌለ ወይም የሌሎች ሰዎች ቸግር እንደሆነ ብቻ ያደርጉታል፡፡

በማንኛውም ቦታ ቢሆን፣ ከቤት ውጭ ማስክ የሚወለቅ ከሆነ አደጋ እንደሚጨምር ግልፅ ነው፡፡ በተለይም በቤት ወይም በክፍል ውስጥ ሲሆን፡፡ ከዚህ ቀደም፣ ቆየት ብሎ በጎሽ ድረ ገፅ ለማስጠንቀቅ የተሞከረው፣ በሥራ ቦታ፣ ምግብ የሚበላባቸው ክፍሎቹ፣ መፀዳጃ ክፍሎች፣ ኢሊቤተሮች አደጋ አላቸው ተብሎ ተገልጧል፡፡ አሁን በቅርብ ከወደ አውስትራልያ በኩል በተደረገ ጥናት፣ ቫይረሱ በአንዳንድ ዕቃዎች ላይ ለሳምንታት እንደሚቆይ ይታወቃል፡፡ ከጠብታ አልፎ ደገሞ በአየር ብናኝ (ኤርቦርን) እንደሚተላለፍም ግልፅ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተጠና ጥናት፣ ቫይረሱ በአየር ላይ አስከ ሶስት ሰአታት ሊቆይ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ አየር በደንብ በማየዛወርባቸው ክፍሎች ማለት ነው፡፡

በሆስፒታል ውስጥ፣ ማስክ የሚወለቀው፣ ሠራተኞቹ በሚመገቡት ጊዜ ነው፡፡ በአብዛኛው ይህ ደግሞ ጠበብ ባሉ የጋራ ምግብ መብያ ወይም (Break room) ክፍሎች ነው፡፡ አሁን የማጋራችሁ፣ በዚህ በ Break room አማካኝነት፣ 15 የሆስፒታል ሠራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀበት፣ ከማሳቹሴትስ የመጣ ሪፖርት ነው፡፡ ሆልዮክ ሜዲካል ሴንተር በሚባል ሆስፒታል በተከሰተው የ15 ሠራተኞች በኮቢድ መያዝ፣ ክትትል ሲደረግ፣ ከአንድ በኮቢድ ከተያዘ ሰው በ Break room ውስጥ ምግብ የተመገቡ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ይሀ የሆነው ሠራተኞቹ ባንድ ላይ በ Break room ምግብ ሲመገቡ ነው፡፡ እንግዲህ ለማንም ገልፅ እንደሆነው፣ ምግብ ሲበላ ማስክ መውለቁ አይቀርም፡፡

የሆስፒታሉ ሃላፊ አንደገለፁት፣ ሠራተኞቹ የህመም ሰሜት የታየባቸው ከሁለት ሳምንታት በፊት ሲሆን፣ በኮቪድ መያዛቸው ከተረጋገጠ ከ15ቱ አስሩ በድንገተኛ ክፍል ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያተኞች ናቸው፡፡ ሰውየው የሚሉት፣ በኮቪድ መሰላቸት ሲመጣ፣ በአካል መራራቅ ስድስት ጫማ ይሁን የተባለው እያነሰ እያነሰ ሰዎችም እየተጠጋጉ መታየታቸው አይቀርም፡፡ ሆስፒታሉ ህብረተሰቡ ውስጥ ያለ ተቋም እንደመሆኑ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ የኮቪድ ሥርጭት በቀጥታም ሀነ በተዘዋዋሪ ያገኘዋል፡፡ ይህ ሆስፒታል ባለበት አካባቢ የኮቪድ ሥርጭት እንደገና አገርሽቶ የታየበት ቦታ ነው፡፡ የታመሙት የጤና ባለሙያተኞች የግድ ከሥራ እንዲገለሉ ተደርገዋል፡፡ አስካሁን ሁለቱ ብቻ፣ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ሥራ የተመለሱት፡፡

በርግጥ ሁላችንም እንደምናስተውለው፣ ኮቪድ አገርሽቶ በአውሮፓ ሁለተኛ ዙር ጀምሯል፡፡ ከሥርጭቱ መክፋት የተነሳ አንዳንድ የአውሮፓ ከተሞች እንቅስቃሴ እንዲገደብ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ በሁለተኛው ዙር ክፉኛ የተመቱ እንደ ቸኮዝሎቫኪያ የመሠሉ አገሮች አሉበት፡፡

