Health and History

ለልጆች የሚሠጠው የኮቪድ ክትባትና የልብ መቁሰል
ወላጆች ሊያነቡት የሚገባ 07/05/2021


ኮቪድ-19 ባህሪያችን እሰካልቀየርን ድረስ የሚለቀን አልመሰለም፡፡ ችግሩ በተወሰኑ አገሮች ብቻ በሽታውን ወይም የቫይረሱን ሥርጭት መቆጣጠር በቂ አይደለም፡፡ አለም በአንድ ላይ መንቀሳቀስ የሚኖርበት ነገር ቢኖር እንደዚህ አይነት ወረርሽኝ ላይ ነው፡፡

በአሜሪካ በአጠቃላይ ሥርጭቱ እየቀነሰ የመጣ ቢመስልም፣ አዲስ የተከሰተው ዴልታ የሚባለው ቫይረስ ደግሞ በዛው ልክ መጠኑን እየጨመረ ነው፡፡ አሁን እሰከዚህ ቀን ድረስ አዲስ በምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከሚታወቁት ሰዎች መሀከል፣ 21 በመቶው በዚሁ በዴልታው ቫይረስ አማካኝነት ነው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃም በ98 አገሮች ውስጥ መሠራጨቱ ተገልጧል፡፡ አንግዲህ አንድ አገር ብቻ መጀመሪያ ታየ የተባለው ቫይረስ እንዴት ተስፋፍቶ እንደሄደ ማየት በቂ ነው፡፡ ከሳምንት በፊት 88 አገሮች ነበር አለብን ያሉት፡፡

ሌላው በአሜሪካ ሥርጭት ያየነው ነገር ቢኖር፣ በአዋቂዎች በኩል የቫይረሱ ሥርጭት በንፅፅር የቀነሰ ሲመሰል፣ በልጆች በኩል ግን ከፍ አያለ ነው የሄደው፡፡ ከዚህ ቀደም በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መሀከል በልጆች በኩል የነበረው ድርሻ በአሁኑ ጊዜ በዕጥፍ አድጓል፡፡ በቫይረሱ የሚያዙ የልጆች ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን የሚታመሙትም ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ይታወቃል፡፡ ከዚ በፊት ልጆች በተለይም ትንንሾቹ የሚያዙት ከቤተሰብ ጋር በሚደረጉ ሰው ለሰው ግንኙነተቶች በመጋለጥ ነበር፡፡ እንግዲህ ት/ቤት ሲከፈት ደግሞ ሌላ ቦታ መጋለጫ ሊኖር ነው፡፡ ሆኖም በት/ቤቶች በኩል በቂ ጥንቃቄ ከተደረገ አደጋው ይቀንሳል የሚሉ መረጃዎችም አሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ትልቅ ርዳታ ሊሠጥ የሚችለው፣ እንደ አዋቂዎች ሁሉ ልጆች የኮቪድ ክትባትን ሲወስዱ ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ በቂ ጥናት ከተደረገ በኋላ ዕድሜያቸው ከ16 አመት በታችና ከ12 አመት በላይ ለሆኑ ልጆች የፋይዘር ክትባት እንዲሠጥ የተፈቀደው፡፡

በመገናኛ ዜናዎች ሰምታችሁ ከሆን፣ ክትባት መሠጠት ከመጀመሩ፣ ክትባት የወሰዱ ልጆች የልብ መቁሰል ስሜት አሳዩ ተብሎ በስፋት ይነገር ነበር፡፡ ይህንንም ጉዳይ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ባለሙያ አማካሪዎች በፍጥነት ሁነታዉን በመመርመር ክትባቱ መሠጠት ይቀጥል ወይስ የሚለውን ውሳኔ ያሰተላለፉት፡፡

እኔ የማቀርብላችሁ፣ ይህንን የልብ መቁስል መጀመሪያ ያገኙት ብዛት ያላቸው ሀኪሞች አንድ ላይ በመሆን በህክምና መፅሄት ይፋ በሆነ መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ለባለሙያተኞችም ሆነ ለህዝቡ እንዲቀርብ ያደረጉትን ጥናት ነው፡፡

