Health and History

አድዋና ዛሬ

በአድዋ ድል 126ኛ አመት አከባበር የቀረበ ንግግር

​​ዕውነት የመንገድ ሥም በከኒንግሃም መሰየም ነበረበት?

በአዲስ አበባ ከተማ ቁጥራቸው በርከት ያሉ በእንግሊዛውያን የተሰየሙ መንገዶችና ትምህረት ቤቶችም አሉ፡፡ ወደኋላ ታሪክ ሲመረመር፣ የጄኔራል ከኒንግሀም ነገር ጥያቄ አስነሳብኝ፡፡

ነገሩ እንግዲህ ሰፋ ያለ፣ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ታሪክ አትማሩ፣ አትስሙ፣ ሲሉ የከረሙት ይህንን ያለፈ አደጋ አንዳይታወቅ፣ ለምናልባትም ያንን ያለፈ አደጋ በተራቀቀ መልክ ለማምጣትም ይሆናል፡፡

ከጣልያን አጭር ወረራ በኋላ፣ ጣልያኖች መሸነፍ ሲጀምሩ፣ በተመሳሳይ ቀን፣ አፄ ኃይለ ሥላሴ ደብረ ማርቆስ በገቡበት ዕለት በእንግሊዙ ጄኔራል በከኒንግሃም የሚመራው ጦር አዲስ አበባ ይገባል፡፡ ልብ በሉ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ መናገሻ ከተማው ወደ አዲስ አበባ ልምጣ ሲሉ፣ ኒውቦልድ ከተባለው እንግሊዛዊ የተሠጠው መልስ፣ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወደ መቶ ሺ አርበኛ ኢትዮጵያውያን ተዋጊዎች በአዲስ አበባ ሰለሚገኙ በንጉሡ መምጣት ምክንያት በደስታ ጣልያኖችን ይፈጃሉ የሚል ነበር፡፡ ጃንሆይ፣ የዚህ መልስ አልጣማቸውም፡፡ ከጃንሆይ ጋር አብሮ የሚገኘው ጄኔራል ዊንጌትም በነገሩ ደስተኛ አልነበረም፡፡

በዚህ መሀል፣ ከአዲስ አበባ የሚመጣው ዜና አስቀያሚ ነበር፡፡ “ነፃ አውጭ” የተባሉት የነጭ መኮንኖች፣ ኢትዮጵያውያኑን በገዛ አገራቸው በአንዳንድ ሆቴሎችና በአንዳንድ የህዝብ ቦታዎች እንዳይገቡ ዕገዳ አደረጉ፡፡ ይች ነችና አፓርታይድ፡፡ በዚህ ላይ የጂኔራል ከኒንግሃም አስተዳደር ከነፃ አውጭ ይልክ አንደ ቅኝ ገዥ አይነት ባህሪም እያሳየ ነበር፡፡ ኢትዮጵያኖችም ሥጋታቸው የነበረው፣ እንግሊዞቹ የያዙትን እንደመሥጠት ጠቅለው ለመያዝ አስበዋል የሚል ነበር፡፡ ለሥጋቱ በቂ ምክንያትም ነበር፡፡ የፈረንሳዩ መሪ ደጎል በዚያን ጊዜም አንዲህ ብሎ ነበር፤ “እንዴት ያለ አንግዳ ነገር ነው፤ ኢንግላንድ አሁን ሁሉንም፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማልያና ሱዳንን ልትይዝ ነው የሚል ነበር፡፡”

በዚህ ላይ ማስታወስ የሚገባን፣ ኤርትራና ሶማሊያ በጣልያን እጅ ሰለነበሩ፣ በእንግሊዞች እጅ ያሉ የጠላት(የኢጣልያ) ቦታዎች ናቸው፣ ሰለዚህ ጣልያን ስምምነት እስክትፈርም ድረስ በእንግሊዞች ሥር መተዳደር ነበረበቸው፡፡ የአስተዳደሩ ፎርሙላ የተያዙ የጠላት ቦታዎች አስተዳደር የሚባል ነበር፡፡ Occupied Enemy Territories Administration በእንግሊዝኛ ምህፃረ ቃል OETA፡፡ ጣልያኖቹ እየተዳከሙ በመምጣታቸው እንግሊዞቹ የያዟቸውን የጣልያን ቦታዎች እንደ ቅኝ ግዛት በመቁጠር የሚይዟቸውን ቦታ ማስፋት ቀጠሉ፡፡ እንደምታስታውሱት ኢትዮጵያን ዙርያዋን በተለይም በደቡቡ በኩል የነበሩ ቦታዎች በእንግሊዞች ቅኝ ግዛት ሥር ነበሩ፡፡ የነዚህ ቦታዎች አገረ ገዥዎች፣ በጣልያኖች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን እየወሰዱ መጠቅለል ይፈልጋሉ፡፡ ይህ አስተዳደር (OETA) ጃንሆይን ሳያማክር በኢትዮጵያም ነፃ የወጡ ቦታዎች በሚል የኢትዮጵያን ቦታዎች ማጠቃለል ጀመረ፡፡ እንግሊዞቹ እየመሠረቱት ከነበረው የፖሊስና ህግ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያውያኑ ሊወስዱ የጠበቁትን የጣልያን ንብረቶች በሙሉ ያለ ምንም ልዩነት መውረስ ጀመሩ፡፡ የኢትዮጵያውያኑ ጥርጣሬም እየጠነከረ ሄደ፡፡ ጃንሆይም ቢሆን በዚህ ጉዳይ እንግሊዞችን ዘራፊዎች ሆኑ በሚል አወገዙ፡፡ የኢትዮጵያ ቦታዎችም አሉ ጃንሆይ፣ ግዛታቸው ለጊዜው ተይዞ ቢሆንም  በቅኝ ግዛት ሥር አልወደቀም፤ ሰለዚህ በ OETA ሥር ሊወድቅ አይችልምና ሙሉ በሙሉ ወደኔ ይመለስ አሉ፡፡  

