Community health 

education in Amharic 

Health and History

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

መነበብ የሚገባው

የአዲሱ የኮሮና ዝርያ የኦሜክሮን ባህሪ ከደቡብ አፍሪካ ተገለጠ

በቅርብ ጊዜ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ቁጥር ሁለት አዲሱ ዝርያ ኦሜክሮን ተብሎ እንደሚጠራ ሁሉም የተገነዘበ ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኳን በደቡብ አፍሪካ መጀመሪያ ተገኘ ቢባልም፣ በአሁኑ ወቅት በሌሎች የአለማት ክፍል በስፋት እየተሠራጨ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ አስከዛሬው ዕለት በአሜሪካ ከቪድ ከተገኘባቸው ሰዎች መሀከል 3 ፐርስንት የሚሆነው ኦሜክሮን መሆኑ ሲገለፅ፣ በኒው ዮርክ ግን፣ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ ሰዎች 17 ፐርሰንቱ ኦሜክሮን መሆኑ ተገልጧል፡፡ ፍጥነት ይላሉ ይህ ነው፡፡

ሳይንቲስቶችን ሆነ የጤና ባለሙያተኞችን ያስጨነቀው ነገር የዚህ ቫይረስ ባህሪ መረዳት ወይም ማወቅ ነው፡፡ ከዚህ በፊት መጀመሪያ በታዩበት አገር ይጠሩ የነበሩ ቫይረሶች፣ ስማቸው በግሪክ አልፋቤት እንዲሆን ተብሎ፣ ይህ ቫይረስ ኦሜክሮን ተብሎ ይጠራል፡፡ ዴልታ፣ አልፋ፣ ቤታን የምታስታውሱ ይመሰለኛል፡፡

በዚህ ውጥረት መሀል፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ዲስኮቨሪ የተባለ፣ በደቡብ አፍረካ የሚገኝ ከ3.7 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ተገልጋዮች ያሉበት የጤና ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ በሶስት ሳምንታት ጥናት በማድረግ፣ ሰለ ኦሜክሮን ቫይረስ ባሀሪ ጠቃሚና ጠቋሚ የሚሆኑ መረጃዎችን አካፍሎናል፡፡

ጥናቱ የየተደረገው ከ211 ሺ የኮቪድ ቫይረስ መገኘቱ ከተረጋገጠባቸው ምርመራ ወጤቶች ነው፡፡ ከነዚህ ውጤቶች 41 ፐርስንቱ የፋይዘር የኮቪድ ሁለቱን ክትባቶች የወሰዱ አዋቂዎች ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ በእንግሊዝኛ Breakthrough infection ሰበር ኢንፌክሽን እንበለው መሆኑ ነው፡: ማለትም ሁለት ክትባት ከወሰዱ በኋላ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ነው፡፡ ከነዚህ ምርመራዎች መሀከል ከህዳር 15 እሰከ ታህሳስ 7 ባለው ጊዜ ውስጥ በተደረገው ምርመራ 78ሺው በኦሜክሮን ቫይረስ ነው፡፡

በጥናቱ ትንተና የታየው ነገር፣ ማለትም የኦሜክሮንን ቫይረስ በተመለከተ

1ኛ የክትባት የመከላከልን አቅም በተመለከተ፣ ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች በኦሜክሮን ቢያዙም 70 ፐርሰንት ከከፍተኛ ህመምና ሆስፒታል ከመግባት መከላከል እንደሚቻል የተገለጠ ሲሆን፣ በቫይረሱ መያዝን የመከላከል አቅም በሚመለከት ግን በ33 ፐርሰንት ብቻ በቫይረሱ ከመያዝ የሚያስጥል ነው ይላሉ፡፡ ይህ እንግዲሀ ሁለት ክትባት ብቻ በወሰዱ ሰዎች ነው፡፡

2ኛ ከዚህ በፊት ኮቪድ ይዟቸው የነበሩ ሰዎች ተመልሶ በዚህ ቫይረሰ የመያዙ ሁኔታ ሲገመገም፣ ከዚህ ቀደም ተይዘው የነበሩ ሰዎች በኦሜክሮን ቫይረስ የመያዝ አደጋው ከዚህ ቀደም ከመጡት ወይም ከታዩት ቫይረሶቸ በበለጠ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተይዣለሁና ተመልሼ አልያዝም ብለው ለሚያስቡ ሰዎች አሳሳቢ ምክር ነው፡፡

በዝርዝር ሲታይ፣ ከዚህ ቀደም ዴልታ በተባለው ቫይረስ ተይዘው የነበሩ ሰዎች፣ተመልሶ የመያዝ አደጋው 40 ፐርስንት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ቤታ በተባለው ቫይረስ ተይዘው የነበሩ ሰዎች ደግሞ ተመልሰው በኦሜክሮን የመያዝ አደጋው በ60 ፐርሰንት ከፍ ያለ ሲሆን፡፡ በመጀመሪያ ዙር በመጣው የኮሮና ቫይረስ ተይዘው የነበሩ ሰዎች ደግሞ በኦሜክሮን የመያዝ አደጋው በ73 ፐርስት ከፍ ያለ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከዚሀ ቀደም በተለያዩ የኮሮና ቫይረሶች ተይዘው የነበሩ ሰዎች የተፈጥሮ መከላከያ ወይም አንቲቦዲ ቢኖራቸውም፣ አዲስ የመጣው ይህ ኦሜክሮን ቫይረስ ግን የሚበገር ሆኖ አልተገኘም፡፡