ከመሰላቸቱ በተጨማሪ፣ አንዳንዶች እንደ ንቀትም አይነት ስሜት ያላቸው ይመስላል ወይም መዘናጋት እንበለው፡፡ በሚቀጥለው ፅሁፍ የማካፍላችሁ፣ በኮቪድ ተይዘው የበሽታ ስሜት የማይሰማቸው ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት፣ ዘላቂ ሊሆን የሚችል አደጋ መታየቱ ነው፡፡ ስለዚህ የሚሞት ሰው ወይም በጠና የታመመ ሰው አላዩምና ወይም በቀላሉ እንወጣዋለን የሚባል አስተሳሰብ አደጋ ሊኖረው እንደሚችል ግንዛቤ መኖር ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ፅሁፍ መረዳት እንደምትችሉት
1ኛ. ለሥርጭት አንድ ሰው ሊበቃ እንደሚችል
2ኛ› ማስክ የሚወለቅበት ቦታ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ
3ኛ. ይህ ችግር ሆስፒታል ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሥራ ቦታዎችም ሊጠነቀቁበት የሚገባ መሆኑን
4ኛ› ከመታመሙ፣ በአንዳንዶችም ላይ የህይወት ማለፍ አደጋ ከማስከተሉ፣ ቫይረሱን መልሶ ማሠራጨት ወይም ከሥራ ቦታ ወደቤት ይዞ መሄድ ባሻገር፣ በሥራ ላይ የሚፈጥረውን ቸግር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የሚሠሩበት ሥራ ቦታ ከተዘጋ፣ ወይም አግልግሎት መሥጠት ካቋረጠ፣ ለሁለት ሳምንታት ቢሆን፣ ከኮቪድ ውጭ ሌላ ችግር ይፈጥራል፡፡ ባጭሩ የኮቪድ ፓንደሚክ ራሱ የኢኮኖሚ ችግርም ነው፡፡ ሰለዚህ በሽታውን ቀለል አድርጎ ማየት፣ እናም ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረግ፣ ኢኮኖሚው እንዲጎዳ አስተዋፅኦ ማድረግም ነው፡፡

ሌላው ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት፣ የግድ ለሥራ ሲባል ከቤት የሚወጣበት ሁኔታ ቢኖርም፡፡ ቤተሰብ ከቤተሰብና ከጓደኛ ጋር ለመገናኘት ሲባል፣ ድግስ አድርጎ መገባበዝም እየታየና እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ በክረምቱ በቤት ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ምግብ ሲበላም ማሰክ አይደረግም፡፡ እና ከሆስፒታል Break room በምን ይለያል? ማሰብ ያለብን፣ ለ15ቱ ሰዎች መያዝ ምክንያት የሆነው ሠራተኛ ምናልባትም ቫይረሱን ከሥራ ቦታ ሳይሆን ከውጭ ሊያገኘው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከበሽተኛ ጋር በሚደረገው ግንኙነት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሰለሚደረግ ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ሥርጭቱ ከፍ ሲል የሰዎች የመያዝ ዕድል ሊጨምር የሚችለው፡፡ በአሜሪካ የሚታየው፣  በቀን በበሽታው መያዛቸው የሚረጋገጡ ሠዎች ቁጥር፣ ኢትዮጵያ በወራት ካስመዝገበችው በላይ ነው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን የምንለው፣ አብዛኛው ሰው በቀላሉ ሊያልፈው ሲችል፣ ቫይረሱ ዞሮ ዞሮ የሚገድለው ሰው ያገኛል፡፡ እነማን አደጋ ላይ እንደሚሆኑ ደግሞ ግልፅ ነው፡፡ የተያዘ ሁሉ በጠና ይታመማል፤ የተያዘ ሁሉ ይሞታል ብለንም አናውቅም፡፡ ግን በስድስት ወር ውስጥ ከእሩብ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሰው ሲሞት ማየት ደግሞ ትንሽ ሰቅጠጥ እንድንል የሚያደርግም ነገር ነው፡፡ ህመሙና ሞቱንም ችላ ለሚሉ፣ ኢኮኖሚው የግድ እንዲዘጋ የሚያደርግ የሥርጭት መጠን ሲፈጠር ሁሉንም እንደሚጎዳ ማስታወስ ነው፡፡

መልካም ንባብ 

ተስፋ የሚሰጥ ዜና፣ የባሰ አታምጣ ሳይሆን፣ የተሻለ ይምጣ!
ሶሰትኛው የኮቪድ-19 ክትባት   11/23/2020


የአፍሪካ እግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር ላይ ቶጎ ግብፅን ቢያሸንፍ ኖሮ በኮቪድ ይሳበብ ነበር
 
