ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

እርግዝናና ኮቪድ-19
የኮቪድ ክትባትና እርግዝና

04/11/2021

ይህ ርዕስ በተለይም እርግዝናና የኮቪድ-19 ክትባትን አስመልክቶ በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚቀርብበት መሆኑ አያስደንቅም፡፡ ወደ ክትባቱ ከመሻገራችን በፊት፣ ኮቪድ-19 እርግዝና ላይ ሰላሳየው ውጤት እንመልከት፡፡ ይህ ወረርሽኝ አንደ ጀመረ፣ ህፃናትና አርግዝና ላይ ብዙ የከፋ በሽታ አላሳየም የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ ያ ግን ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በሽታዎች በአብዛኛው ኢንፍሉዌንዛን ጨምሮ እርግዝና ላይ እንደሚበረቱ ስለሚታወቅ ነው፡፡ ሲውል ሲያድርና መረጃዎች በየቦታው ሲቀርቡ ግን፣ ኮቪድም አንደሌሎች በሽታዎች ሁሉ ነብሰ ጡር በሆኑ ሴቶችም ሆነ በፅንሱ የሚያስከትለው አስከፊ ውጤት እየታወቀ መጣ፡፡ ሰለ በሽታ ውጤቶቸ ስንነጋገር፣ ከታመሙት ምን ያህሉ የከፋ ደረጃ ደረሰባቸው፣ ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር አደጋው ይጨምራል ወይ የሚሉ ጥያቄዎችን መልስ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ሰለዚህ በቫይረሱ የተያዘው ሁሉ መታመም አለበት፣ የታመመው ሁሉ ደግሞ የከፋ ደረጃ መድረስ አለበት በማለት፣ የከፋ ደረጃ ያልደረሱ ሰዎችን በማየት ወደ መዘናጋቱ የሚሄዱ ግለሰቦች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ያ ግን አደገኛ አስተሳሰብ እንደሆነ ሁሉም ሊነገዘበው ይገባል፡፡ በመጀመሪያ ሰዎች ሁላቸንም ለበሽታዎች ተመሳሳይ ምላሽ የለንም፡፡ ነገር ግን ማን ላይ እንደሚበረታ፣ ማንን ወደ ሕይወት ማለፈ ደረጃ እንደሚያደርስ በርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር ሰሌለ ወደ ጥንቃቄው ማዘንበል አስፈላጊ ነው፡፡

በእርግዝና ጊዜ የኮቪድ-19ን መበርታት በሚመለከት ከተለያዩ ጥናቶች የወጣውን ስብስብ መረጃ ላካፍላችሁ፡፡ ይህ ደግሞ ከላይ እንደጠቀስኩት፣ በተመሳሳይ ዕድሜ ክልል ሆነው፣ ግን ነብስ ጡር የነበሩ ሴቶችን ነብሰ ጡር ካልሆኑ ሴቶች ጋር በማወዳደር የተዘገበ ነው፡፡ በጣም ወሳኝ፡፡

ጥናቶቹ የተመለከቱት አንደኛ በኮቪድ ምክንያት መሞት፣ ሁለተኛ በኮቪድ ምክንያት በጠና በመታመማቸው ወደ ICU የገቡ ሴቶችን፣ ሶሰተኛ በሽታው በርትቶባቸው በመተንፈሻ መሳሪያ ርዳታ የተደረገላቸውና ሌላም በጠና በመታመማቸው ምክንያት የተባለ የህክምና ርዳታ የተደረገላቸው ነበር፡፡ በሁሉም ከላይ በተጠቀሱት የከፋ ውጤቶች፣ ጥናቶቹ የሚያሳዩት፣ አደጋው በነብሰ ጡሮች ላይ የበረጋ መሆኑን ነው፡፡

ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ደግሞ በነብሰ ጡር ሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በፅንሱ ላይ የሚደርሰውን አደጋም ጥናቶቹ ተመልክተዋል፡፡ በዚህ በኩል የተመለከቱት ነገር፡

እንደኛ፡ ሕይወት የሌለው ፅንስ መወለድ፣ ሁለተኛ እንደተወለደ መሞት፣ ሶሰተኛ አዲስ የተወለደው ህፃን ሆስፒታል እንዲቆይ መደረግና፣ ሙሉ ቀን ሳይሞላው አስቀድሞ መወለድን ጨምሮ ነበር፡፡ ይህ ሲጠና ንፅፅር የተደረገው ነብሱ ጡር ሆነው ኮቪድ በያዛቸውና ባልያዛቸው መሀከል ነው፡፡ ባጠቃላይ የአርባ አምስት ጥናቶች ስብስብ ውጤት ነው፡፡ በዚህም በኩል ቢሆን፣ በፅንሱ ወይም በተለወደው ልጅ ላይ የከፋ ወይም የበለጠ አደጋ የታየው፣ በእርግዝና ወቅት ኮቪድ -19 በያዛቸው እናቶች በኩል ነው፡፡

ባጠቃላይ፣ አርግዝናና ኮቪድ መገናኘት የሌለባቸው ሁኔታዎች መሆኑን የሚያረጋግጡ ውጤቶች ናቸው፡፡ የከፋ ውጤት ታይቷል ሊደርስም ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ አሁን በቅርቡ የመጡት አዳዲስ ዝርያዎች ሊያደርሱ የሚችሉትን የከፋ ውጤት ሳይጨምር ነው፡፡

ሌላው፣ ከዚህ ቀድም በጎሽ ድረ ገፅ እንደተዘገበው በኮቪድ ከተያዙ ነብሰ ጡሮች ወደ ፅንሱ ወይም ወደ ህፃኑ ኮቪድ የመተላለፍን ሁኔታ በተመለከተ ያለውን መረጃ ላካፍል፡፡ ህፃኑ እንደተወለደ በሚደረግ ጥንቃቄ፣ ከዚህ ቀደም የታዩ ጥናቶች ያሳዩት ቫይረሱን ከመተላለፍ የቀነሱ ርምጃዎች እንዳሉ ነው፡፡እንደተወለዱ ከእናቶቻቸው ጋር ንክኪ ወይም ግንኙነት ባልነበረባቸው ህፃናት ኮቪድ የተገኘባቸው ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ፅንሱ ላይ ጉዳት የሚያመጣውን ያህል፣ ከተወለዱ አንድ ወር ያልሞላቸው ህፃናት ላይ በኮቨድ የመያዝ አደጋው አነስተኛ ነው፡፡ በተያዙትም ቢሆን አብዛኞቹ የበሽታ ምልክት የሌለባቸው ወይም መጠነኛ የበሽታ ስሜት የታየባቸው ናቸው፡፡ ያም ሆኖ፣ ጥንቃቄው መተግበር አለበት፡፡

ነብሰ ጡር የሆኑ ሴቶችና የኮቪድ-19 ክትባትን በተመለከተ ጉዳዩ በቅርበት የሚመለከታቸው የህክምና ባለሙያተኞች ድርጅቶች የሚናገሩት በአንድ ድምፅ ነው፡፡ እነሱም የሚሉት፡

አንደኛ፡ ነብሰ ጡር ሴቶች ክትባቱን መውሰድ ከፈለጉ እንዲወስዱ ነው፡፡ ይህም ሲሆን ከሀኪሞቻቸው ጋር በቂ ምክክር እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡ ምክክሩም ቢሆን ነብሰ ጡሯ ሰለ ክትባቱ ከጠየቀች ነው፡፡ ሁሉም ሊያወቀው የሚገባው፣ አሰቀድሞ ክትባቱን ውሰዱ ያልተባለበት ምክንያት፣ በመጀመሪያዎች የክትባት ጥናቶች ላይ ነብሰ ጡሮች ስላልተሳተፉ ነው፡፡ ያ ባለመደረጉ ክትባቶች አርግዝና ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት ችግር አስቀድሞ ባይታወቅም፣ አሁን ግን፣ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሴቶች ነብሰ ጡር ሆነው ክትባቱን በመወስዳቸው ከተደረጉት ክትትሎች ክትባቱን ሰለወሰዱ የታየ ችግር መኖሩን ወይም አለመኖሩን የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ፡፡

የእርግዝናና መድሀኒቶች ወይም ክትባት ላይ አስቀድሞ ጥናት የሚደረገው በእንስሳት ላይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት፣ ፋይዘር፣ ሞደርና አና ጃንሰን (ያንሰን) ባደረጉት ጥናት በእንስሳቱ ላይ የታየ አሳሳቢ ችግር የለም ነው የሚሉት፡፡

ከዛ ውጭ፣ ድንገት ነብሰ ጡር እያሉ ክትባቱ የወሰዱ ሴቶች ላይ በተደረገ ክትትል፣ ሶስቱንም ክትባቶች በወሰዱ ሴቶች ላይ የታየ አሳሳቢ ቸግር የለም የሚል ነው፡፡

ሁለቱን ክትባቶች በሚመለከት፣ እንደ ሲዲሲ ዘገባ፣ 77፣950 የሚሆኑ ነብሰ ጡር ሴቶች ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ ክትትል ለማድረግ መረጃ መሰብሰቢያ ለሆነው V-Safe በተባለው ፕሮግራም አማካኝነት ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ከነዚህ መሀል 16 039 የፋይዘሩን ክትባት የወሰዱ ሲሆን፣ 14 455 የሚሆኑት የሞደርናውን ክትባት የወሰዱ ነበሩ፡፡ መረጃው የሚያሳየው፣ ነብስ ጡር ሆነው ክትባቱን የወሰዱ ሴቶች ከሌሎች ነብሰ ጡር ካልሆኑት የተለየ ምልክት አልታየባቸውም፡፡ ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ መርፌ የተወጋበት የሰውነት ክፍል መጠነኛ የቁስል ስሜትና ከክትባቱ ጋር ተያይዞ ሌሎች አጠቃላይ ስሜቶች የሚባሉት ስሜቶች ነብሰ ጡር ካልሆኑ ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር በተመሳሳይ ደረጃ ነው የታየው፡፡

