​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

Monkeypox Rash Photos
Photo credit: UK Health Security Agency

https://www.cdc.gov/poxvirus/monkeypox/clinicians/clinical-recognition.html

ስለ ሞንኪ ፖክሰ (Monkeypox) ሊያውቁት የሚገባ

Gebeyehu Teferi, M.D. July 05/2022

 ሰሞኑን በምዕራባውያን የዜና አውታሮችና የሕክምና ማዕከሎች ጠንከር ብሎ እየተነገረለት ያለው ሞንኪ ፖክስ (የዝንጀሮ ፈንጣጣ) ሰለሚባል በሽታ ለአማርኛ አንባቢ ወገኖች ትንሽ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡

ከስሙ አንጀምር

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1958 በላቦራቶሪ ውስጥ ለጥናት በተሰበሰቡ ዝንጀሮዎች ላይ ፈንጣጣ የመሰለ በሽታ በመከሰቱ ነው የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚል ስም የወጣለት፡፡ ላቦራቶሪ በአውሮፓ ነበር፡፡ አሁን ስሙን ለመቀየር እየታሰበ ነው፡፡

በሽታው ምንም ከፍተኛ ድምፅ ቢሰማበትም በጣም አነስ ብለው ከሚከሰቱት በሽታዎች አንዱ ነው፡፡ ይህንን በሽታ የሚያስከትለው ቫይረስ ኦርቶፖክሰ ከሚባሉ የቫይረስ ወገኖች ከዚያም ፖክስቫይሪድ ከሚባል ቤተሰብ ነው፡፡ የዚህ ቫይረስ ወገን የሆኑ ሌሎች ቫይረሶች በተለይም በስፋት የሚታወቀውን የፈንጣጣ በሽታ Small Pox የሚያሰከትለው ቫይረስ ቫሪዮላ ከሚባል ቤተሰብ ሲሆን፣ የከብት ፈንጣጣ (ካው ፖክስ) የሚባለውን ቨሽታ የሚያሰከትለው ካው ፖክስ ቫይረስ ይገኙበታል፡፡

አሁን ለምን አንደ ትልቅ ችግር ታየ ለሚለው ጥያቄ፣ በሽታው በአለም አቀፍ ደረጃ መሠራጨትና መታየት በመጀመሩ ነው፣ እንጂ አፍሪካ ውስጥ በጣም በመጠኑ በየጊዜው ሲከሰት የኖረ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ ሌላ መድልዎ ተብሎ በአፍሪካውያን በኩል ስሞታ የተሰማው፡፡ እሰከዛሬ ግድ ያልነበራቸው፣ አሁን ወደ ነሱ ሲገባ ትኩረት ሰጡት ተብሎ ነው፡፡

ሥርጭቱ፣ ቁጥሩ እየጨመረ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ4ሺ ሰዎች በላይ የተገኘባቸው ሲሆን፣ በአሜሪካ ከ350 ሰዎች፣ ዲሲን ጨምሮ በ27 ስቴቶች ሪፖርት ተደርጓል፡፡ (የሲዲሰ ዘገባ)፡፡

ይህ በሽታ በአብዛኛው የሚታየው ግበረ መሰል ፆታ ግንኙነት በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ነው፡፡ (ወንድ ለወንድ)፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ የአግላይ ስሜት እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ በሽታው በግብረ ሥጋ ግንኙነት መተላለፉ ጠንካራ መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ላይ የሚተላለፈው ለረዥም ሰአት በጣም የተቀራረበ የአካል ግንኙነት ሰለሚያደርጉ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው፣ ሰዎቹ፣ በሰልክ ወይም ኮምፒውተር ላይ በሚጫን (አፕ Apps) አማካኝነት፣ ከማያውቁት ሰው ጋር ለግብረ ሥጋ ግንኙነት ቀጠሮ በመያዝ፣ ከዚያም ግንኙነት ሰለሚያደርጉ ነው፡፡

ሰዎች ለቫይረሱ ከተጋለጡ በኋላ የበሽታ ምልክት የሚታይባቸው ከ5 አስከ አስራ ሶሰት ባሉት ቀናት ውሥጥ ነው፡፡ ይህ በአንግሊዝኛ Incubation Period ተብሎ ይጠራል፡፡

የበሽታ ስሜት፤ የመጀመሪያዎቹ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች ምንም ለየት ያላሉ እንደ ትኩሳት፣ የሰውነት ድካም፣ ራስ ምታት፣ ናቸው፡፡ የመግቢያ ስሜቶች መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ነው እንግዲህ ለየት ያለው የሰውነት ሽፍታ የመከሰተው፡፡ እነዚህ ሰውነት ላይ የሚወጡት ሽፍታዎች በአንድ ላይ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ብቅ ይላሉ፡፡ ሽፍታዎቹ መጥተው አስከሚሄዱ ድረስ አራት ደረጃዎች ይኖራቸዋል፡፡ የቁስሉ አይነት መሆኑ ነው፡፡ መጀመሪያ ጠፍጣፍ ሽፍታ፣ ከዚያ ደግሞ አበጥ ወይም ቁብ ቁብ ያለ፣ ተከትሎ ደግሞ ውሀ ወይም መግል የቋጠረ፣ በመጨረሻም ረግፎ መክሰም ነው፡፡ ቁስሎች በአብዛኛው የህመም ስሜት ይፈጥራሉ፣ እየረገፉ ሲመጡ ደግሞ የማሳከክ ስሜት ይፈጥራሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የዕጢዎች እብጠትም ይከሰታል፡፡ በአብዛኛው በፊትና በመዳፍ ወይም በእግር ጫማ ላይ ይከሰታሉ፡፡

በታመሙ ሰዎች ላይ ህመሙ ባጠቃላይ ከሁሉት አስከ አራት ሳምንታት ሊቆይ ይችላል፡፡

ዋናው ነገር በሽታው ከሰው ወደሰው እንዴት ነው የሚተላለፈው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በተጨማሪም ምን ያህል አሳሳቢ ነው? የመተላለፊያ መንገዶችን በውል መረዳት በጣም ተገቢ ነው፡፡ ማድረግ ሰለሚገባን ጥንቃቄም ከዚሁ ነው መረዳት የምንችለው፡፡ መተላለፊያ መንገዶች

  • በቫይረሱ ምክንያት ከተከሱት ቁሰል ወይም ሽፍታ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ሲኖር፣ ማለትም ቁስሎቹን ወይም ከቁስሉ የሚመነጩ ፈሳቾን መነካካት
  • በትንፋሽ በኩል፣ እንደ ኮቪድ ሳይሆን፣ ለረዘም ላላ ጊዜ በጣም በቅርበትና የአካል ለአካል ግንኙነት ሲኖር፣ ለምሳሌ መሳሳም፣ መተሻሸት፣ መተቃቀፍና የግብረሥጋ ግንኙነት
  • ቁስል ወይም የቁስል ፈሳሽ ጋር የተነካኩ ዕቃዎችን፣ ልብሶችን በመነካካት
  • ነብሰ ጡር ሴቶች ላልተወለደው ልጅ በማህፀን በኩል


  • በዚህ ቫይረስ የተለከፉ አንስሳት ጋርም ንክኪ በማድረግ ወይም ሥጋቸውን ለምግብነት በማዘጋጀት በመብላትም በበሽታው መያዝ እንደሚቻልም ይጠቆማል፡፡


በበሽታው የተያዙ ሰዎች የሚያስተላልፉበት ወቅት የሚጀምረው፣ ከላይ ከተጠቀሰው የመግቢያ ስሜቶች ከተሰማቸው ቀን ጀምሮ፣ ቁስሉ ረግፎ በአዲስ ቆዳ አስከሚተካ ድረስ ነው፡፡