ተስፋ ለሚያደርግ ሰው ተስፋ አለ፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለት ኩባንያዎች ፋይዘርና ሞደርና፣ የክትባት የጥናት ውጤታቸውን ለህዝብ አቅርበው ነበር፡፡ ፋይዘር ደግሞ፣ ውጤቱን በመያዝ የአገልግሎት ፈቃድ እንዲሰጠው ባላፈው ሳምንት ማለቂያ ላይ ለአሜሪካው FDA ማመልከቻ ማስገባቱ ይታወቃል፡፡ ምንም ያህል ሥራውን የሠሩት ኩባንያዎች ጥሩ ውጤት አለን ቢያቀርቡም፣ ለሕዝብ አገልግሎት ከመዋሉ በፊት የFDA ቦርድ አባሎች ተሰብስበው፣ ሥራው በተገቢው ሳይንሳዊ መንገድ መሠራቱን፣ ከዚያም ህብረተሰቡ ላይ ተቀባይነት የማይኖረው ጉዳት አለመድረሱን ገምግመው ነው የሚፈቅዱት፡፡ ሌላ ጊዜ ረዥም የግምገማ ጊዜ የሚወሰድው ፈቃድ አሁን በአለም ላይ ባለው አጣዳፊ ችግር ምክንያት አጣዳፊ ፈቃድ ይሠጣል፡፡ (Emergnecy Use Authorization)፡፡ የፋየዘሩ ክትባት ይህን ፈቃድ እንዳገኘ የክትባቱ ሥርጭት ወዲያውኑ እንደሚጀመር ነው፡፡ ክትባቱ አስቀድሞ ተሠርቶ ፈቃድ ሰለሚጠብቅ፡፡ ግን በቂ አይደለም፣ እናም ለሥርጭት ደግሞ የራሱ የቅዝቃዜ መጠን መመዘኛው ችግር ፈጥሮበታል፡፡

ባለፈው ፅሁፍ እንደገለፅኩት፣ ሞደርና የሚባለው ካምፓኒም ከሥር ሥር እየተከተለ ነው፡፡

አሁን ሶስተኛው ካምፓኒ፣ አሰትራ ዜኒካ የሚባል፣ በደረጃ ሁለት ጥናቱ ውጤት በመመርኮዝ፣ የኔም ክትባት ከ90 ፐረስንት በላይ ይካላከላል ሲል ሰሞኑን መግለጫ አውጥቷል፡፡ ካምፓኒው እንደሚለው፣ ክትባቱ የትራንሰፖርት ቸግር የለበትም፣ ምክንያቱም፣ አንደፋይዘሩ ክትባት በማይነስ 70 ዲግሪ መቀመጥ አያስፈልገውም፡፡ በማንኛውም ሪፍሪጄተር መቀመጥ ሰለሚችል፣ማለትም 2 to 8 degrees Celsius (36 to 46 degrees Fahrenheit) ሥርጭቱ በቀላሉ በየትኛው የአለም ክፍል ይዳረሳል፡፤ እንደምታውቁት ክትባቶች ቀዝቀዝ ባለ ሁኔታ መቀመጥ አለባቸው፡፡

እኔን ያስደሰተኝ ግን የሚቀጥለው ገለፃ ነው፡፡ ክትባቶቹ ወጥተው በዋጋቸው ምክንያት ብቻ ክትባቱን ማግኘትና በበቂ ደረጃ ለሀገራቸው ዜጎች ማዳረስ እንደማይችሉ ፍራቻው አለ፡፡ እንግዳም አይደለም፡፡ አስትራ ዜኔካ የሚለው፣ ቃል በገባሁት መሠረት፣ ለትርፍ አልሄድም ሰለዚህ ክትባቱን በጣም በረከሰ ዋጋ ለህዝብ እንዲደርስ አደርጋለሁ ይላል፡፡ የካፒታልዝም ውበት በአብዛኛው እዚህ ላይ ነው የሚገለፀው፡፡ ጤናማ የገበያ ፉክክር፡፡

በዚህ መሠረት፣ ሲነፃፀር፡

 1. አሰትራ ዜኔካ ክትባቱን በ $2.50 a dose.
 2. የፋይዘር ክትባት ደግሞ $20 a dose,
 3. የሞድርናው ደግሞ ከ$15 to $25 ነው፡፡


ካምፓኒዎቹ ለመንግሠትና ለአለም አቀፍ ድርጅቶች ቃለ በገቡት መሠረት ነው ዋጋቸውን የተመኑት፡፡.አንዳንደ ካምፓኒዎች ጥናቱን ለማካሄድ ከመንግሥት ይህ ነው የማይባል ገንዘብ መውሰዳቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን ሠርተው በረዱን፡፡

አንግዲህ ተስፋው እየዳበረና እየሰፋ ከመጣ፣ በሁሉም መግለጫዎች እንደታየው፣ ክትባቶች ከ90 ፐርስነት በላይ መከላከል የሚያስችሉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ አስከፉ ጉዳት የማያደርሱ መሆናቸው ይነገራል፡፡ አሁን ሥርጭቱ በሚፈለገው ጊዜ ሰለማይደርስ ወረርሽኙ ረዘም ላለ ጊዜ አብሮን ይቆያል፡፡ አስከዛ ድረስ ግን፣ አሁን የምናሳየውን መዘናገት ወይም ቸለልተኝነት አቁመን ጥንቃቄው ላይ ብናተኩር፣ ተጨማሪ ህመም፣ ሞትን መቀነስ እንችላለን፡፡ ኢኮኖሚው ወደባሰ አዘቅተ እንዳይሄድ የምናደርገው ይህንን ወረርሽኝ በመግታት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የእያንዳንዱን ግለሰብ ሰብአዊ ርምጃ ይጠይቃል፡፡ በኮቪድ ጊዜ የሚደረግ ጥንቃቄ ለሌላ ሰው ሲባልም ነው፡፡ ለሰው ማዘን እንዴት ይከብዳል፡፡ ባንድ በኩል ለህዝብ መብት የህይወት መስዋዕትነት በሚያሰከፍል ደረጃ ትግል ሲካሄድ እናያለን፡፡ በዚህኛው ግን…

አሁንም የምመክረው፣ በሚያልፍ ኮቪድ አለመያዝ ሰውን አለማስያዝ ነው፡፡ ፊቱን አላዞረብንም! እኛ ግን ማድረግ የሚገባንን እናድርግ፡፡

ሌላ አልተባለም

 1. ማሰክ ማስክ፣ በተለይ ከቤትዎ ሲወጡ
 2. የአካል ርቀት ጠብቁ፣ በውጭ ከሁለት ሜትር በላይ፣ በቤትና በስብሰባ ቦታዎች ከዛ በላይ 
 3. የሰዎች ስብስብ አቁሙ፣ ከአንድ ቤት ጣሪያ ሥር ካልሆነ ከሌሎቸ ሰዎች ጋር መገናኘት ለጊዜው ይቁም፡፡ ምክንያቱም እሰከ 50 ፐርሰንት የሚሆነው ሰው በቫይረሱ ተይዞ ግን የበሸታ ምልክት የለበትም፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር ላይ ቶጎ ግብፅን ቢያሸንፍ ኖሮ በኮቪድ ይሳበብ ነበር፡፡ ምክንያቱም ታዋቂው ተጫዋቻቸው መሐመድ ሣላህ፣ ሠርግ ቤት ሄዶ በኮቢድ ተይዞ ሲመረመር ሰለተኘበት ነው፡፡
 4. ቫይረሱ በዕቃዎች ላይ ለቀናት ሊቆይ እንደሚችልም ይታወቃል፡፤ ሰለዚህ ዕቃዎችን እንደፈቀደ አይነካኩ፣ እጅዎች በሳሙናና በውሃ ከሌለም በአልኮል ይወልውሉ፡፡


ሁላችንም የከርሞ ሰው ይበለን


ማስክ በማድረግ አፍና አፍንጫን መሸፈን ምን ያህል የኮቪደ-19 ሥርጭት ይቀንሳል?
የሚባልላቸውን ያህል ያስጥላሉ ወይ? 6/15/20 


በግልፅም ሆነ በሥውር፣ ዋናው የኮቨድ-19 ሥርጭት መከላከያው፣ ከሰው ራቁ የሚለው መልክት ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ፣ አፍና አፍንጫችሁን ሸፍኑ ነው፡፡ አፍና አፍንጫን ለመሸፈን የተለያዩ አይነት ማስኮች (መከለያ ወይም ጭምብሎች) አሉ፡፡ ለህብረተሰብ አገልግሎት የሚውሉት፣ በአንግሊዝኛው አጠራር (Surgical masks) የሚባሉት ሲሆን፣ ከጨርቅ የተሠሩ ማስኮችም ለአገልግሎት ይውላሉ፡፡ ለአገራችን ገበሬ ወይም የገጠሬው ሰው ደግሞ በጋቢው አፍና አፍንጫውን ከሸፈነም ይረዳል፡፡

በኮቪድ ተይዘው የነበሩ ሰዎች፣ መልሰው በኮቪድ ይያዛሉ ወይ?

መውደድ እንደገና 08/29/2020
 የፍቅር አይደለም፣ የፈረደበት ኮቪደ-19 ነው፡፡

የሳረስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር 2 (ሳኮ2) ወይም ኮቪድ-19 ሥርጭት ከሚታወቀው በላይ በአስር ዕጥፍ ይበልጣል፡ 07/23/2020
 
በየጊዜው አዳዲስ ግኝቶችን በማሳየት እንደዚህ አይነት በሽታ ታይቶም አይታወቅም፡፡ ከጥያቂዎች አንዱና ዋናው፣ በህብረተሰቡ ውስጥ በሽታው ምን ያህል ተሠራጭቷል የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የበሽታ ምልክት የሌለባቸው ሰዎች ቫይረሱን በስፋት እያሠራጩት እንደሆነ ከታወቀ ስነብቷል፡፡ 

Copyright 2013. Gosh Health. 

All Rights Reserved.

Community health 

education in Amharic