3ኛ አሁን ይህ ቫይረስ በመሠራጨት በኩል ዴልታ ከተባለው አለምን ካጥለቀለቀው የኮሮና ቫይረስ ቁጥር ሁለት ዝርያ በላይ ፈጣን መሆኑን እያስመሰከረ ነው፡፡ ከላይ ክትባቶች ላይ የሚያሳየው ጉልበት ተገልጧል፡፡ የቀረው አንዱ ዋና ጥያቄ ደግሞ በባህሪው ምን ያህል ክፉ ይሆን የሚለው ነው፡፡ ለከፍተኛ ህመምና ሞት ይዳርጋል ወይ፣ ከሆነስ ሲውዳደር ቀድመው ከታዩት ቫይረሶች በላይ ነው ወይ፡፡

የጥናቱ ባለቤቶች የሚገልፁት፣ በኦሜክሮን ቫይረስ በተያዙ ሰዎች ወደ ከፍተኛ ወይም የጠና ህመም ደረጃ መድረስና ወደ ሆስፒታል መግባትን በተመለከተ፣ በመጀመሪያ ዙር ከመጣው ቫይረስ ጋር ሲወዳደር በኦሜክሮን የተያዙ ሰዎቸ በ29 ፐርሰንት ወደ ጠና የህመም ደረጃና  ሆስፒታል የመግባት አደጋው በ29 ፐርሰንት ዝቅ ያለ ሆኖ ታይቷል፡፡ በንፅፅር ሲታይ በፍጥነት የመዛመትና ክትባቶች ያለውን ጉልበት በመገንዘብ ለከፋ የህመም ደረጃ አለማብቃቱ ትንሽ እፎይታ የሚሠጥ ነገር ነው፡፡

ሆኖም ይላሉ አጥኝዎቹ፣ ይህ የሶስት ሳምንታት የጥናት ውጤት ገነ በአፍላነቱ በመሆኑ፣ የቫይረሱ ባህሪም ሊቀየር የሚችል ሰለሚሆን ይህን ውጤት በጥንቃቄ መቀበል አለብን ይላሉ፡፡

እንዳውም ልጆችን በተመለከተ መጀመሪያ ከመጣው ቫይረስ ጋር ሲነፃፀር፣ በኦሜክሮን የተያዙ ልጆች ወደ ሆስፒታል የመግባት አደጋው በሀያ ፐርስንት ከፍ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ልጆች ላይ በርትቷል ማለት ነው፡፡

ታዲያ ምን ይበጃል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡

በመጀመሪያ ቫይረሱ እንዳይሠራጭ በቫይረሱ ላለመያዝ የሚደረጉ የመከላከያ ዘደዎችን ማጥበቅ ተገቢ ነው፡፡

ሁለተኛ፣ በሌሎች ጥናቶችም ተደጋግሞ እንደታየው፣ ክትባት የወሰዱ ሰዎች በቫይረሱ የመያዝ አደጋ ቢኖራቸውም፣ ክትባት በመውሰዳቸው ምክንያት ለከፋ ህመምና ለሆስፒታል አለመድረሳቸው ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ ክትባት መውሰዱ ታላቅ ርዳታ ይሠጣል፡፡ ሆኖም ክትባት መውሰዱ ከበሽታ የማስጣል አቅም ቢኖረውም፣ በቫይረሱ ከመያዝ የማስጣል ችሎታው እያነሰ መሄዱ ግልፅ ነው፡፡ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው፣ ዴልታ በተባለው ቫይረስ እንደታየው ሁሉ፣ ክትባት የወሰዱ ሰዎች ሶስተኛ ወይም ማጠናከሪያ ክትባት (Booster) ሲወስዱ በሰውነታቸው ውሥጥ ከፍተኛ የሆነ የአንቲቦዲ ወይም የመከላከያ አቅም ሰለሚገነቡ በቫይረሱ ከመያዝ የመከላከል አቅማቸው ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ክትባቱ እንደልብ ባላቸው ህገራት ማጠናከሪያ ለሁሉም አንዲሠጥ የሚደረገወ፡፡

 ክትባቱን የማግኘት ዕድሉ ያላችሁ ሰዎች፣ በቂ ግንዛቤ ያገኛችሁ ሰለሚመስለኝ ማጠናከሪያው መውሰዱ ትልቅ ጥቅም እንዳለው መድገምም አስፈላጊ አይሆንም፡፡ እዚህ ላይ ከዚህ በፊት በኮቪድ ተይዘው የነበሩ ሰዎች የተፈጥሮ መከላከያ ሊገነቡ ቢችሉም፣ መከላከያው ክትባት ከወሰዱ ሰዎች ሲወዳደር ደካማ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ የበለጠ ጠቀሜታ የተገኘው ከዚህ በፊት ተይዘው የነበሩ ሰዎች በላዩ ላይ ክትባት ሲወስዱ የመከላከል አቅማቸው ክትባት ብቻ ከወሰዱ ሰዎች በላይ ሆኖ መታየቱ ነው፡፡ ሰለዚህ ተይዤ ነበርና የሚለው ሁኔታ ሊያዘናጋን አይገባም፡፡ ተከተቡ!!