ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

 ስለ አልኮልና እርግዝና አጠቃላይ ምክሮች

 ​በእርግዝና ጊዜ ጤናማ የሚባል የአልኮሆል መጠን የለም

 • ይህም ለእርግዝና በሚዘጋጁበት ያለውን ጊዜም ይጨምራል

 • በእርግዝና ጊዜ አልኮሆል መጠጣት የሚቻልበት ጤናማ ጊዜም የለም

 • ሁለም አይነት አልኮሎች እኩል በሆነ ሁኔታ ጉዳት ያደርሳሉ ይህም ወይንና ቢራን ጨምሮ ነው

 • ነብሰ ጡር ሴት አልኮሆል ስትጠጣ ፅንሱም አብሮ ይጠጣል


 በእርግዝና ጊዜ አልኮሆል መጠጣት ላይ የሚያስከትለው አደጋ

 እንደሚታወቀው፣ ፅንሱ የሚያድገው በእትብቱ በኩል የእናትየዋን ደም በመቀበል ነው፡፡ ሰለዚህ እናትየዋ አልኮሆል በምትጠጣበት ጊዜ በደሟ ውስጥ የሚዘዋወረው አልኮሆል በቀጥታ ወደ ፅንሱ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ አልኮሆል ፅንስ መጨናገፍን፣ ሕይወት የሌለው ልጅ መወለድን በማስከተል የሚታወቅ ሲሆን በተጨማሪ

ሕፃኑ ለአልኮሆል በመጋለጡ ምክንያት፣ ለዕድሜ ልክ የሚዘልቁ በሰውነት አካል፣ በአእምሮና በባህሪ ላይ ችግሮች ያስከትላል፡፡ እነዚህ ችግሮች በእንድ ላይ፣ በእንግሊዝኛ፣ ፊታል አልኮሆል ስፔክተርም ዲሶርደር ተብሎ ይታወቃል (fetal alcohol spectrum disorders (FASDs). ለመግባባት እንዲመች ምህፃረ ቃሉን ማለትም FASDs የሚለውን መጠቀም ይቻላል፡፡

በዝርዝር ሲታይ FASDs ያለባቸው ህፃናት የሚከተሉት ችግሮች ይታዩባቸዋል

 1. ተፈጥሮያዊ ያልሆነ በህፃኑ ፊት ላይ የሚከሰት የተዛባ የሰውነት ክፍል ዕድገት( በላይኛው ከንፈርና በአፍንጫ መሀከል መስመር የሌለው ሰውነት
 2. አናሳ የሆነ ጭንቅላት(የራስ ቅል)
 3. ከአማካይ በታች ቁመት ማጠር
 4. ከመጠን በታች የሆነ የሰውነት ክብደት
 5. የተወሳሰቡ የሰውነት አካላትን ማንቀሳቀስ ድክመት
 6. የአትኩሮት ጉድለት
 7. ደካማ የሆነ የማስታወስ ችሎታ
 8. በትምህርት ላይ ደካማ መሆን በተለይም ሂሳብን በተመለከተ
 9. ቅዥቅዥ ያለ ባህሪ
 10. የመናገር ችሎታና ቋንቋ ማወቅ መዘግየት (ቶሎ ያለመናገር)
 11. የአእምሮ ወይም የደከመ ዕውቀት ችሎታ
 12. የማገናዘብ ችሎታ ማነስ
 13. በህፃንነት ጊዜም የእንቅልፍና የመጥባት ችግር
 14. የዕይታና የማዳመጥ ችግር
 15. በልብ፣ በኩላሊትና በአጥንት ላይ ችግር መፈጠር


 ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች በአብዛኛው በአንድ ላይ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ከላይ እንደተዘረዘረው በየጊዜው የሚታወቁት ለምሳሌ ትምህርት ላይ ደካማ መሆን ቆየት ብለው ነው የሚታወቁት፡፡ ከዚህ በላይ ሌላ ምን አደጋ አለ? ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ያለበት ህፃን መውለድስ ይበጃል ወይ? ይህ ችግር ሁሉም አልኮሆል የጠጡ ነብሰጡሮች ላይ ላይከሰት ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ማን ላይ ሊከሰት እንደሚችል የሚጠቁም ምልክት የለም፡፡ ስለዚህ ሊከሰቱ በሚችሉት በነዚህ ችግሮች ምክንያት፣ አይደለም በእርግዝና ጊዜ፣ ለእርግዝና አየተዘጋጁ ከሆነ እንዳውም ያለመከላከያ ግብረ ሥጋ ግንኙነት የምታደርግ ሴት ከአልኮሆል መቆጠብ አለባት ነው ምክሩ፡፡ ምክንያቱም አብዛኘው እርግዝና ሳይታሰብና ሳይታወቅ ነው የሚጀመረው፤ እናም ሴቶች ነብሰ ጡር መሆናቸውን ሳያውቁ አልኮሆል በመጠጣት ፅንሱን ሊያጋልጥ ስለሚችሉ ነው፡፡ ነብሰ ጡር መሆናቸውን ካወቁ በኋላም ወዲያውኑ ማቆም በጣም ይረዳል፡፡ የሚወለደው ልጅ የጋራ እንደመሆኑ አባቶችም ቢሆን በዚህ ነገር መተባበር ያስፈልጋል፡፡

እንደሞጋቾቹ አሸብር ሚስትን እየጎተቱ መጠጥ መጋበዙ ግብዝነት ነው፡፡ የሞጋቾች ድራማ ፀሀፊዎችም ቢሆን መድረካቸውን ተጠቅመው መልክቱን ቢያስተላልፉ ጥሩ ነው፡፡

ባካችሁ አካፍሉ፡፡ ማንኛውም ሰው ማወቅ የሚገባው ነገር ነው፡፡