የኮቪድ ክትባት ሙሉ በሙሉ በተከተቡና ክትባቱን ባልወሰዱ ሰዎች መሀከል በኮቪድ መያዝ፣ በኮቪድ ምክንያት ሆስፒታል መግባት አንዲሁም በኮቪድ ምክንያት መሞት በሚመለከት የታየውን ልዩነት የአሜሪካው CDC ሪፖርት አቀረበ፡፡ በአሜሪካ በ13 ሪፖረት ከሚያደርጉ አካባቢዎች፣ ከሚያዝያ 4 አሰከ ሐምሌ 17፣ 2021 የቀረበ ሪፖርት ነው፡፡

             መረጃው የተሰበሰበው የ13ቱ አካባቢዎች፡ አላባማ፣ አሪዞና፣ ኮሎራዶ፣ ኢንዲያና፣ ሎስ አንጀለስ ካውንቲ፣ ሉዊዚያና፣ ሜሪላንድ፣ ሚነሶታ፣ ኒው ሜክሲኮ፣ ኒው ዮርክ ከተማ፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ ሲያትል እና ዩታህ ናቸው፡፡ የተሰበሰሰበውን መረጃ፣ በዕድሜ፣ በወራት በመከፋፈል ትንተና የተደረገበት ሲሆን፣ ከሚያዝያ 4 እሰከ ሐምሌ 17 ባለው ጊዜ ውስጥ ከነዚህ አካባቢዎች ባጠቃላይ የኮቪድ ክትባት ሙሉ በሙሉ ሰዎች በኩል በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 569 142፣ ሆስፒታል የገቡ ቁጥር 34 972 በኮቪድ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 6132 ነበር፡፡ ክትባት ሙሉ በሙሉ ከወሰዱ ሰዎች በኩል ደግሞ፣ በኮቪድ የተያዙ 46 312፣ ሆስፒታል የገቡ 2976 በኮቪድ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 616 ነበር፡፡ ይህንን ሪፖረት በዕድሜ ከፋፍሎ ለማየት የሚከተለውን ሠንጠረዥ ይመልከቱ፡፡      
የመረጃ ምንጭ MMWR / September 17, 2021 / Vol. 70 / No. 37

ከቀረበው ሪፖርት መረዳት የምንችለው በግልፅ ክትባቱን በወሰዱና ባልወሰዱ ሰዎች መሀከል በኮቪድ መያዝና ከዛም ሆስፒታል መግባት መሞትም ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ምንም እንኳን ክትባቱን ሙሉ በሙሉ ቢወስዱም የቫይረሱ ሥርጭት እሰከቀጠለ ድረስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ነው፡፡ ክትባቶቹ ሁሉም በመቶ ፐርስንት ደረጃ እንዳልሆኑ ግልፅ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም፣ ክትባት በወሰዱ ሰዎች ላይ በኮቪድ መያዝ ቁጥር ጨመር ብሎ የታየው፣ ዴልታ የተባለው የኮቪድ ቫይረስ ዝርያ ሥርጭቱ እየጨመረ በመሄዱ ነው ይላሉ፡፡ ያም ሆኖ በፐርስነት ሲነፃፀር ከላይ በሠንጠረዡ እንደሚታየው፣ ክተባት ያልወሰዱ ሰዎች በኮቪድ መያዝ ሆነ በኮቪድ ምክንያት ሆሰፒታል መግባትና መሞት ከ92 ፐርሰንት በላይ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡

ክትባቶቹ በተዳጋጋሚ በግልፅ ያሳዩት ወይም የሚያሳዩት ውጤት በኮቪድ ምክንያት ሆሰፒታል መግባትና መሞትን መከላከል እንደሚችሉ ነው፡፡ ከጥዋቱም የክትባቶች ጥናት ሲጀመር ይህንን ልዩነት ለማሳየት እንጂ በቫይረሱ የመያዝ አለመያዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል;; ሜዲያ በሚመቸው መንገድ ሰለሚናገር እንጂ፣ የመጀመሪያ ጥናቶች በቫይረሱ አለመያዝን አላጠኑም፡፡ ከበሽታና ከሞት መከላከልን ነው ያጠኑት፡፡ በዚህ ላይ፣ ክትባቶቹ በመሀከላቸው ልዩነት እንዳለ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክሩ ምንድነው፣ ክትባት ካልወሰዱ ሰዎች ጋር በሚደረገው ግንኙነት፣ ራስን መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ማንዳቶሪ (mandatory) የሚባል ነገር የመጣው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በሌላ ጊዜ ልመለስበት አንጂ፣ ክትባት ወስደው ምንም አይነት የአንቲቦዲ ምላሽ መሥጠት የማይችሉ ሰዎች መኖራቸውን ማወቅ፣ በተጨማሪም በዕድሜ ምክንያት ራሱ፣ ለክትባቱ ጠንካራ ምላሽ መሥጠት የማይችሉ ሰዎች አንዳሉ መገንዘብና እነዚህ ሰዎች እንዳይጋለጡ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ቡሰተር (Booster) ወይም ማጠናከሪያው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ላይ ያተኮረውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይህ እንግዳ ነገር አይደለም፣ ኮቪድ ከመከሰቱ በፊት ሌሎች ክትባቶች በምንሠጥበት ጊዜ፣ የሰውነት መከላከያ አቅም ደከም ባለባቸው ሰዎች ለክትባቱ በቂ ምላሽ እንደማይሠጡም እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ ኤይድሰ ደረጃ የደረሱ ሰዎች፣ መድሐኒት ባግባቡ ወሰድው የመከላከያ አቅማቸውን አስከሚገነቡ ድረስ ክትባቶች ቢሠጡም ላይሠሩ እንደሚችሉ ስለምናውቅ፣ የመከላከያ አቅማቸው ጠንከር ካለ በኋላ ክትባቶችን እንደገና የምንሠጥበት ሁኔታ አለ፡፡

ከዚህ መረጃ ተከትሎ፣ ሲዲሲ ሰለ ክትባቶች ዳርቻ ጉዳት በተመለከተ ያወጣው ዘገባ አለ፡፡ ባጠቃላይ አንደሚወራው ሳይሆን፣ ክትባቶቹ ሰፊ ከፍተኛ ጉዳት ያላደረሱ መሆናቸውን የሚገልፅ ነው፡፡ በሌላ ርዕስ እመለስበታለሁ፡፡ የክትባቶችን ጥቅም በግለፅ በመረጃ ስናይ ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም፣ ከላይ የቀረበው ሪፖርት ሁላችንም ሰለ ኮቪድ ክትባት ጠቀሚታ መልሰን እንድናስብ ያደርገናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ የተለያዬ ምክንያት እያቀረቡ ክትባቱን አንወስድም የሚሉ ሰዎች፣ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብና ለሌሎች ማዘን አለባቸው፡፡ በነገራችን ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ የተሠጠው የክትባት መጠን ስድስ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ይህን ያህል ክትባተ ከተሠጠ፣ ክፋት ቢኖሮው እስካሁን ይታወቅ ነበር፡፡ ምንም የማይለገምበት ሙያና ሥራ ቢሆንም፣ ክትባቱን አንወስድም ብለው፣ ሲታመሙ ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች ላይ የትዝብት ጥያቄ ያላቸው ባለሙያተኞች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ለህክምናው የሚያምኑትንና የሚቀበሉትን ያህል፣ ክትባቱ ላይ ባለሙያተኞችን ያውም ራሳቸው ክትባት የወሰዱትን አለማዳመጥን እንዴት አድርገን እንደምናብራራው ቸግሮናል፡፡  

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History