ወደነሱ ጥናት ከመሄዴ በፊት፣ ክትባቶች ፈቃድ ከተሠጣቸው በኋላ በቂ ክትትል እንደሚደረግ ላስታውሳችሁ ነው፡፡ በተለያዩ ፕሮገራሞች ሰዎች ክትባቶችን ከወሰዱ በኋላ የተሰማቸው ወይም የታየባቸው ዳርቻ ጉዳት ካለ በሪፖርት እንዲሰበሰብ ይደረጋል፡፡ ከዚያ አልፎ ግን ሀኪሞች ደግሞ በአይነ ቁራኛ በጥንቃቄና በጥርጣሪም ሰለሚጠባበቁ በክትባቱ ምክንያት የሚደርስ ጉዳት ካለ ቶሎ እንዲታወቅ ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ነው የዚሀ የልጆች የልብ መቁሰል ስሜትና ምልክት ቶሎ ይፋ እንዲሆን ያደረጉት፡፡ ሰለዚህ እነዚህን የመሳሰሉ የክትትል መንገዶች በመኖራቸው ጉዳቶች ሲታዩ ቶሎ መታወቅ መቻሉ አንድ የሚያረጋጋ ሁኔታ መሆኑን ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ዋናው ነገር ጉዳት ታየ ብቻ ሳይሆን በምን ያህል ሰዎች ላይ ታየ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ትልቁ መደናገርና ስህተት የሚመጣውም፣ መረጃዎች እያሉ፣ ሰዎች በክትባት ምክንያት ጉዳት ደረሰበት የተባለ አንድ ሰው ካወቁ ጠቅላላ የተከተበው ሰው ሁሉ ያ ጉዳት እንደሚደርስበት አድርገው ሰለሚያስቡና ሰለሚናገሩ ክትባት አንወስድም በማለት ለሚያቅማሙ ሰዎች ተጨማሪ ድጋፍ እየሠጡ ነው፡፡

ወደ ልበ መቁሰል ልውሰዳችሁ፣ በአንግሊዝኛ myocarditis ይባላል፡፡ የልብ ጡንቻ መቁሰል ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ልብ ራሱ በጡንቻ የተሠራ የሰውነት ክፍል ነው፡፡ አለዚያማ አንዲት አድርጎ ደም ሲየሰራጭ ይኖራል፡፡ የልብ ጡንቻ መቁሰል ግን በተለያዩ ምክንያቶች ይመጣል፡፡ ከሰባት በላይ የሚሆኑ ቫይረሶች ኢንፍሉዌንዛና ኤች አይ ቪን ጨምሮ፣ ባክቴሪያዎቸ፣ ጥገኛ ተባዮቸ፣ ከዛ ውጭ ደግም ኬሚካሎች ኮኬይንን ጨምሮ፣ መድሐኒቶችና ሌሎች የበሽታ አይነቶች ይህን የልብ መቁሰል በማምጣት ይታወቃሉ፡፡ ሰለዚህ በሽታው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የበሽታውን ግኝት በተመለከት በአሃዝ ሲታይ፣ በየአመቱ በልጆቸ ላይ ከአንድ መቶ ሺ ልጆች መሀከል በ 0.8 ይገኛል፡፡ አንድ እንኳን አይሞላም፡፡ ዕድሜያቸው ከ15-18 አመታት ከሆኑት መከል ከ2015 -2016 በታየው መረጃ ከመቶ ሺ መሀከል በ1.8 ልጆች ላይ ታይቷል፡፡ ምን ያህል አነስተኛ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ የሚገርመው ለምን ለሚለው ጥያቄ መልስ ባይኖርም ይህ በሽታ ከሚገኝባቸው ልጆች መሀል 66 ፐርስንቱ ወንዶች ናቸው፡፡ ዕድሜ በጨመረ ቁጥር የበሽታው ግኝት እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ከተገኘ ደግሞ በአወቂዎች በኩል ሲታይ 76 ከመቶው ወንዶች ላይ ነው፡፡

ለህዘብ ይፋ እንዲቀርብ በተደረገው ጥናት፣ የተለያዩ ሀኪሞች በተለያያ ሙያ ላይ የሚገኙ እንድ ላይ ያቀረቡት ጥናት፣ ጁዲት ጉዝማን-ኮትረል በተባለች ሀኪም መሪነት የተገለጠበት መድረክ ላይ ያየሁትን ነው፡፡ ለማንኛውም ጥናቱ Pediatrics በተባለ የአሜሪካ የህፃናት ሀኪሞች አካዳሚ በኩል በሚዘጋጅ መፅሔት ላይ ታትሟል፡፡ ለምን ፈጥናቹ አቀረባችሁ ሲባሉ፣ ክትባቱ መሠጠት ከመጀመሩ ጉዳቱ ሰለታይ፣ ድንገት ይህ ጉዳት በስፋት የሚታይ ወይም የሚከሰት ከሆነ፣ አደጋ ከመድረሱ በፊት ሰለሁኔታው በቂ ጥናት ተደርጎ መቆም ካለበት እንዲቆም ለማስደረግ ነው፡፡ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ሀኪሞቹ ይህንን ሁነታ ባሰተዋሉበት ወቅት፣ በሌሎች ቦታዎችም ይህ ነገር መከሰቱ ሪፖረት ተደርጓል፡፡ በግለሰቦች ላይ የታየ ቢሆንም ሀኪሞቹ ፈጥነው ይፋ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ለምሳሌ አንደ የ56 አመት ሰው ከዚህ በፊት ኮቪድ ይዞት የነበረ ክትባን ከወሰደ በኋላ ይህ ሁኔታ የታየበት ሲሆን፣ ሌላ ደግሞ የ39 አመት ጎልማሳም ላይ እንዲሁ ታይቷል ተብሎ ሪፖረት ተደርጓል፡፡ ጎልማሳው እንኳን ኮቪድ አልተያዘም ነበር፡፡

ሀኪሞች በህፃናት ህክምናው መፅሄት ያቀረቡት በዚህ የልብ መቁሰል (ማዮካርዳይቲስ) የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ሰባት ነበር፡፡ ሁሉም ጤነኞች የነበሩ ግን የፋይዘር ክትባት ሁለተኛውን ከወሰዱ በአራት ቀናት ውስጥ ነበር ስሜቱ የተሰማቸው፡፡ የፋይዘር የሆነው፣ ለዚህ ዕድሜ ክልል የተፈቀደው ክትባት ሰለሆነ ነው፡፡ ዕድሜያቸው ከ14 -16 አመታት ሲሆን ሁሉም ወንዶች ነበሩ፡፡ ሁሉም በምርመራ ከዚህ ቀደም ለኮቪድ ያልተጋለጡ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የተሰማቸው የህመም ስሜት ደግሞ የደረት ህመም ፣ ትኩሳትና ከግማሽ በታች በሆኑት የድካም ስሜት ነው፡፡ ሶስቱ የትንፋሽ ማጠር ስሜት የተሰማቸው ሲሆን፣ አንድ ብቻ የልብ ትርታ መፍጠን ስሜት ነበረው፡፡ ሁሉም በሆስፒታል ውስጥ ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን ቆይታቸው ከ2 እሰክ 6ቀናት ነበር፡፡ ሁልጊዜም እንደሚደረገው፣ የበሽታ ሰሜት ሲታይ ሌሎች ምክንያቶች መኖርና አለመኖራቸው ምርመራ ይደረጋል፣ በዚህም ከላይ እንደጠቀሰኩት የልብ መቁሰል (ማዮካርዳይቲስ) ሊያመጡ ይችላሉ ለሚባሉ ነገሮች ምርመራ ተደርጎ ከአንደ ልጅ በስተቀር ሌሎቹ ላይ አልታየም፡፡ ይህ የሚሆነው፣ ደግሞ ሌላ ምክንያት ከሌለ ክትባቱ ነው ወደሚለው ሀሳብ ለመጠጋት ነው፡፡ ሁሉም ህክምና ተደርጎላቸው አንደኛው ብቻ የኦክስጅን ርዳታ ሲደረግለት ሌሎቹ አላስፈለጋቸውም፡፡ ሁሉም የተሠጣቸው መድሀኒት፣ ኢንፍላሜሽን ወይም ቁስለት የሚያመጣውን ሂደት የሚያረግቡ መድሐኒቶች ናቸው፡፡ አይቡፐሮፌን (Ibuprofen), steroid, Immuno globulin የሚባሉ መድሐኒቶች ነው የተሠጡት፡፡ የቸግሩ መንስኤ ሰውነት በመቆጣት በሚፈጥረው ኢንፍላሜሽን በሚባል ሂደት የልብ ጡንቻዎች ላይ ቁስለት መፍጠሩ ነው፡፡ ሰለዚህ ዋናው የህክምና መንገድ ደግሞ ቁጣውን ለዘብ ማድረግ ወይም ማቆም ሰለሆን፣ ፀረ ኢንፍላሜሽን የሚባሉ መድሀኒቶችን መጠቀም አይነተኛ መንገድ ነው፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ ቁጠራቸው ሰባት ቢሆንም፣ ልጆቹ የፋየዘር ክትባት ከወሰዱ በኋላ የታመሙ ሲሆን፣ አንደኛቸውም ቢሆን በጠና ያልታመሙ፣ በተደረገላቸው ርዳታ ወዲያውኑ ያገገሙ መሆናቸው ነው፡፡ ወደሆሰፒታል የገቡት፣ የልብ ቁስለት ሰለሆነ፣ የልብን ሁኔታ ያላማቋረጥ በመሳሪያዎች አማካኝነት ሞኒተር ወይም ክትትል ለማድረግ ነው፡፡

ይህ ጥናት እንደቀረበ፣ በጥድፊያ ሁሉም የመንግሥትም አካል ሆነ የባለሙያተኞች አማካሪዎች ጉዳዩን አንዲመለከቱ ሆኖ ማጠቃለያ ምክረ ሀሳብ እንዲሠጡ አድርጓቸዋል፡፡ በርግጥ ልጆች ሰለሆኑ ለተወሰነ ጊዜ የመሸበር ስሜት መታየቱ ይታወቃል፡፡ ፍጥነቱ ደግሞ፣ ክትባቱ በስፋት እየተሠጠ ሰለሆነ ሰፋ ያለ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መደረግ የሚገባውን ርምጃ ለመወስድ ታስቦ ነው፡፡

ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት፣ ክትባቱ ከተሠጠ በኋላ ምን ያህል ሰዎች የዚህ በልብ ጡንቻ መቁሰል በተጨማሪም የልብ ሽፋን መቁሰል (ይኼኛው ፐሪካርዳይቲስ ይባላል) ታይቶባቸዋል በማለት የክትባቶቸን ደህንነት ወይም ጤናማነት ክትትል በሚደረግበት በእንደኛው ፕሮግራም የታየውን ማመሳከር ነበረባቸው፡፡ ይህ የቀረበው ደግሞ ቶም ሺማቡኩሮ በተባለ የሲዲሰ የክትባት ግበረ ሀይል ቡድን አባል በሆነ ሀኪም ነው፡፡

በዚህ መሠረት 300 መቶ ሚሊዮን ሰዎች ከተከተቡ በኋላ፣ የተከሰቱ ዳርቻ ጉዳቶች ክትትል በሚደረግበት ፕሮግረም የታየው (እሰከ ጁን 11፣ 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ)

ማዮካርዳይቲስ ወይም ፐሪካረዳይቲስ (የልብ ጡንቻ ወይም የልብ ሽፋን መቁሰል ምልክት) ተገኝቶባቸዋል የተባለው

የፋይዘር ክትባት በኩል የመጀመሪያውን ክትባት ከወሰዱ በኋላ በ150 ሰዎች፣ ሁለተኛውን ክትባት ከወሰዱ በኋላ በ563 ሰዎች፣ መቼ ክትባት እንደወሰዱ ባልታወቀ በ78 ሰዎች ላይ ተከስቷል

ሌላው ተመሳሳይ ክትባት በሞደርና በኩል የመጀመሪያውን ክትባት ከወሰዱ በኋላ በ117 ሰዎች፣ ሁለተኛውን ከወሰዱ በኋላ በ264 ሰዎች እንዲሁም መቼ እንደወሰዱ ባልታወቀ በ54 ሰዎች ላይ ተከስቷል ተብሎ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ያው ቀደም ብሎ እንደተገለፀው መጀመሪያውን ከወሰዱት መሀከል 66 ፐርስነት ወንዶች ሲሆኑ፣ ሁለተኛውን ወስደው ከተከሰተባቸው መሀከል 79 ፐርሰንቱ ወንዶች ናቸው፡፡ አማካይ ዕድሜ በመጀመሪያው 30 አመት ሲሆን፣ ከሁለተኛው ክትባት በኋላ ደግሞ 24 አመት ነበር፡፡ የተሰማቸው የህመም ስሜት ደግሞ የደርት ህመም በቀዳሚነት የሚገኝ ሲሆን የትንፋሽ ማጠር ስሜት ሌለው ነበር፡፡ ሆስፒታል ውስጥ በምርመራ የታዩ የደምና የልብ ምርመራ በኢልክተሪካል ሆነ በሌላ መንገድ የታዩ ምልክቶች ነበሩ፡፡ የነዚህ ሰዎች ውጤት በተመለከተ፣ የልብ መቁስል ለመሆኑ ሁነታውን ያሟሉ ሰዎች 323 ሲሆን በወቅቱ 295 ከሆስፐታል እንደወጡ 9 ሆሰፒታል ውስጥ እንዳሉ ሪፖረት የተደረገ ሲሆን፣ 14 ደግሞ በድንገተኛ ክፍል ብቻ ታየተው የተመለሱ መሆናቸውን ተገልጧል፡፡

ዋናው ነገር፣ ችግሩ የታየ ሲሆን፣ በምን ያህል ሰዎች፣ እንደገናም ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች አለመኖራቸውን መገንዘብ ጥሩ ነው፡፡ ሁለቱ ክትባቶች ባጠቃላይ ሲታይ ሞደርና የወሰዱ 4.5 ሚሊዮን ሲሆን፣ የፋይዘሩን የወሰዱ ደግሞ 5.7 ሚሊዮን ሰዎች ነበሩ (እስከ ጁን 12 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው)

አነዚህና ሌሎቸ ተጨማሪ ግኝቶችና አሃዞችን በማስላት፣ ይህ የታየው የልብ ጡንቻና የልብ መቁስል በሽታ በክትባቱ ምክንያት ቢሆንም በስፋት ሲሠጥ ለጠቅላላው ህብረተሰብ አደጋ አለው ወይስ የለውም የሚለው ውሰኔ ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ በዚህ በወጣው ስሌት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወሰድውት ሁኔታው የታየባቸው ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ በመሆኑ፣ ሁለተኛ አነስተኛ ሆኖም የተከሰተባቸው ሰዎች በህክምና ርዳታ ቶሎ ማገገማቸው፤ ታይቶ ክትባቱን መወስዱ ጥቅም በጣም ከፍ ያለ በመሆኑ ክትባቱ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ሌላው ማስተዋል ያለብን ነገር ክትባቱን ወስደው የልብ ቁስለት ሊገኝባቸው የሚችልበት አጋጣሚ በጣም አነስተኛ ሲሆን፣ ይልቁንስ ኮቪድ ቢያዙ በክትባቱ ሊያዙ ከሚችሉበት በላይ የልብ መቁስል ሊከሰትባቸው እንደሚችል ይታወቃል፡፡ አንግዲህ ልጆች ኮቪድ ተይዘው ከሚከሰትባቸው ሌሎች ችግሮች ውጭ ነው፡፡ በአሃዝ ሲታይ እነዚህ ሁለት አይነት ክትባቶቸ ከወሰዱ በኋላ ባጠቃላይ የታያው የመጀመሪያውን በወሰዱና የተከሰተባቸው ሰዎች ቁጥር 4.4 ከአንድ ሚሊዮን፣ ሁለተኛውን ከወሰዱ በኋላ 12.6 ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች መሀከል ነው፡፡ ይህ ምን ያህል አነሰተኛ መሆኑን ያሰገነዝበናል፡፡

ክትባቱ አንዲቀጥል ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆን የተለያየ የሀኪሞች ማህበራት በተለይም የህፃናት ሀኪሞች አካዳሚ ክትባቱ መሠጠቱ እንዲቀጥል ይስማማሉ፡፡ ከአቅራቢዎች ሀኪሞች አንደኛው የራሷን ልጅ ያስከተበች መሆኑን ሰትናገር፣ እኔም ልጃችን ሁለቱን ክትባት ከወሰደች የቆየች መሆኑን አስታወስኩ፡፡

ክትባቱ ሲሠጥ፣ ወላጆች ሰለዚህ የልብ መቁሰል ሁኔታ ሊነገራቸው ይገባል፡፡ ማንኛውም መድሐኒት ሲሠጥ ሊከሰት ይቻላል የሚባል ዳርቻ ጉዳት መነገር አለበት፡፡ እንግዳ አይደለም፡፡

ወላጆች ልጆቻችሁን ማሰከተቡ የበለጠ ጥቅም አለው፡፡ ሆኖም ልጆች ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ የደረት ህመም ስሜት ወይም የትንፋሽ ማጠር ስሜት ተሰማን ካሉ ቶሎ ወደ ህክምና ቦታ መውሰድና ለሀኪሞቸም ልጅዎ ክትባት መውሰዱን መናገር ተገቢ ነው፡፡ በአብዘኛው ወንዶች ላይ፣ በአብዛኛው ከሁለተኛው ክትባት በኋለ መታየቱንም ልብ ይበሉ፡፡ እንገዲህ ከአንድ ሚሊዮን ተከታቢዎች መሀል በ14 ሰዎች ላይ ይህ ነገር ተከሰተ ተብሎ፣ ገዳይ ሊሆን የሚችል ራሱም ቢሆን የልብ ቁስለት የሚያሰከትል ቫይረሰን ከመያዝ የሚያስጥል ክትባትን አለመውሰድ አደጋው የጨመረ ነው፡፡ በተለይም አዳዳሲ ቫይረሶች በየጊዜው በሚከሰቱበት ወቅት፡፡ ሌላው ደግሞ ልጆች በአብዛኛው እይተያዙ ከሆነ ወደየቤት ይዘውት እንደሚመጡ ግልፅ ነው፡፡ በተይም በቤት ውስጥ በዕድሜ የታደሉና ሌሎች በኮቪድ ቢያዙ አደጋ ላይ ሊያደርሷቸው የሚችሉ ተደራቢ ህመም ያለባቸው ሰዎች ሊኖሩ ሰለሚችሉ ልጆቹ ተከትበው በሽታው እንዳይሠራጭ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ለሌችም አካፍሉ በተለይም ልጆቻቸውን ለማስከተብ እየተዘጋጁ ላሉና ላስከተቡም ወላጆች፡፡ በነገራችን ላይ ወደ በጋው ማለቂያ ደግሞ ክትባቱ ከ12 አመት ዕድሜ በታች መሠጥት የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ያም በአሁን ወቅት  በዚህ ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች ላይ ጥናቶች እየተካሄዱ ሰለሆነ 

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic