Health and History

አዝጋሚ ኮቪድ  Long Covid  05/26/2021

በኮቪድ ምክንያት የመጣውን አጣዳፊ ህመምና ሞት የደረሰውን ጉዳት መለስ ብለ ከማየታችን በፊት፣ ይህ በሽታ ጥሎት ከሚሄደው ጠንቅ ጋር እየተፋጠጥን ነው፡፡ በህክምናው አለም ማለቴ ነው፡፡ በፈለገበት መልክ መገለፅ እየቻለ ያለው ይህ በሽታ ከአጣዳፊው ህመምና ሞተ ውጭ፣ ተይዘው በነበሩ ሰዎች ላይ ለረዥም ጊዜ መዘግየት ወይም ቶሎ ያልጠሩ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች እያሳየ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በአንግሊዝኛ Long Covid እየተባለ ይጠራል፡፡ ቀለል ያለ የሚያግባባው መጠሪያ ይኸኛው ሰለሆነ እንጂ ሌላም መጠሪያ አለው፡፡ በአማርኛ ደግሞ፣ በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ የታየባቸው የበሽታ ስሜት ሳይጠራ ሰለሚዘገይ አዝጋሚ ኮቪድ ለማለት መርጫለሁ፡፡ በርግጥም የሚስማማው ስም ይመስላል፡፡

ዋናው ነገር አዝጋሚ ኮቪድ ነው ለማለት መመዘኛው ላይ ገና ሙሉ በሙሉ ሰምምነት አልተደረሰም፡፡ አስከዛ ድረስ ግን በተገኛው መመዘኛ ይህ አይነት ክስተት መኖሩን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ልብ ማለት የሚኖርብን፣ በኮቪድ ተይዞ የታመመ ሰው በሙሉ አዝጋሚ ኮቪድ ይኖረዋል ማለት አይደለም፡፡ ሰለዚህ መረበሽም አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን ከተያዙ በኋላ የሚዘገይ፣ ያልጠራ ስሜትና ምልክት ካለ ደግሞ፣ የበሽታው ባህሪ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡

እንግዲህ በኮቪድ ምክንያት በጠና ታመው ሆስፒታል ውስጥ ገብተው በተለይም በመተንፈሻ መሣሪያዎች ርዳታ የተደረገላቸው ሰዎች፣ አገግመው ቢወጡም ዘግየት ያሉ የተለያዩ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች ሊኖረቸው እንደሚችል ይታወቃል፡፡ የዚህ አይነት የህክምና ርዳታ የተደረገላቸው ሰዎች በኮቪድ ምክንያትም ሆነ በሌላ ምክንያት የማገገሚያ ጊዘያቸው ሊረዝም እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡

ትኩረት የተሠጠበት፣ በኮቪድ የተያዙ ቀለል ያለ ወይም መጠነኛ ክብደት ያለው የበሽታ ስሜት ኖሯቸው ነገር ግን ሆስፒታል የማስገባት ደረጃ ያልደረሱ ሰዎች ላይ፣ የሚዘገይ ሰሜትና ምልክት አለ ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እንዴታ አለ፤ እየታየም ነው፡፡ ሌላው ጥያቄ ደግሞ ምን ያህል ሰው ነው ይህ አዝጋሚ ኮቪድ የሚታይበት የሚለው ነው፡፡

አንደተለመደው በመረጃ በተደገፈ አሃዝ፣ ቀለል ያለ ኮቪድ ህመም የነበራቸው ግን ወደ አዝጋሚ ኮቪድ የሚቀየርባቸው ሰዎች ቁጥር በፐርሰንት ሲታይ ከ10 % ይጀምራል፡፡ ይህ ቁጥር ግን ከፍ ሊል እንደሚችል እንዲያውም ከፍ ያለ መሆኑን ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚቀርቡ ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡

ወደ በሽታው ከመሄዴ በፊት በአሜሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕክል በኩል የቀረበ ጥናት ላካፍላችሁ፡፡ ዘገባው በአሜሪካ ከ36 ሰቴቶችና ከዲሰትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ (ዋሽንግተን ዲሲ) የመጣ፣ ከጃንዋሪ 2020 እሰከ ማርች 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ የተከሰተ ነው፡፡ ሪፖርቱ የሚገልፀው በኮቪድ -19 ተይዘው ግን ሙሉ በሙሉ ስላልተሻላቸው ወደ ኮቪድ ማገገሚያ ማዕከሎች የተላኩ ሰዎችን ሁኔታ ነው፡፡ ህም፣ የኮቪድ ማገገሚያ ማዕከል የሚባል ነገር ከተፈጠረ ሰንበት ብሏል፡፡ በአጭሩ አዝጋሚ ኮቪድ ያለባቸውን ሰዎች ለማከም ወይም ለመርዳት የተቋቋሙ ማዕከሎች ናቸው፡፡ አብራራለሁ፡፡ ወደ ዘገባው ስንመለስ እነዚህ አዝጋሚ ኮቪድ የታየባቸው ሰዎች ለምን ያህል ጊዜ ወደ ማዕከሎቹ እንደተመላለሱ፣ የተመላለሱበት መጠን፣ ያም ሲሆን ደግሞ የትኛው የበሽታ ምልክት ወይም ሰሜት ነው ወደ ማዕከሉ እንዲመላለሱ ያደረጋቸው የሚለውን ስንመለከት እንደሚከተለው ነው፡፡

በኮቪድ ተይዘው ከነበሩ ነገር ግን ሆሰፒታል ካልገቡ 3171  ሰዎች መሀከል 69 ፐርስንት የሚሆኑት ከተያዙ በኋላ ከአንድ አስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ አንድና ከአንድ ጊዜ በላይ ለህክምና ርዳታ ወደ ህክምና ቦታዎች ዘልቀዋል፡፡ ከነዚህ መሀል እንግዲሀ እነማን ናቸው የህክምና ርዳታ ፍለጋ የቀረቡት የሚለውን ስንመለክት

ከ69 ፐርስነት ወይም 2177 ሰዎች መሀከል፤ በዕድሜ ሲታይ፣ ከ65 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች 88 % ሲሆን፣ ከሶሰት በላይ ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ደግሞ 83 % ነበሩ፡፡ ነገር ግን ምንም ተደራቢ በሽታ የሌላቸው ሰዎች ደግሞ 60% ድረስ የሚሆኑ ነበሩ፡፡ የመጠኑ ቁጥር ይለያይ እንጂ ይህ አዝጋሚ ነገር ሁሉም አይነት ሰዎች ላይ ይከሰታል ማለት ነው፡፡

ጊዜዎችን በሶሰት በመክፈል ከ29 አስከ 59 ቀናት፣ ከ60 አስከ 119 ቀናት እና ከ120 እሰከ 189 ቀናት ውስጥ

ከ29 አስከ 59 ባሉት ቀናት ውስጥ ሰዎች አብዛኛው ምክንያት ያው ኮቪድ-19 ጠቅላለውን የሚመለከት ምክንያት ከፍተኛ ደረጃ ይዞ ሲገኝ፣ የሚከተሉት ስሜቶች ደግሞ ትንፋሽ ማጠር፣ የጎሮሮና የደረት ህመም፣ ሳል፣ የልብ ትርታ መጨመር አና ድካም ናቸው፡፡ አነዚህ በመጀመሪያው ወቅት የታዩ ምልክቶች ጊዜው እየረዘመ ሲሄድ እየቀነሱ ቢሄዱም ቁጥራቸው መጠነኛ በሆኑ ሰዎች ላይ ግን አስከ 180 ቀን ድረስ እንዳልጠሩ ተዘግቧል፡፡ በዚህ ዘገባ መረዳት የሚቻለው ጠቀም ያለ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በኮቪድ ከተያዙ በኋላ የተለያዩ የበሽታ ምልክትና ስሜቶች እየተሰማቸው እሰከ ስድስት ወራት ድረስ ሊዘልቅባቸው እንደሚችል ነው፡፡

አዝጋሚ ኮቪድ ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚታዮ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች ዘርዘር ያለ ነው፡፡ አዝጋሚ ሲባል እንግዲህ በኮቪድ ከተያዙ ከ28 ቀናት በኋላ ሳይጠሩ የሚቀሩ ወይም ደግሞ ብቅ የሚሉ ምልክቶች ሲኖሩ ነው፡፡ እሰከ 28 ቀናት ድረስ የሚከሰተው የህመም ስሜት በአጣደፊው ኮቪድ በሽታ ይጠቃላል፡፡ በብዛት የሚታዩ ምልክትና ስሜቶች የሚከተሉት ናቸው፤

ድካም (በጣም ዋነኛው ምልክት፣ በብዙ ሰዎች ላይ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ)

ሳል፣ የትንፋሽ ዕጥረት፣ የደረት ውጥረት፣ የአእምሮ አትኩሮት ችሎታ መቀነስ በእንግሊዝኛ Brain Fog ይባላል፡፡

የመገጣጠሚያዎች ህመም፣ የራስ ምታት፣ የማሽትት ችሎታ መጥፋት ሲሆኑ፣ የማዳመጥ ችሎታ መቀነስና ሌሎችም ስሜቶች ተዘግበዋል፡፡

አዝጋሚ ኮቪድ የሚታይባቸው ሰዎች ደግሞ በብዛት ዕድሜያቸው ከ50 አመት በላይ በሆኑ ሰዎች፣ የሰውነት ክብደት ከፍ ያለ ወይም ውፍረት፣ አስም ያለባቸው፣ ከዚህ ቀደም የአዕምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ሌላው ደግሞ ከመጀመሪያው በኮቪድ ሲያዙ አምስት ወይም ከአምስት በላይ የበሽታ ስሜት የነበራቸው ሰዎች ወደ አዝጋሚው ኮቪድ የመሻገር ሁኔታ ከፍ ይላል፡፡ አምስት ከሚባሉት (ሳል፣ ድካም፣ ራስ ምታት፣ ተቅማጥ፣ የማሽተት ችሎታ መጥፋት) እንግዲህ እነዚህ ባንድ ላይ ወይም ከዚህ ተጨማሪ የነበራቸው ሰዎች ናቸው ወደ አዝጋሚ ኮቪድ የመሻገር አደጋው የሚጨምርባቸው፡፡

ብዙ ጊዜ፣ ሰዎች የሚያስቡት በሽታ የሚጠናው ወይም የሚከፋው ተደራቢ ህመም ባላቸው ሰዎች ብቻ ነው ብለው ነው፡፡ በርግጥ በነዚህ ሰዎች ቢጠናም፤ ዕድሜያቸው ከ18 – 34 አመት በሆነ ምንም ተደራቢ በሽታ በሌለባቸው ሰዎች ላይ በ20% በሚሆኑት አዝጋሚ ኮቪድ መከሰቱን ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡

ሌላው በአዝጋሚ ኮቪድ ላይ የታየ ነገር ቢኖር፣ ከዚህ በፊት በግልፅ ያልተከሰተ  የተደበቀ በሽታ ያለባቸው ሰዎች፣ ኮቪድ ከያዛቸው በኋላ እንደ አዲስ ሲከሰትባቸው ታይቷል፡፡ ከነዚህ በሽታዎች አንዱ የስኳር በሸታ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የአእምሮ ህመም ለምሳሌ አልዛይመር የተባለው አይነት ነው፡፡

ለምንድነው አዝጋሚ ኮቪድ የሚታየው ለሚለው ጥያቄ መልስ፣ የሚታሰበው አንደኛ ሰውነታችን ለቫይረሱ የሚሠጠው ቅጥ ያጣ ምላሽ፣ ሌላው ደግሞ፣ በቂ የሆነ መከላከያ አንቲቦዲ ሳይፈጠር ሲቀር፣ ከዚያም ደግሞ ቫይረሱ ቶሎ እንደመጥራት ወደኋለ ዘግየት ብሎ መራባት መቀጠል፣ በአጣዳፊው ወቅት የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ክፉኛ መጎዳት፣ ከዛም ደግሞ የሰውነት የመከላከያ ሥርአት የራሱ የሆነውን የሰውነት ክፍል ለይቶ ማወቅ ተስኖት የራሱን ሰውነት ማጥቃት ነው፡፡ ይህ የመጨረሻው ሁኔታ በእንግሊዝኛ autoimmune disease ይባላል፡፡

ከዚህ በላይ የገለፅኩላችሁ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች በሰዎች ላይ ሲታዩ ምን ያህል ጉዳት ወይም ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ ወይም አዝጋሚ ኮቪድ ያለባቸው ሰዎች ምን ያህል ይቸገራሉ ለሚለው ጥያቄ መልስ አንድ ጥናት ላጋራችሁ፡፡ በጣም ግልፅ አድርጎ የሚያስረዳ ሰለሆነ ይረዳል ብያለሁ፡፡

በጥናቱ ያደረጉት ነገር፣ አዝጋሚ ኮቪድ ያለባቸው ሰዎች ወደ ማገገሚያ ቦታ ከተላኩ በኋላ የታየውን ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን ለማነፃፀር እንዲመች፣ በኮቪድ ምክንያት የሚያገግሙ ሰዎችን፣ ካንሰር ተይዘው ለማገገም የተላኩና፣ ከአጠቃላይ ህዝቡ ደግሞ የተወሰነ ቁጥር ናሙና ተወሰዶ በሶስቱ ወገኖች መሀከል የታያውን ውጤት ነው የማጋራችሁ፡፡ ንፅፅር ጥሩ ነው፣ የችግሩን ክበደትም ያሳያል፡፡ የሰውነት ወይም የአእምሮ መታወክን ሲያወዳድሩ የተለያዩ መለኪያዎችን በመጠቀም ነበር፡፡

የመጀመሪያው በአጠቃለይ የእዕምሮና የሰውነት ጤንነትን በሚመለከት የታዘቡት ነገር፣ ኮቪድ ይዟቸው የነበሩ ሰዎች ካንሰር ይዟቸው ከነበሩ ሰዎች በባሰ ደረጃ እንደሚገኙ ነው፡፡ በዝርዝር ሲታይ

ኮቪድ ተይዘው የነበሩ በ33%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 25% ደረጃ አጠቃላይ ጤንነት የማይሰማቸው መሆኑ
ኮቪድ ተይዘው የነበሩ 19%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 15% ደረጃ የአዕምሮ ጤንነት የማይሰማቸው መሆኑ
ኮቪድ ተይዘው የነበሩ 44%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 33% ደረጃ የአካል ጤንነት የማይሰማቸው መሆኑ  ነው የታየው፡፡ እንግዲህ ኮቪድ ተይዘው የነበሩ ሰዎች በአእምሮም ሆነ በአካል ጤንነት ካንሰር ተይዘው ከነበሩ ሰዎች በባሰ ደረጃ እንደሚሰቃዩ ነው፡፡

ሌሎች መመዘኛዎች ላይ ሲታይ

ኮቪድ ተይዘው የነበሩ በ32%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 24% ደረጃ የስውነት እንቅሰቃሴ አቅማቸው የደከመ
ኮቪድ ተይዘው የነበሩ 40%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 25% ደረጃ የህመም ስሜት ያለባቸው መሆኑ ተዘግቧል፡፡

እንግዲህ እንዲህ አይነት ችግር ሲከሰት ደግሞ በሰዎች በዕለት ከእለት ኑሮና ሥራ ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል ጥያቄም ይነሳል፡፡ ይህን ለማየት የሚከተሉትን መመዘኛዎች ሲጠቀሙ የታየው ነገር፡

ኮቪድ ተይዘው የነበሩ 38%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 25% የጀመሩትን የቤት ውስጥ ሥራ መጨረስ እንደሚያቅታቸው
ኮቪድ ተይዘው የነበሩ 40%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 18% የሚሆኑት ደረጃዎችን መውጣትና መውረድ እንደሚሳናቸው
ኮቪድ ተይዘው የነበሩ 38%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 17% የሚሆኑት የአስራ አምስት ደቂቃ ርምጃ መሄድ እንደሚሳናቸው

ኮቪድ ተይዘው የነበሩ በ34%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 16% ደረጃ ሱቅ ወይመ ገበያ ወይም ሌሎች ከቤት ውጭ የሚደረጉ ግዥና እንቅስቃሴ ማድረግ አንደሚሳናቸው ተዘግቧል፡፡

ከአዕምሮና ከአካል ጤንነት ጉድለት በተጨማሪ ከሌሎች ሰዎች ጋራ በሚደረግ ግንኙነት ምን ያህል ችግር አለ ተብሎ ሲታይ
ኮቪድ ተይዘው የነበሩ በ37%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 20% ደረጃ የተለመደ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚሳናቸው
ኮቪድ ተይዘው የነበሩ በ33%፣ ከካንሰር የሚያገግሙ ሰዎች 19% ደረጃ ከጓደኞች ጋራ የተለመደ ግንኙነት ወይም እንቅሰቃሴ ማድረግ እንደሚሳናቸው ተዘግቧል፡፡