አንግዲህ መድሐኒትም ሆነ ክትባት፣ በነብሰ ጡሮች ሲወሰድ፣ ተጨማሪ ክትትል ይደረጋል፡፡ (Pregnancy Registry) ይባላል፡፡ በዚህ ክትትል ላይ አንድ ሲዲሲ ዘገባ አስከ አፕሪል 5 ባለው ጊዜ ውስጥ 4218 ሴቶች ተመዝገበው ክትትል እየተደረገ ነው፡፡ ከነዚህ መሀል ቀደም ብለው ከተመዘገቡት 1815 ነብሰ ጡሮች ክትትል የታየው፣ 275 የሚሆኑት በየካቲት አጋማሽ ላይ ጌዜውን ጠብቀው የወለዱ መሆናቸውን የሚጠቅሰው፡፡

እንግዲህ ማጠቃለያውን ስንመለከት

ባጣቃላይ ሲታይ በኮቪድ ከተያዙ፣ ነብሰ ጡሮች ላይ ነብሰ ጡር ካልሆነት በበለጠ በሽታው ሊበረታባቸው እንደሚችል ነው፡፡

ነብሰ ጡሮች በኮቪድ ከተያዙ ፅንሱ ላይ የሚፈጠረው አደጋ እንደሚጨምር ነው ያም ያለቀኑ መወለድን ጨምሮ ነው፡፡

እንግዲህ በድንገትም ሆነ አስበው ነብሰ ጡር የሆኑ ሴቶች ክትባቶችን ከወሰዱ በቂ ክትትል በማድረግ ውጤቶችን በወቅቱ ማወቅ የበለጠ እንደሚረዳም ነው፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው ከ75ሺ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ በሚደረገው ክትትል፣ ክትባቱን በመውሰዳቸው ምክንያት የተለየ አሳሳቢ ችግር አለመኖሩን ያሳያል፡፡

ከወለዱ በኋላ ልጆቻቻን ለሚያጠቡ ሴቶች፣ የአሚሪካው የወላዶችና የማሕፀን ሀኪሞችና ሌሎችም የሚመከሩት፣ ለሚያጠቡ ሴቶች የኮቢድ ክትባት እንዲሠጣቸው ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ የኮቪድ-19 ክትባት የወሰዱ የሚያጠቡ እናቶች፣ ማጥባቱን ማቆም ወይም ማቋረጥ እንደማይኖረባቸው ይመከራል፡፡ በዚህ በኩል ጥሩ ዜና ነው ተብሎ የቀረበ ጥናት ውጤት የሚያሳየው፣ ኮቪድ ክትባት የወሰዱ ነብሰ ጡሮች፣ ለፅንሱ በቂ የሆነ እንቲቦዲ ማስተላለፍ እንደቻሉ ነው፡፡ ይህ ነገር እንግዳ ባይሆንም፣ በኮቪድ በኩል በመረጃ ሲቀርብ ደግሞ ጥሩ ነው፡፡ ትርጉሙ፣ የሚወለደው ህፃን ለተወሰነ ጊዜ ከእናቱ በኩል ባገኘው (አንቲቦዲ) አማካኝነት የኮቪድ መከላከያ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ይህንን ከተከተቡ እናቶች ወደ ፅንሱ አንቲቦዲ መሻገሩን በዛ ያሉ ጥናቶች ነው የሚያሳዩት፡፡ የሚገርመው ደግሞ፣ ከእንቲቦዲዎች አንደኛው በጡት ወተት ውስጥ እንደተገኘ መረጃዎች ማሳየታቸው ነው፡፡ ሰለዚህ ማጥባት ታላቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተጨማሪ ድጋፍ የሚሠጥ ነገር ነው፡፡ ሌላው ጠቀሜታ ደግሞ፣ ህፃናቱ አንቲቦዲ በርግዝና ወቅት በማግኘታቸው ሊኖራቸው በሚችለው መከላከያ ምክንያት እንደተወለዱ ከእናቶች ጋር እንዲራራቁ የሚያደርገውን ሁኔታም ይቀንሳል፡፡ የዚህ ፅሁፍ መረጃዎች ብዛት ሰላላቸው እዚህ ላይ አልተጠቀሱም፡፡

መልካም ንባብ

አካፍሉ