በሽታውን ከሌሎቸ በሽታዎች ለመለየት ሀኪሞች ማድረግ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ አንግዲህ ታማሚው የት ሄዶ ነበር፣ ከማን ጋር ተገናኝቶ ነበር የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ጨምሮ ነው፣ በአካል የታዩትን ቁስሎችን በማየት ነው፡፡ ዋናው ነገር፣ ሀኪሞች ታማሚውን ሲመረምሩ፣ የመከላከያ ልብሶች፣ ማስክን ጨምሮ በማደረግ ነው፡፡ ወደ መርማሪዎች የመተላለፍ ዕድል አለ፣ ካልተጠነቀቁ በስተቀር፡፡ በኮቪድ ምርምራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያተኞች የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡

አይነተኛ ምርመራው ግን ከቁስሉ ላይ ናሙናዎችን ወስዶ ለምርመራ መላክ ነው፡፡ በአሜሪካ ይህንን የቫይረስ ምርመራ ማድረግ የሚችሉ ላቦራቶሪዎች ውሱን በመሆናቸው፣ ናሙናዎቹ ለሰቴቶች የጤና ሀላፊዎች እንዲላክ ነው የሚጠየቀው፡፡ ተላላፊ ወይም ተዛማች በሽታ እንደመሆኑ፣ በበሽታው ተይዟል የሚባል ህሙም ካለ፣ መርማሪው ሀኪም ወዲያውኑ ለመንግሥት ማለት ለስቴት የጤና ቢሮ ሰዎች በመደወልና በማስታወቅ መመሪያ መቀበል ይኖርበታል፡፡ ተላላፊ በሽታዎችን ለመንግሥት ሰዎች ማስታወቅ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

በዚህ በሽታ የተያዘ ህሙም ካለም ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዳይገናኝ ተገልሎ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

ህክምና፤ ይህ ፅሁፍ እስከተፃፈ ድረስ፣ የሚታወቀው አንድ ሰው ብቻ መሞቱ ነው፡፡ ሟቹም የሰውነት የመከላከያ አቅሙን ያደከሙ ሌሎች በሽታዎች ነበሩበት፡፡  ለዚህ በሽታ እንደህክምና የሚወሰዱ ከዚህ ቀደም ለፈንጣጣ በሽታ ከተፈቀዱ መድሐኒቶች አንዱ ቲኮቫይራመት የሚባል ፀረ-ቫይረስ በአፍ የሚወሰድ እንክብል ነው፡፡ መድሐኒቱ በመደበኛ ፋርማሲ አይገኝም ነገር ግን በሲዲሲ በኩል ወይም በስቴት የጤና ቢሮዎች በኩል ይገኛል፡፡ ለወደፊት አቅርቦቱን እናሰፋለን ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፣ ለሌሎቸ ቫይረሶች ህክምና የምንገለገልባቸው ሳይዶፎቪር እና ብሪንሳይዶፎቪር የሚባሉ መድሐኒቶች አሉ፡፡ ከመድሐኒቶቹ በተጨማሪ፣ ፀረ- ቫይረስ ኢሙኖገሎቡሊን የሚባል ፕሮቲንም አለ፡፡

ለመከላከያ አገልግሎት ሁለት አይነት አቀራረብ አለ፡፡ የመጀመሪያው በርግጥ በዚህ በሽታ ከተያዙ ሰዎች ጋር የተገናኘና የተጋለጠ ሰው በሽታ እንዳይዘው የሚሠጥ ነው፡፡ Poste Exposure prophylaxis ይባላል፡፡ ለዚህ አገልግሎት የሚውሉ ሁለት የክትባት አይነቶች አሉ፡፡ አንደኛው ለፈንጣጣና ለዝንጀሮ ፈንጣጣ መከላከያ ተብሎ የተሠራና በ2019 ዕድሜያቸው ከ18 አመት በላይ ለሆኑ ሰዎች የተፈቀደ ክትባት ነው፡፡ JYNNEOS ጂኖስ ይበላል፡፡ ሌሎቸ ሰሞችም አሉት( IMVAMUNE, IMVANES, MVA)፡፡ ይህ ክትባት ተመልሶ መራባት ከማይችል ኦርቶፖክስ ከተባለ ቫይረስ የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚህም ተመልሶ መራባት ባለመቻሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ክትባት ነው፡፡ ሌላ ግን ACAM2000 የተባለ ክትባት ደግሞ አለ፡፡ ይህ ግን ነብስ ያለው ተመልሶ መራባት ወይም መሠራጨት ከሚችል ቫይረስ ሰለሚሰራ ተጠቃሚነቱ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ እንደ አማራጭ ግን ይያዛል፡፡ ሌላው የመከላከያ መንገድ፣ በሽታው በተሠራጨበት ቦታ ሊያዙ ይቻላሉ ለሚባሉ ሰዎች የሚሠጥ መከላከያ መንገድ ነው፡፡ አስቀድሞ ማለት ነው በእንግሊዘኛ Pre Exposure prophylaxis PrEP ተብሎ ይጠራል፡፡ እነማን በዚህ መንገድ መከላከያን መውሰድ እንዳለባቸው ጊዜያዊ መመሪያዎች አሉ፡፡ ለሁሉም ሰው የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከላይ እንደተገለጠው የሚያተኩረው በሚያደርጉት ነገር ምክንያት ለበሽታው ሊጋለጡ የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡

ምክሩ፣ ባሁኑ ጊዜ ለአብዛኛው ሕብረተሰብ የሚያሰጋ ደረጃ ያልደረሰ ቢሆንም ሰለጉዳዩ መከታተል ጥሩ ነው፡፡ በወቅቱ በሽታው በብዛት የሚገኝባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ቤተሰብ ከሆኑ ግን፣ ከሌሎች ሰዎች በበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ሁኔታው ሊቀየር ይችላል የሚባል ፍራቻ አለ፣ ስለዚህ ችላ ሳይሉ ማዳመጡ ተገቢ ይሆናል፡፡

ከማጠቃለሌ በፊት ግን፣ በዚሀ በሽታ ቢያዙ ከፍተኛ ወይም የጠና ወይም የከፋ ደረጃ ላይ ሊወድቁ ይቻላሉ ሰዎችን ልዘርዝርላችሁ፤

  • እንደሚታወቀው የሰውነት የበሽታ መከላከያ አቅማቸው ደካማ የሆኑባቸው ሰዎች
  • ዕድሜያቸው በተለይም ከስምንት አመት በታች የሆኑ ህፃናት
  • ነብሰ ጡርና ጡት የሚያጠቡ ሴቶች
  • የቆዳ ሽፍታ የሚወጣባቸው ሰዎች ለምሰሌ በአለርጂ ምክንያት፣ እናም ቆዳቸው በየጊዜው የሚላላጥ ወይም የሚረግፍ ሁኔታ ያለባቸው ሰዎች ይጨምራል፡
  • የሞንኪ ፖክስ ቫይረሰ፣ በአይን በኩል፣ በአፍ፣ በፆታ አካል በኩል የሚገባ ከሆነም ችግሩ ሊከፋ ይችላል፡፡


ወደፊት ነገሩ እየተለወጠ ከመጣ፣ ተጨማሪ ፅሁፎችን አቀርባለሁ፡፡ የሚወጡት ሽፍታዎች ምን እንደሚመስሉ ላማሰየት ምስሎችን ይመልከቱ፡፡ እነዚህን ሽፍታዎች ካዩ፣ በተለይም ትኩሳት አብሮ ከታየ ቀደም ብሎም ቢሆን መጠራጠር ተገቢ ሰለሆነ፣ ቁስሎቹን ሸፈን አድርገው ወደ ህክምና ቦታ መሄድ ተገቢ ነው፡፡ ለራስ ህክምና ማግኘት ተገቢ ሲሆን ወደሌሎች በተለይም የቤተሰብ አባላት እንዳይሻገር ማድረግ ሰብአዊነት ነው፡፡