ነገሩን የሚያከፋው ሌላው የእንግሊዞቹ ድብቅ አላማም ነበር፡፡ ጃንሆይ በደብረ ማርቆስ እንዳሉ፣ በካይሮ የተቀመጠው የእንግሊዙ ባለሥልጣን፣ ሰር ፊሊፕ ሚቸል፣ ጃንሆይን በጎጃም አስቀምጦ እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ፣ ኤርትራን በሚመለከት፣ ከቀሪው ኢትዮጵያ በተለየ በኢጣልያ ቅኝ ሥር ሰለነበረች በ OETA ፎርሙላ መያዝ መፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ ኤርትራ ሲባል ትግራይን ጨምሮ ነው በማለት ትግራይንም በመጨመር ቦታዎቹን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አልፈለገም፡፡ በዚህ ጊዜ፣ እንግሊዞቹ “ታላቋ ኤርትራ” የሚባል ሀሳብ ነበራቸው፡፡

በዚህ ላይ ጃንሆይን ያሳሰባቸው፣ የኢትዮጵያ የባላባት መሪዎች ናቸው፡፡ ከነሱም አንዱ የአፄ ዮሐንስ የልጅ ልጅ ራስ ሰዩም መንገሻ ነበሩ፡፡  በግዞት ከነበሩበት ከኢጣልያ ተመልሰው በጣልያኑ ጁኔራል ናዚ በቦታቸው እንዲያስተዳደሩ ተሹመው ነበር፡፡ አትቸኩሉ፡፡ ከዚያም ከከእንግሊዞቹ ጋር ይገናኛሉ፡፡ በነገራችን ላይ ራስ ሥዩም ተምቤን ላይ በኢጣልያ ያልደረሰባቸው ነገር አልነበረም፡፡ በሠራዊታቸው ላይ ቦምብና የመርዝ ጋዝ ጨምሮ፡፡ ጣልያን ግን ለማባበል እየሞከረ ነበር፡፡ ራስ ስዩም በኃይለ ሥላሴ ላይ ለማኩረፍ በቂ ምክንያት ነበራቸው፡፡ አባታቸው በቁም ሥር እያሉ ነው የሞቱት፡፡ ሰለዚህ ትልቅ ፍራቻ አለ፤ ነገር ግን ራስ ስዩም የመጀመሪያ የሰላምታ ደብዳቤ ለራስ ካሳ ይልካሉ፣ የናፍቆትና የሰላም ምኞት ነበር፡፡ ለኃይለ ሥላሴ አለመላካቸው ፍራቻውን ጨምሮታል፡፡

ጣልያኖች ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲፈልጉ የሚያባብሏቸው መሪዎች ብዙ ነበሩ፡፡ ሁሉም ቢሆን ከጃንሆይ ጋር ቂም ነበራቸው፣ ተበድለናልም ይሉ ነበር፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሰዎች ቁርጥ ቀን ላይ ነው የሚፈተሹት፡፡

ከራስ ስዩም ውጭ፣ የጎጃሙ ራስ ሀይሉ ደግሞ ሌላው ባለጉልበት መሪ ነበሩ፡፡ እሳቸውም ከጃንሆይ ጋር ትልቅ ጠብ ነበራቸው፡፡ በደብረ ማርቆስ የሚገኙት የጃንሆይ ዕጣ በራስ ሀይሉ እጅ ነበር፡፡ የራስ ሀይሉ ጦርና የአርበኞች ቁጥር እየጨመረ ጃንሆይ ከዊንጌት ጋር ይዘውት ከመጡት ጦር በላይ ነበር፡፡ ጃንሆይ እንግሊዞቹን የጠየቁት  ራስ ሀይሉ በካርቱም እንዲዘገዩ እንዲደረግ ነበር፡፡ እንግሊዞቹ የሰሙም አልመሰሉም፡፡ ነገር ግን በዚያን ጊዜ፣ ምንም ባላንጣነት ቢኖራቸውም ራስ ሀይሉ ጃንሆይን እንደሚቀበሉ ገለጡ፡፡ ለጃንሆይ ገቡ፡፡

ንጉሡና አብሯቸው የነበረው ጄኔራል ዊንጌት ሁኔታውን በትግሥት ነው የተቀበሉት፡፡ ይልቁንስ እንዴት ወደፊት እንደሚያጠቁ ነበር የሚያስቡት፡፡ በዚያን ጊዘ ከነበሩ የጣልያን ሀይሎች፣ ሁለት እንዳለ ያልተነኩ ነበሩ፡፡ አንደኛው በወሎ በኩል፣ በደሴ፣ ጄኔራል ፍሩቺ የሚባል ሲሆን ሌላው ደግሞ ጎንደር የመሸገው ጄኔራል ናዚ ነበር፡፡ የፈረደበት ጎንደር አንድ አመት ትርፍ ተይዞ የነበረው በዚሁ በጄኔራል ናዚ ምክንያት ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ጄኔራሎቸ ሁኔታውን ይቀለብሱት ይሆን የሚል ሥጋት ነበር፡፡ ሆኖም ጣልያኖቹን፣ አርበኞቹ እነ ፊታውራሪ ብሩ፣ እነ ዳኘው ተሰማ በደፈጣ ውጊያ ከእንግሊዞቹ ጋር በማቀናጀት ጥቃታቸውን ቀጥለው ነበር፡፡ ደብረ ታቦር ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ደብረ ታቦርን ሳይቆጣጠሩ ጎንደር መግባትም የማይሞከር ነው፡፡

ሌላው ሰው ደግሞ የልጅ ኢያሱ ልጅ የሆኑት ልጅ ዮሐንስ ነበሩ፡፡ ህም በኢያሱና በጃንሆይ ያለፈውን ሁኔታ የሚያውቅ ሰው፣ ልጅ ዮሐንስን መጠቀም ይፈልግ ይሆናል፡፡ ጣልያኖችም ሞክረውት ነበር፡፡ ልጅ ዮሐንስ እንደ ራስ ስዩም ሁሉ ለዙፋኑ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ተፎካካሪ፡፡ ልጅ ዮሐንስ እንደ ብዙ ከጣልያን ጋር አብረው የነበሩ የሚመስሉ በውስጥ ለውስጥ ግን ከአርበኞች ጋር የሚላለኩ ሰዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ከራስ አበበ አረጋይ ጋር ይላላኩም ነበር፡፡ ሰለዚህ ጃንሆይ ተመልሰዋል የሚል ዜናና ብዙ ቃል የተገባበት ደብዳቤ ከጃንሆይ ሲደርሳቸው፣ ምንም እንኳን በጃንሆይ ላይ እምነት ባይኖራቸውም ጦራቸውን ይዘው ተቀላቀሉ፡፡ ሰውየውን አይደለም ያዩት፡፡ ኢትዮጵያን ነበር፡፡

በዚህ መሀል ደግሞ፣ ከጃንሆይ ጋር ቁርሾ የነበራቸው ደጃዝማች አያሌው ብሩ ደግሞ በጄኔራል ናዚ ላይ በመነሳት ከእንግሊዘቹ ጦር ከሲመንድስ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በጌምድር አይገነጠልም፣ አለዚያማ እንግሊዞቹ አያሌውን እንዳባበሉ ይታወቃል፡፡ አደጋው ከፍተኛ ነበር፡፡ ጎጃም፣ በጌምድር፣ ወሎ እና ትግራይን ፈልቅቆ ለማውጣትና ንጉሡን ብቻቸውን ለማስቀረት ታስቦ ነበር፡፡ ደባው የገባቸው መሪዎቹ በቁርጥ ቀን ንጉሡን መነጠል ማለት ኢትዮጵያን መሸንሸን መሆኑ ገብቷቸዋል፡፡

ዋናው የተፈራው ትግራይ ትገነጠል ይሆን የሚል ነበር፡፡ ሰለዚህ የራስ ስዩም አካሄድ ወሳኝ ነበር፡፡ በዚህ መሀል ራስ ስዩም ለጃንሆይ በቀጥታ ደብዳቤ ይልካሉ፡፡ በደብዳቤያቸው የገለፁት ዋናው ነገር፣ ሁሉን የሚችለው ፈጣሪ ወደ አገርዎ ሰለመለሰዎ፣ አሁን መደበኛ ነባር ኢትዮጵያን እንዲመሠርቱ ፈጣሪ ይርዳዎት የሚል ነበር፡፡ በራስ ስዩም፣ አገር ወዳድነት፣ ያ ሁሉ ማባበያ እያለ፣ ኢትዮጵያን መረጡ፡፡ ሰለዚህ ጃንሆይ በየቦታው የነበራቸው ሥጋት አገሬን ባሉ ኢትዮጵያውያን መሪዎች ምክንያት ተወገደላቸው፡፡ አሁን ወደ አዲስ አበባ መመለሱን ነው ያተኮሩበት፡፡ በዚህም ምክንያት እንግሊዞቹ የገቡትን ቃል ይፈፅማሉ ለማለት በቂ ምክንያት አላቸው፡፡

ሰለዚህ ወደ አዲስ አበባ እንቅስቃሴው ሲጀመር፣ ደጃዝማች እንዳልካቸው መኮንን በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ይልካሉ፡፡ የንጉሡን መመለስ እንዲያዘጋጁ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የጦር መኮንኖችም ወደ አዲስ አበባ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር፡፡ ሞጣ ሲደርሱ እንዲመለሱ ታዘዙ፡፡ በአፐሪል 22፣ ሚያዝያ ላይ፣ ከጄኔራል ከኒንግሃም ወደ ዊንጌት ቴሌግራም ይላካል፡፡ ትዛዙም የሚለው ማንኛውንም ንጉሡ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲያቆም ነበር፡፡

ታሪክ ጥሩ ነው፡፡ ዊንሰተን ቸርችል በአፕሪል 9፣ ከከፍተኛ የእንግሊዝ ጦር ባለሥልጣናት (የመከላከያ ኮሚቴ) ጋር ውይይት አድርጎ ነበር እናም ትዛዝ ሲያስተላለፍ ንጉሡ በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ የሚል ነበር፡፡ የዚህ የቸርችል ትዛዝ ሲሰማ ንጉሥ ወደ አዲስ አበባ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ፣ ዊንጌት ችግር ላይ ነበር፡፡ ምከንያቱም የጄኔራል ከኒንግሃም ትዛዝ፣ አትንቀሳቀስ የሚለው አልተነሳለትም ነበር፡፡ ሰለዚህ ንጉሡን በጉልበት ማቆም እንደማይፈልግ ይልቁንሰ አጅቧቸው አዲስ አበባ ድረስ እንደሚሄድ ገለፀላቸው፡፡ ንጉሡም በአፕሪል 27 ከደብረ ማርቆስ ተንቀሳቀሱ፡፡ አዲስ አበባም ገቡ፡፡ ንጉሡ አዲስ አበባ ሲገቡ፣ ራስ አበበ አረጋይ መሉ ሀይላቸውን በመያዝ ሁኔታውን ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ ከኒንግሃምን የራስህ ጉዳይ እንደማለት ነው፡፡

እንግዲህ ባጭሩም ቢሆን ኢትዮጵያ እንዴት እንደተረፈች ተመልክተናል፡፡ ለውጥ ወይም የሽግግር ሁኔታ ሲፈጠር፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ፀረ-ሀገር ሀይሎች የማይሞክሩት ነገር የለም፡፡ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያን ከመሸራረፍ ያዳኗት፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ባላንጣ የነበሩ፣ ለመበደላቸው በቂ መረጃና ምክንያት የነበራቸው ቀንደኛ የኢትዮጵያ መሪዎች፣ ምንም እንኳን ከጣልያኖች ጋር አብረው የሠሩ ቢመስሉ፣ ቀን ሲያዘነብልና ቁርጥ ቀን ሲመጣ ለአገራቸው በማድላት ይኸው አስረከቡን፡፡ በርግጥ የእንግሊዝ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ቸርችል የሠጡት ውሳኔ ወሳኝም ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ቂም እያላቸው አገሬ ትበልጣለች ብለው ለኢትዮጵያ የወገኑት መሪዎች በተለይም ከላይ የተጠቀሱት አራቱ በየፊናቸው ቢሄዱ ኖሮ፣ ቸርችልና ባላሥልጣናቱ ምን ይወስኑ ነበር ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው፡፡

ቢዘህ ጊዜ፣ እንኳን ለጠላት ለወዳጅም የተባበረ ክንድ ማሳየት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ባንዳ ሲባል አንሰማለን፡፡ የውነተኛው ከሀዲ ባንዳ በመሪው ላይ ማኩረፉ ሳይሆን በኩርፊያው አሳቦ አገሪቱን ሊበትኑ ካሰቡ ወገኖች ጋር መወገንና ለጥቃቱ መሳሪያ መሆን ነው፡፡ በተለይም አማራጩ እያለው፡፡ የአገር ጉዳይ ሲመጣ የነሱ የግል ቁርሾ ሚዛን አይመታም፡፡ ለበደል በቂ ምክንያት ቢኖርም እንኳን ቅድሚያ ለሀገር መሠጠት አለበት፤ በተለይም አገሪቱ ላይ ትልቅ ጥፋት በሚያንዣብበት ወቅት፡፡ ከራስ ሀይሉ፣ ከልጅ ዮሐንስ፣ ከደጃዝማች አያሌው ብሩ እናም ከራስ ስዩም መንገሻ የምንማረው ይህንኑ ነው፡፡ ከተፎካካሪ በላይ ባላንጣም ነበሩ፡፡ ይሁንና አገር በልጦባቸው አገር አዳኑ፡፡ አሁን፣ በቀጭኑም በወፍራሙ ሰበብ በመፍጠር ከለየላቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የሚያብሩ፤ ሌሎች ደግሞ ከኩርፊያቸው ብዛት ኢትዮጵያ የራሷ ጉዳይ የሚሉ ወገኖች እየታዩ ነው፡፡ የድሮ ሰዎች ወደው እኮ አይደለም የተቀባ ይንገስ የሚሉት፣ ነጋሽ ነኝ ባዩ በተነሳ ቁጥር ሰላም እንደማይኖር ተገንዘበው ነው፡፡ ወደኋላ ተመልሰን በአዲስ መመዘኛ ባንዳኛቸው ጥሩ ነው፡፡ ያደረጉትን አርገው አገር አስረክበዋል፡፡ አሁን ደግሞ፣ “የተመረጠ ይምራ” ነው፡፡ ህዝቡ በትክክል ተወያይቶበት፣ በነፃና ግልፅ ባለ ሁኔታ መምረጥ ከቻለ፣ ወንበር በዚያ በኩል ነው የሚመጣው፡፡ መምጣትም ያለበት፡፡

እና ስለ ከኒንግሀም መንገድ ምን ትላላችሁ?

ኢትዮጵያውያን፣ አብዛኞቹ፣ ቸርና መሀሪ ናቸው፡፡ ብዙ የታሪክ መረጃዎችም አሉ፡፡ ይቅር ሲሉ ይቅር ነው፡፡ አሁንም በትግሥት እያሳዩት ያለው ባህሪ በማንም አገር ያልታየ ነው፡፡ የተጠበቀው ጎረቤት በጎረቤቱ ይነሳል ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ በአጭሩ፣ የኢትዮጵያ አብዛኛው ህዝብ ያልተዘመረለት ጀግና ነው፡፡

እንደኔ እንደኔ፣ የከኒንግሃም ስም ይቀመጥ፣ እንዲያውም ኢትዮጵያ ከከፍተኛ አደጋ ያመለጠችበትን ሁኔታ ማስታወሻ ይሆናል፡፡

ከወደዳችሁት አካፍሉ

ኢትዮጵያ በአውሮፓ ዲፕሎማሲ እንዴት ተረፈች የሚለው መፅሐፍ ብታነቡ ይጠቅማል፡፡

https://goshbooks.square.site

ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጋር ያገናኘን ነገር

ነብሳቸውን በገነት ያኑረውና በቅርቡ ያረፉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ የተደበቀው ማስታወሻ የተባለውን በእኔና በአቶ ደሳለኝ አለሙ ለህዝብ የቀረበውን መፅሐፍ እንዳነበቡና፣ መፅሐፉን ብዙ ቦታዎች ላይ ምልክት እንዳደረጉበት አንድ ሰው ሹክ ብሎኝ ነበር፡፡ ቆየት ብለው ግን፣ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ፣ የሚከተለውን አስተያየት ፅፈው አነበብኩ፡፡ መፅሐፉን ያነበበ ሰው፣ ፕሮፌሰሩ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ብዙ ቦታ ምልክት ማድረጋቸው የሚያስገርመው አይመስለኝም፡፡ ያላነበባችሁ ብታነቡት ይመከራል፡፡ በማንበባችሁ እንደምተደሰቱ እርግጠኛ ነኝ፡፡ 

_________________________________

A post from Professor Mesfin's page
Mesfin Wolde-Mariam
December 9, 2015 ·


የወኔ ተስፋ

በኢጣልያ ወረራ ጊዜ በደጃዝማች አያሌው ብሩ የጦር ሰፈር አንድ አማርኛን አቀላጥፎ የሚናገር ስዊድን ሀኪም አብሮ ነበረ፤ ትዝብቱን ጽፎ የተተረጎመውን ሳነብ አንድ ልብን በኩራት የሚያሳብጥ ታሪክ አነበብሁ፤ ስለደጃዝማቹ ጦር ሲናገር በከፊል እንደሚከተለው ነው፤--

‹‹በግምት ከየመቶው ሰው ሰባቱ ጎራዴ ብቻ ወይም በትር የያዙ ናቸው፤ በተለይ የማስታውሰው የአሥራ ስምንት ዓመት ወጣት ልጅ በኩራት መንፈስ ዱላውን በቀኝ ትከሻው ላይ አድርጎ ይንጎራደድ ነበር፤ ዱላው የእንጨት ሲሆን ቀይ ቀለም ያለው ሆኖ እላዩ ላይ ጌጥ ተቀርጾበታል፤ የዚህ ወጣት ልጅ የተለየ ኩራትና አካሄድ የሰዎችን ዓይን የመሳብ ችሎታ ፈጥሯል፤

ደጃዝማች አስጠሩትና
ዕድሜህ ስንት ነው?
አባቴ የሚነግረኝ በንጉሥ ሚካኤልና በሸዋ ገዢዎች መሀከል በተደረገው የሰገሌ ጦርነት ወር ነው የተወለድኩት፤
መልካም በዚህ በሚያምር ዱላህ ምን ልታደርግበት ነው?
በዚህ ዱላ ነጭ ልገልበት ነው፤
እንደሱ እንኳን ማድረግ አትችልም፤ በምትኩ ጠመንጃ ልስጥህ፤
የለም አመሰግናለሁ፤ ለአባቴ የማልኩት ቃለ መሐላ ጣልያን ገድዬ ጠመንጃውን ወስጄ አሳያለሁ፤ አለዚያ በዚህ በጦር ሜዳ እቀራለሁ፤››


የተደበቀው ማስታወሻ ከሚል መጽሐፍ፡፡


እኔ መስሎኝ የነበረውና የማምነው ኢትዮጵያውያን

ምርጫ ካላቸው ቀላሉን እንጂ ከባዱን አይመርጡም

የሚል ነበር፤ ይህ ወጣት የቆየ እምነቴን አነከተው!

አንዳንድ ኢጥዮጵያውያን ከባዱን የመምረጥ ወኔ

አላቸው ማለት ነው፤ አምላክ ዘሩን ያበርክተው!

ልቤን በኩራት አሳበጠው፤ የኢትዮጵያዊነት

ክብሬንም አደሰው! የዚህ ወጣት ወኔ በብዙ

መልኩ የሚታይ ነው፤ የዛሬ ወጣቶች አባባሉን

እንዲመረምሩት እተውላቸዋለሁ፡፡


መስፍን ወልደማርያም       የተደበቀው ማስታወሻ  

መልካም ልደት ጃንሆይ!!


ሰውየውን አውሮፓውያንና ባላንጣዎቻቸው እንደሚስሏቸው ጨካኝ በማለት ብዙ ሰው ያስተጋባል፡፡ ቆራጥ ነበሩ፣ የማያወላውል ርምጃ ይወሰዳሉ ግልፅ ነው፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሔር የነበረው ንጉሥ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ያለ የለም፡፡ ሀይለኛ የሆኑት፣ ለህዝቡ የፈለጉትን ያህል ቢጥሩም ምላሹ ሽፍትነት፣ ዘረፋ ሆነ፡፡ የዛን ጊዜው ሽፍታ ደግሞ፣ ንጉሡ ዞር ሲሉ፣ እሳቸውን አምነው የተቀመጡ ገበሬዎችን ቤት ንብረት እያቃጠለ፣ እየዘረፈና እየገደለ ይሸሻል፡፡ እባካችሁ ተውኝ አትሸፍቱ እያሉ ይለምኑ ነበር፣ ያውም በቴዎድሮስ ኩራት ፡፡ ነገር ግን ሰሚ አላገኙም፡፡ በመጨረሻም እንዲህ አሉ ፈጣሪ የላከኝ ህዝቡን እንደረዳ መስሎኝ ነበር ለካስ ተሳስቻለሁ፣ የላከኝ ለቅጣት ነው ብለው ከልባቸው አመኑ፣ ቅጣቱንም ከፈጣሪ የተላከ አደረጉት፡፡ ለዚህ ምስክር፣ አንደኛው መድፋቸው ላይ፣ “ቴዎድሮስ የርጉማኖች መቅሰፍት” የሚል ፅሁፍ አስቀርፀውበት ነበር፡፡ ህዝቡ ከመቶ ሃምሳ አመታት በኋላም ያው ነው፡፡ ያላየ ሰው በቴዎድሮስ ይፈርዳል፡፡


ለድሆች የተለየ እንክብካቤ በማድረግ፣ ችግራቸውን ማዳመጥና፣ ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊትም ምፅዋት ይሰጡ ነበር፡፡ በሰብአዊ ርህራሄ ስሜትና እንደ አሰተዳደራቸው ፖሊሲ በመቁጠር በዘመቱበት ቦታ ሁሉ ለድሆች ገንዘብ ይሰጡ ነበር፡፡ በዶክተር ክረፕ ሚሲዮናዊ ጥናት ውስጥ የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ቴዎድሮስ፣ “እኔ ራሴ ድሃ ነበርኩ፤ ድሆችን ባልረዳ፣ ለፈጣሪ ስሞታ ያቀርባሉ” ይሉ ነበር፡፡ ለናፒየር በፃፉት በመጨረሻው ደብዳቤ፣ “ራሴ የምጦራቸው ሰዎች” በማለት፣ የሚያስተዳድሯቸው ባልቴቶች፣ ሴቶችና ህፃናት እንደነበሩ ይጠቅሳሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሚሠጡት ፍርድም በሰው መወደድንና መደነቅን አትርፎላቸው ነበር፡፡ ለመጥቀስ፣ ሁለት ሰዎች ተካሰው ንጉሡ ፊት ቀረቡ፣ አንደኛው ላንዱ ፈረስ በትውስት ሠጥቶት ኖሮ፣ ተቀባዩ ግን ይክዳል፡፡ ሠጭው ሰጥቸዋለሁ ብሎ ሲምል፣ ተቀባዩ እግዚአብሔርን በመፍራት መቀበሉን ያምናል፡፡ ይህን የሰሙ ቴዎድሮስ፣ ሰውየው በነበረው ፈሪሀ እግዚአብሔር ምክንያት፣ እዳውን አኔ እከፍልሃለሁ በማለት ለከሳሹ ፈረስና ብር ሠጥተዋል፡፡
መቅደላ የቴዎድሮስ ዕጣ ከተባለው መፅሐፍ የተጠቀሰ


ይህን መፅሐፍ ያነበበ ሰው፣ ቴዎድሮስ ማን እንደነበሩ ማወቅ ይችላል፡፡ ሰለፃፍኩት አይደለም፣ ብዙ የማይታወቁ፣ በተለይም ደግ ሥራዎቻቸው እየተመረጡ ለአንባቢ ያልቀረቡ መሆናቸውን አስተውያለሁ፡፡ ቴዎድሮስን የምትወዱ የምታከበሩ አንብቡት፡፡ ትርጉምና ተጨማሪ ሥራዎች ያሉበት ነው፡፡ አርቆ በማሰባቸው የተጎዱ ሰው፣ ግን ይችን አገር መልሰው የሠጡን ሰው ናቸው፡፡


ሥዕሉ የሚያሳያው፣ ቴዎድሮስ አባይን ተሻግረው ሰዎቻቸውን ሲመለከቱ ነው፡፡ የሥዕሉ ምንጭ መልክተኛው ራሳም ነው፡፡


​ዳውንት የጀግና አገር

 
በቅርቡ የዳውንት አስተዳዳሪ የነበረውን ሰው የጀግንነት ታሪክ ስሰማ፣ ወደ ኋላ ተመልሼ የሌላ ታላቅ የዳውንት ሰው ታሪክ ትዝ አለኝ፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፣ በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ በዕድሜ የገፉ አቶ ኦዴሶ የሚባሉ የዳውንት ገዥ ነበሩ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ፣ አስዎ ወይም አንቱ ብለው በአክብሮት ከሚጠሯቸው አራት ሰዎች አንዱ አቶ ኦዴሶ ነበሩ፡፡ በፍፁም የቴዎድሮስ ታማኝ ነበሩ፡፡ አንድም ሽፍታ በሳቸው በኩል ወደ መቅደላ አልፎ እንዳይሄድ ዘግተው ሲከላከሉ ነበር፡፡ ለመቅደላ ቀለብ ቢሰፍሩም ግብር አልተጣለባቸውም ነበር፡፡

ሆኖም አንድ ሽፍታ ከሰማንያ ተከታዮቹ ጋር በመሆን፣ በቀን ያልቻላቸውን አኝህን ኣዛውንት ጀግና፣ በሌሊት አድፍጦ በመሄድ ቤተሰቦቻቸው በቤት ወስጥ እንዳሉ በአሳት ያቃጥላል፡፡ አቶ ኦዲሶም ሆነ አስር ቤተሰቦቻቸው በዚሁ ይሞታሉ፡፡ ይህን ያየ ልጃቸው አባቱን ሳይቀብር ጦር አሰከትሎ ሽፍቶቹን ያሳድዳል፡፡ ሽፍቶቹ ሰንጋ ጥለው ጥሬ ሥጋ እየበሉ ሲዝናኑ ይደርስባቸዋል፡፡ የሽፍቶቹ አለቃ እጄን አልሰጥም በማለቱ በውጊያው ላይ ሲገደል፣ የተረፉት ሽፍቶች ይማረካሉ፡፡ ዳውንቶቹ፣ የተማረኩትን ሰዎች ይዘው ንጉሡ ይፍረዱ ብለው ወደ አጼ ቴዎድሮስ ይልካሉ፡፡ የአቶ ኦዴሶን ሞት የሰሙት ቴዎድሮስ አንድ ሙሉ ቀን በሀዘን ለብቻቸው ዘግተው ዋሉ ተቀመጡ፡፡

በኋላ ግን ሽፍቶቹን አስጠሩና፣ አንዴት አድርጋችሁ ነው አቶ ኦዴሶን የገደላችሁዋቸው ብለው ጠየቁ፡፡ ሽፍቶቹም አቶ ኦዲሶንና ቤተሰቦቻቻን በቤታቸው እንዳሉ በእሳት እንዳቃጠሏቸው ተናገሩ፡፡ ቴዎድሮስ ፍርድ ሲሠጡ፣ በል ኦዴሶን በገደሉበት መንገድ ሽፍቶችንም ቅጡልኝ አሉ፡፡ አውሮፓውያኑ ይህንን ሲሰሙ፣ ሰውየውን ጨካኝ ናቸው ብለው ለፈፉ፡፡ የእንግሊዙ መልክተኛ ራሳም ደግሞ፣ ቴዎድሮስ አዲስ ጭካኔ መንገድ ተማሩ ብሎ ዘገበ፡፡

አንደተሰማው ከሆነ አቶ ዳዊት ሞላ፣ የአሁኑ የዳውንት ገዥ፣ ዳውንትን አላስነካም ብሎ ሲታገል ከርሞ፣ ድንገት ገበያ ላይ ሳይታሰብ ነው የተገደለው፡፡ ሞት እንደሆን አይቀር፣ አሟሟት ነው ዋናው፡፡ ከ150 አመት በኋላም፣ ዳውንት ጀግና ገዥ አፍርቶ አየን፡፡

የአቶ ኦዴሶ ታሪክ “መቅደላ የቴዎድሮስ ዕጣ” ከተባለው መፅሐፍ ነው የተጠቀሰው፡፡

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

ምዕራብን ያመነ ጉም የዘገነ

 ምዕራብ ስል የአቅጣጫውን አይደለም፡፡ ለአሁኑ ትውልድ እንግዳ ይሆን እንደሆነ እንጅ፣ ምዕራብና ኢትዮጵያ የቆየ ታሪክ አላቸው፡፡ በተለይም የምዕራቡ አለም ወደ ሥልጣኔ ጎራ ገብቶ ቀለብ ፍለጋ መውጣት ከጀመረ በኋላ፡፡ ከዛ በፊትማ አገር የሚባል ቢኖር ሮማ ብቻ ነበር፡፡ ዕውነት በዕድሜ ቢሆን ኖሮ ስንቱ አገር ለኢትዮጵያ እጅ በነሳ፡፡

ከቴዎድሮስ እንጀምር፡፡ ገና ብቅ ከማለታቸው፣ ሥልጣኔና ዕድገት የሚወድ ንጉሥ መጣ ተብሎ እየተቻኮሉ መጡ፡፡ ሰውየውም በሰላም ተቀበሏቸው፡፡ የገንዘብ ጉዳይ ላይ ጠፈፍ ያሉት ቴዎድሮስ ብዙዎችን በወፍራም ደሞዝ ቀጠሩ፡፡ ቆየት እያሉ የመጡት ነጮች በተለይም ከመንግስት በኩል ተልከናል የሚሉት፣ ክብር በጎደለ መልክ ሰውየውን እንደፈለጋቸው ለማዘዝ ሞከሩ፡፡ አሁንስ ቢሆን እንደ ልጅ ካልታዘዛችሁን የሚል ቋንቋ አለበት እኮ፡፡ ጠቡ የመጣው ከዚህ ነው፡፡ ከጀርባው በርግጥ ሌላ ደባ አለ፡፡ ግን የመልክተኞቹ ንቀት ለኢትዮጵያዊ የሚመች አልነበረም፡፡ አሁንም እኮ ንቀት ቢሆን ነው እንጂ፣ ማዕቀብ ምናምን የሚሉት፡፡ ሆኖም ቴዎድሮስ የሚመቹ አልሆኑም፡፡ በኋላ ሰውየውን ያመሰገኑትን ያክል፣ ስም ማጥፋት ጀመሩ፡፡ በዚያን ጊዜ በአውሮፓ ጋዜጦች የኢትዮጵያ መሪዎችን የሚስሉበት ገፅታ የሚደገም አይደለም፡፡ ትናንተና ሸልመው ዛሬ ደግሞ ወቀሳና ዛቻውን ስናይ ምን አዲስ ነገር አለ ያስብላል፡፡ የሚችሉትን የሞከሩት ቴዎድሮስ ያሉት፤ “አራሴ ላይ ተሸክሜያችሁ ብዞር ስሜን ከማጉደፍ አትመለሱም” ነበር፡፡ ያንን የምዕራባውያን የዘለፋ ፅሁፍ ያነበበ፣ ፍርድ ሰጬ ሆኖ፣ ሰውየው ጨካኝ ናቸው ከሚለው ጎራ ገባ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አጋጣሚውንና ጊዜውን ባገኝ፣ ከአንድ ትልቅ ሰው ጋር የምወያየው ነገር አለኝ፡፡


አፄ ቴዎድሮስን ያበገናቸው ስደቡ አልነበረም፡፡ ምዕራባውያኑ ከቴዎድሮስ ዋና ጠላት ከቱርክና ከግብፅ ጋር መወገናቸው ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ ነው፣ እንግሊዞቹ በኢየሩሳሌም ላሉት የኢትዮጵያ ገዳማትና ቤተክርሰቲያኖቸ የበላይ ጠባቂነት አንስተው ለአርመንና ለግብፆች ኣሳልፈው የሠጧቸው፡፡ ቱርኮች ኢየሩሳሌምን ይቆጣጠሩ ነበር፡፡ ግብፅና ቱርክ በዚያን ጊዜ ለኢትዮጵያውያኑ ልዩነት አልነበረውም፡፡ “…አርብ አርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም” ትዝ ይላችኋል፡፡ ባዶ ዘፍን እንዳይመስላችሁ፡፡

ወደፊት እንሂድ፣ ከምዕራባውያን በኩል በጣም የሚያሳዝን ክህደት የተፈፀመባቸው ንጉሥ እንደ አፄ ዮሐንስ ያለ የለም፡፡ ከእንግሊዞች ጋር ሰለነበራቸው ግንኙነትና ወዳጅነት ሁሉም ያውቃል፡፡ ለሥልጣንም የበቁት አንዱ ትልቁ ምክንያት ይህ ወዳጅነት ነበር፡፡ ሆኖም ታሪክ የሚመሰክረው በያዙት ሥልጣን አገሪቱን አለመሸንሸናቸው ነው፡፡ ሰለዚህ ግድ የለም እሱን እንለፈው፡፡ የዛሬን አያድርገውና፣ የሱዳን መሀዲሰት እንቅስቃሴ በአንግሊዞችና በተለጣፊዎች ግብፆች ላይ በካርቱም አመፅ ያስነሳል፡፡ መውጫ መግቢያ ያልነበራቸው እንግሊዞች ማለፊያ መውጫ መንገድ ፈልገው ሰለነበር ከአፄ ዮሐንስ ጋር የሄዊት ውል የሚባል ይፈራረማሉ፡፡ ዋናው ነገር፣ እንግሊዞችና ግብፆች ከሱዳን ሲሸሹ በኢትዮጵያ ምድር አልፈው እንዲሄዱ፤ በምትኩ፣ አፄ ዮሐንስ የሚያገኙት ደግሞ በግብፆች ተወስዶ የነበረው የቦጎስ መሬት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ በተጨማሪም በምፅዋ በኩል መሣሪያ አንዲገባ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር በዚያን ጊዜ ውሉ ላይ አንድ አሜሪካዊ ነበር፡፡


እንግሊዞችና ግብፆቹ በኢትዮጵያ ምድር በኩል አመለጡ፡፡ ዮሐንስም ቦጎስን አስመለሱ መሣሪያ ግን አልሆነም፡፡ የእንግሊዝና የተለጣፊ ቅኝ ገዥዎች የግብፆች ማምለጥ ያንገበገበው መሀዲ ቁጣውን ወደ በቀል አዞረው፡፡ እኔ የሰማሁት፣ መሀዲ አለ የተባለው ነገር አሁንም ይገርመኛል፡፡ “እንዴት የአፍሪካ ጠላቶችን ይረዳል የሚል ነበር፡፡” አፄ ዮሐንስን ማለት ነው፡፡ ከዛ በኋላ የበቀልና የቅጣት ዘመቻ በጎንደር ላይ ተካሄደ፡፡ የድርቡሽ ጦር እየጋለበ ጎንደር ድረስ ዘልቆ በመግባት አብያተ ክርስትያንን አቃጠለ፡፡ የበቀል መሆኑ የሚታወቀው የሠራውን ሠርቶ ተመለሰ፡፡ አስካሁን ድረስ ሰውን ጨካኝ ለማለት ድርቡሽ ነው ይባላል፡፡ የተፈፀመውን ጭካኔ ይገልጣል፡፡ በነገራችን ላይ ወደኋላ ራስ ጉግሣ ወሌ ጠንከር ብለው መተማ ላይ ንግድ አስከሚጀምሩ፣ ያ የድርቡሽ ወረራ ጎንደርን ወደኋላ እንድትቀር ነው ያደረጋት፡፡

ታዲያ ይሀ ሁሉ መስዋዕት የተከፈለላቸው እንግሊዞች ያደረጉት አስቀያሚ ነገር በራሱ ኤቢ ዋይልድ በተባለ እንንሊዛዊ ዜጋ ከፍተኛ የቁጭት ወቀሳ ነው ያስከተለው፡፡ (ኢትዮጵያ በአውሮፓ ዲፕሎማሲ ገፅ 55 -56) በመጠኑ ልጥቀስ እንዲህ ይላል፤ “… በአፄ ዮሐንስ ላይ ያሳየነው የኛ ባህሪ… ምንም የሀቅ ፍንጣቂ የሌለበት፤ በኔ አስተሳሰብ ብዙ በአፍሪካ ውስጥ ሀጢያተኛ ከሆንባቸው ካደረግናቸው ሥራዎች ሁሉ በጣም የከፋው ነው፡፡”

ምን ያህል ቢበድሉ ነው የራሳቸው ዜጋ ያውም ዲፕሎማት እንዲህ የወቀሰው፡፡ አንደኛውን አባባል እንወስድ፤ “ምንም የሀቅ ፍንጣቂ የሌለበት” የሚገርም ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ለአንተ ብሎ የዋሸልህ ነገ ደግሞ ባንተ ላይ እንደማይዋሽ ምን ዋስትናስ አለ፡፡ የአገሬ ሰው በተለይም በደንብ አስተውል፡፡ ወደ ክህደቱ ስንመለስ፣ ግብፆቹ ተዳክመው ምፅዋን ሲለቁ፣ በአፄ ዮሐንስ ጀርባ፣ በእንግሊዞቹ ጋባዥነት ጣልያኖች ምፅዋን ወሰዱ፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውን ማወቅ ጥሩ ነው፡፡ በወቅቱ ጣልያኖቹ የዮሐንስ ቀንደኛ ጠላት ነበሩ፡፡

ኢትዮጵያን ከረዷት ምክንያቶች አንዱ፣ የውጭ ሀይሎች አንዱ ጎራ ኢትዮጵያን ሙጭጭ ብሎ ሰለወደደ አይደለም፡፡ ይልቁንስ በመሀከላቸው በነበረው ባላንጣነት ምክንያት ነው፡፡ ለኛ እሰከበጀ ድረስ ለምን ለዕድሜ ልክ ባላንጣ አይሆኑም፡፡ የህልውና ጉዳይ አይደለም እንዴ፡፡ ምስሉ የሚያሳየው፣ በድርቡሽ ጊዜ ሳይቃጠል የተረፈው የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርሰቲያን ነው፡፡

ሌሎች ኢትዮጵያ የተካደችበት ታሪካዊ ሁኔታዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ መልክቱ፣ አሁን ያገዙ የመሰሉት እነዚህ ሀይሎች ወርውረው ሲጥሉም ለነገ አይሉም፡፡ ለምንድን ነው የሚያግዙት ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው፡፡ መልሱ ቀላል ነው፡፡ ለራሳቸው ሲሉ፡፡ ሰለዚህ ገና ለገና ይረዱናል ብሎ የገዛ አገርን አሳልፎ መሥጠት ድርብ ጥፋት ነው፡፡ የሚከፋው ግን አሳልፎ በሚሠጠው ወገን ላይ ነው፡፡ ከሁለት ያጣ ጎመን ይባል የለም ወይ፡፡ ከድሮ ግጥሞች አንደኛዋ ትዝ አለችኝ፤ “አይንህ ብርሃን አይችል አንተ ገመምተኛ፣ ይቆረቁርሃል ና ተመለስ ተኛ”