የዚህ በሽታ መክፋትና አደገኛነቱን የሚጠቁም ሌላ መመዘኛ ቢኖር ሰዎች በስድስት ደቂቃዎች ውስት ምን ያህል ሜትሮች መራመድ ይችላሉ የሚለው ነው፡፡ በዚህ መመዘኛ፣ በስድስት ደቂቃዎች ውስት ከሶስት መቶ ሜትሮች በላይ መራመድ የማይችሉ ሰዎች ለብዙ ችግሮች የሚጋለጡና የጤና አደጋ ላይ እንደሚወድቁ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ በዚህ መመዘኛ ሲታይ ደግሞ

ኮቪድ ተይዘው የነበሩ በስድስት ደቂቃዎች ውስጥ መራመድ የሚችሉት አማካኝ ርቀት 303 ሜትሮች ብቻ ነበር፡፡ የታየው ዘርፍ ከ277 አስከ 329 ድረስ ነበር፡፡ ካንሰር ተይዘው የነበሩ ሰዎች ግን በአማካኝ 377 ሜትሮች መራመድ የሚችሉ ማለትም ከ360 እሰከ 395 ሜትሮች ዘርፍ፡፡ ይህ የሚያሳየው ኮቪድ ተይዘው የነበሩ ሰዎች ለአመል ያህል በሶስት ሜትሮች ጨመሩ እንጂ ከፍተኛ የጤና አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ ሰዎች ውስጥ ናቸው፡፡

የዚህ ትምህርት መልክት

እንደኛ፣ ኮቪድ ተራ ጉንፋን አይደለም፣ ጥሎት የሚሄደው ጠንቅና ጣጣ አለው፡፡ በርግጥ ምን ያህሉ ሰው ወደዚህ እዝጋሚ ህመም ይገባል የሚለው ቁጥር የተለያየ ቢሆንም አደጋው ከፍተኛ ነው፡፡

ሁለተኛ፣ ኮቪድ ይዟቸው ያገገሙ ቤተሰብ አባላት ወይመ ዘመድ ጓደኞችን ሊኖርባቸው የሚችለውን ቸግር መረዳት፣ በተለይም በአእምሮ በኩል የሚመጣውን በማስተዋል፣ ድጋፍ መስጠት ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡

ምንም እንኳን አብዛኛው በተለይም በዕድሜ ገፋ ያላለው ጠንከር ያለ ስሜት እይሰማውም ቢባል የትኛው ሰው ወደዚህ ዘላቂ ወይም አዝጋሚ እንደሚሻገር ሰለማይታወቅ፣ በአጠቃላይ በኮቪድ አለመያዝን ትልቅ ግብ በማድረግ መከላከያ መንገዶችን መተግበር የግድ ነው፡፡

ከላይ የዘረዘርኩላችሁ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች ከተለያያ የሰውነት ክፍል ሰለሚነሱ፣ እነዚህን ህሙማን ለማከም በየቦታው post covid clinics የሚባሉ የጤና ማዕከሎች ተቋቁመዋል፡፡ ታዲያ እነዚህን ህሙማን ለመርዳት አንድ ሀኪም ሳይሆን በተለያዩ ሙያዎች ስፔሽያሊስት የሆኑ ባለሙያተኞች በጋራ የሚሠሩበት ቦታ ነው፡፡ ከሳንባ ሀኪም፣ የቁርጥማት ሀኪም፣ የልብ ሀኪም፣ የተላላፊ በሽታዎች ሀኪም፣ የቆዳ ሀኪም፣ የአእምሮ ሀኪምና ሌሎችንም ይጨምራል፡፡ ለምን ኮቪድ የማየዳስሰው የማይነካው የሰውነት ክፍል የለም፡፡ አስካሁን በሚደረገው ርዳታ ሁለት ነገሮች በበሽተኞች ላይ ለውጥ ሲያመጡ ታይተዋል፡፡ በኤክስፐርቶች መሀል በተደረገ ውይይት፣ በአብዛኛው የሚታየው ሰሜት ድካም መሆኑ ሲታወቅ፣ ለዚህ ደግሞ መፍትሄና ርዳታ የሠጠ ነገር ቢኖር፣ በቂ ዕንቅልፍ መተኛት ነው፡፡ አስፈላጊም ከሆነ ለአጭር ጊዜ የዕንቅልፍ መድሀኒት ርዳታ ማግኝት ተገቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የበቂ እንቅልፍ ማነስ በሰውነት፣ በአእምሮና በሽታ በመከላከል አቅም ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ይታወቃል፡፡

ሌላው እንደዚሁ ርዳታ የሠጠ ነገር ቢኖር፣ በዚህ በአዝጋሚ ኮቪድ የሚንገላቱ ሰዎች፣ የኮቪድ ክትባት ሲወስዱ የነበራቸው የበሽታ ስሜትና ምልክት የተወገደላቸው መሆኑን ለየዶክተሮቻቸው እየደወሉ የገለፁበት ሁኔታ አለ፡፡ ምክንያቱ ግልፅ ባይሆንም፣ የኮቪድ ክትባት ሌላ ጥቅም በዚህ መልክ መታየቱ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ መላ ምት አለ ግን ያዝ ላድርገው፡፡ሰለዚህ ገና ለገና ክትባት ብወሰድ ችግር ሊያጋጥመኝ ይችል ይሆናል ተብሎ፣ ይህን ለመሰለ አስከፊ በሸታ መጋለጥ ወይም መጋለጥ የሚችሉበት ሁኔታን መምረጥ በጣም ሊመከርበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ከበሽታው የሚመጣው አደጋ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚሀ በተጨማሪ የቫይረሱ አመላላሽ ሆነው በስዎ ምክንያት ሌላ ሰው ቢያዝና አደጋ ቢደርስበት ወይም ቢደርስባቸው ደግሞ የከፋ የህሊና ችግርም ይፈጥራል፡፡ ሰለዚህ እናስተውል፡፡ ለዛሬ ሰፋ ብሏል፣ አካፍሉ፡፡ 

_________________________________________________________________________________________________________


የኮቪድ-19 ክትባትን እንዲወስዱ ማስገደድ (mandatory) ይቻላል ወይ? 
06/01/2021

ይህ ጥያቄ በኮቪድ ክትባት ብቻ ሳይሆን በሌሎች፣ ከዚህ ቀድም ሲሰጡ በነበሩ ክትባቶች ላይም የተነሳ ነው፡፡

ለማንኛውም የኮቪድ ክትባቶችን በሚመለከት፣ በዚህ በአሜሪካ ለአገልግሎት እንዲውሉ ፈቃድ የተሠጣቸው ሶስት ክትባቶች ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም ቀደም ብሎ የመጣው የፋየዘር፣ ቀጥሎ የተፈቀደው የሞደርና አና ወደኋላ የተፈቀደው የጃንሰን ክትባት ናቸው፡፡ ፈቃድ የሚሠጠው የመንግሥት አካል አንደሚታወቀው በእንግሊዝኛ በአጭሩ FDA (Food and Drug Administration) ይባላል፡፡ ይሀ የመንግሥት አካል ፈቃድ ከመስጠቱ በፊት፣ ፈቃድ የተጠየቀለት ክትባት ሆነ መድሀኒት በሌሎች መንግሥታዊ ባልሆኑ የአማካሪዎች ቡድን ይገመገማል፡፡ FDA ለሶስቱ ክትባቶች ፈቃድ ሲሰጥ መደበኛ የአግልግሎት ፈቃድ ሳይሆን፣ ጊዜያዊ የአስቸኳይ EUA (Emergency Use Authorization) ፈቃድ ነው የሠጠው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች ክትባቱን እንዲወስዱ አሰገዳጅ mandatory እንዲሆን አይጠየቅም፡፡ FDA ሆነ የአሜሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል(CDC) የኮቪድ ክትባቶች በአስገዳጅነት እንዲጠየቁ መመሪያ አልሠጡም፡፡

ሆኖም፣ CDC፣ ክትባቶች በአስገዳጅነት አንዲጠየቁ መመሪያ ባይሠጥም፣ ይህንን በሚመለከት ጉደዩን ለየስቴቶች ሀላፊነቱን ሠጥቷል፡፡ ቅርብ ጊዜ ለየት ያለ አነጋጋር የሆነው CDC መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸውን የኮቪድ ክትባት መውሰዳቸውና አለመውሰዳቸውን መጠየቅ ይችላሉ ይላል፡፡ ይህም የሆነው ሠራተኞች ባገኙት ቦታ ክትባት አንደወሰዱ ሰለሚታወቅ፣ ክትባት መውሰዳቸውን የሚገልፅ መረጃ እንዲያቀርቡ መሥሪያ ቤቶች መጠየቅ ይቻላሉ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን ሰለ ክትባቱ ብቻ እንጂ፣ ከዚያ ውጭ ሰለ ሠራተኛው የጤና ሁኔታ የመጠየቅ መብት የላቸውም፡፡ ለምሳሌ፣ ተደራቢ በሽታ ቢኖብዎት፣ ያንን ለመሥሪያ ቤትዎ የማካፈል ግዴታ የለብዎትም፡፡

ወደፊት እነዚህ ክትባቶች የጊዜያዊ ፈቃዳቸውን አገባደው መደበኛ የአግልግሎት ፈቃድ ካገኙ፣ አስገዳጅነቱ እየተጠናከረ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህም ሆኖ በተለያዩ ቦታዎች ክሶች ሊነሱ እንደሚችሉም ይጠበቃል፡፡

አስገዳጅነት ሲነሳ፣ ሰዎች ክትባት አልወሰድም በማለት እንዳይከተቡ የሚያደርጓቸው ሁለት አብይ ተቀባይ የሆኑ ምክንያቶች አሉ፡፡

አንደኛው፡፡ የጤንነት ምክንያት ተብሎ የሚታወቀው፣ ለክትባቱ አለርጂ ያለባቸው ወይም በጤና ምክንያት ክትባቱን መውሰድ የማይችሉበት ሁኔታ ሲኖራቸው ነው፡፡

ሁለተኛው፤ የሀይማኖታዊ ምከንያት ይባላል፡፡ ይህም ሰውየው ወይም ሴትዮዋ በሚከተሉት እምነት ምክንያት ከትባት መውሰድ የማይችሉ መሆናቸው ከታወቀ ነው፡፡ ይሀ ትንሽ አሰቸጋሪ ቢሆንም ተቀባይነት አለው፡፡

መሥሪያ ቤቶች እነዚህን ምክንያቶች ተቀብለው በፋይል ማስቀመጥ ይገባቸዋል፡፡ ችግር ያለው በህክምና ማዕከሎች ውሥጥ ነው፡፡ አንድ ሠራተኛ ክትባት አልወሰድም ካለ፣ መደረግ የሚገባው ነገር፣ ክትባቱን ባለመውሰዱ ምክንያት ክትባቱ መከላከያ ይሆነዋል ለተባለው በሽታ እንዳይጋለጥ የሥራ ምደባ ቦታ መቀየርና ሌሎችም አሠራሮች ሊደረጉ ይችላል፡፡

ወደ ኮቪድ ስንመለስ፣ CDC መሥሪያ ቤቶች የኮቪድ ክትባት መረጃ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ክትባቱን ለሠራተኞቻቸው እንዲሠጡ ይመክራሉ፡፡ አዚህ ላይ የሚጨምሩት ነገር አሠራሩ እንደየስቴቱ ህግ አንዲሆን፤ ሠራተኞች ክትባቱን እንዲወሰድ ማባበያ ወይም ማሰገደጃ የሚሆኑ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ሠራተኛች ክትባቱን ያለመውስድ መብት አላቸው (አሁን) ወደፊት አይታወቅም፡፡ አንድ ሠራተኛ ክትባት አልወሰድም ቢል፣ አብረው ከሚሠሩ የሥራ ጓዶች ጋር የሚፈጠረው የሥራ ግንኙነትን እንዴት ማድረግ እንደሚቻል ግልፅ አይደለም፡፡ ሌላው ሠራተኛ አብሮት የሚሠራውን ሰው የመከተብ ወይም ያለመከተብ መረጃ የማወቅ መብት የለውም፡፡ ቀጣሪው ግን አሁን መብት አለው፡፡ ግን ቀጣሪው ደግሞ የእንዱን ሠራተኛ ክትባት መረጃ ለሌሎች ሠራተኞች የመግለፅ መብት የለውም፡፡ ችግር ነው፡፡ የመብት ጉዳይና ፐራይቬሲ ማለትም የአንድን ግለሰብ የግል የጤንነት ደረጃ መጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

አስገዳጅነት ቢመጣ፣ ባንድ በኩል የመብት ክስ ሊነሳ ሲችል፣ በሌላ በኩል ግን እንዲህ አይነትን ወረርሽኝ ለመከላከል አይነተኛው መንገድ ክትባት ከሆነ፣ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወስደውት ክትባቱ በንፅፅር መወሰድ የሚችል ከፍተኛ ጉዳት ያልታየበት ወይም በንፅፅር ጤናማ ነው ከተባለ፣ የተወሰኑ ጥቂት ሠራተኞች ብቻ አልወሰድም በማለት አደጋ የሚፈጥሩ ከሆነ፣ እንደገናም ደግሞ አብሯቸው የሚሠራው ሠራተኛና ተገልጋይ ጤንነት አደጋ ላይ የሚወድቅ ከሆነ፣ ክትባቱን አልወስድም ለሚሉ ሰዎች ከንፈር የሚመጥ አይኖርም፡፡ በተለይም ክትባቱን ላለመውሰድ የጤና ወይም የሀይማኖት ወይም የዕምነት ምክንያት ከሌላቸው፡፡ ፈተና ነው፡፡

በልምድ ከታየው፣ አንዳንድ የሥራ ቦታዎች፣ ሠራተኞች የኢንፍሉዌንዛ ክትባት አንወስድም ካሉ፣ የኢንፍሉዌንዛ ወራት አስከሚያልፍ ድረስ ሠራተኛው ማሰክ እንዲያደርግ ሲያስገድዱ ይታያል፡፡ ይህ እንግዲህ የኢንፍሉዌንዛ ክትባት ላለመውሰድ በቂ ምክንያት ላላቸውም ሰዎች ነወ፡፡ ታዲያ በወረርሽኙ ምክንያት ሊነሳ በሚችለው አደጋ፣ አልከተብም ያለውን ሠራተኛ ከሥራ የማግለል ህጋዊ ሁኔታ ባይኖርም፤ ከሥራው ጋር በተያያዘ ግን፣ ማስክ እንዲያደርጉ የማስገደድ ወይም ከስብስቦች ወጣ ባለ ቦታ እንዲሠሩ የማድረግ መብት አለ፡፡ ዋናው ምክንያት ይህ የሚደረገው የሠራተኛውን ጤንነት ለመጠበቅ በሚል ነው፡፡ እንዲዚህ አይነት አሰራሮች ከዚህ ቀደም በወጡ በሌሎች ክትባቶች ላይ ተግባራዊ ናቸው፡፡ ባጠቃላይ ይሀ አሰራር የበሽታ መከላከያ ኮሜቴ Infection Prevention Committee (IPC) በሚባሉ በየመሥሪያ ቤቶች በሚገኙ የጤና ባለሙያተኞች በሚመሩ ኮሚቴዎች አማካኝነት ነው ተግባራዊ የሚሆኑነት፡፡

የግሌ አስተያየት፣ ሙያዩም ከዚህ ከበሽታ መከላከያ ጋርም የተያያዘ ሰለሆን፣ መደበኛ ፈቃድ ከተሠጠ በኋላ የኮቪድ-19 ክትባቶች አስገዳጅ መሆን የሚቀር አይመስልም፡፡ በወረርሽኝ ምክንያት፣ በህመም፣ በሞት፣ በአዝጋሚ ኮቪድ መሰቃየት በተጨማሪ፣ በህብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታና በኢኮኖሚው ላይ የደረሰው ጉዳት ላስተዋለ ሰው በሁሉም ዘርፍ በሽታው እንዲስፋፋ የሚፈልግ ባለመኖሩ፣ ክትባቶቹ አስገዳጅ ይሁኑ የሚባለው አቀራርብ በህዝቡም በኩል ድጋፍ ይኖዋል፡፡

ሰለዚህ በዚህ ምክንያት ብቻ ሳይሆን የክትባቶቹን ጥቅም በመረዳት ለግል ጤንነት፣ ለቤተሰብ ጤንነት፣ ለማህበረሰቡ ባጠቃላይ ለኢኮኖሚውም ሲባል፣ ይህ ባይረስ ሥርጭቱን እንዳይቀጥል ማድረግ ሰብአዊነት ነው፡፡ የተከታቢዎች ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር በቂ ተቀባይ ምክንያት ሳይኖር የነሱ ህይወት ከዚያ ሁሉ ሰው ህይወት በላይ እንደሆነ አድርጎ ክትባቱን አለመውሰድ ብቻ ሳይሆን ሰለክትባቶቹ የማይመስል ወሬ የሚያናፍሱ ሰዎች፣ የኋላ የኋላ እንኳን ህብረተሰቡ ቤተሰብ በምን አይን ሊያያቸው እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

አካፍሉ

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic