​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

​​የደረት ቃር GERD (Gastroesophageal Reflux Disease) 10/31/2021

በእንግሊዝኛ አጠራር Gastroesophageal Reflux Disease በምህፃረ ቃል GERD ተብሎ ሰለሚጠራው በሽታ ነው ርዕሱ፡፡ በተጨማሪም Acid reflux በመባልም ይታወቃል፡፡ በሽታው ከጨጓራ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ የህመም ስሜቱ በአብዛኛው ደረት ላይ ስለሚከሰት የደረት ቃር የሚል መጠሪያ የበለጠ ይቀርባል፡፡ ሰለ በሽታው ከመግለፃችን በፊት ስለ ሰውነት ክፍሉ አንድ እንበል፡፡

ምግብ ከአፍ ተነስቶ ወደ ታች ወደ ጨጓራ የሚወርድበት መተላለፊያ ኤሶፋገስ ተብሎ ይጠራል፡፡ ምግብ ጨጓራ ውስጥ ከደረሰ በኋላ መድቀቅ ወይመ መፈጨት አለበት፡፡ ያም አልሚ የሆነ ደረጃ እሰከሚደርስ ነው፡፡ ምግብን ለመፍጨት፣ በጨጓራውስጥ አሲድ ይለቀቃል፡፡ ይህ አሲድ በጨጓራው ግድግዳ ላይ ባሉ የተለዩ ሴሎች ነው የሚመነጨው፡፡ ታዲያ ራሱ የሚረጨው አሲድ መልሶ ጨጓራውን እንዳያቃጥለው ወይም እንዳይበላው፣ የጨጓራው የውስጥ ግድግዳ፣ አሲድን መቋቋም በሚችሉ በተለዩ ሴሎች የተሸፈነ ነው፡፡ ይህ አሲድ ከጨጓራ ወጥቶ ወደ ላይ ወደ ምግብ መውረጃው (ኤሶፋገስ) እንዳይመለስ፣ በሁለቱ መሀል ማለትም በጨጓራና በመግብ መውረጃው መገናኛ ቦታ መቋጠሪያ ወይም ሸምቀቆ (Sphincter) አለ፡፡ በተለያየ ምክንያት ይህ ሸምቀቆ በመላላት በደንብ ሳይዘጋ ሲቀር፣ ጨጓራ ውስጥ ያለው አሲድ ወደ ላይ ወደ ምግብ መውረጃው ሲዘልቅ (መዝለቅ አልነበረበትም) ሁኔታው GER Gastroesophageal Reflux  ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ሁኔታ በአማርኛ አጠራር፣ ቅርሻት ከሚባለው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ሰለዚህ ይህን አሲድ ወደ ምግብ መውረጃ መዝለቁን የደረት ቅርሻት ብለን ብንጠራው ተቀራራቢ ይሆናል፡፡

የምግብ መውረጃው ክፍል ግድግዳ እንደ ጨጓራው ግድግዳ አሲድን መቋቋም በሚችሉ ሴሎች የተሸፈነ አይደለም፡፡ ሰለዚህ ለአሲዱ በሚጋለጥበት ጊዜ ጉዳት ይደርስበታል፡፡ ጉዳቱ ነው እንግዲህ በሽታ የሚባለው፡፡ እናም በሽታው ሲከሰት የደረት ቃር በማለት እንጥራው፡፡ በእንግሊዝኛ፣ ከላይ እንደተገለጠው በአጭሩ GERD ተብሎ ይጠራል፡፡ የዚህ በሽታ መንስኤ እንግዲህ አሲድ ያለ ቦታው በምግብ መውረጃው ውስጥ ሲዘልቅ ነው፡፡ ይህንን መሠረታዊ ነገር ማስታወስ በኋላ ለሚሠጠው ምክር ግንዛቤ ይረዳል፡፡

የበሽታው ስሜትና ምልክቶች

  • በመሀል ደረትና በላይኛው የሆድ አካባቢ የማቃጠል ስሜት
  • እንዳንዴም የሚጎረበጥ ወይም የተሰነቀረ ነገር ያለ የሚመስል የህመም ስሜት
  • የጉሮሮ ህመምና ድምፅ መሻከር
  • ማቅለሽለሽና ማስታወክ
  • የጥርስ መሸረፍ፣ የአፍ መጥፎ ጠረን
  • የከፋ ደረጃ ሲደርስ፣ ምግብ ለመዋጥ መቸገር ወይም ምግብ ሲውጡ የህመም ስሜት
  • ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ የአስምና ተመላላሽ ሳምባ ምች (ኒሞንያ) መከሰት
  • በደረት ውስጥ ድምፅ ማሰማት (እንደ አስም ህሙማን)


አንባብያን ሊያስተውሉት የሚገባ ነገር፣ ይህ የደረት ቃር ዋና ምልክት የሆነው የደረት ውስጥ የማቃጠል ስሜት ሁሉም ሰዎች ላይ ላይኖር ይችላል፡፡


ምርመራ

ሐኪምዎ ተጨማሪ ምርመራ ሳያደርጉ፣ የርሰዎን የህምም ስሜት በመገንዘብ፣ መድሐኒት ሊጀመሩልዎት ይችላሉ፡፡ በአብዛኛው ጊዜ፣ መድሐኒት ለአንድ ወር ከወሰዱና የህመሙ ስሜት ከተሻለ፣ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም፣ እርስዎ በሚገልጡት የህመም ስሜት፣ የደረት ቃር መሆኑን በቀላሉ መጠርጠር ስለሚቻል፣ ህክምናውም ቢሆን በአፍ በሚወሰዱ እንክብሎችና እርስዎ ማድረግ በሚገባዎት የአመጋገብና የባህሪ ለውጥ ሰለሆነ ነው፡፡ የህመሙ ሰሜት የበረታ ከሆነና ለውጥ ከሌላው፣ ሀኪምዎ ወደ የአንጀትና የጨጓራ ባለሙያተኞች (ስፔሺያሊስቶች) ይልኩዎታል፡፡

ከምርመራ ዘዴዎች አንዱ Esophageal manometry ይባላል፡፡ ከላይ በመግቢያው እንደጠቀስነው፣ በምግብ መውረጃውና በጨጓራው መገናኛ ላይ ሸምቀቆ ወይም መቋጠሪያ አለ ብለናል፡፡ ይህ ሸምቀቆ፣ ምግብ ሲወርድ ይከፈታል፣ ምግብ በማይበላበት ጊዜ ደግሞ፣ ሸምቀቆው ይዘጋል፣ ያም አሲድ ወደ ላይ ወደ ምግብ መውረጃው እንዳየዘልቅ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ መቋጠሪያ በጡንቻዎች የተገነባ ስለሆነ፣ የዚህ ክፍል ጡንቻዎችን መወጠርና መላላትን መለካት ይቻላል፡፡ ጡንቻው ሲላላ፣ መተላለፊያው በመጠኑም ቢሆን ክፍት ስለሚሆን ነው አሲዱ ወደ ላይ የሚዘልቀው፡፡ ይሕ ምርመራ የሚደረገው፣ የደረት ቃርን በቀዶ ህክምና ለመከላከል ሲታሰብ ነው፡፡ ማለትም ችግሩ የሸምቀቆው መላላት መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ምርመራው የሚደረገው በአፍ በኩል በሚላክ ቀጭን ቱቦ አማካኝነት ሲሆን፣ በምግብ መውረጃው በተለያዩ ክፍሎች የጡንቻውን የመኮማተር መጠን በመለካት ነው፡፡


​ሕክምና

ወደ ሕክምናው ከመሻገራችን በፊት፣ ይህ በሽታ ሊያስከትላቸው የሚችሉ ዘላቂና አደገኛ ቸግሮችን መግለፅ ተገቢ ነው፡፡ ቸግሮችን ካስተዋልን፣ ይህንን በሽታ እንደቀላል መቁጠርና ሕክምና ወይም ምከርን አለመከተል የሚያሰከትለውን አደጋ መገንዘብ ያስችላል፡፡



ዘላቂ ችግሮች

  1. አሲድ በምግብ መውረጃው ክፍል ሲገኝ፣ ግድግዳው ይቆስላል፤ በየጊዜው ወይም በተደጋጋሚ ለአሲድ የሚጋለጥ ከሆነ፣ ቁስለቱ የመግብ መውረጃውን ግድግዳ ወደ መላጥና መብሳትም ሊሄድ ይችላል፡፡ ከመጠን በላይ በሚላጥበት ጊዜ ደግሞ የደም መፍሰስ ያስከትላል፡፡
  2. ለረዥም ጊዜ በሚፈጠረው ቁስለት ምክንያት፣ የምግብ መውረጃ ሴሎች ወደ ካንሰርነት የመቀየር ሁኔታ ይፈጥራሉ፤ ካንሰርም ሊበቅል ይችላል፡፡
  3. ከትንፋሽ ጋር የተያያዘ ባይሆንም፣ መተንፈስ የሚያዳግትበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
  4. በተደጋገሚ ቁስለት ምክንያት ጠባሳ ሲፈጠር፣ በተፈጥሮ መሆን እንደሚገባው፣ የምግብ መውረጃው መለጠጥ ሲያቅተው፣ የመውረጃው ጥበት ይፈጠራል፡፡ ይህ በሚፈጠረብት ጊዜ ምግብ መዋጥ ወይም ጨጓራ ድረስ ለመውረድ ይቸገራል፡፡
  5. ወደ ካንሰር ስንመለስ፣ የምግብ መውረጃው ግድግዳ ላይ ያሉ ሴሎች በተደጋጋሚ ለአሲድ ሲጋለጡ፣ ወደ ጨጓራው አይነት ሴሎች ይቀየራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ Barrett’s esophagus ይባላል፡፡ ይህ ደግሞ፣ አደገኛ የሆነ፣ ለህይወት ህልፈት ምክንያት የሚሆን አደገኛ ካንሰር ያስከትላል፡፡ እንግዲህ ለዚህ ነው፣ ይህ የደረት ቃር መኖሩ ከታወቀ፣ ቅርብ ክትትል ማድረግና፣ የታዘዘውን መድሐኒት መውሰድና የተሠጠውን የባህሪ ለውጥ ምክር መቀበልና መተግበር አስፈላጊ የሚሆነው፡፡ ስሜቱ የሚመጣና የሚሄድ ሰለሆነ፣ ችላ መባል አይገባውም፡፡


ወደ ህክምናው ስንመለስ፣ መታወስ የሚገባው ይህ በሽታ ከጨጓራ በሽታ የተለየ መሆኑን ነው፡፡ ለህክምናው፣ ሶሰት አቀራረቦች አሉ፡፡ የመጀመሪያው አመጋገብን በተመለከተ የባህሪ ለውጥ ማድረግ፤ የሚታዘዙ መድሐኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፤ በሽታው ከከፋ ደግሞ ወደ ቀዶ ህክምና ድረስ እንደሚሄድ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በሽታው እየከፋ ሲሄድና የተለያዩ ስሜቶች፣ ከላይ እንደተገለፀው፣ ሲፈጠሩ፣ ምርመራ የሚደረገው በጉሮሮ በኩል በሚገባ ካሜራ በተጠመደበት ቱቦ (ኢንዶሰኮፒ) አማካኝነት ነው፡፡ የካንሰር ሴል ጥርጣሪ ካለም፣ በዚህ ቱቦ አማካኝነት፣ ቅንጣቢ ናሙና ይወሰድና ተጨማሪ ምርመራ ይደረግበታል፡፡

የሚከተሉትን ምግቦች አለመመገብ የህመም ስሜቱን ሊያሰታግስልዎት ይችላል፡

  • ቡና(ሻይን ጨምሮ፣ ቾኮሌትም)
  • አሲድ ያላቸው ፍራፍሬዎች (ሎሚ፣ ብርቱካን ወዘተ)
  • ለስላሳ መጠጦች
  • አልኮል
  • በርበሬ
  • ቲማቲም
  • ቅባት የበዛባቸው ምግቦች
  • ነጭ ሽንኩርት ይጨምራል፡፡


 ይገባኛል፣ ታዲያ ምን እንብላ ይባል ይሆናል፡፡

  •  ምግብ በመጠኑ ወይም በትንሹ ቶሎ ቶሎ መብላት፤ በጣም በርከት ያለ ምግብ ባንድ ጊዜ መብላጥ፣ ጨጓራው ላይ ጭነት ስለሚፈጥር፣ አሲድ እንዲሾልክ ያደርጋል፡፡ የሰውነት ክብደትም ጤናማ መጠን ማደረግ ያስፈልጋል፡፡


  • ቅባት የበዛበት ምግብ፣ ቶሎ ተፈጨቶ ከጨጓራ ዘግይቶ ስለሚወጣ፣ የሚመገቡትን የቅባት መጠን መቀነስ አስፈላጊ ነው፡፡ ምግብ ጨጓራ ውስጥ እስካለ ድረስ አሲድ መመንጨቱ አይቋረጥም፡፡


  • ከተመገቡ በኋላ፣ ለአንድ ሰአት የሚሆን ማድረግ የማይገባዎት ነገሮች፣ ማጎንበስ፣ ጫማ ለማሰር፣ ወይም  ዕቃ ለማንሳት የመሳሰሉትን ከማድረግ ይቆጠቡ፤ ማለትም ቀና ብለው መቆየት ይረዳል፡፡


  • እንደበሉ ወደ መኝታ አይሂዱ፤ ጋደምም አይበሉ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ከበሉ ከሶስት ሰአታት በኋላ መተኛት ይመከራል፡፡ ምክንያቱም የተፈጨው ምግብ ከጨጓራው ጠቅሎ ለመውጣት ከአራት አስከ አምስት ሰአት ሊወስድበት ይችላል፤ ያም እንደ ምግቡ አይነትና እንደ መጠኑ ነው፡፡ ሰለዚሀ እራት በጊዜ መብላት ይጠቅማል፡፡


  • ሆድ ላይ ለቀቅ ያለ ልብስ መልበስ፤ ጠበቅ ያለ ልብስ ሆድ ላይ ጭነት በመፍጠር ጨጓራውን ያጨናንቃል፡፡


  • ሲጋራ ማጨስ ያቁሙ (የሲጋራ ክፋት እዚህም ላይ አለ)


  • አልጋዎ ቀና ማለት ይኖርበታል፤ ያም በትራስ ብቻ ሳይሆን፣ ፍራሹ ወይም አልጋው ከራስጌዎ በኩል ወደ 8 ኢንች ድረስ ቀና ማለት አለበት፡፡


ሌላው ዋናው ነገር፣ ህመምዎን የሚያባብሰውን ምግብ ለይቶ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ሁሉም ሰው እንድ አይነት ሊሆን ስለማይችል፣ የሚስማማና የማይሰማማዎትን ምግብ መለየት ይረደዎታል፡፡

ሀኪምዎ፣ ባጠቃለይ መጠሪያቸው Proton pump inhibitors (PPIs) የሚባሉ የሚዋጡ እንክብሎች ሊያዙልዎት ይችላሉ፡፡ እነዚህ መድሐኒቶች የተለያዩ አይነቶችና የተለያዩ መጠሪያዎች አሏቸው፡፡ የምንመክረው፣ መድሐኒት ሲወስዱ ሀኪም አማክረው እንዲሆን ነው፡፡